በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዲያብሎስ አፈ ታሪክ የወለደው አይደለም

ዲያብሎስ አፈ ታሪክ የወለደው አይደለም

ዲያብሎስ አፈ ታሪክ የወለደው አይደለም

“መላው አዲስ ኪዳን በአንድ ወገን በአምላክና በበጎ ኃይሎች መካከል በሌላ ወገን ደግሞ በሰይጣን አመራር ሥር ባሉ የክፋት ኃይሎች መካከል ግጭት መኖሩን ያሳያል። ይህ አንድ ወይም ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የነበራቸው አመለካከት ሳይሆን ሁሉም በጋራ የነበራቸው አመለካከት ነው። . . . በመሆኑም አዲስ ኪዳን የሚያቀርበው ማስረጃ አሻሚ አይደለም። ሰይጣን ለአምላክም ሆነ ለአምላክ ሕዝቦች መቼም ቢሆን የማይተኛ አደገኛ የሆነ እውን አካል ነው።”​—⁠ዘ ኒው ባይብል ዲክሽነሪ

ታዲያ የክርስትና እምነት ተከታይ እንደሆኑ የሚናገሩና በመጽሐፍ ቅዱስም እናምናለን የሚሉ ብዙ ሰዎች ዲያብሎስ በእርግጥ አለ የሚለውን ሐሳብ የማይቀበሉት ለምንድን ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን የአምላክ ቃል አድርገው ስለማይቀበሉት ነው። (ኤርምያስ 8:​9) በርካታ ክርስቲያን ነን ባዮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በዙሪያቸው የነበሩት አሕዛብ የሚከተሏቸውን ፍልስፍናዎች ስላንጸባረቁ ከአምላክ የተላከውን እውነት በትክክል አላስተላለፉም ብለው ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ምሁር የሆኑት ሃንስ ኩንግ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሰይጣንና አጋንንቱ አሉ የሚለው አፈ ታሪካዊ ሐሳብ . . . ከባቢሎናውያን አፈ ታሪክ ወደ ቀድሞው የአይሁድ እምነት ከዚያም ወደ አዲስ ኪዳን ሰርጎ ገብቷል።”​—⁠ኦን ቢይንግ ኤ ክርስቺያን

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ቃል አይደለም። በእርግጥ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል ነው። ስለዚህ ዲያብሎስን በተመለከተ የሚናገረውን ጉዳይ በቁም ነገር መመልከታችን ጥበብ ነው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​14-17፤ 2 ጴጥሮስ 1:​20, 21

ኢየሱስ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ዲያብሎስ በእውን ያለ መሆኑን ያምን ነበር። ኢየሱስ የተፈተነው በውስጡ ባለ አንድ ዓይነት ክፋት አልነበረም። ከጊዜ በኋላ “የዚህ ዓለም ገዥ” ሲል የጠራው አንድ እውን አካል ጥቃት ሰንዝሮበታል። (ዮሐንስ 14:​30፤ ማቴዎስ 4:​1-11) በተጨማሪም ሌሎች መንፈሳዊ ፍጡራን ለሰይጣን የክፋት ተግባር ድጋፍ እንደሚሰጡ ያምን የነበረ ሲሆን ‘ጋኔን ያደረባቸውን’ ሰዎች ፈውሷል። (ማቴዎስ 12:​22-28) ሌላው ቀርቶ በአምላክ መኖር የማያምነው ኤ ራሽናሊስት ኢንሳይክሎፔዲያ የተባለው ጽሑፍ እንኳ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በወንጌሎች ላይ የተገለጸው ኢየሱስ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን መኖራቸውን ማመኑ መቼም ቢሆን ለሃይማኖት ምሁራን እንቅፋት እንደሆነባቸው ነው።” ኢየሱስ ስለ ዲያብሎስና ስለ አጋንንቱ ሲናገር ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የባቢሎናውያን አፈ ታሪክ መጥቀሱ አይደለም። ዲያብሎስም ሆነ አጋንንቱ በእርግጥ ሕልውና እንዳላቸው ያውቃል።

ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት የሃይማኖት አስተማሪዎች ከተናገረው ቃል ስለ ዲያብሎስ ብዙ ማወቅ እንችላለን:- “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፣ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።”​—⁠ዮሐንስ 8:44

በዚህ መሠረት ዲያብሎስ (የስሙ ትርጉም “ስም አጥፊ” ማለት ነው) “ሐሰተኛ የሐሰትም አባት” ነው። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አምላክን በተመለከተ ውሸት የተናገረ የመጀመሪያው ፍጡር ሲሆን ይህንም ያደረገው በኤደን ገነት ነበር። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን መልካምንና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ ከበሉ ‘ሞትን እንደሚሞቱ’ ተናግሯል። ሰይጣን በአንድ እባብ አፍ ተጠቅሞ እነዚህ ቃላት ውሸት መሆናቸውን ተናገረ። (ዘፍጥረት 2:​17፤ 3:​4) በመሆኑም “ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው . . . የቀደመው እባብ” ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው።​—⁠ራእይ 12:​9

ዲያብሎስ መልካምንና ክፉን የሚያሳውቀውን ዛፍ በሚመለከት ዋሽቷል። ከዛፉ መብላት መከልከሉ ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም እንደሆነ በመግለጽ ፍትሐዊ አይደለም ሲል ተከራከረ። አዳምና ሔዋን ከዛፉ መብላት ቢፈቀድላቸው ኖሮ ምን ነገር ጥሩ፣ ምን ነገር መጥፎ እንደሆነ ለራሳቸው በመወሰን ረገድ “እንደ እግዚአብሔር” መሆን ይችሉ እንደነበር ተናገረ። የመምረጥ ነፃነት ያላቸው ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን ሙሉ በሙሉ ራሳቸው የመወሰን ሥልጣን ሊኖራቸው ይገባል ማለቱ ነበር። (ዘፍጥረት 3:1-5) በአምላክ አገዛዝ ትክክለኛነት ላይ የተሰነዘረው ይህ ጥቃት አንገብጋቢ ጥያቄዎች አስነስቷል። ስለዚህ ይሖዋ እነዚህ ጥያቄዎች መልስ እስኪያገኙ ድረስ ጊዜ ፈቀደ። ይህም ማለት ሰይጣን ለተወሰነ ጊዜ በሕይወት እንዲኖር ተፈቅዶለታል ማለት ነው። አሁን የተፈቀደለት ውስን ጊዜ በፍጥነት እየተሟጠጠ ነው። (ራእይ 12:​12) አሁንም ቢሆን በኢየሱስ ዘመን ትምህርቱን ለማሰራጨት በጻፎችና ፈሪሳውያን ይጠቀም እንደነበረ ሁሉ ዛሬም እንደነሱ ያሉ ሰዎችን በመጠቀም በውሸትና በማጭበርበር የሰው ልጆችን ከአምላክ ማራቁን ገፍቶበታል።​—⁠ማቴዎስ 23:​13, 15

በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ “ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ” እንዲሁም “በእውነት አልቆመም” ሲል ተናግሯል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እንዲህ ሲባል ግን ይሖዋ ዲያብሎስን “ነፍሰ ገዳይ” አድርጎ ፈጥሮታል ማለት አይደለም። አምላክን የተቃወመ ሁሉ የሚጣልና የሚሰቃይበትን እሳታማ ቦታ የሚቆጣጠር ጭራቅ ተደርጎ አልተፈጠረም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው “ሲኦል” የሰይጣን መኖሪያ ሳይሆን የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ነው።​—⁠ሥራ 2:​25-27፤ ራእይ 20:​13, 14

ዲያብሎስ በመጀመሪያ “በእውነት” ውስጥ ነበር። በአንድ ወቅት ፍጽምና የተላበሰ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ በመሆን የይሖዋ ሰማያዊ ቤተሰብ ክፍል ነበር። ይሁን እንጂ “በእውነት አልቆመም።” የራሱን መንገድ እና የራሱን በውሸት ላይ የተመሠረተ መርሕ መከተል መረጠ። “ከመጀመሪያ” የሚለው አባባል ሆነ ብሎ በይሖዋ ላይ ያመፀበትን እንዲሁም ለአዳምና ለሔዋን የዋሸበትን ጊዜ እንጂ የአምላክ መልአካዊ ልጅ ሆኖ የተፈጠረበትን ጊዜ አያመለክትም። ዲያብሎስ በሙሴ ዘመን በይሖዋ ላይ ካመፁት ሰዎች ጋር ይመሳሰላል። ስለ እነሱ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም አይደሉም፤ ነውርም አለባቸው።” (ዘዳግም 32:​5) ሰይጣንን በተመለከተም ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል። ሰይጣን ባመፀበት ጊዜ እና ለአዳምና ለሔዋን ይባስ ብሎም ለመላው ሰብዓዊ ቤተሰብ ሞት መንስዔ በሆነበት ጊዜ “ነፍሰ ገዳይ” ሆኗል።​—⁠ሮሜ 5:​12

ዓመፀኛ መላእክት

ሌሎች መላእክት ሰይጣንን በዓመፁ ተባብረውታል። (ሉቃስ 11:​14, 15) እነዚህ መላእክት በኖኅ ዘመን ‘ከሰው ሴቶች ልጆች’ ጋር የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ሲሉ ‘መኖሪያቸውን ትተው’ የሰው ሥጋ ለበሱ። (ይሁዳ 6፤ ዘፍጥረት 6:​1-4፤ 1 ጴጥሮስ 3:​19, 20) “የሰማይ ከዋክብት ሲሶ” ማለትም በቁጥር አነስተኛ የሆኑ መንፈሳዊ ፍጡራን ይህን ጎዳና ተከትለዋል።​—⁠ራእይ 12:​4

በርካታ ምሳሌያዊ መግለጫዎችን የሚጠቀመው የራእይ መጽሐፍ ዲያብሎስን “ታላቅ ቀይ ዘንዶ” አድርጎ ይገልጸዋል። (ራእይ 12:​3) ለምን? ይህ የሆነው ቃል በቃል አስፈሪ የሆነ አስቀያሚ መልክ ስላለው አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ መንፈሳዊ ፍጡራን ምን ዓይነት አካል እንዳላቸው አናውቅም። ሆኖም በዚህ ረገድ ሰይጣን ከሌሎች መላእክታዊ መንፈሳዊ ፍጡራን የተለየ እንደማይሆን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሰይጣን “ታላቅ ቀይ ዘንዶ” መባሉ በቃኝ ለማያውቀው፣ አስፈሪ፣ ኃይለኛና አጥፊ ለሆነው ባሕርይው ተስማሚ መግለጫ ነው።

በአሁኑ ጊዜ ሰይጣንና አጋንንቱ ጥብቅ እገዳ ተጥሎባቸዋል። ከዚህ በፊት ያደርጉ እንደነበረው ሥጋዊ አካል መልበስ አይችሉም። በ1914 የአምላክ መንግሥት በክርስቶስ አማካኝነት ከተቋቋመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ምድር አካባቢ ተጥለዋል።​—⁠ራእይ 12:​7-9

ዲያብሎስ በቀላሉ የማይረታ ጠላት ነው

ቢሆንም ዲያብሎስ አሁንም በቀላሉ የማይረታ ጠላት ነው። “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራል።” (1 ጴጥሮስ 5:​8) ዲያብሎስ ኃጢአተኛ በሆነ ሥጋችን የሚያድር ምንነቱን ለመግለጽ የሚያስቸግር አንድ ዓይነት የክፋት ባሕርይ አይደለም። እርግጥ ነው ከራሳችን የኃጢአተኝነት ዝንባሌዎች ጋር በየዕለቱ መታገል እንዳለብን እሙን ነው። (ሮሜ 7:​18-20) ሆኖም በዋነኛነት ትግል የምንገጥመው “ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው።”​—⁠ኤፌሶን 6:​12

የዲያብሎስ ተጽዕኖ ምን ያህል ተስፋፍቶ ይገኛል? ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ዓለምም በሞላው በክፉው ተይዟል’ ብሏል። (1 ዮሐንስ 5:​19) እርግጥ ነው፣ ስለ ዲያብሎስ በማሰብ መጨነቅ ወይም ስለ እሱ በአጉል እምነት ላይ የተመሠረተ ፍርሃት እንዲያሽመደምደን መፍቀድ አንፈልግም። ሆኖም እውነት እንዳይታየንና ለአምላክ ያለንን ጽኑ አቋም ለማበላሸት የሚያደርገውን ጥረት በንቃት መከላከላችን ጥበብ ነው።​—⁠ኢዮብ 2:​3-5፤ 2 ቆሮንቶስ 4:​3, 4

ዲያብሎስ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎችን ለማጥቃት ሁልጊዜ ጭካኔ በተሞላባቸው መንገዶች ይጠቀማል ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ራሱን ‘የብርሃን መልአክ’ አስመስሎ ያቀርባል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን አደጋ በተመለከተ ለክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እባብ በተንኰሉ ሔዋንን እንዳሳታት፣ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።”​—⁠2 ቆሮንቶስ 11:​3, 14

ስለዚህ ‘በመጠን መኖር፣ ንቁ መሆን እንዲሁም እሱን በእምነት ጸንተን መቃወም’ ያስፈልገናል። (1 ጴጥሮስ 5:​8, 9፤ 2 ቆሮንቶስ 2:​11) ከምትሃታዊ ኃይል ጋር ግንኙነት ያለውን ማንኛውንም ነገር እንደ ዋዛ በመመልከት ሰይጣን በቀላሉ እንዲያታልለን መፍቀድ የለብንም። (ዘዳግም 18:​10-12) ኢየሱስ ክርስቶስ በዲያብሎስ ሲፈተን በተደጋጋሚ ከአምላክ ቃል መጥቀሱን በማስታወስ ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሁኑ። (ማቴዎስ 4:​4, 7, 10) የአምላክን መንፈስ ለማግኘት ጸልዩ። የመንፈስ ፍሬ ሰይጣን ስኬታማ በሆነ መንገድ የሚያስፋፋውን የሥጋ ሥራ ማስወገድ እንድትችሉ ይረዳችኋል። (ገላትያ 5:​16-24) በተጨማሪም ዲያብሎስና አጋንንቱ በሆነ መንገድ ግፊት እንዳሳደሩባችሁ ሲሰማችሁ ከልባችሁ ወደ ይሖዋ ጸልዩ።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​6, 7

ዲያብሎስን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ይሖዋ፣ ሰይጣን ከሚያመጣው ከማንኛውም እንቅፋት ጥበቃ እንደሚያደርግልን ቃል ገብቷል። (መዝሙር 91:​1-4፤ ምሳሌ 18:​10፤ ያዕቆብ 4:​7, 8) ሐዋርያው ጳውሎስ “በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ” ብሏል። ይህን በማድረግ ‘የዲያብሎስን ሽንገላ መቃወም ትችላላችሁ።’​—⁠ኤፌሶን 6:​10, 11

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዲያብሎስ እውን አካል መሆኑን ኢየሱስ ያውቅ ነበር

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ዓለምም በሞላው በክፉው ተይዟል’

[ምንጭ]

NASA photo

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ቃል በማጥናትና አዘውትሮ በመጸለይ ዲያብሎስን በጽናት ተቃወሙት