በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደስተኛ የመከሩ ሠራተኞች ሁኑ!

ደስተኛ የመከሩ ሠራተኞች ሁኑ!

ደስተኛ የመከሩ ሠራተኞች ሁኑ!

“መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።”—⁠ማቴዎስ 9:​37, 38

1. የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ወደፊት መግፋታችንን እንድንቀጥል የሚረዳን ምንድን ነው?

 የይሖዋ አገልጋዮች በመሆን የተጠመቅነው በቅርብም ይሁን ከረጅም ዓመታት በፊት ስለዚያ ቀን ስናስብ ልክ ትናንት የሆነ ያክል ይሰማን ይሆናል። ራሳችንን ከወሰንን በኋላ ትኩረታችን ሁሉ ያረፈው ይሖዋን በማወደሱ ሥራ ላይ ነበር። ሌሎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰሙና ምናልባትም እንዲቀበሉ ለመርዳት ጊዜ እንድንዋጅ የሚያደርገን ዋናው ምክንያት ይሖዋን በደስታ ለማገልገል ያለን ፍላጎት ነበር። (ኤፌሶን 5:15, 16) ዛሬም ‘ሁልጊዜ የጌታ ሥራ የበዛልን’ ከሆንን ጊዜው ሳይታወቀን ያልፋል። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ምንም እንኳ ችግሮች ቢገጥሙንም የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ የምናገኘው ደስታ በያዝነው አገልግሎት ወደፊት እንድንገፋ ያንቀሳቅሰናል።​—⁠ነህምያ 8:​10

2. ምሳሌያዊ በሆነው የመከር ሥራ ደስታ እንድናገኝ ምክንያት የሚሆኑን ነገሮች ምንድን ናቸው?

2 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ምሳሌያዊ በሆነ የመከር ሥራ ተሰማርተናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ለዘላለም ሕይወት የመሰብሰቡን ሥራ ከመከር ጋር አመሳስሎታል። (ዮሐንስ 4:35-38) እኛም በእንዲህ ዓይነቱ የመከር ሥራ የምንሳተፍ በመሆናችን የጥንቶቹ ክርስቲያን የመከር ሠራተኞች ያገኙትን ደስታ መመርመራችን አበረታች ሆኖ እናገኘዋለን። በዛሬው ጊዜ በመካሄድ ላይ ባለው የመከር ሥራ ደስታ እንድናገኝ የሚያስችሉንን ሦስት ምክንያቶች እንመለከታለን። እነዚህም (1) ተስፋ ያዘለው መልእክታችን፣ (2) የምናደርገው ፍለጋ ፍሬያማ መሆን እና (3) የመከሩ ሠራተኞች እንደመሆናችን መጠን ሰላማዊ ሰዎች መሆናችን ናቸው።

ለመከር ሥራ የተላኩ

3. የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ደስታ ሊያገኙ የቻሉት በምን ምክንያት ነው?

3 የጥንቶቹ የመከር ሠራተኞች በተለይም አሥራ አንዱ ታማኝ የኢየሱስ ሐዋርያት ትንሣኤ ያገኘውን ክርስቶስን ለማየት በ33 እዘአ ወደ ገሊላ ተራራ በወጡበት ዕለት ሕይወታቸው በእጅጉ ተለውጧል። (ማቴዎስ 28:16) የዚያን ዕለት ‘ከአምስት መቶ የሚበዙ ወንድሞች’ በዚያ ሳይገኙ አልቀሩም። (1 ቆሮንቶስ 15:6) ኢየሱስ የሰጣቸው ተልእኮ ያለማቋረጥ በጆሮአቸው ያቃጭል ነበር። “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) ምንም እንኳ የክርስቶስ ተከታዮች ከባድ ስደት ቢደርስባቸውም በየቦታው ጉባኤዎች ሲቋቋሙ ሲመለከቱ በመከሩ ሥራ እጅግ ተደስተዋል። በጊዜው ‘ምሥራቹ ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ ዘንድ ተሰብኮ ነበር።’​—⁠ቆላስይስ 1:23፤ ሥራ 1:8፤ 16:5

4. የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሰብኩ የተላኩት በምን ሁኔታዎች ሥር ነበር?

4 ኢየሱስ በገሊላ አገልግሎቱን በጀመረበት አካባቢ 12 ሐዋርያቱን ከሰበሰበ በኋላ በተለይ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ እያሉ እንዲያውጁ ላካቸው። (ማቴዎስ 10:1-7) እሱ ራሱም “በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፣ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፣ [በገሊላ] ከተማዎችና መንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር።” ሕዝቡ “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና” ኢየሱስ አዘነላቸው። (ማቴዎስ 9:35, 36) ስሜቱ በጥልቅ በመነካቱ ለደቀ መዛሙርቱ “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” አላቸው። (ማቴዎስ 9:37, 38) ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ለማጠናቀቅ ስድስት ወር ብቻ በቀረው ጊዜ በይሁዳ የመከር ሠራተኞችን አስፈላጊነት በተመለከተ የሰጠው አስተያየትም ተመሳሳይ ነበር። (ሉቃስ 10:2) በሁለቱም ጊዜያት ተከታዮቹን የመከር ሠራተኞች አድርጎ ልኳቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 10:​5፤ ሉቃስ 10:​3

ተስፋ ያዘለው መልእክታችን

5. የምናውጀው ምን ዓይነት መልእክት ነው?

5 ዛሬ እኛ የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የመከር ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ለሚቀርበው ጥሪ በደስታ ምላሽ እንሰጣለን። ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያደርገው አንዱ ትልቁ ምክንያት ለተከዙና ለተጨነቁ ሰዎች ተስፋ ያዘለ መልእክት የምናደርስ መሆናችን ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሁሉ እኛም ‘እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተጥለው’ ለሚገኙ ሰዎች ምሥራች መንገር መቻላችን ምንኛ ታላቅ መብት ነው!

6. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያት በምን ሥራ ተጠምደው ነበር?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን አጋማሽ ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ተጠምዶ ነበር። በ55 እዘአ ገደማ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “ወንድሞች ሆይ፣ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ” በማለት ስለጻፈላቸው ያከናወነው የመከር ሥራ ውጤታማ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። (1 ቆሮንቶስ 15:1) ሐዋርያትም ሆኑ ሌሎች የጥንት ክርስቲያኖች ትጉህ የመከሩ ሠራተኞች ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው ታላቅ ጥፋት በኋላ ምን ያህል ሐዋርያት በሕይወት እንደነበሩ ባይነግረንም እንኳ ከ25 ዓመታት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ በስብከቱ ሥራ ላይ እንደነበረ እናውቃለን።​—⁠ራእይ 1:​9

7, 8. የይሖዋ አገልጋዮች ከምንጊዜውም ይበልጥ በጥድፊያ ስሜት የሚሰብኩት ተስፋ ያዘለ መልእክት ምንድን ነው?

7 ከዚያም ከሃዲው “የዓመፅ ሰው” ማለትም የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ቡድን ለብዙ መቶ ዘመናት በበላይነት ተንሰራፍቶ ቆየ። (2 ተሰሎንቄ 2:​3) ሆኖም በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ሕይወታቸውን በጥንቱ የክርስትና እምነት መሠረት መምራት የፈለጉ ሰዎች መንግሥቱን በማወጅ ይህን ተስፋ ያዘለ መልእክት መናገር ጀመሩ። እንዲያውም የዚህ መጽሔት ርዕስ ገና ከመጀመሪያ እትሙ (ሐምሌ 1879) ጀምሮ “የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ፣” “የክርስቶስ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ” እና “የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ” የሚሉትን ቃላት የሚጨምር ሆነ።

8 በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት በ1914 የተቋቋመ ሲሆን እኛም ይህን ተስፋ ያዘለ መልእክት ከምንጊዜውም ይበልጥ በጥድፊያ ስሜት በማወጅ ላይ እንገኛለን። ለምን? ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት ከሚያመጣቸው በረከቶች አንዱ እጅግ ቀርቦ ያለው የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ነው። (ዳንኤል 2:​44) ከዚህ የተሻለ ምን ዓይነት መልእክት ሊኖር ይችላል? ‘ታላቁ መከራ’ ከመጀመሩ በፊት የአምላክን መንግሥት በማወጁ ሥራ ከመካፈል ይበልጥ ደስታ ሊሰጠን የሚችል ምን ዓይነት ሥራ ሊኖር ይችላል?​—⁠ማቴዎስ 24:​21፤ ማርቆስ 13:​10

የምናደርገው ፍሬያማ የሆነ ፍለጋ

9. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን መመሪያ ሰጠ? ሕዝቡስ ለመንግሥቱ መልእክት የሰጠው ምላሽ ምን ይመስል ነበር?

9 የመከር ሠራተኞች እንደመሆናችን መጠን ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያደርገው ሌላው ነገር ደቀ መዝሙር የሚሆኑና በመከሩ ሥራ ከጎናችን የሚሰለፉ ሰዎች ለማግኘት የምናደርገው ጥረት ስኬታማነት ነው። በ31-32 እዘአ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፣ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ” ሲል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:11) ለመንግሥቱ መልእክት ከሰጡት ምላሽ እንደታየው ምሥራቹ የሚገባቸው ሆነው የተገኙት ሁሉም ሰዎች አልነበሩም። የሆነ ሆኖ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሰዎች በተገኙበት ቦታ ሁሉ ምሥራቹን በቅንዓት መስበካቸውን አላቆሙም።

10. ጳውሎስ የሚገባቸውን ሰዎች መፈለጉን የቀጠለው እንዴት ነበር?

10 ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በኋላም የሚገባቸውን ሰዎች የመፈለጉ ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ መካሄዱን ቀጥሏል። ጳውሎስ በምኩራባቸው ከአይሁዶች እና በአቴንስ በገበያ ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይነጋገር ነበር። በዚህች የግሪክ ከተማ በአርዮስፋጎስ ሲመሰክር “አንዳንዶች ወንዶች . . . ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ።” በተጨማሪም ጳውሎስ በሄደበት ሁሉ ‘በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት በመስበክ’ ረገድ ጥሩ አርአያ ነበር።​—⁠ሥራ 17:17, 34፤ 20:20

11. ከብዙ ዓመታት በፊት አገልግሎቱን ለማከናወን የሚሠራባቸው ዘዴዎች ምን ነበሩ?

11 በ19ኛው መቶ ዘመን በመጨረሻዎቹ አሥርተ ዓመታት ላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ድፍረት በተሞላበት ሁኔታ ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች መፈለግ ጀመሩ። በሐምሌ/ነሐሴ 1881 የወጣው የጽዮን መጠበቂያ ግንብ “ለመስበክ የተቀቡ” በሚል ርዕስ እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “ከእነርሱ መካከል የክርስቶስ አካል የሚሆኑ ተባባሪ ወራሾች ለማግኘት ሲባል የምሥራቹ ስብከት . . . ‘የዋህ ለሆኑ ሰዎች’ ማለትም ፈቃደኛ ሆነው ለመስማት ጆሮአቸውን ለሚሰጡ ሰዎች በመድረስ ላይ ነው።” የአምላክ የመከር ሠራተኞች ምሥራቹ የሚገባቸው ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ ለመቀስቀስ ታስቦ የተዘጋጀውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክት የያዘ ትራክት ከቤተ ክርስቲያን የሚመለሱ ሰዎችን እየጠበቁ ያድሉ ነበር። ይህ ዘዴ ውጤታማ መሆኑ ከታየ በኋላ የግንቦት 15, 1903 መጠበቂያ ግንብ የመከሩ ሠራተኞች ይህን ትራክት “እሁድ ረፋዱ ላይ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ እንዲያሰራጩ አጥብቆ አሳስቧል።”

12. የስብከት ሥራችንን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ የቻልነው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

12 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሰዎችን ቤታቸው ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቦታዎችም በማነጋገር የአገልግሎት አድማሳችንን አስፍተናል። ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ባላቸውና ብዙውን ጊዜ እቤታቸው ስንሄድ ለመዝናናት የሚወጡ ሰዎች በሚበዙባቸው አገሮች ይህ ዘዴ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል። በእንግሊዝ የምትገኝ አንዲት ምሥክርና ጓደኛዋ ሰዎች በባሕሩ ዳርቻ ሲዝናኑ ከዋሉ በኋላ በአውቶቡስ ተሳፍረው እንደሚሄዱ አስተዋሉ። ከዚያም አውቶቡሶቹ ላይ በመሳፈር መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ለማበርከት ተደፋፈሩ። በአንድ ወር ውስጥ 229 ቅጂዎች አሰራጭተዋል። “ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን እንዳለ ስለምናውቅ በባሕር ዳርቻዎች፣ በንግድ አካባቢዎች ወይም በሌሎች አስቸጋሪ ቦታዎች መስበክ ፈጽሞ አያስፈራንም” ሲሉ ሪፖርት አድርገዋል። የመጽሔት ደንበኛ ማፍራትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ከመቻላቸውም በላይ ሁለቱም በረዳት አቅኚነት ተካፍለዋል።

13. በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎታችንን በተመለከተ ምን ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጓል?

13 ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች የመፈለጉ ሥራ በቀጠለ መጠን በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎታችንን በተመለከተ ጥንቃቄ የተሞላበት አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ምንም እንኳ ብዙዎቹ ምሥክሮች በአብዛኛው ከቤት ወደ ቤት የሚመሰክሩት እሁድ ጠዋት ላይ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎቹ ተኝተው ሊያረፍዱ ስለሚችሉ ማለዳ ከቤት ወደ ቤት መሄዱን ውጤታማ ሆኖ አላገኙትም። በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ምሥክሮች ከጠዋት ይልቅ በቀኑ ውስጥ በሌላ ሰዓት ላይ ምናልባትም ከጉባኤ ስብሰባዎች በኋላ ለመሄድ ፕሮግራማቸውን በማስተካከል ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች መፈለጋቸውን ቀጥለዋል። ይህ በእርግጥም ፍሬያማ ሆኖ ተገኝቷል። ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር በ2.3 በመቶ ጨምሯል። ይህም ለመከሩ ጌታ ክብር ለእኛም ደስታ ያመጣል።

በመከሩ ሥራ ሰላምን መከታተል

14. መልእክታችንን ለሰዎች የምናደርሰው በምን ዓይነት መንፈስ ነው? ለምንስ?

14 ሌላው ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያደርገው በመከሩ ሥራ ሰላምን የምንከተል መሆናችን ነው። ኢየሱስ “ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 10:12, 13) የዕብራይስጡ ሰላምታም ሆነ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ግሪክኛ አነጋገር ‘ጤና ይስጥልኝ’ የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ። ምሥራቹን በምንሰብክበት ጊዜ በምን ዓይነት መንፈስ ሰዎችን መቅረብ እንዳለብን ይህ ጥሩ መመሪያ ይሰጠናል። ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ለመልእክቱ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ከኃጢአታቸው ንስሐ በመግባት፣ በመመለስና ፈቃዱን በማድረግ ከአምላክ ጋር የመታረቅ አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል። ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠራቸው ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያስገኝላቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 17:​3፤ ሥራ 3:​19፤ 13:​38, 48፤ 2 ቆሮንቶስ 5:​18-20

15. በስብከት ሥራችን አዎንታዊ ያልሆነ ምላሽ በሚያጋጥመን ጊዜ ሰላማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ሰዎች አዎንታዊ ያልሆነ ምላሽ በሚሰጡበት ጊዜ ሰላማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “[ቤቱ] ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ” በማለት መመሪያ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 10:13) ሰባዎቹ ደቀ መዛሙርት እንዲሰብኩ ስለመላካቸው የሚናገረው የሉቃስ ዘገባ “በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፣ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል” የሚለውን የኢየሱስ አነጋገርም የያዘ ነው። (ሉቃስ 10:6) ምሥራቹን ለሰዎች ስናደርስ በጥሩ ወዳጃዊ መንፈስና ሰላማዊ መሆናችንን በሚያንጸባርቅ ሁኔታ መቅረባችን ተገቢ ነው። የቤቱ ባለቤት የሚያሳየው የግዴለሽነት ስሜት፣ የሚያሰማው ተቃውሞ ወይም የሚሰነዝረው ስድብ የሚያስከትለው ነገር ቢኖር ሰላማዊ መልእክታችን ‘ወደ እኛ እንዲመለስ’ ማድረግ ብቻ ነው። ከእነዚህ ውስጥ የትኛውም ቢሆን የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ የሆነውን ሰላማችንን ሊሰርቅብን አይችልም።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23

የመከር ሠራተኞች ያላቸው ግሩም ግብ

16, 17. (ሀ) ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ ግባችን ምንድን ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች ያሏቸውን ሰዎች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

16 የመከር ሠራተኞች እንደመሆናችን መጠን ሰዎችን ለዘላለም ሕይወት በመሰብሰቡ ሥራ የመካፈል መብት በማግኘታችን ደስተኞች ነን። እንዲሁም የመሰከርንለት ሰው ጥሩ ምላሽ ሲሰጥ፣ የበለጠ ለማወቅ ሲፈልግና “የሰላም ልጅ” መሆኑን ሲያሳይ ምንኛ ደስ ይለናል! ምናልባትም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች ይኖሩትና በአንድ ጉብኝት ብቻ ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ መስጠት አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። በመጀመሪያው ጉብኝት ወቅት ረጅም ሰዓት መቆየት ተገቢ ላይሆን ስለሚችል ምን ብናደርግ የተሻለ ሊሆን ይችላል? ከ60 ዓመታት ገደማ በፊት ከተሰጠ አንድ አስተያየት ጋር የሚመሳሰል ግብ ልንይዝ እንችላለን።

17 “ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ሞዴል ስተዲስ በተባሉት ቡክሌቶች አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል።” ይህ መግለጫ የወጣው ከ1937 እስከ 1941 በታተሙት ሞዴል ስተዲ በተባሉት ተከታታይ ቡክሌቶች መካከል በሦስተኛው እትም ላይ ነው። እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ሁሉም [የመንግሥቱ] አስፋፊዎች በተቻላቸው አቅም ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት የሚያሳዩትን በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በመርዳት ረገድ ትጉዎች መሆን አለባቸው። እነዚህ ሰዎች በተቻለ ፍጥነት ተመላልሶ መጠየቅ ሊደረግላቸውና ጥያቄዎቻቸው ሁሉ ሊመለሱላቸው . . . እንዲሁም ሞዴል ስተዲ በተባለው ቡክሌት ጥናት ሊጀመርላቸው ይገባል።” አዎን፣ ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግበት ዋነኛው ግብ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርና ዘወትር መምራት ነው። a ፍላጎት ላሳየው ሰው ያለን ወዳጃዊ ስሜትና ፍቅራዊ አሳቢነት ጥሩ አድርገን እንድንዘጋጅና ጥናቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድንመራ ይገፋፋናል።

18. አዲሶች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

18 ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍና አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? እንደተባለው ባሉ ብሮሹሮች አማካኝነት ውጤታማ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራትና ፍላጎት ያሳዩ አዲሶች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በመርዳቱ ሥራ መካፈል እንችላለን። በተጨማሪም ታላቁን አስተማሪ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል በምናደርገው ጥረት እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሰላማዊ፣ ደስተኛና ቅን የሆነውን ባሕርያችንን እንዲሁም ይሖዋ ላወጣቸው የአቋም ደረጃዎችና መመሪያዎች ያለንን አክብሮት በመመልከትም ትምህርት ሊቀስሙ ይችላሉ። ለጥያቄዎቻቸው መልስ በመስጠት አዲሶችን በምንረዳበት ጊዜ እግረ መንገዳችንን እነሱም ሲጠየቁ እንዴት ብለው መመለስ እንደሚችሉ ለማስተማር እንጣር። (2 ጢሞቴዎስ 2:​1, 2፤ 1 ጴጥሮስ 2:​21) ምሳሌያዊ የመከር ሠራተኞች እንደመሆናችን መጠን ባለፈው የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ 4, 766, 631 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመመራታቸው እንደምንደሰት ምንም ጥርጥር የለውም። በተለይ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራቱ ሥራ ከሚካፈሉት የመከር ሠራተኞች መካከል እኛም የምንገኝ ከሆን ደስታችን እጥፍ ድርብ ይሆናል።

በመከሩ መደሰታችሁን ቀጥሉ

19. በኢየሱስ አገልግሎት ወቅትም ሆነ ከዚያ ጥቂት ቆየት ብሎ ባሉት ጊዜያት በመከሩ ለመደሰት የሚያበቁ ምን ጥሩ ምክንያቶች ነበሩ?

19 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅትም ይሁን ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ በመከሩ ሥራ ለመደሰት የሚያበቁ ጥሩ ምክንያቶች ነበሩ። በዚያን ወቅት ብዙዎች ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። በተለይ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት 3, 000 የሚያክሉ ሰዎች ጴጥሮስ የሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግና የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ በመቀበል የአምላክ ብሔር መንፈሳዊ እስራኤል አባላት በሆኑበት ወቅት የነበረው ደስታ እጅግ ከፍ ያለ ነበር። “ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር” ስለነበር ቁጥራቸው በየጊዜው እያደገ መሄዱን የቀጠለ ሲሆን ይህም ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንዲሆን አድርጎታል።​—⁠ሥራ 2:37-41, 46, 47፤ ገላትያ 6:16፤ 1 ጴጥሮስ 2:9

20. በመከር ሥራችን ይህ ነው የማይባል ደስታ እንድናገኝ የሚያደርገን ምንድን ነው?

20 በዚያን ወቅት የሚከተለው የኢሳይያስ ትንቢት እውነት መሆኑ ተረጋግጧል:- “[ይሖዋ] ሕዝብን አብዝተሃል፣ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፣ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል።” (ኢሳይያስ 9:3) ምንም እንኳ አሁን የቅቡዓኑ ‘ሕዝብ መብዛቱ’ ሙሉ በሙሉ ያቆመ ቢሆንም የሌሎቹ የመከር ሠራተኞች ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መሄዱን መመልከታችን ይህ ነው የማይባል ደስታ ያመጣልናል።​—⁠መዝሙር 4:​7፤ ዘካርያስ 8:​23፤ ዮሐንስ 10:​16

21. በሚቀጥለው ርዕስ የምንመረምረው ምንድን ነው?

21 በእርግጥም በመከሩ ሥራ መደሰታችንን እንድንቀጥል የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለን። ተስፋ ያዘለው መልእክታችን፣ ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች ለማግኘት የምናደርገው ፍለጋ እና ሰላማዊ ሰዎች መሆናችን እንደ መከር ሠራተኝነታችን መጠን ከፍተኛ ደስታ ያመጡልናል። ሆኖም እነዚህ ነገሮች የብዙዎችን ተቃውሞ ሊያስነሱብን ይችላሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ ይህ ሁኔታ አጋጥሞታል። ‘ስለ እግዚአብሔር በመናገሩና ስለ ኢየሱስ በመመስከሩ’ ምክንያት ፍጥሞ በምትባል ደሴት ታስሯል። (ራእይ 1:​9) ታዲያ ስደትና ተቃውሞ ሲያጋጥመን ደስታችንን ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው? በአሁኑ ጊዜ የምንሰብክላቸው ሰዎች የሚያሳዩትን የልበ ደንዳንነት ዝንባሌ በጽናት እንድንቋቋም የሚረዳን ምንድን ነው? የሚቀጥለው ርዕሳችን ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን ያካፍለናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ቀደም ሲል ጥናት ለመምራት ዝግጅት ይደረግ የነበረው የተወሰኑ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አንድ ላይ በሚሰበሰቡበት ቦታ ነበር። በኋላ ግን ግለሰቦችንና ቤተሰቦችን ማስጠናት ተጀመረ።​—⁠የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን መጽሐፍ ገጽ 574 ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ምሳሌያዊው የመከር ሥራ ምንድን ነው?

• የምናውጀው ምን ዓይነት መልእክት ነው?

• ደቀ መዛሙርት ለማፍራት የምናደርገው ፍለጋ ስኬታማ የሆነው ለምንድን ነው?

• በመከሩ ሥራ ሰላማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

• በመከሩ ሥራ መደሰታችንን የምንቀጥለው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስብከቱ ሥራ በመጀመሪያውና በ20ኛው መቶ ዘመን

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ጳውሎስ ሁሉ ዛሬ ያሉ የመከሩ ሠራተኞችም በማንኛውም ቦታ ሰዎችን አግኝተው ለማነጋገር ይጥራሉ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥሩ የወዳጅነት መንፈስ በማሳየት ምሥራቹን አውጅ