በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውን ዲያብሎስ አለ?

እውን ዲያብሎስ አለ?

እውን ዲያብሎስ አለ?

“ቁጥራቸው እየተመናመነ የመጣ ሰዎች በዛሬው ጊዜም ‘አምላክ’ እውንና ብርቱ አካል ሆኖ እንደሚታያቸው ሁሉ የክፋት ንጉሥ የሆነው ዲያብሎስ ማለትም ብዔልዜቡል ወይም ሰይጣን በክርስትና እምነት ታሪክ ከዚያ በማይተናነስ እውንና ብርቱ አካል እንደሆነ የሚታመንበት ወቅት ነበር። ዲያብሎስ አይሁዶችና የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች በዙሪያቸው የሚያዩትን ክፋት ከአንድ ነገር ጋር ለማያያዝ ሲሉ ግማሽ ሰው፣ ግማሽ አውሬ አድርገው ያቀረቡት ፈጠራ ነው። ከጊዜ በኋላ ክርስቲያኖች ይህ ተጨባጭ መሠረት የሌለው ቅዠት የወለደው አካል መሆኑን ተገንዝበው በስውር ትተውታል።”​—⁠ሉዶቪክ ኬኔዲ ያዘጋጀው ኦል ኢን ዘ ማይንድ​—⁠ኤ ፌርዌል ቱ ጎድ

ደራሲ እንዲሁም የራዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ የሆኑት ሉዶቪክ ኬኔዲ ለበርካታ መቶ ዘመናት የዲያብሎስን ሕልውና የተጠራጠረ አንድም የሕዝበ ክርስትና አባል አልነበረም ሲሉ ገልጸዋል። እንዲያውም አልፎ አልፎ ክርስቲያኖች “ሰይጣንና አጋንንቱ ያላቸው ኃይል በጣም ያስጨንቃቸው” እንደነበር ፕሮፌሰር ኖርማን ኮኸን ገልጸዋል። (ዩሮፕስ ኢነር ዲመንስ) ይህ ጭንቀት የሚሰማቸው ተራና ያልተማሩ ገበሬዎች ብቻ አልነበሩም። ፕሮፌሰር ኮኸን ለዚህ ምሳሌ ሲጠቅሱ ዲያብሎስ ክፋትንና ጸያፍ የአምልኮ ሥርዓቶችን በበላይነት ለመምራት በእንስሳ መልክ ይገለጣል የሚለው እምነት “ፊደል ያልቆጠረው ብዙሐኑ የሚያምንበት ሐሳብ ሳይሆን ከዚህ በተቃራኒ በዓለም አስተያየት የላቀ ደረጃ አላቸው የሚባሉ ምሁራን ያመኑበት ነው” ብለዋል። የተማሩ ቀሳውስትን ጨምሮ እነዚህ “የላቀ ደረጃ ያላቸው ምሁራን” ከ15ኛው እስከ 17ኛው መቶ ዘመን በመላው አውሮፓ ጠንቋዮች እየታደኑ ለተያዙበትና ጠንቋዮች ናችሁ በሚል ውንጀላ ቤተ ክርስቲያንና የሕዝብ ባለሥልጣናት ሥቃይና ግድያ እንደፈጸሙባቸው ለሚነገረው ወደ 50, 000 ገደማ ሕይወት ተጠያቂ ናቸው።

ብዙዎች ዲያብሎስን በተመለከተ ያለው አመለካከት የተጋነነና በአጉል እምነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ በማሰብ ጉዳዩን መተዋቸው ምንም አያስደንቅም። ሌላው ቀርቶ በ1726 እንኳ ዳንየል ዲፎ፣ ዲያብሎስ “የሌሊት ወፍ ክንፍ፣ ቀንድ፣ የተሰነጠቀ ሰኮና፣ ረጅም ጅራት፣ መንታ ምላስ እና የመሳሰሉት ያሉት” አስፈሪ ጭራቅ እንደሆነ ያምኑ የነበሩ ሰዎችን ተችቷል። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ “ዲያብሎስ ይህን ይመስላል በማለት የሌለውን ፈጥረው” “ራሳቸው ባመጡት ዲያብሎስ ምንም የማያውቀውን ዓለም ለማታለል” የሠሩት “ደካማ አእምሮ ያመነጨው ከንቱ ነገር” ነው ብሏል።

ያንተም አመለካከት ይህ ነውን? “እንደ እውነቱ ከሆነ ዲያብሎስ ሰዎች ለኃጢአተኝነታቸው ምክንያት ለማቅረብ የፈጠሩት ነው” በሚለው ሐሳብ ትስማማለህ? ይህ አባባል ዘ ዞንደርቫን ፒክቶሪያል ኢንሳይክሎፔዲያ ኦቭ ዘ ባይብል በተባለው መጽሐፍ ላይ የወጣ ከመሆኑም በላይ ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙዎች እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ አላቸው። ጄፍሪ ብሩቶን ራስል፣ የሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት ምሁራን በጥቅሉ “ዲያብሎስንና አጋንንትን ጥንታዊ አጉል እምነቶች እንደሆኑ በመቁጠር ከአእምሮአቸው አውጥተዋቸዋል” በማለት ተናግረዋል።

ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ዲያብሎስ እውን መሆኑን ፈጽሞ አይጠራጠሩም። በሰው ልጅ ታሪክ በተደጋጋሚ ከታየው ክፋት በስተጀርባ አንድ ዓይነት ከሰው በላይ የሆነ አደገኛ ኃይል መኖር አለበት ብለው ያስባሉ። ራስል “በሀያኛው መቶ ዘመን የተከሰቱት አሰቃቂ ሁኔታዎች ከረጅም ጊዜ በኋላ በዲያብሎስ ሕልውና ማመን ይህን ያህል በፍጥነት እያንሰራራ” ለመጣበት ምክንያት አንድ ማስረጃ ይሆነናል ብለዋል። ደራሲው ዳን ሉዊስ እንዳሉት “መሃይማን የሆኑ አባቶቻቸው” በሚከተሉት አጉል እምነትና ፍርሃት “በንቀት ያፌዙ” የነበሩ በርካታ ዘመናውያን የተማሩ ሰዎች “ከሰብዓዊ ተፈጥሮ ውጪ የሆነ ክፉ አካል መኖሩን ቀስ በቀስ እያመኑ መጥተዋል።”​—⁠ሪሊጅየስ ሱፐርስቲሽን ስሩ ዚ ኤጅስ

ታዲያ እውነታው ምንድን ነው? ዲያብሎስ እንዲያው አጉል እምነት የፈጠረው ነገር ነውን? ወይስ በዚህ በ21ኛው መቶ ዘመን ጭምር ሳይቀር እንደ ተራ ነገር መታየት የሌለበት አካል?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጉስታቭ ዶሬ በቀረጸው በዚህ ሥዕል ላይ እንደሚታየው ጥንታዊ አፈ ታሪኮች ዲያብሎስን ግማሽ ሰው፣ ግማሽ አውሬ አድርገው ይገልጹታል

[ምንጭ]

The Judecca​—Lucifer/The Doré Illustrations For Dante’s Divine Comedy/Dover Publications Inc.