በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ መደምደሚያው ድል መገስገስ!

ወደ መደምደሚያው ድል መገስገስ!

ወደ መደምደሚያው ድል መገስገስ!

“እነሆም፣ አምባላይ ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፣ አክሊልም ተሰጠው፣ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት።”​—⁠ራእይ 6:​2

1. ዮሐንስ በራእይ የተመለከተው ወደፊት ስለሚፈጸም ምን ዓይነት ክንውን ነው?

 ሐዋርያው ዮሐንስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት 1, 800 ከሚያህል ዓመት በኋላ የሚሆነውን ነገር አሻግሮ በመመልከት ክርስቶስ ንጉሥ እንደሚሆን ተናግሯል። ዮሐንስ በራእይ የተመለከተውን ነገር ለመቀበል እምነት ጠይቆበታል። እኛ ግን ዛሬ ይህ በትንቢት የተነገረ ንግሥና በ1914 ፍጻሜውን እንዳገኘ የሚያረጋግጥ ግልጽ ማስረጃ አለን። በእምነት ዓይናችን ኢየሱስ ‘የጀመረውን ድል ለማጠናቀቅ’ ወደፊት ሲገሰግስ ይታየናል።

2. ዲያብሎስ ለመንግሥቱ መቋቋም የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? ይህስ ለምን ነገር ማረጋገጫ ይሆናል?

2 መንግሥቱ ከተቋቋመ በኋላ ሰይጣን ከሰማይ ተባርሯል። በዚህም ምክንያት ሰይጣን በከፍተኛ ኃይልና ቁጣ ጦርነት የከፈተ ቢሆንም ስኬት እንዲያገኝ የሚፈይድለት አንዳች ነገር አይኖርም። (ራእይ 12:​7-12) በቁጣ መነሳቱ የዓለም ሁኔታዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስጨናቂ እንዲሆኑ አድርጓል። ሰብዓዊው ሕብረተሰብ በመፈረካከስ ላይ ያለ ይመስላል። ለይሖዋ ምሥክሮች ይህ ሁሉ ነገር ንጉሣቸው ‘ድሉን ለማጠናቀቅ’ ወደፊት በመገስገስ ላይ እንዳለ የሚያረጋግጥ ግልጽ ማስረጃ ነው።

የአዲሱ ዓለም ሕብረተሰብ ግንባታ

3, 4. (ሀ) መንግሥቱ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በክርስቲያን ጉባኤ ምን ድርጅታዊ ለውጦች ተካሂደዋል? እነዚህን ለውጦች ማድረጉ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው? (ለ) ኢሳይያስ እንደተነበየው እነዚህ ለውጦች መደረጋቸው ምን ጥቅም አስገኝቷል?

3 መንግሥቱ ከተቋቋመ በኋላ ተጨማሪ የመንግሥት ኃላፊነቶች የተሸከመው ተመልሶ የተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ አሠራር ከመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ጋር የበለጠ የሚመሳሰልበት ጊዜ ደርሶ ነበር። በዚህም የተነሳ የሰኔ 1 እና የሰኔ 15, 1938 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች የክርስቲያን ጉባኤ ምን ዓይነት አሠራር መከተል እንዳለበት የሚገልጽ ዝርዝር ሐሳብ አወጡ። ከጊዜ በኋላም የታኅሣሥ 15, 1971 መጠበቂያ ግንብ እትም “የአስተዳደር አካሉ ከሕጋዊ ማኅበር የተለየ ነው” በሚል ርዕስ ዘመናዊውን የአስተዳደር አካል በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ አቀረበ። በ1972 በየጉባኤው ውስጥ እርዳታና መመሪያ የሚሰጡ የሽማግሌዎች አካላት ተሾሙ።

4 ተገቢ የሆነ የበላይ ጥበቃ ተመልሶ መቋቋሙ የክርስቲያን ጉባኤ በእጅጉ እንዲጠናከር አድርጓል። የአስተዳደር አካሉ የፍርድ ጉዳይ አያያዝን ጨምሮ ሽማግሌዎች ኃላፊነቶቻቸውን እንዴት መወጣት እንደሚችሉ ለማሠልጠን የሚረዱ ዝግጅቶችን ማድረጉም ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የአምላክ ምድራዊ ድርጅት ደረጃ በደረጃ ያደረጋቸው ማሻሻያዎችና እነዚህ ማሻሻያዎች ያስገኙት ጥቅም በኢሳይያስ 60:​17 ላይ እንዲህ በሚል ትንቢት ተነግሯል:- “በናስ ፋንታ ወርቅን፣ በብረትም ፋንታ ብርን፣ በእንጨትም ፋንታ ናስን፣ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፣ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ።” እነዚህ ማሻሻያዎች የአምላክ በረከት እንዳላቸውና የእርሱን መንግሥት ለመደገፍ በቅንዓት ለተነሳሱት ሰዎች አምላክ ሞገሱን እንደሰጣቸው የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ናቸው።

5. (ሀ) ይሖዋ ለሕዝቦቹ ያፈሰሰውን በረከት በተመለከተ የሰይጣን ምላሽ ምን ነበር? (ለ) ከፊልጵስዩስ 1:​7 ጋር በሚስማማ መንገድ የይሖዋ ሕዝቦች ለሰይጣን ቁጣ የሰጡት ምላሽ ምንድን ነው?

5 መንግሥቱ ከተቋቋመ በኋላ አምላክ ለሕዝቦቹ ያደረገላቸው ፍቅራዊ እንክብካቤና የሰጣቸው መመሪያ ከሰይጣን ዕይታ አላመለጠም። ለምሳሌ ያህል በ1931 እነዚህ አነስተኛ ቁጥር የነበራቸው ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ብቻ አለመሆናቸውን በይፋ አሳወቁ። በኢሳይያስ 43:​10 መሠረት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው! እንደ አጋጣሚ ሆነም አልሆነ በዚህ ወቅት ዲያብሎስ በመላው ዓለም ቀደም ሲል ከታየው የከፋ የስደት ማዕበል አስነስቷል። እንደ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ እና ጀርመን ያሉ የሃይማኖት ነፃነት ተከብሮባቸዋል በሚባሉ አገሮች እንኳን ሳይቀር ምሥክሮቹ የአምልኮ ነፃነታቸውን ለማስጠበቅ በተደጋጋሚ ጊዜያት ችሎት ፊት ቀርበው መሟገት አስፈልጓቸው ነበር። በ1988 የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮችን የሚመለከቱ 71 ጉዳዮችን የተመለከተ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው ለእነርሱ ተፈርዶላቸዋል። በዛሬ ጊዜም በዓለም ዙሪያ በፍርድ ቤት የሚደረገው ፍልሚያ የቀጠለ ሲሆን በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደሆነው ሁሉ አሁንም ‘ምሥራቹ የሕግ ከለላ እንዲያገኝና በሕግ እንዲከበር’ ማድረግ ተችሏል።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​7

6. ዕገዳዎችና ማዕቀቦች የይሖዋ ምሥክሮች ወደፊት የሚያደርጉትን ግስጋሴ ማስቆም ችለዋል? በምሳሌ አስረዳ።

6 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት በነበሩት በ1930ዎቹ ዓመታት አምባገነን መስተዳድሮች በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ እገዳ ጥለው ነበር። እገዳ ከጣሉት አገሮች መካከል ሦስቱን ብቻ ለመጥቀስ ያህል ጀርመን፣ ስፔይን እና ጃፓን ይገኙበታል። ይሁን እንጂ በ2000 እነዚህ ሦስት አገሮች ብቻ ወደ 500, 000 የሚጠጉ ንቁ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ነበሯቸው። ይህም በ1936 በዓለም ዙሪያ ከነበረው ጠቅላላ የምሥክሮች ቁጥር አሥር ጊዜ ገደማ እጥፍ ነው! ይህም የይሖዋ ሕዝቦች ድል አድራጊ በሆነው መሪያቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር ሆነው ወደፊት የሚያደርጉትን ግስጋሴ ዕገዳና ማዕቀብ ሊያስቆመው እንደማይችል በግልጽ የሚያሳይ ነው።

7. በ1958 ምን ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ክንውን ተካሂዷል? ከዚያን ጊዜ ወዲህስ አስደናቂ የሆኑ ምን ለውጦች ተካሂደዋል?

7 በ1958 በኒው ዮርክ ሲቲ የተደረገውና በይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ አቻ ያልተገኘለት 253, 922 የሚደርስ ከፍተኛ ተሰብሳቢዎች የተገኙበት መለኮታዊ ፈቃድ የተሰኘው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ለተደረገው ለዚህ ግስጋሴ ምንኛ ተስማሚ ማረጋገጫ ነው። በ1970 በወቅቱ ምሥራቅ ጀርመን ተብላ ትታወቅ ከነበረችው አገር በስተቀር ከላይ በተጠቀሱት በሦስቱ አገሮች ሥራው ፈቃድ አግኝቶ ነበር። ይሁን እንጂ ሶቪዬት ሕብረት ተብላ በምትታወቀው ሰፊ አገርና አጋሮቿ በሆኑት የዋርሶ ቃል ኪዳን አባል አገራት ውስጥ በምሥክሮቹ ላይ የተጣለው ዕገዳ አልተነሳም ነበር። በዛሬው ጊዜ በእነዚህ የቀድሞ ኮሚኒስት አገሮች ውስጥ ከግማሽ ሚልዮን የሚበልጡ ምሥክሮች በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

8. ይሖዋ ሕዝቡን በመባረኩ የተገኘው ውጤት ምንድን ነው? በ1950 የወጣው መጠበቂያ ግንብ ስለዚህ ጉዳይ ምን ብሎ ነበር?

8 የይሖዋ ምሥክሮች አስቀድመው “የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም” አለማቋረጥ በመፈለጋቸው ምክንያት የቁጥር ጭማሪ በማግኘት ተባርከዋል። (ማቴዎስ 6:​33) የኢሳይያስ ትንቢት ቃል በቃል ፍጻሜውን አግኝቷል:- “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ።” (ኢሳይያስ 60:​22) ይሁን እንጂ እድገቱ በዚህ ብቻ አያበቃም። ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ ብቻ የመንግሥቱን አገዛዝ የሚደግፉ ሰዎች ቁጥር ከ1, 750, 000 በላይ በሆነ ቁጥር አድጓል። እነዚህ ሰዎች ከአንድ ቡድን ጋር በራሳቸው ፈቃድ የተቀላቀሉ ሲሆን በ1950 የወጣው መጠበቂያ ግንብ ይህን ቡድን በማስመልከት የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝሯል:- “በአሁኑ ጊዜ አምላክ የአዲሱን ዓለም ሕብረተሰብ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል። . . . ይህ የአዲሱ ዓለም ሕብረተሰብ አስኳል አርማጌዶንን ይሻገራል፣ . . . ‘የአዲሱ ምድር’ የመክፈቻ ምዕራፍ ነው . . .፣ በቲኦክራሲያዊ መንገድ የተደራጀ፣ ድርጅታዊ አሠራርን የሚያውቅ ነው።” ይኸው ርዕስ ሲደመድም “ስለዚህ የአዲሱ ዓለም ሕብረተሰብ አባላት የሆንን ሁላችን አንድ ላይ ወደፊት መግፋታችንን እንቀጥል” ብሏል!

9. የይሖዋ ምሥክሮች ባለፉት ዘመናት የቀሰሟቸው ትምህርቶች ጠቃሚ ሆነው የተገኙት እንዴት ነው?

9 በዚህ መሀል ይህ በቁጥር እያደገ ያለው የአዲሱ ዓለም ሕብረተሰብ ያካበተው እውቀት አሁን ይህ ነው የማይባል ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ምናልባትም ከአርማጌዶን በኋላ በሚደረገውም የተሐድሶ ሥራ ከፍተኛ ጥቅም ሊሰጥ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ምሥክሮቹ ትላልቅ ስብሰባዎች ማደራጀትን፣ በተቀላጠፈ መንገድ አስቸኳይ እርዳታ ማቅረብንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕንፃዎች መገንባትን ተምረዋል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች ለይሖዋ ምሥክሮች በብዙዎች ዘንድ አድናቆትንና አክብሮትን አትርፎላቸዋል።

የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ማስተካከል

10, 11. ሌሎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የነበሯቸው የተሳሳቱ ግንዛቤዎች የተስተካከሉት እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

10 የሆነ ሆኖ የይሖዋ ምሥክሮች ከሰብዓዊው ሕብረተሰብ ጨርሶ የተለዩ ሰዎች ናቸው የሚል ክስ የሚያነሱ ሰዎችም አሉ። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ምሥክሮቹ ደምን እንደ መውሰድ፣ ገለልተኝነትን፣ ማጨስንና ሥነ ምግባርን በመሰሉ ጉዳዮች ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አቋም ነው። ይሁን እንጂ ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየተበራከተ የመጣ ሰዎች ምሥክሮቹ ያላቸው አቋም ትኩረት የሚያሻው እንደሆነ መናገር ጀምረዋል። ለምሳሌ ያህል በፖላንድ የሚገኙ አንዲት ሐኪም ወደ ይሖዋ ምሥክሮች አስተዳደር ቢሮ ደውለው እርሳቸውና በሐኪም ቤት ያሉ የሥራ ባልደረቦቻቸው ደምን በደም ሥር መውሰድን በሚመለከት ለበርካታ ሰዓታት ሲከራከሩ እንደቆዩ ገልጸዋል። የውይይቱ መነሻ ጃኒክ ዛሆደኒ የተባለው በፖላንድ ቋንቋ እየታተመ የሚወጣው ዕለታዊ ጋዜጣ በዚያን ዕለት እትሙ ላይ ያወጣው አምድ ነው። “በሕክምናው መስክ ደም ከልክ በላይ ጥቅም ላይ ሲውል ስመለከት በጣም አዝናለሁ” በማለት ሐኪሟ አምነዋል። “ይህ ሁኔታ መለወጥ ይኖርበታል። ይህ ጉዳይ ቀደም ብሎ የተነሣ በመሆኑ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ተጨማሪ መረጃ ባገኝ ደስ ይለኛል።”

11 ባለፈው ዓመት ተደርጎ በነበረ አንድ ጉባኤ ላይ ከካናዳ፣ ከአውሮፓ፣ ከእስራኤል እና ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ የሕክምና ባለሙያዎች ያለ ደም ሕሙማንን ማከም ስለሚችሉበት መንገድ ተወያይተዋል። ስዊዘርላንድ ውስጥ በተደረገው በዚህ ስብሰባ ላይ ብዙውን ጊዜ ከሚባለው በተለየ መልኩ ደም ሳይወስዱ ሕክምና ከሚደረግላቸው ሕሙማን ይልቅ ደም ወስደው ሕክምና ሲደረግላቸው የሚሞቱት ቁጥር እንደሚበዛ ተገልጿል። በጥቅሉ ሲታይ ምሥክር የሆኑ በሽተኞች ደም ተሰጥቷቸው ሕክምና ከሚደረግላቸው ሰዎች ቀድመው ከሐኪም ቤት የሚወጡ ሲሆን ይህም ለሕክምና የሚወጣውን ወጪ በእጅጉ የሚቀንስ ነው።

12. በፖለቲካ ገለልተኛ መሆንን በሚመለከት አንዳንድ ታዋቂ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን አቋም እንዴት እንዳወደሱ የሚገልጽ አንድ ምሳሌ ስጥ።

12 የይሖዋ ምሥክሮች ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊትና ጦርነቱ በተካሄደባቸው ዓመታት በናዚ ይደርስባቸው የነበረውን አሰቃቂ ጥቃት በመቋቋም ያሳዩትን የገለልተኝነት አቋም በማስመልከት በርካታ ገንቢ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጥቃት በጽናት ተቋቁመዋል በሚል ርዕስ የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጁትና ኅዳር 6, 1996 ጀርመን በሚገኘው በራቬንስብሩክ የእስረኞች ማጎሪያ ካምፕ ይፋ የሆነውን የቪድዮ ፊልም በተመለከተ በርካታ ሰዎች ገንቢ አስተያየቶች ሰንዝረዋል። ሚያዝያ 18, 1998 በርገንቤልዘን በሚገኘው በታወቀው የእስረኞች ማጎሪያ ካምፕ ፊልሙ በታየበት ፕሮግራም መክፈቻ ላይ በሎወር ሳክሶኒ የፖለቲካ ትምህርት ማዕከል ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ቮልፍጋንግ ሺል የሚከተለውን ተናግረዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በተለየ ቁርጠኝነት ብሔራዊ ሶሻሊዝምን አንቀበልም ማለታቸው አንገታችንን ያስደፋን የታሪክ ሐቅ ነው። . . . ለይሖዋ ምሥክሮች ትምህርቶችና ሃይማኖታዊ ቅንዓት ያለን አመለካከት ምንም ይሁን ምን በናዚ አገዛዝ ዘመን ያሳዩት ጽናት እንዲከበሩ የሚያደርግ ነው።”

13, 14. (ሀ) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ካልተጠበቀ ምንጭ ያገኙት አስተዋይነት የተሞላበት አስተያየት ምን ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦችን በመደገፍ የተሰጡ ገንቢ አስተያየቶችን አስመልክቶ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

13 ታዋቂ የሆኑ ግለሰቦች ወይም የፍርድ ቤት ብያኔዎች አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የይሖዋ ምሥክሮችን ደግፈው መገኘታቸው በምሥክሮቹ ላይ የሚሰነዘረውን ጭፍን ጥላቻ ሊቀንስና ሰዎች ምሥክሮቹ በጥሩ ዓይን እንዲታዩ ሊያደርግ ይችላል። ይህም ከዚህ ቀደም ፈቃደኛ ያልነበሩ ሰዎችን ለማነጋገር በር ይከፍትላቸዋል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች እንደነዚህ ያሉትን እርምጃዎች በደስታ የሚቀበሉ ከመሆናቸውም በላይ ከልብ ያደንቃሉ። ይህም በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም ተከስቶ የነበረውን አንድ ሁኔታ እንድናስታውስ ያደርገናል። ቅንዓት የተሞላበት ስብከታቸው ያሳሰበው ሳንሄድሪን የተባለው የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ሸንጎ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት ተነስቶ በነበረ ጊዜ ገማልያል የተባለ “በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር” እንዲህ ሲል አስጠንቅቋቸው ነበር:- “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። . . . ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፣ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።”​—⁠ሥራ 5:​33-39

14 እንደ ገማልያል ሁሉ ታዋቂ የሆኑ ግለሰቦች በቅርቡ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ነፃነት እንዲከበር ተሟግተዋል። ለምሳሌ ያህል የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት ዓለም አቀፍ አካዳሚ የቀድሞ ሊቀ መንበር “አንድ ሃይማኖት በጽኑ የሚያምንባቸው ነገሮች በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ስላላገኙ ወይም እንግዳ ስለሆኑ ብቻ ሃይማኖታዊ መብቱ ሊገፈፍ አይገባውም” በማለት ተናግረዋል። በሊፕዚግ ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት ሳይንሳዊ ጥናት ፕሮፌሰር ሃይማኖታዊ ኑፋቄ በተባሉት ቡድኖች ላይ ምርመራ እንዲያደርግ የተቋቋመውን የጀርመን መንግሥት ኮሚሽን በሚመለከት አንድ አግባብነት ያለው ጥያቄ አንስተዋል:- “ምርመራው ዋነኛ የሆኑትን አብያተ ክርስቲያናት [የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የሉተራን ቤተ ክርስቲያን] ሳይጨምር በቁጥር አነስተኛ አባላት ባላቸው ሃይማኖቶች ላይ ብቻ ያነጣጠረው ለምንድን ነው?” መልሱን እንደሚከተለው ብለው ከጻፉት የቀድሞ የጀርመን ባለ ሥልጣን ማግኘት እንችላለን:- “በፖለቲካው ጉዳይ የመስተዳድር ኮሚሽኑን እጅ ይዘው በምሥጢር የሚመሩት ቀናዒ የቤተ ክርስቲያን አባላት እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።”

እፎይታ ለማግኘት ተስፋ የምናደርገው ማንን ነው?

15, 16. (ሀ) ገማልያል የወሰደው እርምጃ ያስገኘው ውጤት ውስን የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ተሰሚነት የነበራቸው ሌሎች ሦስት ሰዎች ኢየሱስን ለመርዳት ማድረግ በሚችሉት ነገር ረገድ አቅማቸው ውስን የነበረው እንዴት ነው?

15 ከገማልያል አነጋገር መገንዘብ እንደሚቻለው መለኮታዊ ድጋፍ ያለውን ሥራ መግታት ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ገማልያል ለሳንሄድሪን ከተናገራቸው ከእነዚህ ቃላት ጥቅም እንዳገኙ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ተከታዮቹ እንደሚሰደዱ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውንም አልዘነጉም። ገማልያል የወሰደው እርምጃ የሃይማኖት መሪዎቹ ደቀ መዛሙርቱን ለማጥፋት የነበራቸውን ውጥን ያስቀረ ቢሆንም ስደት እንዳይደርስባቸው ግን አላስጣላቸውም። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ሰሙትም፣ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፣ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው።”​—⁠ሥራ 5:​40

16 ኢየሱስ ተከሶ በቀረበበት ጊዜ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ምንም ስህተት ስላላገኘበት ሊፈታው ፈልጎ ነበር። ሆኖም አልተሳካለትም። (ዮሐንስ 18:​38, 39፤ 19:​4, 6, 12-16) ለኢየሱስ ጥሩ አመለካከት የነበራቸው ሁለቱ የሳንሄድሪን አባላት ኒቆዲሞስ እና የአርማትያሱ ዮሴፍ ችሎቱ በኢየሱስ ላይ ሊወስደው ያሰበውን እርምጃ ለማስቀረት ማድረግ የሚችሉት ነገር ውስን ነበር። (ሉቃስ 23:​50-52፤ ዮሐንስ 7:​45-52፤ 19:​38-40) የተነሡበት ዓላማ ምንም ይሁን ምን ሰዎች የይሖዋን ሕዝብ ለመታደግ የሚያደርጉት ጥረት የሚያስገኘው ውጤት ውስን ነው። ዓለም ክርስቶስን እንደ ጠላው ሁሉ እውነተኛ ተከታዮቹንም መጥላቱን ይቀጥላል። የተሟላ እፎይታ ማግኘት የሚቻለው ከይሖዋ ብቻ ነው።​—⁠ሥራ 2:​24

17. የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ከእውነታው ያልራቀ አስተሳሰብ ምንድን ነው? ይሁን እንጂ ምሥራቹን መስበካቸውን ለመቀጠል ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ የማያላሉት ለምንድን ነው?

17 የይሖዋ ምሥክሮች ስደት ሊገጥማቸው እንደሚችል የሚጠብቁት ጉዳይ ነው። ተቃውሞ የሚቆመው የሰይጣን ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሲንኮታኮት ብቻ ነው። ይሁንና ስደት የማያስደስት ቢሆንም ምሥክሮቹ መንግሥቱን እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተልእኮ እንዳይፈጽሙ አያደርጋቸውም። ደግሞስ መለኮታዊ ድጋፍ እያላቸው ስደት እንዴት ሊያስቆማቸው ይችላል? ትክክለኛ ምሳሌ አድርገው የሚመለከቱት ደፋር መሪያቸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።​—⁠ሥራ 5:​17-21, 27-32

18. የይሖዋ ሕዝቦች ወደፊት ምን አስቸጋሪ ሁኔታ ይጠብቃቸዋል? ይሁን እንጂ ውጤቱ ምን ስለመሆኑ እርግጠኞች ናቸው?

18 እውነተኛው ሃይማኖት ጠንካራ ተቃውሞዎችን መጋፈጥ የጀመረው ገና ከጅምሩ ነው። በቅርቡ ደግሞ ከሰማይ በመባረሩ ምክንያት በተዋረደ ሁኔታ ላይ በሚገኘው በጎግ ማለትም በሰይጣን ሰፊ ጥቃት ይደርስበታል። ይሁን እንጂ እውነተኛ ሃይማኖት ይህን የስደት ማዕበል ያልፋል። (ሕዝቅኤል 38:​14-16) ‘የዓለም ሁሉ ነገሥታት’ በሰይጣን እየተመሩ “በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል።” (ራእይ 16:​14፤ 17:​14) አዎን፣ ንጉሣችን ወደ መደምደሚያው ድል በመገስገስ ላይ ሲሆን በቅርቡም ‘ድሉን ያጠናቅቃል።’ በቅርቡ የይሖዋ አምላኪዎች ማንም የሚቃወማቸው ሳይኖር ‘እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው’ የሚሉበት ጊዜ እንደሚመጣ በማወቅ ከእርሱ ጋር ወደፊት መገስገስ ምንኛ ትልቅ መብት ነው!​—⁠ሮሜ 8:​31፤ ፊልጵስዩስ 1:​27, 28

ልታብራራ ትችላለህ?

• ይሖዋ መንግሥቱ ከተወለደ ጊዜ አንስቶ ክርስቲያን ጉባኤን ለማጠናከር ምን አድርጓል?

• ክርስቶስ ድሉን እንዳያጠናቅቅ ለመግታት ሰይጣን ምን አድርጓል? ውጤቱስ ምን ነበር?

• ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች ስለወሰዱት በጎ እርምጃ ምን ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

• በቅርቡ ሰይጣን ምን እርምጃ ይወስዳል? ከምንስ ውጤት ጋር?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትላልቅ ስብሰባዎች የይሖዋ ሕዝቦች ወደፊት የሚያደርጉት ግስጋሴ መግለጫ ናቸው

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምሥክሮቹ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የወሰዱት የገለልተኝነት አቋም አሁንም ድረስ ለይሖዋ ውዳሴ እያመጣ ነው