በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አብርሃም—የእምነት ምሳሌ

አብርሃም—የእምነት ምሳሌ

አብርሃም​—⁠የእምነት ምሳሌ

“[አብርሃም] ለሚያምኑ ሁሉ አባት . . . ነው።”​—⁠ሮሜ 4:11

1, 2. (ሀ) ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች አብርሃምን የሚያስታውሱት በምኑ ነው? (ለ) አብርሃም “ለሚያምኑ ሁሉ አባት” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?

 የአንድ ታላቅ ብሔር አባት፣ ነቢይ፣ ነጋዴና መሪ ነበር። ሆኖም ዛሬ ባሉ ክርስቲያኖች ዘንድ በዋነኛነት የሚታወሰው በጠንካራ እምነቱ ነው። ይሖዋም እንደ ወዳጁ አድርጎ እንዲመለከተው የገፋፋው ይህ ባሕርይው ነው። (ኢሳይያስ 41:8፤ ያዕቆብ 2:23) ስሙ አብርሃም ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ “ለሚያምኑ ሁሉ አባት” በማለት ይጠራዋል።​—⁠ሮሜ 4:11

2 ከአብርሃም በፊት እንደ አቤል፣ ሄኖክ እና ኖኅ ያሉት ሰዎች እምነት እንዳላቸው አሳይተው የለምን? አዎን አሳይተዋል። ሆኖም ይሖዋ የምድርን ሕዝብ ለመባረክ ቃል ኪዳን የገባው ከአብርሃም ጋር ነው። (ዘፍጥረት 22:18) በዚህም የተነሳ ተስፋ በተሰጠበት ዘር ላይ እምነት ለሚያሳድሩ ሁሉ ምሳሌያዊ አባታቸው ሆኗል። (ገላትያ 3:8, 9) በሌላ አባባል ያሳየው እምነት ልንኮርጀው የሚገባ ምሳሌ በመሆኑ የእኛም አባት እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። በርካታ መከራዎችንና ፈተናዎችን ያሳለፈ በመሆኑ መላው ሕይወቱ የእምነት መግለጫ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። በእርግጥም አብርሃም ከደረሱበት የእምነት ፈተናዎች በሙሉ የላቀ የሆነውን ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ የሚጠይቀውን ፈተና ከመፈተኑ ከረዥም ጊዜ በፊት በደረሱበት አነስተኛ በሆኑ በርካታ መከራዎች እምነቱን አሳይቷል። (ዘፍጥረት 22:1, 2) እስቲ ቀደም ሲል ከደረሱበት የእምነት ፈተናዎች መካከል አንዳንዶቹን እንመርምርና ዛሬ ለምንኖረው ለእኛ ምን ትምህርት እንደያዙልን እንመልከት።

ዑርን ለቅቆ እንዲወጣ የተሰጠ ትእዛዝ

3. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብራም አስተዳደግ ምን ይነግረናል?

3 አብራም (ከጊዜ በኋላ አብርሃም ተብሏል) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በስም የተጠቀሰው ዘፍጥረት 11:26 ላይ ሲሆን ጥቅሱም “ታራም መቶ [“70፣” የ1980 ትርጉም] ዓመት ኖረ፣ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ” ይላል። አብርሃም ፈሪሃ አምላክ የነበረው የሴም ዘር ነው። (ዘፍጥረት 11:10-24) ዘፍጥረት 11:​31 እንደሚናገረው አብራም ከቤተሰቡ ጋር ይኖር የነበረው በአንድ ወቅት ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ትገኝ በነበረችው ባለ ጠጋ ከተማ ማለትም ‘በከለዳውያን ዑር’ ነው። a ስለዚህ ያደገው ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ በድንኳን እንደሚኖር ዘላን ሳይሆን ከፍተኛ ምቾትና ድሎት በነበረው ከተማ ውስጥ ነው። ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሸቀጦችን በዑር ገበያዎች መግዛት ይቻል ነበር። የተሟላ የቤት ውስጥ የውኃ ቧንቧና 14 ክፍል ያሏቸው ኖራ የተቀቡ ቤቶችን በከተማዋ ጎዳናዎች ማየት ይቻል ነበር።

4. (ሀ) ዑር እውነተኛ የአምላክ አምላኪዎችን የሚፈትኑ ምን ሁኔታዎች ነበሩባት? (ለ) አብራም በይሖዋ ሊያምን የቻለው እንዴት ነው?

4 ዑር ቁሳዊ ጥቅም ይገኝባት የነበረች ከተማ ብትሆንም እውነተኛውን አምላክ ማገልገል ለሚፈልግ ሰው ግን አደገኛ ቦታ ነበረች። ከተማዋ በጣዖት አምልኮና በአጉል እምነት የተሞላች ነበረች። አካባቢው ናና ለተባለችው የጨረቃ አምላክ ክብር በተሠሩ የቤተ መቅደስ ማማዎች የተሞላ ነበር። አብራም እንዲህ ባለው ወራዳ አምልኮ እንዲካፈል ዘመዶቹን ጨምሮ ከሌሎች ሰዎች ከባድ ተጽዕኖ ደርሶበት መሆን አለበት። አንዳንድ የአይሁድ አፈ ታሪኮች እንደሚሉት የአብራም አባት ታራ ራሱ ጣዖት ሠሪ ነበር። (ኢያሱ 24:2, 14, 15) ሁኔታው ምንም ይሁን ምን አብራም ወራዳ የሆነው የሐሰት አምልኮ ተከታይ አልነበረም። በዕድሜ ገፍቶ የነበረው አያቱ ሴም በሕይወት ስለነበረ እውነተኛውን አምላክ በተመለከተ ትክክለኛ እውቀት ሳያካፍለው አልቀረም። በዚህ የተነሳ አብራም በናና ሳይሆን በይሖዋ አመነ።​—⁠ገላትያ 3:6

የእምነት ፈተና

5. አብራም ገና በዑር ሳለ አምላክ ምን ብሎ አዘዘው? ምንስ ቃል ገባለት?

5 አሁን የአብራም እምነት ሊፈተን ነው። አምላክ ተገለጠለትና እንዲህ ሲል አዘዘው:- “ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፣ እባርክሃለሁ፣ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።”​—⁠ዘፍጥረት 12:1-3፤ ሥራ 7:2, 3

6. አብራም ዑርን ለቅቆ ለመውጣት እምነት የጠየቀበት ለምንድን ነው?

6 አብራም በዕድሜ ገፍቶ የነበረ ከመሆኑም በላይ ልጅ አልነበረውም። ታዲያ “ታላቅ ሕዝብ” ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ደግሞስ ሂድ የተባለው የት ነው? አምላክ ቦታውን ለይቶ አልነገረውም ነበር። በመሆኑም አብራም የበለጸገችውንና የተመቻቸ ኑሮ የነበረባትን ዑርን ለቅቆ ለመውጣት በእርግጥ እምነት ይጠይቅበት ነበር። ፋሚሊ፣ ላቭ ኤንድ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ የጥንቱን ጊዜ በማስመልከት የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል:- “አንድ ግለሰብ ከባድ ወንጀል ቢፈጽም የሚጠብቀው ከሁሉ የከፋ ቅጣት ከቤተሰብ ‘አባልነቱ’ ተሰርዞ መገለል ነው። . . . አብርሃም መለኮታዊ ትእዛዝ ተቀብሎ አገሩን ብቻ ሳይሆን ዘመዶቹን ትቶ መውጣቱ ለአምላክ ከፍተኛ ታዛዥነት እንዳሳየና በእርሱ እንደታመነ ተደርጎ የተቆጠረለት ለዚህ ነው።”

7. በዛሬ ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች የአብራም ዓይነት ፈተና ሊገጥማቸው የሚችለው እንዴት ነው?

7 ዛሬም ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል። እንደ አብራም ቁሳዊ ፍላጎቶችን ከቲኦክራሲያዊ ፍላጎቶች እንድናስቀድም ተጽዕኖዎች ይደርሱብን ይሆናል። (1 ዮሐንስ 2:15, 16) ጤናማ ያልሆነ ቅርርብ እንድንመሠርት ሊያባብሉን ከሚሞክሩ የማያምኑ የቤተሰብ አባላትና የተወገዱ ዘመዶቻችን ተቃውሞ ሊያጋጥመን ይችላል። (ማቴዎስ 10:34-36፤ 1 ቆሮንቶስ 5:11-13፤ 15:33) በዚህ ረገድ አብራም ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ከማንኛውም ነገር በላይ ሌላው ቀርቶ ከቤተሰብ ዝምድናው በፊት ያስቀደመው ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ነበር። የአምላክ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት፣ መቼ ወይም የት እንደሆነ በትክክል አያውቅም ነበር። የሆነ ሆኖ ኑሮውን በእነዚህ ተስፋዎች ላይ ለመመሥረት ፈቃደኛ ነበር። በዛሬው ጊዜ መንግሥቱ በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንዲይዝ ለማድረግ ይህ ምንኛ ግሩም ማበረታቻ ነው!​—⁠ማቴዎስ 6:33

8. የአብራም እምነት በቅርብ የቤተሰቡ አባላት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ አሳድሯል? ክርስቲያኖች ከዚህ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?

8 ስለ አብራም የቅርብ የቤተሰብ አባላትስ ምን ለማለት ይቻላል? የአብራም እምነትና ቁርጠኛ አቋም በእነርሱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮ ስለነበር ሚስቱ ሦራ እና ወላጆቹ የሞቱበት የወንድሙ ልጅ ሎጥ አምላክን በመታዘዝ ዑርን ለቅቀው ወጥተዋል። በኋላም የአብራም ወንድም ናኮር እና የተወሰኑ ልጆቹ ዑርን በመልቀቅ ኑሯቸውን በካራን መሥርተው ይሖዋን ያመልኩ ነበር። (ዘፍጥረት 24:1-4, 10, 31፤ 27:43፤ 29:4, 5) የአብራም አባት ታራም ሳይቀር ከልጁ ጋር ለመሄድ ተስማምቷል! የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን መጽሐፍ ቅዱስም ወደ ከነዓን የተደረገውን ጉዞ የመራው እርሱ እንደሆነ አድርጎ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 11:31) እኛም ለዘመዶቻችን በዘዴ ብንመሠክር በተወሰነ መጠን ስኬት ማግኘት እንችል ይሆን?

9. አብራም ለጉዞው ምን ዓይነት ዝግጅት ማድረግ ነበረበት? ይህ መሥዋዕት መክፈልን የሚጠይቅ የሆነው ለምንድን ነው?

9 አብራም ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት የሚያከናውናቸው በርካታ ሥራዎች ነበሩት። ንብረቶቹንና ቁሳቁሶቹን ሁሉ መሸጥና ድንኳን፣ ግመሎች፣ ምግብና አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ዕቃዎችን መግዛት ነበረበት። አብራም እነዚህን ነገሮች በጥድፊያ ማከናወኑ የገንዘብ ኪሳራ አስከትሎበት ሊሆን ቢችልም ይሖዋን በመታዘዙ ደስተኛ ነበር። አብራም ዝግጅቱን ሁሉ አጠናቅቆ ከጨረሰ በኋላ ተጓዦቹ ከዑር ቅጥር ውጭ የተሰለፉበት ዕለት ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ቀን ነበር! ተጓዦቹ የኤፍራጥስን ወንዝ ተከትለው ወደ ሰሜን ምዕራብ አቀኑ። ወደ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሆን ርቀት ለሳምንታት ከተጓዙ በኋላ ምቹ ማረፊያ በሆነችው ከሜሶጶጣሚያ በስተ ሰሜን በምትገኘው ካራን የምትባል ከተማ ደረሱ።

10, 11. (ሀ) አብራም በካራን ለተወሰነ ጊዜ የቆየው ለምን ነበር? (ለ) በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን ለሚንከባከቡ ክርስቲያኖች ምን ማበረታቻ መስጠት ይቻላል?

10 አብራም በዕድሜ ገፍቶ ለነበረው ለአባቱ ለታራ በማሰብ ሳይሆን አይቀርም በካራን መኖር ጀመረ። (ዘሌዋውያን 19:32) በተመሳሳይም በዛሬ ጊዜ ያሉ ብዙ ክርስቲያኖች በዕድሜ ለገፉ ወይም ለታመሙ ወላጆቻቸው እንክብካቤ የሚያደርጉ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶች ለዚህ ሲሉ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ አስፈልጓቸዋል። እንዲህ ማድረጉ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በፍቅር ተገፋፍተው የሚከፍሉት መሥዋዕትነት “በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ” እንደሆነ እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 5:4

11 የተወሰኑ ጊዜያት አለፉ። “የታራም ዕድሜ ሁለት መቶ አምስት ዓመት ሆነ፤ ታራም በካራን ሞተ።” አብራም አባቱን በሞት በማጣቱ ምክንያት ያዘነ ቢሆንም እንኳ የሐዘኑ ጊዜ ካለፈ በኋላ ወዲያው ጉዞውን ጀመረ። “አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ። አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን፣ ያገኙትን ከብት ሁሉና በካራን ያገኙአቸውን ሰዎች ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ወጣ።”​—⁠ዘፍጥረት 11:32፤ 12:4, 5

12. አብራም በካራን በነበረበት ጊዜ ምን አደረገ?

12 አብራም ካራን በቆየባቸው ጊዜያት ‘ሀብት አግኝቶ’ እንደነበር ማወቁ ትኩረት የሚስብ ነው። አብራም ዑርን ለቅቆ ሲወጣ ቁሳዊ ንብረቱን መሥዋዕት ያደረገ ቢሆንም እንኳ ካራንን ለቅቆ የወጣው ባለጠጋ ሆኖ ነው። ይህ በአምላክ በረከት የተገኘ እንደሆነ ግልጽ ነው። (መክብብ 5:19) አምላክ በዛሬ ጊዜ የሚኖሩ ሕዝቡን በሙሉ ባለጠጎች እንደሚያደርጋቸው ቃል ባይገባም ለመንግሥቱ ሲሉ ‘ቤታቸውን፣ ወንድሞቻቸውን ወይም እህቶቻቸውን የተዉ’ ካሉ የሚያስፈልጋቸውን በታማኝነት ያሟላላቸዋል። (ማርቆስ 10:29, 30) አብራምም ‘ሰዎችን’ ማለትም በርካታ ሎሌዎችንም ‘አግኝቷል።’ ጀሩሳሌም ታርገም እና ካልዲ ፓራፍሬዝ ትርጉም አብራም ‘ሃይማኖታቸውን እንዳስለወጣቸው’ ይናገራሉ። (ዘፍጥረት 18:19) እምነትህ ለጎረቤቶችህ፣ ለሥራ ባልደረቦችህ ወይም አብረውህ ለሚማሩት ልጆች እንድትናገር ይገፋፋሃል? አብራም ኑሮውን መሥርቶ የአምላክን ትእዛዝ ከመርሳት ይልቅ በካራን ያሳለፈውን ጊዜ ፍሬያማ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። አሁን ግን በዚያ የሚቆይበት ጊዜ አልቆ ነበር። “አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ።”​—⁠ዘፍጥረት 12:4

ከኤፍራጥስ ባሻገር

13. አብራም የኤፍራጥስን ወንዝ የተሻገረው መቼ ነው? ይህስ ክንውን ትልቅ ትርጉም ያዘለ የሆነው ለምንድን ነው?

13 አብራም እንደገና ጉዞ ለማድረግ ተነሳ። ካራንን ከኋላቸው በመተው የ90 ኪሎ ሜትር ጉዞ ለማድረግ ፊቱን ወደ ምዕራብ አቀና። አብራም የጥንቷን የንግድ ማዕከል ከርከሚሽን ካለፈ በኋላ ኤፍራጥስ አጠገብ ጥቂት አረፍ ሳይል አልቀረም። ብዙውን ጊዜ መንገደኞች ኤፍራጥስን የሚሻገሩት በዚህ በኩል ነው። b አብርሃምና ከእርሱ ጋር የነበሩት ወንዙን የተሻገሩት መቼ ነው? አይሁዳውያን ኒሳን 14, 1513 ከዘአበ ግብፅን ለቅቀው ከመውጣታቸው ከ430 ዓመት በፊት እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። ዘጸአት 12:​41 እንዲህ ይላል:- “አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሠራዊት ሁሉ ከግብፅ ምድር ወጣ።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ከአብርሃም ጋር የተገባው ቃል ኪዳን ሥራውን የጀመረው አብራም በታዛዥነት ኤፍራጥስን በተሻገረ ጊዜ ማለትም በኒሳን 14, 1943 ከዘአበ ሳይሆን አይቀርም።

14. (ሀ) አብራም በእምነት ዓይኑ ምን መመልከት ችሎ ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉት የአምላክ ሕዝቦች ከአብራም ይበልጥ የተባረኩት በምን መንገድ ነው?

14 አብራም የበለጸገችውን ከተማ ትቶ ሄዷል። ሆኖም አሁን የሰውን ዘር በጽድቅ የምታስተዳድረውን “መሠረት ያላትን . . . ከተማ” በዓይነ ሕሊናው መመልከት ይችላል። (ዕብራውያን 11:10) አዎን፣ አብራም የነበረው እውቀት አነስተኛ ቢሆንም አምላክ ሟች የሆነውን የሰው ዘር ለመዋጀት ዓላማ እንዳለው መገንዘብ ጀምሮ ነበር። በዛሬ ጊዜ እኛ የአምላክን ዓላማዎች በተመለከተ ከአብራም ይልቅ ሰፊ እውቀት በማግኘት ተባርከናል። (ምሳሌ 4:18) አብራም ተስፋ አድርጎት የነበረው “ከተማ” ወይም ንጉሣዊ መስተዳድር አሁን እውን ሆኗል። ከ1914 ጀምሮ በሰማይ መግዛት ጀምሯል። በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለንና በእርሱ ላይ እንደምንታመን የሚያሳዩ ሥራዎችን ለመሥራት መገፋፋት አይኖርብንም?

የተስፋይቱ ምድር ኑሮ ተጀመረ

15, 16. (ሀ) አብራም ለይሖዋ መሠዊያ መሥራቱ ድፍረት ይጠይቅበት የነበረው ለምን ነበር? (ለ) በዛሬ ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች እንደ አብራም ደፋር ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?

15 ዘፍጥረት 12:​5, 6 እንዲህ ይለናል:- “ወደ ከነዓንም ምድር ገቡ። አብራምም እስከ ሴኬም ስፍራ እስከ ሞሬ የአድባር ዛፍ ድረስ በምድር አለፈ።” ሴኬም የምትገኘው ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን በኩል 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው “የቅድስቲቱ ምድር ገነት” ተብሎ በሚታወቅ ለምለም ሸለቆ ውስጥ ነበር። ሆኖም “የከነዓን ሰዎችም በዚያን ጊዜ በምድሩ ነበሩ።” ከነዓናውያን በሥነ ምግባር የተበላሹ ስለነበሩ አብራም ከሚያሳድሩት ብልሹ ተጽዕኖ ቤተሰቡን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረበት።​—⁠ዘጸአት 34:11-16

16 “እግዚአብሔርም” ለሁለተኛ ጊዜ “ለአብራም ተገለጠለትና:- ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ አለው።” ምንኛ የሚያስደስት ነው! እርግጥ አብራም ወደፊት ዘሮቹ በሚያገኙት ነገር ለመደሰት እምነት ጠይቆበታል። እንደዚያም ሆኖ አብራም “ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠውያን ሠራ።” (ዘፍጥረት 12:7) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሚከተለውን ሐሳብ ሰንዝረዋል:- “በዚያ መሠዊያ መሥራቱ እምነቱን የማራመድ መብቱን መሠረት በማድረግ ምድሪቱን መውረሱን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው።” እንዲህ ያለ መሠዊያ መሥራት ድፍረት የሚጠይቅ ነበር። ይህ መሠዊያ ከጊዜ በኋላ በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ ተለይቶ እንደተጠቀሰው (ካልተጠረበ) ድንጋይ የተሠራ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። (ዘጸአት 20:24, 25) አሠራሩ ከነዓናውያን ይጠቀሙበት ከነበረው መሠዊያ ፈጽሞ የተለየ ነበር። አብራም ለጥላቻ አልፎ ተርፎም ለኃይል ድርጊት ሊያጋልጠው የሚችል ቢሆንም የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ አምላኪ መሆኑን በይፋ የሚያሳውቅ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ወስዷል። እኛስ? በተለይ ወጣት የሆንን ጎረቤቶቻችን ወይም የትምህርት ቤት ጓደኞቻችን ይሖዋን የምናመልክ መሆናችንን እንዳያውቁብን እንደብቃለን? አብራም ያሳየው ድፍረት የተሞላበት ምሳሌ የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን እንድንኮራ የሚያበረታታን ይሁን!

17. አብራም የአምላክ ስም ሰባኪ መሆኑን ያስመሰከረው እንዴት ነው? ይህስ በዛሬው ጊዜ ላለነው ክርስቲያኖች ምን ያስታውሰናል?

17 አብራም በሄደበት ቦታ ሁሉ ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። “ከዚያም በቤቴል ምሥራቅ ወዳለው ተራራ ወጣ፣ በዚያም ቤቴልን ወደ ምዕራብ ጋይን ወደ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ።” (ዘፍጥረት 12:8) ‘ስም መጥራት’ የሚለው የዕብራይስጡ ሐረግ “ስሙን ማወጅ (መስበክ)” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። አብራም አቅራቢያው ለነበሩት ከነዓናውያን የይሖዋን ስም በድፍረት እንዳወጀ ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘፍጥረት 14:22-24) ይህም በዛሬ ጊዜ ‘ስለ ስሙ በመመሥከር’ ረገድ የተቻለንን ያህል ተሳትፎ የማድረግ ኃላፊነታችንን ያስታውሰናል።​—⁠ዕብራውያን 13:15፤ ሮሜ 10:10

18. አብራም ከከነዓናውያን ነዋሪዎች ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር?

18 አብራም በየትኞቹም ቦታዎች ረዘም ላለ ጊዜ አልቆየም። “አብራምም ከዚያ ተነሣ፣ እየተጓዘም ወደ አዜብ ሄደ።” ይህ ከተራራማው የይሁዳ ምድር በስተ ሰሜን በኩል የሚገኝ ከፊል በረሃማ ምድር ነው። (ዘፍጥረት 12:9) ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወርና በሄደበት ቦታ ሁሉ የይሖዋ አምላኪ መሆኑን በማሳወቅ አብርሃምም ሆነ ቤተሰቡ ‘በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች መሆናቸውን በግልጽ አሳይተዋል።’ (ዕብራውያን 11:13 NW ) ከአረማዊ ጎረቤቶቻቸው ጋር ከልክ ያለፈ ቅርርብ እንዳይመሠርቱ ሁልጊዜ ይጠነቀቁ ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ ‘የዓለም ክፍል ከመሆን’ መራቅ ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 17:16) ለጎረቤቶቻችንና ለሥራ ባልደረቦቻችን ደጎችና ትሑቶች ብንሆንም ከአምላክ ርቆ የሚገኘው ዓለም ውስጥ ያለው መንፈስ በሚያንጸባርቃቸው ባሕርያት እንዳንጠላለፍ እንጠነቀቃለን።​—⁠ኤፌሶን 2:2, 3

19. (ሀ) የዘላንነት ኑሮ ለአብራምና ለሦራ ፈታኝ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አብራም ምን ተጨማሪ ፈተና ከፊቱ ይጠብቀው ነበር?

19 ራስን አስተካክሎ የዘላን ዓይነት ኑሮ መኖር ለአብራምም ሆነ ለሦራ ቀላል እንዳልነበረ መርሳት የለብንም። በዑር ከነበሩት ሁሉ ነገር የሞላባቸው የገበያ ቦታዎች ምግብ ገዝቶ ከመመገብ ይልቅ የመንጎቻቸውን ውጤት ተመግበዋል። በሚያማምሩ ቤቶች ውስጥ ሳይሆን በድንኳን ኖረዋል። (ዕብራውያን 11:9) አብራም ውሎው በሥራ የተሞላ ነበር። ከብቶቹንና አገልጋዮችን በሚመለከት በርካታ የሚሠሩ ሥራዎች ነበሩት። ሦራ ሊጥ እንደ ማቡካት፣ ዳቦ እንደ መጋገር፣ ጥጥ እንደ መፍተልና ልብስ እንደ መስፋት ያሉ በጊዜው በነበረው ባሕል ሴቶች ያከናውኗቸው የነበሩትን ሥራዎች ትሠራ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘፍጥረት 18:6, 7፤ 2 ነገሥት 23:7፤ ምሳሌ 31:19፤ ሕዝቅኤል 13:18) ሆኖም ሌሎች ተጨማሪ ፈተናዎች ከፊታቸው ይጠብቋቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ የአብራምንና የቤተሰቡን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል አንድ ሁኔታ ሊፈጠር ነው! አብራም ይህን ፈታኝ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችል እምነት ይኖረው ይሆን?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በአሁኑ ጊዜ ያለው የኤፍራጥስ ወንዝ የጥንቷ ዑር ትገኝበት ከነበረው ቦታ በስተ ምሥራቅ በኩል አሥራ ስድስት ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ የሚገኝ ቢሆንም እንኳ ጥንት ወንዙ ከከተማዋ በስተ ምዕራብ በኩል ይፈስ እንደነበር የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለ። በዚህ የተነሳ ከጊዜ በኋላ አብራም ‘[ከኤፍራጥስ] ወንዝ ማዶ’ እንደመጣ ተደርጎ ተገልጿል።​—⁠ኢያሱ 24:3

b ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ የአሦር ንጉሥ ዳግማዊ አሱርናሲርፓል የኤፍራጥስን ወንዝ በከርከሚሽ አቅራቢያ በታንኳ ተሻግሯል። አብራም ኤፍራጥስን በታንኳ ይሻገር ወይም እርሱም ሆነ አብረውት የነበሩት ተጓዦች በእግራቸው ያቋርጡት መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የሚናገረው ነገር የለም።

አስተውለሃልን?

• አብራም “ለሚያምኑ ሁሉ አባት” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?

• አብራም የከለዳውያንን ዑር ለቅቆ መውጣት እምነት ይጠይቅበት የነበረው ለምንድን ነው?

• አብራም ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ ይሰጥ እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አብርሃም ያደረገው ጉዞ

ኡር

ካራን

ከርከሚሽ

ከነዓን

ታላቁ ባሕር

[ምንጭ]

Based on a map copyrighted by Pictorial Archive (Near Eastern History) Est. and Survey of Israel

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብራም በዑር የነበረውን የምቾት ኑሮ ትቶ ለመሄድ እምነት ጠይቆበታል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብራምና ቤተሰቡ በድንኳን በመኖር ‘በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች መሆናቸውን በግልጽ አሳይተዋል’