በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ጻድቅ በረከት ያገኛል’

‘ጻድቅ በረከት ያገኛል’

‘ጻድቅ በረከት ያገኛል’

መዝሙራዊው ዳዊት በስተርጅናው “ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 37:​25) ይሖዋ አምላክ ጻድቃንን የሚወዳቸው ከመሆኑም በላይ በጣም ያስብላቸዋል። እውነተኛ አምላኪዎች ጽድቅን እንዲፈልጉ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጥብቅ አሳስቧቸዋል።​—⁠ሶፎንያስ 2:​3

ጽድቅ ማለት አምላክ መልካምና ክፉ ስለሆነው ነገር ካወጣው መስፈርት ጋር በሚስማማ መንገድ በትክክል መኖር ማለት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ 10ኛ ምዕራፍ ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እንድንኖር ሲያበረታታን እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች የሚያገኙትን የተትረፈረፉ መንፈሳዊ በረከቶች ይጠቅሳል። ከእነዚህ በረከቶች መካከል በመንፈሳዊ የሚገነባ የተትረፈረፈ ምግብ፣ መልሶ የሚክስ አርኪ ሥራ እንዲሁም ከአምላክም ሆነ ከሰው ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ይገኙበታል። እንግዲያው ምሳሌ ምዕራፍ 10:​1-14ን እንመርምር።

ግሩም ማበረታቻ

“የሰሎሞን ምሳሌዎች ” የሚሉት የዚህ ምዕራፍ የመክፈቻ ቃላት ቀጣዩን የምሳሌ መጽሐፍ ክፍል ጸሐፊ ማንነት በተመለከተ አንዳችም ጥርጣሬ እንዳያድርብን ያደርጋል። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ቀናውን መንገድ መከተል የሚያስችል ግሩም ማበረታቻ ሲሰጥ “ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን ለእናቱ ኀዘን ነው” ብሏል።​—⁠ምሳሌ 10:​1

ወላጆች ከልጆቻቸው መካከል አንዱ የእውነተኛውንና ሕያው የሆነውን አምላክ አምልኮ ሲተው ማየታቸው ምንኛ ያሳዝናቸዋል! ጠቢቡ ንጉሥ እናት የሚሰማትን ሃዘን ለይቶ የጠቀሰው ሃዘኑ በእርሷ ላይ እንደሚብስ ለመጠቆም ሳይሆን አይቀርም። በዶሪስ ላይ የደረሰው ሁኔታ የዚህን እውነተኝነት ያረጋግጣል። a “የ21 ዓመት ወንድ ልጃችን በእውነት ቤት መመላለሱን ሲያቆም እኔና ባለቤቴ ፍራንክ ልባችን በሃዘን ተሰብሮ ነበር። የስሜት ስቃዩ ከፍራንክ ይልቅ በእኔ ላይ አይሎ ነበር። አሥራ ሁለት ዓመት አልፎ እንኳ ቁስሉ ሊሽር አልቻለም” በማለት ትናገራለች።

ልጆች አባታቸውን ደስታ ሊያሳጡ እናታቸውን ሊያሳዝኑ ይችላሉ። ጥበበኛ በመሆን ወላጆቻችንን የምናስደስት እንሁን። እንዲሁም ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰማዩ አባታችንን የይሖዋን ልብ ደስ የምናሰኝ እንሁን።

‘የጻድቁን ነፍስ ያጠግባል’

ንጉሡ “በኃጢአት የተገኘ መዝገብ ጥቅም የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ያድናል” ይላል። (ምሳሌ 10:​2) ወደ መጨረሻው ዘመን ጠልቀው ለገቡ እውነተኛ ክርስቲያኖች እነዚህ ቃላት በእርግጥም የላቀ ትርጉም አላቸው። (ዳንኤል 12:​4) ከአምላክ የራቀው የዚህ ዓለም ጥፋት ቀርቧል። ቁሳዊ ንብረት፣ ገንዘብ ወይም ወታደራዊ ደህንነትን የመሳሰሉ ሰዎች የሚመኩባቸው ነገሮች ከመጪው “ታላቅ መከራ” መከታ ሊሆኑ አይችሉም። (ራእይ 7:​9, 10, 13, 14) “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና።” (ምሳሌ 2:​21) እንግዲያው ‘የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋችንን’ እንቀጥል።​—⁠ማቴዎስ 6:​33

የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክን በረከቶች ለማግኘት ቃል የተገባው አዲስ ዓለም እስኪመጣ መጠበቅ አያስፈልጋቸውም። “እግዚአብሔር የጻድቁን ነፍስ አያስርብም፤ የኀጥኣንን ምኞት ግን ይገለብጣል።” (ምሳሌ 10:​3) ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አቅርቧል። (ማቴዎስ 24:​45) ጻድቅ ‘ከልቡ ደስታ የተነሣ እንዲዘምር’ የሚያደርጉ በቂ ምክንያቶች አሉት። (ኢሳይያስ 65:​14) እውቀት ነፍሱን ያረካለታል። መንፈሳዊ ሃብት ለማግኘት በሚያደርገው ፍለጋ ይደሰታል። ክፉ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ደስታ አግኝቶ አያውቅም።

‘ትጋት ባለጠጋ ታደርጋለች’

ጻድቅ ሰው በሌላም መንገድ ይባረካል። “የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች። በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል። ”​—⁠ምሳሌ 10:​4, 5

ንጉሡ በመከር ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሠራተኞች የተናገራቸው ቃላት ይበልጥ ትርጉም አላቸው። የመከር ወቅት ያለ ሐሳብ የሚተኛበት ጊዜ አይደለም። ረጅም ሰዓት ተግቶ የሚሠራበት ወቅት ነው። በእርግጥም የጥድፊያ ጊዜ ነው።

ኢየሱስ እህል የሚሰበሰብበትን የመከር ወቅት ሳይሆን ሰዎች የሚሰበሰቡበትን ጊዜ በአእምሮው በመያዝ ደቀ መዛሙርቱን “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ [ይሖዋ አምላክ] ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው።” (ማቴዎስ 9:​35-38) በ2000 ዓመት ከ14 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ይኸውም የይሖዋ ምሥክሮችን በሁለት እጥፍ የሚበልጡ ሰዎች በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል። ታዲያ ‘አዝመራው ነጥቶ ለአጨዳ መድረሱን’ ማን ሊክድ ይችላል? (ዮሐንስ 4:​35) እውነተኛ አምላኪዎች ከጸሎታቸው ጋር በሚስማማ መንገድ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ በትጋት እየተካፈሉ የመከሩ ጌታ ተጨማሪ ሠራተኞች እንዲልክ ይለምናሉ። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ይሖዋ ጥረታቸውን ምንኛ ባርኮላቸዋል! በ2000 የአገልግሎት ዓመት ከ280, 000 የሚበልጡ አዳዲስ ሰዎች ተጠምቀዋል። እነዚህም በበኩላቸው የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ። ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በሙሉ አቅማችን በመካፈል በዚህ የመከር ወቅት ደስታና እርካታ እናግኝ።

“በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው”

ሰሎሞን ቀጥሎ “በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፤ የኀጥኣንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል” ይላል።​—⁠ምሳሌ 10:​6

ልቡ ንጹሕና ጻድቅ የሆነ ሰው ጻድቅ መሆኑ በግልጽ ይታያል። አነጋገሩ ደግነት የተሞላበትና የሚያንጽ ሲሆን የሚያደርገው ነገር ሁሉ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ ለጋስነቱን የሚያሳይ ነው። ሌሎች ከእሱ ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። እንዲህ ያለ ሰው በመልካም ስለሚያነሱት የእነርሱን አድናቆት ወይም በሌላ አባባል በረከት ያተርፋል።

በሌላ በኩል ክፉ ሰው ጥላቻን የተሞላ ወይም ተንኮለኛ ሲሆን ሌሎችን ለመጉዳት ታጥቆ የተነሳ ነው። ምላሱን በማጣፈጥ በልቡ ያዘለውን ‘ክፋት መሸፈን’ ይችል ይሆናል፤ ሆኖም ውሎ አድሮ ሌሎችን በአካልም ሆነ በቃላት መተንኮስ ይጀምራል። (ማቴዎስ 12:​34, 35) ወይም በሌላ በኩል “የኀጥኣንን አፍ ግፍ ይከድነዋል [ወይም ይዘጋዋል]።” (ምሳሌ 10:​6) ይህ እንደሚያመለክተው ክፉ ሰው ብዙውን ጊዜ የእጁን ያገኛል ይኸውም ጥላቻን ያተርፋል። ይህ አፉን ስለሚከድነው ወይም ስለሚዘጋው ዝም ያሰኘዋል። እንዲህ ያለው ሰው ከሌሎች በረከትን እንዴት ሊጠብቅ ይችላል?

የእስራኤል ንጉሥ “የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፤ የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 10:​7) ጻድቅ ሰው ሌሎች በተለይ ደግሞ በይሖዋ አምላክ ዘንድ በበጎ ይታወሳል። ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆኑ ከመላእክት ይልቅ “እጅግ የሚበልጥ ስምን” ወርሷል። (ዕብራውያን 1:​3, 4) በቅድመ ክርስትና የነበሩ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ዛሬ እውነተኛ ክርስቲያኖች በምሳሌነት ያስታውሷቸዋል። (ዕብራውያን 12:​1, 2) ይህ ሁኔታ ጸያፍና ወራዳ ስም ካተረፉ ክፉ ሰዎች ምንኛ የተለየ ነው! አዎን፣ “መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት ይሻላል፣ መልካምም ሞገስ ከብርና ከወርቅ ይበልጣል።” (ምሳሌ 22:​1) በይሖዋና በሌሎች ሰዎች ዘንድ መልካም ስም እናትርፍ።

“ያለ ነውር የሚሄድ ተማምኖ ይሄዳል”

ሰሎሞን ጠቢብንና ሞኝን ሲያነጻጽር “በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፤ በከንፈሩ የሚሰንፍ ግን ይወድቃል” ብሏል። (ምሳሌ 10:​8) ‘ሰው በራሱ አካሄዱን አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል’ ጠቢብ የሆነ ሰው ጠንቅቆ ያውቃል። (ኤርምያስ 10:​23) የይሖዋን መመሪያ ማግኘት እንደሚያስፈልገው የሚገነዘብ ሲሆን የአምላክን ትእዛዛት ለመቀበል ፈጣን ነው። በሌላ በኩል በከንፈሩ ሰነፍ የሆነ ሰው ይህን መሠረታዊ ሃቅ መረዳት ይከብደዋል። ከንቱ ልፍለፋው ለጥፋት ይዳርገዋል።

በተጨማሪም ጻድቅ ሰው ክፉዎች የሌላቸው የተረጋጋ ሕይወት ይኖረዋል። “ያለ ነውር የሚሄድ ተማምኖ ይሄዳል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል። በዓይኑ የሚጠቅስ መከራን ያመጣል፤ ደፍሮ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል።”​—⁠ምሳሌ 10:​9, 10

ያለ ነውር የሚሄድ ሰው ሥራዎቹን ሁሉ በሃቀኝነት ያከናውናል። የሌሎችን አክብሮትና አመኔታ ያተርፋል። ሃቀኛ ሰው በጣም ተፈላጊ ሠራተኛ ሲሆን ብዙውን ጊዜም ከፍ ያለ የኃላፊነት ቦታ ይሰጠዋል። በሃቀኝነት በመመላለስ ያተረፈው መልካም ስም ሥራ በቀላሉ በማይገኝበት ጊዜ እንኳ ከሥራ የመባረርም ሆነ ሥራ ፈልጎ የማጣት ዕጣ አይገጥመውም። ከሁሉም በላይ ታማኝነቱ አስደሳችና ሰላማዊ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖረው አስተዋጽኦ ያደርግለታል። (መዝሙር 34:​13, 14) ከቤተሰቡ አባላት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ይኖረዋል። በእርግጥም ያለ ነውር መመላለስ የተረጋጋ ሕይወት መምራት ያስችላል።

ይህም በራስ ወዳድነት ጥቅም ለማግኘት ሲል እምነት የማጉደል ድርጊት የተለየ ነው። አታላይ ሰው ውሸቱን በጠማማ አነጋገር ወይም በሰውነት እንቅስቃሴው ለመሸፈን ጥረት ያደርግ ይሆናል። (ምሳሌ 6:​12-14) ተንኮል ባዘለ ሁኔታ ወይም ለማታለል ሲል በዓይኑ ሲጠቅስ የጥቃት ሰለባው ላይ የአእምሮ ጭንቀት ይፈጥርበታል። ሆኖም ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ የዚህ ሰው ጠማማነት ይጋለጣል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው ፍርድንም ያመለክታል፣ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል፤ እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው፣ ያልተገለጠም ከሆነ ሊሰወር አይችልም” በማለት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​24, 25) ይህን ያደረገው ወላጅም ይሁን ወዳጅ ወይም የትዳር ጓደኛ አሊያም የምናውቀው ሌላ ሰው እምነት ማጉደሉ አንድ ቀን ይፋ መውጣቱ አይቀርም። እምነት በማጉደል መጥፎ ስም ያተረፈን ሰው ማን ያምነዋል?

‘አፉ የሕይወት ምንጭ ነው’

ሰሎሞን “የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ናት፤ የኀጥኣንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል” ይላል። (ምሳሌ 10:​11) ከአፍ የሚወጣ ቃል ሊፈውስ ወይም ሊያቆስል ይችላል። ቃላት አንድን ሰው ሊያነቃቁ እንዲሁም ሊያድሱ ወይም ቅስሙን ሊሰብሩ ይችላሉ።

የእስራኤል ንጉሥ አንድ ሰው እነዚያን ቃላት እንዲናገር ሊያደርጉት የሚችሉትን ምክንያቶች ሲጠቅስ “ጥል ክርክርን ታስነሣለች፤ ፍቅር ግን ኃጢአትን ሁሉ ትከድናለች ” ይላል። (ምሳሌ 10:​12) ጥላቻ በሰዎች መካከል አለመስማማት እንዲፈጠር በማድረግ አምባጓሮ እንዲነሳ ያደርጋል። ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ከሕይወታቸው ውስጥ ጥላቻን ማስወገድ ይገባቸዋል። እንዴት? በፍቅር በመተካት ነው። “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።” (1 ጴጥሮስ 4:​8) ፍቅር “ሁሉን ነገር ችሎ ያልፋል” ማለትም “ሁሉን ነገር ይሸፍናል።” (1 ቆሮንቶስ 13:​7 ኪንግደም ኢንተርሊኒየር ) አምላካዊ ፍቅር ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ፍጽምናን እንዲያሳዩ አይጠብቅም። እንደዚህ ያለው ፍቅር ከባድ ኃጢአት እስካልተፈጸመ ድረስ ሌሎች የሠሩትን ስህተት ከማውራት ይልቅ ስህተታቸውን ችላ ብለን እንድናልፈው ይረዳናል። ፍቅር ሌላው ቀርቶ በመስክ አገልግሎት፣ ተቀጥረን በምንሠራበት ቦታ ወይም በትምህርት ቤት የሚፈጸመውን በደል ችሎ ያልፋል።

ጠቢቡ ንጉሥ ቀጥሎ “በብልሃተኛ ከንፈር ጥበብ ትገኛለች፤ በትር ግን አእምሮ ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው” ይላል። (ምሳሌ 10:​13) የአስተዋይ ሰው ጥበብ መንገዱን ያቀናለታል። ከአፉ የሚወጡት የሚያንጹ ቃላት ሌሎች በጽድቅ መንገድ ላይ እንዲጓዙ ይረዳቸዋል። እሱም ሆነ እሱን የሚያዳምጡ ሌሎች ሰዎች ትክክለኛውን አቅጣጫ እንዲከተሉ ኃይል ወይም በትር አያስፈልጋቸውም።

“እውቀትን ይሸሽጋሉ”

ቃላችን ፍሬከርስኪ ወሬ የሞላበት ጅረት ከመሆን ይልቅ ‘ጥበብ የሚፈልቅበት ፈሳሽ ወንዝ’ እንዲሆን ምን ሊረዳን ይችላል? (ምሳሌ 18:​4) ሰሎሞን “ጠቢባን እውቀትን ይሸሽጋሉ፤ የሰነፍ አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል” የሚል መልስ ይሰጣል።​—⁠ምሳሌ 10:​14

የመጀመሪያው ብቃት አእምሯችንን በአምላክ የሚያንጽ እውቀት መሙላት ነው። ይህን እውቀት ማግኘት የሚቻልበት ምንጩ አንድ ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) ተሰውሮ የነበረን ውድ ሃብት እንደሚፈልግ ሰው እውቀትን ለማግኘት መጣጣርና የአምላክን ቃል መቆፈር ይገባናል። እንዲህ ያለው ፍለጋ ምንኛ አስደሳችና መልሶ የሚክስ ነው!

ከከንፈራችን ጥበብ እንዲፈልቅ ከተፈለገ ከቅዱሳን ጽሑፎች የምናገኘው እውቀት ልባችንን ሊነካው ይገባል። ኢየሱስ ለአድማጮቹ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፣ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል” ሲል ነግሯቸው ነበር። (ሉቃስ 6:​45) ስለሆነም በምንማራቸው ነገሮች ላይ የማሰላሰል ልማድ ሊኖረን ይገባል። ጥናትና ማሰላሰል ጥረት የሚጠይቁ መሆናቸው እውነት ነው፤ ሆኖም እንደዚህ ያለው ጥናት በመንፈሳዊ ምንኛ የሚገነባ ነው! ማንም ቢሆን እንዳመጣለት የሚናገርን ለፍላፊ ሰው የጥፋት መንገድ የሚከተልበት ምክንያት የለም።

አዎን፣ ጠቢብ ሰው በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን የሚያደርግ ሲሆን በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ተትረፍርፎ የቀረበለትን መንፈሳዊ ምግብ የሚመገብ ሲሆን በረከት በሚያስገኘው የጌታ ሥራ ብዙ የሚሠራቸው ነገሮች አሉት። (1 ቆሮንቶስ 15:​58) ታማኝነቱን ጠብቆ የሚኖር ሰው ያለ ስጋት ይሄዳል እንዲሁም የአምላክ ሞገስ አለው። በእርግጥም ጻድቅ ሰው የሚያገኛቸው በረከቶች ብዙ ናቸው። አምላክ መልካም እና ክፉ ለሆነው ነገር ካወጣው መስፈርት ጋር ተስማምተን በመኖር ጽድቅን እንፈልግ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄ]

a ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታማኝነት ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ለመመሥረት ያስችላል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ጠቢባን እውቀትን ሸሽገው ይይዛሉ ’