አመስጋኝ በመሆን ደስታ አትርፉ
አመስጋኝ በመሆን ደስታ አትርፉ
ካልጋሪ ሄራልድ የተባለ አንድ የካናዳ ጋዜጣ “ለማመስገን መገፋፋት የሰው ልጅ መሠረታዊ ባሕርይ ነው” በማለት ዘግቧል። ጋዜጣው የሚያመሰግኑት ምን ምን ስለተደረገላቸው እንደሆነ እንዲጽፉ አስተማሪያቸው ያዘዛቸውን አንዳንድ የዘጠኝ ዓመት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጠቅሷል። አንድ ወጣት ቤተሰቦቹ ‘እሱን ለማሳደግ ስላደረጉት ጥረት’ እንደሚያመሰግናቸው ተናግሯል። አንዲት ወጣት ልጅም እንዲሁ “ችግር እንዳይደርስብኝ ይጠብቁኛል፣ ጤንነቴን ይንከባከባሉ፣ ያስቡልኛል፣ ይወዱኛል እንዲሁም ይመግቡኛል። ወላጆቼ ባይኖሩ ኖሮ በዚች ምድር ላይ በሕይወት አልኖርም ነበር” ስትል ቤተሰቧን አመስግናለች።
ምስጋና ቢስ መሆን እርካታ ወደ ማጣት ይመራል። ፈላስፋና የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ጄ አይ ፓከር እንደተናገሩት “የተፈጠርነው በአምላክ ላይ ጥገኞች ሆነን እንድንኖር ሲሆን እርስ በርሳችንም አንዳችን የሌላው ጥገኞች ነን።” ይህ አባባል ከብዙ ዘመናት በፊት የተነገረውን “የምታመሰግኑም ሁኑ” የሚለውን ጥበብ ያለበት የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ያስታውሰናል። (ቆላስይስ 3:15) አመስጋኝነትን በተለያዩ መንገዶች መግለጽና ሌሎችን ከልብ ማድነቅ እርስ በርስ የመተሳሰብ ስሜት እንዲዳብር ይረዳል።
ከዚህም በተጨማሪ እርስ በርስ በመመሰጋገንና አንዱ ለሌላው ከፍ ያለ ግምት በመስጠት ለይሖዋ ያለንን አመስጋኝነት ማሳየት የምንችል ሲሆን ይሖዋም ይህን ይመለከትልናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና” በማለት ይናገራል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) አምላክ ሰዎች ለስሙ የሚያሳዩትን ፍቅር እንደማይረሳና ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጠው ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ዕብራውያን 6:10) አዎን ይህን አምላካዊ ባሕርይ በየዕለቱ ማሳየታችን ይሖዋን ስለሚያስደስትና እኛም እንድንደሰት አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ አመስጋኞች የምንሆንበት በቂ ምክንያት አለን። ምሳሌ 15:13 እንደሚናገረው “ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል።”