በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኦሪጀን—ትምህርቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽእኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

ኦሪጀን—ትምህርቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽእኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

ኦሪጀን—ትምህርቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽእኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

“ከሐዋርያት በኋላ የነበረ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን መሪ።” የላቲን ቩልጌት መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሆነው ጀሮም በሦስተኛው መቶ ዘመን የሃይማኖት ምሁር የነበረውን ኦሪጀንን ያወደሰው እንዲህ በማለት ነበር። ይሁን እንጂ ለኦሪጀን እንዲህ ዓይነት ከፍ ያለ ግምት ያለው ሁሉም ሰው አልነበረም። መናፍቅነት እንዲያቆጠቁጥ ያደረገ መጥፎ ሥር እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱት ሰዎችም ነበሩ። የኦሪጀን ተቺዎች “ሃይማኖታዊ ትምህርቱ ፍሬ ከርስኪና አደገኛ ከመሆኑም በላይ ገዳይ የሆነ የእባብ መርዙን በዓለም ላይ ረጭቷል” ሲሉ መናገራቸውን አንድ የ17ኛው መቶ ዘመን ጸሐፊ አስፍሯል። እንዲያውም ከሞተ ሦስት መቶ ዓመታት ገደማ ካለፉ በኋላ ኦሪጀን በይፋ መናፍቅ ተብሎ ተወግዟል።

ኦሪጀን አድናቆትም ጠላትነትም ያተረፈው ለምንድን ነው? በቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶች ላይ ምን ተጽእኖ አሳድሯል?

ለቤተ ክርስቲያን የሚቀና

ኦሪጀን በግብፅዋ እስክንድርያ ከተማ በ185 እዘአ ገደማ ተወለደ። ኦሪጀን የግሪክን ሥነ ጽሑፍ ጠንቅቆ የተማረ ቢሆንም ቅዱሳን ጽሑፎችን ለማጥናትም የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርግ አባቱ ሊዮኔዲስ ያስገድደው ነበር። ኦሪጀን የ17 ዓመት ልጅ ሳለ የሮም ንጉሠ ነገሥት ሃይማኖትን መቀየር ወንጀል እንደሆነ የሚገልጽ አዋጅ አውጥቶ ነበር። የኦሪጀን አባት ክርስቲያን ሆኖ ስለነበር ወኅኒ እንዲወርድ ተደረገ። በወጣትነት ቅንዓት የተሞላው ኦሪጀን ከአባቱ ጋር ወደ ወኅኒ ለመውረድና ሰማዕት ለመሆን ቆርጦ ነበር። ይህን የተመለከተችው እናቱ ከቤት እንዳይወጣ ልብሶቹን ደበቀችበት። ኦሪጀን ደብዳቤ በመጻፍ “አደራ ለእኛ ስትል ሐሳብህን እንዳትቀይር ተጠንቀቅ” በማለት አባቱን ተማጸነው። ሊዮኔዲስ በአቋሙ በመጽናት ቤተሰቡን ሜዳ ላይ በትኖ ተገደለ። ሆኖም ኦሪጀን በትምህርቱ ደህና ገፍቶ ስለነበረ የግሪክ ሥነ ጽሑፍ በማስተማር እናቱንና ስድስት ታናናሽ ወንድሞቹን ማስተዳደር ችሏል።

የንጉሠ ነገሥቱ ዓላማ ክርስትና እንዳይስፋፋ መግታት ነበር። አዋጁ ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን አስተማሪዎችን ጭምር የሚመለከት ስለነበረ የክርስትና ሃይማኖት መምህራን በጠቅላላ እስክንድርያን ጥለው ተሰደዱ። ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ሲፈልጉ ወጣቱ ኦሪጀን እንዲረዳቸው ይለምኑት የነበረ ሲሆን እሱም ይህን ሥራ አምላክ የሰጠው ተልእኮ እንደሆነ አድርጎ ተቀበለው። አብዛኞቹ ተማሪዎቹ በሰማዕትነት የተገደሉ ሲሆን አንዳንዶቹ የተገደሉት ገና ትምህርታቸውን እንኳ ሳይጨርሱ ነበር። ዳኛ ፊት በሚቀርቡበት ጊዜ ይሁን፣ እስር ቤት ሳሉ ወይም ሊገደሉ ሲሉ ኦሪጀን በሕይወቱ ቆርጦ ተማሪዎቹ በአቋማቸው እንዲጸኑ በግልጽ ያበረታታ ነበር። ኦሪጀን ተማሪዎቹ ወደሚገደሉበት ቦታ በሚወሰዱበት ጊዜ “ምንም ሳይፈራ እየሳመ ይሰናበታቸው” እንደነበር የአራተኛው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊ ዩሴቢየስ ዘግቧል።

ጓደኞቻችን ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩና እንዲገደሉ ያደረገው እሱ ነው በማለት ክርስቲያን ያልሆኑ ብዙዎች በኦሪጀን በጣም ይናደዱ ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜ በሕዝባዊ ዓመፅ ተወግሮ ከመገደል ለጥቂት አምልጧል። ኦሪጀን ከአሳዳጆቹ ለማምለጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተሽሎከሎከ ለመኖር ቢገደድም የማስተማር ሥራውን ቸል ብሎ አያውቅም። እንዲህ ዓይነቱ የኦሪጀን ድፍረትና ቆራጥነት የእስክንድርያውን ጳጳስ ዚሚትሪኦስን በእጅጉ ማርኮታል። ስለሆነም ዚሚትሪኦስ ኦሪጀንን በእስክንድርያ የሚገኘው ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤት ዋና ኃላፊ አድርጎ የሾመው ኦሪጀን ገና የ18 ዓመት ልጅ ሳለ ነበር።

በመጨረሻም ኦሪጀን የታወቀ ምሁርና ብዙ መጻሕፍትን የጻፈ ሰው ለመሆን በቃ። ምንም እንኳ ይህ በጣም የተጋነነ ሊሆን ቢችልም አንዳንዶች 6, 000 መጻሕፍትን እንደጻፈ ይናገራሉ። ኦሪጀን ይበልጥ የሚታወቀው ሄክሳፕላ በሚባለው በጣም ትልቅ ባለ 50 ጥራዝ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች እትም ነው። ኦሪጀን ሄክሳፕላን ያዘጋጀው በሚከተሉት ስድስት ረድፎች ከፋፍሎ ነው:- (1) የዕብራይስጡና የአረማይኩ ጥቅስ፣ (2) የጥቅሱ ግሪክኛ ትርጉም፣ (3) የአኩዌላ የግሪክኛ ትርጉም፣ (4) የሲመአከስ የግሪክኛ ትርጉም፣ (5) ከዕብራይስጡ ጥቅስ ጋር ይበልጥ እንዲመሳሰል በማድረግ ኦሪጀን አሻሽሎ ያዘጋጀው የሰፕቱጀንት ትርጉም እና (6) የቲኦዶሸን የግሪክኛ ትርጉም። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ጆን ሆርት “ኦሪጀን ጥቅሶችን በዚህ መንገድ አቀናጅቶ ያዘጋጀው የሰፕቱጀንት ትርጉም ብቻ በእጁ ለሚገኝ ግሪክኛ አንባቢ ግር ሊሉ ወይም ሊያሳስቱ የሚችሉ ብዙ ጥቅሶችን ግልጽ ለማድረግ በማሰብ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

‘ከተጻፈው ማለፍ’

ያም ሆኖ በሦስተኛው መቶ ዘመን የነበረው ሃይማኖታዊ ግራ መጋባት ኦሪጀን ቅዱሳን ጽሑፎችን የሚያስተምርበትን መንገድ በእጅጉ ነክቷል። በዚያን ጊዜ ሕዝበ ክርስትና ገና ጨቅላ ብትሆንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ትምህርቶች ተበክላ የነበረ ሲሆን በየቦታው ተበታትነው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናቷም የተለያዩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ያስተምሩ ነበር።

ኦሪጀን የሐዋርያት ትምህርቶች ናቸው በማለት እነዚህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ተቀብሏቸው ነበር። ሆኖም በሌሎች ጥያቄዎች ላይ የራሱን ግምታዊ ሐሳብ የመስጠት ነፃነት እንዳለው ተሰምቶታል። በዚያን ወቅት አብዛኞቹ ተማሪዎቹ በወቅቱ ይነሱ ከነበሩት የፍልስፍና ጥያቄዎች ጋር በመታገል ላይ ነበሩ። ስለሆነም እነሱን ለመርዳት ሲል የወጣት ተማሪዎቹን አእምሮ በመቅረጽ ላይ ያሉትን የተለያዩ መምህራንን ፍልስፍናዎች በጥንቃቄ አጠና። ከዚያም ተማሪዎቹ ለሚያነሷቸው የፍልስፍና ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጥ ጀመረ።

ኦሪጀን መጽሐፍ ቅዱስን ከፍልስፍና ጋር ለማስታረቅ በሚያደርገው ሙከራ ቅዱሳን ጽሑፎች የተሰወረ መንፈሳዊ ትርጉም እንዳላቸው አድርጎ በመተርጎም ዘዴ ተጠቅሟል። አንድ ጥቅስ ምንጊዜም ቢሆን መንፈሳዊ ትርጉም አለው፤ ቀጥተኛ ትርጉም ግን የግድ ላይኖረው ይችላል የሚል አመለካከት ነበረው። ይህም “ምንም እንኳ ኦሪጀን የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ በመተርጎም ረገድ ከማንም ይበልጥ ጥብቅና ታማኝ እንደሆነ ቢናገርም ከራሱ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ጋር የሚስማሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ሐሳቦችን እንዲጨምር” በር እንደከፈተለት አንድ ምሁር ተናግረዋል።

ኦሪጀን ለአንድ ተማሪው የጻፈው ደብዳቤ የነበረውን አስተሳሰብ ለማስተዋል ይረዳል። ኦሪጀን እስራኤላውያን ከግብፃውያን በወሰዱት ወርቅ ለይሖዋ ቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ እቃዎችን መሥራታቸውን ጠቁሟል። እሱም ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ የግሪክን ፍልስፍና በመጠቀም ክርስትናን ማስተማር እንደሚችል አስቧል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከግብፅ የወሰዷቸው ቁሳቁሶች እስራኤላውያንን በእጅጉ ጠቅመዋቸዋል። ግብፃውያኑ እነዚህን ቁሳቁሶች ለተገቢው ዓላማ ጥቅም ላይ አላዋሏቸውም ነበር። ዕብራውያኑ ግን በአምላክ ጥበብ በመመራት ለአምላክ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውሉ አድርገዋቸዋል።” በተመሳሳይ ሁኔታ ኦሪጀን ተማሪው “ክርስትናን ለማጥናት የሚረዱ ጽንሰ ሐሳቦችን ከግሪክ ፍልስፍና ውስጥ ፈልጎ እንዲያወጣ” አበረታትቶታል።

እንዲህ ዓይነቱ መጽሐፍ ቅዱስን እንደፈለጉ የመተርጎም አካሄድ በክርስትና ትምህርትና በግሪክ ፍልስፍና መካከል ያለውን ልዩነት አደብዝዞታል። ለምሳሌ ያህል ኦሪጀን ኦን ፈርስት ፕሪንስፕልስ በተባለው መጽሐፉ ላይ ኢየሱስን ‘አንድያ ልጅ ሆኖ የተወለደ ነገር ግን መጀመሪያ የሌለው’ ሲል ገልጾታል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- ‘ትውልዱም ዘላለማዊና መጨረሻ የሌለው ነው። የልጅነትን ቦታ ያገኘው በራሱ የአምላክነት ባሕርይ እንጂ የሕይወትን እስትንፋስ በመቀበል ወይም በሌላ ውጫዊ ኃይል እርዳታ አይደለም።’

ቅዱሳን ጽሑፎች የይሖዋ አንድያ ልጅ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር” እና “በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ” እንደሆነ ስለሚያስተምሩ ኦሪጀን ይህን ሐሳብ ያገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ አይደለም። (ቆላስይስ 1:15፤ ራእይ 3:14) የሃይማኖት ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ኦውግስተስ ኔአንደር እንደሚሉት ከሆነ ኦሪጀን “ትውልዱ ዘላለማዊ” የሚለውን ሐሳብ ያገኘው “የፕላቶን ፍልስፍና ባጠናበት” ወቅት ነው። በመሆኑም ኦሪጀን “ከተጻፈው አትለፍ” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ተላልፏል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 4:6

መናፍቅ ተብሎ ተወገዘ

አስተማሪ በሆነባቸው የመጀመሪያ ዓመታት አንድ የእስክንድርያ ሲኖዶስ የቅስና ማዕረጉን ገፍፎታል። ምናልባትም ይህን ያደረገው የኦሪጀን ዝነኛ እየሆነ መምጣት ያስቀናው ጳጳሱ ዚሚትሪኦስ ሊሆን ይችላል። ኦሪጀን አሁንም ጥሩ የክርስትና ትምህርት ጠበቃ እንደሆነ ተደርጎ ወደሚታይበት ወደ ጳለስጢና የሄደ ሲሆን በዚያም በቅስና ማገልገሉን ቀጥሏል። እንዲያውም በምሥራቅ “መናፍቃን” በተነሱበት ወቅት ኦሪጀን ከጥንታዊው ልማዳዊ እምነት ወጣ የሚሉትን ጳጳሳት አሳምኖ እንዲመልሳቸው ይጠየቅ ነበር። የኦሪጀን ስም ይበልጥ በክፉ መነሳት የጀመረው በ254 እዘአ ከሞተ በኋላ ነው። ለምን?

ቤተ ክርስቲያን እንደ ትክክለኛ ሃይማኖታዊ ትምህርት አድርጋ የተቀበለችው ሐሳብ በግልጽ የተቀመጠው ስመ ክርስትና ገናና ሃይማኖት ከሆነ በኋላ ነበር። ስለሆነም መላምታዊ እንዲሁም አልፎ አልፎ አጠራጣሪ የሆኑትን አብዛኞቹን የኦሪጀንን አመለካከቶች በኋለኞቹ ትውልዶች የተነሱ ሃይማኖታዊ ምሁራን አልተቀበሏቸውም። ስለዚህ የኦሪጀን ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጦፈ ክርክር እንዲነሳ ምክንያት ሆነዋል። ቤተ ክርስቲያን ለክርክሩ እልባት ለማስገኘትና መከፋፈል እንዳይፈጠር ለማድረግ ስትል ኦሪጀንን በይፋ ከመናፍቃን ፈርጃዋለች።

ለዚህ ስህተት ተጠያቂው ኦሪጀን ብቻ አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ከትክክለኛው የክርስቶስ ትምህርት የማፈንገጥ ሁኔታ እንደሚኖር ተንብዮአል። ይህ ዓይነቱ ክህደት መስፋፋት የጀመረው የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ነው። (2 ተሰሎንቄ 2:6, 7) በመጨረሻም ራሳቸውን “እውነተኞች” እንደሆኑ አድርገው የሚመለከቱ ሌሎቹ ሁሉ “መናፍቃን” ናቸው የሚሉ የተወሰኑ ክርስቲያን ነን ባዮች ተነሱ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሕዝበ ክርስትና ከእውነተኛው ክርስትና በእጅጉ ርቃለች።

“በውሸት እውቀት ከተባለ”

ምንም እንኳ አብዛኞቹ የኦሪጀን ሐሳቦች በመላምት ላይ የተመሠረቱ ቢሆኑም ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎችም አሉት። ለምሳሌ ያህል በኦሪጀን የተዘጋጀው ሄክሳፕላ የተሰኘው መጽሐፍ ቴትራግራማተን ተብለው የሚጠሩትን የአምላክን ስም የሚወክሉትን የመጀመሪያዎቹን አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ይዞ ይገኛል። ይህም የጥንት ክርስቲያኖች ይሖዋ የሚለውን የአምላክ መጠሪያ ስም ያውቁትና ይጠቀሙበት እንደነበረ የሚያሳይ ትልቅ ማስረጃ ነው። ቴዎፍሎስ የተባለው የአሥራ አምስተኛው መቶ ዘመን ፓትሪያርክ በአንድ ወቅት የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር:- “የኦሪጀን ሥራ ሁሉም ዓይነት አበባ እንደበቀለበት መስክ ነው። ከዚያ ውስጥ ቆንጆ አበባ ካገኘሁ ቀጥፌ እወስዳለሁ፤ እንደ እሾህ የሚዋጋ መስሎ የታየኝን ደግሞ በሩቁ እሸሸዋለሁ።”

የኦሪጀን መንፈሳዊ ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶችና የግሪክን ፍልስፍና ቀላቅሎ የያዘ በመሆኑ በስሕተት የተሞላ ሲሆን ይህም በሕዝበ ክርስትና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል። የኦሪጀን እንግዳ ፍልስፍናዎች ከጊዜ በኋላ ተቀባይነት ያጡ ቢሆንም ስለ ክርስቶስ “ዘላለማዊ ትውልድ” ያስፋፋው አመለካከት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት እንዲጸነስ አስተዋጽኦ አድርጓል። ዘ ቸርች ኦፍ ዘ ፈርስት ስሪ ሴንቸሪስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚከተለው ይላል:- “[ኦሪጀን የጀመረው] ፍልስፍና ለረጅም ጊዜ ዘልቋል።” በውጤቱስ ምን ተከሰተ? “ቀላልና ግልጽ የነበረው የክርስትና እምነት ተበከለ፤ እንዲሁም ይህ ነው የማይባል ስህተት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰርጎ ገባ።”

ኦሪጀን የሐዋርያው ጳውሎስን ጥብቅ ምክር መከተልና ‘በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር በመራቅ’ ለዚህ ክህደት አስተዋጽኦ ከማድረግ መቆጠብ ይችል ነበር። ኦሪጀን ግን እንዲህ ያለውን “እውቀት” ለትምህርቱ መሠረት በማድረግ ‘ከእምነት ሳተ።’​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21፤ ቆላስይስ 2:8

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኦሪጀን የተዘጋጀው “ሄክሳፕላ” የተሰኘው መጽሐፍ የአምላክ ስም በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንደተሠራበት ያሳያል

[ምንጭ]

Published by permission of the Syndics of Cambridge University Library, T-S 12.182

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Culver Pictures