በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን ፈትነነዋል

ይሖዋን ፈትነነዋል

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋን ፈትነነዋል

ፖል ስክራይብነር እንደተናገረው

“እንደምን አደሩ ሚስስ ስታክሃውስ? ከሰዎች የፋሲካ ኬክ ትእዛዝ እየተቀበልኩ ነው። እርስዎም ለቤተሰብዎ አንድ ማዘዝ እንደሚፈልጉ እርግጠኛ ነኝ።” ጊዜው የ1938 የጸደይ ወቅት መጀመሪያ ሲሆን አትኮ ኒው ጀርሲ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ ለጄነራል የዳቦ አቅራቢ ኩባንያ ተቀጥሬ እሠራ በነበረበት ጊዜ ለሽያጭ ወጥቼ ከአንድ ጥሩ ደንበኛችን ጋር እየተነጋገርኩ ነበር። የሚገርመው ሚስስ ስታክሃውስ ጥያቄዬን ሳይቀበሉ ቀሩ።

“አይ አይመስለኝም። ፋሲካን አናከብርም” አሉኝ።

ምን እንደምል ግራ ገባኝ። ፋሲካን አናከብርም? እርግጥ የሽያጭ የመጀመሪያው ደንብ ደንበኛህ ሁልጊዜ ትክክል ነው የሚል ነው። ታዲያ አሁን ምንድን ነው ማድረግ ያለብኝ? “በጣም ጥሩ ኬክ ነው። አሠራራችንን እንደሚወዱት ደግሞ አውቃለሁ። እ. እ. እ. . ፋሲካን ባታከብሩም እንኳ ቤተሰብዎ የሚወደው አይመስልዎትም?” በማለት ትንሽ ላግባባቸው ሞከርኩ።

“አይ አይመስለኝም” በማለት ደገሙልኝ። “ሚስተር ስክራይብነር፣ ስለ አንድ ነገር ላዋይዎ ሳስብ ነበር። ከሁሉ የተሻለው አጋጣሚ ደግሞ አሁን ይመስለኛል።” ይህ ውይይት ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ለውጦታል! ኒው ጀርሲ የሚገኘው የበርሊን ጉባኤ አባል የነበሩት ሚስስ ስታክሃውስ የፋሲካን በዓል አመጣጥ ካብራሩልኝ በኋላ ሦስት ቡክሌቶች ሰጡኝ። የመጀመሪያው ሴፍቲ፣ ሁለተኛው አንከቨርድ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ፕሮቴክሽን የሚል ነበር። ለማወቅ በመጓጓት ቡክሌቶቹን ይዤ ወደ ቤት ሄድኩ። ሆኖም ትንሽ ስጋት አድሮብኝ ነበር። ሚስስ ስታክሃውስ የተናገሩት ነገር በልጅነቴ ከማውቀው ጋር ትንሽ ይመሳሰል ነበር።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ መተዋወቅ

የተወለድኩት ጥር 31, 1907 ሲሆን ስምንት ዓመት ሲሞላኝ ማለትም በ1915 አባቴ በካንሰር ሞተ። በዚህም ምክንያት እኔና እናቴ ማልደን ማሳቹሴትስ በሚገኘው በወላጆቿ ትልቅ ቤት ውስጥ መኖር ጀመርን። ቤንጃሚን ራንሰም የተባለው የእናቴ ወንድምና ሚስቱ በዚሁ ቤት ሦስተኛ ፎቅ ላይ ይኖሩ ነበር። አጎቴ ቤን ሃያኛው መቶ ዘመን ከመጀመሩ በፊት በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል ከሚታወቁት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ይሰበሰብ ነበር። አጎቴን በጣም ብወደውም የሜቶዲስት እምነት ተከታዮች የሆኑት የእናቴ ቤተሰቦች ግን ልክ አንድ ችግር እንዳለበት ሰው አድርገው ይመለከቱት ነበር። ሚስቱ ከዓመታት በኋላ ፈትታዋለች፤ ከዚያ በፊት ግን በእምነቱ ምክንያት የአእምሮ ሕክምና ወደሚሰጥበት ቦታ ወስዳው ነበር! የሆስፒታሉ ዶክተሮች አጎቴ ቤን ጤነኛ መሆኑን ሲያረጋግጡ ወዲያው ይቅርታ ጠይቀው አሰናበቱት።

አጎቴ ቤን ቦስተን የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ሲሄድ እኔንም ይወስደኝ ነበር። በተለይ ጎብኚ ተናጋሪዎች በሚመጡበትና ልዩ ዝግጅት በሚኖርበት ወቅት ወደ ስብሰባዎች ይዞኝ ይሄዳል። በአንድ ወቅት ጎብኚ ተናጋሪው በወቅቱ የስብከቱን ሥራ በበላይነት ይቆጣጠር የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል ነበር። ሌላ ጊዜ ደግሞ የፍጥረት ፎቶ ድራማ የተባለው የስላይድ ፊልም የሚታይበት ልዩ አጋጣሚ ነበር። ይህ የሆነው በ1915 ቢሆንም አሁን ድረስ አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ተራራ ይዞት ሲወጣ የሚያሳየው ምስል በዓይነ ሕሊናዬ ቁልጭ ብሎ ይታየኛል። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 22) አብርሃምና ይስሐቅ እንጨት ተሸክመው ዳገቱን ሲወጡ አብርሃም ምን ያህል በይሖዋ ላይ ተማምኖ እንደነበረም አስታውሳለሁ። አባት ስላልነበረኝ ሁኔታው በጣም ነክቶኝ ነበር።

በኋላም አጎቴ ቤንና ባለቤቱ ወደ ሜን የተዛወሩ ሲሆን እናቴም በድጋሚ አገባችና ቤተሰቡን ይዛ ወደ ኒው ጀርሲ ሄደች። በመሆኑም አጎቴ ቤንን ለረዥም ጊዜ ሳላየው ቆየሁ። በመሃሉ ግን የአሥራዎቹ ዕድሜዬን ባሳለፍኩበት በኒው ጀርሲ ማሪዮን ኔፍ ከተባለች ልጅ ጋር ተዋወቅሁ። ማሪዮን ያደገችው ስምንት ልጆች ባሉት የፕሪስባይቴሪያን እምነት ተከታይ ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን ይህንን ቤተሰብ ሄዶ መጠየቅ ያስደስተኝ ነበር። ብዙ እሁድ ምሽቶችን ከዚህ ቤተሰብና ወጣቶችን ካቀፈው የቤተ ክርስቲያን ቡድን ጋር በማሳለፌ ብዙም ሳልቆይ እኔው ራሴ የፕሪስባይቴሪያን እምነት ተከታይ ሆንኩ። ያም ሆኖ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ስብሰባዎች ላይ የተማርኳቸውን አንዳንድ ትምህርቶች አልረሳኋቸውም ነበር። በ1928 ማሪዮንና እኔ ተጋባንና በ1935 እና በ1938 ዶሪስና ሉዊዝ የተባሉ ሴቶች ልጆችን ወለድን። አዲሱ ቤተሰባችን ድክ ድክ የምትል ሕፃንና አራስ ልጅ ስለነበረው እነዚህን ሕፃናት ለማሳደግ መንፈሳዊ መመሪያ እንደሚያስፈልገን ሆኖ ተሰማን።

ከቡክሌቶቹ እውነትን መማር

ማሪዮንና እኔ አባል የምንሆንበት አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት ለማግኘትና ከዚህ ጋር ለመሰብሰብ እቅድ አወጣን። በእያንዳንዱ እሁድ ተራ በመግባት አንዳችን ቤት ቆይተን ልጆቹን ስንጠብቅ አንዳችን ደግሞ ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን እንሄድ ነበር። አንድ ቀን ግን ቤት የመቆየት ተራው የማሪዮን ቢሆንም ሚስስ ስታክሃውስ ከሰጡኝ ቡክሌቶች ውስጥ ሴፍቲ የተባለውን ለማንበብ ስል ቤት ለመቆየት ፈቃደኛ ሆንኩ። ሆኖም አንዴ ማንበብ ከጀመርኩ በኋላ ማስቀመጥ አቃተኝ! የትኛውም ቤተ ክርስቲያን ሊሰጠኝ የማይችለውን ነገር እንዳገኘሁ ሆኖ ተሰማኝ። በሚቀጥለውም ሳምንት ተመሳሳይ ሁኔታ ተከሰተ። አንከቨርድ የተሰኘውን ቀጣይ ቡክሌት ለማንበብ ስል ቤት ቀርቼ ልጆቹን ለመጠበቅ ፈቃደኛ ሆንኩ። ሆኖም ያነበብኩት ሐሳብ ድሮ ከማውቀው ጋር ተመሳሰለብኝ። ይህ አጎቴ ቤን ያምንበት የነበረው ነገር ይሆን? ቤተሰባችን የእርሱ ሃይማኖት ውሉ የጠፋበት እንደሆነ ያምን ነበር። ማሪዮንስ ምን ትል ይሆን? ብዙ መጨነቅ አላስፈለገኝም። ቡክሌቱን ካነበብኩ ከጥቂት ቀን በኋላ ከሥራ ስመለስ “ቤት ያመጣሃቸውን እነዚያን ቡክሌቶች አነበብኳቸው። እንዴት ደስ ይላሉ!” ስትለኝ ተገረምኩ። ይህንን መስማቴ ለእኔ እፎይታ ነበር!

በቡክሌቶቹ ጀርባ ኢነሚስ የተባለውን በቅርቡ የወጣ መጽሐፍ የሚመለከት መረጃ ቀርቦ ነበር። ይህ መጽሐፍ የሃሰት ሃይማኖትን የሚያጋልጥ ሲሆን እኛም መጽሐፉን ለማግኘት ወሰንን። ሆኖም ቅጹን ሞልተን ከመላካችን በፊት አንድ ምሥክር ቤታችንን አንኳኩቶ ያንኑ መጽሐፍ ሰጠን። ይህ መጽሐፍ ውሳኔ ላይ እንድንደርስ ረድቶናል! ቤተ ክርስቲያን መሄዳችንን አቆምንና ኒው ጀርሲ ከሚገኘው ከካምደን የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር መሰብሰብ ጀመርን። ከጥቂት ወራት በኋላ እሁድ ሐምሌ 31, 1938 እኔን ጨምሮ 50 የሚሆኑ ሌሎች ሰዎች የፋሲካን ኬክ ለመሸጥ በሞከርኩበት በእህት ስታክሃውስ ቤት ግቢ ውስጥ ተሰብስበን ጀጅ ራዘርፎርድ የሰጠውን በቴፕ የተቀዳ የጥምቀት ንግግር አዳመጥን። ከዚያም 19 የምንሆነው ቤት ገብተን ልብሳችንን ቀየርንና አቅራቢያችን ባለው ጅረት ውስጥ ተጠመቅን።

አቅኚ ለመሆን ቆረጥኩ

ከተጠመቅሁ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በጉባኤያችን የምትገኝ አንዲት እህት የመስክ አገልግሎትን ዋነኛ ሥራቸው ስላደረጉ አቅኚ ስለሚባሉ ወንድሞች ነገረችኝ። ወዲያው የማወቅ ጉጉት ስላደረብኝ ከአንድ አቅኚ ቤተሰብ ጋር ተዋወቅሁ። በዕድሜ የገፋው ወንድም ኮኒግ ሚስቱና ሴት ልጁ አቅራቢያችን በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ አቅኚዎች ሆነው ያገለግሉ ነበር። ወጣት የቤተሰብ ራስ እንደመሆኔ መጠን የኮኒግ ቤተሰብ በአገልግሎቱ ባገኘው ጥልቅ ደስታ ተነካሁ። ብዙውን ጊዜ የዳቦ ማድረሻ መኪናዬን አንድ ጥግ አስይዝና ከዚህ ቤተሰብ ጋር ከቤት ወደ ቤት አገለግል ነበር። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ እኔው ራሴ አቅኚ መሆን ፈለግሁ። ግን እንዴት? ማሪዮንና እኔ ሁለት ትንንሽ ልጆች አሉን፤ ሥራዬ ደግሞ አድካሚ ነው። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ሲጀምር ብዙ ወጣቶች ከዩናይትድ ስቴትስ የጦር ኃይል ጎን በመሰለፋቸው በሥራ መስክ በተሰማራነው ላይ ጫና ተፈጥሮብን ነበር። ተጨማሪ የሽያጭ ጉዞ እንዳደርግ ጥያቄ እየቀረበልኝ ስለነበር በዚህ አያያዜ በምንም ዓይነት አቅኚ መሆን እንደማልችል ተገነዘብኩ።

አቅኚ መሆን እንደምፈልግ ለወንድም ኮኒግ ስነግረው “በይሖዋ አገልግሎት ጠንክረህ መሥራትህን ቀጥል። አቅኚ መሆን እንደምትፈልግ ለይሖዋ ከመንገር ወደኋላ አትበል። እርሱም ግብህ ላይ እንድትደርስ ይረዳሃል” ሲል መከረኝ። ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ልክ ወንድም ኮኒግ እንዳለኝ አደረግሁ። ብዙ ጊዜ ይሖዋ እኛ ሳንጠይቀው የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚያውቅ በሚያረጋግጡልን እንደ ማቴዎስ 6:​8 ባሉት ጥቅሶች ላይ አሰላስል ነበር። ከዚህም በላይ መንግሥቱንና ጽድቁን እንድናስቀድም የሚያበረታታንን በማቴዎስ 6:​33 ላይ የሰፈረውን ምክር ለመከተል እጥር ነበር። በተጨማሪም የዞን አገልጋይ (አሁን የወረዳ የበላይ ተመልካች ማለት ነው) የሆነው ወንድም ሜልቪን ዊንችስተር ማበረታቻ ሰጠኝ።

አቅኚ የመሆን ግብ እንዳለኝ ለማሪዮን ነገርኳትና ይሖዋን በመፈተን በረከትን ያፈስስልን እንደሆነና እንዳልሆነ እንድናረጋግጥ በሚያበረታቱን የሚልክያስ 3:​10 ቃላት ላይ ተወያየን። ማሪዮን “አቅኚ መሆን ከፈለግህ በእኔ ምክንያት ወደ ኋላ አትበል። አንተ አቅኚ ሆነህ ስታገለግል እኔ ደግሞ ልጆቹን እንከባከባለሁ። ደግሞም ብዙ ቁሳዊ ነገሮች አያስፈልጉንም” በማለት የሰጠችኝ መልስ አበረታታኝ። በትዳር 12 ዓመት ስንኖር ማሪዮን ቆጣቢና ጥንቁቅ የቤት እመቤት መሆኗን አውቄአለሁ። ባለፉት ዓመታት ሁሉ ማሪዮን ጥሩ የአገልግሎት ጓደኛ የሆነችኝ ሲሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፍናቸው 60 ዓመታት ውስጥ ላገኘነው ስኬት አንዱ ምስጢር ባሉን ጥቂት ቁሳዊ ነገሮች የመርካትና እነርሱኑ አብቃቅታ ብዙ የማስመሰል ችሎታዋ ነው።

በ1941 የበጋ ወቅት ብዙ ወራት ከፈጀ ጸሎትና እቅድ በኋላ ማሪዮንና እኔ ባጠራቀምናት ጥቂት ገንዘብ ለቤተሰባችን መኖሪያ የምትሆን አምስት በአምስት ተጎታች ቤት ገዛን። ከዚያም ሥራዬን አቆምኩና ሐምሌ 1941 የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከዚህ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ እገኛለሁ። የመጀመሪያው ምድቤ ከኒው ጀርሲ ሴንት ሉዊስ በሚወስደው ራውት 50 በተባለው ጎዳና 10 ፌርማታ ርቆ የሚገኝ ቦታ ነበር። በዚህ ቦታ ደግሞ ነሐሴ መጀመሪያ ላይ ትልቅ ስብሰባ ለማድረግ ታቅዶ ነበር። በመንገዳችን ላይ የምናገኛቸው ወንድሞችና እህቶች ስምና አድራሻ ተልኮልኝ ስለነበር መቼ እንደምመጣ አስቀድሜ ጻፍኩላቸው። ስብሰባው ቦታ ስንደርስ ግን ከአቅኚነት አገልግሎት ዴስክ ሌላ ምድብ መቀበል ነበረብኝ።

“ይሖዋን ልፈትነው ነው”

ትንሿን ተጎታች ቤታችንን በጽሑፎች ሞላንና በካምደን የመጨረሻ ስብሰባችንን ለማድረግና እግረ መንገዳችንንም ወንድሞችን ለመሰናበት ሄድን። እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ትንንሽ ልጆች ይዘን ከስብሰባው በኋላ የምንሄድበትን ቦታ ሳናውቅ መነሣታችን አንዳንድ ወንድሞችን ሳያስገርማቸው አልቀረም። አብዛኞቹም “ብዙም ሳትቆዩ ትመለሳላችሁ” ብለውን ነበር። “አንመለስም ማለት አልችልም። ሆኖም ይሖዋ እንደሚንከባከበን ቃል ገብቶልናል። ስለዚህ እርሱን ልፈትነው ነው” የሚል መልስ መስጠቴን አስታውሳለሁ።

ከማሳቹሴትስ እስከ ሚሲሲፒ ባሉት 20 ከተሞች ውስጥ ስድስት አሥርተ ዓመታት በአቅኚነት ካሳለፍን በኋላ ይሖዋ ቃሉን ከሚገባው በላይ ጠብቋል ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። በማሪዮን፣ በእኔና በሁለቱ ሴቶች ልጆቼ ላይ ያፈሰሰው በረከት በ1941 ይሆናል ብለን ልንገምተው ከምንችለው በላይ ነው። እነዚህ በረከቶች ሁለቱ ልጆቻችን በአቅራቢያችን ባሉት ጉባኤዎች ውስጥ ታማኝ አቅኚዎች ሆነው ማገልገላቸውን እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ ምሥራቃዊ ጠረፍ ተበታትነው የሚያገለግሉ ወደ መቶ የሚጠጉ መንፈሳዊ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ማግኘትን ይጨምራል። ሃምሳ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ የረዳሁ ሲሆን ማሪዮን ደግሞ 48 የሚያክሉ ሰዎች ረድታለች።

ነሐሴ 1941 ወደ ሴንት ሉዊስ የተጓዝን ሲሆን እዚያም በቤቴል ከሚያገለግለው ከወንድም ቲ ጄ ሱልቪያን ጋር ተገናኘን። ጦርነት አጥልቶና ወንዶች ለውትድርና ይመለመሉ ስለነበር አገልጋይ ሆኜ እንደተሾምኩ የሚገልጽ ደብዳቤ ያስፈልገኝ ነበር። ወንድም ሱልቪያን ይህን ደብዳቤ አመጣልኝ። ማሪዮን እኔ በአገልግሎቱ የማሳልፈውን ያህል ሰዓት በአገልግሎት እንደምታሳልፍና አቅኚ መሆንም እንደምትፈልግ ለወንድም ሱልቪያን ነገርኩት። በስብሰባው ቦታ የአቅኚነት አገልግሎት ዴስክ ገና ያልተደራጀ ቢሆንም ወንድም ሱልቪያን ማሪዮንን ወዲያውኑ በአቅኚዎች ዝርዝር ውስጥ ጨመራትና “ከስብሰባው በኋላ አቅኚ ሆናችሁ የምታገለግሉት የት ነው?” ሲል ጠየቀን። እንዳላወቅን ነገርነው። “ስጋት አይግባችሁ። በስብሰባው ላይ አቅኚዎችን በሚፈልግ ክልል ውስጥ ያለ ሰው ታገኙና ችግራችሁ ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። ወዲያው የት እንዳላችሁ ከጻፋችሁልን የሹመት ደብዳቤውን እንልክላችኋለን” አለን። ሁኔታው ልክ እርሱ እንዳለው ሆነ። ቀድሞ የዞን አገልጋይ የነበረው ወንድም ጃክ ደዊት በኒው ማርኬት ቨርጂኒያ ተጨማሪ አቅኚዎችን የሚፈልግ የአቅኚዎች ቡድን እንዳለ ሲነግረን ከስብሰባው በኋላ ወደ ኒው ማርኬት አቀናን።

ኒው ማርኬት ስንደርስ ያልጠበቅነው አቀባበል ተደረገልን። ቤንጃሚን ራንሰም ከእኛ ጋር በአቅኚነት አገልግሎት ለመካፈል ከፊላዴልፊያ ይመጣል ብዬ ፈጽሞ አልገመትኩም! አዎን፣ የመጣው አጎቴ ቤን ነበር። ቦስተን እያለሁ የእውነትን ዘር በልቤ ውስጥ ከተከለ ከ25 ዓመታት በኋላ ከእርሱ ጋር ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ምንኛ አስደሳች ነው! ለዓመታት ከቤተሰቡ ግድ የለሽነት፣ ፌዝና ስደት ሳይቀር ቢደርስበትም ለይሖዋና ለአገልግሎቱ ያለውን ፍቅር ፈጽሞ አላጣም።

ኒው ማርኬት በሚገኘው የአቅኚዎች ቤት ውስጥ ለስምንት ወራት ያደረግነው ቆይታ አስደሳች ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከተማርናቸው ነገሮች መካከል ጽሑፎችን በዶሮዎችና በእንቁላሎች መለወጥ ይገኝበታል። ከዚያም አጎቴ ቤን፣ ማሪዮን፣ እኔ እና ሌሎች ሦስት ሰዎች በሃንኦቨር ፔንሲልቬኒያ ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል ተመደብን። ይህ ምድብ ፔንሲልቬኒያ በቆየንባቸው ከ1942 እስከ 1945 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከተሰጡን ስድስት ምድቦች መካከል የመጀመሪያው ነበር።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ልዩ አቅኚዎች ሆኖ ማገልገል

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በገለልተኝነት አቋማችን የተነሳ የጥላቻ ዒላማ የነበርን ቢሆንም የይሖዋ ድጋፍ ፈጽሞ ተለይቶን አያውቅም። በአንድ ወቅት ማሳቹሴትስ ፕሮቪንስታውን ውስጥ እያለሁ አሮጌዋ ቢዩክ መኪናችን ተበላሸች። ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ስለነበረብኝ ከፍተኛ ጥላቻ ባለው የካቶሊክ መንደር ውስጥ ማለፌ የግድ ነበር። መጓዝ ስጀምር ዱርዬዎቹ ለይተው ስላወቁኝ መጮኽ ጀመሩ። የሚወረውሩት ድንጋይ በጆሮዬ በኩል ሽው እያለ ያልፍ ነበር። ወጣቶቹ እየተከተሉኝ እንዳልሆነ ተስፋ በማድረግ ፈጠን ፈጠን እያልኩ መራመድ ጀመርኩ። ከዚያ ጉዳት ሳይደርስብኝ ፍላጎት ያሳየው ሰው ቤት ደረስኩ። ሰውዬው የተከበረ የአሜሪካ ሠራዊት አባል ሲሆን “ለካ ዛሬ ፊልም ለማየት ወደ መኻል ከተማ እንደምንሄድ አልነገርኩህም። ይቅርታ አድርግልኝ። ዛሬ ላነጋግርህ አልችልም” ሲለኝ ማዕዘኑ ላይ የሚጠብቁኝ ድንጋይ የሚወረውሩ ዱርዬዎች ትዝ አሉኝና ደነገጥኩ። ይሁን እንጂ ሰውዬው “ታዲያ ለምን እስከዚያ ድረስ ከእኛ ጋር አብረህ አትሄድም። በዚያውም ትንሽ መነጋገር እንችላለን” ሲለኝ ተደሰትኩ። በዚህ ጊዜ ለሰውዬው ጥሩ ምሥክርነት የሰጠሁት ሲሆን ያንን አደገኛ ክልልም ምንም ጉዳት ሳይደርስብኝ አለፍኩ።

ቤተሰብንና አገልግሎትን ሚዛናዊ ማድረግ

ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ልዩና የዘወትር አቅኚ በመሆን በቻርሎትስቫይል ያደረግነውን የስምንት ዓመት ቆይታ ጨምሮ በቨርጂኒያ ብዙ የአገልግሎት ምድቦች ተሰጥተውናል። በ1956 ሁለቱም ልጆቼ በማግባታቸው እኔና ማሪዮን በሃሪስንበርግ ቨርጂኒያ በአቅኚነት እንዲሁም በሊንኮልተን ኖርዝ ካሮላይና በልዩ አቅኚነት ማገልገል ጀመርን።

በ1966 ወንድም ዊንቼስተር በ1930ዎቹ ዓመታት በኒው ጀርሲ ያደርግልን እንደነበረው ወንድሞችን ለማበረታታት ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላ ጉባኤ በመጓዝ በወረዳ ሥራ እንዳገለግል ተመደብኩ። ለሁለት ዓመታት በቴናሲ የሚገኙ ጉባኤዎችን አገልግያለሁ። ከዚያም ማሪዮንና እኔ በጣም ወደምንወደው የአገልግሎት መስክ ማለትም ወደ ልዩ አቅኚነት እንድንመለስ ተጠየቅን። ከ1968 እስከ 1977 ባሉት ዓመታት በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስና ከጆርጂያ እስከ ሚሲሲፒ ባሉት የተለያዩ ቦታዎች በልዩ አቅኚነት አገልግለናል።

ኢስት ማን ጆርጂያ ውስጥ ለብዙ ዓመታት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለገለውንና አሁን ዕድሜው በመግፋቱ ጤናው እያሽቆለቆለ የሄደውን ፓውል ኪርክላንድን በመተካት የጉባኤ የበላይ ተመልካች (አሁን ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ማለት ነው) ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። በጣም አመስጋኝና ተባባሪ ነበር። በጉባኤው ውስጥ ግጭት በመፈጠሩና በግጭቱ መካከልም አንዳንድ ጎላ ብለው የሚታዩ ግለሰቦች ስለነበሩ የእርሱ ድጋፍ የግድ ያስፈልግ ነበር። ሁኔታው በጣም በመባባሱ ለይሖዋ በመጸለይ ብዙ ሰዓታት አሳልፌያለሁ። በዚህ ወቅት “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” እንደሚለው የምሳሌ 3:​5, 6 ያሉ ጥቅሶች ወደ አእምሮዬ ይመጡ ነበር። ነገሮችን ነጻና ግልጽ በሆነ መንገድ ለመወያየት ጥረት በማድረግ ለሁሉም በሚጠቅም መንገድ የጉባኤውን አንድነት መጠበቅ ችለናል።

በ1977 የዕድሜ መግፋት የሚያስከትለው ተጽእኖ እየተሰማን ስለመጣ ሁለቱ ልጆቻችን ከነቤተሰቦቻቸው በሚኖሩበት በቻርሎትስቫይል አካባቢ እንድናገለግል በድጋሚ ተመደብን። ላለፉት 23 ዓመታት በዚህ አካባቢ በማገልገል ቨርጂኒያ ሩከርስቪሊ የተባለ ጉባኤ እንዲቋቋም በመርዳታችን እንዲሁም የቀድሞ መጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ልጆችና የልጅ ልጆች የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ አቅኚዎችና ቤቴላውያን ሲሆኑ በማየታችን ተደስተናል። ማሪዮንና እኔ አሁንም ጥሩ የአገልግሎት ፕሮግራም ያለን ሲሆን መጽሐፍ ጥናት በመምራትና የሕዝብ ንግግሮች በመስጠት ቻርሎትስቫይል በሚገኘው ኢስት ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ በንቃት አገለግላለሁ።

ባለፉት ዓመታት በሁሉም ላይ እንደሚደርሰው በእኛም ላይ ችግር ደርሶብን ነበር። ለምሳሌ ምንም ያህል ብንጥርም ዶሪስ በአሥራዎቹ ዕድሜዋ መጨረሻ አካባቢ ለተወሰነ ጊዜ በመንፈሳዊ በመዳከሟ ምሥክር ያልሆነ ሰው አገባች። ሆኖም ለይሖዋ ያላትን ፍቅር ሙሉ በሙሉ አላጣችም ነበር። ልጅዋ ቢል ዎልኪል ኒው ዮርክ በሚገኘው ቤቴል ውስጥ ለ15 ዓመታት አገልግሏል። ዶሪስና ሉዊዝ አሁን ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ቢሆኑም አቅኚዎች ሆነው አቅራቢያቸው በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ ያገለግላሉ።

በእነዚህ ዓመታት ያገኘናቸው ትምህርቶች

ይሖዋን ስኬታማ በሆነ መንገድ ለማገልገል የሚረዱ ጥቂት መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግን ተምሬአለሁ። ሕይወትህን ቀላል አድርግ። የግል ሕይወትህን ጨምሮ በሁሉም የሕይወትህ ዘርፎች ምሳሌ ሁን። “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚሰጠውን መመሪያ በሁሉም የሕይወትህ ዘርፍ ተግባራዊ አድርግ።​—⁠ማቴዎስ 24:​45

ማሪዮን ልጆች እያሳደጉ ስኬታማ አቅኚ ለመሆን የሚረዱ አጫጭር ግን ውጤታማ ምክሮች ያዘለ ዝርዝር አዘጋጅታ ነበር። ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ፕሮግራም አውጣ። እንዲሁም በሥራ ተርጉመው። የአቅኚነትን አገልግሎት ሥራዬ ብለህ ያዝ። ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ ተመገብ። በቂ እረፍት አድርግ። በመዝናኛ ረገድ ልከኛ ሁን። ሁሉንም የአገልግሎት ዘርፎች ጨምሮ እውነት በልጆችህ ሕይወት ውስጥ አስደሳች ነገር እንዲሆን አድርግ። አገልግሎቱ ሁልጊዜ አስደሳች እንዲሆንላቸው አድርግ።

አሁን ዕድሜያችን 90ዎቹ ውስጥ ገብቷል። የመጀመሪያውን የጥምቀት ንግግር በእህት ስታክሃውስ ግቢ ውስጥ ከሰማን ስልሳ ሁለት ዓመታት አልፈዋል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ደግሞ 60 ዓመታት አሳልፈናል። ማሪዮንና እኔ ባሳለፍነው ሕይወት በጥልቅ ረክተናል ብለን በሙሉ ልባችን መናገር እንችላለን። ወጣት አባት በነበርኩበት ወቅት መንፈሳዊ ግቦችን እንዳወጣና እነርሱ ላይ ለመድረስ ጥረት እንዳደርግ ለተሰጠኝ ማበረታቻ እንዲሁም ለውዷ ባለቤቴ ለማሪዮንና ባለፉት ዓመታት ሁለቱ ልጆቼ ለሰጡን ድጋፍ ከልብ አመስጋኝ ነኝ። ቁሳዊ ሃብት ባይኖረንም አብዛኛውን ጊዜ ‘እንደ እኔስ የበላና የጠጣ ማን ነው?’ የሚሉት የመክብብ 2:​25 [NW ] ቃላት በእኔ ላይ እንደሚሠሩ ሆኖ ይሰማኛል።

በእርግጥም በእኛ ሁኔታ እንደታየው ይሖዋ በሚልክያስ 3:​10 ላይ የሰጠውን ተስፋ እጅግ አብልጦ ፈጽሟል። ‘ምንም እስከማይጎድለን ድረስ በረከትን አትረፍርፎ አፍስሶልናል!’

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የጦርነቱ ዓመታት ትዝታዎች

ጦርነቱ ካበቃ 60 የሚጠጉ ዓመታት ቢያልፉም መላው ቤተሰብ ስለ እነዚያ የጦርነት ዓመታት የማይጠፉ ትዝታዎች አሉት።

“ፔንሲልቬኒያ ቀዝቃዛ ይሆን ነበር” ስትል ዶሪስ ታስታውሳለች። “በአንድ ምሽት ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች 35 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሶ ነበር።” ሉዊዝ እንዲህ ትላለች:- “ዶሪስና እኔ በአሮጌዋ ቢዩክ መኪናችን ኋለኛ መቀመጫ ላይ ሆነን አንዳችን በሌላዋ እግር ላይ በመቀመጥ እግራችንን እናሞቅ ነበር።”

ዶሪስ “ሆኖም ፈጽሞ ድሆች እንደሆንን ወይም የቀረብን ነገር እንዳለ ሆኖ ተሰምቶን አያውቅም” በማለት ታክላለች። “ከብዙ ሰዎች በተለየ መኖሪያችንን ቶሎ ቶሎ ብንቀያይርም ሁልጊዜ ጥሩ እንመገብና ጥራት ያላቸው ልብሶች እንለብስ ነበር። እነዚህን ልብሶች የሚሰጡን ኦሃዮ የሚገኙ ከእኛ ትንሽ ከፍ ከፍ የሚሉ ልጆች ያሏቸው ወዳጆቻችን ነበሩ።”

“እማማና አባባ ሁልጊዜ እንደሚወድዱንና እንደሚያደንቁን እንዲሰማን ያደርጉ ነበር” በማለት ሉዊዝ ትናገራለች። “በአገልግሎት አብረናቸው ብዙ ሰዓት እናሳልፍ ነበር። ይህም ልዩ ስሜት እንዲያድርብንና ይበልጥ ወደ እነርሱ እንደቀረብን ሆኖ እንዲሰማን አድርጎናል።”

“በ1936 የተሠራች ለየት ያለች ቢዩክ መኪና ነበረችኝ” በማለት ፖል ያስታውሳል። “እነዚህ መኪናዎች ደግሞ ሻሲ በመስበር የታወቁ ነበሩ። እኔ እንደሚመስለኝ የሞተሩ ኃይል ከሌሎቹ የመኪናው ክፍሎች አቅም ጋር የሚመጣጠን አልነበረም። ይህ ደግሞ ሁልጊዜ የሚከሰተው ብርዳማ በሆኑት ምሽቶች ላይ የነበረ ይመስላል። ከዚያ ወደ ወዳደቁ መኪናዎች ሄጄ ሌላ ሻሲ መፈለግ ነበረብኝ። በኋላ ግን ሻሲ በመለወጡ ሥራ ተካንኩ።”

ማሪዮን ደግሞ “የራሽን ካርዱም የሚረሳ አይደለም” ትላለች። “በወቅቱ ሥጋ፣ ቤንዚንና ለመኪና የሚሆነውን ጎማ ጨምሮ ሁሉም ነገር የሚሰጠው በራሽን ነበር። ወደ አንድ አዲስ ምድብ በሄድን ቁጥር የራሽን ካርድ እንዲሰጠን ማመልከት ነበረብን። ይህንን ካርድ ማግኘት በወራት የሚቆጠር ጊዜ ይፈጃል። ብዙውን ጊዜ ደግሞ የራሽን ካርዱ እንደተሰጠን ወደ ሌላ የአገልግሎት ምድብ እንዛወር ነበር። በአዲሱ ምድባችንም እንዲህ ዓይነቱን ውጣ ውረድ እንደገና ሀ ብለን እንጀምር ነበር። ይሖዋ ግን ሁልጊዜ ተንከባክቦናል።”

[ሥዕል]

በ1918 የአሥራ አንድ ዓመት ልጅ ሳለሁ ከእናቴ ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1948 ልጆቼ ሲጠመቁ ከሉዊዝ፣ ከማሪዮንና ከዶሪስ ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥቅምት 1928 ለሠርጋችን የተነሳነው ፎቶ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1955 ልጆቼ (በስተ ግራና በስተ ቀኝ ጥግ) እና እኔ በያንኪ ስታዲየም

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ2000 ማሪዮንና እኔ ከልጆቻችን ከዶሪስ (በስተ ግራ) እና ሉዊዝ ጋር