የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
ኢዮብ ሥቃይ የደረሰበት ለምን ያህል ጊዜ ነበር?
አንዳንድ ሰዎች ኢዮብ ብዙ የመከራ ዓመታትን እንዳሳለፈ ይሰማቸው እንጂ የኢዮብ መጽሐፍ ሥቃዩ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ እንደነበር አያመለክትም።
በኢዮብ ላይ የደረሰው መከራ የመጀመሪያ ክፍል ይኸውም የቤተሰቡን አባላት በሞት ማጣቱና በንብረቱ ላይ የደረሰው ጥፋት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከሰተ ይመስላል። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር” ይላል። ኢዮብ በበሬዎቹ፣ በአህዮቹ፣ በበጎቹ፣ በግመሎቹና እነዚህን እንስሳት በሚጠብቁ እረኞች ላይ አደጋ መድረሱን በተከታታይ ሰማ። ከዚያ ተከትሎ ይመስላል ኢዮብ “በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ” የነበሩት ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ማለቃቸውን ተረዳ። ይህ ሁሉ የተከሰተው በአንድ ቀን ይመስላል።—ኢዮብ 1:13-19
በኢዮብ ላይ የደረሰው መከራ ሁለተኛ ክፍል ከዚህ የበለጠ ጊዜ ወስዶ መሆን አለበት። ሰይጣን በይሖዋ ፊት ቀርቦ ኢዮብ በሰውነቱ ላይ ሥቃይ ቢደርስበት በአቋሙ እንደማይጸና ተናገረ። ከዚያም ኢዮብን “ከእግሩ ጫማ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቁስል መታው።” ቁስሉ መላ አካላቱን እስኪያዳርስ ድረስ የተወሰነ ጊዜ ወስዶ ሊሆን ይችላል። እንዲሁም ይህ ወሬ “የደረሰበትን ክፉ ነገር ሁሉ” ሰምተው ወደ እርሱ ለመጡት አጽናኝ ተብዬ ወዳጆቹ ጆሮ እስኪደርስ ድረስ ጊዜ ወስዶ መሆን አለበት።—ኢዮብ 2:3-11
ኤልፋዝ ከኤዶም ምድር የመጣ ቴማናዊ ሲሆን ሶፋር ደግሞ ከአረቢያ በስተ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ የመጣ በመሆኑ የሚኖሩበት አካባቢ ኢዮብ ከሚኖርበት አካባቢ ይኸውም ከአረቢያ በስተ ሰሜን ከምትገኘው ከዖፅ ብዙም ሩቅ አልነበረም። ይሁን እንጂ በልዳዶስ ሹሐዊ ሲሆን ዘሮቹ በኤፍራጥስ ወንዝ ዳርቻ ይኖሩ እንደነበር ግልጽ ነው። በልዳዶስ በወቅቱ በመኖሪያ አካባቢው ከነበረ በኢዮብ ላይ የደረሰውን ሰምቶ ወደ ዖፅ እስኪመጣ ድረስ ሳምንታት ወይም ወራት ሊወስድበት ይችላል። እርግጥ በኢዮብ ላይ መከራ መድረስ በጀመረ ጊዜ ሦስቱ ሰዎች ኢዮብ ከሚኖርበት እምብዛም በማይርቅ አካባቢ ኖረውም ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች ከደረሱ በኋላ ምንም ሳይናገሩ “ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊትም ከእርሱ ጋር በምድር ላይ” ተቀምጠው ነበር።—ኢዮብ 2:12, 13
በኢዮብ ላይ የደረሰው መከራ የመጨረሻ ክፍል የተከሰተው ከዚህ በኋላ ሲሆን ታሪኩም የኢዮብን መጽሐፍ አብዛኛውን ምዕራፍ ይሸፍናል። በአጽናኝ ተብዬዎቹና አብዛኛውን ጊዜ መልስ በመስጠት በተወሰነው በኢዮብ መካከል ክርክር ተደርጎ ነበር። ከዚያ በኋላ ወጣቱ ኤሊሁ ተግሳጽ የሰጠ ሲሆን ይሖዋም ከሰማይ ሆኖ ኢዮብን አርሞታል።—ኢዮብ 32:1-6፤ 38:1፤ 40:1-6፤ 42:1
በመሆኑም በኢዮብ ላይ የደረሰው ሥቃይና ውጤቱ በጥቂት ወራት ምናልባትም ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተፈጸመ ሊሆን ይችላል። ከባድ መከራ ሲደርስ ማቆሚያ ያለው እንደማይመስል ከተሞክሮ ታውቅ ይሆናል። ሆኖም የኢዮብ ፈተና ማብቂያ እንደነበረው ሁሉ በእኛ ላይ የሚደርሰው መከራም ማብቂያ እንዳለው መዘንጋት አይኖርብንም። ይሁን እንጂ ለረጅም ጊዜ መከራ ቢደርስብን “ቀላልና ጊዜያዊ የሆነ መከራችን፣ ወደር የሌለውን እጅግ ታላቅ የሆነ ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል” የሚሉት በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቃላት እንደሚያረጋግጡት አምላክ እንደሚረዳን አንዘንጋ። (2 ቆሮንቶስ 4:17 የ1980 ትርጉም ) ሐዋርያው ጴጥሮስ “በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል” በማለት ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 5:10