በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታምንበት ነገር በምን ላይ የተመሠረተ ነው?

የምታምንበት ነገር በምን ላይ የተመሠረተ ነው?

የምታምንበት ነገር በምን ላይ የተመሠረተ ነው?

ማመን ማለት “እውነት፣ ሐቅ ወይም ተጨባጭ እንደሆነ አድርጎ መቀበል” ማለት ነው። የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ እያንዳንዱ ሰው ያለውን “የሐሳብ፣ የሕሊናና የሃይማኖት ነፃነት መብት” ያስከብራል። ይህ መብት አንድ ሰው ከፈለገ “ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን ለመቀየር” ያለውን ነፃነት ያካትታል።

ይሁን እንጂ ማንኛውም ሰው ቢሆን ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን መለወጥ የሚፈልግበት ምክንያት ምን ይሆን? “የራሴ እምነት አለኝ፤ ሌላ አልፈልግም” የሚለው አነጋገር የተለመደ ነው። ብዙ ሰዎች ትክክል ያልሆኑ አመለካከቶች እንኳ በማንም ላይ ጉዳት እንደማያስከትሉ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል ምድር ጠፍጣፋ ነች ብሎ የሚያምን ሰው በራሱም ሆነ በሌላ ሰው ላይ የሚያመጣው ጉዳት የለም። አንዳንዶች “የአመለካከት ልዩነት መኖሩን በጸጋ አምነን መቀበል አለብን” ይላሉ። ይህ ምንጊዜም ጥበብ ነውን? አንድ ዶክተር ከሥራ ባልደረባዎቹ አንዱ በሬሳ ክፍል አስከሬን ሲነካካ ቆይቶ በቀጥታ አልጋ ወደያዙ ታካሚዎች ሄዶ ማከም ችግር የለውም የሚል እምነት ቢኖረው ዝም ብሎ ይቀበለዋል?

በሃይማኖት ረገድ የተሳሳተ እምነት መከተል ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን ታሪክ ያሳያል። በመካከለኛው ዘመን በተካሄደው ቅዱስ የመስቀል ጦርነት ተብሎ በሚጠራው ውጊያ የሃይማኖት መሪዎች “ቀናኢ ክርስቲያኖችን ጭካኔ ለተሞላበት ጭፍጨፋ ሲያነሳሱ” የደረሰውን አሰቃቂ ሁኔታ አስታውስ። ወይም “በሰይፋቸው እጀታ ላይ የቅዱሳንን ስሞች ይከትቡ እንደነበረው የመካከለኛው ዘመን ጦረኞች ሁሉ በጠመንጃቸው ሰደፍ ላይ የማርያምን ስዕል የሚለጥፉትን” በቅርቡ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ላይ የተሰለፉትን የዘመናችንን “ክርስቲያን” ታጣቂዎች ተመልከት። እነዚህ ቀናኢ ክርስቲያኖች ትክክል እንደሆኑ አምነው ነበር። ሆኖም ከእነዚህም ሆነ ከሌሎች ሃይማኖታዊ ግጭቶችና ጦርነቶች በስተጀርባ አንድ ትልቅ ችግር አለ።

ይህን ያህል ትርምስና ግጭት ያለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስ ‘ዓለሙን ሁሉ ማሳቱ’ ያስከተለው ውጤት እንደሆነ ይነግረናል። (ራእይ 12:​9፤ 2 ቆሮንቶስ 4:​4፤ 11:​3) ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ የሃይማኖት ሰዎች ‘አሳሳች ተአምራትንና ምልክቶችን በሚያደርገው’ በሰይጣን በመታለላቸው ምክንያት ‘ጥፋት እንደሚጠብቃቸው’ አስጠንቅቋል። ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች “ለመዳን የሚያበቃቸውን እውነት ስላልወደዱ” ተታልለው ‘ውሸት የሆነውን ለማመን’ ይዳረጋሉ ብሏል። (2 ተሰሎንቄ 2:​9-12የ1980 ትርጉም) ውሸት የሆነን ነገር የማመን አጋጣሚህን ማጥበብ የምትችለው እንዴት ነው? ለመሆኑ አሁን የምትከተለውን እምነት የያዝከው በምን ምክንያት ነው?

ከወላጆችህ የወረስከው ነውን?

ምናልባት ቤተሰቦችህ የሚያምኑባቸውን ነገሮች ከልጅነትህ ጀምረህ ስትከተል ቆይተህ ይሆናል። ይህ ጥሩ ሊሆን ይችላል። አምላክ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ ይፈልጋል። (ዘዳግም 6:​4-9፤ 11:​18-21) ለምሳሌ ያህል ወጣቱ ጢሞቴዎስ እናቱና አያቱ የሰጡት ትምህርት በእጅጉ ጠቅሞታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:​5፤ 3:​14, 15) ቅዱሳን ጽሑፎች ወላጆች ለሚያምኑባቸው ነገሮች አክብሮት ማሳየትን ያበረታታሉ። (ምሳሌ 1:​8፤ ኤፌሶን 6:​1) ሆኖም ፈጣሪያችሁ ወላጆቻችሁ የሚያምኑትን ሁሉ በደፈናው እንድትቀበሉ ይፈልጋል ማለት ነውን? እንደ እውነቱ ከሆነ የቀድሞዎቹ ትውልዶች ያመኑበትንና ያደረጉትን ሁሉ በጭፍን መከተል አደገኛ ሊሆን ይችላል።​—⁠መዝሙር 78:​8፤ አሞጽ 2:​4

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተነጋገረች አንዲት ሳምራዊት ሴት ያደገችው በሳምራውያን ሃይማኖት ነበር። (ዮሐንስ 4:​20) ኢየሱስ የፈለገችውን የማመን ነፃነቷን ቢያከብርላትም “እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ” ብሏታል። እንዲያውም አብዛኞቹ ሃይማኖታዊ እምነቶቿ ስህተት ስለሆኑ አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማለትም “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ ከፈለገች በምታምንባቸው ነገሮች ረገድ ለውጥ ማድረግ እንዳለባት ነግሯታል። ከፍ አድርጋ ትመለከተው የነበረውን እምነት የሙጥኝ ብላ ከመያዝ ይልቅ እሷና ሌሎች መሰሎቿ ከጊዜ በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለተገለጠው ‘ሃይማኖት መታዘዝ’ ነበረባቸው።​—⁠ዮሐንስ 4:​21-24, 39-41፤ ሥራ 6:​7

በትምህርት ያገኘኸው ነውን?

በተለያዩ የእውቀት ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ በርካታ መምህራንና ጠበብት ከፍተኛ አክብሮት ሊቸራቸው ይገባል። ሆኖም የታሪክ መዝገብ ፈጽሞ የተሳሳተ አመለካከት በነበራቸው የታወቁ ምሁራን የተሞላ ነው። ለምሳሌ ያህል ግሪካዊው ፈላስፋ አርስቶትል በሳይንሳዊ ጉዳዮች ረገድ የጻፋቸውን ሁለት መጻሕፍት በተመለከተ የታሪክ ምሁር የሆኑት በርትራንድ ራስል “በሁለቱም ላይ ከዘመናዊ ሳይንስ አንጻር ሲታይ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችል አንድም ሐረግ አይገኝም” ሲሉ ተናግረዋል። በዘመናችን ያሉ ጠበብት እንኳ አብዛኛውን ጊዜ ፈጽሞ ከእውነታው የራቀ ድምዳሜዎች ላይ ይደርሳሉ። በ1895 ብሪታኒያዊው ሳይንቲስት ሎርድ ከልቪን “ከአየር የበለጠ ክብደት ያለው ተንሳፋፊ መሣሪያ ሊኖር አይችልም” ሲሉ በእርግጠኝነት ተናግረው ነበር። ስለዚህ አስተዋይ የሆነ ሰው አንድን ጉዳይ በተመለከተ አንድ ምሁር ትክክል ነው ብሎ በእርግጠኝነት ስለተናገረ ብቻ እንዲሁ በጭፍን አምኖ አይቀበልም።​—⁠መዝሙር 146:​3

ሃይማኖታዊ ትምህርትን በተመለከተም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከሃይማኖታዊ መምህራን በሚገባ የተማረ ከመሆኑም በላይ ‘ለአባቶቹ ወግ ከመጠን ይልቅ ይቀና’ ነበር። ሆኖም የቀድሞ አባቶቹ ያምኑባቸው ለነበሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ ለቆዩ እምነቶች የነበረው ቅንዓት በእርግጥ ለችግር ዳርጎታል። ‘የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ እንዲያሳድድና እንዲያጠፋ’ አነሳስቶታል። (ገላትያ 1:​13, 14፤ ዮሐንስ 16:​2, 3) ከዚያም ይባስ ብሎ ጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምን የሚያስችሉትን ሁኔታዎች ለረጅም ጊዜ አልቀበልም በማለት ‘የመውጊያውን ብረት መቃወሙን’ ቀጠለ። ጳውሎስ እምነቱን እንዲያስተካክል ለማድረግ ኢየሱስ ራሱ ተአምራዊ በሆነ መንገድ በቀጥታ ጣልቃ መግባቱ የግድ ሆኗል።​—⁠ሥራ 9:​1-6፤ 26:​14

መገናኛ ብዙሃን ተጽዕኖ አሳድሮብሃልን?

ምናልባት መገናኛ ብዙሃን በአመለካከትህ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል። ብዙ ሰዎች ጠቃሚ የሆነ መረጃ እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው በመገናኛ ብዙሃን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት መኖሩ ያስደስታቸዋል። ይሁን እንጂ መገናኛ ብዙሃንን እንደፈለጉ መጠቀሚያ ማድረግ የሚችሉ ደግሞም አብዛኛውን ጊዜ ይህን የሚያደርጉ ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች አሉ። በአብዛኛው የሚቀርበው ነገር አስተሳሰብህን ቀስ በቀስ መቀየር የሚችል የተዛባ መረጃ ነው።

መገናኛ ብዙሃን በርካታ ቁጥር ያለውን ታዳሚ ለመማረክ ወይም ለመሳብ ከመፈለጋቸውም በተጨማሪ ስሜት ቀስቃሽና ለየት ያለ ነገር ለሕዝብ የማቅረብ ዝንባሌ አላቸው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ብዙሃኑ እንዲሰማው ወይም እንዲያነብበው የማይደረግ ጉዳይ በዛሬው ጊዜ የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል። ነባራዊ የሆኑ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጥቃት እየደረሰባቸውና ቀስ በቀስ እየተሸረሸሩ ናቸው። የሰዎች አስተሳሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ በመሄድ ላይ ነው። “ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ” ብለው ማመን ጀምረዋል።​—⁠ኢሳይያስ 5:​20፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10

ለማመን የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ማግኘት

እምነትን በሰዎች ሐሳብና ፍልስፍና ላይ መገንባት በአሸዋ ላይ ከመገንባት ተለይቶ አይታይም። (ማቴዎስ 7:​26፤ 1 ቆሮንቶስ 1:​19, 20) ታዲያ እምነትህን በእርግጠኝነት መመሥረት የምትችለው በምን ላይ ነው? አምላክ በዙሪያህ ያለውን ዓለም የምትመረምርበትንና መንፈሳዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ጥያቄዎች ማንሳት የምትችልበትን የማሰብ ችሎታ እስከሰጠህ ድረስ ለጥያቄዎችህ ትክክለኛ መልስ የምታገኝበትን መንገድ ጭምር ይሰጣል ቢባል ምክንያታዊ አይሆንም? (1 ዮሐንስ 5:​20) አዎን፣ እንደሚሰጥ የተረጋገጠ ነው! ሆኖም በአምልኮ ጉዳዮች ረገድ እውነት፣ ሐቅና ተጨባጭ የሆነውን ነገር ማረጋገጥ የምትችለው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ማድረግ የምትችልበትን ብቸኛውን መሠረት እንደሚያስገኝ አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን።​—⁠ዮሐንስ 17:​17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17

በዚህ ጊዜ አንድ ሰው “ቆይ እንጂ፣ በዓለም ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ግጭትና ብጥብጥ ያስከተሉት በመጽሐፍ ቅዱስ እናምናለን የሚሉ ሰዎች አይደሉም እንዴ?” ይል ይሆናል። እውነት ነው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እንመራለን የሚሉ የሃይማኖት መሪዎች ግራ የሚያጋቡና እርስ በርስ የሚቃረኑ በርካታ ሐሳቦች ማፍለቃቸው አይካድም። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ሊሆን የቻለው የሚያምኑባቸው ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ባለመሆናቸው ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የሚያጠፋ ኑፋቄን” የሚፈጥሩ “ሐሰተኞች ነቢያት” እና “ሐሰተኞች አስተማሪዎች” ሲል ገልጿቸዋል። ጴጥሮስ ከአድራጎታቸው የተነሳ “የእውነት መንገድ ይሰደባል” ሲል ተናግሯል። (2 ጴጥሮስ 2:​1, 2) ጴጥሮስ እንዲህ ሲልም ጽፏል:- “እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ . . . ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።”​—⁠2 ጴጥሮስ 1:​19፤ መዝሙር 119:​105

መጽሐፍ ቅዱስ የምናምንባቸውን ነገሮች በውስጡ ከሚገኙት ትምህርቶች ጋር እንድናመሳክር ያበረታታናል። (1 ዮሐንስ 4:​1) ይህን መጽሔት የሚያነብቡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ማድረጋቸው ለሕይወታቸው ዓላማና ጽናት እንዳስገኘላቸው ሊመሰክሩ ይችላሉ። ስለዚህ ልበ ሰፊ እንደነበሩት የቤሪያ ሰዎች ሁን። በምን ማመን እንዳለብህ ከመወሰንህ በፊት ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ በጥንቃቄ መርምር።’ (ሥራ 17:​11) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ማድረግ እንድትችል ለመርዳት ደስተኞች ናቸው። እርግጥ ነው፣ በምን ማመን እንደምትፈልግ የምትወስነው አንተው ነህ። ይሁን እንጂ የምታምንበት ነገር በሰው ጥበብና ፍላጎቶች ላይ ሳይሆን አምላክ በገለጸው የእውነት ቃል ላይ የተመሠረተ መሆኑን ማረጋገጥህ የጥበብ መንገድ ነው።​—⁠1 ተሰሎንቄ 2:​13፤ 5:​21

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እምነትህን በእርግጠኝነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መመሥረት ትችላለህ