በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ እንባዋን አበሰላት

አምላክ እንባዋን አበሰላት

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት

አምላክ እንባዋን አበሰላት

ሕይወታቸውን ከይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር አስማምተው የሚኖሩ ሁሉ በእጅጉ ይባረካሉ። አስፈላጊውን ለውጥ ማድረጉ ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም እርዳታና ማበረታቻ ማግኘት ይቻላል። (መዝሙር 84:​11) ከደቡብ ምሥራቅ እስያ የተገኘው የሚከተለው ተሞክሮ ይህንን ያሳያል።

ለእረፍት ከፈረንሳይ የመጣች አንዲት ምሥክር ኪም a ለተባለች የሱቅ ባለቤት ይሖዋ ለምድር ስላለው ዓላማ ነገረቻት። በተጨማሪም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ ሰጠቻት። ኪም መጽሐፉን ስታገላብጥ “እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል” የሚለውን ሐረግ ተመለከተች። (ራእይ 21:​4) ኪም “ይህ ጥቅስ በጣም ነካኝ” በማለት ታስታውሳለች። “ቀኑን ሙሉ ሱቅ ውስጥ ስስቅና ስጫወት ለሚያየኝ ሁሉ ማታ ቤቴ ገብቼ እንቅልፍ እስኪወስደኝ ድረስ የማለቅስ አልመስልም።” ኪም የምታለቅስበትን ምክንያት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “ከአንድ ሰው ጋር ለ18 ዓመታት አብሬ ብኖርም እርሱ ሊያገባኝ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ደስተኛ አልነበርኩም። ከእንዲህ ዓይነቱ አኗኗር መላቀቅ ብፈልግም አብሬው ብዙ ዓመታት ስለቆየሁ እርምጃ ለመውሰድ ወኔ አጣሁ።”

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኪም ሊን ከተባለች የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ኪም “የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ተግባራዊ የማድረግ ጉጉት ነበረኝ” በማለት ትናገራለች። “ለምሳሌ ከቤተሰቦቼ ተቃውሞ ቢያስከትልብኝም የቀድሞ አባቶቼን ማምለኬን አቆምኩ። ጋብቻችንንም ሕጋዊ ለማድረግ ሞክሬ ነበር። እርሱ ግን ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሁሉ ፈረንሳይ የምትኖረው ምሥክር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች መላኳን የቀጠለች ሲሆን ሊንም ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ሆናልኝ ነበር። የእነዚህ እህቶች ትዕግሥትና ፍቅራዊ ድጋፍ የሰውዬውን እውነተኛ ማንነት እስክገነዘብ ድረስ በጽናት እንድቀጥል ረድቶኛል። ሰውዬው 5 ‘ሚስቶችና’ 25 ልጆች እንዳሉት ተገነዘብኩ! ይህንን ማወቄ ጥዬው ለመሄድ እንድቆርጥ ድፍረት ሰጠኝ።

ትልቅና ምቹ መኖሪያ ለምዶ ትንሽ ቤት ውስጥ መኖር ቀላል አልነበረም። በተጨማሪም የቀድሞው ጓደኛዬ ተመልሼ ከእርሱ ጋር እንድኖር ተጭኖኝ ነበር። እንዲያውም እምቢ ካልኩ ፊቴን በአሲድ እንደሚያበላሸው ዝቶብኝ ነበር። ሆኖም በይሖዋ እርዳታ ትክክል የሆነውን ማድረግ ችዬአለሁ።” ኪም እድገት ማድረጓን በመቀጠል በመጨረሻ ሚያዝያ 1998 ተጠመቀች። ሁለት እህቶቿና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ወንድ ልጅዋ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምረዋል።

ኪም “ሕይወቴ ተስፋ እንደሌለው አድርጌ አስብ ነበር” በማለት ተናግራለች። “ዛሬ ግን ደስተኛ ነኝ። ማታ ማታ ማልቀሴንም ትቼያለሁ። ይሖዋ ገና ከወዲሁ እንባዬን አብሶልኛል።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሞቹ ተቀይረዋል።