በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፈለግኸውን ለማመን ያለህ መብት

የፈለግኸውን ለማመን ያለህ መብት

የፈለግኸውን ለማመን ያለህ መብት

የፈለግከውን የማመን መብትህን ሳታደንቅ እንደማትቀር የታወቀ ነው። ሁሉም ሰው ለማለት ይቻላል ይህን መብቱን ከፍ አድርጎ ይመለከታል። ስድስት ቢልዮን የሚሆኑት የምድራችን ነዋሪዎች በዚህ መብት በመጠቀም ብዙ ዓይነት አመለካከት አዳብረዋል። በፍጥረት ሥራዎች ላይ የቀለም፣ የቅርጽ፣ የልስላሴ፣ የጣዕም፣ የጠረንና የድምፅ ልዩነቶች እንዳሉ ሁሉ የአመለካከት ልዩነቶችም አብዛኛውን ጊዜ ሕይወት የሚጥም፣ የሚያስደስትና የሚያረካ እንዲሆን ያደርጋሉ። በእርግጥም ይህን የመሰለ የዓይነት ልዩነት መኖሩ ሕይወት የማይሰለችና አስደሳች እንዲሆን ያስችላል።​—⁠መዝሙር 104:​24

ሆኖም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አንዳንድ አመለካከቶች የተለዩ ብቻ ሳይሆኑ ጎጂም ናቸው። ለምሳሌ ያህል በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ አንዳንድ ሰዎች አይሁዶችና ፍሪማሶኖች “ክርስትናን የማኮላሸት እና ጣምራ አገዛዝ በመመሥረት ዓለም አቀፍ ግዛት የማቋቋም ዕቅድ አላቸው” የሚል አመለካከት ይዘው ነበር። የዚህ አንዱ ምንጭ ፕሮቶኮልስ ኦቭ ዘ ለርንድ ኤልደርስ ኦቭ ዛዮን የሚል ርዕስ ያለው ፀረ-​ሴማዊ ትራክት ነው። ትራክቱ የዕቅዱ አካል እንደሆኑ አድርጎ ከጠቀሳቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ የአሕዛብን ብልጽግና በአጭር ጊዜ ለማውደም ይቻል ዘንድ ከፍተኛ ቀረጥ መጣል፣ የጦር መሣሪያ በስፋት ማምረትና ታላላቅ የሞኖፖል ይዞታዎች እንዲመሠረቱ ማበረታታት እንዲሁም ሥርዓተ ትምህርቱን እንደ መሣሪያ በመጠቀም ‘አሕዛብ የማሰብ ችሎታ የሌላቸው እንስሳት እንዲሆኑ’ ማድረግ አልፎ ተርፎም የአይሁድ ሽማግሌዎች ‘ማንኛውንም የተቃዋሚዎች ቡድን ድምጥማጡን በማጥፋት መቅጨት’ እንዲችሉ በመሬት ውስጥ ለውስጥ የሚሄድ የባቡር መስመር በመዘርጋት ዋና ዋና ከተማዎችን ማገናኘት ናቸው።

በእርግጥ እነዚህ አባባሎች ፀረ-ሴማዊ ስሜት ለማቀጣጠል የተቀነባበሩ የውሸት ወሬዎች ነበሩ። የብሪቲሽ ሙዚየም ባልደረባ የሆኑት ማርክ ጆንስ ‘ይህ ርካሽ የፈጠራ ወሬ’ በ1903 ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ጋዜጣ አምድ ላይ ከወጣበት ‘ከሩሲያ ተነስቶ በሰፊው ተሰራጨ’ ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ጉዳይ ግንቦት 8, 1920 በለንደኑ ዘ ታይምስ ላይ ወጣ። ከአንድ ዓመት በላይ ካለፈ በኋላ ዘ ታይምስ ትራክቱ የፈጠራ ወሬ መሆኑን አጋለጠ። በዚህ መሀል ግን ወሬው የሰዎችን አመለካከት አዛብቷል። ጆንስ ‘እንደዚህ ዓይነቱን የውሸት ወሬ መግታት አስቸጋሪ ነው’ ብለዋል። አንዴ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ካገኘ በጥላቻ የተሞላ፣ መርዘኛና ጎጂ የሆነ አንድ ዓይነት አመለካከት እንዲቀረጽ ያደርጋል። ይህ የ20ኛው መቶ ዘመን ታሪክ እንደሚያሳየው አብዛኛውን ጊዜ ከባድ መዘዝ ያስከትላል።​—⁠ምሳሌ 6:​16-19

እምነትና እውነት

እርግጥ ነው፣ የተሳሳተ አመለካከት እንዲይዙ የሚያደርገው ሆን ተብሎ የተነገረ ውሸት ብቻ ነው ማለት አይደለም። ነገሮችን በተሳሳተ መንገድ የምንረዳባቸው ጊዜያት አሉ። ትክክል እንደሆነ ያመኑበትን ነገር በማድረጋቸው ያለ ጊዜያቸው የተቀጩ ስንቶቹ ናቸው? በተጨማሪም አብዛኛውን ጊዜ እንዲሁ አምነን መቀበል ስለፈለግን ብቻ የምናምነው ነገር አለ። አንድ ፕሮፌሰር እንደተናገሩት ሳይንቲስቶች እንኳ ሳይቀር “አብዛኛውን ጊዜ ራሳቸው ላረቀቋቸው ንድፈ ሐሳቦችና ድምዳሜዎች ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ።” የራሳቸው አመለካከት ነገሮችን ያለ አድልዎ እንዳይመለከቱ ይጋርድባቸዋል። ከዚያም የተሳሳተ አመለካከታቸውን የሚደግፍ ማስረጃ ለማግኘት ዕድሜ ልካቸውን በከንቱ ይደክሙ ይሆናል።​—⁠ኤርምያስ 17:​9

ከፍተኛ ቅራኔዎች በሚታዩባቸው ሃይማኖታዊ አመለካከቶችም ረገድ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ተከስተዋል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​1፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:​3, 4) አንድ ሰው በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ይኖረው ይሆናል። ሌላው ደግሞ ይህ ሰው ሃይማኖታዊ እምነት የያዘው እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ነው ይላል። አንዱ ከሞት በኋላ በሕይወት የምትቀጥል የማትሞት ነፍስ አለች ብሎ ያምናል። ሌላው ደግሞ ሞት ማለት ሙሉ በሙሉ ከሕልውና ውጭ መሆን ነው ብሎ ያምናል። እርስ በርስ የሚቃረኑ እንደዚህ ያሉ አመለካከቶች ሁለቱም እውነት ሊሆኑ እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ታዲያ የምታምንበት ነገር እንዲሁ ማመን የምትፈልገው ስለሆነ ብቻ ሳይሆን በትክክል እውነት መሆኑን ማረጋገጥህ ጥበብ አይሆንም? (ምሳሌ 1:​5) እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ ያለው ርዕስ ይህን ጉዳይ ይመረምራል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1921 “ፕሮቶኮልስ ኦቭ ዘ ለርንድ ኤልደርስ ኦቭ ዛዮን” የተባለውን ትራክት ያጋለጠው ርዕስ