ልማድ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለበጎ ተጠቀሙበት
ልማድ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለበጎ ተጠቀሙበት
ሰውዬው ከአቴንስ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ ለ12 ዓመታት ኖሯል። በየቀኑ ከሥራ ወደ ቤት የሚመላለሰው በተመሳሳይ መንገድ ነበር። በኋላ ግን በተቃራኒ አቅጣጫ በሚገኘው የከተማዋ ዳርቻ መኖር ጀመረ። አንድ ቀን ከሥራ ወጥቶ ወደ ቤቱ መጓዝ ይጀምራል። በተሳሳተ አቅጣጫ መጓዙን የተገነዘበው የቀድሞ ሰፈሩ ሲደርስ ነበር። ወደ ድሮ ቤቱ የሄደው በደመ ነፍስ ነው!
አንዳንድ ጊዜ ልማድ አንድን ነገር በደመ ነፍስ እንድናደርግ የሚገፋፋ ኃይል ነው መባሉ አያስደንቅም። ይህም በሕይወታችን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል የሚጠቁም ነው። ከዚህ አንጻር ልማድ ከእሳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እሳት በጨለማ ቦታ እንደ ብርሃን ሆኖ ያገለግላል፤ እንዲሁም ሰውነታችንን ሊያሞቅልንና ምግባችንን ሊያበስልልን ይችላል። ሆኖም እሳት ሕይወትንና ንብረትን የሚያወድም አስፈሪ ጠላትም ሊሆን ይችላል። ልማድም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። በትክክለኛው መንገድ ከዳበረ ከፍተኛ ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል። ይሁን እንጂ አጥፊም ሊሆን ይችላል።
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ሰው ባዳበረው ልማድ ምክንያት ያጣው ነገር ቢኖር በትራፊክ መጨናነቅ የባከነውን የተወሰነ ሰዓት ብቻ ነው። ይበልጥ አስፈላጊ ወደሆኑት ነገሮች ስንመጣ ግን ልማድ ስኬት ሊያስገኝልን ወይም መከራ ሊያስከትልብን ይችላል። እስቲ ልማድ ሊጠቅመን አሊያም ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ሊነካም ሆነ ለእርሱ የምናቀርበውን አገልግሎት ሊያስተጓጉል የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ጥቂት የሕይወት ታሪኮችን ተመልከት።
በጥሩና መጥፎ ልማድ ረገድ የተጠቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች
ኖኀ፣ ኢዮብና ዳንኤል ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና በመመሥረት ተባርከዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ስለ ጽድቃቸው’ ያሞግሳቸዋል። (ሕዝቅኤል 14:14) የሦስቱም አኗኗር ጥሩ ልማድ አዳብረው እንደነበረ የሚያሳይ ነው።
ኖኀ መርከብ እንዲሠራ ተነግሮት ነበር። ይህ መርከብ ከአንድ የእግር ኳስ ሜዳ የሚበልጥ ስፋትና ከአምስት ፎቅ የሚበልጥ ከፍታ ያለው ነበር። እንዲህ ያለው ግዙፍ የግንባታ ሥራ ማንኛውንም የጥንት መርከብ ሠሪ እንደሚያስደነግጥ የታወቀ ነው። ኖኀና ሰባት የቤተሰቡ አባላት መርከቡን ሠርተው ያጠናቀቁት ያላንዳች ዘመናዊ መሣሪያ እገዛ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ኖኀ በዘመኑ ለነበሩት ሰዎች መስበክ ነበረበት። የቤተሰቡን መንፈሳዊና ሥጋዊ ፍላጎት እያሟላ እንደነበረም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (2 ጴጥሮስ 2:5) ኖኀ ይህንን ሁሉ ለማከናወን ጥሩ የሥራ ልማድ አዳብሮ መሆን አለበት። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ኖኅ እንደሚከተለው ተብሎ ተገልጿል:- “ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ . . . እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።” (ዘፍጥረት 6:9, 22፤ 7:5) ኖኅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ከበደል የራቀ” [NW ] ተብሎ ስለተገለጸ ከውኃ ጥፋት በኋላና በባቤል በይሖዋ ላይ ማመፅ ከተጀመረበት ጊዜ በኋላ ሳይቀር አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጎ መሆን አለበት። በእርግጥም ኖኅ በ950 ዓመት ዕድሜው እስከሞተበት ጊዜ ድረስ አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጓል።—ዘፍጥረት 9:29
ኢዮብ ያዳበራቸው ጥሩ ልማዶች “ፍጹምና ቅን” እንዲሆን አስችለውታል። (ኢዮብ 1:1, 8፤ 2:3) ኢዮብ የግብዣው ቀኖች ባለፉ ቁጥር “ምናልባት ልጆቼ በድለው፣ እግዚአብሔርንም በልባቸው ሰድበው ይሆናል” ብሎ ስለሚያስብ ለቤተሰቡ እንደ ካህን በመሆን እነርሱን ወክሎ መሥዋዕት የማቅረብ ልማድ ነበረው። “እንዲሁ ኢዮብ ሁልጊዜ ያደርግ ነበር።” (ኢዮብ 1:5፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በኢዮብ ቤተሰብ ውስጥ የይሖዋን አምልኮ የሚመለከቱ ልማዶች ከፍተኛ ቦታ ይሰጣቸው እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም።
ዳንኤል ረዥሙን ዕድሜውን ያሳለፈው ይሖዋን “ያለማቋረጥ” በማገልገል ነው። (ዳንኤል 6:16, 20 NW ) ዳንኤል ምን ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶች ነበሩት? በመጀመሪያ ደረጃ ዳንኤል አዘውትሮ ወደ ይሖዋ ይጸልይ ነበር። ድርጊቱን የሚከለክል የንጉሥ ትእዛዝ ቢወጣም ዳንኤል “ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም።” (ዳንኤል 6:10፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ለሕይወቱ አስጊ ቢሆንም ዳንኤል ለአምላክ የመጸለይ ልማዱን አልተወም። ይህ ልማድ ዳንኤል አስገራሚ የአቋም ጽናት የተንጸባረቀበት የሕይወት ጎዳና እንዲመራ እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ዳንኤል ጥሩ የጥናትና በአምላክ ድንቅ ተስፋዎች ላይ በጥልቅ የማሰላሰል ልማድም ነበረው። (ኤርምያስ 25:11, 12፤ ዳንኤል 9:2) እነዚህ ጥሩ ልማዶች የሕይወትን ሩጫ በታማኝነት በመሮጥ እስከ መጨረሻው እንዲጸና እንደረዱት ምንም አያጠራጥርም።
ከዚህ በተቃራኒው ግን ዲና የነበራት መጥፎ ልማድ ለአሳዛኝ ውጤት ዳርጓታል። ዲና የይሖዋ አምላኪዎች ያልነበሩትን “የዚያን አገር ሴቶች ልጆች ለማየት ትወጣ ነበር።” (ዘፍጥረት 34:1 NW ) ይህ ብዙም ጎጂ የማይመስል ልማድ መጥፎ ውጤት አስከትሏል። በመጀመሪያ ‘በአባቱ ቤት ካሉት ሁሉ የከበረ’ ተደርጎ የሚታየው ሴኬም የተባለ ወጣት አስነወራት። ከዚያም ሁለቱ ወንድሞቿ የበቀል እርምጃ በመውሰድ የከተማውን ወንዶች በሙሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ። ምንኛ አሳዛኝ ውጤት ነው!—ዘፍጥረት 34:19, 25-29
እኛስ ያዳበርናቸው ልማዶች የሚጎዱን ሳይሆን የሚጠቅሙን ስለመሆናቸው እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
ከልማድ ጥቅም ማግኘት
አንድ ፈላስፋ “ልማድ የአርባ ቀን እድል ነው” በማለት ጽፏል። ሆኖም ልማድ የአርባ ቀን እድል ሊሆን አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎውን ልማድ መተውና ጥሩውን መኮትኮት እንደምንችል በግልጽ ያሳያል።
ጥሩ ልማዶች ካሉ ክርስቲያናዊው ጉዞ ይበልጥ ውጤታማና ቀላል ይሆናል። አሌክስ የተባለ በግሪክ የሚኖር ክርስቲያን እንዲህ ብሏል:- “የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን ያወጣሁትን ፕሮግራም ሙጥኝ የማለት ልማዴ ውድ ጊዜዬን ቆጥቦልኛል።” ቴዎፍሎስ የተባለ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ውጤታማ ስላደረገው እቅድ የማውጣት ልማድ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ጥሩ እቅድ የማውጣት ልማድ ባይኖረኝ ኖሮ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቼን በተሳካ መንገድ መወጣት እንደማልችል ተገንዝቤአለሁ።”
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ‘በደረስንበት የእድገት ደረጃ በዚያው ልማድ በሥርዓት መመላለሳችንን እንድንቀጥል’ ተመክረናል። (ፊልጵስዩስ 3:16 NW ) ልማድ አንድን ‘ቋሚ አሠራር በመከተል የሚከናወን የተዘወተረ ተግባር’ ነው። እንዲህ ያሉት ጥሩ ልማዶች ይጠቅሙናል። ምክንያቱም ሥራችንን የምናከናውነው አንድን ቋሚ አሠራር ተከትለን ስለሚሆን ተመልሰን እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ በማሰብ ጊዜ ማጥፋት አያስፈልገንም። ለብዙ ጊዜ የቆዩ ልማዶች በደመ ነፍስ የሚደረጉ ይሆናሉ ለማለት ይቻላል። ጥሩ የማሽከርከር ልማድ አንድ አሽከርካሪ በመንገዱ ላይ አደገኛ ሁኔታ ሲገጥመው ሕይወትን የሚያድን ፈጣን ውሳኔ እንዲያደርግ እንደሚረዳው ሁሉ ጥሩ ልማዶች በክርስቲያናዊ ጉዟችንም ወቅት በፍጥነት ተገቢ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ይረዱናል።
ጀረሚ ቴይለር የተባለው እንግሊዛዊ ጸሐፊ እንዳስቀመጠው “ልማድ የተግባር ውጤት ነው።” ጥሩ ልማድ ካዳበርን በትንሽ ጥረት ጥሩ ነገሮች ማከናወን እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያን አገልጋዮች በመሆን በስብከቱ ሥራ አዘውትሮ የመካፈል ልማድ ካለን የመስክ አገልግሎት ይበልጥ ቀላልና አስደሳች ይሆንልናል። ሐዋርያትን አስመልክቶ እንዲህ እናነብባለን:- “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።” (ሥራ 5:42 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ 17:2) በሌላው በኩል ግን አገልግሎት አልፎ አልፎ ብቻ የምንወጣ ከሆነ በዚህ ወሳኝ ክርስቲያናዊ ሥራ መካፈሉ ሊያስጨንቀንና የሚያስፈልገውን ድፍረት ለማግኘት ተጨማሪ ጊዜ ሊወስድብን ይችላል።
በሌሎች ክርስቲያናዊ ልማዶቻችንም ረገድ ይህ እውነት ነው። ጥሩ ልማድ ‘የአምላክን ቃል በቀንና በሌሊት’ በማንበብ ረገድ አዘውታሪዎች እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። (ኢያሱ 1:8፤ መዝሙር 1:2) አንድ ክርስቲያን ከመተኛቱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ከ20 እስከ 30 ደቂቃዎች የማንበብ ልማድ አለው። በጣም ደክሞት እያለም እንኳ ሳያነብብ ከተኛ ጥሩ እንቅልፍ ስለማይወስደው ከመኝታው ተነስቶ ይህንን መንፈሳዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ይገደዳል። ይህ ጥሩ ልማድ ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ በዓመት አንድ ጊዜ ለበርካታ ዓመታት አንብቦ እንዲጨርስ አስችሎታል።
ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት በሚደረግበት ስብሰባ ላይ የመገኘት ልማድ ነበረው። “እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፣ ሊያነብም ተነሣ።” (ሉቃስ 4:16) ትልቅ ቤተሰብ ያለውና ረዥም ሰዓት የሚሠራው ጆ የተባለው ክርስቲያን ሽማግሌ ያዳበረው ልማድ የስብሰባዎችን አስፈላጊነት እንዲገነዘብና በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ እንዲገኝ ረድቶታል። እንዲህ ይላል:- “ይህ ልማድ ፈተናዎችንና ችግሮችን ስኬታማ በሆነ መንገድ በመቋቋም ረገድ በጣም የሚያስፈልገኝን መንፈሳዊ ኃይል በመስጠት ወደፊት እንድገፋ አስችሎኛል።”—ዕብራውያን 10:24, 25
እንዲህ ያሉት ልማዶች ለሕይወት በሚደረገው ክርስቲያናዊ ሩጫ የግድ አስፈላጊ ናቸው። የይሖዋ ሕዝቦች 2 ጢሞቴዎስ 4:2
በስደት ላይ ከነበሩበት አንድ አገር የተላከ ሪፖርት እንዲህ ይነበባል:- “ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶችና ለእውነት ጥልቅ አድናቆት ያላቸው ወንድሞች ፈተናዎች ሲነሱ ብዙውን ጊዜ ጽኑ አቋም የመያዝ ችግር አይገጥማቸውም። ሆኖም ‘አመቺ በሆነው ጊዜ’ ከስብሰባዎች የሚቀሩ፣ በመስክ አገልግሎት አዘውታሪ ያልሆኑና ጥቃቅን በሚመስሉ ጉዳዮች ረገድ ታማኝነታቸውን የሚያጎድሉ ወንድሞች ብዙውን ጊዜ ‘እንደ እሳት’ ያሉ ፈተናዎች ሲገጥሟቸው አይጸኑም።”—ከመጥፎ ልማድ በመራቅ ጥሩ ልማድ አዳብሩ
‘አንድ ሰው ማዳበር የሚኖርበት በእርሱ ላይ እንዲሰለጥን የሚፈልገውን ልማድ ብቻ ነው’ የሚል አባባል አለ። መጥፎ ልማድ ልክ እንደ ጨቋኝ ጌታ ነው። ያም ሆኖ ሊወገድ አይችልም ማለት አይደለም።
ስቴላ ለተወሰነ ጊዜ ቴሌቪዥን የማየት ሱስ ይዟት ነበር። እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “ካሸነፈኝ ከእያንዳንዱ መጥፎ ልማድ ጀርባ አብዛኛውን ጊዜ ‘ጥሩ’ የሚመስል አንድ ምክንያት ይኖራል።” ቴሌቪዥን የመመልከት ሱስ የጀመራት በዚህ መልኩ ነበር። ቴሌቪዥን የምታየው እንዲያው “ትንሽ ለመዝናናት” ወይም ደግሞ “ለለውጥ ያህል” ብቻ እንደሆነ ለራስዋ ደጋግማ ትናገር ነበር። ሆኖም ይህ ልማዷ ከቁጥጥሯ ውጪ እየሆነ በመምጣቱ ረዥም ሰዓት ቴሌቪዥን በመመልከት ታጠፋ ነበር። “ቢያንስ ይህ መጥፎ ልማድ መንፈሳዊ እድገቴን ገትቶታል” በማለት ተናግራለች። በመጨረሻ ግን ቁርጥ ውሳኔ የታከለበት ጥረት በማድረግ ቴሌቪዥን በመመልከት የምታሳልፈውን ጊዜ መቀነስና ይበልጥ መራጭ መሆን ቻለች። “ሁልጊዜ ይህንን ልማድ ለምን መተው እንደፈለግሁ ለማስታወስ እሞክር ነበር” በማለት ተናግራለች። “በውሳኔዬ መጽናት እንድችል በይሖዋ እታመን ነበር።”
ካራላምቡስ የተባለ አንድ ክርስቲያን መንፈሳዊ እድገት እንዳያደርግ እንቅፋት የሆነበትን ዛሬ ነገ የማለት ልማድ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ዛሬ ነገ ማለት ጎጂ መሆኑን ከተገነዘብኩ በኋላ ሕይወቴን ለመለወጥ መጣር ጀመርኩ። ግብ ሳወጣ እዚህ ግብ ላይ መቼና እንዴት እንደምደርስ አስቀድሜ እወስናለሁ። ውሳኔዎቼንና እቅዶቼን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አዘውታሪ መሆኔ ለችግሩ መፍትሄ ያስገኘ ሲሆን እስካሁንም ጥሩ ልማድ ሆኖልኛል።” በእርግጥም መጥፎ ልማዶች በጥሩ ልማዶች መተካታቸው አማራጭ የለውም።
በተጨማሪም ባልንጀሮቻችን ጥሩ አሊያም መጥፎ ልማዶች እንድናዳብር ሊያደርጉን ይችላሉ። መጥፎ ልማድ ተላላፊ እንደሆነ ሁሉ ጥሩ ልማድም ተላላፊ ነው። ‘ክፉ ባልንጀሮች መልካሙን አመል እንደሚያጠፉ’ ሁሉ ጥሩ ባልንጀሮችም ልንኮርጃቸው በሚገቡ ጤናማ ልማዶች ረገድ ምሳሌ ሊሆኑን ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ከሁሉም በላይ ደግሞ ልማዶቻችን ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያጠነክሩልን አሊያም ሊያዳክሙብን ይችላሉ። ስቴላ እንደሚከተለው ብላለች:- “ጥሩ ልማዶች ካዳበርን ይሖዋን ለማገልገል የምናደርገው ትግል ቀላል ይሆንልናል። ጎጂ ልማዶች ካዳበርን ግን ጥረታችን ይገታል።”
ስለዚህ ጥሩ ልማድ አዳብሩ። እንዲሁም እነዚህ ልማዶች እንዲመሯችሁ ፍቀዱላቸው። እንዲህ ካደረጋችሁ እነዚህ ልማዶች በሕይወታችሁ ውስጥ ብርቱና ጠቃሚ ኃይል ሊሆኑላችሁ ይችላሉ።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልክ እንደ እሳት ልማድም ጠቃሚ ወይ አጥፊ ሊሆን ይችላል
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ የአምላክን ቃል ሲነበብ የማዳመጥ ልማድ ነበረው
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶች ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ያጠነክሩልናል