በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥርጣሬ እምነትህን እንዲያጠፋ አትፍቀድ

ጥርጣሬ እምነትህን እንዲያጠፋ አትፍቀድ

ጥርጣሬ እምነትህን እንዲያጠፋ አትፍቀድ

አንድ ቀን ጥሩ ጤንነት እንዳለህ ይሰማሃል። በማግሥቱ ደግሞ እንደማመም ይልህና በድንገት አቅም አጥተህ መንቀሳቀስ ያቅትሃል። ራስህን ያምሃል እንዲሁም ሰውነትህን ይቆረጣጥምሃል። ምን ነካህ? አደገኛ የሆኑ በሽታ አምጪ ሕዋሳት የሰውነትህን በሽታ የመከላከል አቅም አዳክመው ዋና ዋና የሰውነት አካልህን አጥቅተዋል። ቶሎ ሕክምና ካላገኘህ እነዚህ በሽታ አምጪ ሕዋሳት የማይድን በሽታ ሊያመጡብህ አልፎ ተርፎም ሊገድሉህ ይችላሉ።

እርግጥ ነው፣ የታመምከው ሰውነትህ ተዳክሞ እያለ ከነበረ በይበልጥ ሊያጠቃህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል የተመጣጠነ ምግብ በማጣት ምክንያት ሰውነትህ ተዳክሞ ከነበረ በሽታ የመከላከል አቅምህ “በጣም ዝቅተኛ ስለሚሆን የመጨረሻ ቀላል የሚባል በሽታ እንኳን ሞት ሊያስከትልብህ ይችላል” በማለት ፒተር ዊንጌት የተባሉ ስለ ሕክምና የሚጽፉ ሰው ተናግረዋል።

እንግዲያው ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ እየተራበ መኖር የሚፈልግ ማን ይኖራል? በሚገባ በመመገብ ጤነኛ ሆነህ ለመኖር የተቻለህን ማድረግ እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። በተጨማሪም በቫይረስ ወይም በባክቴሪያ አማካኝነት በሚመጡ በሽታዎች እንዳትጠቃ የምትችለውን ሁሉ እንደምታደርግ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ‘በእምነት ጤናማ’ ሆኖ በመኖር ረገድም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ጥንቃቄ ታደርጋለህ? (ቲቶ 2:​2) ለምሳሌ ያህል ረቂቅ በሆነ መንገድ የሚዘሩ ጥርጣሬዎች አደጋ እንዳያስከትሉብህ ትጠነቀቃለህ? በዚህ መንገድ የሚዘሩ ጥርጣሬዎች በቀላሉ በአእምሮህና በልብህ ውስጥ ሊሰራጩና እምነትህንና ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ሊያበላሹብህ ይችላሉ። አንዳንድ ሰዎች ይህ ሁኔታ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል የተገነዘቡ አይመስልም። ራሳቸውን ለመንፈሳዊ ረሃብ በማጋለጥ በጥርጣሬ እንዲዋጡ ይፈቅዳሉ። በአንተም ላይ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊደርስ ይችል ይሆን?

ጥርጣሬ​—⁠ሁልጊዜ ጎጂ ነውን?

ሁሉም ዓይነት ጥርጣሬ ጎጂ እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። አንዳንድ ጊዜ አንድን ነገር ከመቀበልህ በፊት እውነት መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልግህ ይሆናል። የሚነገርህን ሁሉ ሳትጠራጠር መቀበል አለብህ የሚል ሃይማኖታዊ ምክር አደገኛና አታላይ ነው። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “ሁሉን ያምናል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 13:​7) አንድ አፍቃሪ ክርስቲያን ቀደም ሲል በታማኝነታቸው የሚያውቃቸው ሰዎች የሚናገሩትን ሳይጠራጠር ይቀበላል። ሆኖም የአምላክ ቃል ‘ቃልን ሁሉ ከማመን’ እንድንቆጠብ ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 14:​15) አንዳንድ ጊዜ የአንድ ሰው ያለፈ ታሪክ እንድንጠራጠር የሚያደርግ ምክንያት ሊሰጠን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “[አታላይ ሰው] በቃሉ አሳምሮ ቢናገርህ አትመነው” በማለት ያስጠነቅቃል።​—⁠ምሳሌ 26:​24, 25

ሐዋርያው ዮሐንስም ክርስቲያኖች በጭፍን የሚያምኑ እንዳይሆኑ አስጠንቅቋል። “መንፈስን [“በመንፈስ የተነገሩ ቃላትን፣” NW ] ሁሉ አትመኑ፣ ነገር ግን መናፍስት [“በመንፈስ የተነገሩት ቃላት፣” NW ] ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:​1) አንድ ‘ቃል፣’ አንድ ትምህርት ወይም ሐሳብ ከአምላክ የመነጨ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ በእርግጥ ከአምላክ የመጣ ነውን? ሐዋርያው ዮሐንስ “ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና” በማለት ስለተናገረ በመጠኑም ቢሆን መጠራጠር ወይም ለመቀበል አለመቸኮል በእርግጥም ጥበቃ ሊሆን ይችላል።​—⁠2 ዮሐንስ 7

መሠረተ ቢስ ጥርጣሬ

አዎን፣ አንድ ነገር እውነት መሆኑን በቅን ልቦና ተነሳስቶ በትሕትና መመርመር ብዙውን ጊዜ አስፈላጊ ነው። ይህ ጽኑ እምነታችንን እንዲሁም ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ሊያናጋ የሚችል መሠረተ ቢስና ጎጂ የሆነ ጥርጣሬን በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ እንዲያድግ ከመፍቀድ የተለየ ነው። ይህ ዓይነቱ ጥርጣሬ ብዙውን ጊዜ እምነት እንድናጣ በማድረግ ወይም አመለካከታችንን በማዛባት ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ እንቅፋት ይሆንብናል። ሔዋን ይሖዋን እንድትጠራጠር ለማድረግ ሰይጣን በአእምሮዋ ውስጥ ጥርጣሬ እንዴት እንደዘራ ታስታውሳለህ? “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?” በማለት ጠየቃት። (ዘፍጥረት 3:​1) ይህ ቅን የሚመስል ጥያቄ የፈጠረባት ጥርጣሬ በውሳኔዋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይህ የሰይጣን ዓይነተኛ ዘዴ ነው። በመርዛማ ብዕሩ እንደሚናደፍ ጸሐፊ የአግቦ አነጋገርን፣ ከፊል እውነትነት ያላቸውን ነገሮችና ሐሰትን መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም ረገድ የተካነ ነው። ሰይጣን በዚህ መንገድ ጥርጣሬ በመዝራት ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን ጤናማና በመተማመን ላይ የተመሠረቱ ወዳጅነቶችን አበላሽቷል።​—⁠ገላትያ 5:​7-9

ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ይህ ዓይነቱ ጥርጣሬ የሚያስከትለውን ጉዳት በግልጽ ተገንዝቧል። ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ አምላክን በነፃነት የመቅረብ ግሩም መብት እንዳለን ጽፏል። ሆኖም ያዕቆብ ወደ አምላክ የሚጸልይ ሰው “በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን” በማለት አስጠንቅቋል። ከአምላክ ጋር ባለን ወዳጅነት ረገድ ተጠራጣሪዎች ከሆንን ‘በነፋስ እየተገፋና እየተነቃነቀ እንዳለ የባሕር ማዕበል’ ያደርገናል። ‘ሁለት አሳብ እንዳለው በመንገዱ ሁሉ እንደሚወላውል’ ሰው እንሆናለን። (ያዕቆብ 1:​6-8) እምነታችን በጥርጣሬ ሊሞላና በመጨረሻም ወላዋይ ልንሆን እንችላለን። ከዚያም በሔዋን ላይ እንደደረሰው አደገኛ ለሆኑ ለሁሉም ዓይነት አጋንንታዊ ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች ጥቃት የተጋለጥን እንሆናለን።

ጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት ይኑርህ

እንግዲያው ራሳችንን ጎጂ ከሆነ ጥርጣሬ መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? መልሱ በጣም ቀላል ነው:- ከሰይጣን ፕሮፓጋንዳዎች በመራቅና እኛን ‘በእምነት ለማጽናት’ አምላክ ካዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ነው።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​8-10

ጥሩ መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማድ ማዳበር የግድ አስፈላጊ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ደራሲ ዊንጌት “ሰውነታችን በሚያርፍበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር በውስጡ ለሚያካሂደው ኬሚካላዊ ሂደትና ወሳኝ የሆኑት አባላካላት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የማያቋርጥ ኃይል ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። እንዲሁም ብዙዎቹ ሕብረ ሕዋሳት የተገነቡበት ሕዋሳት አለማቋረጥ በአዲስ መተካት ይኖርባቸዋል” በማለት ተናግረዋል። በመንፈሳዊ ጤንነታችን ረገድም ሁኔታው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። መንፈሳዊ ምግብ ዘወትር ካልተመገብን እምነታችን ምግብ እንዳጣ ሰውነት ቀስ በቀስ ይዳከምና በመጨረሻም ይሞታል። ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሎ በተናገረ ጊዜ ይህን ጠበቅ አድርጎ ተናግሯል።​—⁠ማቴዎስ 4:​4

እስቲ አስበው፣ ገና ከጅምሩ ጠንካራ እምነት የገነባነው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “እምነት ከመስማት ነው” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 10:​17) በመጀመሪያ የአምላክን ቃል በመመገብ በይሖዋ፣ በተስፋዎቹና በድርጅቱ ላይ ያለንን እምነትና ትምክህት ገንብተናል ማለቱ ነው። እርግጥ ነው፣ የሰማነውን ሁሉ እንዲሁ በጭፍን አላመንንም። በቤርያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እንዳደረጉት አድርገናል። ‘ነገሩ እንደተባለው መሆኑን ለማረጋገጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ዕለት ዕለት መረመርን።’ (ሥራ 17:​11) ‘በጎ፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ ፈትነን ያወቅን’ ሲሆን የሰማነው ነገር እውነት መሆኑን ፈትነን አረጋገጥን። (ሮሜ 12:​2፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​20, 21) ከዚያ ወዲህ አምላክ የተናገረው ቃልና የገባቸው ተስፋዎች ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ይበልጥ እየተገነዘብን ስንሄድ እምነታችን ተጠናክሮ መሆን አለበት።​—⁠ኢያሱ 23:​14፤ ኢሳይያስ 55:​10, 11

በመንፈሳዊ አትራብ

አሁን ፈታኝ የሚሆነው ነገር እምነታችንን ጠብቀን መኖር እንዲሁም በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለንን ትምክህት ሊያዳክም የሚችል ማንኛውንም ዓይነት ጥርጣሬ ማስወገድ ነው። ይህንንም ለማድረግ ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር ይገባናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች [መጀመሪያ ላይ ጠንካራ እምነት የነበራቸው የሚመስሉ] የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​1) እነዚህ አሳሳች አነጋገሮችና ትምህርቶች በአንዳንዶች አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬን በመፍጠር ከአምላክ ያርቃቸዋል። ታዲያ መከላከያችን ምንድን ነው? ‘በእምነትና በተከተልነው በመልካም ትምህርት ቃል መመገባችንን’ መቀጠል ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​6

እንደዚህ ያለው ምግብ ተትረፍርፎ ባለበት በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶች ‘የእምነትን ቃል ለመመገብ’ ፈቃደኞች አለመሆናቸው የሚያሳዝን ነው። ከምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊዎች መካከል አንዱ እንደተናገረው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በቀረበበት ቦታ ወይም በምሳሌያዊ አነጋገር ድል ያለ መንፈሳዊ ድግስ ባለበት ግብዣ ላይ ቢገኙም ምግቡን ለመጉረስና ለማላመጥ የሚታክቱ ሰዎች ይኖራሉ።​—⁠ምሳሌ 19:​24፤ 26:​15

ይህ በጣም አደገኛ ነው። ዊንጌት የተባሉት ደራሲ “ሰውነት ያከማቸውን የራሱን ፕሮቲን መመገብ ሲጀምር ጤንነት ወዲያው መቃወስ ይጀምራል” ብለዋል። ረሃብ ሲያጠቃህ ሰውነትህ በመላው አካልህ ውስጥ የተከማቸውን ኃይል መጠቀም ይጀምራል። ይህ ኃይል ሲሟጠጥ ሰውነትህ እድገት ለማድረግና ሕብረ ሕዋስን ለማደስ አስፈላጊ የሆነውን ፕሮቲን መጠቀም ይጀምራል። ወሳኝ የሆኑ የሰውነት አካላት ሥራቸውን ማከናወን ያቆማሉ። ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ጤንነትህ ይቃወሳል።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በነበሩ አንዳንዶች ላይ በመንፈሳዊ ሁኔታ የደረሰው ነገር ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው። ቀደም ሲል በተመገቡት መንፈሳዊ ምግብ ብቻ ለመቆም ሞከሩ። የግል ጥናታቸውን ችላ በማለታቸው ምክንያት ሳይሆን አይቀርም በመንፈሳዊ የተዳከሙ ሆኑ። (ዕብራውያን 5:​12) ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፣ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል” በማለት ይህ ሁኔታ ያለውን አደጋ ገልጿል። “እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል” የምንል ከሆነ ወደ መጥፎ ልማድ ለመንሸራተት ምን ያህል ቀላል እንደሆነ ያውቅ ነበር።​—⁠ዕብራውያን 2:​1, 3

የሚያስገርመው የተመጣጠነ ምግብ የማይመገብ ሰው ሁሉ የግድ ገመምተኛ ይመስላል ወይም ይከሳል ማለት አይደለም። በተመሳሳይም አንድ ሰው በመንፈሳዊ የተራበ መሆኑ ቶሎ ላይታወቀው ይችላል። በመንፈሳዊ በሚገባ ሳትመገብም እንኳ ጤነኛ መስለህ ልትታይ ትችላለህ! ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። በመንፈሳዊ መዳከምህ፣ መሠረተ ቢስ ለሆነ ጥርጣሬ መጋለጥህና ለእምነት በብርቱ መጋደልህን ማቆምህ የማይቀር ነው። (ይሁዳ 3) ለሌላ ሰው በግልጽ ባይታይም እንኳ እውነተኛውን መንፈሳዊ አመጋገብህን በሚገባ ታውቀዋለህ።

ስለሆነም የግል ጥናት ማድረግህን ቀጥል። ጥርጣሬን በብርቱ ተዋጋ። ቀላል የሚመስልን ህመም ወይም እየተመላለሰ ወደ አእምሮ የሚመጣን ጥርጣሬ ችላ ብሎ ማለፍ አደገኛ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 11:​3) ‘የምንኖረው በእርግጥ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ሁሉ ታምንበታለህን? ይህ በእርግጥ የይሖዋ ድርጅት ነውን?’ ሰይጣን እንደነዚህ ያሉትን የጥርጣሬ ዘሮች በአእምሮህ ውስጥ መዝራት ይወዳል። ለመንፈሳዊ አመጋገብህ የቸልተኝነት ዝንባሌ በማሳየት አሳሳች የሆኑ ትምህርቶቹ በቀላሉ እንዲያጠምዱህ አትፍቀድ። (ቆላስይስ 2:​4-7) ለጢሞቴዎስ የተሰጠውን ምክር ሥራበት። “በተማርህበትና በተረዳህበት [“እንድታምን በተደረግህበት፣” NW ] ነገር ጸንተህ” መኖር እንድትችል ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ በደንብ አጥና።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​13-15

እንዲህ ለማድረግ እርዳታ ማግኘት ያስፈልግህ ይሆናል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ጸሐፊ እንደሚከተለው ብለዋል:- “አንድ ሰው ለከፍተኛ ረሃብ ከተጋለጠ ምግብ ፈጭ አባልአካላት (digestive organs) በቫይታሚኖችና ለሰውነት አስፈላጊ በሆኑ በሌሎች ንጥረ ነገሮች እጥረት ምክንያት ጉዳት ሊደርስባቸው ስለሚችል ጠንከር ያለ ምግብ በሚያገኙበት ጊዜ መፍጨት ሊያቅታቸው ይችላል። በዚህ ሁኔታ ላይ ያሉ ሰዎች ለተወሰኑ ጊዜያት በቀላሉ ሊፈጩ የሚችሉ ምግቦችን ብቻ መመገብ ያስፈልጋቸው ይሆናል።” በረሃብ ምክንያት በሰውነት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማሻሻል ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በተመሳሳይም አንድ ሰው ቸልተኛ ሆኖ በግል የሚያደርገውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እርግፍ አድርጎ ቢተው መንፈሳዊ የምግብ ፍላጎቱን ለመቀስቀስ ከፍተኛ እርዳታና ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልገዋል። አንተም እንደዚህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ ከሆነ ከመንፈሳዊ በሽታህ እንድታገግምና ጥንካሬህን መልሰህ እንድታገኝ እርዳታ እንዲደረግልህ ጠይቅ፤ እንዲሁም የሚደረግልህን ማንኛውንም ዓይነት እርዳታ በደስታ ተቀበል።​—⁠ያዕቆብ 5:​14, 15

‘በአለማመን ምክንያት አትጠራጠር’

አንዳንዶች ፓትርያርኩ አብርሃም ስለነበረበት ሁኔታ ሲያስቡ እንዲጠራጠር የሚያደርግ በቂ ምክንያት እንደነበረው ይሰማቸው ይሆናል። አምላክ ቃል ይግባለት እንጂ ‘የብዙ ሕዝብ አባት የመሆን ተስፋ አልነበረውም’ ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይመስላል። ለምን? ሁኔታውን ከሰው አመለካከት አንጻር ስንመለከተው ተስፋ የሚሰጥ ምንም ነገር አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃም ‘እንደ ምውት የሆነውን ሥጋና የሣራን ማኅፀን ምውት መሆኑን ተመለከተ’ ሲል ይዘግባል። ሆኖም አምላክንና እሱ የሰጠውን ተስፋ በሚመለከት በአእምሮውና በልቡ ውስጥ ጥርጣሬ ፈጽሞ ሥር እንዲሰድድ አልፈቀደም። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በእምነቱ አልደከመም’ ወይም ‘በአለማመን ምክንያት አልተጠራጠረም’ ሲል ጽፏል። አብርሃም “[አምላክ] የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ” ተረድቷል። (ሮሜ 4:​18-21) ባሳለፋቸው ብዙ ዓመታት ከይሖዋ ጋር የጠበቀና መተማመን የሰፈነበት ወዳጅነት መሥርቶ ነበር። የመሠረተውን ይህን ወዳጅነት ሊያዳክምበት የሚችል ምንም ዓይነት ጥርጣሬ እንዲፈጠርበት አልፈቀደም።

አንተም በመንፈሳዊ በደንብ እየተመገብህ “የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ” አጥብቀህ የምትይዝ ከሆነ እንዲሁ ማድረግ ትችላለህ። (2 ጢሞቴዎስ 1:​13) ጥርጣሬ ከባድ አደጋ እንደሚያስከትል አትዘንጋ። ሰይጣን መንፈሳዊ ባክቴሪያዎችን በመጠቀም ውጊያ ከፍቶብናል ለማለት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስን በግልህ በማጥናትና በክ​ርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ተስማሚ የሆነውን መንፈሳዊ ምግብ መመገብህን ችላ ካልህ እንደዚህ ላለው ጥቃት ራስህን ታጋልጣለህ። ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት በጊዜው የሚቀርብልንን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በሚገባ ተጠቀም። (ማቴዎስ 24:​45) ‘ጤናማውን ቃል በመጠጋት’ ‘በእምነት ጤናማ’ ሆነህ ኑር። (1 ጢሞቴዎስ 6:​3፤ ቲቶ 2:​2) ጥርጣሬ እምነትህን እንዲያጠፋብህ አትፍቀድ።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራስህን በመንፈሳዊ ምን ያህል ጥሩ አድርገህ ትመግባለህ?