በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእርግጥ ታጋሽ ነህን?

በእርግጥ ታጋሽ ነህን?

በእርግጥ ታጋሽ ነህን?

የአንድ ሰው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት በጣም አናድዶህ ያውቃል? በካይ ተጽእኖዎች በቅርብ ወዳጆችህ መካከል ሰርገው በመግባት ላይ መሆናቸውን ስትመለከት ፈጣን እርምጃ ትወስዳለህን?

አንድ ከባድ ኃጢአት እንዳይዛመት ለመግታት አንዳንድ ጊዜ ፈጣንና ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ለምሳሌ በ15ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እስራኤላውያን ዓይን ባወጣ የብልግና ድርጊት የመበከል አደጋ አንዣብቦባቸው ሳለ የአሮን የልጅ ልጅ የሆነው ፊንሐስ ክፉውን ከመካከላቸው ለማስወገድ ቆራጥ እርምጃ ወስዷል። ይሖዋ አምላክም “ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቁጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ” ብሎ በመናገር ፊንሐስ ያደረገውን መቀበሉን አሳይቷል።​—⁠ዘኁልቊ 25:​1-11

ፊንሐስ ይህ በካይ ድርጊት እንዳይዛመት ለመግታት ተገቢ እርምጃ ወስዷል። ሆኖም ሌሎች በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት ሲሳሳቱ ከልክ በላይ ስለመቆጣትስ ምን ለማለት ይቻላል? በችኮላ ወይም አንዳች መሠረት ሳይኖረን እርምጃ ከወሰድን ይህ ድርጊት የጽድቅ ጠበቆች ሳይሆን ትዕግሥት የለሾችና የሌሎችን አለፍጽምና ግምት ውስጥ የማናስገባ ሰዎች ያደርገናል። ይህንን ስውር ወጥመድ ለማስወገድ ምን ሊረዳን ይችላል?

‘ይሖዋ ኃጢአታችሁን ሁሉ ይቅር ይላል’

ይሖዋ “ተቀናቃኙን የማይታገሥ ቀናተኛ (ቀናኢ) አምላክ ነው።” (ዘጸአት 20:​5የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን እርሱን ብቻ እንድናመልከው የመጠየቅ መብት አለው። (ራእይ 4:​11) ይሁን እንጂ ይሖዋ የሰዎችን ድክመት ይታገሣል። ስለሆነም መዝሙራዊው ዳዊት ስለ ይሖዋ እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፣ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። ሁልጊዜም አይቀሥፍም [“ስህተትን አይፈላልግም፣” NW ] . . . እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፣ እንደ በደላችንም አልከፈለንም።” አዎን፣ ንስሐ ከገባን አምላክ ‘ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር ይለናል።’​—⁠መዝሙር 103:​3, 8-10

ይሖዋ የሰዎችን የኃጢአተኝነት ዝንባሌ ስለሚገነዘብ መጥፎ ድርጊት ፈጽመው ንስሐ በገቡ ሰዎች ላይ ‘ስህተት መፈላለጉን’ አይቀጥልም። (መዝሙር 51:​5፤ ሮሜ 5:​12) እንዲያውም አምላክ ኃጢአትንና አለፍጽምናን የማስወገድ ዓላማ አለው። ሆኖም ይህ ሙሉ በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ ‘እንደ በደላችን ከመክፈል’ ይልቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ምሕረቱን ዘርግቶልናል። ይሖዋ ተገቢ ሆኖ ሲያገኘው ምሕረት ባያደርግልን ኖሮ ማናችንም ብንሆን ሕይወት የሚገባን ሰዎች ሆነን አንገኝም ነበር። (መዝሙር 130:​3) ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት ያለው ሰማያዊ አባታችን መሐሪ አምላክ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

ሚዛናዊነት ያስፈልጋል

የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ፍጹማን ካልሆኑት የሰው ልጆች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ረገድ ታጋሽ ከሆነ እኛስ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አይኖርብንም? መታገሥ የሚለው ቃል የሌሎችን አመለካከትና ተግባር በተመለከተ ቻይ መሆን ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። እኛስ አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ከባድ ኃጢአት ባይሠሩም እንኳ ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲናገሩ ስንሰማ ወይም ሲያደርጉ ስናይ በግላችን እንዲህ ያለውን ባሕርይ እናንጸባርቃለንን?

እርግጥ ወደ ሌላኛው ጽንፍም እንዳንሄድ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለምሳሌ ሃይማኖታዊ ባለሥልጣናት ወንዶችንም ሆነ ሴቶች ልጆችን በተደጋጋሚ ጊዜ በጾታ የሚያስነውሩትን ምግባረ ብልሹ ቄሶች መታገሣቸው አሳዛኝ ውጤት አስከትሏል። በአየርላንድ የሚገኝ አንድ ጋዜጠኛ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት በልጆቹ ላይ የተፈጸመውን ወንጀል በአጋጣሚ የተከሰተ ኃጢአት እንደሆነ አድርገው በመቁጠራቸው ጥፋት የፈጸመውን ቄስ [ወደ ሌላ ቦታ] አዛውረውታል።”

እንዲህ ያለ ድርጊት የፈጸመን ሰው ወደ ሌላ ቦታ ማዛወሩ ብቻ ተገቢ የታጋሽነት ምሳሌ ነውን? በፍጹም! አንድ የሕክምና ቦርድ በሽተኞቹን እየገደለ ወይም አካላቸውን እያጎደለ ያለን አንድ ግድየለሽ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ከአንድ ሆስፒታል ወደ ሌላ ሆስፒታል በማዛወር ቀዶ ሕክምና ማድረጉን እንዲቀጥል ፈቀደለት እንበል። በሕክምና ባለሙያዎች መካከል ያለውን ሙያዊ ትስስር ጠብቆ ለማቆየት ሲባል የተወሰደው ይህ እርምጃ እንዲህ ያለውን “ታጋሽነት” ሊያፈራ ይችላል። ይሁን እንጂ በዚህ የቸልተኝነት አልፎ ተርፎም የጭካኔ ድርጊት ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ ወይም ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችስ?

በተጨማሪም ትዕግሥት የለሽ የመሆን አደጋም አለ። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ዜሎትስ የተባሉ አንዳንድ አይሁዳውያን ድርጊታቸውን ተገቢ አስመስለው ለማቅረብ ሲሉ የፊንሐስን ምሳሌ በተሳሳተ መንገድ ለመጠቀም ሞክረዋል። አንዳንድ ዜሎትስ ከሚወስዷቸው ጽንፈኛ እርምጃዎች መካከል አንደኛው “በበዓሎችና በሌሎች ተመሳሳይ ወቅቶች በኢየሩሳሌም ከሚሰባሰቡት ሰዎች ጋር በመቀላቀል የጥላቻቸው ዒላማ የሆኑትን ሰዎች ሳያስቡት በጩቤ መውጋት” ነው።

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ዜሎትስ እንዳደረጉት ባስቀየሙን ሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳት እንደማናደርስ እሙን ነው። ይሁን እንጂ በተወሰነ ደረጃ ችሎ ማለፍ ስለሚከብደን የማንወዳቸውን ሰዎች በሌሎች መንገዶች ምናልባትም ስለ እነርሱ የዘለፋ ቃላት በመሰንዘር ለማጥቃት እንገፋፋ ይሆን? ከልባችን ታጋሾች ከሆንን እንዲህ ያለውን ጎጂ አነጋገር አንጠቀምም።

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ፈሪሳውያንም ትዕግሥት የለሽ በመሆን ረገድ የሚጠቀሱ ምሳሌዎች ነበሩ። ሰብአዊ አለፍጽምናን ጭራሽ ግምት ውስጥ ባለማስገባት ሌሎችን ያለማቋረጥ ይነቅፉ ነበር። ኩራተኞቹ ፈሪሳውያን ተራውን ሕዝብ “ርጉም” ብለው በመጥራት ዝቅ አድርገው ይመለከቱት ነበር። (ዮሐንስ 7:​49) ኢየሱስ ተመጻዳቂዎቹን ፈሪሳውያን እንደሚከተለው ሲል ማውገዙ የተገባ ነበር:- “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፣ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፣ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፣ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።”​—⁠ማቴዎስ 23:​23

ኢየሱስ ይህንን ሲል የሙሴን ሕግ የመጠበቁን አስፈላጊነት አቅልሎ መመልከቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ‘ዋና ዋናዎቹ’ ወይም ይበልጥ አስፈላጊዎቹ የሕጉ ዘርፎች ሕጉን ምክንያታዊ በሆነና ምሕረትን በተላበሰ መንገድ ተግባራዊ ማድረግን እንደሚጠይቁ ማመልከቱ ነበር። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ትዕግሥት የለሾች ከሆኑት ፈሪሳውያንና ዜሎትስ ምንኛ የተለዩ ናቸው!

ይሖዋ አምላክም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ክፋትን ችላ ብለው አያልፉም። በቅርቡ ‘እግዚአብሔርን በማያውቁትና ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በማይታዘዙት’ ላይ የበቀል እርምጃ ይወሰዳል። (2 ተሰሎንቄ 1:​6-10) ሆኖም ኢየሱስ ለጽድቅ ስለሚቀና ትክክል የሆነውን ማድረግ ለሚፈልጉ ሰዎች ጥቅም ሲል የሰማያዊ አባቱን የታጋሽነት፣ የመሐሪነትና የፍቅራዊ አሳቢነት ባሕርይ ከማንጸባረቅ ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም። (ኢሳይያስ 42:​1-3፤ ማቴዎስ 11:​28-30፤ 12:​18-21) ኢየሱስ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!

እርስ በእርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ

ትክክል ለሆነው ነገር ከፍተኛ ቅንዓት ቢኖረንም የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር እንከተል:- “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።” (ቆላስይስ 3:​13፤ ማቴዎስ 6:​14, 15) ታጋሽነት በዚህ ፍጽምና በጎደለው ዓለም ውስጥ ስንኖር አንዳችን የሌላውን ድክመትና ስህተት ችሎ ማለፍን ይጠይቃል። ከሌሎች በምንጠብቃቸው ነገሮች ረገድ ምክንያታዊ መሆን ይኖርብናል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​5 NW 

ይሁን እንጂ ታጋሽ መሆን ማለት በምንም መንገድ በተፈጸመው መጥፎ ድርጊት መስማማት ወይም ስህተቶችን አይቶ እንዳላየ መሆን ማለት አይደለም። የአንድ የእምነት ባልንጀራችን አስተሳሰብ ወይም ባሕርይ ከይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ጋር በተወሰነ መጠን የሚቃረን ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳ ሁኔታው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እስከማሳጣት የሚያደርስ ባይሆንም ግለሰቡ አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ እንደሚኖርበት የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። (ዘፍጥረት 4:​6, 7) መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንድሞች የተሳሳተውን ሰው በየዋህነት መንፈስ ለማስተካከል ሲጥሩ አፍቃሪ መሆናቸውን ያሳያሉ! (ገላትያ 6:​1) ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ ስኬታማ ለመሆን በነቃፊነት መንፈስ ሳይሆን በአሳቢነት ተነሳስቶ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።

‘በየዋህነትና በጥልቅ አክብሮት’

ከእኛ የተለየ ሃይማኖታዊ አመለካከት ላላቸው ሰዎች ትዕግሥት ማሳየትን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? በ1831 አየርላንድ ውስጥ በተቋቋሙት በሁሉም ብሔራዊ ትምህርት ቤቶች ውስጥ “ለጠቅላላ እውቀት” ተብሎ የቆመ አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል:- “ኢየሱስ ክርስቶስ የዓመፅ ድርጊቶችን ተጠቅሞ ሃይማኖቱን በሰዎች ላይ ለመጫን አልሞከረም . . . ከጎረቤቶቻችን ጋር መጣላትና እነርሱን መስደብ እነርሱ መሳሳታቸውን እኛ ግን ትክክል መሆናችንን የምናሳምንበት ተገቢ መንገድ አይደለም። እንዲያውም ይህ ድርጊት ክርስቲያናዊ ባሕርይ እንደሌለን የማሳመን አጋጣሚው የሰፋ ነው።”

ኢየሱስ ሰዎች ወደ አምላክ ቃል እንዲሳቡ በሚያደርግ መንገድ እንዳስተማረና እንደተመላለሰ ሁሉ እኛም እንዲሁ ማድረግ ይኖርብናል። (ማርቆስ 6:​34፤ ሉቃስ 4:​22, 32፤ 1 ጴጥሮስ 2:​21) ኢየሱስ ከአምላክ የተሰጠ ልዩ ማስተዋል ያለው ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን ልብን ማንበብ ይችላል። ስለዚህ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በይሖዋ ጠላቶች ላይ ኃይለኛ የውግዘት ቃላት ሰንዝሯል። (ማቴዎስ 23:​13-33) ይህንን ማድረጉ ታጋሽ አይደለም አያሰኘውም።

እኛ ግን እንደ ኢየሱስ ልብን የማንበብ ችሎታ የለንም። ስለዚህ የሐዋርያው ጴጥሮስን ምክር መከተል ይኖርብናል:- “ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፣ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት [“በጥልቅ አክብሮት፣” NW ] ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 3:​15) የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለተመሠረተው እምነታችን ጥብቅና መቆም ይኖርብናል። ይሁን እንጂ ይህን ስናደርግ ለሌሎችና ከልብ ለሚያምኑባቸው ነገሮች አክብሮት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ መሆን ይኖርበታል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ ይሁን።”​—⁠ቆላስይስ 4:​6

ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ላይ የሚከተለውን ብሏል:- “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።” (ማቴዎስ 7:​12) እንግዲያው እርስ በርሳችን ትዕግሥትን እናድርግ እንዲሁም ምሥራቹን ለምንሰብክላቸው ሰዎች አክብሮት እናሳይ። ለጽድቅ ባለን ቅንዓት ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ታጋሽነት ስናክልበት ይሖዋን እናስደስተዋለን። እንዲሁም ታጋሾች መሆናችንን እናሳያለን።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፈሪሳውያንን የትዕግሥት የለሽነት ዝንባሌ አስወግድ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የአባቱን የታጋሽነት መንፈስ አንጸባርቋል። አንተስ?