የመሥፈርቶች መለዋወጥ አለመተማመንን ይፈጥራል
የመሥፈርቶች መለዋወጥ አለመተማመንን ይፈጥራል
በእንግሊዙ ንጉሥ ቀዳማዊ ሄንሪ ዘመን (1100-1135) አንድ ያርድ “ከንጉሡ አፍንጫ ጫፍ አንስቶ ወደፊት እስከተዘረጋው እጃቸው አውራ ጣት ድረስ ያለው ርዝመት” እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። የንጉሥ ሄንሪ ተገዢዎች የሚጠቀሙበት የያርድ መለኪያ ምን ያህል ትክክለኛ ነበር? እርግጠኛ መሆን የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ንጉሡ ዘንድ ቀርቦ በመጠየቅ ሳይሆን አይቀርም።
በዛሬው ጊዜ የመለኪያ መሣሪያዎችን ትክክለኛ መጠን የሚደነግግ መሥፈርት አለ። በመሆኑም የአንድ ሜትር ርዝመት፣ ብርሃን በአንድ ሴኮንድ ውስጥ በባዶ ስፍራ ውስጥ የሚጓዝበት ርቀት በ299, 792, 458 ሲካፈል የሚገኘው ውጤት ነው። ትክክለኛ ውጤት ለማግኘት ሲባል ይህ ብርሃን ቋሚ የሞገድ ርዝመት ያለው ሲሆን የሚረጨውም በዓይነቱ ልዩ ከሆነ መሣሪያ ነው። የትኛውም ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች መሥፈርቱን በድጋሚ ማሳየት የሚችል መሣሪያ ካላቸው እነሱ የለኩት ርዝመት ሌሎች ሰዎች ከለኩት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ማረጋገጥ ይችላሉ።
የቱንም ያህል ጥቂት ቢሆን በመለኪያ መሣሪያዎች መሥፈርት ላይ የሚደረግ ለውጥ አለመተማመንን ሊያስከትል ስለሚችል መሥፈርቶቹ እንዳይቀያየሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል። ለምሳሌ ያህል በብሪታኒያ የክብደት መለኪያ መሥፈርት ሆኖ የሚያገለግለው፣ አንድ ኪሎ ግራም የሚመዝን የፕላቲኒየምና የኢሪዲየም ቅልቅል የሆነ ቁራጭ ብረት ነው። ይህ ብረት ብሔራዊ የፊዚካዊ ቤተ ሙከራ ውስጥ ተቀምጧል። በተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴና በአቅራቢያው በሚበር አውሮፕላን ምክንያት የሚፈጠረው የአየር ብክለት ቋሚ የኪሎ ግራም መሥፈርቱ በየቀኑ ክብደቱ እንዲጨምር ያደርጋል። ሆኖም ይህ ቁራጭ ብረት ወይም ሲሊንደር በሴቭር ፈረንሳይ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የክብደትና የመለኪያ መሣሪያዎች ቢሮ፣ ምድር ቤት ባለ ክፍል ውስጥ የደወል ቅርጽ ባላቸው ሦስት የመስታወት መክደኛዎች ተከድኖ የተቀመጠው የዓለም መሥፈርት ቅጂ ነው። ይሁን እንጂ የዚህ ዕቃ ክብደት እንኳ በአጉሊ መነጽር በሚታዩ ብናኞች ንክኪ የተነሳ ይዛነፋል። እስካሁን ድረስ የዓለማችን የክብደትና የርቀት መለኪያ መሣሪያ ሳይንቲስቶች ይበልጥ ቋሚ የሆነ መሥፈርት ማግኘት ተስኗቸዋል።
ምንም እንኳ ለአንድ ተራ ሰው ኢምንት የሆኑ ለውጦች ምንም ነገር የማያስከትሉ መስለው ቢታዩም በመሥፈርት ረገድ የሚደረግ ፍጹም ለውጥ ግራ መጋባት ሊያስከትል ይችላል። ብሪታንያ ውስጥ ኦፊሴላዊው የክብደት መለኪያ (ፓውንድና ኦውንስ) ወደ ሜትሪክ (ኪሎ ግራምና ግራም) ሲቀየር ከፍተኛ አለመተማመን አስከትሏል። ይህም አለምክንያት አይደለም። አንዳንድ ይሉኝታ ቢስ ባለ ሱቆች የአብዛኛውን ሰው ለአዲሱ አሠራር እንግዳ የመሆን አጋጣሚ ተጠቅመው ደንበኞቻቸውን አጭበርብረዋል።
የቤተሰብና የሥነ ምግባር መሥፈርቶች
በቤተሰብና በሥነ ምግባር መሥፈርቶች ረገድ የሚደረጉትን ለውጦች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? በዚህ ረገድ የሚደረጉ ለውጦች ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። በጊዜያችን የሚሰማው የቤተሰብ መፈራረስ፣ ልቅ የፆታ ሥነ ምግባርና በከፍተኛ መጠን የተስፋፋው በልጆች ላይ የሚፈጸም ግፍ ለብዙዎች አስደንጋጭ ከመሆኑም በላይ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እያሽቆለቆሉ ባለበት ዘመን ውስጥ እንደምንኖር ያረጋግጣሉ። በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች፣ ተመሳሳይ ፆታ ያላቸው “ወላጆች” የሚያሳድጓቸው ልጆች እና በየአካባቢው ባሉ ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ልጆች ላይ የሚደርሰው ዘግናኝ ወሲባዊ ጥቃት ሰዎች ተቀባይነት ያላቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ወደ ጎን ገሸሽ ማድረጋቸውን የሚያሳዩ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ከሁለት ሺ ዓመታት ገደማ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-4
በፊት እንደተነበየው ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ “ራሳቸውን የሚወዱ፣ . . . ፍቅር የሌላቸው፣ . . . መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ . . . ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” እየሆኑ መጥተዋል።—የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ማሽቆልቆልና እምነት የሚጣልበት ሆኖ በመገኘት ረገድ የሚታየው ግዴለሽነት ጎን ለጎን የሚሄዱ ነገሮች ናቸው። በሰሜናዊ እንግሊዝ የምትገኘው የሀይዴ ከተማ ነዋሪዎች “በተከበሩትና በታመኑት” የቤተሰብ ዶክተሮቻቸው ላይ ከፍተኛ አመኔታ ይጥሉ የነበረ ሲሆን በቅርቡ ግን ከሕክምና ባለሙያዎች ከሚጠበቀው ሙያዊ የሥነ ምግባር ግዴታ ውጭ የሆነ ነገር ይፋ ወጥቷል። አመኔታቸው እንዲያው መና ሆኗል። እንዴት? አንድ ዶክተር ቢያንስ 15 ለሚሆኑ ሴት ታካሚዎቹ ሞት መንስዔ መሆኑን የፍርድ ቤት የምርመራ ሪፖርቶች ጠቁመዋል። እንዲያውም ፖሊሶች የዶክተሩ እጅ አለበት ያሉትን ከ130 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሞት በድጋሚ ለመመርመር ተገድደዋል። ዶክተሩ ወንጀለኛ መሆኑ ተረጋግጦ እስራት ሲፈረድበት ሰዎች ምን ያህል እምነት የማይጣልባቸው እየሆኑ እንደመጡ ለማየት ተችሏል። እናታቸው በዶክተሩ እጅ ተገድለው ሊሆን እንደሚችል የሚገመት ሁለት የእስር ቤት ፖሊሶች ይህን አረመኔ እስረኛ እንዳይገድሉት ሲባል ሌላ የሥራ ምድብ ተሰጥቷቸዋል። ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ ላይ የተላለፈውን ፍርድ በተመለከተ የወጣ ሪፖርት ወንጀለኛውን ዶክተር “‘ሰይጣኑ’ ዶክተር” ሲል መግለጹ ምንም አያስገርምም።
በበርካታ የሕይወት ዘርፎች እየተቀየሩና እያዘቀጡ ካሉት መሥፈርቶች አንጻር ሲታይ በእርግጠኝነት እምነት መጣል የምትችለው በማን ላይ ይሆን? የማስከበር ኃይል ባለው ባለሥልጣን የሚደገፉ የማይቀያየሩ መሥፈርቶች የት ማግኘት ትችላለህ? ቀጥሎ ያለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።