በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ይሖዋ ባገኛችሁት እውቀት ደስ ይበላችሁ

ስለ ይሖዋ ባገኛችሁት እውቀት ደስ ይበላችሁ

ስለ ይሖዋ ባገኛችሁት እውቀት ደስ ይበላችሁ

“ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው።”​—⁠ሉቃስ 11:28

1. ይሖዋ ለሰዎች እውቀት ማካፈል የጀመረው መቼ ነው?

 ይሖዋ የሰው ልጆችን ይወድዳል፤ ስለ ደህንነታቸውም አጥብቆ ያስባል። በመሆኑም እውቀት ቢያካፍላቸው ምንም አያስገርምም። ይህን እውቀት ማካፈል የጀመረው በኤደን ገነት ነው። በዘፍጥረት 3:​8 ላይ “ቀኑ በመሸ ጊዜ” አዳምና ሔዋን ‘የይሖዋ አምላክን ድምፅ እንደሰሙ’ ተጠቅሷል። አንዳንዶች ይህ መግለጫ ይሖዋ በዚህ ሰዓት ምናልባትም በየዕለቱ ከአዳም ጋር የመነጋገር ልማድ እንደነበረው ያመለክታል የሚል አስተያየት አላቸው። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን አምላክ ለመጀመሪያው ሰው መመሪያ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ኃላፊነቱን ለመወጣት ይችል ዘንድ ሊያውቃቸው የሚገቡትን ነገሮች ለማስተማርም ጊዜ መድቦ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይጠቁማል።​—⁠ዘፍጥረት 1:​28-30

2. የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ከይሖዋ መመሪያ የራቁት እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?

2 ይሖዋ ለአዳምና ሔዋን ሕይወትን፣ በእንስሳት ላይ የመግዛትን መብትና መላዋን ምድር የማስተዳደር ሥልጣን ሰጥቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ነገር ተከልክለው ነበር። መልካምና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ እንዲበሉ አልተፈቀደላቸውም። አዳምና ሔዋን ለሰይጣን ተጽዕኖ በመሸነፍ የአምላክን ትእዛዝ አፈረሱ። (ዘፍጥረት 2:​16, 17፤ 3:​1-6) ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በመወሰን በራሳቸው መመራትን መረጡ። ይህንን ማድረጋቸው ከአፍቃሪ ፈጣሪያቸው የሚያገኙትን መመሪያ የሚያሳጣ የሞኝነት ድርጊት ነበር። መዘዙ ለእነርሱም ሆነ ገና ወደፊት ለሚወለዱት ልጆቻቸው አስከፊ ነበር። አዳምና ሔዋን እያረጁ ሄደው በመጨረሻ ትንሣኤ የሌለው ሞት ሞቱ። የእነርሱም ዘሮች ኃጢአትንና የእርሱ ውጤት የሆነውን ሞትን ወረሱ።​—⁠ሮሜ 5:​12

3. ይሖዋ ቃየንን የመከረው ለምንድን ነው? ቃየንስ ምን ምላሽ ሰጠ?

3 በኤደን ዓመፅ ቢፈጸምም እንኳ ይሖዋ ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ እውቀት ማካፈሉን አላቆመም። የአዳምና ሔዋን የበኩር ልጅ የሆነው ቃየን ለኃጢአት እንዲሸነፍ በሚያደርግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ይሖዋ፣ ቃየን ችግር ውስጥ እየገባ እንዳለ በማስጠንቀቅ ‘መልካም እንዲያደርግ’ መከረው። ቃየን ግን ይህንን ፍቅራዊ ምክር ለመቀበል አሻፈረኝ በማለቱ ወንድሙን ገደለ። (ዘፍጥረት 4:​3-8) በዚህ መንገድ በምድር ላይ የነበሩት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ሰዎች የሕይወታቸው ምንጭ ከሆነውና ሕዝቦቹ ራሳቸውን መጥቀም ይችሉ ዘንድ ከሚያስተምራቸው አምላክ የተሰጣቸውን ግልጽ መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። (ኢሳይያስ 48:​17) ይህ ይሖዋን ምንኛ አሳዝኖት መሆን አለበት!

ይሖዋ ጥንት ለነበሩ ሰዎች ተገልጦላቸዋል

4. የአዳምን ልጆች በተመለከተ ይሖዋ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር? ይሖዋ ይህንን በማሰብ ምን ተስፋ ያዘለ መልእክት ተናግሯል?

4 ይሖዋ ከሰዎች ጋር የሚያደርገውን የሐሳብ ግንኙነት ማቋረጥ የሚችልበት በቂ ምክንያት የነበረው ቢሆንም እንደዚያ አላደረገም። አንዳንዶቹ የአዳም ልጆች የእርሱን መመሪያ በመቀበል የጥበብን ጎዳና እንደሚመርጡ እርግጠኛ ነበር። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ በአዳምና ሔዋን ላይ የቅጣት ፍርድ ባስተላለፈበት ጊዜ እባቡን ማለትም ሰይጣን ዲያብሎስን በመቃወም የሚነሳ “ዘር” እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሯል። ከጊዜ በኋላም ሰይጣን ጭንቅላቱ ተቀጥቅጦ ከህልውና ውጭ ይሆናል። (ዘፍጥረት 3:​15) ‘የአምላክን ቃል ሰምተው ለሚጠብቁ ሁሉ’ ይህ ትንቢት ተስፋ ያዘለ አስደሳች መልእክት ነው።​—⁠ሉቃስ 11:​28

5, 6. ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ቀደም ብሎ በነበረው ጊዜ ይሖዋ ለሕዝቡ ትምህርት የሰጠው እንዴት ነው? ይህስ የጠቀማቸው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ኢዮብ ላሉት የታመኑ የእምነት አባቶች ፈቃዱን አሳውቋቸዋል። (ዘፍጥረት 6:​13፤ ዘጸአት 33:1፤ ኢዮብ 38:1-3) ከጊዜ በኋላ ደግሞ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤል ብሔር በጽሑፍ የሰፈረ የተሟላ ሕግ ሰጥቷቸዋል። የሙሴ ሕግ በብዙ መንገድ ጠቃሚ ሆኖላቸው ነበር። እስራኤላውያን ይህንን ሕግ በመጠበቃቸው ከሌሎች ብሔራት ሁሉ የተለዩ የአምላክ ሕዝብ ሆነዋል። እስራኤላውያን ሕጉን ቢታዘዙ በሰብዓዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ብሔር እንዲሆኑ በማድረግ በመንፈሳዊ ጭምር እንደሚባርካቸው ማረጋገጫ ሰጥቷቸው ነበር። ሕጉ ለጥሩ ጤንነት የሚበጁ የአመጋገብና የንጽሕና አጠባበቅ ደንቦችንም አካትቶ የያዘ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሳይታዘዙ መቅረታቸው የሚያስከትለውን አሳዛኝ መዘዝም በሚመለከት አስጠንቅቋቸዋል።​—⁠ዘጸአት 19:​5, 6፤ ዘዳግም 28:​1-68

6 ከጊዜ በኋላ ሌሎች በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆነው ተጨመሩ። ታሪካዊ ዘገባዎቹ ይሖዋ ከብሔራትና ከሕዝቦች ጋር ስለነበረው ግንኙነት ይገልጻሉ። የግጥም ይዘት ያላቸው መጻሕፍት ባሕርያቱን ግሩም በሆነ መንገድ ያብራራሉ። ትንቢታዊ መጻሕፍቱ ደግሞ ወደፊት ስለሚከናወነው የይሖዋ ፈቃድ አፈጻጸም ይተነብያሉ። ጥንት የነበሩ የታመኑ ሰዎች በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን እነዚህን መጻሕፍት በጥንቃቄ አጥንተዋቸዋል እንዲሁም ሠርተውባቸዋል። ከእነርሱ መካከል አንዱ “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 119:105) ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለነበሩ ሁሉ ይሖዋ ትምህርትና መንፈሳዊ ማስተዋል ሰጥቷቸዋል።

ብርሃኑ እየደመቀ ይሄዳል

7. ኢየሱስ ብዙ ተአምራት ያደረገ ቢሆንም በዋነኝነት ይታወቅ የነበረው በምንድን ነው? ለምንስ?

7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በሕጉ ላይ ሰብዓዊ ወጎችን ጨምረው ነበር። ሕጉን በተሳሳተ መንገድ የተጠቀሙበት ሲሆን በእነዚህ ወጎች ምክንያት ሕጉ የመንፈሳዊ ማስተዋል ምንጭ መሆኑ ቀርቶ ሸክም ሆኖ ነበር። (ማቴዎስ 23:​2-4) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በ29 እዘአ መሲሕ ሆኖ ብቅ አለ። ተልዕኮው ነፍሱን ለሰው ልጆች አሳልፎ መስጠት ብቻ ሳይሆን ‘ስለ እውነት መመስከርንም’ ይጨምር ነበር። ብዙ ተአምራት ያደረገ ቢሆንም በዋነኛነት ይታወቅ የነበረው “መምህር” በሚለው መጠሪያ ነበር። ትምህርቱ በሰዎች አእምሮ ላይ ባጠላው መንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እንደፈነጠቀ ብርሃን ነበር። ኢየሱስ ራሱ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሲል ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 8:12፤ 11:​28፤ 18:37

8. በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? የጥንቶቹን ክርስቲያኖች የጠቀሟቸውስ እንዴት ነው?

8 ከጊዜ በኋላ ደግሞ ወንጌሎች ማለትም ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚናገሩ አራት የጽሑፍ ዘገባዎች እንዲሁም ከክርስቶስ ሞት በኋላ ስለ ክርስትና መስፋፋት የሚገልጸው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ተጨምረዋል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ አነሳሽነት የጻፏቸው መልእክቶችና ትንቢታዊ ይዘት ያለው የራእይ መጽሐፍም ነበሩ። እነዚህ መጻሕፍት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጋር አንድ ላይ ተዳምረው የተሟላውን መጽሐፍ ቅዱስ አስገኝተዋል። ክርስቲያኖች በመንፈስ አነሳሽነት በተዘጋጀው በዚህ ቤተ መጻሕፍት እገዛ ‘ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የእውነትን ስፋትና ርዝመት ከፍታውንም ጥልቀቱንም’ መገንዘብ ይችሉ ነበር። (ኤፌሶን 3:14-18) ‘የክርስቶስንም አስተሳሰብ’ ማዳበር ይችሉ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 2:​16 NW ) የሆነ ሆኖ እነዚያ የጥንት ክርስቲያኖች ሁሉንም የአምላክ ዓላማ ዘርፎች በተመለከተ የተሟላ ግንዛቤ አልነበራቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት አጋሮቹ “ዛሬስ በመስተዋት [“በብረት መስተዋት፣” NW ] በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:12) እንዲህ ያለ መስተዋት ጠቅላላውን የምስሉን ቅርጽ እንጂ ዝርዝር ሁኔታዎቹን በግልጽ አያሳይም። ስለ አምላክ ቃል ሙሉ ግንዛቤ የሚያገኝበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር።

9. ‘በመጨረሻው ቀን’ ምን መንፈሳዊ ማስተዋል ተገኝቷል?

9 ዛሬ የምንኖረው ‘የመጨረሻ ቀን’ እየተባለ በሚጠራው ‘የሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ነቢዩ ዳንኤል በዚህ ወቅት ‘እውነተኛ እውቀት እንደሚበዛ’ ትንቢት ተናግሯል። (ዳንኤል 12:​4 NW ) በመሆኑም ፈቃዱን የሚገልጸው ታላቁ አምላክ ይሖዋ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ የቃሉን ትርጉም እንዲያስተውሉ ረድቷቸዋል። ዛሬ በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ክርስቶስ ኢየሱስ ከ1914 ጀምሮ በማይታየው ሰማይ ንግሥናውን እንደያዘ ተገንዝበዋል። በቅርቡም ክፋትን ጠራርጎ በማስወገድ መላዋን ምድር ወደ ገነትነት እንደሚለውጣትም ያውቃሉ። የአምላክ መንግሥት ምሥራች አብይ ክፍል የሆነው ይህ መልእክት በመላዋ ምድር ላይ እየታወጀ ነው።​—⁠ማቴዎስ 24:​14

10. ባለፉት መቶ ዘመናት ሰዎች ለይሖዋ ምክር ምን ዓይነት ምላሽ ሲሰጡ ኖረዋል?

10 አዎን፣ ባለፉት ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ፈቃዱንና ዓላማውን በምድር ላይ ላሉ ሰዎች ሲያሳውቅ ኖሯል። የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ አምላክ ለገለጸው እውቀት ጆሮአቸውን ስለሰጡ፣ አምላካዊውን ጥበብ ስላንጸባረቁና በዚህም ምክንያት በረከት ስላገኙ ሰዎች ይናገራል። የአምላክን ፍቅራዊ ምክር ቸል ብለው የአዳምንና ሔዋንን የጥፋት አካሄድ ስለተከተሉ ሰዎችም ይናገራል። ኢየሱስ ስለ ሁለቱ ምሳሌያዊ መንገዶች በተናገረ ጊዜ ስለዚህ ሁኔታ አስረድቷል። አንደኛው ወደ ጥፋት የሚመራ ነው። ሰፊና የተንጣለለ በመሆኑ የአምላክን ቃል የናቁ ብዙ ሰዎች የሚጓዙበት ጎዳና ነው። ሌላኛው መንገድ ደግሞ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ነው። ጠባብ ቢሆንም እንኳ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ እንደ አምላክ ቃል አድርገው የተቀበሉና ከዚያ ጋር ተስማምተው የሚመላለሱ ጥቂቶች የሚሄዱበት መንገድ ነው።​—⁠ማቴዎስ 7:​13, 14

ያገኘነውን እውቀት ማድነቅ

11. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያገኘነው እውቀትና በእርሱ ላይ ያለን እምነት የምን ማስረጃ ነው?

11 አንተ የሕይወትን መንገድ ከመረጡት ሰዎች መካከል ነህን? ከሆነ በዚህ መንገድ ላይ መጓዝህን ለመቀጠል እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህንን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቅህ ያስገኘልህን በረከት አዘውትረህ በአድናቆት ስሜት አሰላስል። ለምሥራቹ ምላሽ መስጠትህ ራሱ የአምላክ በረከት አንደኛው ማስረጃ ነው። ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ በጸለየ ጊዜ ይህ አባባል እውነት መሆኑን ጠቁሟል:- “አባት ሆይ፣ የሰማይና የምድር ጌታ፣ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ።” (ማቴዎስ 11:25) ከፍተኛ ትምህርት የነበራቸው ሃይማኖታዊ መሪዎች የኢየሱስን ትምህርት መገንዘብ ሲሳናቸው ዓሣ አጥማጆችና ቀረጥ ሰብሳቢዎች ተገንዝበውት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” ብሏል። (ዮሐንስ 6:44) መጽሐፍ ቅዱስን የምታውቅ ትምህርቶቹንም የምታምንና የምትከተል ከሆነ ይሖዋ እንደሳበህ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በዚህም ደስ ሊልህ ይገባል።

12. መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ማስተዋል የሚሰጠን በምን መንገዶች ነው?

12 የአምላክ ቃል ነፃ የሚያወጣ እውነት ያዘለ ከመሆኑም ሌላ መንፈሳዊ ማስተዋል ይሰጣል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኙት እውቀት መሠረት የሚመላለሱ ሁሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ከተቆጣጠሩት አጉል እምነቶች፣ የሐሰት ትምህርቶችና ድንቁርና ተላቅቀዋል። ለምሳሌ ያህል ስለ ነፍስ እውነቱን ማወቃችን ሙታን ሊጎዱን ይችላሉ ወይም የምንወዳቸው ሰዎች በሥቃይ ላይ ናቸው ከሚለው ፍርሃት ነፃ ያወጣናል። (ሕዝቅኤል 18:​4) ክፉ መላእክትን በተመለከተ እውነቱን ማወቃችን አደጋ ከሚያስከትለው የመናፍስት አምልኮ ይጠብቀናል። የትንሣኤ ትምህርት የሚወድዷቸውን ሰዎች በሞት ላጡ ሰዎች እጅግ የሚያጽናና ነው። (ዮሐንስ 11:​25) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በጊዜ ሂደት ውስጥ ምን ነጥብ ላይ እንዳለን የሚጠቁሙን ከመሆኑም ሌላ አምላክ ወደፊት እንደሚፈጸሙ በገባቸው ተስፋዎች ላይ ትምክህት እንዲኖረን ይረዱናል። እንዲሁም ለዘላለም የመኖር ተስፋችንን ያጠናክሩልናል።

13. የአምላክን ቃል መታዘዝ በሰብዓዊ መንገድ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሰብዓዊ መንገድም የሚጠቅም ጎዳና እንድንከተል ያስተምሩናል። ለምሳሌ ያህል ትንባሆና ሌሎች መድኃኒቶችን አላግባብ እንደ መጠቀም ካሉ ሰውነታችንን ከሚያረክሱ ልማዶች እንድንርቅ እንማራለን። የአልኮል መጠጦችን አላግባብ ከመጠቀምም እንርቃለን። (2 ቆሮንቶስ 7:​1) የአምላክን የሥነ ምግባር ሕጎች መታዘዝ በፆታ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ይጠብቀናል። (1 ቆሮንቶስ 6:​18) ገንዘብን ከመውደድ እንድንርቅ የሚመክረንን የአምላክ ቃል በመታዘዛችን ሃብትን ከሚያሳድዱ ብዙ ሰዎች በተለየ መንገድ የአእምሮ ሰላማችንን እንጠብቃለን። (1 ጢሞቴዎስ 6:10) የአምላክን ቃል በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ በማድረግህ አንተ በግልህ በምን መንገዶች ተጠቅመሃል?

14. መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

14 በአምላክ ቃል መሠረት ሕይወታችንን የምንመራ ከሆነ የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ እናገኛለን። እንደ ምሕረትና ርኅራኄ ያሉ ባሕርያትን ያቀፈ የክርስቶስን ዓይነት ባሕርይ እናዳብራለን። (ኤፌሶን 4:24, 32) የአምላክ መንፈስም እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃትና ራስን መግዛት ያሉትን ፍሬዎች በውስጣችን ያፈራል። (ገላትያ 5:22, 23) እነዚህ ባሕርያት ደግሞ የቤተሰባችንን አባላት ጨምሮ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ደስታ የሞላበትና ትርጉም ያለው እንዲሆን ይረዱናል። ፈተናዎችን በድፍረት መቋቋም እንድንችል የሚረዳንን ውስጣዊ ጥንካሬ እናገኛለን። መንፈስ ቅዱስ በሕይወትህ ውስጥ ያሳደረውን በጎ ተጽእኖ አስተውለሃል?

15. ሕይወታችንን ከአምላክ ፈቃድ ጋር በማስማማታችን የምንጠቀመው እንዴት ነው?

15 ሕይወታችንን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ስናስማማ ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት ይጠናከራል። ሁኔታችንን እንደሚረዳልንና እንደሚወደን ያለን ጽኑ እምነት እያደገ ይሄዳል። በአስቸጋሪ ወቅቶች ሳይቀር እንደሚደግፈን ከራሳችን ተሞክሮ እንማራለን። (መዝሙር 18:​18) ጸሎታችንን በእርግጥ እንደሚሰማ እናስተውላለን። (መዝሙር 65:​2) እንደሚጠቅመን ፍጹም እርግጠኛ ሆነን እርሱ በሚሰጠን መመሪያ እንታመናለን። አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለእርሱ የታመኑ ሆነው የሚገኙትን ሰዎች ወደ ፍጽምና እንደሚያደርሳቸውና የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው የምንጠብቅበት ድንቅ ተስፋ አለን። (ሮሜ 6:​23) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 4:8) ወደ ይሖዋ ይበልጥ በቀረብህ መጠን ከእርሱ ጋር ያለህ ዝምድና የዚያኑ ያህል እንደተጠናከረ ተሰምቶሃልን?

አቻ የማይገኝለት ውድ ሀብት

16. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ለውጥ አድርገዋል?

16 ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ቀደም ሲል አመንዝሮች፣ ቀላጮች፣ ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ፣ ሌቦች፣ ስግብግቦች፣ ሰካራሞች፣ ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች እንደነበሩ አስታውሷቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንዲያደርጉ የረዳቸው ሲሆን ‘ታጥበው ነጽተዋል።’ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርከው ነፃ የሚያወጣው እውነት ባይኖር ኖሮ ሕይወትህ ምን ሊመስል እንደሚችል አስብ። በእርግጥም እውነት አቻ የማይገኝለት ውድ ሃብት ነው። ይሖዋ እውቀቱን የሚገልጽልን በመሆኑ ምንኛ ደስተኞች ነን!

17. የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመንፈሳዊ የተመገቡት እንዴት ነው?

17 ከዚህም በላይ በዓለም ባለ ብዙ ብሔር የወንድማማች ማኅበራችን አማካኝነት ስላገኘናቸው በረከቶች አስብ! “ታማኝና ልባም ባሪያ” በብዙ ቋንቋዎች የሚወጡትን መጽሐፍ ቅዱሶች፣ መጽሔቶችና ሌሎች ጽሑፎች ጨምሮ መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው ያቀርብልናል። (ማቴዎስ 24:45-47) በ2000 በተደረጉት የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በብዙ አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ስምንት በሚያክሉ ትላልቅ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን ጎላ ያሉ ቁም ነገሮች ከልሰዋል። ስለተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርቶች በሚገልጹ የመጽሐፍ ክፍሎች ላይም ተወያይተዋል። እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍና የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! ከተባለው መጽሐፍ ብዙ ምዕራፎች ሸፍነዋል። ከመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችም ከ52 የጥናት ርዕሶች በተጨማሪ ሰላሳ ስድስት ተጨማሪ ርዕሶች ተጠንተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ሕዝብ በ12 የመንግሥት አገልግሎታችን እትሞችና በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በሚቀርቡት ሳምንታዊ የሕዝብ ንግግሮች አማካኝነት በመንፈሳዊ ተመግበዋል። የቀረበው መንፈሳዊ እውቀት በእጅጉ የተትረፈረፈ ነው!

18. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት እርዳታ እናገኛለን?

18 በዓለም ዙሪያ ከ91, 000 የሚበልጡ ጉባኤዎች በስብሰባዎችና በወንድማማች ኅብረት አማካኝነት ድጋፍና ማበረታቻ ይሰጣሉ። እንዲሁም እኛን በመንፈሳዊ ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑትን የጎለመሱ ክርስቲያኖችም ድጋፍ እናገኛለን። (ኤፌሶን 4:11-13) አዎን፣ የእውነትን እውቀት በመቀበላችን ያገኘነው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ነው። ይሖዋን ማወቅና ማገልገል የሚያስደስት ነገር ነው። “እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW ] ነው” ሲል የጻፈው መዝሙራዊ ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው።​—⁠መዝሙር 144:15

ታስታውሳለህን?

• በቅድመ ክርስትና ዘመን ይሖዋ እውቀት ያካፈለው ለማን ነው?

• መንፈሳዊው ብርሃን በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይበልጥ የደመቀው እንዴት ነው? በኋለኛው ዘመንስ?

• ስለ ይሖዋ ካገኘነው እውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖራችን ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል?

• ስለ አምላክ ባገኘነው እውቀት ደስ የሚለን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ለኖኅ፣ ለአብርሃም እና ለሙሴ ፈቃዱን ገልጾላቸዋል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዘመናችን ይሖዋ በቃሉ ላይ ብርሃን ፈንጥቋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተለያዩ ዘሮችን ካቀፈው የወንድማማች ማኅበራችን ስላገኘናቸው በረከቶች አስብ!