በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎችን አንድ ሊያደርግ የሚችል ነገር ይኖር ይሆን?

ሰዎችን አንድ ሊያደርግ የሚችል ነገር ይኖር ይሆን?

ሰዎችን አንድ ሊያደርግ የሚችል ነገር ይኖር ይሆን?

እምነትህ ምንም ይሁን ምን በሁሉም ሃይማኖት ውስጥ ማለት ይቻላል እውነትን የሚወዱ ሰዎች መኖር አለባቸው ቢባል ሳትስማማ አትቀርም። በሂንዱ፣ በካቶሊክ፣ በአይሁድና በሌሎችም ሃይማኖቶች ውስጥ እውነት ለሆነው ነገር ከፍተኛ አድናቆት ያላቸውንና ይህንንም እውነት ለመፈለግ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ማግኘት ይቻላል። ሆኖም ሃይማኖት የሰው ልጆችን የሚከፋፍል ይመ​ስላል። እንዲያውም አንዳንዶች ሃይማኖትን ለክፉ ድርጊቶቻቸው ከለላ አድርገው ይጠቀሙበታል። ትክክልና እውነተኛ ለሆነው ነገር ፍቅር ያላቸውን በየሃይማኖቱ የሚገኙ ቅን ሰዎች አንድ ማድረግ ይቻል ይሆን? ሁሉም ለአንድ ዓላማ መቆም ይችሉ ይሆን?

ሃይማኖት እያደር ለሰው ልጆች መከፋፈል መንስኤ እየሆነ መምጣቱ ምንኛ አሳሳቢ ጉዳይ ነው! ከእነዚህ ግጭቶች ውስጥ አንዳንዶቹን ተመልከት። በስሪ ላንካ ሂንዱዎች ከቡዲስቶች ጋር ይዋጋሉ። ፕሮቴስታንቶች፣ ካቶሊኮችና አይሁዳውያን ባደረጓቸው የተለያዩ ግጭቶች ብዙ ደም ፈስሷል። “ክርስቲያኖች” በቦስኒያ፣ በቼችንያ፣ በኢንዶኔዥያና በኮሶቮ ከሚገኙት ሙስሊሞች ጋር ተዋግተዋል። እንዲሁም መጋቢት 2000 ሁለት ቀን የፈጀው ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ግጭት ለ300 ናይጄሪያውያን ሞት ምክንያት ሆኗል። በእርግጥም ሃይማኖታዊ ጥላቻ ግጭቶቹን ይበልጥ አስከፊ አድርጓቸዋል።

አብዛኛውን ጊዜ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በሃይማኖት ስም በሚፈጸሙ ክፉ ድርጊቶች በጣም ያዝናሉ። ለምሳሌ ያህል ብዙ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች አንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖች ልጆችን በጾታ ባስነወሩ ቀሳውስት ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳልወሰዱ ሲገነዘቡ በጣም ደንግጠዋል። ሌሎች አማኞች ደግሞ ግብረ ሰዶምንና ውርጃን በመሳሰሉ ጉዳዮች ረገድ ክርስቲያን ነን በሚሉ ብዙ ኑፋቄዎች መካከል ያለውን መከፋፈል ሲመለከቱ በጣም አፍረዋል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሃይማኖት የሰው ልጆችን አንድ አላደረገም። ሆኖም የሚከተሉት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ እውነትን ከልባቸው የሚወዱ ሰዎች አሉ።

እውነትን ለማግኘት ሲናፍቁ ኖረዋል

ፊዴልያ፣ ቦሊቪያ ላ ፓዝ ውስጥ የሚገኘው የሳን ፍራንሲስኮ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባልና ለእምነቷ ያደረች ቅን አምላኪ ነበረች። በማርያም ምስል ፊት ወድቃ ትሰግድ የነበረ ሲሆን ከሥነ ስቅለቱ ፊት በጣም ምርጥ የምትላቸውን ሻማዎች ገዝታ ታስቀምጥ ነበር። በየሳምንቱ ብዙ ምግብ እያመጣች ለድሆች እንዲያከፋፍል ለቄሱ ትሰጠው ነበር። ሆኖም አምስቱም ትንንሽ ልጆችዋ ከመጠመቃቸው በፊት ሞቱ። ቄሱ የሞቱት ልጆችዋ በሊምቦ ጨለማ ውስጥ እየተሰቃዩ እንደሆነ ሲነግራት ‘አምላክ አፍቃሪና ደግ ከሆነ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?’ በማለት አሰበች።

የሕክምና ዶክተር የሆነችው ታራ፣ ኔፓል ካትማንዱ ውስጥ የሂንዱ እምነት ተከታይ ሆና አደገች። ዘመናት ያስቆጠረውን የአባቶቿን ልማድ በመከተል በሂንዱ ቤተ መቅደስ የሚገኙትን አማልክት ታመልክ የነበረ ሲሆን ቤቷ ውስጥም ጣዖታት ነበሯት። ሆኖም ታራ እንደሚከተሉት ባሉ ጥያቄዎች ግራ ተጋብታ ነበር:- እንደዚህ መከራ የበዛው ለምንድን ነው? ሰዎች ለምን ይሞታሉ? ለእነዚህ ጥያቄዎች በሃይማኖቷ ውስጥ አጥጋቢ መልስ አላገኘችም።

በሌላ በኩል ደግሞ ፓንያ፣ ባንኮክ ታይላንድ ውስጥ ከውኃ አጠገብ በሚገኝ ቤት ውስጥ የቡዲስት እምነት ተከታይ ሆኖ አድጓል። መከራ የሚመጣው በቀድሞ ሕይወት በተፈጸሙ ኃጢአቶች ምክንያት እንደሆነና ከሁሉም ዓይነት ምኞት ራስን ነጻ በማድረግ ከመከራ መላቀቅ እንደሚቻል ተምሮ ነበር። ቅን ልብ እንዳላቸው እንደ ሌሎቹ ቡዲስቶች ሁሉ እርሱም ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ምጽዋት ለመቀበል ወደ ቤት የሚመጡትና ቢጫ ልብስ የሚለብሱት መነኩሴዎች ላላቸው ጥበብ ጥልቅ አክብሮት እንዲኖረው ተምሮ ነበር። በቡድሃ እምነት ውስጥ እንደሚደረገው ያሰላስልና ከመጥፎ ነገር ይጠብቃሉ የሚባሉትን የተለያዩ የቡድሃ ምስሎች ይሰበስብ ነበር። ከወገቡ በታች ሽባ ያደረገው ከባድ አደጋ ሲደርስበት ተአምራዊ ፈውስ አገኛለሁ በሚል ተስፋ ወደተለያዩ የቡድሃ ገዳማት ሄዷል። ሆኖም አካላዊ ፈውስም ሆነ መንፈሳዊ የእውቀት ብርሃን አላገኘም። እንዲያውም ለመናፍስታዊ እምነት በመጋለጡ መናፍስታዊ ድርጊቶችን ይፈጽም ጀመር።

ቨርጂል የተወለደው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሲሆን ኮሌጅ ሲገባ ብላክ ሙስሊም ከተባለው ቡድን ጋር ተቀላቀለ። ነጭ የተባለ ሁሉ ሰይጣን ነው የሚል መልእክት ያላቸውን ጽሑፎቻቸውን በቅንዓት ያሰራጭ ነበር። ነጮች በጥቁሮች ላይ እንዲህ ያለ ብዙ ግፍ የሚፈጽሙት ለዚህ ነው ብለው ያምኑ ነበር። ቨርጂል እምነቱን በቅንነት ተቀብሎ የነበረ ቢሆንም እንደሚከተሉት ያሉት ጥያቄዎች እረፍት ነሱት:- እንዴት ሁሉም ነጮች መጥፎ ይሆናሉ? ሃይማኖታዊ ስብከትና ገንዘብ ይህን ያህል የተሳሰሩት ለምንድን ነው?

ቻሮ ካቶሊኮች በሚበዙባት በደቡብ አሜሪካ ያደገች ብትሆንም ቅን ልብ ያላት ፕሮቴስታንት ነበረች። ዙሪያዋን በከበባት የጣዖት አምልኮ ባለመካፈሏ ደስተኛ ነበረች። በየሳምንቱ እሁድ እሁድ የአድማጮችን ስሜት በሚያነሳሳው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያስደስታት ነበር። እዚያም “ሃሌ ሉያ” ብላ ትጮኽና ይህንን ተከትሎ በሚመጣው ሃይማኖታዊ መዝሙርና ዳንስ ትካፈላለች። እንደዳነችና እንደገና እንደተወለደች በቅን ልብ ታምን ነበር። የደሞዝዋን አሥር በመቶ ለቤተ ክርስቲያን የምትሰጥ ሲሆን በጣም የምትወደው የቴሌቪዥን ወንጌላዊ መዋጮ ሲጠይቅ አፍሪካ ለሚገኙ ልጆች የሚሆን ገንዘብ ላከችለት። የፍቅር አምላክ ነፍሳትን በሲኦል የሚያቃጥለው ለምንድን ነው ብላ ፓስተሩን ስትጠይቀው ትርጉም ያለው መልስ እንዳልሰጣት ተረዳች። ያደረገችው መዋጮም ቢሆን በአፍሪካ የሚገኙትን ሕፃናት ለመርዳት እንዳልዋለ ተገነዘበች።

እነዚህ አምስት ግለሰቦች የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ቢሆኑም ሁሉም አንድ የጋራ የሆነ ነገር አላቸው። እውነትን የሚወዱ ሲሆን ለጥያቄዎቻቸው ትክክለኛ መልስ ለማግኘት ከልብ ጥረዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በእውነተኛው አምልኮ በእርግጥ አንድ ይሆኑ ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተለያየ ባህልና አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች በእርግጥ አንድ ማድረግ ይቻላል?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

G.P.O., Jerusalem