በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለእድገትህ እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን አሸንፍ!

ለእድገትህ እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን አሸንፍ!

ለእድገትህ እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን አሸንፍ!

የመኪናህ ማርሽ ገብቷል፣ ሞተሩም እየሠራ ነው። ሆኖም መኪናህ ወደፊት መንቀሳቀስ አልቻለም። ሞተሩ ችግር ይኖረው ይሆን? አይደለም። አንድ ትልቅ ድንጋይ በአንደኛው የመኪና ጎማ ሥር ተቀርቅሮ ይዞታል። መኪናው ወደፊት እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ያለው አማራጭ ድንጋዩን ማንሳት ብቻ ነው።

በተመሳሳይም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እያጠኑ ያሉ አንዳንድ ሰዎች መንፈሳዊ እድገት እንዳያደርጉ እንቅፋት የሆኑባቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል “የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል” የመሳሰሉ ነገሮች የእውነትን ‘ቃል አንቀው’ ሊይዙና እድገትን ሊያቀጭጩ እንደሚችሉ ኢየሱስ አስጠንቅቋል።​—⁠ማቴዎስ 13:​22

ሌሎች ደግሞ ሥር የሰደዱ ልማዶች ወይም ድክመቶች እድገት እንዳያደርጉ ያግዳቸዋል። ዩታካ የተባለ አንድ ጃፓናዊ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ያስደሰተው ቢሆንም እንኳ ቁማር የመጫወት ሱስ ነበረበት። ይህን መጥፎ ልማድ ለማሸነፍ ብዙ ጊዜ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ሊሳካለት አልቻለም። ይህ መጥፎ ሱስ ጥሪቱን፣ ሦስት ቤቶችን፣ የቤተሰቡን አክብሮት፣ እንዲሁም ለራሱ የነበረውን ክብር አሳጥቶታል። ታዲያ ይህ ሰው የተጋረጠበትን እንቅፋት አስወግዶ ክርስቲያን መሆን ይችል ይሆን?

ወይም ደግሞ ኬኮ የተባለችን የአንዲት ሴት ሁኔታ ተመልከት። በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ ከጣዖት አምልኮ፣ ከሥነ ምግባር ብልግና፣ ከጥንቆላና እነዚህን ከመሰሉ መጥፎ ምግባሮች ርቃለች። ይሁን እንጂ ኬኮ “ለእኔ ትልቅ እንቅፋት የሆነብኝ ማጨስ ነበር። ለማቆም ብዙ ጊዜ የሞከርኩ ቢሆንም አልተሳካልኝም” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች።

አንተም በተመሳሳይ ለእድገትህ ማነቆ የሆነ የሚወገድ የማይመስል እንቅፋት ይኖርብህ ይሆናል። እንቅፋቱ ምንም ይሁን ምን በአምላክ እርዳታ ልታሸንፈው እንደምትችል እርግጠኛ ሁን።

ደቀ መዛሙርቱ የሚጥል በሽታ ከነበረበት አንድ ሰው ጋኔን ማውጣት ባቃታቸው ጊዜ ኢየሱስ የሰጣቸውን ምክር አስታውስ። ኢየሱስ እነርሱ ያቃታቸውን ጋኔን ካወጣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ተራራ:- ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም” አላቸው። (ማቴዎስ 17:​14-20፤ ማርቆስ 9:​17-29) አዎን፣ ለእኛ የተራራ ያህል ገዝፎ የሚታየን አንድ ችግር ከሁሉ በላይ ኃያል ለሆነው ፈጣሪያችን ኢምንትና ከቁጥር የማይገባ ነው።​—⁠ዘፍጥረት 18:​14፤ ማርቆስ 10:​27

ለእድገት እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ለይቶ ማወቅ

እንቅፋት የሆኑብህን ነገሮች ለማስወገድ ከመነሳትህ በፊት እንቅፋቶቹ ምን እንደሆኑ ለይተህ ማወቅ ይገባሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ የሚገኝ ሽማግሌ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናህ ሰው አንድ ጉዳይ ጠቆም ሊያደርግህ ይችላል። እንዲህ ያለ ፍቅራዊ ምክር ስለተሰጠህ ቅር ከመሰኘት ይልቅ በትህትና ‘ምክሩን ተቀብለህ ጠቢብ መሆን’ ይገባሃል። (ምሳሌ 8:​33 NW ) በሌሎች ጊዜያት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ አማካኝነት ድክመቶችህን ትገነዘብ ይሆናል። አዎን፣ የአምላክ ቃል ‘ሕያውና የሚሠራ’ ነው። (ዕብራውያን 4:​12) መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ማንበብ ውስጣዊ ሐሳብህን፣ ስሜትህንና ምኞትህን እንድትገነዘብ ሊያደርግህ ይችላሉ። ይሖዋ ባወጣቸው ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች መሠረት ራስህን እንድትመረምር ይረዳሃል። መንፈሳዊ እድገት እንዳታደርግ እንቅፋት የሆኑብህ ነገሮች ግልጥ ሆነው እንዲታዩህ ይረዳሃል።​—⁠ያዕቆብ 1:​23-25

ለምሳሌ ያህል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የጾታ ብልግና ቅዠቶችን በአእምሮው የማውጠንጠን ልማድ አለው እንበል። ምንም የተሳሳተ ነገር እንዳልፈጸመ አድርጎ በማሰብ እንዲህ ማድረጉ ጉዳት እንዳለው ሆኖ አልታየው ይሆናል። በጥናቱ እየገፋ ሲሄድ ግን “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች” የሚሉትን በያዕቆብ 1:​14, 15 ላይ የሚገኙትን ቃላት ያነብባል። አሁን በዚህ ልማድ መቀጠሉ ለእድገቱ ከፍተኛ ጠንቅ እንደሆነበት ይገነዘባል! ይህን እንቅፋት እንዴት ማስወገድ ይችላል?​—⁠ማርቆስ 7:​21-23

እንቅፋቶችን ማሸነፍ

ምናልባት አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን በሚያደርግለት እርዳታ ተማሪው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ ተጠቅሞ በአምላክ ቃል ላይ ተጨማሪ ምርምር ያደርግ ይሆናል። a ለምሳሌ ያህል “Thoughts” (ሐሳቦች) የሚለው ርዕስ አንባቢው ጎጂ ቅዠቶችን ማሸነፍ የሚቻልባቸውን መንገዶች ወደያዙ የተለያዩ ርዕሰ ትምህርቶች ይመሩታል። እነዚህ ርዕሰ ትምህርቶች “እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ” የሚለውን ፊልጵስዩስ 4:​8ን በመሳሰሉ ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። አዎን፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ሐሳብ በንጹሕና በሚያንጽ ሐሳብ መተካት አለበት!

ተማሪው ምርምር በሚያደርግበት ጊዜ ችግሩን የሚያባብሱበትን ነገሮች እንዲያስወግድ የሚረዱ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደሚያገኝ ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል ምሳሌ 6:​27 እና ማቴዎስ 5:​28 አእምሮን የጾታ ስሜት በሚቀሰቅሱ ጽሑፎች መመገብ አደገኛ መሆኑን ያስጠነቅቃሉ። መዝሙራዊው “ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዓይኖቼን መልስ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 119:​37) እርግጥ ነው፣ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማንበቡ ብቻውን በቂ አይደለም። ጠቢቡ ሰው “የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 15:​28) ተማሪው የአምላክ ትእዛዝ ምን እንደሆነ ብቻ ሳይሆን እነዚህን ትእዛዛት ለምን እንደሰጠ ማሰላሰሉ የይሖዋ መንገዶች ጥበብ የሞላባቸውና ምክንያታዊ መሆናቸውን በጥልቅ እንዲገነዘብ ይረዳዋል።

በመጨረሻም ለእድገቱ ጋሬጣ የሆኑበትን ነገሮች ለማሸነፍ ጥረት የሚያደርገው ይህ ግለሰብ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ፈጥኖ መጠየቅ ይኖርበታል። አምላክ አፈጣጠራችንን ማለትም ከአፈር የተሠራንና ፍጹም አለመሆናችንን በሚገባ ስለሚያውቅ እንዲህ ማድረጉ የተገባ ነው። (መዝሙር 103:​14) አምላክ እንዲረዳን ያለማቋረጥ ከምናቀርበው ጸሎት በተጨማሪ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ቅዥቶችን ለማስወገድ ብርቱ ጥረት ማድረጋችን የኋላ ኋላ አስደሳች ውጤት ማለትም ንጹሕና የማይቆረቁር ሕሊና ያስገኛል።​—⁠ዕብራውያን 9:​14

ተስፋ አትቁረጥ

እየታገልክ ያለኸው ችግር ምንም ይሁን ምን አልፎ አልፎ ሊያገረሽብህ እንደሚችል መገንዘብ አለብህ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም ልትበሳጭና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሊያድርብህ ይችላል። ይሁን እንጂ “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት” የሚሉትን በገላትያ 6:​9 ላይ ያሉትን ቃላት አስታውስ። ዳዊትንና ጴጥሮስን የመሳሰሉ ለአምላክ ያደሩ አገልጋዮች አንዳንድ አሳፋሪ ስህተቶች ፈጽመዋል። ሆኖም ተስፋ አልቆረጡም። የተሰጣቸውን ምክር በትህትና ተቀብለው አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸው የይሖዋ አገልጋዮች መሆናቸውን ቀጥለዋል። (ምሳሌ 24:​16) ዳዊት ስህተቶች ፈጽሞ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ “እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ” ሲል ጠርቶታል። (ሥራ 13:​22) ጴጥሮስም በተመሳሳይ ስህተቶቹን አርሞ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ዓምድ እስከ መሆን ደርሷል።

ዛሬም ብዙ ሰዎች የገጠሟቸውን እንቅፋቶች በማሸነፍ ተመሳሳይ ስኬት አግኝተዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዩታካ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ። እንዲህ ብሏል:- “አንድ እርምጃ በወሰድኩ ቁጥር ይሖዋ ያደረገልኝ እርዳታና የሰጠኝ በረከት ቁማር የመጫወት ሱሴን እንዳሸንፍ ረድቶኛል። እምነት ‘ተራሮችን’ ሊያንቀሳቅስ እንደሚችል ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን በራሴ ሕይወት ላይ ለማየት በመቻሌ ከፍተኛ ደስታ አግኝቻለሁ።” ከጊዜ በኋላ ዩታካ በጉባኤው ውስጥ የጉባኤ አገልጋይ ሆነ።

ሲጋራ የማጨስ ሱስ የነበረባት ኬኮን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናት እህት የሲጋራን ሱስ አስመልክቶ በንቁ! መጽሔት ላይ የወጡ የተለያዩ ርዕሶች እንድታነብብ ሐሳብ አቀረበችላት። ኬኮ በይሖዋ ፊት ንጹሕ ሆኖ መቆየትን ዘወትር እንዲያስታውሳት በማሰብ 2 ቆሮንቶስ 7:​1 ላይ የሚገኙትን ቃላት ጽፋ መኪናዋ ውስጥ እስከ መለጠፍ ደርሳ ነበር። እንዲህም ሆኖ ማቆም አልቻለችም። ኬኮ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “በራሴ በጣም በመበሳጨት ለመሆኑ ማገልገል የምፈልገው ማንን ነው? ይሖዋን ወይስ ሰይጣንን? ብዬ ራሴን ጠየቅኩ።” ይሖዋን ማገልገል እንደምትፈልግ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ካደረገች በኋላ እሱ እንዲረዳት አምርራ ጸለየች። “ብዙም ሳልቸገር ማጨስ ማቆም መቻሌ በጣም አስገረመኝ። እንዲያውም ቀደም ብዬ እርምጃ ሳልወስድ በመቅረቴ ቆጭቶኛል” በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።

አንተም እንዲሁ እድገት እንዳታደርግ እንቅፋት የሆኑብህን ነገሮች ለማስወገድ የምታደርገው ጥረት ሊሰምርልህ ይችላል። አስተሳሰብህን፣ ምኞቶችህን፣ የምትናገራቸውን ቃላትና ድርጊትህን ከመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ጋር ባስማማህ መጠን ለራስህ ያለህ አክብሮትና በራስ የመተማመን መንፈስህ የዚያኑ ያህል እያደገ ይሄዳል። መንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ እንዲሁም የቤተሰብህ አባላት ከአንተ ጋር በሚሆኑበት ጊዜ ይነቃቃሉ እንዲሁም ይበረታታሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለህ ወዳጅነት ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል። ሕዝቦቹ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ላለመውደቅ ሲጥሩ ‘ከመንገዳቸው ላይ ዕንቅፋትን እንደሚያስወግድ’ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 57:​14) መንፈሳዊ እድገት እንዳታደርግ እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ለማስወገድና ለማሸነፍ ብርቱ ጥረት የምታደርግ ከሆነ ይሖዋ በእጅጉ እንደሚባርክህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የይሖዋ ምሥክሮች በብዙ ቋንቋዎች ያሳተሙት መጽሐፍ።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ እንደ ተራራ ያሉ እንቅፋቶችን በእምነት ማሸነፍ እንደሚቻል ተናግሯል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ መንፈሳዊ ድክመቶችን እንድናሸንፍ ያጠነክረናል