በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመከሩ ሥራ ወደፊት ግፉ!

በመከሩ ሥራ ወደፊት ግፉ!

በመከሩ ሥራ ወደፊት ግፉ!

“በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ።”—⁠መዝሙር 126:5

1. ዛሬ ‘የመከሩ ጌታ ሠራተኞችን ወደ መከሩ እንዲልክ መለመን’ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

 ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ገሊላ ካደረገው ሦስተኛ የስብከት ጉዞ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 9:37) በይሁዳም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። (ሉቃስ 10:2) ከ2,000 ዓመት ገደማ በፊት ሁኔታው ይህ ከነበረ ዛሬስ ምን ይመስላል? ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ከ6, 000, 000 በላይ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች 6, 000,​000, 000 በሚሆነው የዓለም ሕዝብ መካከል በምሳሌያዊው የመከር ሥራ ተሰማርተው የነበረ ሲሆን ከዚህ የዓለም ሕዝብ መካከልም አብዛኞቹ ‘እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች የተጨነቁና የተጣሉ’ ናቸው። ስለዚህ ኢየሱስ “የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” ሲል የሰጠው ማሳሰቢያ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አስፈላጊ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም የዚያኑ ያህል አንገብጋቢ ነው።​—⁠ማቴዎስ 9:​36, 38

2. የሰዎች ትኩረት እንዲያርፍብን የሚያደርገው ምንድን ነው?

2 የመከሩ ጌታ የሆነው ይሖዋ አምላክ ተጨማሪ ሠራተኞችን እንዲልክ ለቀረበለት ልመና ምላሽ ሰጥቷል። በአምላክ አመራር በሚከናወነው በዚህ የመከር ሥራ መካፈል ምንኛ የሚያስደስት ነው! ከዓለም ሕዝብ አንጻር ሲታይ ቁጥራችን ትንሽ ቢሆንም በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት መካፈላችን የዓለምን ትኩረት ይስባል። በብዙ አገሮች በተደጋጋሚ ጊዜ በመገናኛ ብዙሐን እንጠቀሳለን። አንዳንድ ጊዜ በቴሌቪዥን በሚቀርብ ድራማ ላይ የበር ደወል ሲደወል የቤቱ ባለቤቶች እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው የሚል አስተያየት ሲሰጡ ይታያል። አዎን፣ ምሳሌያዊ የመከር ሠራተኞች በመሆን የምናደርገው ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ በ21ኛው መቶ ዘመን በሚገባ ታውቋል።

3. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የመንግሥቱ ስብከት እንቅስቃሴ የሰዎችን ትኩረት ስቦ እንደነበር እንዴት እናውቃለን? (ለ) መላእክት አገልግሎታችንን ይደግፋሉ ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

3 በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ዓለም የመንግሥቱን ስብከት እንቅስቃሴ ከማስተዋሉም በላይ ምሥራቹን የሚያውጁትን አሳድዷል። ስለሆነም ሐዋርያው ጳውሎስ “[እኛ ሐዋርያት] ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናልና፤ እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች እንዳደረገን ይመስለኛልና” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 4:9) በተመሳሳይም ስደት ቢኖርም እንኳ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን የምናሳየው ጽናት የዓለምን በይበልጥ ደግሞ የመላእክትን ትኩረት ይስባል። ራእይ 14:​6 እንዲህ ይላል:- “[እኔም ሐዋርያው ዮሐንስ] በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ።” አዎን፣ በአገልግሎታችን ማለትም በመከር ሥራችን መላእክታዊ ድጋፍ አለን!​—⁠ዕብራውያን 1:​13, 14

“የተጠላችሁ ትሆናላችሁ”

4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው? (ለ) በዘመናችን ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ‘የሚጠሉት’ ለምንድን ነው?

4 የኢየሱስ ሐዋርያት የመከር ሠራተኞች ሆነው በተላኩበት ጊዜ ኢየሱስ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ” ሲል የሰጣቸውን መመሪያ ተከትለዋል። በተጨማሪም ኢየሱስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:- “ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ በምኵራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤ ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፣ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ። . . . በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።”​—⁠ማቴዎስ 10:16-22

5 ‘ዓለም በሞላ በክፉው’ ማለትም የአምላክና የሕዝቦቹ ቀንደኛ ጠላት በሆነው በሰይጣን ዲያብሎስ ስለተያዘ ዛሬም ‘እንጠላለን።’ (1 ዮሐንስ 5:​19) ጠላቶቻችን የእኛን መንፈሳዊ ብልጽግና ይመለከታሉ፤ ይህን መንፈሳዊ ብልጽግና ያገኘነው ከይሖዋ መሆኑን ለመቀበል ግን አይፈልጉም። በመከሩ ሥራ ስንካፈል ያለንን ደስታና በፈገግታ የተሞላ ፊት ተቃዋሚዎች ይመለከታሉ። ባለን አንድነት እጅግ ይገረማሉ! እንዲያውም አንዳንዶች ወደ ሌላ አገር በሚሄዱበት ጊዜ በአገራቸው ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሲሠሩ ያዩትን ተመሳሳይ ሥራ በዚያም ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሲሠሩ ሲመለከቱ በእርግጥም አንድነት እንዳለን ሳይወዱ በግድ ይቀበላሉ። እርግጥ ነው፣ ደጋፊያችንና የአንድነታችን ምንጭ የሆነው ይሖዋ ለጠላቶቻችን ጭምር ራሱን የሚያሳውቅበት ጊዜ እንዳለ እናውቃለን።​—⁠ሕዝቅኤል 38:​10-12, 23

6. በመከሩ ሥራ በምንሰማራበት ጊዜ ምን ማረጋገጫ ተሰጥቶናል? ሆኖም ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?

6 የመከሩ ጌታ ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” ሰጥቶታል። (ማቴዎስ 28:18) ስለሆነም በሰማይ መላእክትና እዚህ ምድር ላይ በሚገኘው የቅቡዓን ክፍል ማለትም በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት የመከሩን ሥራ በበላይነት እንዲመራ ይሖዋ ኢየሱስን ይጠቀምበታል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ራእይ 14:6, 7) ሆኖም የጠላትን ተቃውሞ መቋቋምና ደስታችንን ጠብቀን በመከሩ ሥራ ወደፊት መግፋት የምንችለው እንዴት ነው?

7. ተቃውሞ ወይም ስደት ሲያጋጥመን ምን ዓይነት ጠባይ ማሳየት ይኖርብናል?

7 ተቃውሞ አልፎ ተርፎም ቀጥተኛ ስደት ሲያጋጥመን ጳውሎስ ያሳየው ዓይነት ባሕርይ ለማንጸባረቅ እንድንችል የአምላክን እርዳታ እንጠይቅ። ጳውሎስ “ሲሰድቡን እንመርቃለን፣ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፣ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 4:12, 13) እንዲህ ያለው ባሕርይ ጥበብ የተሞላበት አገልግሎታችን ሲታከልበት አንዳንድ ጊዜ ተቃዋሚዎቻችን አመለካከታቸውን እንዲቀይሩ ሊያደርግ ይችላል።

8. በ⁠ማቴዎስ 10:​28 ላይ ተመዝግበው ከሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ምን ዋስትና ታገኛለህ?

8 ሌላው ቀርቶ የግድያ ዛቻ እንኳ ቢሆን ለመከሩ ሥራ ያለንን ቅንዓት አያቀዘቅዘውም። በተቻለ መጠን የመንግሥቱን መልእክት ያለምንም ፍርሃት በይፋ እናውጃለን። እንዲሁም “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ” ሲል ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት የሚያበረታታ ዋስትና ይሰጡናል። (ማቴዎስ 10:28) ሕይወት የሚሰጠን የሰማዩ አባታችን እንደሆነ እናውቃለን። ለእርሱ ያላቸውን ጽኑ አቋም ጠብቀው ለሚኖሩና በመከሩ ሥራ በታማኝነት ወደፊት ለሚገፉ ሰዎች ሽልማት በመስጠት ይክሳቸዋል።

ሕይወት አድን መልእክት

9. አንዳንዶች ሕዝቅኤል ለተናገረው መልእክት ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው? ዛሬም ተመሳሳይ ሁኔታ እየታየ ያለውስ እንዴት ነው?

9 ነቢዩ ሕዝቅኤል ‘ለዓመፀኛ ሰዎች’ ማለትም ለእስራኤልና ለይሁዳ መንግሥታት የይሖዋን መልእክት ባወጀበት ወቅት እሱ የሚናገረውን መስማት ደስ የሚላቸው አንዳንድ ግለሰቦች ነበሩ። (ሕዝቅኤል 2:3) ይሖዋ “እነሆ፣ አንተ መልካም ድምፅ እንዳለው እንደሚወደድ መዝሙር ማለፊያም አድርጎ በገና እንደሚጫወት ሰው ሆነህላቸዋል” ሲል ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 33:32) ምንም እንኳ ሕዝቅኤል የሚናገረውን ቢወዱትም በዚያ መሠረት እርምጃ ሳይወስዱ ቀርተዋል። ዛሬስ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? ቅቡዓን ቀሪዎችና ጓደኞቻቸው የይሖዋን መልእክት በድፍረት በሚያውጁበት ጊዜ አንዳንዶች የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች መስማት ደስ ይላቸዋል፤ ይሁን እንጂ አድናቆታቸውን በሚያሳይ መንገድ ምላሽ በመስጠትና ደቀ መዛሙርት በመሆን በመከሩ ሥራ አይካፈሉም።

10, 11. በ20ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ሕይወት አድን መልእክታችንን ለሰዎች በማሳወቅ ረገድ ምን ጥረት ተደርጓል? ውጤቱስ ምን ነበር?

10 በሌላ በኩል ደግሞ ለመከሩ ሥራ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡና የአምላክን መልእክት በማወጁ እንቅስቃሴ የሚካፈሉ ብዙዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል ከ1922 እስከ 1928 በተከታታይ በተደረጉት ትላልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የክፉውን የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት የሚያወግዙ መልእክቶች በቀጥታ ተላልፈዋል። የራዲዮ ጣቢያዎች በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የቀረቡትን የሰይጣንን ዓለም የሚያወግዙ ቃላት አስተላልፈዋል። ከዚያም በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ይህን የሰይጣን ዓለም የሚያወግዙ ቃላት የታተመባቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅጂዎችን አሰራጭተዋል።

11 በ1930ዎቹ ማብቂያ አካባቢ ‘የማስታወቂያ ሰልፍ’ የሚባል ሌላ ዓይነት የምስክርነት እንቅስቃሴ ተጀመረ። በመጀመሪያ የይሖዋ ሕዝቦች የሕዝብ ንግግር ማስታወቂያዎችን በደረታቸውና በጀርባቸው ላይ አንግበው ይሄዱ ነበር። በኋላ “ሃይማኖት ወጥመድና ማጭበርበሪያ ነው” እና “አምላክንና ንጉሡን አገልግሉ” እንደሚሉት ያሉ መፈክሮች የተጻፉባቸውን ማስታወቂያዎች አንግበው ይሄዱ ጀመር። እነዚህን መፈክሮች በጀርባቸውና በደረታቸው አንግበው በጎዳናዎች ላይ ሲሄዱ የአላፊ አግዳሚውን ትኩረት ይስቡ ነበር። በእንግሊዝ ሰው በሚበዛባቸው የለንደን አውራጎዳናዎች ላይ ይህን መፈክር አንግቦ በመሄድ ብዙ ጊዜ ይካፈል የነበረ አንድ ወንድም ‘ይህ ሥራ የይሖዋ ምሥክሮች የሰዎችን ትኩረት እንዲስቡ ከማስቻሉም በላይ ድፍረት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል’ ሲል አስተያየት ሰጥቷል።

12. ከአምላክ የፍርድ መልእክት በተጨማሪ በአገልግሎታችን ምን መልእክት እንናገራለን? በአሁኑ ጊዜ ምሥራቹን አንድ ሆነው በመስበክ ላይ የሚገኙት እነማን ናቸው?

12 የአምላክን የፍርድ መልእክት በምናውጅበት ጊዜ በመንግሥቱ አማካኝነት የሚመጡትንም በረከቶች እንናገራለን። በዓለም መድረክ ላይ በድፍረት መመስከራችን የሚገባቸውን ሰዎች እንድናገኝ ይረዳናል። (ማቴዎስ 10:11) አብዛኞቹ የቅቡዓን ክፍል የመጨረሻ አባላት በ1920ዎቹ እና በ1930ዎቹ የመከር ሠራተኞችን በተመለከተ ለቀረበው ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል። ከዚያም በ1935 በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ወደፊት ገነት በሆነች ምድር ላይ የሚያገኙትን በረከት በተመለከተ አስደናቂ ምሥራች ተነገረ። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16) የአምላክን የፍርድ መልእክት በመስማት ሕይወት አድን በሆነው የምሥራቹ ስብከት ሥራ ከቅቡዓን ጋር ተባብረዋል።

13, 14. (ሀ) ከ⁠መዝሙር 126:​5, 6 ምን ማጽናኛ ማግኘት ይቻላል? (ለ) መዝራታችንንና ማጠጣታችንን ከቀጠልን ምን ውጤት ይገኛል?

13 በ⁠መዝሙር 126:​5, 6 ላይ የሚገኙት “በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ [“ያጭዳሉ፣” NW ]። በሄዱ ጊዜ፣ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ” የሚሉት ቃላት ለአምላክ የመከር ሠራተኞች በተለይም ስደት እየደረሰባቸው ላሉት ትልቅ ማጽናኛ ይሆናሉ። ስለ መዝራትና ማጨድ የሚናገሩት የመዝሙራዊው ቃላት ከጥንቷ ባቢሎን ከምርኮ የተመለሱትን ቀሪዎች ይሖዋ እንደተንከባከባቸውና እንደባረካቸው የሚያሳዩ ናቸው። ነፃ በወጡበት ወቅት እጅግ ተደስተው የነበረ ቢሆንም በግዞት በቆዩባቸው 70 ዓመታት ምንም ባልተሠራበት ጠፍ መሬት ላይ ዘራቸውን በመዝራታቸው አልቅሰው ሊሆን ይችላል። ሆኖም መዝራታቸውንና የግንባታ እንቅስቃሴያቸውን የገፉበት የድካማቸውን ፍሬ እንዲሁም እርካታ አግኝተዋል።

14 እኛ ራሳችን ፈተና ሲያጋጥመን ወይም እኛም ሆንን የእምነት ባልንጀሮቻችን ለጽድቅ ስንል መከራ ሲደርስብን ልናለቅስ እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 3:14) መጀመሪያ ላይ በአገልግሎቱ ምንም ያህል ብንደክም ፍሬ አናገኝ ይሆናል፤ ይህም የመከሩ ሥራችንን አስቸጋሪ እንዲሆን ሊያደርግብን ይችላል። ይሁን እንጂ መዝራታችንንና ማጠጣታችንን ከቀጠልን አምላክ ብዙውን ጊዜ እኛ ከጠበቅነው በላይ እንዲያድግ ያደርገዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:6) መጽሐፍ ቅዱስንና ቅዱስ ጽሑፋዊ ጽሑፎችን በማሰራጨት ያገኘነው ውጤት ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው።

15. ክርስቲያናዊ ጽሑፎች በመከሩ ሥራ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።

15 ለምሳሌ ያህል ጂም የተባለውን ሰው ሁኔታ ተመልከት። እናቱ ስትሞት ከንብረቶቿ መካከል ሕይወት እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? a የተባለ መጽሐፍ አገኘ። በከፍተኛ ጉጉት አነበበው። ጂም አንዲት የይሖዋ ምሥክር መንገድ ላይ አግኝታ ስታነጋግረው ተመላልሶ መጠየቅ እንዲደረግለት ተስማማና በዚያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት። ጂም ፈጣን መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ራሱን ለይሖዋ ወስኖ ተጠምቋል። ስለተማረው ነገር ለሌሎች የቤተሰቡ አባላት የተናገረ ሲሆን ከዚህም የተነሳ እህቱና ወንድሙ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። በኋላም ጂም ለንደን በሚገኘው ቤቴል ውስጥ ፈቃደኛ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የመሆን መብት አግኝቷል።

ስደት ቢኖርም ደስተኛ መሆን

16. (ሀ) በመከሩ ሥራ ውጤት ሊገኝ የቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ምሥራቹ የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ ኢየሱስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? ሆኖም መልእክቱን ለሰዎች የምናደርሰው ምን ዝንባሌ ይዘን ነው?

16 በመከሩ ሥራ እንዲህ የመሰለ ውጤት ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው? ቅቡዓን ክርስቲያኖችና ጓደኞቻቸው ኢየሱስ “በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ” ሲል የሰጣቸውን መመሪያ በመከተላቸው ነው። (ማቴዎስ 10:27) ሆኖም ኢየሱስ “ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፣ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል” ብሎ ስላስጠነቀቀ ችግር ይደርስብናል ብለን እንጠብቃለን። በተጨማሪም ኢየሱስ “በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም” ብሏል። (ማቴዎስ 10:21, 34) ኢየሱስ ሆን ብሎ ቤተሰብን የመለያየት ዓላማ አልነበረውም። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ምሥራቹ ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል። ዛሬ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ምሥራቹን ለተለያዩ ቤተሰቦች በምንሰብክበት ጊዜ ዓላማችን ቤተሰቡን መከፋፈል አይደለም። ሁሉም ምሥራቹን ቢቀበል ምኞታችን ነው። ስለሆነም መልእክታችን “ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ” ያላቸውን ሁሉ የሚስብ ይሆን ዘንድ ሁሉንም የቤተሰቡን አባላት በደግነትና በርኅራኄ ቀርበን እናነጋግራለን።​—⁠ሥራ 13:​48 NW

17. የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚደግፉ ሰዎች የሚለዩት እንዴት ነው? ለዚህስ አንዱ ምሳሌ ምንድን ነው?

17 የመንግሥቱ መልእክት የአምላክን ሉዓላዊነት የሚደግፉትን ይለያቸዋል። ለምሳሌ ያህል በጀርመን የብሔራዊ ሶሻሊዝም ዘመን የእምነት ባልንጀሮቻችን ‘የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ማስረከባቸው’ ከሌሎች የተለዩ ሆነው እንዲታዩ እንዳደረጋቸው ተመልከት። (ሉቃስ 20:25) የይሖዋ አገልጋዮች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚያስጥስ ነገር አናደርግም በማለት ከሃይማኖት መሪዎችና ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን የተለየ አቋም እንዳላቸው አሳይተዋል። (ኢሳይያስ 2:4፤ ማቴዎስ 4:10፤ ዮሐንስ 17:16) ዘ ናዚ ስቴት ኤንድ ዘ ኒው ሪሊጅንስ የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ፕሮፌሰር ክርስቲን ኪንግ እንዲህ ብለዋል:- “[የናዚ] መንግሥት ጥረቱ ያልተሳካለት በምሥክሮቹ ላይ ብቻ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩትን ቢገድሉም ሥራው የቀጠለ ሲሆን ግንቦት 1945 ብሔራዊ ሶሻሊዝም ባከተመበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ሕያው ነበር።”

18. የይሖዋ ሕዝቦች ስደት ቢደርስባቸውም ምን ዓይነት ዝንባሌ ያንጸባርቃሉ?

18 የይሖዋ ሕዝቦች ስደት ሲያጋጥማቸው የሚያሳዩት ዝንባሌ በእርግጥም ትኩረት የሚስብ ነው። ዓለማዊ ባለሥልጣናት በእምነታችን ሊደነቁ ቢችሉም በውስጣችን የበቀል ወይም የጥላቻ ስሜት አለማሳደራችን ግን በጣም ያስገርማቸዋል። ከናዚ ሆሎኮስት የተረፉ የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ ያሳለፉትን ሁኔታ መለስ ብለው ሲያስቡ ብዙውን ጊዜ ደስታና እርካታ ይሰማቸዋል። ይሖዋ “ከወትሮው የተለየ ኃይል” እንደሰጣቸው ያውቃሉ። (2 ቆሮንቶስ 4:​7) በመካከላችን ያሉ ቅቡዓን ‘ስማቸው በሰማያት እንደተጻፈ’ ማረጋገጫ አላቸው። (ሉቃስ 10:20) ጽናታቸው የማያሳፍር ተስፋ ያስገኝላቸዋል፤ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ታማኝ የመከር ሠራተኞችም ተመሳሳይ ጽናት ያሳያሉ።​—⁠ሮሜ 5:​4, 5

በመከሩ ሥራ ጽኑ

19. በክርስቲያናዊ አገልግሎት የተሠራበት ውጤታማ ዘዴ ምንድን ነው?

19 ይሖዋ እስከ መቼ ድረስ በምሳሌያዊው የመከር ሥራ እንድንቀጥል እንደሚፈቅድ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን የመከር ሠራተኞች ሥራቸውን የሚያከናውኑበት የተወሰነ ዘዴ እንዳላቸው ማስታወስ ይኖርብናል። ተሞክረውና ተፈትነው ውጤታማ ሆነው በተገኙት የስብከት ዘዴዎች በመጠቀም ረገድ ታማኝ መሆናችን ፍሬያማ እንደሚያደርገን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ጳውሎስ ክርስቲያን ባልደረቦቹን “እኔን የምትመስሉ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ” ብሏቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 4:16) ጳውሎስ የኤፌሶንን ሽማግሌዎች በሚሊጢን ሲያገኛቸው ‘በጉባኤም በየቤታቸውም’ ከማስተማር ወደኋላ እንዳላለ አስታውሷቸዋል። (ሥራ 20:20, 21) የጳውሎስ ጓደኛ ጢሞቴዎስ የሐዋርያውን የስብከት ዘዴ ተምሮ ስለነበረ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሊያሳያቸው ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 4:17) አምላክ የጳውሎስን የስብከት ዘዴ እንደባረከው ሁሉ እኛም ከቤት ወደ ቤት በመሄድ፣ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራትና ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ምሥራቹን በመስበክ የምናሳየውን ጽናት ይባርካል።​—⁠ሥራ 17:​17

20. ኢየሱስ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ መከር እንዳለ የጠቆመው እንዴት ነው? ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ እውነት ሆኖ የተገኘውስ እንዴት ነው?

20 ኢየሱስ በ30 እዘአ በሲካር አቅራቢያ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት ከመሰከረ በኋላ ስለ መንፈሳዊው መከር ተናግሯል። ለደቀ መዛሙርቱ እንደሚከተለው ሲል ነግሯቸዋል:- “ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ። የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፣ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል።” (ዮሐንስ 4:34-36) ለሳምራዊቷ ሴት በሰጠው ምስክርነት የተነሳ ብዙዎች በእሱ ስላመኑ ኢየሱስ ከእሷ ጋር መነጋገሩ ያስከተለውን ውጤት ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። (ዮሐንስ 4:39) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ አገሮች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥለው የነበረውን እገዳ በማንሳታቸው ወይም ለምሥክሮቹ ሕጋዊ እውቅና በመስጠታቸው የተነሳ አዲስ የመከር ማሳ በመገኘት ላይ ነው። በውጤቱም የተትረፈረፈ የመከር አዝመራ በመሰብሰብ ላይ ይገኛል። እንዲያውም በመንፈሳዊው መከር ተሠማርተን በደስታ መሥራታችንን ስለቀጠልን በመላው ዓለም የተትረፈረፈ በረከት በመገኘት ላይ ነው።

21. ደስተኛ የመከሩ ሠራተኞች በመሆን ወደፊት እንድንገፋ የሚያደርገን ምንድን ነው?

21 አዝመራው ከነጣና ለአጨዳ ከደረሰ ሠራተኞች ቶሎ ብለው እርምጃ መውሰድ አለባቸው። ነገ ዛሬ ሳይሉ በሥራው መሰማራት አለባቸው። ዛሬ ‘በፍጻሜው ዘመን’ ላይ ስለምንገኝ በትጋትና በጥድፊያ ስሜት መሥራት ያስፈልገናል። (ዳንኤል 12:4) እርግጥ ነው የተለያዩ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙን አይካድም፤ ሆኖም ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ አምላኪዎች በመከሩ ሥራ በመሰብሰብ ላይ ናቸው። ስለዚህ ይህ የደስታ ጊዜ ነው። (ኢሳይያስ 9:3) ስለሆነም ደስተኛ ሠራተኞች እንደመሆናችን መጠን በመከሩ ሥራ ወደፊት መግፋታችንን እንቀጥል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የይሖዋ ምሥክሮች እያተሙ የሚያሰራጩት መጽሐፍ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

የመከሩ ጌታ ተጨማሪ ሠራተኞችን እንዲልክ ለቀረበለት ልመና ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

‘ብንጠላም’ እንኳ ምን ዓይነት ጠባይ እናሳያለን?

ስደት ቢደርስብንም እንኳ ደስተኞች የሆንነው ለምንድን ነው?

በጥድፊያ ስሜት በመከሩ ሥራ መጽናት ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመንፈሳዊው የመከር ሥራ የተሰማሩ ሁሉ የመላእክት ድጋፍ አላቸው

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማስታወቂያ ሰልፍ ብዙዎች የመንግሥቱን መልእክት ልብ እንዲሉት አድርጓል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኛ ስንተክልና ስናጠጣ አምላክ ያሳድገዋል