በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ላገኘኋቸው ጥሩ ትዝታዎች አመስጋኝ ነኝ!

ላገኘኋቸው ጥሩ ትዝታዎች አመስጋኝ ነኝ!

የሕይወት ታሪክ

ላገኘኋቸው ጥሩ ትዝታዎች አመስጋኝ ነኝ!

ድሩሲላ ኬን እንደተናገረችው

ዓመቱ 1933 ሲሆን እንደ እኔው ኮልፖልተር ማለትም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ከሆነው ከዛኖዋ ኬን ጋር ገና መጋባታችን ነበር። ደስታዬ ወሰን አልነበረውም። በዚህ ጊዜ በአገልግሎት ምድቡ ከባለቤቴ ጋር ለማገልገል እቅድ አወጣሁ። ሆኖም ለዚህ ተግባር ብስክሌት ያስፈልገኝ ነበር። ኢኮኖሚያዊ ድቀቱ ሁኔታውን አስቸጋሪ አድርጎት ስለነበር እንዲህ ያለውን የቅንጦት ዕቃ መግዛት አልቻልኩም። ታዲያ ምን ማድረግ እችላለሁ?

ሦስቱ የባለቤቴ ታናናሽ ወንድሞች የነበርኩበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲሰሙ ያረጁ ዕቃዎች ወደሚጣሉበት ቦታ በመሄድ የተለያዩ የብስክሌት ክፍሎች ፈልገው አገኙ። ከዚያም እነዚያን ገጣጥመው ብስክሌት ሠሩልኝ! ብስክሌት መንዳት እንደተማርኩ ወዲያው ከዛኖዋ ጋር ዎርሴስተርና ሄርፎርድ የተባሉትን የእንግሊዝ ግዛቶች በብስክሌት በማቆራረጥ ላገኘናቸው ሰዎች ሁሉ በደስታ መመስከር ጀመርን።

እንዲህ ያለው ቀላል የእምነት እርምጃ በጥሩ ትዝታዎች ለተሞላ ሕይወት ፈር የሚቀድድ መሆኑን አልተገነዘብኩም ነበር። ሆኖም የሕይወቴን መንፈሳዊ መሠረት የጣሉልኝ ወላጆቼ ነበሩ።

የታላቁ ጦርነት አስቸጋሪ ዓመታት

የተወለድኩት ታኅሣሥ 1909 ነበር። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እናቴ መለኮታዊው የዘመናት ዕቅድ የተባለው መጽሐፍ ደረሳት። በ1914 ወላጆቼ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተሰኘውን ፊልም እንድመለከት ወደ ኦልድሃም ላንክሻየር ይዘውኝ ሄዱ። (መጽሐፉም ሆነ ፊልሙ የተዘጋጀው ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች በመባል በሚታወቁት ሰዎች ነበር።) ምንም እንኳ በወቅቱ ልጅ ብሆንም ባየሁት ነገር ከመደሰቴ የተነሣ ወደ ቤት የሄድኩት እየዘለልኩ እንደነበር በደንብ አስታውሳለሁ! ከዚያም ፍራንክ ሂሊ በምንኖርበት በሮችዴል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አቋቋመ። በቤተሰብ መልክ በዚህ ስብሰባ ላይ መገኘታችን ቅዱሳን ጽሑፎችን ይበልጥ ማስተዋል እንድንችል ረድቶናል።

ሆኖም በዚሁ ዓመት ዛሬ አንደኛ የዓለም ጦርነት ብለን የምንጠራው ታላቅ ጦርነት በመፈንዳቱ ሰላማዊ ሕይወታችን ተናጋ። አባቴ ለውትድርና ቢመለመልም ገለልተኛ አቋሙን ጠብቋል። በችሎት ፊት “በጣም ጨዋ ሰው” መሆኑ የተመሠከረለት ሲሆን “በውትድርና ላለመሳተፍ የወሰደው እርምጃ ከበስተጀርባው ሌላ ተንኮል የሌለበት መሆኑን ከሚያምኑ የተከበሩ ሰዎች” በርካታ ደብዳቤዎች እንደተላኩ አንድ የአካባቢው ጋዜጣ ዘግቧል።

አባቴ ከማንኛውም ግዴታ ነጻ ባይደረግም “ከወታደራዊ አገልግሎት” ግን ነጻ ሆኖ ነበር። ወዲያው ልክ እንደ እኔ እና እናቴ ሁሉ እርሱም የፌዝ ዒላማ ሆነ። መጨረሻ ላይ ግን ሁኔታው እንደገና ታይቶ በእርሻ ሥራ ተመደበ። ሆኖም አንዳንድ ገበሬዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ሲያሻቸው ጥቂት ገንዘብ ይሰጡት ሲያሻቸው ደግሞ ጭራሽ ይከለክሉት ነበር። እናቴ ቤተሰቡን ለመደገፍ ስትል በአንድ የልብስ ንጽሕና መስጫ በትንሽ ክፍያ ተቀጥራ ከባድ ሥራ መሥራት ጀመረች። በልጅነቴ እንዲህ ያለውን ከባድ ችግር ማሳለፌ ምን ያህል እንዳጠነከረኝ አሁን ተገንዝቤአለሁ። ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን መንፈሳዊ ነገሮች እንዳደንቅ ረድቶኛል።

አነስተኛ ጅምር

ዳንኤል ሂዩዝ የተባለ ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት ጀመረ። ዳንኤል ሂዩዝ እኛ ከተዛወርንበት ከኦዝወስትሪ 20 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ በሚገኘው በሩወበን መንደር ማዕድን በማውጣት ሥራ ተሠማርቶ ነበር። አጎቴ ዳን ብዬ የምጠራው ዳንኤል ከቤተሰባችን ጋር ቅርርብ መሥርቶ የነበረ ሲሆን ሊጠይቀን ሲመጣ ሁልጊዜ የሚያወራው ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ነበር። ተራ ወሬ ፈጽሞ አውርቶ አያውቅም። በ1920 በኦዝወስትሪ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን የተቋቋመ ሲሆን በ1921 አጎቴ ዳን የአምላክ በገና የተሰኘውን መጽሐፍ ሰጠኝ። ይህ መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በቀላሉ ለመረዳት ስላስቻለኝ እንደ ውድ ነገር እመለከተው ነበር።

በተጨማሪም ከጊዜ በኋላ በለንደን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች የሆነው ፕራይስ ሂዩዝ a ከቤተሰባችን ጋር መቀራረብ ጀመረ። ከቤተሰቡ ጋር በዌልሽ ጠረፍ ከሚገኘው ከብሮንጋርዝ ብዙም ሳይርቅ ይኖር የነበረ ሲሆን ሲሲ የተባለችው እህቱ የእናቴ የቅርብ ጓደኛ ሆና ነበር።

በ1922 ‘ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ’ የሚለው ጥሪ ሲቀርብ የነበረውን ደስታ አስታውሳለሁ። ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት ገና ተማሪ ብሆንም ለተለየ ዓላማ የተዘጋጁትን ትራክቶች በተለይም በ1924 የታተመውን ካህናት ተወነጀሉ የሚለውን ትራክት በማሰራጨቱ ሥራ በጉጉት ተካፍዬ ነበር። ያንን አሥርተ ዓመት መለስ ብዬ ሳስበው ከብዙ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ጋር መሰብሰብ ምንኛ ታላቅ መብት እንደነበረ እገነዘባለሁ። ከእነርሱም ውስጥ ሞድ ክላርክ b እና ጓደኛዋ ማሪ ግራንት፣* ኤድገር ክሌ፣* ሮበርት ሃድሊንተን፣ ኬቲ ሮበርትስ፣ ኤድዊን ስኪነር* እና በካናዳ የሚካሄደውን ሥራ ለማገዝ ወደዚያው የሄዱት ፐርሲ ቻፕማን እና ጃክ ናታን* ይገኙበታል።

“ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር በሰፊው ክልላችን ውስጥ ወቅታዊ ምሥክርነት ሰጥቷል። ግንቦት 14, 1922 ስታንሌይ ሮጀርስ የተባለው የፕራይስ ሂዩዝ ዘመድ ይህንን ንግግር ቀን ከከተማችን በስተ ሰሜን በምትገኘው መንደር በቻርክ ማታ ደግሞ ኦዝወስትሪ በሚገኘው ዘ ፒክቸር ቲያትር ቤት ለመስጠት ከሊቨርፑል መጥቶ ነበር። ለዚህ ልዩ ወቅት ተብሎ የተዘጋጀው የመጋበዣ ወረቀት አሁን ድረስ ከእኔ ጋር አለ። በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ትንሹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቡድናችን ኸርበርት ሲንየር፣ አልበርት ሎይድና ጆን ብላኒ የተባሉት የበላይ ተመልካቾች በሚያደርጉለት ጉብኝት ተጠናክሮ ነበር። እነዚህን የበላይ ተመልካቾች ፒልግሪም በማለት እንጠራቸው ነበር።

የውሳኔ ጊዜ

በ1929 ለመጠመቅ ወሰንኩ። በዚህ ጊዜ 19 ዓመት ሞልቶኝ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያውን ከባድ ፈተና የተጋፈጥኩት በዚሁ ወቅት ነበር። አባቱ የፖለቲካ ሰው ከሆነ አንድ ወጣት ጋር ተዋወቅሁ። ተዋድደን ስለነበር ሊያገባኝ እንደሚፈልግ ገለጸልኝ። ከዓመት በፊት የወጣውን መንግሥት የተባለ መጽሐፍ ብሰጠውም ብዙም ሳይቆይ ለዚህ መጽሐፍ ጭብጥ ማለትም ለሰማያዊው መንግሥት ፍላጎት እንደሌለው አሳየ። የጥንት እስራኤላውያን ከማያምኑ ጋር በትዳር እንዳይጠላለፉ ታዝዘው እንደነበርና ይህ መሠረታዊ ሥርዓትም ለክርስቲያኖች እንደሚሠራ ከጥናቴ ተገንዝቤ ነበር። በመሆኑም ከባድ ቢሆንብኝም ጥያቄውን ሳልቀበል ቀረሁ።​—⁠ዘዳግም 7:​3፤ 2 ቆሮንቶስ 6:​14

“ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት” ከሚሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ብርታት አግኝቻለሁ። (ገላትያ 6:​9) በተጨማሪም ውድ አጎቴ ዳን የጻፈልኝ ደብዳቤ አበረታቶኛል። “ቀላልም ሆነ ከባድ ፈተና ሲያጋጥምሽ በሮሜ 8 ቁጥር 28 ላይ የሰፈሩትን ቃላት አስታውሺ።” ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።” ቀላል ባይሆንም ትክክለኛውን ውሳኔ እንዳደረግሁ አውቅ ነበር። በዚያው ዓመት ኮልፖልተር ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ።

ፈተናውን መጋፈጥ

በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን አዲሱን ስማችንን የተቀበልን ሲሆን በዚሁ ዓመት የዓለም ተስፋ የሆነው መንግሥት የሚለውን ቡክሌት ተጠቅመን መጠነ ሰፊ ዘመቻ አካሂደናል። በዚህ ወቅት ለእያንዳንዱ ፖለቲከኛ፣ ቄስና ነጋዴ አንዳንድ ቅጂ አበርክተን ነበር። ክልሌ ከኦዝወስትሪ አንስቶ በስተ ሰሜን 25 ኪሎ ሜትር ርቃ እስከምትገኘው እስከ ሬክስሃም ድረስ ስለነበር ክልሉን መሸፈኑ ከብዶኝ ነበር።

በተከታዩ ዓመት በበርሚንግሃም በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ 24 ፈቃደኛ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ተገለጸ። ምን ዓይነት የአገልግሎት ዘርፍ እንደሆነ ባናውቅም ሃያ አራታችንም ጓጉተን ስለነበር ስማችንን ሞልተን ሰጠን። ሁለት ሁለት ሆነን መንግሥቱን የሚያሳውቁ ከፊትና ከኋላ በትከሻ ላይ የሚንጠለጠሉ ማስታወቂያዎች በማንገት የዓለም ተስፋ የሆነው መንግሥት የሚለውን ያንኑ ቡክሌት እንድናበረክት ስንመደብ ምን ያህል እንደተደሰትን ልትገምቱ ትችላላችሁ።

በካቴድራሉ አካባቢ ማገልገል በጣም ቢያሳፍረኝም እዚህ ከተማ ውስጥ ማንም የሚያውቀኝ አይኖርም ብዬ በማሰብ ራሴን አጽናናሁ። በመጀመሪያ ያገኘኋት ግን የቀድሞ የትምህርት ቤት ጓደኛዬን ነበር። ዓይኗን ፍጥጥ አድርጋ እየተመለከተችኝ “ምንድን ነው የማየው? እንዲህ ለብሰሽ ደግሞ ምንድን ነው የምትሠሪው?” ስትል ጠየቀችኝ። ይህ አጋጣሚ የነበረብኝን የሰው ፍርሃት አስወግዶልኛል!

ራቅ ወዳሉ ቦታዎች መጓዝ

በ1933 በ25 ዓመት የሚበልጠኝንና ሚስቱ የሞተችበትን ዛኖዋን አገባሁ። የመጀመሪያ ሚስቱ ቀናተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የነበረች ስትሆን እርሷ ከሞተች በኋላ ዛኖዋ በተመደበበት ቦታ በታማኝነት ጸንቷል። ብዙም ሳይቆይ እኔና ዛኖዋ ከእንግሊዝ 150 ኪሎ ሜትር ወደሚርቀውና ኖርዝ ዌልስ ወደሚገኘው አዲሱ ምድባችን ተጓዝን። ካርቶኖችን፣ ሻንጣዎችንና ሌሎች ውድ ዕቃዎቻችንን በብስክሌቶቻችን መሪ ላይ አስቀምጠን ከማፈናጠጫው ብረት ጋር ካሰርንና በዕቃ መጫኛው ላይ የቻልነውን ያህል ዕቃ ከጫንን በኋላ ጉዟችንን ጀመርን። ሆኖም እንደፈራነው ሳይሆን ክልላችን በሰላም ደረስን! በዚያ የአገልግሎት ምድብ ብስክሌቶቻችን በጣም ጠቅመውናል። ወደ የትኛውም ቦታ ሌላው ቀርቶ 900 ሜትር ከፍታ ወዳለው ከደር አይድሪስ የተባለው የዌልሽ ተራራ ጫፍ ድረስ የምንሄደው በብስክሌቶቻችን ነበር። ‘ይህንን የመንግሥት ወንጌል’ ለመስማት የጓጉ ሰዎች ማግኘታችን እጅግ የሚክስ ነበር!​—⁠ማቴዎስ 24:​14

እዚያ ያሉት ሰዎች ቶም ፒራይስ የተባለ ልክ እንደ እኛ የሚሰብክ ሰው እንዳለ ሲነግሩን እዚያ ብዙም አልቆየንም። በመጨረሻ ቶምን ከዌልሽፑል አጠገብ በሚገኘው ሎንግ ማውንቴን ስናገኘው በጣም ተደሰትን። ስብከት እንደጀመርን አካባቢ ሪኮንሲሊዬሽን የተሰኘውን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ መጽሐፍ ሰጥቼው ነበር። መጽሐፉን ራሱ ካጠናው በኋላ ከለንደን ተጨማሪ ጽሑፎች እንዲላኩለት ጠየቀ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ አዲሱን እምነቱን ለሌሎች በቅንዓት ሲያካፍል ቆይቷል። ሦስታችንም በአንድ ላይ እያጠናን እርስ በርስ በመበረታታት ብዙ አስደሳች ጊዜያት አሳልፈናል።

የደረሰው የተፈጥሮ አደጋ ለበረከት ሆነ

በ1934 በሰሜናዊ ዌልስ አቅራቢያ የሚገኙ ኮልፖልተሮች በሙሉ ወደ ሬክስሃም ከተማ በመጓዝ ራይቸስ ሩለር የተባለውን ቡክሌት በማሰራጨቱ ሥራ እንዲካፈሉ ተጋበዙ። ይህንን ልዩ ዘመቻ ከመጀመራችን ከአንድ ቀን በፊት በአገሪቱ ከባድ አደጋ ደርሶ ነበር። ከሰሜናዊው ሬክስሃም 3 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በግራስፎርድ ከሰል ማውጫ የተከሰተው ፍንዳታ 266 ሠራተኞችን የገደለ ሲሆን ከ200 በላይ የሚሆኑ ልጆችን አባት አልባ 160 የሚያክሉ ሴቶችን ደግሞ ባል አልባ አድርጓል።

የሟቾቹን ቤተሰቦች መመዝገብ፣ በግል ሄደን ማነጋገርና ቡክሌት መስጠቱን ተያያዝነው። ከተሰጡኝ ስሞች መካከል የ19 ዓመት ወንድ ልጃቸውን ያጡት ሚስስ ቻድዊክ ይገኙበታል። ላነጋግራቸው ስሄድ ትልቁ ልጃቸው ጃክ ሊያጽናናቸው መጥቶ ነበር። ይህ ወጣት ቢያውቀኝም አንድም ቃል ትንፍሽ አላለም ነበር። በኋላ ግን ቡክሌቱን ካነበበ በኋላ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሰጠሁትን ዘ ፋይናል ዋር የተሰኘ ሌላ ቡክሌት ፈልጎ አገኘ።

ከዚያም ጃክና ባለቤቱ ሜይ ያለሁበትን ቦታ አጠያይቀው ተጨማሪ ጽሑፍ እንድሰጣቸው ወደ እኔ መጡ። በ1936 ሬክስሃም በሚገኘው ቤታቸው ስብሰባዎች እንዲደረጉ ተስማሙ። ከስድስት ወራት በኋላ አልበርት ሎይድ ያደረገላቸውን ጉብኝት ተከትሎ በጃክ ቻድዊክ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካችነት አንድ ጉባኤ ተቋቋመ። በአሁኑ ጊዜ በሬክስሃም ሦስት ጉባኤዎች ይገኛሉ።

በጂፕሲዎች ተጎታች ቤት ውስጥ መኖር

እስከዚህ ጊዜ ድረስ ከቦታ ቦታ ስንዘዋወር ባገኘናቸው ቤቶች ውስጥ እንኖር ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ዛኖዋ ከቦታ ቦታ ሊጎተት የሚችል የራሳችን ቤት መሥራት እንዳለብን ተሰማው። ባለቤቴ የጂፕሲ ዝርያ ያለው ጎበዝ አናጢ ስለነበረ የጂፕሲዎች ዓይነት ተጎታች ቤት ሠራ። ቤቱን ኤሊዛቤት ብለን ሰየምነው። ይህ ስም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ትርጉሙም “የመትረፍረፍ አምላክ” ማለት ነው።

ቆይታ ካደረግንባቸው ቦታዎች መካከል አንድ በጣም የማስታውሰው ቦታ አለ። ይህ ወንዝ ዳር የሚገኝና የተለያየ ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎች የሚገኙበት ቦታ ሲሆን ለእኔ ልክ እንደ ገነት ነበር! ብዙም የሚያፈናፍን ባይሆንም በዚያ ተጎታች ቤት ውስጥ ያሳለፍናቸው ዓመታት በደስታ የተሞሉ ናቸው። ሆኖም አየሩ ቀዝቃዛ በሚሆንበት ጊዜ የአልጋ ልብሱ ከቤቱ ግድግዳ ጋር የሚጣበቅ ሲሆን የሚፈጠረው እርጥበት የማያቋርጥ ችግር አስከትሎብን ነበር። አንዳንድ ጊዜ ውኃ ከሩቅ ቦታ ማመላለስ አስፈልጎን የነበረ ቢሆንም ችግሩን በጋራ ተወጥተነዋል።

አንድ ክረምት ታምሜ ሳለ ከጥቂት ምግብ በስተቀር ምንም ገንዘብ አልነበረንም። ዛኖዋ ከአልጋው ጫፍ ቁጭ አለና እጄን ያዝ አድርጎ መዝሙር 37:​25ን አነበበልኝ:- “ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም።” ከዚያም ትኩር ብሎ እያየኝ እንዲህ አለኝ:- “ፈጥኖ አንድ ነገር ካልተፈጠረ ልመና መግባታችን ነው። አምላክ ደግሞ ይህ እንዲደርስብን እንደማይፈቅድ እርግጠኛ ነኝ!” ከዚያም ለጎረቤቶቻችን ለመመስከር ሄደ።

እኩለ ቀን ላይ ለእኔ አንድ የሚጠጣ ነገር ለማዘጋጀት ሲመለስ አንድ ፖስታ ጠበቀው። ፖስታው ከአባቱ የተላከ ሲሆን በውስጡ 75 የአሜሪካ ዶላር ይዞ ነበር። ዛኖዋ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በማጭበርበር ወንጀል በሐሰት ተከስሶ የነበረ ቢሆንም ጥፋተኛ አለመሆኑ የተረጋገጠው በዚህ ጊዜ ነበር። ይህ ስጦታ የተሰጠው ለደረሰበት ነገር ካሳ እንዲሆን ነው። ምንኛ ወቅታዊ ስጦታ ነበር!

ጠቃሚ ትምህርት

አንዳንድ ጊዜ ትምህርት የምናገኘው የተወሰኑ ዓመታት ካለፉ በኋላ ነው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በ1927 ትምህርት ከማቆሜ በፊት ላቪንያ ፋርክሎ ከምትባል አንዲት መምህር በስተቀር ለሁሉም የክፍል ጓደኞቼና መምህሮቼ መስክሬላቸው ነበር። ሕይወቴን እንዴት ልጠቀምበት እንዳሰብኩ ስገልጽ ብዙም የማወቅ ጉጉት ያለው ሰው ስላልነበረና ከሚስስ ፋርክሎ ጋር ደግሞ ብዙም አግባብ ስላልነበረኝ ለእርሷ ላለመንገር ወሰንኩ። እናቴ፣ ከ20 ዓመታት በኋላ ይህች መምህር የይሖዋ ምሥክር መሆኗን ለድሮ ጓደኞቿና ተማሪዎቿ ለመንገር እንደመጣች ስትነግረኝ ምን ያህል እንደተገረምኩና እንደተደሰትሁ ገምቱ!

ከእርሷ ጋር ስንገናኝ ስለ እምነቴና በሕይወቴ ላደርግ ስላሰብኩት ነገር ለምን እንዳልነገርኳት አብራራሁላት። በእርጋታ ካዳመጠችኝ በኋላ እንዲህ አለች:- “ሁልጊዜ እውነትን እፈልግ ነበር። እውነት በሕይወቴ ሙሉ ስፈልገው የኖርኩት ነገር ነው!” ይህ ሁኔታ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቶኛል። ላገኘሁት ሰው ሁሉ ከመስበክ ወደ ኋላ ማለትና በማንም ሰው ላይ አስቀድሜ መፍረድ እንደሌለብኝ አስተምሮኛል።

ሌላ ጦርነትና ከዚያ በኋላ ያሳለፍኩት ሕይወት

በ1930ዎቹ ማብቂያ አካባቢ እንደገና የጦርነት ደመና ማንዣበብ ጀመረ። በአሥር ዓመት የምበልጠው ዴኒስ የተባለው ታናሽ ወንድሜ ወታደራዊ አገልግሎት የማይመለከተው ሰብዓዊ ሥራው ላይ እስከቆየ ድረስ ብቻ እንደሆነ ተነግሮት ከግዴታው ነፃ ሆነ። ዴኒስ ብዙም ለእውነት ፍላጎት ስላልነበረው እኔና ባለቤቴ ሩፐርት ብራድቤሪ እና ዴቪድ የተባሉ በአካባቢው የሚገኙ ወንድማማች አቅኚዎች እንዲያነጋግሩት ጠየቅናቸው። እነርሱም ሄደው አነጋገሩትና መጽሐፍ ቅዱስ አስጠኑት። ዴኒስ በ1942 የተጠመቀ ሲሆን በኋላም አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። በ1957 ደግሞ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ።

በ1938 ኤሊዛቤት የተባለችው ልጃችን በመወለዷ የቤተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ሲል ዛኖዋ ተጎታች ቤታችንን አሰፋት። ዮነስ የተባለችው ሁለተኛዋ ልጃችን በ1942 ስትወለድ ቋሚ የሆነ መኖሪያ ማግኘት ጥበብ መስሎ ስለታየን ዛኖዋ ለተወሰኑ ዓመታት አቅኚነቱን አቆመ። ከዚያም ራክስሃም አቅራቢያ የምትገኝ ትንሽ ቤት ውስጥ መኖር ጀመርን። በኋላም በአዋሳኙ በቼሻየር ውስጥ በሚገኘው በሚድሊች መኖር ጀመርን። እዚያው ሳለን በ1956 ውዱ ባለቤቴ ሞተ።

ሁለቱ ሴቶች ልጆቻችን የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሲሆኑ ሁለቱም ደስታ የሰፈነበት ትዳር መስርተዋል። ዩነስና ሽማግሌ የሆነው ባለቤቷ አሁንም በለንደን ልዩ አቅኚዎች ሆነው ያገለግላሉ። የኤሊዛቤት ባለቤትም የጉባኤ ሽማግሌ ሲሆን እነርሱ፣ ልጆቻቸውና አራት የልጅ ልጆቼ የሚኖሩት እኔ ከምኖርበት ከፕሪስቶን ላንክሻየር አቅራቢያ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ።

ከቤቴ ተነስቼ ከመንገዱ ባሻገር እስካለው የመንግሥት አዳራሽ ድረስ በእግሬ መሄድ በመቻሌ አመስጋኝ ነኝ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጉጃራቲ ተናጋሪ ከሆነው እዚያ እኛው አዳራሽ ውስጥ ከሚሰበሰበው ቡድን ጋር መሰብሰብ ጀምሬአለሁ። አሁን ትንሽ የመስማት ችግር ስላለብኝ ቋንቋውን መማር ቀላል አልሆነልኝም። አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች በቀላሉ የሚሰሟቸውን አነስተኛ ድምፆች መስማት ይቸግረኛል። ሁኔታው ተፈታታኝ ቢሆንም አስደሳች ነው።

አሁንም ከቤት ወደ ቤት መስበክና በቤቴ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት እችላለሁ። ወዳጆቼ ሊጠይቁኝ ሲመጡ በሕይወቴ ያሳለፍኳቸውን አንዳንድ ተሞክሮዎች መናገር ሁልጊዜ ያስደስተኛል። ወደ 90 ለሚጠጉ ዓመታት ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር በመሰብሰቤ ያገኘሁትን በረከት መለስ ብዬ ማሰብ በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የፕራይስ ሂዩዝ የሕይወት ታሪክ “ከታመነው ድርጅት ጋር እኩል መራመድ” በሚል ርዕስ በሚያዝያ 1, 1963 (እንግሊዝኛ) መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቷል።

b የእነዚህ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የሕይወት ታሪክ ቀደም ባሉ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ ወጥቷል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ግንቦት 14, 1922 የሰማሁትን “ዛሬ ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም ” የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር የሚያስተዋውቅ የስብሰባ ጥሪ ወረቀት

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1933 ከዛኖዋ ጋር ከተጋባን ከጥቂት ጊዜ በኋላ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለቤቴ በሠራት “ኤሊዛቤት” በተባለችው ተጎታች ቤት አጠገብ ቆሜ