በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያለብህ ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያለብህ ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያለብህ ለምንድን ነው?

ቢል ፈርጠም ያለ ቁመና ያለው፣ የተማረና ጥሩ ገቢ ያለው ወጣት ነበር። ሆኖም እርካታ አልነበረውም። ሕይወቱ ዓላማ ስላልነበረው በእጅጉ ይረበሽ ነበር። የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ የተለያዩ ሃይማኖቶችን የመረመረ ቢሆንም የፈለገውን ማግኘት ግን አልቻለም። በ1991 ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወት ትርጉም ምን እንደሚል የሚያስረዳ መጽሐፍ ሰጠው። ቢል ይህንንም ሆነ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችን መገንዘብ ይችል ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ዝግጅት ተደረገለት።

ቢል እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “ጥናት በጀመርኩበት ዕለት በተደጋጋሚ መጽሐፍ ቅዱስ እየገለጥን ስለምናነብ ስፈልገው የነበረውን ነገር እንዳገኘሁ ተረዳሁ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ በጣም አስደሳች ነበር። ከጥናቱ በኋላ መኪና አስነስቼ ወደ አንድ ተራራ ሄድኩና ከመኪናዬ ወርጄ ከደስታዬ የተነሳ ጩኸቴን አቀለጥኩት። በመጨረሻ ለጥያቄዎቼ መልስ በማግኘቴ በጣም ተደስቼ ነበር።”

እርግጥ ነው፣ ሁሉም ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲያገኝ ቃል በቃል በደስታ ይጮኻል ማለት አይደለም። ሆኖም በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሙ ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ለብዙዎች የሚያስደስት ተሞክሮ ነው። ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ በእርሻው መካከል ውድ ሃብት ተሰውሮ ያገኘው ሰው የተሰማው ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል። ኢየሱስ “ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 13:​44

ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት የሚያስችል ቁልፍ

ቢል የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ያሳስበው ነበር። ፈላስፎች፣ የሃይማኖት ምሁራን እና ሳይንቲስቶች የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ለብዙ ሺህ ዓመታት ጥረዋል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የተለያዩ ግለሰቦች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው መጻሕፍት ጽፈዋል። ጥረታቸው ሁሉ መና ሆኖ የቀረ ሲሆን ብዙዎቹም ጥያቄው መልስ የለውም ወደሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ይሁን እንጂ መልስ አለው። መልሱ ጥልቀት ያለው ቢሆንም ውስብስብ ግን አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። ደስተኛና ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲኖረን ከፈለግን ፈጣሪያችንና የሰማዩ አባታችን ከሆነው ከይሖዋ ጋር ተገቢ የሆነ ዝምድና መመሥረት አለብን። በዚህ ረገድ ሊሳካልን የሚችለው እንዴት ነው?

ከይሖዋ ጋር ለመቀራረብ የሚያስችሉ ሆኖም እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ የሚመስሉ ሁለት ገጽታዎች አሉ። ከአምላክ ጋር የሚቀራረቡ ሁሉ ይፈሩታል እንዲሁም ይወዱታል። ይህን ሐሳብ የሚደግፉ ሁለት ጥቅሶችን እስቲ እንመልከት። ከረጅም ዘመን በፊት ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ስለ ሰው ዘር ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር ካደረገ በኋላ ውጤቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ አስፍሯል። የምርምሩን ውጤት በሚከተለው መንገድ ጠቅለል አድርጎ አስቀምጧል:- “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ።” (መክብብ 12:​13፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ለሙሴ ከተሰጠው ሕግ ውስጥ የትኛው ታላቅ እንደሆነ በተጠየቀ ጊዜ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” የሚል መልስ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 22:​37፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አምላክን መፍራትም መውደድም አለብን የሚለው አባባል ግር ያሰኝህ ይሆን? አምላክን መፍራትና መውደድ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያትና ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት ሁለቱም በጣምራ አስፈላጊ የሆኑት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመርምር።

አምላክን መፍራት ሲባል ምን ማለት ነው?

አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ ከፈለግን አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየት የግድ አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ይላል። (መዝሙር 111:​10) ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 12:​28) በተመሳሳይም ሐዋርያው ዮሐንስ በሰማይ መካከል ሲበር በራእይ የተመለከተው መልአክ ምሥራቹን ማወጅ የጀመረው “እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት” በሚሉት ቃላት ነው።​—⁠ራእይ 14:​6, 7

ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ የተገለጸው ይህ አምላካዊ ፍርሃት ከሚያርበተብት ፍርሃት ጋር አንድ አይደለም። ጨካኝና አደገኛ ከሆነ ወንጀለኛ ዛቻ ቢሰነዘርብን በከፍተኛ ፍርሃት ልንዋጥ እንችላለን። ፈሪሃ አምላክ ወይም አምላካዊ ፍርሃት ግን ለፈጣሪ ካለን ጥልቅ አክብሮት የሚመነጭ ባሕርይ ነው። እንዲሁም አምላክ የማይታዘዙትን ለመቅጣት የሚያስችል ኃይልም ሆነ ሥልጣን ያለው ታላቅ ፈራጅና ሁሉን ቻይ በመሆኑ እሱን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት ማሳየትንም ይጨምራል።

ፍርሃትና ፍቅር አብረው ይሄዳሉ

ሆኖም ይሖዋ ሰዎች እሱን በመፍራት ብቻ እንዲያገለግሉት አይፈልግም። ይሖዋ ከሁሉም በላይ የፍቅር አምላክ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ ‘አምላክ ፍቅር ነው’ ብሎ ለመጻፍ ተገፋፍቷል። (1 ዮሐንስ 4:​8) ይሖዋ አምላክ ሰዎችን የሚይዘው በፍቅር ሲሆን እነርሱም በአጸፋው እንዲወዱት ይፈልጋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ከአምላካዊ ፍርሃት ጋር ሊስማማ የሚችለው እንዴት ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ሁለቱ እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው ነው” ሲል ጽፏል።​—⁠መዝሙር 25:​14

አንድ ልጅ ብርቱና አስተዋይ ለሆነው አባቱ የሚኖረውን በአድናቆት ላይ የተመሠረተ ፍርሃት ለአንድ አፍታ አስብ። በተመሳሳይም እንደዚህ ያለው ልጅ አባቱ ለሚያሳየው ፍቅር ምላሽ ይሰጣል። ልጁ በአባቱ ይተማመናል እንዲሁም አባቱ የሚሰጠው መመሪያ እንደሚጠቅመው ስለሚያውቅ መመሪያ ለማግኘት ወደ አባቱ ዞር ይላል። በተመሳሳይም እኛ ይሖዋን የምንወድና የምንፈራ ከሆነ መመሪያውን እንቀበላለን። ይህም ጥቅም ያስገኝልናል። ይሖዋ እስራኤላውያንን በማስመልከት ምን እንዳለ ልብ በል:- “ለእነርሱ ለዘላለምም ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ፣ እንዲፈሩኝ ሁልጊዜም ትእዛዜን ሁሉ እንዲጠብቁ እንዲህ ያለ ልብ ምነው በሆነላቸው!”​—⁠ዘዳግም 5:​29

አዎን፣ አምላካዊ ፍርሃት የሚመራው ወደ ባርነት ሳይሆን ወደ ነጻነት፣ ወደ ሃዘን ሳይሆን ወደ ደስታ ነው። ኢሳይያስ ስለ ኢየሱስ “እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 11:​3) እንዲሁም መዝሙራዊው “እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድድ ሰው ምስጉን ነው” በማለት ጽፏል።​—⁠መዝሙር 112:​1

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላክን የማናውቀው ከሆነ ልንፈራውም ሆነ ልንወድደው አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጣም አስፈላጊ የሆነውም ለዚህ ነው። እንደዚህ ያለው ጥናት የአምላክን ባሕርያት እንድናውቅና መመ​ሪያውን መከተል ጥበብ መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ወደ አምላክ ይበልጥ እየቀረብን በሄድን መጠን ፈቃዱን የማድረግ ፍላጎት ያድርብናል እንዲሁም ትእዛዛቱ ጥቅም እንደሚያስገኙልን በመገንዘብ እንድንጠብቃቸው እንነሳሳለን።​—⁠1 ዮሐንስ 5:​3

አንድ ሰው በትክክለኛው የሕይወት መንገድ ላይ እየተጓዘ እንዳለ ማወቁ ደስታ ያስገኝለታል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ቢል የተሰማው ስሜት ይኸው ነው። በቅርቡ እንዲህ ብሎ ነበር:- “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመርኩበት ቀን አንስቶ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከይሖዋ ጋር የመሠረትኩት ዝምድና ተጠናክሯል። በመጀመሪያው ቀን ገንፍሎ የወጣው ደስታዬ በእርግጥም አስደሳች ወደ ሆነ የሕይወት መንገድ መርቶኛል። ስለ ሕይወት ያለኝ አመለካከት ብሩህ ነው። ሕይወቴ እንዲያው ደስታን ለማግኘት በሚደረግ ከንቱ ሩጫ ሳይሆን ትርጉም ባላቸው ሥራዎች የተሞላ ነው። ይሖዋ እንደ አንድ አካል እውን የሆነልኝ ሲሆን ለእኔም ከልቡ እንደሚያስብልኝ አውቃለሁ።”

በሚቀጥለው ርዕስ ከይሖዋ የምናገኘው እውቀት ደስታ የሚያስገኘው እንዴት እንደሆነና በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርጉ ሁሉ እንዴት ጥቅም ሊያገኙ እንደሚችሉ በጥልቀት እንመረምራለን።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወደ አምላክ መቅረብ ማለት እሱን እንወድደዋለን እንዲሁም እንፈራዋለን ማለት ነው

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ይሖዋን በመፍራት ደስታ አግኝቷል