በመስጠት ከሚገኘው ደስታ ተካፋይ ሁኑ!
በመስጠት ከሚገኘው ደስታ ተካፋይ ሁኑ!
“ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” Nw ] ነው።”—ሥራ 20:35
1. ይሖዋ መስጠት ደስታ እንደሚያስገኝ ያሳየው እንዴት ነው?
እውነትን በማወቃችን ያገኘነው ደስታና ከእርሱ ጋር ተያይዘው የሚመጡት በረከቶች ከአምላክ ያገኘናቸው ውድ ስጦታዎች ናቸው። ይሖዋን የሚያውቁ ሰዎች የሚደሰቱባቸው ብዙ ምክንያቶች አሏቸው። ይሁንና አንድን ስጦታ መቀበል እንደሚያስደስት ሁሉ መስጠትም እንዲሁ ያስደስታል። ይሖዋ ‘የበጎ ስጦታ ሁሉና ፍጹም በረከት ሁሉ’ ምንጭ ሲሆን ‘ደስተኛ አምላክም’ ነው። (ያዕቆብ 1:17፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW ) ጆሮአቸውን ለሚሰጡ ሁሉ ጤናማውን ትምህርት የሚያካፍል ሲሆን ወላጆች ለሚሰጡት ፍቅራዊ መመሪያ ልጆቻቸው ምላሽ ሲሰጡ ደስ እንደሚላቸው ሁሉ ይሖዋም የሚያስተምራቸው ሰዎች በሚያሳዩት ታዛዥነት ይደሰታል።—ምሳሌ 27:11
2. (ሀ) ኢየሱስ ስለ መስጠት ምን ብሏል? (ለ) ሌሎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስናስተምር ምን ዓይነት ደስታ እናገኛለን?
2 በተመሳሳይም ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ለትምህርቱ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን ሲያገኝ ደስ ይለው ነበር። ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW ] ነው” እንዳለ ሐዋርያው ጳውሎስ ጠቅሷል። (ሥራ 20:35) መጽሐፍ ቅዱስን ለሌሎች ስናስተምር የምናገኘው ደስታ ከእኛ ሃይማኖታዊ እምነት ጋር የሚስማማ ሰው በማግኘታችን ብቻ የሚመነጭ የእርካታ ስሜት አይደለም። እውነተኛና ዘላቂ ጠቀሜታ ያለው ነገር እንደሰጠን ከመገንዘብ የሚመነጭ ነው። መንፈሳዊ ስጦታ በመስጠት ሰዎች ዛሬም ሆነ ለዘላለም ራሳቸውን እንዲጠቅሙ ልንረዳቸው እንችላለን።—1 ጢሞቴዎስ 4:8
መስጠት ደስታ ያስገኛል
3. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስና ሐዋርያው ዮሐንስ ሌሎችን በመንፈሳዊ በመርዳት ያገኙትን ደስታ የገለጹት እንዴት ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለገዛ ልጆቻችን ማካፈል የፍቅር መግለጫ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
3 አዎን፣ ይሖዋ እና ኢየሱስ መንፈሳዊ ስጦታን በማካፈል እንደሚደሰቱ ሁሉ ክርስቲያኖችም እንዲሁ ደስ ይላቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሌሎች ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የእውነት ቃል እንዲማሩ እንደረዳቸው ማወቁ ደስታ አስገኝቶለታል። በተሰሎንቄ ለነበረው ጉባኤ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን? እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።” (1 ተሰሎንቄ 2:19, 20) በተመሳሳይም ሐዋርያው ዮሐንስ መንፈሳዊ ልጆቹን በማስመልከት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም።” (3 ዮሐንስ 4) የገዛ ልጆቻችን መንፈሳዊ ልጆቻችን ጭምር እንዲሆኑ መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ አስብ! ልጆችን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ማሳደግ ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸው ፍቅር መግለጫ ነው። (ኤፌሶን 6:4) በዚህ መንገድ ወላጆች በለጋ ዕድሜ ላይ ያሉት ልጆቻቸው ዘላለማዊ ደህንነት እንደሚያሳስባቸው ያሳያሉ። ከልጆቻቸው ጥሩ ምላሽ ሲያገኙም ወላጆች ታላቅ ደስታና እርካታ ያገኛሉ።
4. በመንፈሳዊ መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ የሚያሳይ ምን ተሞክሮ አለ?
4 ዴል የሙሉ ጊዜ አቅኚና የአምስት ልጆች እናት ነች። እንዲህ ትላለች:- “አራቱ ልጆቼ ‘በእውነት እየሄዱ’ በመሆናቸው በውስጤ ካለው የአመስጋኝነት ስሜት አንጻር ሐዋርያው ዮሐንስ ከተናገራቸው ቃላት በስተ ጀርባ ያለውን ስሜት መረዳት አይከብደኝም። ቤተሰቦች በእውነተኛው አምልኮ አንድ ሆነው ሲጓዙ ለይሖዋ ክብር እንደሚያመጣ አውቃለሁ። በመሆኑም እውነትን በልጆቼ ውስጥ ለመትከል ያደረግሁትን ጥረት እንደባረከልኝ ስመለከት ጥልቅ እርካታ ይሰማኛል። ከቤተሰቤ ጋር ፍጻሜ በሌለው ሕይወት በገነት ውስጥ የመኖር ድንቅ አጋጣሚ እንዳለኝ ሳስብ ውስጤ በተስፋ ይሞላና ችግሮችና መሰናክሎች ቢኖሩብኝም እንኳ በጽናት እንድቋቋም ያንቀሳቅሰኛል።” የሚያሳዝነው ከዴል ሴት ልጆች መካከል አንዷ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ጎዳና በመከተሏ ምክንያት ከክርስቲያን ጉባኤ ተወግዳለች። ያም ሆኖ ግን ዴል አዎንታዊ አመለካከት ይዛ ለመቀጠል ትጥራለች። “ሴት ልጄ አንድ ቀን ራሷን ዝቅ አድርጋ በቀና ልብ ወደ ይሖዋ ትመለሳለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብላለች። “ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ ልጆቼ ይሖዋን እስከዛሬ ድረስ በታማኝነት ማገልገላቸውን ስመለከት አምላክን አመሰግናለሁ። ያገኘሁት ደስታ የኃይል ምንጭ ሆኖልኛል።”—ነህምያ 8:10
ዘላለማዊ ወዳጆች ማፍራት
5. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ራሳችንን ስንሰጥ ስለ ምን ነገር ማወቃችን እርካታ ያስገኝልናል?
5 ኢየሱስ ተከታዮቹ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት እንዲያፈሩና ስለ ይሖዋና እርሱ ስለሚፈልግባቸው ነገሮች እንዲያስተምሯቸው መመሪያ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይሖዋና ኢየሱስ ምንም ሳይቆጥቡ ሰዎች የእውነትን መንገድ እንዲማሩ ረድተዋቸዋል። በመሆኑም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ራሳችንን ስናቀርብ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እኛም የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን እንደሆነ ስለምናውቅ እርካታ እናገኛለን። (1 ቆሮንቶስ 11:1) በዚህ መንገድ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክና ከተወደደው ልጁ ጋር ስንተባበር ሕይወታችን እውነተኛ ትርጉም ይኖረዋል። ከአምላክ ጋር ‘አብረን የመሥራት’ መብት ማግኘት ምንኛ ታላቅ በረከት ነው! (1 ቆሮንቶስ 3:9) በዚህ ምሥራቹን በመስበኩ እንቅስቃሴ መላእክትም ድርሻ ያላቸው መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም?—ራእይ 14:6, 7
6. መንፈሳዊ ስጦታ በመስጠቱ ሥራ ስንካፈል እነማን ወዳጆቻችን ይሆናሉ?
6 እንዲያውም በዚህ መንፈሳዊ ስጦታ የማካፈል ሥራ ስንሳተፍ ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ከመሆንም አልፈን ከእርሱ ጋር ዘላለማዊ ወዳጅነት ልንመሠርት እንችላለን። አብርሃም በነበረው እምነት ምክንያት የይሖዋ ወዳጅ ተብሎ ተጠርቷል። (ያዕቆብ 2:23) እኛም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ስንጥር የእርሱ ወዳጆች ልንሆን እንችላለን። እንደዚያ ካደረግን የኢየሱስም ወዳጆች እንሆናለን። ለደቀ መዛሙርቱ “ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፣ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና” ሲል ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 15:15) ብዙ ሰዎች ከፍ ያለ ቦታ ያላቸው ወይም የታላላቅ ባለ ሥልጣናት ወዳጅ ሆነው በመቆጠራቸው ደስ ይላቸዋል። እኛ ግን በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ሁለት ታላላቅ አካላት ወዳጆች ተደርገን ነው የምንቆጠረው!
7. (ሀ) አንዲት ሴት እውነተኛ ወዳጅ ልታገኝ የበቃችው እንዴት ነው? (ለ) አንተስ ተመሳሳይ ተሞክሮ አግኝተሃል?
7 ከዚህም በላይ አምላክን እንዲያውቁ የምንረዳቸው ሰዎች የእኛም ወዳጆች ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ደስታ ይሰጠናል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ጆን ከአንዲት ቴልማ ከተባለች ሴት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ትጀምራለች። ቴልማ በጥናቷ ምክንያት ከቤተሰቧ ተቃውሞ ቢገጥማትም በአቋሟ በመጽናት ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠመቀች። ጆን እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ግንኙነታችን በዚያ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ወዳጅነታችን ከመጠንከሩ የተነሣ ይኸው እስከ ዛሬ ለ35 ዓመታት ያህል ሊዘልቅ ችሏል። ብዙ ጊዜ ወደ አገልግሎትና ወደ አውራጃ ስብሰባዎች አብረን ሄደናል። በመጨረሻ እኔ መኖሪያዬን ቀይሬ 800 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ቦታ ሄድሁ። ይሁንና ቴልማ ዘወትር እንደምታስታውሰኝ በመግለጽና ጓደኛና ምሳሌ ስለሆንኳት እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ስላስተማርኳት በማመስገን በጣም እንደምትወደኝ የሚገልጹ አስደሳች ደብዳቤዎችን ትልክልኛለች። እንዲህ ዓይነት የተወደደች የቅርብ ጓደኛ ማግኘቴ ስለ ይሖዋ እንድትማር እርሷን ለመርዳት ላደረግሁት ጥረት ታላቅ ካሳ ነው።”
8. በአገልግሎት ምን ዓይነት አዎንታዊ አመለካከት መያዛችን ይረዳናል?
8 የምናገኛቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች ለይሖዋ ቃል ግዴለሽ ወይም ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌላቸው ቢሆኑ እንኳ እውነትን መማር የሚፈልግ አንድ ሰው አገኛለሁ የሚለው ተስፋ እንድንጸና ሊረዳን ይችላል። እንዲህ ያለው የሰዎች ዝንባሌ እምነታችንን እና ጽናታችንን ሊፈታተነው ይችላል። ይሁንና አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ይረዳናል። ከጓቲማላ የመጣው ፎውስቶ እንዲህ ብሏል:- “ለሌሎች ሰዎች በምመሰክርበት ጊዜ የማነጋግረው ግለሰብ ወደፊት መንፈሳዊ ወንድም (ወይም እህት) ሊሆን ቢችል እንዴት ግሩም ይሆናል እያልኩ አብሰለስላለሁ። ቢያንስ ቢያንስ ከማነጋግራቸው ሰዎች መካከል አንዱ የኋላ ኋላ እውነትን ይቀበል ይሆናል ብዬ አስባለሁ። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በምሥክርነቱ ሥራ እንድገፋበት የረዳኝ ከመሆኑም ሌላ ደስተኛ እንድሆን አድርጎኛል።”
በሰማይ ሃብት ማከማቸት
9. ኢየሱስ በሰማይ መዝገብ ስለማከማቸት ምን ብሏል? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?
9 ልጆቻችንንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ጊዜ፣ ትዕግሥትና ጽናት ሊጠይቅ ይችላል። ብዙ ሰዎች ግን ደስታ ላያስገኝላቸውና ለዘላለም ላይዘልቅ የተትረፈረፈ ቁሳዊ ሀብት ለማከማቸት ላባቸው ጠብ እስኪል ለመሥራት ፈቃደኛ እንደሚሆኑ አስታውስ። ኢየሱስ መንፈሳዊ ሀብት ለማከማቸት መሥራት የተሻለ እንደሆነ ለአድማጮቹ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቈፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቈፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ።” (ማቴዎስ 6:19, 20) በጣም አስፈላጊ በሆነው ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ መካፈልን ጨምሮ መንፈሳዊ ግቦችን በመከታተል የአምላክን ፈቃድ እያደረግን እንዳለንና እርሱም መልሶ እንደሚክሰን በማወቃችን እርካታ እናገኛለን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር፣ . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።”—ዕብራውያን 6:10
10. (ሀ) ኢየሱስ መንፈሳዊ መዝገብ ማከማቸት የቻለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ራሱን የሰጠው እንዴት ነው? ይህስ ለሌሎች ምን ታላቅ ጥቅም አስገኝቷል?
10 ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ተግተን የምንሠራ ከሆነ ኢየሱስ እንዳለው ለራሳችን “በሰማይ መዝገብ” እየሰበሰብን ነው ማለት ነው። ይህም በመቀበል የሚገኘውን ደስታ እንድናጭድ ያደርገናል። ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት የምንሰጥ ከሆነ የኋላ ኋላ እኛም ባለጠጋ እንሆናለን። ኢየሱስ ራሱ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። በሰማይ ምን ዓይነት መዝገብ እንዳከማቸ እስቲ አስበው! ሆኖም ኢየሱስ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ አልፈለገም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[ኢየሱስ] ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ።” (ገላትያ 1:4፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ራሱን የሰጠው በአገልግሎቱ መስክ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰዎች በሰማይ መዝገብ የመሰብሰብ አጋጣሚ ያገኙ ዘንድ ሕይወቱንም ቤዛ አድርጎ በማቅረብ ነው።
11. መንፈሳዊ ስጦታዎች ከቁሳዊ ስጦታዎች የተሻሉ የሆኑት ለምንድን ነው?
11 ሰዎችን ስለ አምላክ በማስተማር እነርሱም የማይጠፋ መንፈሳዊ ሃብት እንዴት ማከማቸት እንደሚችሉ እንዲያስተውሉ እንረዳቸዋለን። ከዚህ የበለጠ ምን ስጦታ ልታካፍላቸው ትችላለህ? ለአንድ ወዳጅህ ውድ ዋጋ ያለው የእጅ ሰዓት፣ መኪና ሌላው ቀርቶ ቤት እንኳ ብትሰጠው ወዳጅህ በጣም እንደሚያመሰግንህና እንደሚደሰት ግልጽ ነው፤ አንተም በመስጠትህ ደስ ይልሃል። ይሁን እንጂ ከ20፣ ከ200 ወይም ከ2, 000 ዓመት በኋላ ስጦታው ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖረዋል? በሌላ በኩል ግን አንድ ሰው ይሖዋን እንዲያገለግል ለመርዳት ራስህን ብታቀርብ የረዳኸው ግለሰብ ከዚህ ስጦታ ለዘላለም ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
እውነትን የሚፈልጉ ሰዎችን ለማግኘት መጣር
12. ብዙዎች ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ሲሉ ራሳቸውን የሰጡት እንዴት ነው?
12 መንፈሳዊ ስጦታ ማካፈል ከሚያስገኘው ደስታ ተቋዳሽ ለመሆን የይሖዋ አገልጋዮች እስከ ምድር ዳር ድረስ ተጉዘዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አዲስ ቋንቋና ባሕል መልመድን በሚጠይቁባቸው አካባቢዎች በሚስዮናዊነት ለማገልገል ሲሉ የትውልድ ስፍራቸውንና ቤተሰባቸውን ጥለው ሄደዋል። ሌሎች ደግሞ በየአገራቸው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተንቀሳቅሰዋል። እንዲሁም የባዕድ አገር ቋንቋዎችን በመማር በአካባቢያቸው ላሉ ከውጭ አገር የመጡ ሰዎች መስበክ የሚችሉበትን አጋጣሚ የከፈቱም አሉ። ለምሳሌ ያህል በዩ ኤስ ኤ፣ ኒው ጀርሲ የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት ዛሬ በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በማገልገል ላይ ያሉትን ሁለት ልጆቻቸውን ካሳደጉ በኋላ የአቅኚነት አገልግሎት በመጀመር የቻይናን ቋንቋ ተማሩ። በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በአቅራቢያቸው በሚገኝ አንድ ኮሌጅ ለሚማሩ 74 የሚያክሉ የቻይና ቋንቋ ተናጋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መርተዋል። አንተስ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የበለጠ ደስታ ለማጨድ አገልግሎትህን ማስፋት ትችላለህ?
13. ይበልጥ ፍሬያማ የሆነ አገልግሎት ለማከናወን ምን ልታደርግ ትችላለህ?
13 ምናልባት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት እየናፈቅህ እስካሁን ድረስ አልተሳካልህ ይሆናል። በአንዳንድ ቦታዎች ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ምናልባት የምታገኛቸው ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት አይኖራቸው ይሆናል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራውን በጉጉት እንደሚከታተሉና በግ መሰል ወደ ሆኑ ሰዎች ሊመሩህ እንደሚችሉ በመገንዘብ ምኞትህን ከበፊቱ ይበልጥ ደጋግመህ በጸሎት ልትገልጽ ትችላለህ። ይበልጥ ተሞክሮ ካላቸው ወይም በአገልግሎታቸው ውጤታማ ከሆኑ የጉባኤህ አባላት ምክር ጠይቅ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጠውን ሥልጠናና የሚቀርቡትን ሐሳቦች ተጠቀምባቸው። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው ከሚሰጡት ምክር ተጠቀም። ከሁሉ በላይ ግን ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጥ። ጠቢቡ ሰው እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ማናቸው እንዲበቅል . . . አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ፣ በማታም እጅህን አትተው።” (መክብብ 11:6) ደግሞም እንደ ኖኅና ኤርምያስ ያሉ የታመኑ ሰዎችን ሁኔታ አስታውስ። ለስብከታቸው አዎንታዊ ምላሽ የሰጡት ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት ቢሆንም ያከናወኑት አገልግሎት ውጤታማ ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ ተደስቶበታል።
አቅማችሁ የሚፈቅድላችሁን ማድረግ
14. ይሖዋ ዕድሜያቸውን እርሱን በማገልገል ያሳለፉትን ሰዎች የሚያያቸው እንዴት ነው?
14 ሁኔታችሁ በአገልግሎት የምትፈልጉትን ያህል እንድትሠሩ አይፈቅድላችሁ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል የዕድሜ መግፋት በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን የምትችሉትን ነገር ሊገድብባችሁ ይችላል። ሆኖም ጠቢቡ ሰው “የሸበተ ጠጉር በጽድቅ መንገድ ሲገኝ የውበት ዘውድ ነው” በማለት እንደተናገረ አስታውሱ። (ምሳሌ 16:31 NW ) በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፋችሁት ሕይወት በእርሱ ዘንድ ውብ ነው። ከዚህም በላይ ቅዱስ ጽሑፉ “እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ [ይሖዋ] ነኝ፣ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻለሁ እኔም አነሣለሁ፤ እኔ እሸከማለሁ እኔም አድናለሁ” ይላል። (ኢሳይያስ 46:4) አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን የታመኑ አገልጋዮቹን እንደሚደግፍ ቃል ገብቷል።
15. ይሖዋ ሁኔታዬን ይረዳልኛል ብለህ ታምናለህ? ለምን?
15 ምናልባት ከሕመም፣ ከማያምን የትዳር ጓደኛ ከሚደርስባችሁ ስደት፣ ከከባድ የቤተሰብ ኃላፊነት ወይም ከሌሎች ችግሮች ጋር እየታገላችሁ ይሆናል። ይሖዋ ያለብንን የአቅም ገደብና ሁኔታዎቻችንን ይገነዘባል። እንዲሁም እርሱን ለማገልገል በምናደርገው ልባዊ ጥረት ምክንያት ይወድደናል። እኛ የምናከናውነው ተግባር ከሌሎች ያነሰ እንኳ ቢሆን ለእኛ የሚኖረው አመለካከት አይለወጥም። (ገላትያ 6:4) ይሖዋ ፍጹም እንዳልሆንን ያውቃል። ከእኛ የሚጠብቀውም ነገር ሚዛናዊ ነው። (መዝሙር 147:11) የተቻለንን ሁሉ ካደረግን በአምላክ ዓይን ውድ እንደሆንንና የእምነት ሥራችንንም እንደማይረሳ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—ሉቃስ 21:1-4
16. ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ መላው ጉባኤ አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
16 ደቀ መዝሙር የማድረጉ ጥረት የቡድን ሥራ መሆኑንም አስታውስ። ጠብታ ውኃ አንድን ተክል እንደማታረካ ሁሉ ብቻውን ደቀ መዝሙር የሚያፈራ ማንም ሰው የለም። ፍላጎት ያሳየን ሰው የሚያገኘውና መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናው አንድ ምሥክር ሊሆን እንደሚችል አይካድም። ይሁንና ያ አዲስ ሰው ወደ መንግሥት አዳራሽ ከመጣ በኋላ ግን እውነትን እንዲያስተውል የሚረዳው መላው ጉባኤ ነው። በመካከላቸው የሚታየው ሞቅ ያለ የወንድማማች መዋደድ የአምላክ መንፈስ እንዳላቸው የሚያሳይ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 14:24, 25) ሕፃናትና በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ ልጆች የሚያነቃቁ መልሶች መስጠታቸው በመካከላችን ያሉ ወጣቶች በዓለም ካሉት ወጣቶች የተለዩ መሆናቸውን ለእንግዳው ሰው የሚያረጋግጥ ይሆናል። በጉባኤ ውስጥ ያሉት የታመሙ፣ የአካል ጉዳት ያለባቸውና አረጋውያን ጽናት ምን ማለት እንደሆነ ለአዲሶች የሚያስገነዝቡ ምሳሌዎች ናቸው። የዕድሜ መግፋት ወይም ሌላ የአቅም ገደብ ቢኖርብንም አዲሶች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያላቸው ፍቅር ይበልጥ እያደገ እንዲሄድና ወደ ጥምቀት እድገት እንዲያደርጉ ሁላችንም ጠቃሚ ድርሻ እናበረክታለን። በአገልግሎት የምናሳልፈው እያንዳንዱ ሰዓት፣ እያንዳንዱ ተመላልሶ መጠየቅና በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ፍላጎት ካለው ሰው ጋር የምናደርገው እያንዳንዱ ውይይት በራሱ ሲታይ ይሄን ያህል የጎላ ጠቀሜታ ያለው ላይመስል ቢችልም ይሖዋ እያከናወነው ያለው ታላቅ ሥራ አካል ነው።
17, 18. (ሀ) ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ ከመካፈል በተጨማሪ በመስጠት ከሚገኘው ደስታ ልንካፈል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በመስጠት በሚገኘው ደስታ ስንካፈል የማንን ምሳሌ መኮረጃችን ነው?
17 እርግጥ በጣም አስፈላጊ በሆነው ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ከመካፈላችንም ሌላ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በሌሎች መንገዶችም በመስጠት ከሚገኘው ደስታ እንካፈላለን። እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍና የተቸገሩትን ለመርዳት የሚያስችል መዋጮ ለማድረግ የተወሰነ ገንዘብ ልንመድብ እንችላለን። (ሉቃስ 16:9፤ 1 ቆሮንቶስ 16:1, 2) የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ለማሳየት የሚያስችሉ ሌሎች አጋጣሚዎችንም ልንፈልግ እንችላለን። (ሮሜ 12:13) “ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም” ለማድረግ ልንጥር እንችላለን። (ገላትያ 6:10) እንዲሁም ደብዳቤ እንደ መጻፍ፣ ስልክ እንደ መደወል ስጦታ እንደ መስጠት፣ ተግባራዊ እርዳታ እንደ መለገስና የማበረታቻ ቃል እንደ መሰንዘር ባሉት ቀላል በሆኑ ነገር ግን የማይናቅ ድርሻ ባላቸው መንገዶችም ለሌሎች መስጠት እንችላለን።
18 በመስጠት ሰማያዊ አባታችንን እንደኮረጅነው እናሳያለን። እንዲሁም የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነውን የወንድማማች ፍቅር እናንጸባርቃለን። (ዮሐንስ 13:35) እነዚህን ነገሮች ማስታወሳችን በመስጠት ከሚገኘው ደስታ እንድንካፈል ይረዳናል።
ልታብራራ ትችላለህን?
• መንፈሳዊ ነገሮችን በመስጠት በኩል ይሖዋና ኢየሱስ ምሳሌ የሆኑት እንዴት ነው?
• ዘላለማዊ ወዳጆችን ማፍራት የምንችለው እንዴት ነው?
• አገልግሎታችን ይበልጥ የተሳካ እንዲሆን ምን እርምጃዎች ልንወስድ እንችላለን?
• በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ በመስጠት ከሚገኘው ደስታ መካፈል የሚችሉት እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆች የተሰጣቸውን ሥልጠና ሥራ ላይ ሲያውሉ ወላጆች ከፍተኛ የሆነ ደስታና እርካታ ያገኛሉ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ደቀ መዛሙርት በማፍራት እውነተኛ ወዳጆችን ልናገኝ እንችላለን
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በእርጅና ዘመናችን ይሖዋ ይሸከመናል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀላል በሆኑ ነገር ግን የማይናቅ ድርሻ ባላቸው መንገዶች በመስጠት ልንደሰት እንችላለን