በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ በረከት ያገኝህ ይሆን?

የይሖዋ በረከት ያገኝህ ይሆን?

የይሖዋ በረከት ያገኝህ ይሆን?

“የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል ያገኙህማል።”​—⁠ዘዳግም 28:​2

1. እስራኤላውያን በረከት ማግኘታቸው ወይም እርግማን መቀበላቸው የተመካው በምን ላይ ነበር?

 እስራኤላውያን ለ40 ዓመት በምድረ በዳ ያደረጉትን ጉዞ ለማጠናቀቅ በተቃረቡበት ወቅት በሞዓብ ሜዳ ተሰብስበው ነበር። ተስፋይቱ ምድር ከፊት ለፊታቸው ነች። በዚህ ወቅት ሙሴ የበረከቶችንና የእርግማኖችን ዝርዝር አካትቶ የያዘውን የዘዳግምን መጽሐፍ ጻፈ። የእስራኤል ሕዝብ ይሖዋን በመታዘዝ ‘የእግዚአብሔርን ቃል ሁልጊዜ ቢሰሙ’ ኖሮ በረከቶች ‘ይመጡላቸው’ ነበር። ይሖዋ እንደ ‘ልዩ ንብረቱ’ አድርጎ ወድዷቸው የነበረ ሲሆን ለእነርሱም ጥቅም ሲል ኃይሉን ለመግለጥ ፈቃደኛ ነበር። ይሁን እንጂ እርሱን መስማታቸውን ካቆሙ እርግማን ይደርስባቸዋል።​—⁠ዘዳግም 8:10-14፤ 26:18 NW፤ 28:2, 15

2. ዘዳግም 28:​2 ላይ “ብትሰማ” እና “ያገኙህማል” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥ ግሶች ምን ትርጉም ያስተላልፋሉ?

2 በዘዳግም 28:​2 ላይ የሚገኘው “ብትሰማ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ ቀጣይነት ያለውን ድርጊት የሚያመለክት ቃል ነው። የይሖዋ ሕዝቦች እሱን የሚሰሙት አልፎ አልፎ መሆን የለበትም፤ ምንጊዜም እሱን መስማት አለባቸው። የአምላክን በረከቶች ማግኘት የሚችሉት እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው። “ያገኙህማል” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ግስ ብዙውን ጊዜ “አንድን ነገር አሳድዶ መያዝ” ወይም “መድረስ” የሚል ትርጉም ያለው ከአደን ጋር የተያያዘ ቃል ነው።

3. እንደ ኢያሱ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 የእስራኤላውያን መሪ የነበረው ኢያሱ ይሖዋን ለመስማት በመምረጡ ተባርኳል። ኢያሱ “የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ፣ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” በማለት ተናግሯል። በዚህ ጊዜ ሕዝቡም “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ” በማለት መለሱ። (ኢያሱ 24:15, 16) ኢያሱ በነበረው ጥሩ ዝንባሌ የተነሳ በእርሱ ትውልድ ከነበሩት ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገቡ መብት ካገኙት ጥቂት ሰዎች መካከል ለመሆን በቅቷል። እኛም በዛሬው ጊዜ ከተስፋይቱ ምድር እጅግ የላቁ ገጽታዎች ወዳሉት ምድር ለመግባት ደፍ ላይ እንገኛለን። ይህ የአምላክን ሞገስ ያገኙ ሁሉ በኢያሱ ዘመን ከነበሩት እጅግ የላቁ በረከቶችን የሚያገኙበት ምድራዊ ገነት ነው። እነዚህ በረከቶች ያገኙህ ይሆን? ይሖዋን መስማትህን ከቀጠልክ እነዚህን በረከቶች ታገኛለህ። ይህን ቁርጥ ውሳኔህን ማጠናከር ትችል ዘንድ የጥንቱን የእስራኤል ብሔርና አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ታሪክ መርምር።​—⁠ሮሜ 15:4

በረከት ወይስ እርግማን?

4. ሰሎሞን ባቀረበው ጸሎት መሠረት አምላክ ምን ሰጠው? እንዲህ ላሉት በረከቶች ምን ዓይነት ስሜት ሊያድርብን ይገባል?

4 ይሖዋ በንጉሥ ሰሎሞን አብዛኛው የግዛት ዘመን እስራኤላውያንን በእጅጉ ባርኳቸዋል። ያላንዳች ስጋት በጸጥታ ይኖሩ የነበረ ሲሆን የተትረፈረፉ መልካም ነገሮችንም አግኝተዋል። (1 ነገሥት 4:25) ሰሎሞን በብልጥግናው የሚታወቅ ቢሆንም እንኳ ቁሳዊ ብልጽግና ለማግኘት አምላክን አልጠየቀም። ከዚያ ይልቅ ገና ብላቴና ሳለና ተሞክሮ ባልነበረው ጊዜ ታዛዥ ልብ ለማግኘት ጸልዮአል። ይሖዋም ጥበብና ማስተዋል በመስጠት ልመናውን ሰምቶለታል። ይህም ሰሎሞን ጥሩና መጥፎ የሆኑትን ነገሮች በመለየት በሕዝቡ መካከል በትክክል እንዲፈርድ አስችሎታል። ይሖዋ ሃብትና ክብር የሰጠው ቢሆንም እንኳ ሰሎሞን ገና ወጣት ሳለ መንፈሳዊ ብልጽግና ያለውን የላቀ ዋጋ ተገንዝቦ ነበር። (1 ነገሥት 3:9-13) በቁሳዊ ነገር ረገድ ያለን ጥቂትም ይሁን ብዙ የይሖዋን በረከት ካገኘንና በመንፈሳዊ ባለጠጋ ከሆንን ምንኛ አመስጋኞች ነን!

5. የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ይሖዋን መስማታቸውን ባቆሙ ጊዜ ምን ደረሰባቸው?

5 እስራኤላውያን ይሖዋ ለሰጣቸው በረከቶች አመስጋኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል። እርሱን መስማታቸውን በማቆማቸው ምክንያት አስቀድሞ የተነገሩት እርግማኖች ደርሰውባቸዋል። ከዚህም የተነሳ የእስራኤል እና የይሁዳ ነዋሪዎች በጠላቶቻቸው ድል ተደርገው በምርኮ ተወስደዋል። (ዘዳግም 28:36፤ 2 ነገሥት 17:22, 23፤ 2 ዜና መዋዕል 36:17-20) መለኮታዊ በረከት የሚያገኙት ምንጊዜም ይሖዋን የሚሰሙ ሰዎች መሆናቸውን የአምላክ ሕዝቦች በዚህ ጊዜ ከደረሰባቸው መከራ ተምረዋል? በ537 ከዘአበ ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን ቀሪዎች ‘ጠቢብ ልብ’ እንዳገኙና ምንጊዜም አምላክን መስማት አስፈላጊ መሆኑን እንደተገነዘቡ የማሳየት አጋጣሚ ተከፍቶላቸው ነበር።​—⁠መዝሙር 90:12

6. (ሀ) ይሖዋ ለሕዝቡ ትንቢት እንዲናገሩ ሐጌንና ዘካርያስን የላከው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ በሐጌ በኩል ባስተላለፈው መልእክት የትኛው መሠረታዊ ሥርዓት ግልጽ ሆኖ ተብራርቷል?

6 ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን መሠዊያ የሠሩ ሲሆን ኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስም መገንባት ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ ኃይለኛ ተቃውሞ በገጠማቸው ጊዜ ቅንዓታቸው ተዳከመና የግንባታውን ሥራ አቆሙ። (ዕዝራ 3:1-3, 10፤ 4:1-4, 23, 24) ከዚያም አልፈው የራሳቸውን ኑሮ ወደማደላደል ዞር አሉ። በዚህም የተነሳ አምላክ ለእውነተኛው አምልኮ የሕዝቡን ቅንዓት እንደገና ለማቀጣጠል ሲል ሐጌ እና ዘካርያስ የተባሉ ነቢያቶቹን ላከ። ይሖዋ በሐጌ በኩል እንዲህ አለ:- “በውኑ ይህ [የአምልኮ] ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? . . . ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ብዙ ዘራችሁ፣ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፣ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ . . . ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ።” (ሐጌ 1:4-6) ቁሳዊ ጥቅሞችን ለማሳደድ ሲባል መንፈሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረግ የይሖዋን በረከት አያስገኝም።​—⁠ሉቃስ 12:15-21

7. ይሖዋ ለአይሁዳውያን “ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ” ያላቸው ለምንድን ነው?

7 በዕለታዊ ጉዳዮቻቸው የተጠመዱት አይሁዳውያን አምላክ ዝናብና ፍሬ የሚሆንበትን ወራት በመስጠት ሊባርካቸው የሚችለው በተቃውሞ ጊዜ እንኳ ሳይቀር ለእርሱ ታዛዥ ሆነው ከተገኙ ብቻ እንደሆነ ዘነጉ። (ሐጌ 1:9-11) በዚህም የተነሳ “ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ” የሚለው ጥብቅ ምክር ምንኛ ተስማሚ ነው! (ሐጌ 1:7) ይሖዋ ‘እስቲ አስቡት! በእርሻችሁ ፍሬ ማጣታችሁን ፈራርሶ ከሚገኘው የአምልኮ ቤቴ ጋር ያለውን ግንኙነት እስቲ ተመልከቱ!’ ብሎ እየተናገራቸው ያለ ያህል ነበር። በመጨረሻ የይሖዋ ነቢያት በመንፈስ አነሳሽነት የተናገሯቸው ቃላት ተቀባይ ልብ አግኝተው ሕዝቡ የቤተ መቅደሱን ሥራ እንደገና ጀመረና በ515 ከዘአበ አጠናቀቀ።

8. ይሖዋ በሚልክያስ ዘመን ለነበሩ አይሁዳውያን ምን ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጣቸው? ለምንስ?

8 ከጊዜ በኋላ በነቢዩ ሚልክያስ ዘመን አይሁዳውያን እንደገና በመንፈሳዊ ከመዋዠቃቸው የተነሳ ለአምላክ የማይገባ መሥዋዕት እስከ ማቅረብ ደረሱ። (ሚልክያስ 1:6-8) በዚህም የተነሳ ይሖዋ የምርታቸውን አሥራት ወደ ጎተራው እንዲያመጡና የሰማይን መስኮት በመክፈት አትረፍርፎ ይባርካቸው እንደሆነና እንዳልሆነ በዚህ እንዲፈትኑት ለሕዝቡ በመንገር አጥብቆ አሳሰባቸው። (ሚልክያስ 3:10) አይሁዳውያን ይሖዋን መስማታቸውን ቢቀጥሉ ኖሮ አምላክ አትረፍርፎ ይሰጣቸው የነበሩትን ነገሮች ለማግኘት ሲሉ በራሳቸው መንገድ መድከማቸው ምንኛ ሞኝነት ነው!​—⁠2 ዜና መዋዕል 31:10

9. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪካቸው የተመዘገበውን የየትኞቹን ሦስት ሰዎች የሕይወት ታሪክ እንመረምራለን?

9 መጽሐፍ ቅዱስ የእስራኤላውያንን ብሔራዊ ታሪክ በውስጡ ከመያዙም በተጨማሪ ሁልጊዜ ይሖዋን በመስማታቸው መለኮታዊ በረከት ያገኙ ወይም ባለመስማታቸው እርግማን የደረሰባቸው የበርካታ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ መዝግቦልናል። ከእነዚህ መካከል ከሦስቱ ማለትም ከቦዔዝ፣ ከናባል እና ከሐና ምን ትምህርት ልናገኝ እንደምንችል እንመልከት። በዚህ ረገድ የሩትን መጽሐፍ እንዲሁም 1 ሳሙኤል 1:​1–2:​21 እና 1 ሳሙኤል 25:​2-42ን ማንበብ ትፈልግ ይሆናል።

ቦዔዝ አምላክን ሰማ

10. ቦዔዝ እና ናባል የሚመሳሰሉባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

10 ምንም እንኳ ቦዔዝ እና ናባል በአንድ ዘመን የኖሩ ሰዎች ባይሆኑም የሚመሳሰሉባቸው አንዳንድ ነገሮች ነበሯቸው። ለምሳሌ ያህል ሁለቱም የኖሩት በይሁዳ ምድር ነው። ሁለቱም ሀብታም ባለርስቶች ሲሆኑ ለተቸገረ ሰው ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ ነበራቸው። ሆኖም የእነዚህ ሰዎች መመሳሰል ከዚህ በኋላ አልቀጠለም።

11. ቦዔዝ ሁልጊዜ ይሖዋን የሚሰማ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

11 ቦዔዝ ይኖር የነበረው በእስራኤል መሳፍንት ዘመን ነበር። ሰው አክባሪ ሲሆን እህል አጫጆቹም ለእርሱ ከፍ ያለ አክብሮት ነበራቸው። (ሩት 2:4) ቦዔዝ ሕጉ በሚያዘው መሠረት በማሳው ላይ ለድሆችና ለችግረኞች የሚቃረም እህል ያስቀር ነበር። (ዘሌዋውያን 19:9, 10) ቦዔዝ ስለ ሩትና ስለ ኑኃሚን በሰማ ጊዜና ሩት በዕድሜ የገፋችውን አማቷን ለመደገፍ ስትል በትጋት ስትሠራ በተመለከተ ጊዜ ምን አደረገ? ለሩት ለየት ያለ አስተያየት ያደረገላት ከመሆኑም በላይ ከእሱ ማሳ እንድትቃርም እንዲፈቅዱላት ለሰዎቹ ነገራቸው። ቦዔዝ በቃሉም ሆነ በፍቅራዊ ድርጊቱ ይሖዋን የሚሰማ መንፈሳዊ ሰው መሆኑን አሳይቷል። በዚህም የተነሳ የይሖዋን ሞገስና በረከት አግኝቷል።​—⁠ዘሌዋውያን 19:18፤ ሩት 2:5-16

12, 13. (ሀ) ይሖዋ መቤዠትን በተመለከተ ላወጣው ሕግ ቦዔዝ ጥልቅ አክብሮት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ቦዔዝ ምን መለኮታዊ በረከት አግኝቷል?

12 ቦዔዝ ሁልጊዜ ይሖዋን የሚሰማ ሰው እንደነበር የሚያሳየው ከሁሉ የላቀው ማስረጃ አምላክ መቤዠትን በተመለከተ ላወጣው ሕግ ያሳየው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ታዛዥነት ነው። ቦዔዝ የዘመዱን ማለትም የሟቹን የኑኃሚንን ባል የአቤሜሌክን ውርስ ከአቤሜሌክ ቤተሰብ እንዳይወጣ ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ አደረገ። ‘የባል ወንድምን ስለማግባት’ በወጣው ሕግ መሠረት ባል የሞተባት አንዲት ሴት የሟች ባሏን የቅርብ ዘመድ ማግባት ነበረባት። በዚህ መንገድ ውርሻው ለተወለደው ወንድ ልጅ ይተላለፍ ነበር። (ዘዳግም 25:5-10፤ ዘሌዋውያን 25:47-49) ኑኃሚን ልጅ መውለድ በማትችልበት ዕድሜ ላይ ትገኝ ስለነበር ሩት በኑኃሚን ምትክ ራሷን ለትዳር አቅርባለች። አንድ የአቤሜሌክ የቅርብ ዘመድ ኑኃሚንን ለመርዳት ፈቃደኛ ሆኖ ባለመገኘቱ ምክንያት ቦዔዝ ሩትን እንደ ሚስቱ አድርጎ ወሰዳት። የወለዱት ኢዮቤድ የተባለው ልጅ የኑኃሚን ልጅና የአቤሜሌክ ሕጋዊ ወራሽ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል።​—⁠ሩት 2:19, 20፤ 4:1, 6, 9, 13-16

13 ቦዔዝ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ሁኔታ ከአምላክ ሕግ ጋር በሚስማማ መንገድ በመመላለሱ የተትረፈረፉ በረከቶችን አግኝቷል። ኢዮቤድ በተባለው ልጃቸው አማካኝነት እርሱና ሩት የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት የመሆን መብት በማግኘት ተባርከዋል። (ሩት 2:12፤ 4:13, 21, 22፤ ማቴዎስ 1:1, 5, 6) ለሌሎች ሰዎች ፍቅር የሚያሳዩና አምላክ ካወጣቸው መስፈርቶች ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሁሉ በረከት እንደሚያገኙ ቦዔዝ ካሳየው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ድርጊት እንማራለን።

ናባል ይሖዋን አልሰማም

14. ናባል ምን ዓይነት ሰው ነበር?

14 ቦዔዝ ይሖዋን እንደሰማ ናባል ይሖዋን አልሰማም። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን የአምላክን ሕግ ተላልፏል። (ዘሌዋውያን 19:18) ናባል መንፈሳዊ ሰው አልነበረም። ‘ባለጌና ግብሩ ክፉ ነበረ።’ አገልጋዮቹ እንኳ ሳይቀሩ የሚመለከቱት እንደ “ምናምንቴ ሰው” አድርገው ነበር። ናባል እንደ ስሙ ትርጉም “ሰነፍ” ወይም “ደደብ” ነበር። (1 ሳሙኤል 25:3, 17, 25) ታዲያ ናባል ለአንድ የተቸገረ ሰው ማለትም የይሖዋ ቅቡዕ ለነበረው ለዳዊት ደግነት ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ አግኝቶ በነበረ ጊዜ ምን አደረገ?​—⁠1 ሳሙኤል 16:13

15. ናባል ዳዊትን እንዴት ተቀበለው? በዚህ ረገድ አቢጋኤል ከባሏ የተለየች መሆኗን ያሳየችው እንዴት ነው?

15 ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች የናባል መንጎች ወደሚገኙበት አካባቢ በሚሰፍሩበት ጊዜ ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይጠይቁ መንጎቹን ከሽፍታ ይጠብቁለት ነበር። “ሌሊትና ቀን አጥር ሆነውን ነበር” በማለት አንዱ የናባል አገልጋይ ተናግሯል። ይሁን እንጂ የዳዊት መልእክተኞች ምግብ እንዲሰጣቸው በጠየቁት ጊዜ ናባል ‘ሰድቦ’ አባረራቸው። (1 ሳሙኤል 25:2-16) የናባል ሚስት አቢጋኤል ፈጥና ለዳዊት ምግብ ይዛ ሄደች። ዳዊት በጣም ስለተናደደ ናባልን እና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ለማጥፋት ተነስቶ ነበር። አቢጋኤል በራሷ ተነሳሽነት የወሰደችው እርምጃ የብዙዎች ሕይወት እንዲተርፍ ከማድረጉም በላይ ዳዊትን ከደም ባለዕዳነት አድናዋለች። ይሁን እንጂ ናባል ያሳየው የስግብግብነትና የክፋት ባሕርይ እንዲህ በዋዛ የሚታለፍ አልነበረም። ከአሥር ቀን ገደማ በኋላ “እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው። እርሱም ሞተ።”​—⁠1 ሳሙኤል 25:18-38

16. ቦዔዝን መኮረጅና ከናባል መንገድ መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

16 ቦዔዝ እና ናባል ጨርሶ የተለያዩ ሰዎች ነበሩ! ከናባል መጥፎና የራስ ወዳድነት አካሄድ በመራቅ ደግና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ባሕርይ ያሳየውን የቦዔዝን ምሳሌ እንከተል። (ዕብራውያን 13:16) ጳውሎስ “ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ” በማለት የሰጠውን ምክር ሥራ ላይ በማዋል ይህንን ማድረግ እንችላለን። (ገላትያ 6:10) የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” የሆኑት በዛሬው ጊዜ ያሉት ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ይሖዋ ለቀባቸው በሰማይ የማይሞት ሕይወት ለሚያገኙት ለ144, 000 ቀሪዎች መልካም የማድረግ መብት አላቸው። (ዮሐንስ 10:16፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50-53፤ ራእይ 14:1, 4) ኢየሱስ እነዚህን መልካም ተግባሮች ልክ ለእርሱ እንደተደረጉ አድርጎ የሚመለከታቸው ሲሆን እነዚህ መልካም ተግባሮች የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛሉ።​—⁠ማቴዎስ 25:34-40፤ 1 ዮሐንስ 3:18

ሐና የደረሰባት መከራና ያገኘቻቸው በረከቶች

17. ሐና ምን ፈተና ደረሰባት? ምን ዓይነት አመለካከትስ አንጸባረቀች?

17 ለአምላክ ያደረችውን ሐናንም የይሖዋ በረከት አግኝቷታል። በተራራማው በኤፍሬም አገር ሕልቃና ከተባለ ሌዋዊ ባሏ ጋር ትኖር ነበር። ሕልቃና ሕጉ በሚፈቅደውና በሚደነግገው መሠረት ፍናና የተባለች ሌላ ሚስትም ነበረችው። ሐና መካን የነበረች ሲሆን ይህ ደግሞ ለአንዲት እስራኤላዊት ሴት የሚያሳፍር ነገር ነበር። ፍናና ግን ልጆች ነበሯት። (1 ሳሙኤል 1:1-3፤ 1 ዜና መዋዕል 6:16, 33, 34) ይሁን እንጂ ፍናና ሐናን ከማጽናናት ይልቅ ሐና እስክታለቅስና ምግብ አልበላ እስኪላት ድረስ ፍቅር በጎደለው ድርጊት ታበሳጫት ነበር። ቤተሰቡ ሴሎ ወደሚገኘው የይሖዋ ቤት “በየዓመቱ” በሚሄዱበት ጊዜ ሁሉ ፍናና ከፍተኛ በደል ትፈጽምባት ነበር። (1 ሳሙኤል 1:4-8) በፍናና የጭካኔ ድርጊት ሐና ምንኛ ተፈትናለች! ሆኖም ሐና ፈጽሞ በይሖዋ ላይ አላማረረችም እንዲሁም ከባሏ ጋር ወደ ሴሎ ከመሄድ ይልቅ ቤቷ አልቀረችም። ስለሆነም የይሖዋ በረከት እንደሚያገኛት የተረጋገጠ ነው።

18. ሐና ምን ዓይነት ምሳሌ ትታልናለች?

18 ሐና በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች በተለይ ደግሞ በሌሎች ደግነት የጎደለው አነጋገር ለተጎዱ ሰዎች ግሩም ምሳሌ ትሆናለች። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች በሚደርሱበት ጊዜ ራስን ማግለል መፍትሔ አይሆንም። (ምሳሌ 18:1) ሐና የደረሰባት ፈተና ሰዎች የአምላክን ቃል በሚማሩበትና ሕዝቦቹ ለአምልኮ በሚሰበሰቡበት ቦታ ለመገኘት ያላትን ፍላጎት እንዲቀንስባት አልፈቀደችም። ስለሆነም በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆና ልትቀጥል ችላለች። አንደኛ ሳሙኤል 2:​1-10 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ውብ ጸሎቷን መመልከቱ ጥልቅ መንፈሳዊ አቋም እንደነበራት ለማወቅ ያስችላል። a

19. ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

19 በዛሬው ጊዜ የምንገኝ የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን አምልኳችንን የምናከናውነው በቤተ መቅደስ ውስጥ አይደለም። የሆነ ሆኖ ልክ እንደ ሐና እኛም ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለንን አድናቆት ማሳየት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ በወረዳና በልዩ ስብሰባዎች እንዲሁም በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን በመገኘት ለመንፈሳዊ ሃብት ጥልቅ አድናቆት እንዳለን ልናሳይ እንችላለን። ስለዚህ እነዚህን አጋጣሚዎች “ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው” መብት በሰጠን በይሖዋ እውነተኛ አምልኮ ውስጥ አንዳችን ሌላውን ለማበረታታት እንጠቀምባቸው።​—⁠ሉቃስ 1:74, 75፤ ዕብራውያን 10:24, 25

20, 21. ሐና ላሳየችው ለአምላክ የማደር ባሕርይ የተካሰችው እንዴት ነው?

20 ይሖዋ ሐና ያሳየችውን ለአምላክ የማደር ባሕርይ የተመለከተ ሲሆን ለዚህም በብዙ ክሷታል። በአንድ ወቅት ቤተሰቡ ወደ ሴሎ አድርጎት በነበረው ዓመታዊ ጉዞ ላይ “አቤቱ፣ የሠራዊት ጌታ ሆይ፣ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፣ እኔንም ባትረሳ፣ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፣ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፣ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም” ብላ ከእንባ ጋር በመጸለይ ለአምላክ ተሳለች። (1 ሳሙኤል 1:9-11) አምላክ የሐናን ልመና ሰምቶ ወንድ ልጅ በመስጠት ባርኳታል። ልጁንም ሳሙኤል ብላ ጠራችው። ልጁ ጡት በጣለ ጊዜ በቤተ መቅደሱ ያገለግል ዘንድ ወደ ሴሎ ይዛው ሄደች።​—⁠1 ሳሙኤል 1:20, 24-28

21 ሐና ለአምላክ ፍቅር እንዳላት ያሳየች ሲሆን ከሳሙኤል ጋር በተያያዘም የገባችውን ስእለት ፈጽማለች። የሚወዱት ልጃቸው በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የማገልገል መብት በማግኘቱ እርሷና ሕልቃና ያገኙትን ከፍ ያለ በረከት አስብ! በተመሳሳይም በርካታ ክርስቲያን ወላጆች ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው የሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋዮች፣ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ወይም ይሖዋን በሚያስከብር በሌላ የአገልግሎት መስክ ሲካፈሉ በማየታቸው ደስታና በረከት አግኝተዋል።

ይሖዋን መስማታችሁን ቀጥሉ!

22, 23. (ሀ) የይሖዋን ድምፅ ሁልጊዜ የምንሰማ ከሆነ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? (ለ) በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት የምንመረምረው ምንድን ነው?

22 ይሖዋን ሁልጊዜ የምንሰማ ከሆነ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? አምላክን በሙሉ ነፍሳችን የምንወድና ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን የምንኖር ከሆነ በመንፈሳዊ ባለጠጎች እንሆናለን። መከራ የሚያስከትልብን ቢሆን እንኳ በዚህ መጓዛችንን ከቀጠልን እኛ ከምንገምተው በላይ የይሖዋን ታላላቅ በረከቶች ልናገኝ እንችላለን።​—⁠መዝሙር 37:4፤ ዕብራውያን 6:10

23 የአምላክ ሕዝቦች ወደፊት ብዙ በረከቶች ይጠብቋቸዋል። “እጅግ ብዙ ሰዎች” ይሖዋን በታዛዥነት የሚያዳምጡ በመሆናቸው ‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት አልፈው በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ከሕይወት የሚገኘውን ደስታ ያጣጥማሉ። (ራእይ 7:9-14፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) በዚያ ይሖዋ የሕዝቦቹን ሁሉ መልካም ፍላጎት በሚገባ ያሟላል። (መዝሙር 145:16) ይሁን እንጂ የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እንደሚያሳየው የይሖዋን ድምፅ ሁልጊዜ የሚሰሙ ሁሉ አሁንም ቢሆን ‘ከላይ የሚመጡትን በጎ ስጦታዎችና ፍጹም በረከቶች’ ያገኛሉ።​—⁠ያዕቆብ 1:17

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ሐና የተናገረቻቸው ቃላት ድንግል የነበረችው ማርያም የመሲሑ እናት እንደምትሆን ካወቀች በኋላ ብዙም ሳትቆይ ከተናገረቻቸው ቃላት ጋር በተወሰነ መጠን ተመሳሳይነት አላቸው።​—⁠ሉቃስ 1:46-55

ታስታውሳለህ?

• መለኮታዊ በረከት ማግኘትን በሚመለከት ከእስራኤል ታሪክ ምን እንማራለን?

• ቦዔዝና ናባል የሚለያዩት እንዴት ነው?

• ሐናን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

• የይሖዋን ድምፅ ሁልጊዜ መስማት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሥ ሰሎሞን ታዛዥ ልብ እንዲኖረው ጸልዮአል፤ ይሖዋም ጥበብ በመስጠት ባርኮታል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቦዔዝ ሰዎችን በአክብሮትና በደግነት ይይዝ ነበር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐና በይሖዋ በመታመኗ በብዙ ተባርካለች