በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ በረከት ባለጠጋ ታደርገናለች

የይሖዋ በረከት ባለጠጋ ታደርገናለች

የይሖዋ በረከት ባለጠጋ ታደርገናለች

“የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም።”—ምሳሌ 10:22

1, 2. ደስታ ከቁሳዊ ብልጥግና ጋር የማይዛመደው ለምንድን ነው?

 በዛሬው ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው የተጠመደው ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ነው። ይሁን እንጂ ቁሳዊ ነገሮች ደስተኛ ያደርጓቸዋልን? “የዛሬውን ያክል ሰዎች የወደፊት ዕጣቸው የጨለመበት ጊዜ ትዝ አይለኝም” በማለት ዚ አውስትራሊያን ውሜንስ ዊክሊ ተናግሯል። አክሎም “ይህ በጣም ግራ የሚያጋባ ነው። አውስትራሊያ በአስተማማኝ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝና ኑሮ እንደ አሁኑ የተሻሻለበት ጊዜ እንደሌለ ይነገራል። . . . አሁንም በሕዝቡ ዘንድ አፍራሽ አመለካከት ሰፍኖ ይገኛል። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በሕይወታቸው ውስጥ አንድ የጎደለባቸው ነገር እንዳለ ይሰማቸዋል። ምን እንደሆነ ግን አያውቁትም።” ቅዱሳን ጽሑፎች ያሉን ቁሳዊ ነገሮች ደስታም ሆነ ሕይወት ሊያስገኙልን እንደማይችሉ መናገራቸው ምንኛ ትክክል ነው!​—⁠መክብብ 5:10፤ ሉቃስ 12:15

2 ከሁሉ የላቀ ደስታ ማግኘት የሚቻለው በይሖዋ በረከት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ይህን በማስመልከት ምሳሌ 10:​22 “የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም” በማለት ይገልጻል። ብዙውን ጊዜ ቁሳዊ ሃብትን ለማግኘት መስገብገብ ሥቃይ ያስከትላል። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተስማሚ ነው:- “ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።”​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10

3. የአምላክ አገልጋዮች መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

3 በሌላው በኩል ደግሞ ‘የይሖዋን ድምፅ ሁልጊዜ የሚሰሙ’ ሁሉ ሥቃይን የማይጨምር በረከት ያገኛቸዋል። (ዘዳግም 28:​2) ይሁን እንጂ አንዳንዶች ‘የይሖዋ በረከት ኀዘንን የማይጨምር ከሆነ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?’ ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ። አምላክ መከራ እንዲ​ደርስብን ሊፈቅድ ቢችልም መከራ የሚደርስብን ከሰይጣን፣ እርሱ ከሚቆጣጠረው ክፉ ሥርዓትና ከራሳችን አለፍጽምና መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 6:5፤ ዘዳግም 32:4, 5፤ ዮሐንስ 15:19፤ ያዕቆብ 1:14, 15) ይሖዋ ‘የበጎ ስጦታ ሁሉ የፍጹምም በረከት ሁሉ’ ምንጭ ነው። (ያዕቆብ 1:17) ስለዚህ የእርሱ በረከት ፈጽሞ መከራን አይጨምርም። ፍጹም ከሆኑት የይሖዋ በረከቶች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

የአምላክ ቃል​—⁠በዋጋ ሊተመን የማይችል ስጦታ

4. የይሖዋ ሕዝቦች ‘በዚህ የፍጻሜ ዘመን’ ምን በረከትና ልዩ ስጦታ አግኝተዋል?

4 የዳንኤል ትንቢት ‘የፍጻሜውን ዘመን’ በማስመልከት “እውቀትም ይበዛል” በማለት ይናገራል። ይሁን እንጂ “ክፉዎችም ሁሉ አያስተውሉም፣ ጥበበኞች ግን ያስተውላሉ” የሚል መግለጫም በዚህ ትንቢት ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። (ዳንኤል 12:4, 10) እስቲ ቆም በልና ይህን አስብ! የአምላክ ቃል በተለይ ደግሞ ትንቢቶቹ በመለኮታዊ ጥበብ የተገለጡ በመሆናቸው ክፉዎች ትክክለኛ ትርጉማቸውን ሊያውቁ አይችሉም። የአምላክ ሕዝቦች ግን ይችላሉ። የአምላክ ልጅ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ” በማለት ጸልዮአል። (ሉቃስ 10:21) በዋጋ ሊተመን የማይችለውን በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክን ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘትና ይሖዋ መንፈሳዊ ማስተዋል ከሚሰጣቸው ሰዎች መካከል መሆን ምንኛ በረከት ነው!​—⁠1 ቆሮንቶስ 1:​21, 27, 28፤ 2:14, 15

5. ጥበብ ምንድን ነው? እንዴትስ ልናገኘው እንችላለን?

5 ‘ላይኛይቱን ጥበብ’ ባናገኝ ኖሮ መንፈሳዊ ማስተዋል ፈጽሞ አይኖረንም ነበር። (ያዕቆብ 3:​17) ጥበብ ችግሮችን ለመፍታት፣ ከአደጋ ለመጠበቅ ወይም ለመሰወር፣ ግብ ላይ ለመድረስ ወይም ትክክለኛ ምክር ለመስጠት እውቀትንና ማስተዋልን የመጠቀም ችሎታ ነው። አምላካዊ ጥበብን የምናገኘው እንዴት ነው? ምሳሌ 2:​6 “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ” በማለት ይናገራል። አዎን፣ ይሖዋ ለንጉሥ ሰሎሞን “ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና” እንደሰጠው ሁሉ እኛም አጥብቀን ከጸለይን ጥበብን በመስጠት ይባርከናል። (1 ነገሥት 3:11, 12፤ ያዕቆብ 1:5-8) ጥበብን እንድናገኝ ቃሉን አዘውትረን በማጥናትና በሥራ ላይ በማዋል ሁልጊዜ ይሖዋን መስማት ይገባናል።

6. የአምላክን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ላይ ተግባራዊ ማድረጋችን የጥበብ ጎዳና የሆነው ለምንድን ነው?

6 የአምላካዊ ጥበብ ዋና ዋና ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህም በየትኛውም መስክ ማለትም በአካላዊ፣ በአእምሯዊ፣ በስሜታዊና በመንፈሳዊ ይጠቅሙናል። መዝሙራዊው እንደሚከተለው ብሎ መዘመሩ የተገባ ነው:- “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል። የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፣ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፣ ዓይንንም ያበራል። የእግዚአብሔር ፍርሃት ንጹሕ ነው፤ ለዘላለም ይኖራል፤ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ነው። ከወርቅና ከክቡር ዕንቁ ይልቅ ይወደዳል።”​—⁠መዝሙር 19:7-10፤ 119:72

7. የአምላክን የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች ችላ ማለት ምን ያስከትላል?

7 በሌላው በኩል ደግሞ የአምላክን የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች ችላ የሚሉ ሁሉ የሚፈልጉትን ደስታና ነፃነት አያገኙም። ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ አምላክ እንደማይዘበትበትና አንድ ሰው የሚዘራውን ያንኑ ደግሞ እንደሚያጭድ ይገነዘባሉ። (ገላትያ 6:7) የአምላክን ቃል ችላ የሚሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያልተፈለገ እርግዝናን፣ አስከፊ በሽታን ወይም አካልን በሚያመነምኑ ሱሶች መጠመድን የመሳሰሉ አሳዛኝ ውጤቶች ያጭዳሉ። ተጸጽተው አካሄዳቸውን እስካልለወጡ ድረስ ይህ የሚከተሉት ጎዳና ውሎ አድሮ ለሞት ምናልባትም አምላክ ለሚያመጣው ጥፋት ይዳርጋቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 7:13, 14

8. የአምላክን ቃል የሚወድዱ ሰዎች ደስተኞች የሆኑት ለምንድን ነው?

8 ይሁን እንጂ የአምላክን ቃል የሚወድዱና በሥራ ላይ የሚያውሉ አሁንም ሆነ ወደፊት የተትረፈረፉ በረከቶች ያገኟቸዋል። የአምላክ ሕግ ነፃ እንዳወጣቸው ይሰማቸዋል እንዲሁም ደስተኞች ናቸው። ከኃጢአትና የኃጢአት ውጤት ከሆነው ሞት ነፃ የሚሆኑበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ። (ሮሜ 8:20, 21፤ ያዕቆብ 1:​25) ይህ ተስፋ አምላክ በፍቅሩ ተገፋፍቶ ለሰው ዘር በሰጠው ማለትም በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ እርግጠኛ ተስፋ ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 6:23) እንዲህ ያለው ወደር የማይገኝለት ስጦታ አምላክ ለሰው ዘሮች ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያረጋግጣል፤ እንዲሁም ይሖዋን ሁልጊዜ የሚሰሙ ሰዎች ማለቂያ የሌለው በረከቶችን እንደሚያገኙ ዋስትና ይሰጣል።​—⁠ሮሜ 8:32

ለመንፈስ ቅዱስ ስጦታ አመስጋኞች ነን

9, 10. ከይሖዋ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? አንድ ምሳሌ ጥቀስ።

9 አመስጋኝ የምንሆንበት ሌላው የአምላክ ፍቅራዊ ስጦታ መንፈስ ቅዱሱ ነው። በ33 እዘአ በዋለው በጰንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሩሳሌም ተሰብስበው የነበሩትን እጅግ ብዙ ሰዎች “ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” በማለት በጥብቅ አሳስቧቸው ነበር። (ሥራ 2:38) ዛሬም ይሖዋ መንፈሱን ለማግኘት ለሚጸልዩና ፈቃዱን ለማድረግ ለሚፈልጉ ራሳቸውን ለእርሱ ለወሰኑ አገልጋዮቹ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 11:9-13) በጥንት ጊዜ ይህ በአጽናፈ ዓለሙ ሁሉ አቻ የማይገኝለት ኃይል ማለትም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል የጥንት ክርስቲያኖችን ጨምሮ ለታመኑ ወንዶችና ሴቶች የኃይል ምንጭ ሆኗቸዋል። (ዘካርያስ 4:6፤ ሥራ 4:31) የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ከባድ መሰናክል ወይም ችግር ቢገጥመን እንኳ ለእኛም በተመሳሳይ ኃይል ሊሰጠን ይችላል።​—⁠ኢዩኤል 2:​28, 29

10 በልጅነት ልምሻ የአካል ጉዳት የደረሰባትንና ለ37 ዓመታት እንደ ሳንባ ሆኖ በሚያገለግል ሰው ሠራሽ መሣሪያ ውስጥ ትኖር የነበረችውን የሎረልን ምሳሌ ተመልከት። a የነበረችበት ሁኔታ እጅግ ፈታኝ ቢሆንም እንኳ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ አምላክን በቅንዓት አገልግላለች። ሎረል ለብዙ ዓመታት የይሖዋን በረከቶች አግኝታለች። ለምሳሌ ያህል 24 ሰዓት ሙሉ ከማሽኑ የማትወጣ ቢሆንም እንኳ 17 የሚያክሉ ግለሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ መርዳት ችላለች! የነበረችበት ሁኔታ ሐዋርያው ጳውሎስ “ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝ” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ያስታውሱናል። (2 ቆሮንቶስ 12:10) አዎን፣ ምሥራቹን በመስበክ የምናገኘው ማንኛውም ዓይነት ስኬት አምላክ ድምፁን ሁልጊዜ ለሚሰሙ ሰዎች በሚሰጠው በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እንጂ በራሳችን ችሎታና ኃይል የሚገኝ አይደለም።​—⁠ኢሳይያስ 40:29-31

11. የአምላክ መንፈስ ‘አዲሱን ሰው’ በሚለብሱ ሰዎች ላይ የትኞቹን ባሕርያት ያፈራል?

11 አምላክን በታዛዥነት ብንሰማው መንፈሱ በውስጣችን የፍቅርን፣ የደስታን፣ የሰላምን፣ የትዕግሥትን፣ የቸርነትን፣ የበጎነትን፣ የእምነትን፣ የየውሃትንና የራስ መግዛትን ባሕርያት ያፈራል። (ገላትያ 5:22, 23) ይህ “የመንፈስ ፍሬ” ክርስቲያኖች ቀደም ሲል ያንጸባርቁት በነበረው አውሬ መሰል ባሕርይ ምትክ የሚለብሱት ‘የአዲሱ ሰው’ ክፍል ነው። (ኤፌሶን 4:20-24፤ ኢሳይያስ 11:6-9) ከዚህ ፍሬ የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዘው “የፍጻሜ ማሰሪያ” የተባለው ፍቅር ነው።​—⁠ቆላስይስ 3:14

ክርስቲያናዊ ፍቅር —⁠ከፍተኛ ዋጋ ያለው ስጦታ

12. ጣቢታ እና ሌሎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ፍቅርን ያሳዩት እንዴት ነው?

12 ክርስቲያናዊ ፍቅር የይሖዋ የበረከት ስጦታ ሲሆን አንድ ሰው ከፍ አድርጎ ሊመለከተው ይገባል። ይህ ፍቅር በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ሲሆን ከሥጋ ዝምድና ይልቅ አማኞችን ሊያቀራርብ የሚችል ከፍተኛ የመዋደድ ስሜት ነው። (ዮሐንስ 15:12, 13፤ 1 ጴጥሮስ 1:22) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ትኖር የነበረችውን ግሩም ክርስቲያን ጣቢታን እንደ ምሳሌ አድርገህ ተመልከት። በተለይ በጉባኤ ውስጥ ለነበሩ መበለቶች “መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች።” (ሥራ 9:36) እነዚህ ሴቶች በሥጋ የሚዛመዷቸው ሰዎች ይኖሯቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ጣቢታ እነርሱን ለመርዳትና ለማበረታታት የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ ፈለገች። (1 ዮሐንስ 3:18) ጣቢታ ምንኛ ግሩም ምሳሌ ትታለች! ጵርስቅላ እና አቂላ ለጳውሎስ ሲሉ ‘ነፍሳቸውን ለሞት እንዲያቀርቡ’ የገፋፋቸው የወንድማማች ፍቅር ነው። እንዲሁም ኤጳፍራ፣ ሉቃስ፣ ሄኔሲፎሩ እና ሌሎች ሰዎች ሮም በሚገኘው እስር ቤት ታስሮ በነበረበት ጊዜ ሐዋርያውን ለመርዳት ፍቅር ገፋፍቷቸዋል። (ሮሜ 16:3, 4፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:16፤ 4:11፤ ፊልሞና 23, 24) አዎን፣ እንደዚያን ጊዜ ሁሉ በዛሬውም ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖች የኢየሱስን እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ለይቶ የሚያሳውቀው የአምላክ የበረከት ስጦታ የሆነው ‘ፍቅር በመካከላቸው አለ።’​—⁠ዮሐንስ 13:34, 35

13. ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበራችንን ከልብ የምናደንቅ መሆናችንን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?

13 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚንጸባረቀውን ፍቅር እንደ ውድ ነገር አድርገህ ትመለከታለህ? ዓለም አቀፍ ለሆነው ለመንፈሳዊ የወንድማማች ማኅበራችን አመስጋኝ ነህ? እነዚህም ቢሆኑ በደስታ እንድንፍለቀለቅ የሚያደርጉና ባለጠጋ ከሚያደርጉን ከላይ ከሚመጡት በረከቶች መካከል የሚመደቡ ናቸው። ከፍ አድርገን እንደምንመለከታቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና ፍቅርንና ሌሎች የመንፈስ ፍሬዎችን በማፍራት ነው።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:9፤ ዕብራውያን 10:24, 25

“ስጦታ የሆኑ ወንዶች”

14. አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ እንዲያገለግል ምን ብቃት ይጠየቅበታል?

14 ሽማግሌዎች ወይም የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው የአምልኮ ባልንጀሮቻቸውን የማገልገል ምኞት ያላቸው ክርስቲያን ወንዶች ግሩም ግብ አላቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1, 8) ለእነዚህ መብቶች ብቁ ሆኖ ለመገኘት አንድ ወንድም መንፈሳዊ ሰው፣ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠንቅቆ የሚያውቅና በመስክ አገልግሎት ቀናተኛ መሆን ይገባዋል። (ሥራ 18:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:15፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:5) ትዕቢተኛ፣ ኩሩና የሥልጣን ጥም ያላቸው ሰዎች መለኮታዊ በረከቶችን ስለማያገኙ የትሕትናን፣ ልክን የማወቅንና የትዕግሥትን ባሕርያት ማንጸባረቅ ይኖርበታል። (ምሳሌ 11:2፤ ዕብራውያን 6:15፤ 3 ዮሐንስ 9, 10) ያገባም ከሆነ ቤተሰቡን በሚገባ የሚያስተዳድር አፍቃሪ የቤተሰብ ራስ መሆን አለበት። (1 ጢሞቴዎስ 3:4, 5, 12) እንዲህ ያለው ሰው መንፈሳዊ ሃብትን ከፍ አድርጎ ስለሚመለከት የይሖዋን በረከት ያገኛል።​—⁠ማቴዎስ 6:19-21

15, 16. ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ መሆናቸውን ያስመሰከሩት እነማን ናቸው? ምሳሌ ጥቀስ።

15 በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆነው እያገለገሉ ያሉት በወንጌላዊነት፣ በእረኝነትና በአስተማሪነት ሥራ በትጋት ሲካፈሉ ስናይ እነዚህን ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ከፍ አድርገን እንድንመለከታቸው ያነሳሳናል። (ኤፌሶን 4:8, 11 NW ) ከእነርሱ አገልግሎት ጥቅም የሚያገኙት አድናቆታቸውን ሁልጊዜ የሚገልጹ ላይሆኑ ቢችሉም ይሖዋ ግን እነዚህ ታማኝ ሽማግሌዎች የሚያከናውኑትን አገልግሎት ይመለከታል። ሕዝቦቹን በማገልገል ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር ፈጽሞ አይረሳም።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 5:17፤ ዕብራውያን 6:10

16 የአንጎል ቀዶ ሕክምና ለማድረግ በዝግጅት ላይ የነበረችን አንዲት ክርስቲያን የጎበኘ አንድ ትጉህ ሽማግሌ ያደረገውን ተመልከት። “በጣም ደግ፣ ደጋፊና አሳቢ ነው” በማለት አንዲት የቤተሰቡ የቅርብ ወዳጅ ጽፋለች። “አብሮን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይችል እንደሆነ ፈቃድ ጠየቀን። እየጸለየ ሳለ አባትየው [የይሖዋ ምሥክር አይደለም] ማልቀስ ጀመረ። በሐኪም ቤቱ መኝታ ክፍል ውስጥ የነበሩ ሁሉ እንባቸውን መቆጣጠር አልቻሉም። ይህ ሽማግሌ ያቀረበው ጸሎት ምንኛ ልብን የሚነካ ነው! ይሖዋ እንዲህ ባለው ወቅት እርሱን መላኩ ምንኛ የፍቅር መግለጫ ነው!” በሕመም ላይ የምትገኝ አንዲት ሌላ ምሥክርም መጥተው ስለጎበኟት ሽማግሌዎች ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “ልዩ የሕክምና ክትትል የሚደረግበት ክፍል ድረስ መጥተው ከጠየቁኝ በኋላ የሚገጥመኝን ማንኛውንም ነገር መቋቋም እንደምችል ሆኖ ተሰማኝ። ብርታትና ውስጣዊ ሰላም አገኘሁ።” እንዲህ ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት መግዛት የሚችል ሰው አለ? በጭራሽ! ይህ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት የተገኘ የአምላክ ስጦታ ነው።​—⁠ኢሳይያስ 32:1, 2

ስጦታ የሆነው የመስክ አገልግሎት

17, 18. (ሀ) ይሖዋ ለሁሉም ሕዝቦቹ የሰጠው የአገልግሎት ስጦታ ምንድን ነው? (ለ) አገልግሎታችንን መፈጸም እንችል ዘንድ አምላክ ምን እርዳታ ሰጥቶናል?

17 ሰዎች ሉዓላዊውን አምላክ ይሖዋን ከማገልገል ጋር ሊተካከል የሚችል ታላቅ ክብር ሊያገኙ አይችሉም። (ኢሳይያስ 43:10፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) ያም ሆኖ ግን ወጣትም ሆነ በዕድሜ የገፋ፣ ወንድም ሆነ ሴት አምላክን ለማገልገል ልባዊ ምኞት ያለው ማንኛውም ሰው ለሕዝብ በሚሰጠው አገልግሎት የመካፈል መብት ተዘርግቶለታል። በዚህ ውድ ስጦታ ትካፈላለህ? አንዳንዶች እንደማይበቁ ሆኖ ስለሚሰማቸው በዚህ ሥራ ለመካፈል ያቅማሙ ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ እርሱን ለሚያገለግሉት መንፈስ ቅዱስ በመስጠት የጎደላቸውን ሁሉ እንደሚያሟላላቸው አስታውስ።​—⁠ኤርምያስ 1:6-8፤ 20:11

18 ይሖዋ የመንግሥቱን የስብከት ሥራ የሰጠው ኩሩና በራሳቸው ችሎታ ለሚታመኑ ሰዎች ሳይሆን ትሑት ለሆኑ አገልጋዮቹ ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:20, 26-29) ትሑትና ልካቸውን የሚያውቁ ሰዎች አቅማቸው ውስን መሆኑን ስለሚገነዘቡ በመስክ አገልግሎት በሚካፈሉበት ጊዜ አምላክ በሚሰጣቸው ድጋፍ ላይ ይታመናሉ። እንዲሁም “በታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት የሚያቀርበውን መንፈሳዊ እርዳታ በአድናቆት ይቀበላሉ።​—⁠ሉቃስ 12:42-44፤ ምሳሌ 22:4

ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት​—⁠ግሩም ስጦታ

19. ልጆችን በማሳደግ ረገድ ስኬታማ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

19 ጋብቻና ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ከአምላክ የሚገኝ ስጦታ ነው። (ሩት 1:9፤ ኤፌሶን 3:14, 15) ልጆችም አምላካዊ ባሕርያትን በውስጣቸው ለተከሉላቸው ወላጆች ደስታ የሚያመጡ ውድ “የእግዚአብሔር ስጦታ” ናቸው። (መዝሙር 127:3) ወላጅ ከሆንክ ልጆችህን በቃሉ መሠረት በማሠልጠን የይሖዋን ድምፅ ሁልጊዜ መስማትህን ቀጥል። እንዲህ የሚያደርጉ ሁሉ የይሖዋን ድጋፍና የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያገኙ የተረጋገጠ ነው።​—⁠ምሳሌ 3:5, 6፤ 22:6፤ ኤፌሶን 6:1-4

20. እውነተኛውን አምልኮ የተዉ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ምን ነገር ሊረዳቸው ይችላል?

20 አምላክን የሚፈሩ ወላጆች ትጋት የተሞላበት ጥረት ቢያደርጉም ከልጆቻቸው መካከል አንዳንዶቹ ትልልቅ በሚሆኑበት ጊዜ እውነተኛውን አምልኮ ሊተዉ ይችላሉ። (ዘፍጥረት 26:34, 35) ይህ የወላጆችን ቅስም የሚሰብር ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 17:21, 25) ይሁን እንጂ ተስፋ ቆርጦ ቁጭ ከማለት ይልቅ ኢየሱስ አባካኙን ልጅ በማስመልከት የሰጠውን ምሳሌ ማስታወሱ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በምሳሌው ላይ የተገለጸው ልጅ ከቤት ወጥቶ ጋጠወጥ ሆኖ የኖረ ቢሆንም እንኳ ከጊዜ በኋላ ወደ አባቱ ቤት በተመለሰ ጊዜ አባቱም በደስታና በፍቅር ተቀብሎታል። (ሉቃስ 15:11-32) ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ታማኝ ክርስቲያን ወላጆች ችግራቸውን ይሖዋ እንደሚረዳላቸው፣ ፍቅራዊ እንክብካቤውን እንደማይነፍጋቸውና ያልተቋረጠ ድጋፉን እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ።​—⁠መዝሙር 145:14

21. መስማት ያለብን ማንን ነው? ለምንስ?

21 እንግዲያው ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ በእርግጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለማወቅ እንሞክር። በእኛም ሆነ በቤተሰባችን ላይ ሥቃይ ሊያስከትል የሚችለውን ቁሳዊ ሃብት በማሳደድ ላይ ነንን? ወይስ ‘ከሰማያት አባት’ የሚመጡትን ‘በጎ ስጦታና ፍጹም በረከቶችን’ እየተከታተልን ነው? (ያዕቆብ 1:17) ‘የሐሰት አባት’ የሆነው ሰይጣን ቁሳዊ ሀብት በማሳደድ እንድንጠመድና ደስታም ሕይወትም እንድናጣ ይፈልጋል። (ዮሐንስ 8:44፤ ሉቃስ 12:15) ሆኖም ይሖዋ የሚጠቅመንን ነገር በትክክል ያውቃል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ስለዚህ ሰማያዊ አባታችንን ሁልጊዜ እንስማ፤ እንዲሁም በእርሱ ‘ደስ ይበለን።’ (መዝሙር 37:4) እንዲህ ያለውን ጎዳና ከተከተልን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የይሖዋ ስጦታዎችና የተትረፈረፈ በረከት እናገኛለን። እንዲህ ያለው በረከት ኃዘንን አይጨምርም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የጥር 22, 1993 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 18-21ን ተመልከት።

ታስታውሳለህን?

• ከሁሉ የላቀውን ደስታ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

• ይሖዋ ለሕዝቡ ከሰጣቸው ስጦታዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

• የመስክ አገልግሎት ስጦታ የሆነው ለምንድን ነው?

• ወላጆች ልጆቻቸውን በሚያሳድጉበት ጊዜ የአምላክን በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ ይችላሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ስጦታ ለሆነው በጽሑፍ ለሰፈረው ቃሉ አድናቆትህን ታሳያለህን?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሎረል ኒዝቤት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለችም አምላክን በቅንዓት አገልግላለች

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በሚያከናውኑት ፍቅራዊ ተግባር እንደ ጣቢታ የታወቁ ናቸው

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለእምነት ባልደረቦቻቸው ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳያሉ