በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ሰላምን ፈልግ ተከተለውም’

‘ሰላምን ፈልግ ተከተለውም’

‘ሰላምን ፈልግ ተከተለውም’

“ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።”​—⁠ሮሜ 12:18

1, 2. ሰው ሠራሽ ሰላም ዘላቂ የማይሆንባቸው አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

 መሠረቱ የተናጋ፣ ቋሚዎቹ የበሰበሱ፣ ጣሪያው ያዘመመ አንድ ቤት በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። በእ​ንዲህ ዓይነት ቤት ውስጥ ለመኖር ታስባለህ? አታደርገውም። ቀለሙ ቢታደስ እንኳ ቤቱ አስተማማኝ ሊሆን አይችልም። አንድ ቀን መደርመሱ አይ​ቀርም።

2 ማንኛውም የዚህ ዓለም ሰላምም ልክ እንደዚህ ቤት ነው። የተገነባው በማይረባ መሠረት ላይ ማለትም ‘ማዳን የማይችሉ’ የሰው ልጆች በሚሰጡት ተስፋና በሚቀይሱት ስልት ላይ ነው። (መዝሙር 146:3) ያለፉት ዘመናት በብሔራት፣ በዘርና በጎሳ መካከል በተደረጉ ማለቂያ በሌላቸው ግጭቶች የተሞሉ ናቸው። እርግጥ ነው ለአጭር ጊዜ ሰላም የተገኘባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም ምን ዓይነት ሰላም? እርስ በርሳቸው ሲዋጉ የቆዩ ሁለት መንግሥታት አንዱ ድል በመደረጉ ምክንያት ወይም ሁለቱም ከጦርነት ምንም ጥቅም እንደማይገኝ በመገንዘባቸው ምክንያት መዋጋታቸውን አቁመው ሰላም ቢያውጁ ይህ ምን ዓይነት ሰላም ነው? ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት የሆኑት ጥላቻ፣ ጥርጣሬና ቅናት አሁንም አልተወገዱም። እንደ ቀለም ‘ቅቡ’ ሁሉ ሰው ሠራሹም ሰላም ጥላቻን ሊደብቅ ቢችልም ዘለቄታ ግን የለውም።​—⁠ሕዝቅኤል 13:10

3. የአምላክ ሕዝቦች ያላቸው ሰላም ከሰው ሠራሽ ሰላም የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?

3 የሆነ ሆኖ በዚህ በጦርነት በሚታመስ ዓለም ውስጥ እንኳ እውነተኛ ሰላም አለ። የት? የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በሚከተሉ፣ በሚታዘዙትና አኗኗሩን ለመኮረጅ ጥረት በሚያደርጉ እውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል። (1 ቆሮንቶስ 11:1፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) እንዲህ ያለው ሰላም በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ በማመንና ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ዝምድና በመመሥረት የተገኘ በመሆኑ የተለያየ ዘር፣ የኑሮ ደረጃና ዜግነት ባላቸው በእነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ሰላም እውነተኛ ነው። በመካከላቸው ያለው ሰላም በሰዎች ጥረት የተገኘ ሳይሆን ከአምላክ ያገኙት ነው። (ሮሜ 15:33፤ ኤፌሶን 6:23, 24) “የሰላም አለቃ” ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ራሳቸውን በማስገዛታቸውና “የፍቅርና የሰላምም አምላክ” የሆነውን ይሖዋን በማምለካቸው ምክንያት የተገኘ ነው።​—⁠ኢሳይያስ 9:6፤ 2 ቆሮንቶስ 13:11

4. አንድ ክርስቲያን ሰላምን ‘የሚከታተለው’ እንዴት ነው?

4 ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ሰላምን እንዲሁ ያለ ምንም ጥረት ሊያገኙት አይችሉም። ስለሆነም ጴጥሮስ እያንዳንዱ ክርስቲያን ‘ሰላምን መፈለግና መከታተል’ እንዳለበት ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 3:11) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በጥንት ጊዜ የተነገረ አንድ ትንቢት መልሱን ይጠቁመናል። ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 54:13፤ ፊልጵስዩስ 4:9) አዎን፣ እውነተኛውን ሰላም የሚያገኙት ይሖዋ የሚሰጠውን ትምህርቶች የሚከታተሉ ናቸው። ከዚህም በላይ ‘ፍቅርን፣ ደስታን፣ ትዕግሥትን፣ ቸርነትን፣ በጎነትን፣ እምነትን፣ የውሃትን፣ ራስ መግዛትን’ ጨምሮ ሰላም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ ነው። (ገላትያ 5:22, 23) አፍቃሪ፣ ደስተኛ፣ ትዕግሥተኛ፣ ደግ፣ ታማኝ ያልሆነ ወይም ኃይለኛ፣ ክፉና ራሱን የማይገዛ ሰው ሰላም ሊኖረው አይችልም።

“ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ”

5, 6. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት ሰላማዊ መሆን ምን ማለት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ከእነማን ጋር ሰላማዊ ለመሆን ይጣጣራሉ?

5 ሰላም የሚለው ቃል የመረጋጋት ስሜት ወይም ጸጥታ የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ይህ ፍቺ ግጭት አለመኖሩን ብቻ አያመለክትም። የሞተ ሰው እንኳ አረፈ ይባል የለ! ይሁን እንጂ እውነተኛ ሰላም ለማግኘት አንድ ሰው ሰላማዊ ከመሆን የበለጠ ነገር እንዲያደርግ ይጠበቅበታል። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “የሚያስተራርቁ [“ሰላማዊ የሆኑ፣” NW ] ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:9) እዚህ ላይ ኢየሱስ መንፈሳዊ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን አጋጣሚ የሚኖራቸውንና በኋላም በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት የሚያገኙትን ሰዎች በማስመልከት መናገሩ ነበር። (ዮሐንስ 1:12፤ ሮሜ 8:14-17) ሰማያዊ ተስፋ የሌላቸው የተቀሩት ታማኝ የሰው ዘሮችም ‘ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት ይደርሳሉ።’ (ሮሜ 8:21) እንዲህ ያለው ተስፋ የሚኖረው ሰላማዊ የሆነ ሰው ብቻ ነው። “ሰላማዊ” ለሚለው የገባው ግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ሰላም ፈጣሪዎች” ማለት ነው። ብዙውን ጊዜ ለራስ በሰላም በመኖርና ሰላም ፈጣሪ በመሆን መካከል ልዩነት አለ። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሰላማዊ መሆን ማለት ሰላምን ለማስፈን ልባዊ ጥረት ማድረግን፣ አንዳንድ ጊዜ ቀደም ሲል ሰላም ጠፍቶ በነበረበት ቦታ ሰላምን መመለስ ለማመልከት ይሠራበታል።

6 ይህን በአእምሯችን ይዘን ሐዋርያው ጳውሎስ “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” በማለት ለሮሜ ክርስቲያኖች የጻፈውን ደብዳቤ እንመርምር። (ሮሜ 12:18) ምንም እንኳ የተረጋጋ መንፈስ መያዝ ጥሩ ቢሆንም ጳውሎስ የሮሜ ክርስቲያኖችን ይህን መንፈስ እንዲይዙ እየነገራቸው አልነበረም። ሰላም እንዲፈጥሩ እያበረታታቸው ነበር። ከማን ጋር? “ከሰው ሁሉ” ማለትም ከቤተሰብ አባላት፣ ከክርስቲያን ባልደረቦች ሌላው ቀርቶ እምነታቸውን ከማይጋሯቸው ሰዎች ጋር ሳይቀር ሰላም መፍጠር ነበረባቸው። የሮሜ ክርስቲያኖች ‘በእነርሱ በኩል’ ከሌሎች ጋር ሰላም እንዲፈጥሩ አበረታቷቸዋል። ሰላም ለመፍጠር ሲሉ እምነታቸውን እንዲያላሉ አልፈለገም። ሳያስፈልግ ሌሎችን ከማስቆጣት ይልቅ ሰላማዊ ዝንባሌ ይዘው ሊቀርቧቸው ይገባል። ክርስቲያኖች በጉባኤም ሆነ ከጉባኤ ውጭ ካሉ ሰዎች ጋር በዚህ መንገድ ሊመላለሱ ይገባ ነበር። (ገላትያ 6:10) ከዚህ ጋር በመስማማት ጳውሎስ “ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ” በማለት ጽፏል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:15

7, 8. ክርስቲያኖች እምነታቸውን ከማይጋሯቸው ሰዎች ጋር በሰላም የሚኖሩት እንዴትና ለምንድን ነው?

7 እምነታችንን ከማይጋሩን አልፎ ተርፎም ከሚቃወሙን ሰዎች ጋር ሰላማውያን መሆን የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ከሌሎች ልቀን ለመታየት ባለመሞከር ነው። ለምሳሌ ያህል ሌሎችን የሚያንቋሽሽ አነጋገር እየተናገርን ከሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖረን አይችልም። ይሖዋ በአንዳንድ ድርጅቶችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ እንደሚፈርድባቸው ገልጦልናል። ይሁን እንጂ በማንም ግለሰብ ላይ የፍርድ ቃላት የመናገር መብት የለንም። በማንም ላይ በተቃዋሚዎች እንኳ ሳይቀር አንፈርድም። ጳውሎስ በቀርጤስ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሰብዓዊ ባለ ሥልጣናት ፊት ሊኖራቸው ስለሚገባ ጠባይ ምክር እንዲለግሳቸው ለቲቶ ከገለጸለት በኋላ “ማንንም የማይሰድቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ” አሳስቧቸዋል።​—⁠ቲቶ 3:1, 2

8 እምነታችንን ከማይጋሩን ሰዎች ጋር በሰላም መኖራችን እውነትን ለእነርሱ ለማድረስ ይበልጥ ቀላል ያደርግልናል። እርግጥ ነው ‘መልካሙን አመላችንን ሊያጠፋብን’ የሚችል ወዳጅነት እንመሠርታለን ማለት አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ሆኖም አሳቢነት ልናሳይና ሁሉንም ሰው በአክብሮትና በደግነት ልንይዝ ይገባናል። ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፣ በሚጐበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።”​—⁠1 ጴጥሮስ 2:12

በአገልግሎት ሰላም ፈጣሪ መሆን

9, 10. የማያምኑ ሰዎችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መያዝን በሚመለከት ጳውሎስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

9 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በደፋርነታቸው የሚታወቁ ነበሩ። መልእክታቸውን ለስለስ አድርገው ለማቅረብ አልሞከሩም፤ እንዲሁም ተቃውሞ በሚገጥማቸው ጊዜ ቁርጥ ውሳኔያቸው ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያቸው አድርገው መታዘዝ ነበር። (ሥራ 4:29፤ 5:29) ደፋሮች ቢሆኑም ግን ሰዎችን የሚያንጓጥጡ አልነበሩም። ጳውሎስ በዳግማዊ ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ ፊት ቀርቦ ለእምነቱ በተከራከረ ጊዜ የተጠቀመበትን አቀራረብ ልብ በል። ሄሮድስ አግሪጳ ከእህቱ ከበርኒቄ ጋር የፆታ ግንኙነት ይፈጽም ነበር። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ሥነ ምግባርን በሚመለከት ሊነግረው አልፈለገም። ከዚያ ይልቅ አግሪጳ የአይሁድን ልማድ ጠንቅቆ የሚያውቅና በነቢያት የሚያምን መሆኑን አድንቆ በመግለጽ ሁለቱም በጋራ በሚስማሙበት ነጥብ ላይ ትኩረት አድርጓል።​—⁠ሥራ 26:2, 3, 27

10 ጳውሎስ ከእስር እንዲፈታው በማሰብ በውሸት እያሞካሸው ነበር? በጭራሽ። ጳውሎስ ራሱ የሰጠውን ምክር በመከተል እውነቱን ተናግሯል። ለሄሮድስ አግሪጳ የተናገረው ነገር ሁሉ እውነት ነበር። (ኤፌሶን 4:15) ሆኖም ጳውሎስ ሰላም ፈጣሪ ከመሆኑም በላይ “ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ” እንዴት መሆን እንደሚቻል ያውቅ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 9:22) ዋነኛ ዓላማው ስለ ኢየሱስ የመስበክ መብቱን ማስጠበቅ ነበር። ውጤታማ አስተማሪ እንደመሆኑ መጠን እርሱንና አግሪጳን ሊያስማሙ የሚችሉ ነገሮችን በመጥቀስ ንግግሩን ጀመረ። በዚህ መንገድ ጳውሎስ ይህ ሥነ ምግባር የጎደለው ንጉሥ ለክርስትና እምነት የተሻለ አመለካከት እንዲኖረው ረድቶታል።​—⁠ሥራ 26:28-31

11. በአገልግሎታችን ሰላማውያን መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

11 እኛም በአገልግሎታችን ሰላማውያን መሆን የምንችለው እንዴት ነው? እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ጭቅጭቅ ውስጥ ከመግባት መቆጠብ ይኖርብናል። እርግጥ ነው አልፎ አልፎ “የእግዚአብሔርን ቃል . . . ያለ ፍርሃት” በመናገር ለእምነታችን ድፍረት የተሞላበት መከላከያ ማቅረብ ይኖርብን ይሆናል። (ፊልጵስዩስ 1:14) ይሁን እንጂ በአብዛኛው ዋነኛው ዓላማችን ምሥራቹን መስበክ ነው። (ማቴዎስ 24:14) አንድ ሰው አምላክ ስለገባቸው ተስፋዎች የሚናገረውን እውነት ካወቀ የሃሰት ሃይማኖት አስተሳሰቦችን መተውና ርኩስ ከሆኑ ድርጊቶች ራሱን ማንጻት ሊጀምር ይችላል። ስለዚህ በተቻለ መጠን ከእነርሱ ጋር የምንስማማባቸውን ነጥቦች በማንሳት አድማጮቻችንን የሚማርኩ ነገሮችን ጎላ አድርጎ መግለጹ ጥሩ ይሆናል። በዘዴ ብንቀርበው መልእክታችንን ሊያዳምጥ ይችል የነበረውን ግለሰብ ብናስቆጣ ዓላማችንን የሚያከሽፍ ይሆናል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:3

በቤተሰብ ውስጥ ሰላም ፈጣሪ መሆን

12. በቤተሰብ ውስጥ ሰላም ፈጣሪ መሆን የምንችለው በምን መንገዶች ነው?

12 ጳውሎስ ያገቡ “በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) የተለያዩ ችግሮች ያጋጥማሉ። ከሌሎች ችግሮች በተጨማሪ በአንዳንድ ባልና ሚስት መካከል አልፎ አልፎ አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። ይህ መፈታት ያለበት እንዴት ነው? ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፈታት ይኖርበታል። ሰላም ፈጣሪ የሆነ ሰው ሁኔታዎች ከመባባሳቸው በፊት የተፈጠረው ግጭት በአጭሩ እንዲቀጭ ያደርጋል። እንዴት? በመጀመሪያ አንደበቱን በመቆጣጠር ነው። ሽሙጥና የስድብ ቃላት ለመሰንዘር ከተጠቀምንበት ይህ ትንሽ ብልት “የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት” ይሆናል። (ያዕቆብ 3:8) ሰላም ፈጣሪ የሆነ ሰው አንደበቱን የሚጠቀምበት ለማፍረስ ሳይሆን ለመገንባት ነው።​—⁠ምሳሌ 12:18

13, 14. በአንደበታችን በምንስትበት ወይም በስሜት በምንግልበት ጊዜ ሰላምን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ፍጹም ባለመሆናችን ምክንያት ሁላችንም አልፎ አልፎ በኋላ የምንጸጸትበትን ቃል ልንሰነዝር እንችላለን። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ሰላምን ለመፍጠር ፈጣን እርምጃ እንውሰድ። (ምሳሌ 19:11፤ ቆላስይስ 3:13) ‘በቃላት በሚደረግ ክርክር ውስጥ ከመግባትና ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮች ከመጨቃጨቅ’ ራቅ። (1 ጢሞቴዎስ 6:4, 5 NW ) ከዚያ ይልቅ ጉዳዩን በጥልቀት በመመልከት የትዳር ጓደኛህን ስሜቶች ለመረዳት ሞክር። ሻካራ ቃላት ቢሰነዘርብህ አጸፋውን አትመልስ። “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች” የሚለውን አስታውስ።​—⁠ምሳሌ 15:1

14 አንዳንድ ጊዜ ምሳሌ 17:​14 ላይ የሚገኘውን “ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው” የሚለውን ምክር መመልከት ይኖርብህ ይሆናል። በቀላሉ አምባጓሮ እንዲፈጠር ሊያደርጉ ከሚችሉ ሁኔታዎች ራቅ። ቆየት ብለህ በሰከነ መንፈስ ችግሩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት ትችል ይሆናል። አንዳንዴ የጎለመሰ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች እርዳታ መጠየቅ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ተሞክሮ ያካበቱና የሰውን ችግር የሚረዱ እንደነዚህ ያሉት ወንዶች በትዳር ውስጥ ያለው ሰላም በሚናጋበት ጊዜ አስፈላጊውን እርዳታ በመስጠት እንደ መጠጊያ ሊሆኑ ይችላሉ።​—⁠ኢሳይያስ 32:1, 2

በጉባኤ ውስጥ ሰላም ፈጣሪ መሆን

15. ያዕቆብ እንደተናገረው በአንዳንድ ክርስቲያኖች ዘንድ ምን መጥፎ ባሕርይ አቆጥቁጦ ነበር? ይህስ መንፈስ “የምድር፣” ‘የሥጋ፣’ እና ‘የአጋንንት’ እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸው ለምንድን ነው?

15 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የሰላም ፍጹም ተቃራኒ የሆነው የቅናትና የራስ ወዳድነት መንፈስ ይታይባቸው ነበር። ያዕቆብ እንዲህ አለ:- “ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፣ የሥጋም ነው፣ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና።” (ያዕቆብ 3:14-16) አንዳንዶች “አድመኝነት” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በራስ ወዳድነት ላይ ተመሥርቶ ሥልጣን ለማግኘት ጥረት ማድረግን ያመለክታል ይላሉ። ያዕቆብ “የምድር ነው፣ የሥጋም ነው፣ የአጋንንትም ነው” ብሎ የተናገረው ያለ ምክንያት አይደለም። በታሪክ ዘመናት ሁሉ የዓለም ገዥዎች እንደ አውሬ እርስ በርስ ሲባሉ ኖረዋል። አድመኝነት በእርግጥም “የምድር” እና ‘የሥጋ’ እንዲሁም ‘የአጋንንት’ ነው። እንዲህ ያለውን መሰሪ ባሕርይ ለመጀመሪያ ጊዜ ያንጸባረቀው የሥልጣን ጥም ያሰከረውና ይሖዋን በመቃወም ራሱን የአጋንንት ገዥ ያደረገው ሰይጣን ነው።

16. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የሰይጣን ዓይነት መንፈስ ያንጸባረቁት እንዴት ነው?

16 ያዕቆብ አድመኝነት የሰላም ፀር በመሆኑ ይህን ባሕርይ እንዲዋጉት ክርስቲያኖችን አሳስቧል። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ [“ከሥጋዊ ምኞታችሁ፣” የ1980 ትርጉም ] አይደሉምን? (ያዕቆብ 4:1) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘ምኞት’ የሚለው ቃል በመስገብገብ ቁሳዊ ነገሮችን መመኘት ወይም ታዋቂ፣ የበላይ ወይም በሌሎች ላይ የመሠልጠንን ምኞት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹን አስመልክቶ እንደተናገረው ከሌሎች ‘አንሰው’ ከመታየት ይልቅ እንደ ሰይጣን ልቀው መታየት የሚፈልጉ ይመስላል። (ሉቃስ 9:48) እንዲህ ያለው መንፈስ ጉባኤውን ሰላም ሊነሳ ይችላል።

17. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ሰላም ፈጣሪዎች መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

17 በዛሬውም ጊዜ ፍቅረ ነዋይን፣ ቅናትን ወይም ከሌሎች ልቆ የመታየትን ምኞት መቋቋም ይገባናል። በእርግጥ ሰላም ፈጣሪዎች ከሆንን በጉባኤ ውስጥ አንዳንዶች ከእኛ የተሻለ ችሎታ ቢኖራቸው ቅር አንሰኝም ወይም የውስጥ ግፊታቸው አጠያያቂ እንደሆነ አድርገን በማቅረብ ሌሎች በጥርጣሬ ዓይን እንዲመለከቷቸው አናደርግም። አንድ ዓይነት ለየት ያለ ችሎታ ቢኖረን ጉባኤው ሊባረክ የሚችለው በእኛ ችሎታና እውቀት እንደሆነ በሚያስመስልና ከሌሎች የተሻልን እንደሆንን አድርጎ በሚያሳይ መንገድ አንጠቀምበትም። እንዲህ ያለው መንፈስ መከፋፈልን እንጂ ሰላምን አያመጣም። ሰላም ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች በተሰጥዎቻቸው ከሌሎች ልቀው ለመታየት አይሞክሩም። ከዚያ ይልቅ ትሁቶች በመሆን ወንድሞቻቸውን ለማገልገልና ለይሖዋ ክብር ለማምጣት ይጠቀሙበታል። ደግሞም እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይቶ የሚያሳውቃቸው ችሎታ ሳይሆን ፍቅር እንደሆነ ይገነዘባሉ።​—⁠ዮሐንስ 13:35፤ 1 ቆሮንቶስ 13:1-3

“አለቆችሽንም ሰላም . . . አደርጋለሁ”

18. ሽማግሌዎች በመካከላቸው ሰላም ማስፈን የሚችሉት እንዴት ነው?

18 ሰላም ፈጣሪ በመሆን ረገድ የጉባኤ ሽማግሌዎች ቀዳሚ ሆነው ይገኛሉ። ይሖዋ ሕዝቡን በተመለከተ “በናስ ፋንታ ወርቅን፣ በብረትም ፋንታ ብርን፣ በእንጨትም ፋንታ ናስን፣ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፣ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ” በማለት ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 60:17) ከእነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ጋር በመስማማት ክርስቲያን እረኞች ሆነው የሚያገለግሉ ሁሉ በመካከላቸውም ሆነ በመንጋው መካከል ሰላምን ለማስፈን ጠንክረው ይሠራሉ። ሽማግሌዎች ‘የላይኛይቱ ጥበብ’ ክፍል የሆኑትን ሰላምንና ምክንያታዊነትን በማንጸባረቅ በመካከላቸው ያለውን ሰላም መጠበቅ ይችላሉ። (ያዕቆብ 3:17) በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች ከአስተዳደጋቸውና ካላቸው ተሞክሮ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል። ይህ ማለት ታዲያ በመካከላቸው ሰላም የለም ማለት ነው? እንዲህ ያለው ሁኔታ ተገቢ በሆነ መንገድ ከተያዘ እንደዚያ ማለት አይደለም። ሰላም ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች በትህትና ሐሳባቸውን ይገልጣሉ እንዲሁም ሌሎች ሲናገሩ በአክብሮት ያዳምጣሉ። ሰላም ፈጣሪ የሆነ ሰው እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ ከማለት ይልቅ የወንድሙን አመለካከት በጸሎት ይመረምራል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ የተለያዩ አመለካከቶችን ለማስተናገድ ፈቃደኛ መሆን ምንም አይደለም። ሰላም ፈጣሪ የሆነ ሰው ሌሎች የእርሱን ሐሳብ በማይደግፉበት ጊዜ በብዙሃኑ ሐሳብ ይስማማል። በዚህ መንገድ ምክንያታዊ መሆኑን ያሳያል። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 3) ተሞክሮ ያላቸው የበላይ ተመልካቾች ለሰላም ሲባል የራስን አመለካከት ወደጎን ማድረጉ የተሻለ እንደሆነ ያውቃሉ።

19. ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ሰላም ፈጣሪዎች የሚሆኑት እንዴት ነው?

19 ሽማግሌዎች መንጋውን በመደገፍና የሚያደርጉትን ጥረት ከመንቀፍ በመቆጠብ በመንጋው መካከል ሰላምን ያሰፍናሉ። እርግጥ ነው አንዳንዶች አልፎ አልፎ መስተካከል ያስፈልጋቸው ይሆናል። (ገላትያ 6:1) ይሁን እንጂ የክርስቲያን የበላይ ተመልካች ተቀዳሚ ሥራ እርማት መስጠት አይደለም። ብዙውን ጊዜ ያመሰግናሉ። አፍቃሪ ሽማግሌዎች የሌሎችን መልካም ባሕርይ ለመመልከት ጥረት ያደርጋሉ። የበላይ ተመልካቾች ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ጠንክረው ሲሠሩ አድናቆታቸውን ይገልጹላቸዋል እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቻቸው አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ያህል እየሠሩ እንዳሉ ይተማመኑባቸዋል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 2:3, 4

20. ሁሉም ሰላም ፈጣሪ መሆኑ ጉባኤውን የሚጠቅመው እንዴት ነው?

20 ስለዚህ በቤተሰብ ውስጥ፣ በጉባኤ ውስጥና እምነታችንን ከማይጋሩ ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ሰላምን ለመከታተልና ሰላምን ለማስፈን እንጥራለን። ሰላምን በመኮትኮት ረገድ ትጉዎች ከሆንን ጉባኤው ደስተኛ እንዲሆን አስተዋጽዖ እናበረክታለን። በተመሳሳይም በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው በብዙ መንገድ ጥበቃና ብርታት እናገኛለን።

ታስታውሳለህ?

• ሰላማዊ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

• ምሥክር ካልሆኑ ሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ሰላማዊ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

• በቤተሰብ ውስጥ ሰላምን መኮትኮት የሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

• ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ሰላምን ማስፈን የሚችሉት እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰላም ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ከሌሎች ልቀው ለመታየት አይሞክሩም

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች በአገልግሎት፣ በቤትና በጉባኤ ውስጥ ሰላም ፈጣሪዎች ናቸው