በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰምታችሁ የምትረሱ አትሁኑ

ሰምታችሁ የምትረሱ አትሁኑ

ሰምታችሁ የምትረሱ አትሁኑ

“ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።”—⁠ያዕቆብ 1:​22

1. የጥንቶቹ እስራኤላውያን የትኞቹን ተአምራት የመመልከት መብት አግኝተዋል?

 ይሖዋ በጥንቷ ግብፅ ውስጥ የፈጸማቸው ተአምራት ፈጽሞ “የማይረሱ” ናቸው። በእርግጥም አሥሩም መቅሰፍቶች በጣም አስፈሪ ነበሩ። እነዚህን መቅሰፍቶች ተከትሎ የእስራኤል ሕዝብ ለሁለት በተከፈለው ቀይ ባሕር በመሻገር አስደናቂ መዳን አገኙ። (ዘዳግም 34:​10-12) በአካል ተገኝተህ እነዚህ ተአምራት ሲፈጸሙ በዓይንህ ተመልክተህ ቢሆን መቼም እንዲህ ያደረገውን አካል ፈጽሞ እንደማትረሳ የታወቀ ነው። ሆኖም መዝሙራዊው “ታላቅ ነገርንም በግብጽ፣ ድንቅንም በካም ምድር፣ ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባሕር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ” በማለት ዘምሯል።​—⁠መዝሙር 106:​21, 22

2. እስራኤላውያን ለይሖዋ ኃያል ሥራዎች የነበራቸው አድናቆት የቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?

2 እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ከተሻገሩ በኋላ “እግዚአብሔርን ፈሩ፣ በእግዚአብሔርም በባሪያውም በሙሴ አመኑ።” (ዘጸአት 14:​31) የእስራኤል ወንዶች ከሙሴ ጋር ለይሖዋ የድል መዝሙር የዘመሩ ሲሆን ማርያምና ሌሎች ሴቶችም በከበሮና በጭፈራ አጅበዋቸዋል። (ዘጸአት 15:​1, 20) አዎን፣ የአምላክ ሕዝብ ይሖዋ ባደረጋቸው ኃያል ሥራዎች ተደንቆ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህን ድንቅ ሥራዎች ላከናወነው አካል የነበራቸው አድናቆት የቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ብዙዎቹ ያሳዩት ጠባይ የማስታወስ ችሎታን በሚያሳጣ በሽታ የተያዙ ያህል ነበር። በይሖዋ ላይ የሚያጉረመርሙና የሚያማርሩ ሆኑ። አንዳንዶች በጣዖት አምልኮና በፆታ ብልግና ተካፈሉ።​—⁠ዘኁልቁ 14:​27፤ 25:​1-9

እንድንረሳ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል?

3. ፍጽምና የጎደለን ሰዎች በመሆናችን ምክንያት ምን ልንረሳ እንችላለን?

3 የእስራኤላውያን አድናቆት ማጣት በእርግጥም በጣም የሚያስገርም ነው። በእኛም ላይ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊደርስ ይችላል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያሉ መለኮታዊ ተአምራት ሲፈጸሙ በዓይናችን አላየንም። ይሁን እንጂ ከአምላክ ጋር ባለን ዝምድና ረገድ ፈጽሞ ሊረሱ የማይችሉ ሁኔታዎችን እንዳሳለፍን የተረጋገጠ ነው። አንዳንዶቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበልንበትን ጊዜ እናስታውስ ይሆናል። ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን ለይሖዋ በጸሎት የገለጽንበትና እውነተኛ ክርስቲያኖች ሆነን በውኃ የተጠመቅንበት ጊዜ ካሳለፍናቸው አስደሳች ወቅቶች መካከል የሚመደቡ ናቸው። ብዙዎቻችን በአንድ ወቅት የይሖዋን የእርዳታ እጆች ተመልክተናል። (መዝሙር 118:​15) ከሁሉም በላይ ደግሞ በአምላክ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የመዳንን ተስፋ አግኝተናል። (ዮሐንስ 3:​16) የሆነ ሆኖ ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ስለሆንን የተሳሳቱ ምኞቶች ሲያድሩብንና የኑሮ ጭንቀቶች ሲጫኑን ይሖዋ ያደረገልንን መልካም ነገሮች በቀላሉ ልንረሳ እንችላለን።

4, 5. (ሀ) ያዕቆብ ሰምቶ የመርሳት አደጋ እንዳለ ያስጠነቀቀው እንዴት ነው? (ለ) ያዕቆብ ስለ ሰውና ስለ መስተዋት የተናገረውን ምሳሌ በሥራ ላይ ልናውል የምንችለው እንዴት ነው?

4 የኢየሱስ ግማሽ ወንድም ያዕቆብ ለክርስቲያን ባልደረቦቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሰምቶ የመርሳት አደጋ እንዳለ አስጠንቅቋል። እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፣ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል።” (ያዕቆብ 1:​22-24) ያዕቆብ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው?

5 ብዙውን ጊዜ ጠዋት ከአልጋችን ከተነሳን በኋላ መልካችንን በመስተዋት ውስጥ እየተመለከትን አንዳንድ ማስተካከያዎችን እናደርጋለን። ከዚያም በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ስንጠመድና አእምሯችን በሌሎች ጉዳዮች ላይ ማተኮር ሲጀምር በመስተዋቱ ውስጥ ስለ ተመለከትነው ነገር ማሰብ እናቆማለን። በመንፈሳዊም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። የአምላክን ቃል በምንመለከትበት ጊዜ ራሳችንን ይሖዋ ከሚጠብቅብን ነገር ጋር ልናወዳድር እንችላለን። ይህም ድክመቶቻችን ቁልጭ ብለው እንዲታዩን ያደርጋል። በዚህ መንገድ ያገኘነው እውቀት በባሕርያችን ላይ ለውጥ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል። ይሁን እንጂ በተለመደው ዕለታዊ እንቅስቃሴያችን ስንጠመድና ከችግሮቻችን ጋር መታገል ስንጀምር ወዲያው ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ማሰብ ልናቆም እንችላለን። (ማቴዎስ 5:​3፤ ሉቃስ 21:​34) ይህም አምላክ በፍቅሩ ተነሳስቶ ለእኛ ያደረጋቸውን ነገሮች የመርሳት ያህል ነው። ይህ ደግሞ ለኃጢአተኛ ዝንባሌዎች የተጋለጥን ያደርገናል።

6. የይሖዋን ቃል እንዳንረሳ የትኛውን ጥቅስ መመርመራችን ሊረዳን ይችላል?

6 ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው በመጀመሪያው መልእክቱ ላይ በምድረ በዳ የነበሩ የተደረገላቸውን ሁሉ የዘነጉትን እስራኤላውያን ጠቅሶ ጽፏል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ጳውሎስ ከጻፋቸው ቃላት ጥቅም እንዳገኙ ሁሉ እኛም የጻፋቸውን ነገሮች መለስ ብለን መከለሳችን የይሖዋን ቃል እንዳንረሳ ሊረዳን ይችላል። እስቲ 1 ቆሮንቶስ 10:​1-12ን እንመርምር።

ዓለማዊ ምኞቶችን መካድ

7. እስራኤላውያን ይሖዋ እንደሚወዳቸው የሚያሳይ ምን ጠንካራ ማስረጃ አግኝተዋል?

7 ጳውሎስ ስለ እስራኤላውያን የተናገረው ለክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ሆኖ ያገለግላል። ጳውሎስ የጻፈው በከፊል እንዲህ ይላል:- “ወንድሞች ሆይ፣ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ።” (1 ቆሮንቶስ 10:​1-4) በሙሴ ዘመን የነበረው የእስራኤል ሕዝብ በቀን ይመራቸው የነበረውንና በቀይ ባሕር ውስጥ እንዲያመልጡ የረዳቸውን ተዓምራዊውን የደመና ዐምድ ጨምሮ ታላላቅ የይሖዋ ኃይል መግለጫዎችን ተመልክቷል። (ዘጸአት 13:​21፤ 14:​21, 22) አዎን፣ እነዚያ እስራኤላውያን ይሖዋ እንደሚወዳቸው የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ አግኝተዋል።

8. እስራኤላውያን መንፈሳዊ ነገሮችን የሚረሱ መሆናቸው ምን አስከትሎባቸዋል?

8 “እግዚአብሔር ግን” ይላል ጳውሎስ በመቀጠል “ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፣ በምድረ በዳ ወድቀዋልና።” (1 ቆሮንቶስ 10:​5) ይህ እንዴት የሚያሳዝን ነው! ግብፅን ለቅቀው ከወጡት እስራኤላውያን መካከል ብዙዎቹ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ሳይበቁ ቀርተዋል። እምነት በማጣታቸው ምክንያት አምላክ ስላልተደሰተባቸው በምድረ በዳ ሞተዋል። (ዕብራውያን 3:​16-19) ከዚህ ምን ልንማር እንችላለን? ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​6

9. ይሖዋ ለሕዝቡ ዝግጅት ያደረገው እንዴት ነው? እስራኤላውያንስ ምን ምላሽ ሰጡ?

9 እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ወቅት መንፈሳዊ እይታቸው እንዳይደበዝዝ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ነበሩ። ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት ለእርሱ የተወሰነ ሕዝብ ሆነዋል። ከዚህም በላይ በክህነት የማገልገል መብት፣ የአምልኮ ማዕከል የሆነው የማደሪያው ድንኳንና ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን አግኝተው ነበር። በእነዚህ መንፈሳዊ ስጦታዎች ከመደሰት ይልቅ አምላክ በሰጣቸው ቁሳዊ ዝግጅቶች ሳይረኩ ቀሩ።​—⁠ዘኁልቁ 11:​4-6

10. አምላክን ሁልጊዜ ማስታወስ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

10 በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች በምድረ በዳ ከነበሩት እስራኤላውያን በተለየ መልኩ የአምላክን ሞገስ አግኝተዋል። ሆኖም በግለሰብ ደረጃም አምላክን ዘወትር ማስታወስ ያስፈልገናል። እንዲህ ማድረጋችን መንፈሳዊ ዕይታችንን ሊያደበዝዙብን የሚችሉ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረቱ ምኞቶችን እንድናስወግድ ይረዳናል። “ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፣ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፣ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን” ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። (ቲቶ 2:​12) ከልጅነታችን ጀምረን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያደግን ሁሉ የቀረብን ነገር እንዳለ አድርገን ማሰብ ፈጽሞ አይኖርብንም። እንደነዚህ ያለ ሐሳብ ወደ አእምሯችን ቢመጣ እንኳ ይሖዋንና ወደፊት ያዘጋጀልንን ድንቅ በረከቶች እናስታውስ።​—⁠ዕብራውያን 12:​2, 3

ይሖዋን ሙሉ በሙሉ መታዘዝ

11, 12. አንድ ሰው ለተቀረጸ ምሥል በሚቀርብ አምልኮ ባይካፈልም ጣዖትን የሚያመልክ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

11 ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ሌላ የማስጠንቀቂያ ቃል አስፍሮልናል:- “ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ።” (1 ቆሮንቶስ 10:​7) እዚህ ላይ ጳውሎስ ሕዝቡ አሮንን በማግባባት የወርቅ ጥጃ እንዲሠራላቸው ያደረጉበትን ጊዜ መጥቀሱ ነው። (ዘጸአት 32:​1-4) እንዲያው በቀጥታ ወደ ጣዖት አምልኮ ዞር እንላለን ማለት ባይሆንም የራስ ወዳድነት ምኞቶቻችን ይሖዋን በሙሉ ነፍስ እንዳናመልክ እንቅፋት እንዲሆንብን በመፍቀድ ጣዖት የምናመልክ ልንሆን እንችላለን።​—⁠ቆላስይስ 3:​5

12 በሌላ ወቅት ጳውሎስ ዋነኛ ትኩረታቸውን በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ከማድረግ ይልቅ ቁሳዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ያደረጉ ሰዎችን በማስመልከት ጽፏል። ‘ለክርስቶስ የመከራ እንጨት ጠላቶች ሆነው የሚመላለሱትን’ በማስመልከት ሲጽፍ “መጨረሻቸው ጥፋት ነው፣ ሆዳቸው አምላካቸው ነው” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 3:​18, 19) እንደ ጣዖት አድርገው ያመለኩት የተቀረጸ ምስል አይደለም። ለቁሳዊ ሃብት ያላቸውን ምኞት ነው። እርግጥ ነው፣ ሁሉም ዓይነት ምኞት ስህተት ነው ማለት አይደለም። ይሖዋ የፈጠረን ሰብዓዊ ፍላጎቶች እንዲኖሩንና በተለያዩ ነገሮች መደሰት እንድንችል አድርጎ ነው። ይሁን እንጂ ከአምላክ ጋር የመሠረቱትን ዝምድና ቸል ብለው ደስታን በአንደኛ ደረጃ የሚያሳድዱ ሁሉ በእርግጥም ጣዖትን የሚያመልኩ ሆነዋል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5

13. ቀልጦ ስለተሠራው ጥጃ ከሚገልጸው ዘገባ ምን ልንማር እንችላለን?

13 እስራኤላውያን ግብፅን ለቅቀው ከወጡ በኋላ የወርቅ ጥጃ ሠርተው አመለኩ። ጣዖትን ስለማምለክ ማስጠንቀቂያ ከመስጠትም በተጨማሪ በዚህ ዘገባ ውስጥ ሌላ አስፈላጊ የሆነ ትምህርትም ይገኛል። እስራኤላውያን ይሖዋ የሰጣቸውን ግልጽ መመሪያ ጥሰዋል። (ዘጸአት 20:​4-6) ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላካችን አይደለም ለማለት አላሰቡም። ቀልጦ ለተሠራው ጥጃ መሥዋዕት ካቀረቡ በኋላ ወቅቱን “የእግዚአብሔር በዓል” በማለት ሰየሙት። ታዛዥ አለመሆናቸውን አምላክ ችላ እንደሚለው አድርገው በማሰብ ራሳቸውን አታልለዋል። ይህ ደግሞ ለይሖዋ ስድብ ነበር፤ በጣምም አስቆጥቶታል።​—⁠ዘጸአት 32:​5, 7-10፤ መዝሙር 106:​19, 20

14, 15. (ሀ) እስራኤላውያን ሰምተው የሚረሱ ሰዎች የሚሆኑበት ምንም ምክንያት የሌላቸው ለምንድን ነው? (ለ) ሰምተን የምንረሳ ዓይነት ሰዎች ላለመሆን ከቆረጥን የይሖዋን ትእዛዛት በተመለከተ ምን እናደርጋለን?

14 አንድ የይሖዋ ምሥክር የነበረ ሰው የሃሰት ሃይማኖት አባል ይሆናል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነው። ይሁን እንጂ አንዳንዶች በጉባኤ ውስጥ እያሉም የይሖዋን መመሪያ የማይቀበሉባቸው አንዳንድ መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ። እስራኤላውያን ሰምተው የሚረሱበት ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። አሥርቱን ትእዛዛት ሰምተዋል፤ እንዲሁም ሙሴ “የብር አማልክት የወርቅም አማልክት ለእናንተ አታድርጉ” በማለት የአምላክን ትእዛዝ ሲናገር እዚያው ነበሩ። (ዘጸአት 20:​18, 19, 22, 23) እንደዚያም ሆኖ እስራኤላውያን የወርቅ ጥጃ አመለኩ።

15 እኛም ሰምተን የምንረሳ ዓይነት ሰዎች የምንሆንበት ምንም ምክ​ንያት የለንም። አምላክ የተለያዩ የኑሮ ዘርፎችን የሚዳስሱ መመሪያዎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አስፍሮልናል። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ ቃል ተበድሮ ያለመክፈልን ልማድ በቀጥታ ያወግዛል። (መዝሙር 37:​21) ልጆች ወላጆቻቸውን መታዘዝ ያለባቸው ሲሆን አባቶች ደግሞ ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል። (ኤፌሶን 6:​1-4) ነጠላ ክርስቲያኖች ‘በጌታ ብቻ’ እንዲያገቡ ታዝዘዋል። እንዲሁም ያገቡ የአምላክ አገልጋዮች እንዲህ ተብለዋል:- “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።” (1 ቆሮንቶስ 7:​39፤ ዕብራውያን 13:​4) ሰምተን የምንረሳ ዓይነት ሰዎች ላለመሆን ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን እነዚህንና አምላክ የሰጠንን ሌሎች መመሪያዎች በቁም ነገር እንመለከታቸዋለን እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ተስማምተን እንኖራለን።

16. የወርቅ ጥጃውን ማምለክ ምን ውጤት አስከተለ?

16 እስራኤላውያን በራሳቸው መንገድ ይሖዋን ለማምለክ ያደረጉትን ሙከራ ይሖዋ አልተቀበለውም። ከዚያ ይልቅ ምናልባትም የወርቅ ጥጃውን በማምለኩ ድርጊት ዋነኛ የዓመፁ ጠንሳሽ ሳይሆኑ አይቀርም 3, 000 ሰዎች ጠፍተዋል። ሌሎች ዓመፀኞችም ከይሖዋ በመጣ መቅሰፍት ተገድለዋል። (ዘጸአት 32:​28, 35) የአምላክን ቃል እያነበቡ ሆኖም የሚፈልጉትን ብቻ መርጠው ለሚታዘዙ ሰዎች ይህ እንዴት ያለ ትምህርት ነው!

“ከዝሙት ሽሹ”

17. አንደኛ ቆሮንቶስ 10:​8 የሚጠቅሰው በየት የደረሰውን ሁኔታ ነው?

17 ሥጋዊ ምኞቶች መንፈሳዊ ጉዳዮችን እንድንረሳ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉበት አንዱ መስክ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን” ብሎ በተናገረው ሐሳብ ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል። (1 ቆሮንቶስ 10:​8) እዚህ ላይ ጳውሎስ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ያደረጉትን የ40 ዓመት ጉዞ ወደ ማጠናቀቁ በተቃረቡበት ወቅት በሞዓብ ሜዳ ላይ ሳሉ የተከሰተውን ሁኔታ መጥቀሱ ነው። እስራኤላውያን በይሖዋ እርዳታ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚገኘውን ምድር ድል ያደረጉት በቅርቡ ነው። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ሰምተው የሚረሱ አድናቆት የጎደላቸው ሰዎች ሆኑ። ተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ተቃርበው ሳሉ በፆታ ብልግናና ርኩስ በሆነው በብዔልፌጎር አምልኮ ተታለሉ። በዚህም ምክንያት 1, 000 ቀንደኛ መሪዎችን ጨምሮ 24, 000 ሰዎች እንዲጠፉ ተደርጓል።​—⁠ዘኁልቁ 25:​9

18. ምን ዓይነት ድርጊቶች ወደ ፆታ ብልግና ሊመሩ ይችላሉ?

18 በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ በመጠበቅ ረገድ ጥሩ ስም አትርፈዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ክርስቲያኖች የፆታ ብልግና ፈተና ሲገጥማቸው ስለ ይሖዋና ስለ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ማሰብ አቁመዋል። ሰምተው የሚረሱ ሆኑ። መጀመሪያ ላይ ፈተናው ዝሙትን በቀጥታ የሚመለከት ላይሆን ይችላል። ወሲባዊ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን የመመልከት ጉጉት፣ ተገቢ ያልሆነ ቀልድ የመናገር ወይም የማሽኮርመም ወይም በሥነ ምግባር ደካማ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር የመቀራረብ ዝንባሌ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ክርስቲያኖችን የኃጢአት ድርጊት ወደመፈጸም መርተዋቸዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​33፤ ያዕቆብ 4:​4

19. የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ‘ከዝሙት እንድንሸሽ’ ይረዳናል?

19 ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም በምንፈተንበት ጊዜ ስለ ይሖዋ ማሰባችንን ማቆም አይገባንም። ከዚያ ይልቅ በቃሉ ውስጥ የሚገኙትን ማሳሰቢያዎች መከተል ይኖርብናል። (መዝሙር 119:​1, 2) ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ብዙዎቻችን በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነን ለመኖር የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። ይሁን እንጂ በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን ማድረግ ያልተቋረጠ ጥረት ይጠይቃል። (1 ቆሮንቶስ 9:​27) ጳውሎስ ሮም ለነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ጽፏል:- “መታዘዛችሁ ለሁሉ ተወርቶአልና፤ እንግዲህ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ለበጎ ነገር ጥበበኞች ለክፉም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ።” (ሮሜ 16:​19) በፈጸሙት ኃጢአት ምክንያት 24, 000 እስራኤላውያን እንደጠፉ ሁሉ አመንዝሮችና ሌሎች መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች በቅርቡ የይሖዋን የቅጣት ፍርድ ይቀበላሉ። (ኤፌሶን 5:​3-6) ስለዚህ ሰምተን የምንረሳ ከመሆን ይልቅ ‘ከዝሙት መሸሻችንን’ መቀጠል ይገባናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​18

ለይሖዋ ዝግጅቶች ምንጊዜም አድናቆት ይኑራችሁ

20. እስራኤላውያን ይሖዋን የተፈታተኑት እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?

20 ብዙዎቹ ክርስቲያኖች በፆታ ብልግና አይሸነፉም። ሆኖም የአምላክን ሞገስ ሊያሳጣ የሚችል አጉረምራሚ ወደ መሆን የሚያደርስ ጎዳና እንዳንከተል ጠንቃቆች መሆን አለብን። ጳውሎስ እንዲህ በማለት አጥብቆ መክሮናል:- “ከእነርሱም [ከእስራኤላውያን] አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጐራጐሩ [“እንዳጉረመረሙ፣” የ1980 ትርጉም ] በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐራጒሩ [“አታጉረምርሙ፣” የ1980 ትርጉም ]።” (1 ቆሮንቶስ 10:​9, 10) እስራኤላውያን ተዓምራዊ በሆነ መንገድ በሚያገኙት መና ላይ በማማረር በሙሴና በአሮን አልፎ ተርፎም በአምላክ ላይ አጉረምርመዋል። (ዘኁልቁ 16:​41፤ 21:​5) ይሖዋ ዝሙት በፈጸሙት ሰዎች ያዘነውን ያህል ባጉረመረሙት ሰዎች አዝኗልን? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው ያጉረመረሙ በርካታ ሰዎች በእባብ ተገድለዋል። (ዘኁልቁ 21:​6) ከዚህ ቀደም ብሎ በደረሰ አንድ ክስተት ከ14, 700 የሚበልጡ ዓመፀኛ አጉረምራሚዎች ተገድለዋል። (ዘኁልቁ 16:​49) ስለዚህ ለይሖዋ ዝግጅቶች አክብሮት በማጣት የይሖዋን ትዕግሥት አንፈታተን።

21. (ሀ) ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ምን ምክር ጽፏል? (ለ) በያዕቆብ 1:​25 መሠረት እውነተኛ ደስታ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?

21 ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልደረቦቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የዘረዘራቸውን ማስጠንቀቂያዎች የደመደመው በሚከተለው ጥብቅ ምክር ነው:- “ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፣ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ። ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።” (1 ቆሮንቶስ 10:​11, 12) እንደ እስራኤላውያን ሁሉ እኛም ከይሖዋ ብዙ በረከቶችን ተቀብለናል። ይሁን እንጂ እንደ እነርሱ አምላክ ያደረገልንን መልካም ነገሮች የምንረሳና ምስጋና ቢሶች መሆን የለብንም። የኑሮ ጭንቀቶች በሚጫኑን ጊዜ በቃሉ ውስጥ በሚገኙት ድንቅ ተስፋዎቹ ላይ እናሰላስል። ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ውድ ዝምድና የምናስታውስና በአደራ የተሰጠንን የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ሳናሰልስ የምናከናውን እንሁን። (ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20) እንዲህ ያለው ጎዳና እውነተኛ ደስታ እንደሚያመጣልን የተረጋገጠ ነው። ምክንያቱም ቅዱሳን ጽሑፎች የሚከተለውን ተስፋ ይሰጡናል:- “ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፣ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፣ በሥራው የተባረከ [“ደስተኛ፣” NW ] ይሆናል።”​—⁠ያዕቆብ 1:​25

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ሰምተን የምንረሳ ዓይነት ሰዎች ሊያደርገን የሚችለው ምንድን ነው?

• አምላክን ሙሉ በሙሉ መታዘዝ የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ‘ከዝሙት መሸሽ’ የምንችለው እንዴት ነው?

• ለይሖዋ ዝግጅቶች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን ይሖዋ ያደረገላቸውን ታላላቅ ሥራዎች ዘነጉ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ሕዝቦች ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎችን ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል