በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሞት በኋላ ሕይወት አለን?

ከሞት በኋላ ሕይወት አለን?

ከሞት በኋላ ሕይወት አለን?

ከዛሬ 3,500 ዓመታት ገደማ በፊት ፓትርያርኩ ኢዮብ “በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን?” በማለት ጠይቆ ነበር። (ኢዮብ 14:​14) ይህ ጥያቄ የሰውን ልጅ ለብዙ ሺህ ዓመታት ግራ ሲያጋባ ቆይቷል። በየትኛውም ማኀበረሰብ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ሲያወጡና ሲያወርዱ ከቆዩ በኋላ የተለያዩ ንድፈ ሐሳቦችን አፍልቀዋል።

ብዙ ስመ ክርስቲያኖች በመንግሥተ ሰማያትና በሲኦል ያምናሉ። ሂንዱዎች ደግሞ በሪኢንካርኔሽን ያምናሉ። በአንድ የእስልምና ሃይማኖት ማዕከል ውስጥ ረዳት የሆኑት አሚር ሚአዊያ ሙስሊሞች በዚህ ረገድ ያላቸውን አመለካከት አስመልክተው ሲናገሩ “ከሞት በኋላ የፍርድ ቀን እንዳለ እናምናለን፤ አምላክ ማለትም አላህ ፊት ስትቀርቡ ልክ ችሎት ፊት እንደቀረባችሁ ያህል ነው” ብለዋል። በእስልምና እምነት መሠረት አላህ የእያንዳንዱን ሰው አኗኗር ይመረምርና ወይ ወደ ገነት ያስገባዋል አሊያም እሳታማ ሲኦል ይከተዋል።

በስሪ ላንካ ቡዲስቶችም ሆኑ ካቶሊኮች የቤተሰባቸው አባል ሲሞት የቤቱን በሮችና መስኮቶች ክፍት አድርገው ይተውአቸዋል። ፋኖስ አብርተው የሟቹ እግር ፊት ለፊት ባለው በር ትይዩ እንዲሆን አድርገው የሬሳ ሳጥኑን ያስቀምጡታል። እንዲህ ማድረጋቸው የሟቹ መንፈስ ወይም ነፍስ ከቤቱ እንዲወጣ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል ብለው ያምናሉ።

በዌስተርን አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ሮናልድ ኤም በርንት የአውስትራሊያ አቦርጂኖች “ሰዎች ሊጠፋ የማይችል መንፈስ አላቸው” ብለው ያምናሉ ሲሉ ገልጸዋል። አንዳንድ የአፍሪካ ጎሳዎች ተራ ሰዎች ሲሞቱ ጣረ ሞት የሚሆኑ ሲሆን ታዋቂ ሰዎች ደግሞ መናፍስት በመሆን ክብር የሚሰጣቸውና ሰዎች የሚለማመኗቸው የማይታዩ የማኅበረሰቡ መሪዎች ሆነው ያገለግላሉ ብለው ያምናሉ።

በአንዳንድ አገሮች ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ያሉት እምነቶች የአካባቢውን ባሕልና የስመ ክርስትናን ትምህርት አዋህደው የያዙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ ብዙ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች አንድ ሰው ሲሞት ማንም ሰው የሟቹን መንፈስ በመስታወቱ ውስጥ እንዳይመለከት ለማድረግ ሲባል መስታወቶችን የመሸፈን ልማድ አላቸው።

‘ስንሞት ምን እንሆናለን?’ ለሚለው ጥያቄ ሰዎች የሚሰጡት መልስ በእርግጥም የተለያየ ነው። ሆኖም እነዚህ የተለያዩ መልሶች የሚያስተላልፉት አንድ መሠረታዊ የሆነ ሐሳብ ነው:- በሰው ውስጥ የማይሞትና ከሞት በኋላ በሕይወት የሚቀጥል ነገር አለ። አንዳንዶች ይህ “ነገር” መንፈስ ነው ብለው ያምናሉ። ለምሳሌ በአንዳንድ የአፍሪካና የእስያ ክፍሎች እንዲሁም እንደ ፖሊኔዥያ፣ ሚላኔዥያና፣ ማይክሮኔዥያ ባሉት የፓስፊክ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ነፍስ ሳይሆን መንፈስ አይሞትም ብለው ያምናሉ። እንዲያውም አንዳንድ ቋንቋዎች ጭራሽ “ነፍስ” የሚለው ቃል የላቸውም።

በሰው ውስጥ መንፈስ አለ? በሞት ወቅት መንፈስ በእርግጥ ከሥጋ ይለያልን? የሚለይ ከሆነ በኋላ ምን ይሆናል? ሙታን ያላቸው ተስፋስ ምንድን ነው? እነዚህ ጥያቄዎች እንዲሁ በቸልታ ሊታለፉ አይገባም። ምንም ዓይነት ባሕል ወይም ሃይማኖት ይኑርህ ሞት ልትሸሸው የማትችለው እውነታ ነው። ስለሆነም እነዚህ አከራካሪ ጥያቄዎች አንተን በግል ይነኩሃል። ጉዳዩን በጥልቅ እንድትመረምረው እናበረታታሃለን።