በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

አንደኛ ጴጥሮስ 4:​3 አንዳንድ ክርስቲያኖች በአንድ ወቅት “ነውርም ባለበት በጣዖት አምልኮ” ተካፍለው እንደነበር ይናገራል። ይሁን እንጂ ሁሉም ዓይነት የጣዖት አምልኮ በአምላክ ዘንድ እንደ ነውር የሚታይ፣ የተወገዘና የተከለከለ አይደለምን?

አዎን፣ በአምላክ ዓይን ማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ የተወገዘ ነው። የእርሱን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ጣዖትን ከማምለክ መራቅ አለባቸው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 5:11፤ ራእይ 21:8

ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጴጥሮስ እዚህ ላይ እየጠቀሰ ያለው ሌላ ዓይነት የጣዖት አምልኮ ሳይሆን አይቀርም። ይህ የሆነበት አንደኛው ምክንያት ጥንት በነበሩ በርካታ ብሔራት ዘንድ የጣዖት አምልኮ የተለመደ ከመሆኑም በላይ በባለ ሥልጣናት ዘንድ የተፈቀደ ነበር። ይህም ማለት የአገሩ ሕግ እንዲህ ያለውን የጣዖት አምልኮ አይከለክልም ነበር። እንዲያውም አንዳንዱ የጣዖት አምልኮ በብሔሩ ወይም በመንግሥት ፖሊሲ ውስጥ የታቀፈ ነበር። በዚህ መንገድ አንዳንዶች ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት ‘ምንም የሕግ ገደብ ሳይኖርባቸው በጣዖት አምልኮ ተካፍለዋል።’ (የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የ1950 እትም) ለምሳሌ ያህል የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር እንደ ጣዖት የሚመለክ ከወርቅ የተሠራ ምሥል እንዳቆመ መመልከት ይቻላል። ይሁን እንጂ የይሖዋ አገልጋዮች የነበሩት ሲድራቅ፣ ሚሳቅ እና አብደናጎ ምስሉን ለማምለክ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።​—⁠ዳንኤል 3:1-12

ከሌላ አቅጣጫ ስንመለከተው ደግሞ ብዙዎቹ የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች ከተፈጥሮ ሕግ ወይም በተፈጥሮ ከተገኘ ሕሊና ጋር በቀጥታ በሚጋጩ ጸያፍ ድርጊቶች የተሞሉ ናቸው። (ሮሜ 2:​14, 15) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ለባሕርይ የማይገቡ’ እና “ነውር” የሆኑ ወራዳ ተግባራትን ጠቅሶ የጻፈ ሲሆን እነዚህም ብዙውን ጊዜ በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ የሚከናወኑ ነበሩ። (ሮሜ 1:26, 27) ነውር ባለበት የጣዖት አምልኮ የሚካፈሉ ወንዶችና ሴቶች ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን ለመለየት የሚያስችላቸውን በተፈጥሮ ያገኙትን መመሪያ አይከተሉም። በእርግጥም እነዚህ ክርስቲያን የሚሆኑ ሰዎች እንዲህ ካለው ብልሹ ተግባር መራቃቸው የተገባ ነበር።

ከዚህም በላይ አይሁዳውያን ባልሆኑ አሕዛብ ዘንድ ተስፋፍተው የነበሩት የጣዖት አምልኮዎች በይሖዋ አምላክ ዘንድ የተወገዙ ነበሩ። በዚህም የተነሳ ሕገ ወጥ ናቸው። a​—⁠ቆላስይስ 3:5-7

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በአንደኛ ጴጥሮስ 4:​3 ላይ የሚገኘው ግሪክኛው ጥቅስ ቃል በቃል “ሕገ ወጥ የሆነ የጣዖት አምልኮ” የሚል ትርጉም አለው። ሐረጉ በእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ “የተከለከለ የጣዖት አምልኮ፣” “ያልተፈቀደ የጣዖት አምልኮ” እና “ሕገ ወጥ የጣዖት አምልኮ” እንደሚሉ ባሉ ስያሜዎች በተለያየ መንገድ ተተርጉሟል።