በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አምላክ በእርግጥ ሰዎችን በእሳታማ ሲኦል ይቀጣል?”

“አምላክ በእርግጥ ሰዎችን በእሳታማ ሲኦል ይቀጣል?”

“አምላክ በእርግጥ ሰዎችን በእሳታማ ሲኦል ይቀጣል?”

“የቲኦሎጂ ተማሪዎች ናችሁ እንዴ?”

ይህ ጥያቄ ጆኤልን እና ካርልን አስገረማቸው። ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው የሚያገለግሉት እነዚህ ሁለት ወጣቶች በአቅራቢያቸው በሚገኝ የመጽሐፍ መደብር ውስጥ መጽሐፎችን ይመለከቱ ነበር። ጆኤል የመጽሐፍ ቅዱስ ኮንኮርዳንሶችን እየተመለከተ ሳለ ካርል አገልግሎት ላይ ስላደረገው አንድ ውይይት ይነግረዋል። አጠገባቸው የነበረ አንድ ሰው ይህን ጭውውታቸውን ሰምቶ ኖሮ ቀርቦ አነጋገራቸው።

ሆኖም ሰውዬውን ይበልጥ ያሳሰበው እነዚህ ሁለት ወጣቶች የቲኦሎጂ ተማሪዎች መሆን አለመሆናቸው ሳይሆን ሌላ ጉዳይ ነበር። እንዲህ አላቸው:- “እኔ አይሁዳዊ ነኝ። ሆኖም አንዳንድ ክርስቲያን ጓደኞቼ አይሁዳውያን ክርስቶስን አንቀበልም በማለታቸው ምክንያት በእሳታማ ሲኦል ውስጥ እንደምቃጠል ነገሩኝ። ይህ ጉዳይ በጣም አስጨንቆኛል። አፍቃሪ ከሆነ አምላክ እንዲህ ያለ ቅጣት መምጣቱ ፍትሕ አይመስልም። አምላክ በእርግጥ ሰዎችን በእሳታማ ሲኦል ይቀጣል?”

ጆኤልና ካርል ለዚህ ቅን ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መሆናቸውን ነገሩት። ሙታን አንዳች እንደማያውቁና ሞተው ትንሣኤ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩት። በመሆኑም በእሳታማ ሲኦል ሥቃይ አያጋጥማቸውም። (መዝሙር 146:​3, 4፤ መክብብ 9:​5, 10፤ ዳንኤል 12:​13፤ ዮሐንስ 11:​11-14, 23-26) ለ45 ደቂቃ ከተነጋገሩ በኋላ ሰውዬው ለጆኤል እና ለካርል አድራሻውን ሰጣቸውና በዚህ ርዕስ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡት ለመናቸው።

ሲኦል እሳታማ የመሠቃያ ቦታ ቢሆን ኖሮ ወደዚያ ለመሄድ የሚጠይቅ ሰው ይኖር ነበር? ሆኖም ፓትርያርኩ ኢዮብ ከደረሰበት መከራ ለመገላገል በማሰብ “በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቁጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ!” ሲል ለምኗል። (ኢዮብ 14:​13) ኢዮብ ሲኦል የሥቃይ ቦታ ነው የሚል እምነት እንዳልነበረው ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ እዚያ መሸሸግ ፈልጎ ነበር። ሞት ማለት ከሕልውና ውጪ መሆን ማለት ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ሲኦል ደግሞ የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ነው።

ስንሞት ምን እንደምንሆንና ሙታን ምን ተስፋ እንዳላቸው ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ቀጥሎ የቀረበውን ግብዣ እንድትቀበል እናበረታታሃለን።