በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማይሞት መንፈስ አለህን?

የማይሞት መንፈስ አለህን?

የማይሞት መንፈስ አለህን?

ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከእውነተኛው አምላክ ከይሖዋ የመጣ የእውነት መጽሐፍ ነው።​—⁠መዝሙር 83:​18

ይሖዋ የሰው ልጆችን ጨምሮ የሁሉም ነገሮች ፈጣሪ ስለሆነ ስንሞት ምን እንደምንሆን አሳምሮ ያውቃል። (ዕብራውያን 3:​4፤ ራእይ 4:​11) ስለዚህ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሞት በኋላ ስላለው ሁኔታ እውነተኛና አጥጋቢ መልስ ሰጥቷል።

መንፈስ ምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መንፈስ” ተብለው የተተረጎሙት ቃሎች መሠረታዊ ትርጉም “እስትንፋስ” ማለት ነው። ሆኖም “መንፈስ” የሚለው ቃል ከመተንፈስ የበለጠ ነገርንም ይጨምራል። ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ “ከነፍስ [“ከመንፈስ፣” NW ] የተለየ ሥጋ የሞተ” ነው ሲል ገልጿል። (ያዕቆብ 2:​26) ስለዚህ መንፈስ ለሥጋ ሕይወት የሚሰጥ ኃይል ነው ማለት ነው።

ይህ ሕይወት ሰጪ ኃይል እንዲያው ዝም ብሎ እስትንፋስ ወይም በሳንባ ውስጥ የሚዘዋወረው አየር ሊሆን አይችልም። ለምን? ምክንያቱም እስትንፋስ ካቆመም በኋላ ሕይወት ለአጭር ጊዜ፣ ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚለው ደግሞ “በርከት ላሉ ደቂቃዎች” በሰውነት ሴሎች ውስጥ ይቆያል። ሰውዬው እንደገና ነፍስ እንዲዘራ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ሊሳካ የሚችለው በዚህ ምክንያት ነው። ሆኖም የማይታየው የሕይወት ኃይል አንዴ ከሁሉም የሰውነት ሴሎች ከወጣ ሰውዬው እንደገና ነፍስ እንዲዘራ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ሁሉ ከንቱ ነው። የቱንም ያህል መጠን ያለው እስትንፋስ ወይም አየር ቢሆን በአንዲት ሴል ላይ እንኳ ሕይወት መዝራት አይችልም። ስለዚህ መንፈስ የማይታይ የሕይወት ኃይል ማለትም ሴሎችንም ሆነ ሰውዬውን በሕይወት እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ኃይል ነው። ይህ የሕይወት ኃይል ተጠብቆ የሚቆየው በመተንፈስ ነው።​—⁠ኢዮብ 34:​14, 15

ይህ መንፈስ የሚሠራው በሰዎች ውስጥ ብቻ ነውን? በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ይረዳናል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን የሰዎችም ሆነ የእንስሳት “እስትንፋስ [“መንፈስ፣” NW ] አንድ ነው” ካለ በኋላ “የሰው ልጆች ነፍስ [“መንፈስ፣” NW ] ወደ ላይ እንደምትወጣ የእንስሳም ነፍስ [“መንፈስ፣” NW ] ወደ ታች ወደ ምድር እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው?” ሲል ጠይቋል። (መክብብ 3:​19-21) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንስሳትም ሆኑ ሰዎች መንፈስ እንዳላቸው ይናገራል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

መንፈስ ወይም የሕይወት ኃይል አንድን መሣሪያ ከሚያሠራው የኤሌክትሪክ ዥረት (Current) ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የማይታየው የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያንቀሳቅሰው መሣሪያ ዓይነት የተለያዩ ሥራዎችን ሊያከናውን ይችላል። ለምሳሌ የኤሌክትሪክ ማብሰያ ሙቀት እንዲያወጣ፤ ኮምፒውተር መረጃ እንዲያጠናቅር እንዲሁም ቴሌቪዥን ምስልና ድምፅ እንዲያወጣ ተደርጎ ሊሠራ ይችላል። ሆኖም የኤሌክትሪኩ ኃይል የሚያንቀሳቅሰውን መሣሪያ ቅርጽና ባሕርይ ሊወስድ አይችልም። እንዲሁ ኃይል ብቻ ነው። በተመሳሳይም የሕይወት ኃይል ሕያው አድርጎ የሚያንቀሳቅሰውን ፍጥረት ባሕርይ ወይም ቅርጽ ሊወስድ አይችልም። ይህ ኃይል ስብዕናም ሆነ የማሰብ ችሎታ የለውም። የሰዎችም ሆነ የእንስሳት ‘መንፈስ አንድ ነው።’ (መክብብ 3:​19) ስለዚህ አንድ ሰው ሲሞት መንፈሱ ወደ ሌላ መንፈሳዊ ዓለም ሄዶ በሕይወት መኖሩን አይቀጥልም።

ታዲያ ሙታን የሚገኙበት ሁኔታ ምንድን ነው? እንዲሁም አንድ ሰው ሲሞት መንፈሱ ምን ይሆናል?

“ወደ አፈርም ትመለሳለህ”

የመጀመሪያው ሰው አዳም ሆነ ብሎ የአምላክን ትእዛዝ ሲጥስ አምላክ እንዲህ አለው:- “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህ።” (ዘፍጥረት 3:​19) ይሖዋ አዳምን ከአፈር ከመፍጠሩ በፊት አዳም የት ነበረ? የትም አልነበረም! አዳም ከዚህ በፊት ሕልውና አልነበረውም! ስለዚህ ይሖዋ አምላክ አዳም ‘ወደ አፈር ይመለሳል’ ብሎ ሲናገር አዳም እንደሚሞትና ከመሬት ንጥረ ነገሮች ጋር እንደሚቀላቀል ማመልከቱ ነበር። አዳም ወደ መንፈሳዊው ዓለም አይሸጋገርም። አዳም ሲሞት ቀድሞ ወደ ነበረበት ሕይወት አልባነት ይመለሳል። ቅጣቱ ሞት ወይም በሌላ አነጋገር በሕይወት አለመኖር እንጂ ወደ ሌላ መንፈሳዊ ዓለም መሸጋገር አልነበረም።​—⁠ሮሜ 6:​23

ስለሞቱት ሌሎች ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? ከዚህ በፊት የሞቱት ሰዎች የሚገኙበት ሁኔታ በመክብብ 9:​5, 10 ላይ በግልጽ ሰፍሯል:- “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም . . . በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም።” ስለዚህ ሞት ማለት ከሕልውና ውጭ መሆን ማለት ነው። መዝሙራዊው አንድ ሰው ሲሞት ‘ነፍሱ [“መንፈሱ፣” NW ] እንደምትወጣ ወደ መሬቱም እንደሚመለስ፤ ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ እንደሚጠፋ’ ተናግሯል።​—⁠መዝሙር 146:​4

ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ሙታን ሕይወት አልባ ናቸው። ምንም ነገር ሊያውቁ አይችሉም። ሊያዩህም ሆነ ሊሰሙህ ወይም ሊያነጋግሩህ አይችሉም። ሊረዱህም ሆነ ሊጎዱህ አይችሉም። ሙታንን መፍራት ፈጽሞ አያስፈልግህም። ሆኖም አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ መንፈሱ ከሰውዬው ‘የሚወጣው’ እንዴት ነው?

መንፈስም ‘ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል’

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ሲሞት “ነፍሱ [“መንፈሱ፣” NW ] ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር” እንደሚመለስ ይገልጻል። (መክብብ 12:​7) ይህ ማለት መንፈሱ ቃል በቃል ጠፈርን አቋርጦ ወደ አምላክ ይሄዳል ማለት ነውን? በፍጹም እንደዚያ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ይመለሳል” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት መንገድ የግድ ቃል በቃል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዛወርን አያመለክትም። ለምሳሌ ታማኝ ያልሆኑት እስራኤላውያን “ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” ተብሎ ተነግሯቸው ነበር። (ሚልክያስ 3:​7) የእስራኤላውያን ወደ ይሖዋ “መመለስ” ማለት መጥፎ ድርጊት መፈጸማቸውን በማቆም ራሳቸውን ከአምላክ የጽድቅ መስፈርቶች ጋር ማስማማታቸውን የሚያመለክት ሲሆን የይሖዋ ወደ እስራኤላውያን መመለስ ደግሞ ይሖዋ እንደገና ትኩረቱን በሕዝቡ ላይ ማድረጉን የሚያመለክት ነው። በሁለቱም ሁኔታዎች “መመለስ” የሚለው ቃል ዝንባሌን እንጂ ቃል በቃል ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላኛው አካባቢ መሄድን አያመለክትም።

በተመሳሳይም በሞት ወቅት መንፈስ ‘ወደ እግዚአብሔር ሲመለስ’ ከምድር ወደ መንፈሳዊው ዓለም የሚደረግ ምንም ዓይነት ሽግግር የለም። የሕይወት ኃይል አንዴ ከሰውነት ከወጣ በኋላ ይህንን ኃይል ለሰውዬው በመመለስ ዳግመኛ ሕያው ሊያደርገው የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። ስለዚህ መንፈሱ “ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል” ሲባል የሰውዬው ወደፊት የመኖር ተስፋ ሙሉ በሙሉ የተመካው በአምላክ ላይ ነው ማለት ነው።

ለምሳሌ ያህል ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የሚናገሩትን ተመልከት። የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ:- አባት ሆይ፣ ነፍሴን [“መንፈሴን፣” NW ] በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን [“መንፈሱን፣” NW ] ሰጠ።” (ሉቃስ 23:​46) መንፈሱ ስትወጣ ኢየሱስ ቃል በቃል ወደ ሰማይ ተጉዟል ማለት አይደለም። ኢየሱስ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ ከሞት አልተነሳም ነበር። እንዲያውም ወደ ሰማይ የሄደው ከ40 ቀናት በኋላ ነበር። (ሥራ 1:​3, 9) ሆኖም ኢየሱስ በሚሞትበት ወቅት ይሖዋ ወደ ሕይወት ሊመልሰው እንደሚችል በመተማመን መንፈሱን ለአባቱ በአደራ ሰጥቶት ነበር።

አዎን፣ አምላክ አንድን የሞተ ሰው ወደ ሕይወት ሊመልሰው ይችላል። (መዝሙር 104:​30) ይህ ምንኛ አስደናቂ ተስፋ ነው!

እርግጠኛ ተስፋ

መጽሐፍ ቅዱስ “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል” በማለት ይናገራል። (ዮሐንስ 5:​28, 29) አዎን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በይሖዋ መታሰቢያ ውስጥ ያሉት ሁሉ ትንሣኤ እንደሚያገኙ ወይም ወደ ሕይወት እንደሚመለሱ ቃል ገብቷል። ከእነርሱም ውስጥ የጽድቅ ጎዳና የተከተሉ የይሖዋ አገልጋዮች እንደሚገኙበት ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ከአምላክ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ሳያገኙ የሞቱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ይሖዋ ምን እንደሚፈልግባቸው የማያውቁ ወይም ደግሞ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ጊዜ ያላገኙ ናቸው። እንዲህ ያሉት ሰዎች በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነርሱ ሲገልጽ ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሳሉ’ ይላል።​—⁠ሥራ 24:​15

በዛሬው ጊዜ ምድር በጥላቻና በግጭት፣ በዓመፅና በደም መፋሰስ፣ በብክለትና በበሽታ ተሞልታለች። ሙታን እንዲህ ባለው ሁኔታ ለመኖር ወደ ሕይወት የሚመለሱ ቢሆን ደስታቸው ዘላቂነት እንደማይኖረው የተረጋገጠ ነው። ሆኖም ፈጣሪ ዛሬ በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ያለውን ክፉ የነገሮች ሥርዓት በቅርቡ ወደ ፍጻሜው እንደሚያመጣው ቃል ገብቷል። (ምሳሌ 2:​21, 22፤ ዳንኤል 2:​44፤ 1 ዮሐንስ 5:​19) ከዚያም አስደናቂ የሆነው ጻድቅ የሰው ልጆች ሕብረተሰብ ማለትም “አዲስ ምድር” እውን ይሆናል።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​13

በዚያን ጊዜ “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም።” (ኢሳይያስ 33:​24) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” በማለት ስለሚናገር ሞት የሚያስከትለው ከባድ ሐዘን ጭምር ይቀራል። (ራእይ 21:​4) “በመታሰቢያ መቃብር” ላሉት ይህ ምንኛ አስደናቂ ተስፋ ነው!

ይሖዋ ክፋትን ከምድር በሚያስወግድበት ወቅት ጻድቃንን ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ አያጠፋም። (መዝሙር 37:​10, 11፤ 145:​20) እንዲያውም “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች አሁን ያለውን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ከሚያጠፋው “ታላቅ መከራ” በሕይወት ይተርፋሉ። (ራእይ 7:​9-14) ስለዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ሙታንን ለመቀበል በዚያ ይገኛሉ።

በሞት የተለዩህን የምትወዳቸውን ሰዎች እንደገና ለማየት ትጓጓለህ? ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ? የምትፈልግ ከሆነ ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ይኖርብሃል። (ዮሐንስ 17:​3) የይሖዋ ፈቃድ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​3, 4

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህ ”

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንፈስ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ሊመሳሰል ይችላል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትንሣኤ ዘላቂ ደስታ ያስገኛል