በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ዋጋ ያለው ምንድን ነው?

እውነተኛ ዋጋ ያለው ምንድን ነው?

እውነተኛ ዋጋ ያለው ምንድን ነው?

እውነተኛ ዋጋ ያለው ነገር ማግኘት አስደሳች ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ምን ሊሆን ይችላል? በጣም ብዙ ገንዘብ? በጣም ውድ ወይም ልዩ የሆነ ጌጥ? ዝነኛና ታዋቂ መሆን? ብዙ ሰዎች ለእነዚህ ነገሮች ከፍ ያለ ግምት ይሰጣሉ። ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች መተዳደሪያ ሊያስገኙልን፣ ሕይወት ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ሊያደርጉ ወይም በሌሎች ዘንድ እውቅና የማግኘትና ስኬታማ የመሆን ውስጣዊ ፍላጎታችንን ሊያረኩልን ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች የወደፊት ግቦቻችንንና ምኞቶቻችንን ሊያሟሉልን እንደሚችሉ ተስፋ በማድረግ እነሱን ለማግኘት እየተፍጨረጨርን ነውን?

በአመዛኙ ሰዎች ለአንድ ነገር ዋጋ የሚሰጡት በምን መንገድ ፍላጎታቸውን እንደሚያሟላላቸው ወይም የግል ምኞታቸውን እንደሚያረካላቸው በማየት ነው። ደህንነት እንዲሰማን እንዲሁም ለወደፊት ዋስትና እንዲኖረን የሚያደርጉንን ነገሮች ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። ወዲያው እፎይታና መጽናኛ የሚያመጡልንን ወይም እውቅና የሚያስገኙልንን ነገሮች እንደ ውድ ሀብት እንቆጥራቸዋለን። ሆኖም ተለዋዋጭ በሆኑ ምኞቶቻችንና ፍላጎቶቻችን ላይ ተመሥርቶ የአንድን ነገር ዋጋማነት መገመት ጥልቀትና አርቆ አስተዋይነት የጎደለው ድርጊት ይሆናል። በመሠረቱ የአንድን ነገር እውነተኛ ዋጋ ለመለካት የሚያስችለው መሠረት ከሁሉ ይበልጥ ያስፈልገናል ወይስ አያስፈልገንም? የሚለው ነው።

ከሁሉ ይበልጥ የሚያስፈልገን ነገር ምንድን ነው? ሕይወት ከሌለ ማንኛውም ነገር ዋጋ የለውም። በሕይወት ባንኖር ሕልውና አለን ሊባል አይችልም። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል:- ‘ሙታን አንዳች አያውቁም . . . [የሰው ልጆች የጋራ መቃብር በሆነው] በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም።’ (መክብብ 9:​5, 10) ስንሞት ያለንን ሁሉ ጥለን ለመሄድ እንገደዳለን። በመሆኑም ከሁሉ ይበልጥ የሚያስፈልገን ሕይወታችንን ጠብቆ ሊያቆይ የሚችል ነገር ማግኘታችን ነው። ሕይወታችንን ጠብቆ ሊያቆይ የሚችለው ምንድን ነው?

ሕይወታችንን ጠብቆ ሊያቆይ የሚችለው ምንድን ነው?

ንጉሥ ሰሎሞን ‘ገንዘብ ጥላ ከለላ ነው’ ሲል ጽፏል። (መክብብ 7:​12 አ.መ.ት) በቂ ገንዘብ ካለን ምግብና ምቹ ቤት ማግኘት እንችላለን። ገንዘብ ካለን ራቅ ወዳሉ ቦታዎች በመጓዝ መደሰት እንችላለን። በእርጅና ወይም በሕመም ምክንያት መሥራት ሲያቅተን ገንዘብ ካለን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማግኘት እንችላለን። ገንዘብ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ሆኖም ገንዘብ ሕይወታችንን ጠብቆ ሊያቆይልን አይችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ሲል አጥብቆ መክሮታል:- “በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።” (1 ጢሞቴዎስ 6:17) በዓለም ላይ ያለው ገንዘብ ሁሉ ቢሰበሰብ ሕይወትን ሊገዛልን አይችልም።

የሂቶሺን ተሞክሮ ተመልከት። ሂቶሺ ያደገው በድሃ ቤተሰብ ውስጥ ስለነበር ሀብታም የመሆን ከፍተኛ ምኞት ነበረው። ገንዘብ ባለው ኃይል ላይ ከፍተኛ እምነት ስላሳደረ ሌላው ቀርቶ በገንዘብ ወዳጆች ማፍራት እንደሚቻል ይሰማው ነበር። ከዚያም አንድ ሰው ወደ ቤቱ መጥቶ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእሱ እንደሞተለት ያውቅ እንደሆነ ጠየቀው። ሂቶሺ እንደ እሱ ላለ ሰው ለመሞት ፈቃደኛ የሚሆን ይኖራል ብሎ ስላልገመተ ጥያቄው የማወቅ ጉጉት አሳደረበት። የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር በሚሰጥበት ስብሰባ ላይ ተገኘና ‘ዓይናችሁ ቀና ይሁን’ በሚል ርዕስ የቀረበውን ምክር ሲሰማ በጣም ተገረመ። ተናጋሪው “ቀና” ዓይን አሻግሮ እንደሚመለከትና በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ አብራራ። (ሉቃስ 11:​34 NW ) ሂቶሺ ለገንዘብ ከመልፋት ይልቅ በሕይወቱ ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም ጀመረ።

በተጨማሪም ቁሳዊ ሀብት በተወሰነ መጠን የተረጋጋና ዋስትና ያለው ሕይወት ሊያስገኝልን ይችላል። ጠቀም ያለ ገንዘብ ካለ ስለ ዕለታዊ ፍላጎቶቻችን ከመጨነቅ ሊያሳርፈን ይችላል። ደስ በሚል አካባቢ የሠራነው ቆንጆ ቤት አንድ ነገር እንዳከናወንን እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል። ዘመናዊ ልብስና ቆንጆ መኪና የሌሎችን አድናቆት ሊያተርፉልን ይችላሉ።

‘በድካማችን ሁሉ ደስ መሰኘት’ መቻላችን በረከት ነው። (መክብብ 3:​13) እንዲሁም ተረፍ ያለ ገንዘብ ካለን የምናፈቅራቸው ሰዎች ‘ሳይቸገሩ እንዲኖሩ፣ የሚበሉትና የሚጠጡት እንዲያገኙ እንዲሁም እንዲደሰቱ’ ያስችላቸዋል። ይሁን እንጂ ቁሳዊ ነገሮች ያላቸው ዋጋ በንኖ ይጠፋል። ኢየሱስ ክርስቶስ መጎምጀትን በተመለከተ ሲያስጠነቅቅ “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፣ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” ብሏል። (ሉቃስ 12:​15-21) ያፈራነው ንብረት ብዛት ወይም ዋጋ ምንም ያህል ቢሆን ሕይወት ሊያስገኝልን አይችልም።

ለምሳሌ ያህል ሊዝ ደህና ገንዘብ ያለው ሰው አግብታ ነበር። እንዲህ ትላለች:- “አንድ ቆንጆ ቤትና ሁለት መኪናዎች ነበሩን። ደግሞም ያለን ገንዘብ በቁሳዊ ረገድ ዓለም በሚያቀርባቸው ነገሮች ሁሉ የመደሰት ነፃነት ሰጥቶን ነበር። . . . የሚያስገርመው ግን እንደዚያም ሆኖ ስለ ገንዘብ እጨነቅ ነበር።” ይህንንም ስታብራራ “ብዙ ያጣነው ነገር ነበር። ብዙ ባለህ መጠን የዚያኑ ያህል ለአደጋ የተጋለጥክ እንደሆንህ ይሰማሃል” ብላለች።

በተጨማሪም ዝነኛና ታዋቂ መሆንም ውዳሴና ክብር ሊያስገኙ ስለሚችሉ ብዙዎች ከፍ ያለ ግምት ይሰጧቸዋል። ዛሬ ጥሩ ሥራ ማግኘት የሚያስቀና ነገር ነው። ለየት ያለ ችሎታ ወይም ሙያ ማዳበራችን እውቅናን እንድናተርፍ ሊረዳን ይችላል። ሌሎች ሊያወድሱን፣ ለእኛ አመለካከት ከፍ ያለ ግምት ሊሰጡ እንዲሁም ከእኛ ጋር የመወዳጀት ምኞት ሊያድርባቸው ይችላል። ይህ ሁሉ ለጊዜው የሚያስደስትና የሚያረካ ሊሆን ቢችልም ውሎ አድሮ እየከሰመ መሄዱ አይቀርም። ሰሎሞን አንድ ንጉሥ ሊያገኝ የሚችለው ክብርና ሥልጣን በሙሉ የነበረው ቢሆንም እንኳ እንዲህ ሲል ምሬቱን ገልጿል:- ‘ጥበበኛንም ሆነ ሰነፍን ሁለቱንም የሚያስታውሳቸው አይገኝም፤ ሁላችንም የተረሳን ሆነን እንቀራለን።’ (መክብብ 2:​16 የ1980 ትርጉም) ክብርም ሆነ ዝና ለአንድ ሰው ሕይወት ሊያስገኙለት አይችሉም።

ቼሎ የሚባል አንድ የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ ዝነኛ ከመሆን የበለጠ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነገር እንዳለ ማስተዋል ችሏል። ልዩ ተሰጥዖ ስለነበረው ሙያውን ለማሻሻል የሚረዳው ትምህርት ተከታትሏል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራው የመገናኛ ብዙሐንንና የኪነ ጥበብ ገምጋሚዎችን አድናቆት አተረፈለት። አብዛኞቹ የቅርጻ ቅርጽ ሥራዎቹ በታላላቅ የአውሮፓ ከተሞች ለሕዝብ ዕይታ ቀርበዋል። ቼሎ እንዲህ ሲል ይናገራል:- “ሐቁን ለመናገር ለተወሰነ ጊዜ ኪነ ጥበብ የሕይወቴ ዓቢይ ክፍል ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ በሙያዬ መግፋት ማለት ሁለት ጌቶች ለማገልገል ከመጣር ተለይቶ እንደማይታይ ተገነዘብኩ። (ማቴዎስ 6:​24) ላከናውነው የምችለው ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊ ሥራ የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ እንደሆነ አመንኩ። በመሆኑም የቅርጻ ቅርጽ ሙያዬን ለመተው የግል ውሳኔ ላይ ደረስኩ።”

ከሁሉ የላቀ ዋጋ ያለው ነገር ምንድን ነው?

ያለ ሕይወት ማንኛውም ነገር ትርጉም ወይም ዋጋ ስለማይኖረው በሕይወት ለመቀጠል ዋስትና የሚሆነን ምን ነገር ማግኘት እንችላለን? የሕይወት ሁሉ ምንጭ ይሖዋ አምላክ ነው። (መዝሙር 36:​9) በእርግጥም “በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።” (ሥራ 17:​28) ለሚወድዳቸው ሰዎች የዘላለም ሕይወት ስጦታን ይሰጣቸዋል። (ሮሜ 6:​23) ለዚህ ስጦታ ብቁ እንድንሆን ምን ማድረግ አለብን?

የዘላለም ሕይወት ስጦታ ማግኘታችን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና በመመሥረታችን ላይ የተመካ ነው። ስለዚህ የእሱን ሞገስ ማግኘት ሊኖረን ከሚችለው ከማንኛውም ንብረት የበለጠ ከፍተኛ ዋጋ አለው። የአምላክን ሞገስ ስናገኝ እውነተኛና ዘላለማዊ ደስታ የማግኘት ተስፋ ይኖረናል። የአምላክን ሞገስ ካጣን ግን ዘላለማዊ ጥፋት ይጠብቀናል። በመሆኑም ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት የሚረዳን ማንኛውም ነገር ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ግልጽ ነው።

ማድረግ ያለብን ነገር

ስኬታማ መሆናችን የተመካው እውቀት በማግኘታችን ላይ ነው። የትክክለኛ እውቀት ምንጭ የይሖዋ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አምላክን ለማስደሰት ምን ማድረግ እንዳለብን የሚነግረን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። በመሆኑም ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥንቃቄ ማጥናት ይገባናል። ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የቻልነውን ያህል ለማወቅ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረጋችን ‘የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ የሚያስችለውን እውቀት’ ይሰጠናል። (ዮሐንስ 17:​3) እንዲህ ዓይነቱ እውቀት ከፍ አድርገን ልንመለከተው የሚገባ ሀብት ነው!​—⁠ምሳሌ 2:​1-5

ከአምላክ ቃል የምናገኘው እውቀት ቀጣዩን እርምጃ እንድንወስድ ያዘጋጀናል፤ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው። ይሖዋ ወደ እሱ የሚመጡ ሁሉ በኢየሱስ በኩል መቅረብ እንዳለባቸው ደንግጓል። (ዮሐንስ 14:​6) ደግሞም “መዳን በሌላ በማንም የለም።” (ሥራ 4:​12) የመጨረሻ መዳናችን የተመካው “በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን . . . በክቡር የክርስቶስ ደም” ነው። (1 ጴጥሮስ 1:​18, 19) በኢየሱስ ትምህርቶች በማመንና ምሳሌውን በመከተል እምነታችንን ማሳየት አለብን። (ዕብራውያን 12:​1-3፤ 1 ጴጥሮስ 2:​21) መሥዋዕቱ ምንኛ የላቀ ዋጋ ያለው ነው! መሥዋዕቱ የሚያስገኘው ፋይዳ ጠቅላላ የሰው ልጆችን ዘላለማዊ ዕጣ ይወስናል። ቤዛዊ መሥዋዕቱ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ሲውል እውነተኛ ዋጋ ያለው የዘላለም ሕይወት ስጦታ ያስገኝልናል።​—⁠ዮሐንስ 3:​16

ኢየሱስ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” ብሏል። (ማቴዎስ 22:​37) ይሖዋን መውደድ ማለት ‘ትእዛዛቱን መጠበቅ’ ማለት ነው። (1 ዮሐንስ 5:​3) ትእዛዛቱ ከዓለም የተለየን እንድንሆን፣ ከፍ ያለ የሥነ ምግባር ደረጃ እንድንጠብቅ እንዲሁም መንግሥቱን በታማኝነት እንድንደግፍ ይጠይቁብናል። ከሞት ይልቅ ‘ሕይወትን የምንመርጥበት’ መንገድ ይህ ነው። (ዘዳግም 30:​19) ‘ወደ አምላክ ከቀረብን እሱም ወደ እኛ ይቀርባል።’​—⁠ያዕቆብ 4:​8

የዓለምን ውድ ሀብት በጠቅላላ ከማግኘት የአምላክን ሞገስ እንዳገኘን እርግጠኛ መሆን የላቀ ዋጋ አለው። በምድር ላይ የመጨረሻ ባለጸጋ የአምላክን ሞገስ ያገኙ ሰዎች ናቸው! በመሆኑም እውነተኛ ዋጋ ያለውን ሀብት ማለትም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ጥረት እናድርግ። በእርግጥም፣ ቀጥሎ ያለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር መከተላችን የተገባ ነው:- “ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፣ . . . የዘላለምን ሕይወት ያዝ።”​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​11, 12

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከፍ ያለ ዋጋ የምትሰጠው ነገር ምንድን ነው? ገንዘብ፣ ቁሳዊ ሀብት፣ ዝና፣ ወይስ ሌላ ነገር?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥንቃቄ ማጥናት ይገባናል