በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አውራጃ ስብሰባ—የወንድማማችነታችን ማረጋገጫ የሆነ አስደሳች ወቅት

አውራጃ ስብሰባ—የወንድማማችነታችን ማረጋገጫ የሆነ አስደሳች ወቅት

ምሉዓን ሆናችሁና ጽኑ እምነት ኖሯችሁ ቁሙ

አውራጃ ስብሰባ​—⁠የወንድማማችነታችን ማረጋገጫ የሆነ አስደሳች ወቅት

ወደ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ያላግባብ በመታሰሩ ጤናው የተጓደለው የ50 ዓመቱ ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ አስተናባሪ በመሆን በደስታ እያገለገለ ነው። የክርስቲያን ባልንጀሮቹን ሻንጣዎች በመያዝ ሆቴል ውስጥ ወደተዘጋጁላቸው ማረፊያ ክፍሎቻቸው እንዲሄዱ ለመርዳት ይጣደፋል። ቀደም ሲል ከእርሱ ጋር ታስረው የነበሩ ሌሎች ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ደግሞ ማረፊያ ለማግኘት ይጠባበቁ ለነበሩት ብዙ ሰዎች ክፍል ይደለድላሉ። ሥራው እስከ እኩለ ሌሊትና ከዚያም በኋላ ቀጥሎ የነበረ ሲሆን ሁሉም የደስታ መንፈስ ይነበብባቸው ነበር። ይህ አጋጣሚ ምንድን ነው?

ዓመቱ 1919 ሲሆን በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በመባል የሚታወቁት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከደረሰባቸው ከባድ ስደት ገና በማገገም ላይ ነበሩ። ወንድማማችነታቸውን ለማጠናከር ሲሉ ከመስከረም 1 እስከ 8, 1919 ባሉት ቀናት ሴዳር ፓይንት ኦሃዮ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ የአውራጃ ስብሰባ ሊያደርጉ ነው። በስብሰባው የመጨረሻ ቀን በደስታ የፈኩት 7, 000 የሚያክሉ ወንድሞች ወንድም ራዘርፎርድ “እናንተ የጌታችንን ክብራማ መንግሥት ለሰዎች የምታሳውቁ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ አምባሳደሮች ናችሁ” በማለት በስብሰባው ላይ የተገኙትን ሁሉ ሲያበረታታ በትኩረት አዳምጠዋል።

የይሖዋ ሕዝቦች ትልልቅ ስብሰባዎች ማድረግ የጀመሩት ከጥንቷ እስራኤል ዘመን አንስቶ ነው። (ዘጸአት 23:14-17፤ ሉቃስ 2:41-43) እነዚህ ስብሰባዎች በዚያ የተገኙት ሁሉ አእምሮአቸው በአምላክ ቃል ላይ እንዲያተኩር የሚያደርጉ አስደሳች ወቅቶች ነበሩ። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጓቸው የአውራጃ ስብሰባዎች በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮሩ ናቸው። እነዚህ አስደሳች ስብሰባዎች ምሥክሮቹ በማይበጠስ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት እንደተሳሰሩ ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ሁሉ የማያሻማ ማረጋገጫ ይሰጣሉ።

በስብሰባዎቹ ላይ ለመገኘት የተደረጉ ጥረቶች

በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ክርስቲያኖች የአውራጃ ስብሰባዎች በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን መመሪያና መንፈሳዊ ማነቃቂያ የሚያገኙባቸው ወቅቶች እንደሆኑ ይገነዘባሉ። እነዚህ ትልልቅ ስብሰባዎች ‘ምሉዓን ሆነውና ጽኑ እምነት ኖሯቸው መቆም’ እንዲችሉ የተደረጉ አማራጭ የማይገኝላቸው ዝግጅቶች እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። (ቆላስይስ 4:12) ስለዚህ ምሥክሮቹ እነዚህን ስብሰባዎች በሙሉ ልብ ይደግፋሉ እንዲሁም በስብሰባዎቹ ላይ ለመገኘት ከልብ ይጥራሉ።

ለአንዳንዶች በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እምነት ማሳየትንና ተራራ መሰል እንቅፋቶችን መወጣትን ጠይቆባቸዋል። ለምሳሌ ያህል በኦስትሪያ የምትኖረውን አንዲት በዕድሜ የገፋች ምሥክር ሁኔታ ተመልከት። በነበረባት የስኳር በሽታ ምክንያት በየቀኑ ኢንሱሊን መወጋት ቢኖርባትም በአገሯ በሚደረገው የሦስት ቀን አውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝታለች። በህንድ የሚኖር አንድ በጣም ደሃና ብዙ አባላት ያሉት የምሥክሮች ቤተሰብ በአውራጃ ስብሰባ ላይ መገኘት አስቸጋሪ ሆኖበት ነበር። በዚህ ጊዜ ግን አንዲት የቤተሰቡ አባል የእርዳታ እጅዋን ዘረጋች። “ስብሰባው እንዲያመልጠን ስላልፈለግሁ ለጉዞው የሚሆነንን ገንዘብ ለማግኘት የጆሮ ወርቄን ሸጥኩ” በማለት ተናግራለች። “ከወንድሞች ጋር አንድ ላይ መሰብሰባችንና የሰማናቸው ተሞክሮዎች እምነታችንን ስላጠነከሩልን የከፈልነው መሥዋዕት ከዚህ ጋር ሲወዳደር የሚያስቆጭ አይደለም።”

በፓፑዋ ኒው ጊኒ ፍላጎት ያላቸው ያልተጠመቁ በርከት ያሉ ሰዎች በዋና ከተማው በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ። ከዚያም መንደራቸው ውስጥ የሚገኘውን የአንድ የሕዝብ ማመላለሻ ባለንብረት ቀረብ አሉና ወደ ስብሰባው ቦታ በምን ያህል ገንዘብ ሊወስዳቸው እንደሚችል ጠየቁት። ሆኖም የተጠየቀው ገንዘብ ከአቅማቸው በላይ ስለነበር የሰውዬውን ወጥ ቤት አፍርሰው እንደገና ለመሥራት ዝግጅት አደረጉ። በዚህ መንገድ ወደ ስብሰባው በመሄድ ከጠቅላላው የስብሰባ ፕሮግራም መካፈል በመቻላቸው ተጠቅመዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ እንዳይገኙ ርቀት አያግዳቸውም። በ1978 አንድ ከፖላንድ የመጣ ወጣት ልዑክ ፈረንሳይ ሊሊ ውስጥ በሚደረግ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት በብስክሌት ለስድስት ቀናት 1, 200 ኪሎ ሜትር ተጉዟል። በ1997 የበጋ ወቅት ከሞንጎሊያ የመጡ ሁለት ምሥክሮች ኢሩኩትስክ ሩሲያ ውስጥ በሚደረግ አንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ለመገኘት 1, 200 ኪሎ ሜትር ተጉዘዋል።

እውነተኛ ወንድማማችነት በተግባር ሲገለጽ

ምሥክሮቹ በአውራጃ ስብሰባዎቻቸው ላይ የሚያሳዩት አንድነትና ወንድማማችነት ቅን ለሆኑ ተመልካቾች ግልጽ ሆኖ ይታያል። ብዙዎች በስብሰባው ተካፋዮች መካከል ምንም ዓይነት ክፍፍል እንደሌለና ገና ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙት ምሥክሮች መካከል እንኳ ሳይቀር ሞቅ ያለ መንፈስ መኖሩን በመመልከታቸው ተደንቀዋል።

በቅርቡ አውስትራሊያ ውስጥ በተደረገው አንድ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የመጡትን ልዑካን ለአንድ ሳምንት ያስጎበኘ ግለሰብ ከልዑካኑ ጋር መሆን ስላስደሰተው ጥቂት ጊዜ አብሯቸው መቆየት ፈልጎ ነበር። አብዛኞቹ እርስ በርስ የማይተዋወቁ ሆነው ሳለ እንደዚያ መግባባት መቻላቸው በመካከላቸው ያለውን ፍቅርና አንድነት እንዲያደንቅ አድርጎታል። መሄጃው ሲደርስ አንድ ጊዜ እንዲያዳምጡት ጠየቀ። “ወንድሞችና እህቶች” በማለት ምስጋና ማቅረብ ቢጀምርም ወዲያው እንባ ስለተናነቀው ንግግሩን መቀጠል አልቻለም።

በ1997 ስሪ ላንካ በአንድ ትልቅ ስታዲየም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት ቋንቋ የተዘጋጀ የአውራጃ ስብሰባ አድርጋ ነበር። ጠቅላላው ፕሮግራም በእንግሊዝኛ፣ በሲንሃሊስና በታሚል ቋንቋዎች በተመሳሳይ ጊዜ ቀርቦ ነበር። የጎሳ ግጭት በበዛበት በዚህ ጊዜ የሦስት ቋንቋ ቡድኖች እንዲህ በአንድነት መሰብሰባቸው የሰዎችን ትኩረት መሳቡ አልቀረም። አንድ ፖሊስ አንድን ወንድም “ፕሮግራሙን የሚያካሂደው የትኛው ቡድን ነው? ሲንሃሊሶቹ፣ ታሚሎቹ ወይስ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ” በማለት ጠየቀው። ወንድምም “የትኛውም ቡድን አይደለም ፕሮግራሙን የምናካሂደው ሁላችንም በጋራ ነው” ሲል መለሰ። ፖሊሱ ወንድምን አላመነውም። የመዝጊያ ጸሎት ተደርጎ ሦስቱም የቋንቋ ቡድኖች በአንድነት “አሜን” እንዳሉ ወዲያው ስታዲየሙ ውስጥ ጭብጨባ አስተጋባ። ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ የማያለቅስ ሰው አልነበረም ማለት ይቻላል። አዎን፣ የአውራጃ ስብሰባዎች በእርግጥም የወንድማማችነታችን ማረጋገጫ የሆኑ አስደሳች ወቅቶች ናቸው።​—⁠መዝሙር 133:1 a

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋ​ሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 66-77 እንዲሁም ከ254-82 ተመልከት።