በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለረጅም ዓመታት የጸኑ ዛፎች

ለረጅም ዓመታት የጸኑ ዛፎች

ለረጅም ዓመታት የጸኑ ዛፎች

ገደል ላይ በተለይ ደግሞ በተራራ ጫፍ ላይ በሚገኝ ቦታ ቤትህን ለመሥራት እንደማትመርጥ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ የአልፓይን ዛፎች ለእድገት አመቺ ባይሆንም እንኳ እንዲህ ባሉት ዓለታማ ገደሎች ላይ እንደ ሙጫ ተጣብቀው ቀዝቃዛውን ክረምትና ደረቁን የበጋ ወቅት ተቋቁመው ያሳልፋሉ።

እነዚህ ውርጭና በረዶ የማይበግራቸው ዛፎች በቆላ አካባቢ እንዳሉት ዝርያዎቻቸው ግርማ ሞገስ የተላበሱ አይደሉም። ግንዳቸው ጉጥ የበዛበትና ጎበጥባጣ ሲሆን እድገታቸውም የቀጨጨ ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከአስቸጋሪው የአየር ንብረትና ከአፈር እጥረት የተነሳ ቁመታቸው አጫጭር ነው።

እነዚህ ዛፎች የሚበቅሉት በምድር ላይ እጅግ አስቸጋሪ የአየር ንብረት ባለበት አካባቢ በመሆኑ ረጅም ዕድሜ አይኖሩም ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ እውነታው ከዚህ ተቃራኒ ነው። እንዲያውም አንዳንዶች ማቱሳላ የሚባለው ካሊፎርኒያ በሚገኘው ዋይት ማውንቴን በተባለው ተራራ በ3, 000 ሜትር ከፍታ ላይ የሚያድገው ብሪስትልኮን ፓይን የተባለው ዛፍ 4, 700 ዓመት ዕድሜ እንዳለው ይናገራሉ። ዘ ጊነስ ቡክ ኦቭ ሪኮርድስ 1997 ይህን የዛፍ ዓይነት በመጥቀስ በዚህች ፕላኔት ላይ ከኖሩት ሁሉ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ እንደሆነ ዘግቧል። በእነዚህ ጥንታዊ ዛፎች ላይ ጥናት ያደረጉት ኤድመንድ ሹልማን እንዲህ በማለት ይገልጻሉ:- “ብሪስትልኮን ፓይን . . . የደረሰበትን መከራ ሁሉ ተቋቁሞ አልፏል። በዋይት ማውንቴይን ላይ የሚገኙት ረጅም ዓመት ያስቆጠሩት እነዚህ [ፓይን ዛፎች] የተገኙት ደረቅና ዓለታማ በሆነ 3, 000 ሜትር ከፍታ ላይ ነው።” ሹልማን በአስቸጋሪ ሁኔታ ሥር ያደጉ ረዥም ዓመት ያስቆጠሩት ሌሎች የፓይን ዛፎችንም አግኝተዋል።

እነዚህ ለጽናት ምሳሌ የሚሆኑ ዛፎች ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም ቢኖርባቸውም ከሁለት አቅጣጫ ከፍተኛ ጥቅም ያገኛሉ። ሌሎች ተክሎች እምብዛም በሌሉበት አካባቢ የሚገኙ መሆናቸው የዛፎች ዋነኛ ጠንቅ ከሆነው ከሰደድ እሳት ጠብቋቸዋል። እንዲሁም ሥሮቻቸው ከዓለት ጋር በኃይል አጣብቆ የያዛቸው በመሆኑ ከመሬት መንቀጥቀጥ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር አይበግራቸውም።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከዛፎች ጋር ተነጻጽረው ተገልጸዋል። (መዝሙር 1:1-3፤ ኤርምያስ 17:7, 8) የአምላክ አገልጋዮችም በሚገኙበት ሁኔታ የተነሳ መከራ ሊደርስባቸው ይችላል። ስደት፣ የጤና እክል ወይም ድህነት በተለይ ደግሞ ለረጅም ዓመት የሚዘልቅ ከሆነ እምነታቸውን በእጅጉ ሊፈታተነው ይችላል። ይሁን እንጂ ዛፎች መከራዎችን መቋቋም እንዲችሉ አድርጎ የሠራው ፈጣሪያቸው አምላኪዎቹን እንደሚደግፍ ማረጋገጫ ሰጥቷል። መጽሐፍ ቅዱስ በጽናት ለመቀጠል ለሚጥሩት “ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል” በማለት ቃል ይገባል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:9, 10

‘ካሉበት ንቅንቅ አለማለት፣ ጽኑ ሆኖ መኖር ወይም ፍንክች አለማለት’ የሚሉት አገላለጾች ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መጽናት” እየተባለ የሚተረጎመውን ግሪክኛ ግስ ሐሳብ የሚያስተላልፉ ናቸው። የአልፓይን ዛፎች ጽኑ ሆነው እንዲኖሩ የሚረዳቸው ሥራቸው ነው። ክርስቲያኖችም ጽኑ ሆነው እንዲቆሙ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በጥብቅ ሥር መስደድ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፣ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፣ ምስጋናም ይብዛላችሁ።”​—⁠ቆላስይስ 2:6, 7

ጳውሎስ ጠንካራ መንፈሳዊ ሥር አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቧል። እርሱ ራሱ ከነበረበት ‘የሥጋ መውጊያ’ ጋር ይታገል ነበር፤ እንዲሁም ባሳለፈው የአገልግሎት ዘመን ሁሉ የደረሱበትን ከባድ ስደቶች ተቋቁሞ አሳልፏል። (2 ቆሮንቶስ 11:23-27፤ 12:7) ይሁን እንጂ ወደፊት መግፋቱን መቀጠል የቻለው ከአምላክ ባገኘው ጥንካሬ እንደሆነ ተገንዝቧል። “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” በማለት ተናግሯል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:13

ከጳውሎስ ምሳሌ ማየት እንደሚቻለው ክርስቲያናዊ ጽናት የተመካው በሁኔታዎች መመቻቸት ላይ አይደለም። የሚፈራረቅባቸውን መጥፎ የአየር ንብረት ለዘመናት ተቋቁመው እንደሚኖሩት የአልፓይን ዛፎች ሁሉ እኛም በክርስቶስ ላይ ሥር ከሰደድንና አምላክ በሚሰጠን ኃይል ላይ ከተማመንን በእምነታችን ጸንተን መኖር እንችላለን። ከዚህም በላይ እስከ መጨረሻው ከጸናን “የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና” የሚለው ሌላ መለኮታዊ ተስፋ በራሳችን ላይ ሲፈጸም የመመልከት አጋጣሚ ይኖረናል።​—⁠ኢሳይያስ 65:22፤ ማቴዎስ 24:13