በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቶስ ሰላም በልባችን ሊገዛ የሚችለው እንዴት ነው?

የክርስቶስ ሰላም በልባችን ሊገዛ የሚችለው እንዴት ነው?

የክርስቶስ ሰላም በልባችን ሊገዛ የሚችለው እንዴት ነው?

“በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ።”—⁠ቆላስይስ 3:15

1, 2. “የክርስቶስ ሰላም” በአንድ ክርስቲያን ልብ ውስጥ የሚገዛው በምን መንገድ ነው?

 መገዛት የሚለው ቃል ማስገደድንና ጭቆናን ወደ አእምሯቸው ስለሚያመጣ በብዙዎች ዘንድ የሚወደድ ቃል አይደለም። ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ “የኢየሱስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ” በማለት የሰጠው ጥብቅ ምክር አንዳንዶች ምክንያታዊነት የጎደለው እንደሆነ አድርገው እንዲያስቡ አድርጓቸው ሊሆን ይችላል። (ቆላስይስ 3:15) የፈለግነውን የመምረጥ ነፃነት ያለን ፍጡራን አይደለንም? ማንም ወይም ምንም ነገር በልባችን እንዲገዛ የምንፈቅድበት ምክንያት ምንድን ነው?

2 ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች የመምረጥ ነፃነታችሁን ታጣላችሁ እያላቸው አልነበረም። ቆላስይስ 3:​15 ላይ የሚገኘው ‘ይግዛ’ ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በዘመኑ ይደረግ በነበረው የስፖርት ውድድር ላይ ሽልማት የሚሰጥን ዳኛ ለማመልከት ከሚሠራበት ቃል ጋር ተዛማጅነት አለው። ተወዳዳሪዎቹ የጨዋታውን ሕግ ሳይጥሱ በተወሰነ መጠን ነፃነት ነበራቸው። ሆኖም በመጨረሻ ማን ሕጉን እንደተከተለና በዚህም መሠረት ውድድሩን እንዳሸነፈ የሚወስነው ዳኛው ነው። በተመሳሳይም እኛ በሕይወታችን ውስጥ በርካታ ውሳኔዎችን የማድረግ ነፃነት አለን። ሆኖም እንዲህ ስናደርግ የክርስቶስ ሰላም ሁልጊዜ በልባችን ውስጥ “ሊዳኝ” ወይም ኤድገር ጆንሰን ጄ ጎድስፒድ የተባሉ ተርጓሚ እንዳስቀመጡት ልባችንን “ሊቆጣጠረው” ይገባል።

3. “የክርስቶስ ሰላም” ምንድን ነው?

3 “የክርስቶስ ሰላም” ምንድን ነው? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስንሆን የምናገኘውና በይሖዋ አምላክ እና በልጁ ዘንድ የተወደድንና ተቀባይነት ያገኘን መሆናችንን በማወቅ የሚሰማን ውስጣዊ የመረጋጋት ስሜት ነው። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ተለይቶ የሚሄድበት ጊዜ ተቃርቦ በነበረበት ጊዜ “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ . . . ልባችሁ አይታወክ አይፍራም” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:27) የክርስቶስ አካል አባላት የሆኑት ታማኝ ቅቡዓን ላለፉት 2, 000 ዓመታት ገደማ ይህ ሰላም አብሯቸው የነበረ ሲሆን በዛሬው ጊዜ ያሉት ጓደኞቻቸው የሆኑት ‘ሌሎች በጎችም’ ይህ ሰላም አላቸው። (ዮሐንስ 10:16) ይህ ሰላም ልባችንን ሊቆጣጠር ይገባል። ከባድ መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ ይህ ሰላም በፍርሃት እንዳንብረከረክ ወይም በከፍተኛ ጭንቀት እንዳንዋጥ ሊረዳን ይችላል። በደል በሚፈጸምብን ጊዜ፣ በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜና ዋጋ እንደሌለን ሆኖ በሚሰማን ጊዜ ይህ እውነት የሆነው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

በደል በሚፈጸምብን ጊዜ

4. (ሀ) ኢየሱስ ግፍ የተፈጸመበት እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ለተፈጸመባቸው ግፍ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?

4 ንጉሥ ሰሎሞን “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” በማለት ተናግሯል። (መክብብ 8:9) ኢየሱስ እነዚህ ቃላት እውነት መሆናቸውን ያውቃል። ሰማይ በነበረበት ጊዜ ሰዎች በሰዎች ላይ ይፈጽሙ የነበረውን ከባድ ግፍ ተመልክቷል። ምድር እያለም ከኃጢአት ነፃ ሆኖ ሳለ አምላክን ሰድበሃል ተብሎ ተከስሶ እንደ ወንጀለኛ በተገደለ ጊዜ በእርሱም ላይ ከሁሉ የከፋ ግፍ ተፈጽሞበታል። (ማቴዎስ 26:63-66፤ ማርቆስ 15:27) በዛሬውም ጊዜ ግፍ በሰፊው የሚፈጸም ሲሆን እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘በአሕዛብ ሁሉ የተጠሉ’ በመሆናቸው ከሌሎች የበለጠ ተጠቂዎች ናቸው። (ማቴዎስ 24:9) በናዚ የሞት ካምፕና በሶቪዬት የጉልበት ሥራ በሚሠራበት ካምፕ ውስጥ አሰቃቂ በደል እየተፈጸመባቸው፣ የሕዝብ ዓመፅ፣ የሐሰት ክስና ጥቃት እየተሰነዘረባቸው እንኳ የክርስቶስ ሰላም አጽንቷቸዋል። “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፣ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ” የተባለለትን የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለዋል።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:23

5. በጉባኤ ውስጥ በደል እንደተፈጸመ ቢነገረን በመጀመሪያ ማጤን ያለብን ምንድን ነው?

5 ከላይ የተገለጸውን ሁኔታ ያህል ጎልቶ የሚጠቀስ ባይሆንም እንኳ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም በአንድ ግለሰብ ላይ በደል እንደተፈጸመ ሆኖ ይሰማን ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ “የሚሰናከል ማን ነው፣ እኔም አልናደድምን?” ብሎ እንደተናገረው እንደ ጳውሎስ ሊሰማን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 11:29) ምን ልናደርግ እንችላለን? ‘በእርግጥ በደል ተፈጽሟልን?’ ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ ጥሩ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ አይኖረንም። ጉዳዩን ከአንድ ሰው እንደሰማን ወዲያው ልንቆጣ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “የዋህ [“ሞኝ ሰው፣” የ1980 ትርጉም ] ቃልን ሁሉ ያምናል” ብሎ የተናገረው ያለ ምክንያት አይደለም። (ምሳሌ 14:15) ስለዚህ ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል።

6. በጉባኤ ውስጥ በደል እንደተፈጸመ ሆኖ ቢሰማን እንዴት ብለን ምላሽ ልንሰጥ እንችላለን?

6 ሆኖም በእኛ በራሳችን ላይ በደል እንደተፈጸመብን ተሰማን እንበል። በልቡ ውስጥ የክርስቶስ ሰላም ያለው ሰው ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው? ጎድቶናል ብለን ካሰብነው ሰው ጋር በግል መነጋገር እንደሚያስፈልገን ይሰማን ይሆናል። ጉዳዩን ላገኘነው ሰው ሁሉ ከመንዛት ይልቅ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያዝ እንደሚያደርግ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ለምን ለይሖዋ በጸሎት አንነግረውም? (መዝሙር 9:10፤ ምሳሌ 3:5) እንዲህ ማድረጋችን ጉዳዩን በልባችን እንድንይዝና ‘ዝም እንድንል’ ይረዳናል። (መዝሙር 4:4) ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ” በማለት የሰጠው ምክር ብዙውን ጊዜ ተግባራዊ ይሆናል።​—⁠ቆላስይስ 3:13

7. ከወንድሞቻችን ጋር በሚኖረን ግንኙነት ሁልጊዜ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

7 ምንም እናድርግ ምን የተፈጠረውን ነገር ማስቀረት ባንችል እንኳ ስሜታችንን መቆጣጠር እንደምንችል ግን ማስታወስ ይኖርብናል። ተፈጸመ ለምንለው በደል ሚዛኑን የሳተ ምላሽ ብንሰጥ ከበደሉ ይልቅ ይህ በሰላማችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትልብን ይችላል። (ምሳሌ 18:14) ልንሰናከልና ተገቢው የፍትሕ እርምጃ ካልተወሰደ አልመጣም ብለን ከጉባኤ ልንርቅ እንችላለን። መዝሙራዊው የይሖዋን ሕግጋት የሚወዱ ሰዎች ‘ዕንቅፋት የለባቸውም’ በማለት ጽፏል። (መዝሙር 119:165) አልፎ አልፎ በደል የማይደርስበት ማንም ሰው የለም። እንዲህ ያለው ቅር የሚያሰኝ ሁኔታ ለይሖዋ የምታቀርበውን አገልግሎት እንዲያደናቅፍብህ ፈጽሞ አትፍቀድ። ከዚያ ይልቅ የክርስቶስ ሰላም በልብህ እንዲገዛ አድርግ።

በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ

8. ጭንቀት ሊፈጥሩ የሚችሉ አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ጭንቀት ምን ሊያስከትል ይችላል?

8 በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ ጭንቀት አንዱ የዕለት ተዕ​ለት የሕይወት ገጽታ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ኢየሱስ “ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ” ብሎ መናገሩ ትክክል ነው። (ሉቃስ 12:22) ይሁን እንጂ ጭንቀት ሁሉ የሚፈጠረው ስለ ቁሳዊ ነገሮች በማሰብ ነው ማለት አይደለም። ሎጥ ሰዶም በነበረው ልቅ አኗኗር በእጅጉ ‘ተጨንቆ’ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:7) ጳውሎስ ‘በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ’ ተጨንቆ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 11:28) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት በጣም ከመጨነቁ የተነሳ “ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ” ሆኖ ነበር። (ሉቃስ 22:44) በግልጽ ለማየት እንደምንችለው ጭንቀት ሁሉ የእምነት መዳከም ምልክት ነው ማለት አይደለም። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ከባድና ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ጭንቀት ሰላማችንን ሊያደፈርስብን ይችላል። አንዳንዶች የደረሰባቸው ጭንቀት በይሖዋ አገልግሎት ያሉባቸውን ኃላፊነቶች መሸከም እንደማይችሉ ሆኖ እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 12:25) ታዲያ በጭንቀት ከተዋጥን ምን ልናደርግ እንችላለን?

9. ጭንቀትን ለማርገብ ሊወሰዱ የሚችሉ አንዳንድ ተግባራዊ እርምጃዎች ምንድን ናቸው? ሆኖም የትኛውን የጭንቀት መንሥኤ ማስወገድ አይቻልም?

9 በአንዳንድ ሁኔታዎች ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ እንችል ይሆናል። ላደረብን ጭንቀት መንስዔው የጤና ችግር ከሆነ እንዲህ ያለው ጉዳይ ለግል ውሳኔ የሚተው ቢሆንም እንኳ አቅልለን ልንመለከተው እንደማይገባ መዘንጋት የለብንም። a (ማቴዎስ 9:12) ኃላፊነት በዝቶብን ከሆነ አንዳንዶቹን ለሌሎች ማካፈል እንችል ይሆናል። (ዘጸአት 18:13-23) ይሁን እንጂ እንደ ወላጅ ያሉ ያሉባቸውን ከባድ ኃላፊነቶች ለሌሎች ማካፈል የማይችሉትስ? ተቃዋሚ የትዳር ጓደኛ ያለው ክርስቲያን ምን ሊያደርግ ይችላል? ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ያለበት ወይም በጦርነት አካባቢ የሚኖር ቤተሰብስ? በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ያሉትን የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሁሉ ማስወገድ እንደማንችል የታወቀ ነው። ሆኖም በልባችን ውስጥ የክርስቶስን ሰላም መጠበቅ እንችላለን። እንዴት?

10. አንድ ክርስቲያን ከጭንቀቱ እፎይታ ሊያገኝ የሚችልባቸው ሁለት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

10 ከአምላክ ቃል ማጽናኛ ለማግኘት ጥረት ማድረግ አንዱ መንገድ ነው። ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 94:19) የይሖዋን ‘ማጽናኛ’ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት ይቻላል። ይህን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ አዘውትረን ማንበባችን በልባችን ውስጥ ያለውን የክርስቶስ ሰላም እንድንጠብቅ ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 55:22) በተመሳሳይም ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ዘወትር አጥብቆ መጸለይ ሰላማችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል።

11. (ሀ) ጸሎትን በተመለከተ ኢየሱስ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው? (ለ) ለጸሎት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

11 በዚህ ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። በተለያዩ ጊዜያት በጸሎት አማካኝነት ከሰማዩ አባቱ ጋር ለረዥም ሰዓት የተነጋገረባቸው ወቅቶች ነበሩ። (ማቴዎስ 14:23፤ ሉቃስ 6:12) የደረሰበትን ከሁሉ የከፋ መከራ በጽናት እንዲወጣ የረዳው ጸሎት ነው። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ከፍተኛ ጭንቀት ተሰምቶት ነበር። ምን አደረገ? “አጽንቶ” ጸለየ። (ሉቃስ 22:44) አዎን፣ ፍጹም የነበረው የአምላክ ልጅ የጸሎት ሰው ነበር። ታዲያ ፍጹም ያልሆኑት ተከታዮቹማ ምን ያህል የመጸለይ ልማድ ሊያዳብሩ ይገባል! ኢየሱስ ተከታዮቹን “ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው” አስተምሯቸዋል። (ሉቃስ 18:1) ጸሎት እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ከሚያውቀን አካል ጋር የሚያገናኘን እውነተኛና ጠቃሚ የመገናኛ መሥመር ነው። (መዝሙር 103:14) የክርስቶስን ሰላም በልባችን ውስጥ መጠበቅ ከፈለግን ‘ሳናቋርጥ እንጸልያለን።’​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:17

ያሉብንን የአቅም ገደቦች ማሸነፍ

12. አንዳንዶች አገልግሎታቸው በቂ እንዳልሆነ ሆኖ የሚሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

12 ይሖዋ እያንዳንዱን አገልጋዩን እንደ ውድ አድርጎ ይመለከተዋል። (ሐጌ 2:7) ሆኖም ብዙዎች ይህን መቀበል ይከብዳቸዋል። አንዳንዶች በእድሜ መግፋት፣ ተደራራቢ በሆኑ የቤተሰብ ኃላፊነቶች ወይም በጤና እክል ምክንያት ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ በልጅነታቸው በደረሰባቸው መጥፎ ነገር የተነሳ ራሳቸውን ያልታደሉ እንደሆኑ አድርገው ይቆጥራሉ። ሌሎች ደግሞ ባለፉት ጊዜያት የሠሯቸውን ስህተቶች ይሖዋ ይቅር እንዳላቸው ሆኖ ስለማይሰማቸው ይሠቃዩ ይሆናል። (መዝሙር 51:3) እንደነዚህ ያሉትን ስሜቶች ለማሸነፍ ምን ማድረግ ይቻላል?

13. እንደማይበቁ ሆኖ ለሚሰማቸው ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማጽናኛ አለ?

13 የክርስቶስ ሰላም ይሖዋ እንደሚወድደን ማረጋገጫ ይሰጠናል። ኢየሱስ ዋጋማነታችን የሚለካው የእኛን ሥራ ከሌሎች ጋር በማወዳደር እንደሆነ አድርጎ ፈጽሞ አለመናገሩን ማሰላሰላችን የክርስቶስን ሰላም በልባችን ውስጥ ጠብቀን እንድናቆይ ይረዳናል። (ማቴዎስ 25:14, 15፤ ማርቆስ 12:41-44) ኢየሱስ ጠበቅ አድርጎ የገለጸው ታማኝነትን ነው። ደቀ መዛሙርቱን “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” በማለት ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 24:13) ኢየሱስ ራሱ በሰዎች ‘ቢናቅም’ አባቱ እንደሚወድደው ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አልነበረውም። (ኢሳይያስ 53:3፤ ዮሐንስ 10:17) ደቀ መዛሙርቱም ቢሆኑ የተወደዱ እንደሆኑ ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 14:21) ኢየሱስ ይህንን ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ የሚከተለውን ተናግሯል:- “ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር እንኳ ተቈጥሮአል። እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።” (ማቴዎስ 10:29-31) ይህ የይሖዋን ፍቅር በተመለከተ እንዴት ያለ ማረጋገጫ ነው!

14. ይሖዋ እያንዳንዳችንን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተን ምን ማረጋገጫ አለን?

14 በተጨማሪም ኢየሱስ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:44) ኢየሱስን እንድንከተል የሳበን ይሖዋ እንደመሆኑ መጠን እንድንድንም እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 18:14) ስለዚህ በሙሉ ልብ የምታገለግል ከሆነ በምታከናውነው መልካም ሥራዎች ልትደሰት ትችላለህ። (ገላትያ 6:4) ከዚህ ቀደም በሠራሃቸው ስህተቶች የምትሠቃይ ከሆነ ይሖዋ እውነተኛ ንስሐ የገቡትን ‘በብዙ’ ይቅር እንደሚላቸው እርግጠኛ ሁን። (ኢሳይያስ 43:25፤ 55:7) ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እንዲያድርብህ ያደረገው ምክንያት ምንም ይሁን ምን “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” የሚለውን አስታውስ።​—⁠መዝሙር 34:18

15. (ሀ) ሰይጣን ሰላማችንን ለመንጠቅ የሚሞክረው እንዴት ነው? (ለ) በይሖዋ ላይ ምን ትምክህት ልንጥል እንችላለን?

15 ሰይጣን ሰላም አጥተህ ስትሰቃይ ማየት ይፈልጋል። ሁላችንም የምንታገለውን የወረስነውን ኃጢአት ያመጣብን እሱ ነው። (ሮሜ 7:21-24) ፍጹም አለመሆንህ አገልግሎትህ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኝ ያደርጋል ብለህ እንድታስብ እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። ዲያብሎስ ተስፋ እንዲያስቆርጥህ ፈጽሞ አትፍቀድ! ዘዴውን ጠንቅቀህ እወቅ። ይህም ለመጽናት ቆርጠህ እንድትነሳ የሚያደርግህ ይሁን። (2 ቆሮንቶስ 2:11፤ ኤፌሶን 6:11-13) “እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል” የሚለውን አስታውስ። (1 ዮሐንስ 3:19, 20) ይሖዋ የሚመለከተው ስህተታችንን ብቻ አይደለም። ውስጣዊ ግፊታችንንና ዝንባሌያችንንም ይመለከታል። ስለዚህ “እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፣ ርስቱንም አይተውምና” በሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ተጽናና።​—⁠መዝሙር 94:14

በክርስቶስ ሰላም አንድ መሆን

16. ለመጽናት በምናደርገው ጥረት ብቻችንን አይደለንም የምንለው በምን መንገድ ነው?

16 ጳውሎስ ‘በአንድ አካል የተጠራን’ በመሆናችን ምክንያት የክርስቶስ ሰላም በልባችን እንዲገዛ መፍቀድ እንዳለብን ጽፏል። ጳውሎስ የጻፈላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዛሬው ጊዜ እንዳሉት ቅቡዓን ቀሪዎች የክርስቶስ አካል ክፍል እንዲሆኑ ተጠርተው ነበር። ጓደኞቻቸው የሆኑት ‘ሌሎች በጎችም’ ‘በአንዱ እረኛ’ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር ከእነርሱ ጋር አንድ ሆነዋል። (ዮሐንስ 10:16) ይህ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያቀፈው “መንጋ” አባላት የክርስቶስ ሰላም በልባቸው እንዲገዛ ፈቅደዋል። ብቻችንን አለመሆናችንን ማወቃችን እንድንጸና ይረዳናል። ጴጥሮስ “በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” በማለት ጽፏል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:9

17. የክርስቶስ ሰላም በልባችን እንዲገዛ ፈቃደኞች እንድንሆን የሚገፋፋን ምንድን ነው?

17 እንግዲያው ሁላችንም እጅግ ጠቃሚና የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ የሆነውን ሰላምን ማዳበራችንን እንቀጥል። (ገላትያ 5:22, 23) በይሖዋ ዘንድ ነውርና ነቀፋ የሌለባቸው እንዲሁም ሰላማዊ ሆነው የተገኙ ሁሉ በመጨረሻ ጻድቃን በሚኖሩበት ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በማግኘት ይባረካሉ። (2 ጴጥሮስ 3:13, 14) የክርስቶስ ሰላም በልባችን እንዲገዛ የምንፈቅድባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በአንዳንድ ወቅቶች እንደ ድባቴ (clinical depression) ያሉ ሕመሞች ጭንቀት ሊፈጥሩ ወይም ሊያባብሱ ይችላሉ።

ታስታውሳለህን?

• የክርስቶስ ሰላም ምንድን ነው?

• በደል እንደተፈጸመብን ሆኖ በሚሰማን ጊዜ የክርስቶስ ሰላም በልባችን ሊገዛ የሚችለው እንዴት ነው?

• የክርስቶስ ሰላም ጭንቀትን እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?

• ዋጋ እንደሌለን ሆኖ በሚሰማን ጊዜ የክርስቶስ ሰላም የሚያጽናናን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በከሳሾቹ ፊት ሕይወቱን ለይሖዋ በአደራ ሰጥቷል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አፍቃሪ በሆነ አባቱ እቅፍ ውስጥ ያለ ሕፃን ደስ እንደሚለው ሁሉ የይሖዋ ማጽናኛም ጭንቀታችንን ሊያቃልልልን ይችላል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ጽናትን ከፍ አድርጎ ይመለከታል