በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በብርሃን ከተማ ብርሃን አብሪ መሆን

በብርሃን ከተማ ብርሃን አብሪ መሆን

በብርሃን ከተማ ብርሃን አብሪ መሆን

ፍሉክቱአት ኔክ ሜርጊቱር ወይም “በማዕበል ብትንገላታም ፈጽሞ አትሰጥምም” የሚለው አባባል የፓሪስ ከተማ መፈክር ነው።

አንዲት መርከብ ላለመስጠም ከምታደርገው ትግል በማይተናነስ ሁኔታ ፓሪስም ባለፉት 2, 000 ዓመታት ስፍር ቁጥር የሌላቸው የውጭ ማዕበሎችንና ከውስጧ የተቆሰቆሱ ዓመፆችን ተቋቁማ አልፋለች። እጅግ ውብ ከሚባሉት የዓለማችን ከተሞች አንዷ የሆነችው ፓሪስ ድንቅ የምህንድስና ጥበብ በሚታይባቸው ሕንፃዎቿ፣ ዳርና ዳር በተርታ የተተከሉ ዛፎች በሚገኙባቸው ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎቿ እና በዓለም ድንቅ በሆኑት ሙዚየሞቿ የምትታወቅ ናት። አንዳንዶች የባለቅኔዎች፣ የሠዓሊያንና የፈላስፎች መናኸሪያ አድርገው ይመለከቷታል። ሌሎች ደግሞ የፓሪስን እጅ የሚያስቆረጥሙ ምግቦች በማጣጣም ይደሰታሉ እንዲሁም የፋሽን ልብሶች የሚዘጋጁባቸውን ሱቆች በመጎብኘት ያደንቃሉ።

ፓሪስ ለረጅም ዘመናት የካቶሊክ እምነት ጠንካራ ይዞታ ሆና ቆይታለች። ፓሪስ ኢንላይትንመንት በመባል በሚታወቀው የአውሮፓ ምሁራዊ ንቅናቄ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት በተጫወተችው ወሳኝ ሚና የተነሳ የብርሃን ከተማ ተብላ ለመጠራት በቅታለች። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ የፓሪስ ነዋሪዎች አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት ከሃይማኖት ይልቅ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድርባቸው በዚያን ዘመን የነበረው ፍልስፍና ነው።

ይሁን እንጂ የሰው ጥበብ የተጠበቀውን ያህል ለሰዎች ሕይወት ብርሃን አልፈነጠቀም። ዛሬ ብዙዎች ከተለያየ ምንጭ የእውቀት ብርሃን ለማግኘት በመጣር ላይ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ላለፉት 90 ዓመታት በፓሪስ ‘ብርሃን ሲያበሩ’ ቆይተዋል። (ፊልጵስዩስ 2:​15) የይሖዋ ምሥክሮች ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጡ ዕቃዎችን’ ለማሳፈር ሲሉ ጥሩ ችሎታ እንዳላቸው መርከበኞች ተለዋዋጭ ከሆኑ አዝማሚያዎች ወይም ክስተቶች ጋር በየጊዜው መላመድ ጠይቆባቸዋል።​—⁠ሐጌ 2:​7

አስቸጋሪ የሆነች ከተማ

በ1850 ፓሪስ 600, 000 ነዋሪዎች ነበሯት። በዛሬው ጊዜ በከተማዋ ዳርቻ የሚኖሩትን ጨምሮ ከዘጠኝ ሚልዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች አሏት። ይህ ዓይነቱ እድገት ደግሞ ፓሪስ በፈረንሳይ ካሉት ከተሞች ሁሉ ይበልጥ የተለያዩ ዜጎች የሚኖሩባት ከተማ አድርጓታል። ፓሪስ የዓለም የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል፣ በዓለማችን ላይ ካሉ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የሚገኝባት እንዲሁም ወደ 250, 000 ገደማ የኮሌጅ ተማሪዎች የሚኖሩባት ከተማ ነች። በርካታ ሰማይ ጠቀስ የመኖሪያ ሕንፃዎች ያሏቸው በፓሪስ ዳርቻ የሚገኙ አካባቢዎች ወንጀል የሚፈጸምባቸውና ሥራ አጥነት የተስፋፋባቸው በመሆናቸው የፓሪስን መጥፎ ገጽታ ያሳያሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ምሥራቹን ማራኪ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ጥሩ ችሎታና ራስን ከሁኔታዎች ጋር ማስማማት እንደሚጠይቅባቸው የታወቀ ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​10

በየዓመቱ ከ20 ሚልዮን በላይ ቱሪስቶች ፓሪስን ይጎበኛሉ። እነዚህ ቱሪስቶች ኤፍል ታወር ላይ ሊወጡ፣ በሴይን ወንዝ አካባቢ ሊንሸራሸሩ ወይም በጎዳናዎቹ ዳር ወደሚገኙ ሻይ

ቤቶችና ምግብ ቤቶች ጎራ ብለው ሊዝናኑ ይችላሉ። ሆኖም ለፓሪስ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ጥድፊያ የሞላበት ሊሆን ይችላል። የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነችው ክሪስቲያ “ሰዎች ሁልጊዜ እንደተጣደፉ ነው። ከሥራ የሚመለሱት ደግሞ ድክም ብሏቸው ነው” ስትል ገልጻለች። እነዚህን ውክቢያ የበዛባቸው ሰዎች ማነጋገር ቀላል አይደለም።

ሆኖም በፓሪስ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል ዋነኛው ሰዎችን ቤታቸው ማነጋገር አለመቻላቸው ነው። አንዳንድ ሕንፃዎች ከነዋሪዎቹ ጋር መነጋገር የሚቻልበት መሣሪያ አላቸው። ይሁን እንጂ ወንጀል እየጨመረ በመምጣቱ አብዛኞቹ የመኖሪያ ሕንፃዎች የመግቢያ ኮድ ስላላቸው መግባት አይቻልም። ይህ ሁኔታ በአንዳንድ አካባቢዎች ሬሾው 1 የይሖዋ ምሥክር ለ1, 400 ሰዎች የሆነበትን ምክንያት ግልጽ ያደርገዋል። ከዚህ የተነሳ የስልክ ምሥክርነት እና መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ይበልጥ እየተሠራባቸው ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በሌሎች መንገዶች ‘ብርሃናቸውን ማብራት’ ችለዋልን?​—⁠ማቴዎስ 5:​16

መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት መስጠት የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎችና ቦታዎች አሉ። ማርቲን ያዘነች የምትመስል አንዲት ሴት ፌርማታ ላይ ቆማ አየች። ሴትዮዋ በቅርቡ አንድያ ሴት ልጅዋን በሞት ያጣች ነበረች። ማርቲን መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን የሚያጽናና የትንሣኤ ተስፋ የያዘ አንድ ብሮሹር ሰጠቻት። ከዚያም ለጥቂት ወራት ከሴትዮዋ ጋር ሳትገናኝ ከቆየች በኋላ ድጋሚ ስታገኛት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልትጀምርላት ቻለች። ሴትዮዋ ከባልዋ ተቃውሞ ቢገጥማትም እንኳ የይሖዋ ምሥክር ሆነች።

ፍሬያማ የሆነ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት

የፓሪስ የሕዝብ ትራንስፖርት መዋቅር በዓለማችን ላይ ካሉት እጅግ ቀልጣፋ መዋቅሮች አንዱ ነው። ዝነኛው የመሬት ውስጥ የባቡር መሥመር (ሜትሮ) በየቀኑ 5, 000, 000 መንገደኞች ያጓጉዛል። ሻትሌ ሌ አል የሚባለው የፓሪስ ማዕከላዊ የምድር ውስጥ ጣቢያ በዓለማችን ላይ ያለው ትልቁና ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት እንደሆነ ይነገራል። እዚህ ቦታ ከሰዎች ጋር መገናኘት የሚቻልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። አሌክሳንድራ በየቀኑ ወደ ሥራ የምትሄደው በመሬት ውስጥ ባቡር ነው። አንድ ቀን ቀሳፊ በሆነ የሉኪሚያ በሽታ ከተያዘ አንድ ወጣት ጋር ተነጋገረች። አሌክሳንድራ ስለ ገነት ተስፋ የሚናገር ትራክት ሰጠችው። በየቀኑ በተመሳሳይ ጊዜና ቦታ ለስድስት ሳምንታት የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት አደረጉ። ከዚያም አንድ ቀን ሰውዬው ሳይመጣ ቀረ። ይህ ከሆነ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ባለቤቱ ወደ አሌክሳንድራ ደውላ ባልዋ ሞት አፋፍ ላይ ስለሆነ ወደ ሆስፒታል እንድትመጣ ነገረቻት። የሚያሳዝነው አሌክሳንድራ በሕይወት እያለ አልደረሰችበትም። ባልዋ ከሞተ በኋላ ሚስቲቱ በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ ወደምትገኘው ወደ ቦርዶ የተዛወረች ሲሆን እዚያ የሚኖሩ ምሥክሮች ቤቷ መጥተው አነጋገሯት። ከአንድ ዓመት በኋላ አሌክሳንድራ ይህች ባልዋ የሞተባት ሴት ባልዋ ትንሣኤ ሲያገኝ ለማየት በተስፋ የምትጠባበቅ የተጠመቀች የይሖዋ ምሥክር መሆኗን ስትሰማ ምን ያህል እንደተደሰተች ልትገምት ትችላለህ!​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29

አንዲት አረጋዊት ክርስቲያን ከፓሪስ ተነስታ በማዕከላዊ የፈረንሳይ ክፍል ወደምትገኘው ወደ ሊሞዝ በባቡር ትጓዝ የነበረችውን ሬናታን አነጋገሩ። ሬናታ በትውልድ አገሯ በፖላንድ ለአምስት ዓመታት ቲኦሎጂ፣ ዕብራይስጥ እና ግሪክኛ አጥንታለች። ሆኖም በአምላክ ላይ የነበራትን እምነት አጣች። ከሦስት ወር በፊት ወደ አምላክ ጸልያ ነበር። ምንም እንኳ ሬናታ አረጋዊቷ እህት የሚነግሯት ነገር ባይስባትም እንዲሁም በሌላ ጊዜ አገኛቸዋለሁ ብላ ባታስብም ስልክ ቁጥሯን ሰጠቻቸው። ሆኖም እህት ግንኙነታቸው እንዳይቋረጥ ጥረት ያደረጉ ከመሆኑም በላይ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሬናታን ሄደው እንዲያነጋግሯት ዝግጅት አደረጉ። ባልና ሚስት የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ሊያነጋግሯት ሲመጡ ሬናታ ‘ምን የሚያስተምሩኝ ነገር ይኖራል?’ ብላ አሰበች። ሬናታ ቲኦሎጂ ያጠናች ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በትህትና ተቀበለች። “እውነት መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም” ስትል ተናግራለች። አሁን እሷም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች በማካፈል ላይ ነች።

ሚሼል የመኪና ማሽከርከር የቃል ትምህርት በመውሰድ ላይ ነበረች። አብረዋት ይማሩ የነበሩ ሌሎች ተማሪዎች ከጋብቻ በፊት ስለሚፈጸም ወሲብ ያወሩ ጀመር። ሚሼል እንዲህ ዓይነት ድርጊት ተገቢ እንዳልሆነ ገለጸች። ከአንድ ሳምንት በኋላ፣ የማሽከርከር ትምህርት የምትሰጠው ሲልቪ “የይሖዋ ምሥክር ነሽ?” ስትል ጠየቀቻት። ሲልቪ የሚሼል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አመለካከት አስገረማት። ሲልቪ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች፤ ከዚያም ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠመቀች።

በፓሪስ የሚገኙ በርካታ መዝናኛ ቦታዎችና መናፈሻዎች ከሰዎች ጋር ለመወያየት አመቺ የሆነ ሁኔታ ይፈጥራሉ። ዦዜት በእረፍት ጊዜዋ ኤሌን የሚባሉ አንዲት አረጋዊት ወይዘሮ እየተንሸራሸሩ ወዳሉበት መናፈሻ ሄደች። ዦዜት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን አስደናቂ ተስፋ ገለጸችላቸው። ኤሌን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚያደርጉበት ዝግጅት ተደረገና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ጥምቀት ደረጃ ደረሱ። በአሁኑ ጊዜ ኤሌን በ74 ዓመት ዕድሜያቸው ላይ የሚገኙ ሲሆን ለሌሎች የክርስትናን እውነት ማካፈል የሚያስደስታቸው በጣም ውጤታማ የሆኑ የዘወትር አቅኚ ናቸው።

ለብሔራት ሁሉ ብርሃን ማብራት

በፓሪስ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የተለያዩ ባሕሎችን ለማየት ወደ ሩቅ አገሮች መጓዝ አያስፈልጋቸውም። ከሕዝቡ መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት የውጭ ዜጎች ናቸው። ወደ 25 በሚጠጉ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚካሄዱ የክርስቲያን ጉባኤዎችና ቡድኖች አሉ።

በዚህ ልዩ የወንጌላዊነት ምድብ ዘዴና ብልሃት መጠቀም አብዛኛውን ጊዜ ለጥሩ ውጤት አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። አንዲት ፊሊፒናዊት ምሥክር የራሷን ልዩ የአገልግሎት ክልል አቋቋመች። በምትገበይበት ጊዜ መደብር ውስጥ ከምታገኛቸው ሌሎች ፊሊፒናውያን ጋር ውይይት በመክፈት በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማስጀመር ችላለች።

በስብከቱ ሥራ ላይ ቅድሚያውን ወስዶ ሰዎችን ማነጋገር ፍሬ ያስገኛል። በውጭ አገር ቋንቋ በሚካሄድ ጉባኤ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም የታወቀ አንድ የሰርከስ ቡድን ታኅሣሥ 1996 ወደ ከተማዋ እንደሚመጣ ሲሰሙ አርቲስቶቹን አግኝተው ለማነጋገር ወሰኑ። ምሥክሮቹ አንድ ቀን ማታ ትርዒቱ ካበቃ በኋላ ወዳረፉበት ሆቴል በመመለስ ላይ የነበሩትን አርቲስቶች ማነጋገር ቻሉ። በራሳቸው ተነሳሽነት ያደረጉት ይህ ጥረት 28 መጽሐፍ ቅዱሶች፣ 59 ክርስቲያናዊ መጻሕፍት፣ 131 ብሮሹሮች እና 290 መጽሔቶች እንዲያበረክቱ አስችሏል። በሦስት ሳምንት ቆይታቸው ማብቂያ ላይ ከአርቲስቶቹ አንዱ “የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ማድረግ ያለብኝ ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ። ሌላው ደግሞ “አገሬ ስገባ እኔም እሰብካለሁ!” ብሏል።

የተደበቀ ሀብት በመገኘት ላይ ነው

ወደ ፓሪስ የሚመጡ ጎብኚዎች በሄዱበት ሁሉ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ የምህንድስና ጥበብ የሚታይባቸው አስደሳች ቅርሶች ያያሉ። ሆኖም ገና የሚገኙ ይበልጥ ውድ የሆኑ ነገሮች አሉ። አኒዛ ወደ ፈረንሳይ የመጣችው ዲፕሎማት ከሆነው አጎቷ ጋር ነው። ቤት ውስጥ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስ ታነብባለች። አንድ ቀን ከቤት ተቻኩላ እየወጣች ሳለች አንዲት አቅኚ መጽሐፍ ቅዱስን ማመን የሚችሉት ለምንድን ነው? የተባለውን ትራክት ሰጠቻት። በሚቀጥለው ሳምንት ለመገናኘት ቀጠሮ ያዙና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። አኒዛ ከፍተኛ የቤተሰብ ተቃውሞ ደረሰባት። በጥናቷ እድገት አድርጋ ወደ ጥምቀት ደረጃ ደረሰች። ያገኘችውን እውነት ለሌሎች የማካፈል መብት እንዴት ትመለከተዋለች? “ዓይናፋር በመሆኔ መጀመሪያ ላይ በስብከቱ ሥራ መካፈል አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብብ ብርታት አገኛለሁ። ካልሰበክሁ አእምሮዬ ዕረፍት አይሰጠኝም።” ይህ አመለካከት ‘የጌታ ሥራ የበዛላቸው’ የሆኑ በፓሪስ የሚኖሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችን ለይቶ ያሳውቃል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​58

በተጨማሪም በፓሪስ ዙሪያ በሚካሄዱ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጭምር የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብርሃን እየበራ ነው። ይህም ሌሎች “ዕንቁዎች” እንዲገኙ አስችሏል። ብሩስ የተወሰኑ ክሮች ለመዋስ ብሎ በቅርቡ የይሖዋ ምሥክር ወደሆነ አንድ ጓደኛው ሄደ። ብሩስ ጓደኛው ቤት ሲደርስ ጓደኛው ብሩስ ከሚያውቃቸው አንዳንድ ወዳጆቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ሲወያይ አገኘውና እሱም ውይይቱን መከታተል ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና በቀረበለት ሐሳብ ቢስማማም አንዳንድ ችግሮች ነበሩበት። “ሰፈር ውስጥ በጣም የታወቅሁ ሰው ነበርኩ። ታላቅ ወንድሜ ሁልጊዜ ከሰዎች ጋር መደባደብ ነበር ሥራው፤ እኔ ደግሞ ቅልጥ ያለ ፓርቲ በማዘጋጀት የታወቅሁ ነበርኩ። ሌሎች እኔ የይሖዋ ምሥክር ልሆን እንደሆነ ሲሰሙ ምን ይሉ ይሆን?” ብሎ አሰበ። ብሩስ ፓርቲ እንዲያዘጋጅ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም ይህን ከማድረግ ተቆጠበ። ከአንድ ወር በኋላ መስበክ ጀመረ:- “የሰፈሩ ነዋሪዎች ሁሉ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የፈለግኩበትን ምክንያት ማወቅ ፈለጉ።” ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቀ። ከጊዜ በኋላ በአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመካፈል መብት አግኝቷል።

የተደበቀ ሀብት መፈለግ ከፍተኛ ጥረት ሊጠይቅ ይችላል። ሆኖም ጥረቱ ፍሬ ሲያስገኝ ምንኛ ያስደስታል! ዣኪ፣ ብሩኖ እና ዳሚየ በፓሪስ የሚኖሩ ዳቦ ጋጋሪዎች ናቸው። ዣኪ “ምንጊዜም ሥራ ላይ ስለሆንን እኛን እቤት ማግኘት የሚቻልበት መንገድ አልነበረም” ሲል ይገልጻል። የዘወትር አቅኚ የሆነው ፓትሪክ እነሱ የሚኖሩበት ሕንፃ አናት ላይ የተወሰኑ ጠባብ ክፍሎች መኖራቸውን አየና ቢያንስ አንደኛው ውስጥ ሰው አይጠፋም ሲል አሰበ። በመጨረሻ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ለአጭር ጊዜ ቤት ውስጥ የነበረውን ዣኪን በማግኘቱ ነዋሪዎቹን ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ጥሩ ውጤት አስገኘለት። ውጤቱ ምን ነበር? ሦስቱ ጓደኛሞች የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ከመሆናቸውም በላይ በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን ሌላ ሥራ መቀየር ችለዋል።

ማዕበሉን ጸጥ ማሰኘት

በቅርቡ ፈረንሳይ ውስጥ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የይሖዋ ምሥክሮች አደገኛ ሃይማኖታዊ ኑፋቄ እንደሆኑ አድርገው ገልጸዋል። በ1996 የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ማወቅ የሚያስፈልግዎት ጉዳይ የሚል ርዕስ ያለው ልዩ መረጃ የያዘ ትራክት ከዘጠኝ ሚልዮን ቅጂ በላይ በማሰራጨት ሥራ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ልባቸው ተካፍለዋል። የተገኘው ውጤት በጣም አመርቂ ነበር።

እያንዳንዱን ሰው ለማግኘት ጥረት ተደርጓል። በርካታ ባለሥልጣኖች ለይሖዋ ምሥክሮች ምስጋናቸውን ገልጸዋል። አንድ የማዘጋጃ ቤት አማካሪ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ትራክት ማሰራጨታቸው በጣም ጥሩ አድርገዋል። ትራክቱ የተሰራጨውን የሐሰት ወሬ ለማጋለጥ አስችሏል።” አንድ ዶክተር “ይህን መረጃ ለረጅም ጊዜ ስጠባበቅ ነበር!” የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል። በፓሪስ አካባቢ የሚኖር አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ማወቅ የሚያስፈልግዎት ጉዳይ የተባለውን ትራክት ያነበብኩት በአጋጣሚ አግኝቼ ነው። ተጨማሪ እውቀት ማግኘት እና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እፈልጋለሁ።” ሌላ ሴት ደግሞ “ሐቀኝነታችሁን አደንቃለሁ” ስትል ጽፋለች። የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑ አንዲት ወይዘሮ ለይሖዋ ምሥክሮች “በመጨረሻ ለዚያ ሁሉ ውሸት መልስ መስጠታችሁ ያስደስታል!” ብለዋቸዋል።

በ1997 የዓለም የካቶሊክ ወጣቶች ሳምንት የተካሄደው የስብከት ዘመቻ በፓሪስ አካባቢ ለሚኖሩ ወጣት ምሥክሮች ልዩ ደስታ አስገኝቶላቸው ነበር። ምንም እንኳ የሙቀቱ መጠን ከ35 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የነበረ ቢሆንም ወደ 2, 500 ገደማ ምሥክሮች ተሳትፈዋል። በጥቂት ቀናት ውስጥ ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለውን ብሮሹር 18, 000 ቅጂዎች ከመላው ዓለም ለመጡ ወጣቶች አበርክተዋል። ዘመቻው ለይሖዋ ስም ግሩም ምሥክርነት ከመስጠቱና የእውነት ዘር እንዲዘራ ከማድረጉ በተጨማሪ የወጣት ምሥክሮችን ግለት አቀጣጥሏል። በዚህ ልዩ ዘመቻ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ እንድትችል የዓመት እረፍቷን የወሰደች አንዲት ወጣት እህት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ይሖዋ ኃይላቸውን የእሱን ስም ለማወደስ የሚጠቀሙበት በምድር ዙሪያ ደስተኛ ሕዝቦች አሉት። በጣም አርኪና አስደሳች የሆኑት እነዚህ ሁለት ቀናት አንድ ሰው የዕድሜ ልክ የእረፍት ቀኑን ቢሠዋላቸው እንኳ የሚያስቆጩት አይሆኑም! (መዝሙር 84:​10)”

የካቲት 28, 1998 ሂትለር በጀርመን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ እንዲታገድ አዋጅ ያወጣበት 65ኛ ዓመት ነበር። በዚህ ዕለት በፈረንሳይ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የይሖዋ ሕዝቦች የደረሰባቸውን ስደት በዝርዝር የሚያቀርበውን የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጥቃት በጽናት ተቋቋሙ የተባለውን ቪዲዮ በተከራዩአቸው አዳራሾች ውስጥ ለሕዝብ አሳይተዋል። ከሰባት ሚልዮን በላይ የመጋበዣ ወረቀቶች ተሰራጭተው ነበር። የታሪክ ምሁራንና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ታስረው የነበሩ ሰዎች ስሜት ቀስቃሽ ምሥክርነት ሰጥተዋል። በፓሪስ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተጋባዦች ጨምሮ ወደ 5, 000 ገደማ ሰዎች ቪዲዮውን ተመልክተዋል።

በፓሪስ የሚኖሩ ብዙዎች ለመንፈሳዊ ብርሃን ከፍተኛ አድናቆት ያላቸው ከመሆኑም በላይ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ብርሃናቸውን ቦግ አድርገው በማብራታቸው ደስተኞች ናቸው። ኢየሱስ “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” ሲል እንደገለጸው ነው። (ማቴዎስ 9:​37) የይሖዋ ምሥክሮች ፓሪስ ውስጥ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለማሸነፍ ያሳዩት ቆራጥነት የተሞላበት መንፈስ ከተማዋ ልዩ በሆነ መንገድ ማለትም ለይሖዋ ውዳሴ በማምጣት ረገድ የብርሃን ከተማ እንድትሆን አስችሏታል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማዘጋጃ ቤት አዳራሽ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሉቭር ሙዚየም

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኦፔራ ጋርኒየ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሥራ ለሚበዛባቸው ሰዎች በተገኙበት ቦታ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ማካፈል