‘መልካሙንና ክፉውን መለየት’ ትችላላችሁ?
‘መልካሙንና ክፉውን መለየት’ ትችላላችሁ?
“ጌታን ደስ የሚያሰኘው ነገር ምን እንደሆነ መርምሩ።”—ኤፌሶን 5:10 “1980 ትርጉም”
1. በዛሬው ጊዜ ሕይወት ውስብስብ የሆነው በምን መንገድ ነው? ለምንስ?
“አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” (ኤርምያስ 10:23) ማስተዋል የተሞላበት ይህ የኤርምያስ አስተያየት በጊዜያችን የበለጠ ይሠራል። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በተነበየው መሠረት ‘በሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ ስለምንኖር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በየዕለቱ ውሳኔ እንድናደርግ የሚያስገድዱ የተለያዩ ውስብስብ ሁኔታዎች ይገጥሙናል። የምናደርጋቸው ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ ውሳኔዎች በደኅንነታችን ማለትም በአካላዊ፣ በስሜታዊና በመንፈሳዊነታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።
2. እንደ ቀላል ተደርገው የሚታዩት ምርጫዎች የትኞቹ ናቸው? ሆኖም ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች እንዴት ይመለከቷቸዋል?
2 በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምናደርጋቸውን ምርጫዎች የተለመዱ ወይም ቀላል እንደሆኑ አድርገን ልናያቸው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል በየቀኑ የምንለብሰውን ልብስ፣ የምንመገበውን ምግብ፣ አብረውን እንዲሆኑ የምንፈልጋቸውን ሰዎችና ሌሎች እነዚህን የመሰሉ ምርጫዎች እናደርጋለን። እነዚህ ብዙም ማሰብ የማይጠይቁብን ወዲያው የምናደርጋቸው ምርጫዎች ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ በእርግጥ በቀላሉ የምንመለከታቸው ምርጫዎች ናቸው? ራሳችንን የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በአለባበሳችንና በአጋጌጣችን፣ በአመጋገባችንና በመጠጥ አወሳሰዳችን እንዲሁም በአነጋገራችንና በጠባያችን የምናደርገው ምርጫ ምንጊዜም የልዑሉ አምላክ የይሖዋ አገልጋዮች እንደሆንን የሚያሳይ መሆን ስላለበት በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። “የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” የሚሉትን የሐዋርያው ጳውሎስን ቃላት እናስታውሳለን።—1 ቆሮንቶስ 10:31፤ ቆላስይስ 4:6፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10
3. ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻቸው ምርጫዎች የትኞቹ ናቸው?
3 የበለጠ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሌሎች ምርጫዎችም አሉ። ለምሳሌ ያህል ለማግባትም ሆነ ነጠላ ሆኖ ለመኖር የሚደረግ ውሳኔ በአንድ ሰው ሕይወት ላይ ዘላቂ የሆነ ትልቅ ለውጥ ማስከተሉ አይቀርም። ለትዳር ተስማሚ የሆነ የዕድሜ ልክ ጓደኛ መምረጥ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። a (ምሳሌ 18:22) በተጨማሪም በጓደኛና አብረናቸው በምንውላቸው ሰዎች፣ በትምህርት፣ በሥራና በመዝናኛ ረገድ የምናደርገው ምርጫ በመንፈሳዊነታችን ከዚያም በላይ በዘላለማዊ ደህንነታችን ላይ ከፍተኛና ወሳኝ ሚና ይጫወታል።—ሮሜ 13:13, 14፤ ኤፌሶን 5:3, 4
4. (ሀ) ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ችሎታ የትኛው ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች መመርመር ይኖርብናል?
4 እነዚህን ሁሉ ምርጫዎች ለማድረግ ትክክልና ስህተት በሆኑ ነገሮች መካከል ወይም ትክክል መስለው በሚታዩና በእርግጥ ትክክል በሆኑ ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት የማወቅ ችሎታ ማዳበራችን በእርግጥም ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 14:12) ስለዚህ እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን የመለየት ችሎታ ማዳበር የምችለው እንዴት ነው? ውሳኔ በማደርግበት ጊዜ አስፈላጊውን መመሪያ ለማግኘት ወዴት ዞር ማለት እችላለሁ? በጥንትም ሆነ በዛሬ ጊዜ ያሉ ሰዎች በዚህ ረገድ ምን አድርገዋል? ምንስ ውጤት አግኝተዋል?’
በዓለም ያለ ‘ፍልስፍና እና ከንቱ መታለል’
5. የጥንት ክርስቲያኖች የነበሩበት ዓለም ምን ይመስል ነበር?
5 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይኖሩ የነበሩት የግሪካውያንና የሮማውያን ምግባርና አመለካከት በገነነበት ዓለም ውስጥ ነበር። በአንድ በኩል የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ምቾትና ቅንጦት የሞላበት የሮማውያን አኗኗር አለ። በሌላ በኩል ደግሞ በዘመኑ የነበረው የተማረው ኅብረተሰብ በፕላቶ እና በአርስቶትል የፍልስፍና አስተሳሰቦች ብቻ ሳይሆን እንደ ኤፊቆሮሳውያን እና እንደ ኢስጦኢኮች ያሉ አዳዲስ ፈላስፎችም በሚያፈልቋቸው ሐሳቦች ተማርኮ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት አቴንስ ሄዶ በነበረበት ጊዜ ራሳቸውን ከዚህ “ለፍላፊ” ከጳውሎስ የላቁ እንደሆኑ አድርገው ከሚቆጥሩት ከኤፊቆሮሳውያን እና ከኢስጦኢኮች ፈላስፎች ጋር ተገናኝቶ ነበር።—ሥራ 17:18
6. (ሀ) አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች ምን ፈተና ገጥሟቸው ነበር? (ለ) ጳውሎስ ምን በማለት አስጠነቀቀ?
6 እንግዲያው ከጥንት ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶች አካባቢያቸው በነበሩ ሰዎች ልቅ አኗኗርና ሥነ ምግባር ለምን ተማርከው እንደተወሰዱ መረዳት አይከብደንም። (2 ጢሞቴዎስ 4:10) በጊዜው የነበሩት ሰዎች ይመላለሱበት ከነበረው ሥርዓት ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያገኙና በዚህም የተነሳ ትክክለኛ ምርጫ ያደረጉ መስለው ይታዩ ነበር። ዓለም ክርስቲያናዊ ሕይወት ከሚያስገኘው የተሻለ ዋጋ ያለው ነገር የሚያቀርብ ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ” በማለት አስጠንቅቋል። (ቆላስይስ 2:8) ጳውሎስ ይህን የተናገረው ለምንድን ነው?
7. የዓለም ጥበብ በእርግጥ ጥቅም አለው?
7 ጳውሎስ ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጠው በዓለም ተማርከው የነበሩት ሰዎች አስተሳሰብ አደጋ ላይ መውደቁን በመገንዘቡ ነው። በተለይ ‘ፍልስፍና እና ከንቱ መታለል’ በሚሉት መግለጫዎች መጠቀሙ ትኩረት የሚስብ ነው። “ፍልስፍና” የሚለው ቃል ጥሬ ፍቺ “ጥበብን መውደድና መከታተል” ማለት ነው። ይህ በራሱ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በተለይ ደግሞ የምሳሌ መጽሐፍ ትክክለኛ እውቀትንና ጥበብን እንድንፈልግ ያበረታታል። (ምሳሌ 1:1-7፤ 3:13-18) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ‘ፍልስፍናን’ ‘ከከንቱ መታለል’ ጋር አያይዞ ጠቅሷል። በሌላ አባባል ጳውሎስ በዓለም ያለውን ጥበብ ከንቱና አታላይ እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል። ልክ አየር እንደሞላው ፊኛ ሲያዩት ጠንካራ ይመስላል፣ ውስጡ ግን ባዶ ነው። እንደ ‘ፍልስፍናና ከንቱ መታለል’ ባሉ ምንም እርባና በሌላቸው በዓለም አመለካከቶች ላይ ተመሥርቶ ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን ለመምረጥ መሞከር በእርግጥም ከንቱ አልፎ ተርፎም አጥፊ ነው።
“ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ የሚሉ”
8. (ሀ) ሰዎች ምክር ለማግኘት ዞር የሚሉት ወዴት ነው? (ለ) የሚያገኙትስ ምክር ምን ዓይነት ነው?
8 ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የሰው ልጆችን ሕይወት በሚዳስሱ በሁሉም መስኮች ለማለት ይቻላል ቁጥር ስፍር የሌላቸው ባለሙያዎች አሉ። ገንዘብ በማስከፈል ምክር የሚሰጡ የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪዎች፣ የምክር ዓምድ አዘጋጆች፣ ቴራፒስቶች፣ ኮከብ ቆጣሪዎች፣ መናፍስት ጠሪዎችና ሌሎች በርካታ ባለሙያዎች አሉ። ይሁን እንጂ የሚሰጡት ምክር ምን ዓይነት ነው? ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎች ገሸሽ ተደርገው ዘመን አመጣሽ በሆኑ አዳዲስ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ይተካሉ። ለምሳሌ ያህል ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል በተባለ የካናዳ ዋነኛ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ዓምድ መንግሥት “የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን” ሕጋዊ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑን በማስመልከት ሲናገር “በ2000 ዓመት የሚፈቃቀሩና የሚዋደዱ ተጋቢዎችን ተመሳሳይ ፆታ ያላቸው በመሆናቸው ብቻ የመጋባት ምኞታቸውን መንፈግ ተገቢ አይደለም” ብሏል። በአሁኑ ጊዜ ያለው ዝንባሌ መንቀፍ ሳይሆን ተቻችሎ መኖር ነው። ሁሉም አንጻራዊ በሆነ መንገድ የሚታይ ሲሆን ፍጹም ትክክል ወይም ስህተት የሚባል ነገር የለም።—መዝሙር 10:3, 4
9. በማኅበረሰቡ ዘንድ አክብሮት ያተረፉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ምን ሲያደርጉ ይታያሉ?
9 ሌሎች ደግሞ ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ እንደ አርአያቸው አድርገው የሚመለከቱት በኅብረተሰቡ ዘንድ እውቅናን ያተረፉና በገንዘብ የተሳካላቸውን ማለትም ባለጠጋና ዝነኛ የሆኑ ሰዎችን ነው። ሃብታምና ዝነኛ የሆኑ ሰዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ የተከበሩ ሆነው ይታዩ እንጂ እንደ ሃቀኝነትና ታማኝነት ያሉትን በጎ ምግባሮች በአፋቸው ካልሆነ በስተቀር በተግባር አያውቋቸውም። ብዙዎች ሥልጣንና ጥቅም የሚያስገኝላቸው ከሆነ ሕግና የሥነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከመጣስ ወደኋላ አይሉም። አንዳንዶች ዝናንና ተወዳጅነትን ለማትረፍ ሲሉ የሥነ ምግባር ደንቦችን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ አሳፋሪ ድርጊት ይፈጽማሉ። ይህም “ሁሉም ነገር ያስኬዳል” የሚል መርህ የሚከተል ጥቅሙን ብቻ የሚያሳድድና ልል የሆነ ኅብረተሰብ እንዲፈጠር አድርጓል። ታዲያ ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ ሰዎች ግራ ቢጋቡና የሚያደርጉትን ቢያጡ ምን ያስገርማል?—ሉቃስ 6:39
10. ኢሳይያስ መልካምና ክፉ ስለሆኑ ነገሮች የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸው የተረጋገጠው እንዴት ነው?
10 በተሳሳቱ መመሪያዎች ላይ በመመሥረት የሚደረጉ ጥበብ የጎደላቸው ውሳኔዎች በአካባቢያችን የሚታዩ በርካታ አሳዛኝ ውጤቶችን አስከትለዋል። ከእነዚህም መካከል የፈራረሱ ትዳሮችና ቤተሰቦች፣ ዕጽ መውሰድና የአልኮል መጠጦችን አለገደብ መጠጣት፣ ሥርዓት አልበኛ የሆኑ ወጣቶች፣ ሴሰኝነት፣ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ጥቂቶቹ ናቸው። ደግሞስ ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚያስችሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ወይም መመሪያዎችን ችላ ያሉ ሰዎች ከዚህ የተለየ ምን ነገር ሊጠብቁ ይችላሉ? (ሮሜ 1:28-32) ልክ ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው ነው:- “ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፣ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፣ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው! በዓይናቸው ጥበበኞች በነፍሳቸውም አስተዋዮች ለሆኑ ወዮላቸው!”—ኢሳይያስ 5:20, 21
11. ትክክልና ስህተት የሆነውን በመለየት ረገድ በራስ ላይ መደገፍ ጥበብ የማይሆነው ለምንድን ነው?
11 ‘በራሳቸው ዓይን ጥበበኞች’ የነበሩት የጥንቶቹ አይሁዳውያን በአምላክ ዘንድ ተጠያቂዎች መሆናቸው ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን በመለየት ረገድ በራሳችን ከመታመን እንድንርቅ ሊያደርገን ይገባል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች “ልብህ የሚልህን ስማ፣” ወይም “ትክክል መስሎ የታየህን አድርግ” የሚል አስተሳሰብ አላቸው። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ትክክል ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?” በማለት በግልጽ ስለሚናገር ትክክል አይደለም። (ኤርምያስ 17:9) ተንኮለኛና ክፉ የሆነ ሰው በሚሰጥህ መመሪያ ላይ ተማምነህ ውሳኔ ታደርጋለህ? እንደማታደርግ የታወቀ ነው። እንዲያውም የምታደርገው ነገር ሁሉ እሱ ከሚነግርህ ተቃራኒ የሆነውን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ ነው፤ በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል” በማለት ማሳሰቢያ የሚሰጠንም በዚህ የተነሳ ነው።—ምሳሌ 3:5-7፤ 28:26
በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ነገር ማወቅ
12. ‘የአምላክ ፈቃድ’ ምን እንደሆነ መፈተን የሚኖርብን ለምንድን ነው?
12 ትክክልና ስህተት የሆነውን በተመለከተ በዓለም ጥበብም ሆነ በራሳችን ላይ መደገፍ የማይኖርብን ከሆነ ማድረግ ያለብን ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን የሚከተለውን ግልጽና የማያሻማ ምክር ልብ በል:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12:2) የአምላክን ፈቃድ ፈትነን ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው? ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው” በማለት ቀጥተኛ ሆኖም ጠንካራ ምክንያት ይሰጠናል። (ኢሳይያስ 55:9) ስለዚህ እንዲሁ በራሳችን ማስተዋል ወይም ስሜት ከመመራት ይልቅ ‘ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እንድንመረምር’ ተመክረናል።—ኤፌሶን 5:9-10
13. በዮሐንስ 17:3 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት አምላክን ደስ የሚያሰኘውን የማወቅን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሎ በመናገር የዚህን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ዮሐንስ 17:3) ‘ማወቅ’ የሚለው መግለጫ እንዲሁ አንድን ነገር ከማወቅ የበለጠ ትርጉም አለው። ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ እንደሚለው ‘ማወቅ’ የሚለው ቃል “በሚያውቀው ሰውና በሚታወቀው ነገር መካከል ያለውን ዝምድና ያመለክታል። በዚህ ረገድ የሚታወቀው ነገር ለሚያውቀው ሰው ከፍ ያለ ዋጋ ወይም ጥቅም እንዳለው ሁሉ በመካከላቸው የተመሠረተው ዝምድናም የዚያኑ ያህል ዋጋ ወይም ጥቅም አለው።” ከአንድ ሰው ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት ማለት ግለሰቡን እንዲያው ሰውዬውን ወይም ስሙን ብቻ ማወቅ ማለት አይደለም። ግለሰቡ የሚወድደውንና የሚጠላውን ማወቅ፤ ምግባሩንና የአቋም ደረጃዎቹን ማወቅና እነዚህን ማክበርንም ያጠቃልላል።—1 ዮሐንስ 2:3፤ 4:8
የማስተዋል ችሎታችንን ማሠልጠን
14. ጳውሎስ በመንፈሳዊ ሕፃናት በሆኑትና በጎለመሱ ሰዎች መካከል ያለው ዋነኛ ልዩነት ምንድን ነው ብሏል?
14 ታዲያ ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች የመለየት ችሎታ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈው መልእክት መልሱን ይሰጠናል። እንዲህ በማለት ጻፈ:- “ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅም። ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ለሚያሰለጥኑት ለጎለመሱ ሰዎች ነው።” እዚህ ላይ ጳውሎስ ቀደም ባሉት ቁጥሮች ላይ ‘ስለ እግዚአብሔር ቃላት የሚናገሩ መሠረታዊ ትምህርቶች’ በማለት የገለጸውን ‘ወተት’ ‘መልካሙንና ክፉውን ለመለየት የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት የሚያሰለጥኑ የጎለመሱ ሰዎች’ ከሚመገቡት “ጠንካራ ምግብ” ጋር አወዳድሯል።—ዕብራውያን 5:12-14 NW
15. የአምላክን ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ይህም ማለት በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሰፈራቸውን የአቋም ደረጃዎች በትክክል ለማወቅ መጣር አለብን ማለት ነው። ይህን አድርግ ይህን አታድርግ የሚሉ ዝርዝር ደንቦች እንዲሰጡን መጠበቅ አይኖርብንም። መጽሐፍ ቅዱስም እንዲህ ያለ መጽሐፍ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ገልጿል:- “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ከዚህ ትምህርት፣ ተግሣጽና ምክር ጥቅም ለማግኘት አእምሯችንንና የማሰብ ችሎታችንን ማሠራት አለብን። እንዲህ ማድረጉ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም እንኳ በመጨረሻ ‘ለመልካም ሥራ ሁሉ ሙሉ በሙሉ የታጠቅንና የተዘጋጀን ስለሚያደርገን’ የሚያስቆጭ አይደለም።—ምሳሌ 2:3-6
16. የማስተዋል ችሎታን ማሰልጠን ሲባል ምን ማለት ነው?
16 ከዚያም ጳውሎስ እንዳመለከተው የጎለመሱ ሰዎች ‘የማስተዋል ችሎታቸው መልካሙንና ክፉውን መለየት እንዲችል ያሰለጥኑታል።’ ፍሬ ነገሩ ያለው እዚህ ላይ ነው። ‘የማስተዋል ችሎታቸውን ያሰለጥኑታል’ የሚለው መግለጫ ቃል በቃል ሲተረጎም “(ጅምናስቲክ እንደሚሠራ ስፖርተኛ) የስሜት አባላካላትን ማሠልጠን” ማለት ነው። (ኪንግደም ኢንተርሊኒየር ትርጉም) ከፍተኛ ልምድ ያለው የጅምናስቲክ ስፖርተኛ በጅምናስቲክ መሥሪያው ላይ ምንም ሳይደናቀፍ ወይም ሳይወድቅ በቅልጥፍና ሲገለባበጥ ሲታይ የስበት ወይም ሌላ የተፈጥሮ ሕግ በእሱ ላይ የማይሰራ ይመስላል። ሰውነቱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ስለሚችል እግሮቹንና እጆቹን የት ማሳረፍ እንዳለበት ማሰብ እንኳ ሳያስፈልገው የጀመረውን ስፖርት ያጠናቅቃል። ይህ ሁሉ እንዲሁ የሚገኝ ሳይሆን የከፍተኛ ሥልጠናና የረዥም ጊዜ ልምምድ ውጤት ነው።
17. ልክ እንደ ጅምናስቲክ ስፖርተኛ የሆንነው በምን መንገድ ነው?
17 የምናደርጋቸው ውሳኔዎችና ምርጫዎች ሁልጊዜ ትክክል እንዲሆኑልን የምንፈልግ ከሆነ በመንፈሳዊ አነጋገር እኛም እንደ አንድ የጅምናስቲክ ስፖርተኛ መሠልጠን አለብን። ስሜቶቻችንንና የሰውነት አካላችንን ሁልጊዜ መቆጣጠር መቻል ይኖርብናል። (ማቴዎስ 5:29, 30፤ ቆላስይስ 3:5-10) ለምሳሌ ያህል ዓይኖችህ የብልግና ፊልሞችንም ሆነ ጽሑፎችን እንዳያዩ ወይም ጆሮዎችህ ወራዳ ሙዚቃ ወይም ንግግር እንዳይሰሙ ትገስጻቸዋለህ? እንደነዚህ ያሉ ንጹህ ያልሆኑ ነገሮች በዙሪያችን እንደሞሉ እሙን ነው። ሆኖም በልባችንና በአእምሯችን ውስጥ ሥር እንዳይሰድዱ መከላከል የእኛ ፋንታ ነው። እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን መዝሙራዊ መምሰል እንችላለን:- “በዓይኔ ፊት ክፉን ነገር አላኖርሁም፤ ሕግ ተላላፊዎችን ጠላሁ። . . . ዓመፅን የሚናገር በዓይኔ ፊት አይቀናም።”—መዝሙር 101:3, 7
የማስተዋል ችሎታችሁን በማሠራት አሠልጥኑት
18. ጳውሎስ የማስተዋል ችሎታን ስለማሰልጠን በሰጠው መግለጫ ውስጥ የሚገኘው ‘ማሠራት’ የሚለው መግለጫ ምን መልእክት ያስተላልፋል?
18 የማስተዋል ችሎታችን ትክክልና ስህተት የሆነውን መለየት ይችል ዘንድ ማሠልጠን የምንችለው ‘በማሠራት’ እንደሆነ አስታውስ። በሌላ አባባል ውሳኔ የሚጠይቅ ሁኔታ በገጠመን ቁጥር የማሰብ ችሎታችን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው እንዴትስ በሥራ ላይ ላውላቸው እችላለሁ ብሎ እንዲጠይቅ ማድረግ ማለት ነው። ‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ የሚያዘጋጃቸውን መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ ጽሑፎችን ተጠቅመህ ምርምር የማድረግ ልማድ አዳብር። (ማቴዎስ 24:45) እርግጥ ነው የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲረዱን ልንጠይቅ እንችላለን። የሆነ ሆኖ መመሪያና መንፈሱን እንዲሰጠን ይሖዋን በጸሎት በመጠየቅ የአምላክን ቃል ለማጥናት በግላችን የምናደርገው ጥረት ውሎ አድሮ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኝልናል።—ኤፌሶን 3:14-19
19. የማስተዋል ችሎታችንን ደረጃ በደረጃ ካሠለጠንን ምን በረከቶችን ልናገኝ እንችላለን?
19 የማስተዋል ችሎታችንን ደረጃ በደረጃ የምናሠለጥንበት ዋነኛ ዓላማ የሚከተለው ነው:- “እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኰል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም።” (ኤፌሶን 4:14) በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ነገሮች አውቀንና ተረድተን የምናደርገው ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ለእኛ ጥቅም የሚያመጣ፣ የእምነት ባልደረቦቻችንን የሚያንጽና ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰማያዊ አባታችንን የሚያስደስት ይሆናል። (ምሳሌ 27:11) በዚህ አስጨናቂ ዘመን ይህ ምንኛ በረከትና ጥበቃ ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቶማስ ሆልምስ እና ሪቻርድ ራ የተባሉ ሐኪሞች በሰዎች ሕይወት ላይ ውጥረት በማስከተል ረገድ ከ40 የሚበልጡ ዝርዝሮችን በቅደም ተከተል ያስቀመጡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ተርታ የያዙት የትዳር ጓደኛ ሞት፣ ፍቺና መለያየት ሲሆኑ ማግባት ሰባተኛውን ተርታ ይዟል።
ልታብራራ ትችላለህ?
• ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ ምን ዓይነት ችሎታ ሊኖረን ይገባል?
• ትክክልና ስህተት የሆነውን በመወሰን ረገድ ታዋቂ ከሆኑ ሰዎች መመሪያ መጠበቅ ወይም በራሳችን ስሜት ላይ መደገፍ ጥበብ ያልሆነው ለምንድን ነው?
• ውሳኔ ስናደርግ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ምን እንደሆነ ማረጋገጥ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
• ‘የማስተዋል ችሎታን ማሠልጠን’ ሲባል ምን ማለት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለጠጎችና ታዋቂ ከሆኑ ሰዎች መመሪያ መጠበቅ ከንቱ ነው
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ አንድ የጅምናስቲክ ስፖርተኛ መላውን አካላችንንና ስሜቶቻችንን መቆጣጠር መቻል ይኖርብናል