በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በፈረንሳይ ምን እየተከናወነ ነው?”

“በፈረንሳይ ምን እየተከናወነ ነው?”

“በፈረንሳይ ምን እየተከናወነ ነው?”

“ላ ማርሴዬዝ” በተባለው የፈረንሳይ ብሔራዊ መዝሙር ላይ “ነፃነት፣ ክቡር የሆነው ነፃነት” የሚሉት ቃላት ይገኛሉ። ነፃነት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነገር እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። ሆኖም በፈረንሳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናወኑ ያሉት ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት መሠረታዊ የነፃነት መብቶች እየተረገጡ መምጣታቸው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። ለዚህም ነው ዓርብ፣ ኅዳር 3, 2000 በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች “በፈረንሳይ ምን እየተከናወነ ነው? ነፃነት እየጠፋ ይሆን?” የሚል ርዕስ ያለውን አንድ ልዩ ትራክት 12 ሚልዮን ቅጂዎች አሰራጭተዋል።

በፈረንሳይ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ ዓመታት ከተለያዩ የፖለቲካ ሰዎችና ፀረ ኑፋቄ ቡድኖች ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል። ይህ በግለሰብ፣ በጉባኤ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሯል። ይሁን እንጂ ሰኔ 23, 2000 ኮንሴይ ዴታ የሚባለው የፈረንሳይ ከፍተኛ የአስተዳደር ፍርድ ቤት ከ1, 100 በላይ በሚሆኑ ክሶች ላይ 31 የበታች ፍርድ ቤቶች የነበራቸውን አቋም የሚያጸና አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነ ውሳኔ አስተላልፏል። ከፍተኛው ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት አምልኮ ከፈረንሳይ ሕግ ጋር ሙሉ በሙሉ ስምም እንደሆነ እንዲሁም የመንግሥት አዳራሾቻቸው እንደ ሌሎች ሃይማኖቶች ከቀረጥ ነፃ የመሆን መብት ማግኘት እንደሚችሉ አረጋግጧል።

ይሁን እንጂ የፈረንሳይ ገንዘብ ሚኒስቴር ይህን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ የአገሪቱ ሕግ ለሃይማኖታዊ ድርጅቶች የሰጠውን ከቀረጥ ነፃ የመሆን መብት የይሖዋ ምሥክሮችን እንደነፈገ ነው። የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በፈረንሳይ በሚገኙ 1, 500 ጉባኤዎች ውስጥ የሚሰበሰቡ ምሥክሮችና ጓደኞቻቸው በሚሰጡት መዋጮ ላይ የ60 በመቶ ቀረጥ ጥሏል። በአሁኑ ጊዜ ይህ ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ ነው።

ከላይ የተጠቀሰው ዘመቻ ዓላማ ይህን አወዛጋቢ ጉዳይ ማጋለጥ ከመሆኑም በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ በፍርደ ገምድልነት የሚጣል ቀረጥና የሰዎችን ሁሉ ሃይማኖታዊ ነፃነት ሊገድብ የሚችለው ረቂቅ አዋጅ ለሚያስከትሉት አደጋ ትኩረት እንዲሰጥ ማድረግ ነው። a

ረጅም ቀን

በአንዳንድ ጉባኤዎች የሚገኙ ምሥክሮች ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ በባቡር ጣቢያዎችና ፋብሪካዎች ከዚያም በአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ትራክቱን ማሰራጨት ጀመሩ። ከጠዋቱ በ12 ሰዓት ፓሪስ ሕይወት ትዘራለች። ወደ 6, 000 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሥራ የሚሄዱ የፈረቃ ሠራተኞችን ለማግኘት አመቺ ቦታዎች ላይ ቆመዋል። አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “የሃይማኖት ነፃነት እንዲከበር የምታደርጉት ጥረት የሚያስመሰግን ነው። ጉዳዩ የይሖዋ ምሥክሮችን ብቻ የሚመለከት አይደለም።” በማርሴይ ከ350 በላይ ምሥክሮች በምድር ውስጥ የባቡር ጣቢያዎችና በጎዳናዎች ላይ ትራክቱን አበርክተዋል። በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ የፈረንሳይ ብሔራዊ ራዲዮ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ቀርበው ቢያነጋግሯቸው ግር እንዳይላቸው አድማጮቹን በማሳሰብ ዘመቻውን አስተዋወቀ። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት በስትራስቡርግ ብሔራዊ ባቡር ጣቢያ የነበሩ መንገደኞች ተሰልፈው በመጠበቅ የግል ቅጂያቸውን ወስደዋል። አንድ ጠበቃ የእኛ እምነት ተከታይ ባይሆንም እንኳ የምንታገልለት ጉዳይ አስፈላጊና ተገቢ ስለሆነ የፍርድ ቤት ጉዳያችንን በከፍተኛ ጉጉት እየተከታተለ መሆኑን ተናግሯል።

ጠዋት ሁለት ሰዓት ላይ የአልፓይን ከተማ በሆነችው በግረኖብል ኃይለኛ ዝናብ ቢጥልም እንኳ 507 ምሥክሮች በጎዳናዎች ላይ ለሚያገኙት ለእያንዳንዱ ሰው ትራክቱን ሰጥተዋል አሊያም ፓስታ ሣጥኖች ውስጥ ከትተዋል። ሹፌሮችና የከተማ ባቡር አሽከርካሪዎች አንድ ነገር እየተካሄደ መሆኑን በመመልከት ተሽከርካሪዎቻቸውን አቁመው ትራክት እንዲሰጣቸው ይጠይቁ ነበር። በስተ ምዕራብ ወደምትገኘው ፕዋትዬ በባቡር ተጉዘው ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ የደረሱ መንገደኞች ገና ከመነሻቸው ትራክቱ ደርሷቸው ነበር። ጀርመን ጠረፍ አቅራቢያ በምትገኘው በመሉዝ 40, 000 ቅጂዎች ተበርክተዋል።

ከቀኑ አራት ሰዓት ላይ ብዙ ጉባኤዎች በእጃቸው ከነበረው ትራክት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን አበርክተዋል። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ እየተገባደደ ሲሄድ በርካታ አስደሳች ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን ትራክቱን መውሰድ ያልፈለጉት ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ከስዊስ ጠረፍ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በበዛንሶ የሚኖር አንድ ወጣት መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎት እንዳለው የገለጸ ከመሆኑም በላይ አምላክ ለምን ሥቃይ እንዲኖር እንደፈቀደ ጠይቋል። ምሥክሩ በአቅራቢያው ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ሄደው ውይይቱን ለመቀጠል ሐሳብ ያቀረበለት ሲሆን እዚያም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተባለው ብሮሹር አማካኝነት ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ።

እኩለ ቀን ላይ ብዙ ምሥክሮች የምሳ ሰዓት እረፍታቸውን በመጠቀም ለአንድ ወይም ለሁለት ሰዓት ያህል አገልግለዋል። ከሰዓት በኋላም ስርጭቱ ቀጥሎ በርካታ ጉባኤዎች ዘጠኝ ወይም አሥር ሰዓት ገደማ ትራክቱን አበርክተው ጨርሰዋል። አንጋፋ ሻምፓኝ አምራች ከተማ በሆነችው በሪምዝ የሚኖሩ ከዚህ በፊት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያጠኑና ይሰበሰቡ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ከጉባኤ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በአዲስ መልክ የመጀመር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። በቦርዶ ሦስት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተጀምረዋል። በዚያው ከተማ አንዲት ምሥክር ጋዜጣ ለመግዛት ወደ ሱቅ ገብታ መደርደሪያው ላይ ብዙ ትራክት ተከምሮ አየች። ከዚህ ቀደም የይሖዋ ምሥክር የነበረችው የሱቁ ባለቤት ትራክቱ የደረሳት ከመሆኑም በላይ አስፈላጊነቱን ስለተገነዘበች ራሷ የምታበረክተው እንዲኖራት ብዙ ፎቶ ኮፒዎች አዘጋጅታ ነበር።

በለ አቭር፣ ኖርሞንዲ የምትኖር አንዲት ፕሮቴስታንት ወይዘሮ የይሖዋ ምሥክሮች ከሚሰጡት መዋጮ ላይ ቀረጥ እንደሚወሰድ በራዲዮ ስትሰማ በጣም ተገረመች። ትራክቱን በደስታ የተቀበለች ከመሆኑም በላይ ምሥክሮቹ እንዲህ ዓይነቱን የፍትሕ መጓደል በድፍረት በመቃወማቸው አድናቆቷን ገልጻለች። ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ20 ላይ በሊዮን ክልል የሚቀርበው የቴሌቪዥን ዜና ስርጭቱን በተመለከተ እንደሚከተለው በማለት ዘግቧል:- “ዛሬ ጠዋት ከይሖዋ ምሥክሮች ትራክት ለማምለጥ ከመሞከር ይልቅ በዝናብ ውስጥ የዝናብ ጠብታ ሳይነካችሁ መሄድ ይቀልል ነበር።” ሁለት ምሥክሮች ቃለ መጠይቅ ቀርቦላቸው ዘመቻው የተካሄደበትን ምክንያት አስረድተዋል።

ከሥራ ሲወጡ በዘመቻው መካፈል የፈለጉ ምሥክሮች የተወሰኑ ትራክቶችን ከፈረቃ ሥራ ለሚመለሱ ሰዎች ማበርከትና ሌሎች ትራክቶችን ደግሞ የፖስታ ሣጥኖች ውስጥ ማስቀመጥ ችለዋል። እንደ ብሬስት እና ሊሞዝ በመሳሰሉ በሸክላ ሥራ በታወቁ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ትራክቱ የደረሳቸው ከሌሊቱ 5 ሰዓት ከፊልም ቤት ሲወጡ ሲሆን በዕለቱ የመጨረሻዎቹ ሰዎች ነበሩ። ቀሪዎቹ ትራክቶች በቀጣዩ ቀን ጠዋት ተበርክተዋል።

የተገኙ ውጤቶች

አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ባላጋራዎቻችን እያዳከሙን እንዳሉ ይሰማቸው ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እየታየ ያለው የዚያ ተቃራኒ ነው።” በአብዛኞቹ ጉባኤዎች ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑ ምሥክሮች በዕለቱ በዘመቻው የተሳተፉ ከመሆናቸውም በላይ አንዳንዶቹ በዚህ እንቅስቃሴ 10, 12 ወይም 14 ሰዓት አሳልፈዋል። በሰሜን ፈረንሳይ በምትገኘው በኢም የሚኖር የሌሊት ተረኛ የሆነ አንድ ምሥክር ከሥራ መልስ ከማለዳው 11 ሰዓት ጀምሮ እስከ ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ትራክቱን አሠራጭቷል። በአቅራቢያዋ በምትገኘው በደነ ከ1906 አንስቶ ጉባኤ የነበረ ሲሆን አርብ ዕለት 75 ምሥክሮች ትራክቱን በማበርከት 200 ሰዓት አሳልፈዋል። ሌሎች ደግሞ እርጅናና የአካል ጉዳት እንዲሁም መጥፎ የአየር ጠባይ ሳይበግራቸው በዘመቻው ተሳትፈዋል። ለምሳሌ ያህል ለ ማ በምትባለው ከተማ የሚኖሩ በ80ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሦስት እህቶች ትራክቱን ፖስታ ሣጥኖች ውስጥ በመጨመር ወደ ሁለት ሰዓት ያሳለፉ ሲሆን በተሽከርካሪ ወንበር የሚንቀሳቀስ አንድ ወንድም ደግሞ ባቡር ጣቢያው ፊት ለፊት ትራክቱን አበርክቷል። በፊት አገልግሎት አቁመው የነበሩ በርካታ ምሥክሮች በዚህ ልዩ እንቅስቃሴ ተሳትፎ ሲያደርጉ ማየቱ ምንኛ አበረታች ነበር!

ይህ የትራክት ስርጭት ከፍተኛ ምሥክርነት መስጠት እንዳስቻለ ጥርጥር የለውም። የተለያየ የኑሮ ደረጃ ያላቸው፣ አብዛኞቹም ቤታቸው የማይገኙ ሰዎች የትራክቱን ቅጂ አግኝተዋል። በርካታ ግለሰቦች ይህ ዘመቻ የምሥክሮቹን ጥቅም ከማስጠበቅም በላይ የላቀ ተግባር እንዳከናወነ ተሰምቷቸዋል። ብዙዎች ዘመቻው የመላውን የፈረንሳይ ሕዝብ የሕሊናና የአምልኮ ነፃነት የሚያስከብር እንደሆነ አድርገው ተመልክተውታል። ሰዎች ትራክቱን ለጓደኞቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው ወይም ለዘመዶቻቸው ለመስጠት ተጨማሪ ቅጂ መጠየቃቸው ለዚህ ማስረጃ ነው።

አዎን፣ በፈረንሳይ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የይሖዋን ስም በማሳወቃቸውና የመንግሥቱን ፍላጎቶች በማስጠበቃቸው ኩራት ይሰማቸዋል። (1 ጴጥሮስ 3:​15) ‘እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለው ለመኖር’ እንዲሁም ሰማያዊ አባታቸው ይሖዋን በማወደስ ረገድ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ከእነሱ ጋር እንዲተባበሩ ልባዊ ምኞታቸው ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​2

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በጥር 1999 ሃይማኖታዊ መድልዎን በመቃወም ተመሳሳይ ዘመቻ ተካሂዶ ነበር። የነሐሴ 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 9ን እና የ 2000 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 24-6ን ተመልከት።