በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ አገልግሎት የገጠሙን ያልጠበቅናቸው ነገሮች

በይሖዋ አገልግሎት የገጠሙን ያልጠበቅናቸው ነገሮች

የሕይወት ታሪክ

በይሖዋ አገልግሎት የገጠሙን ያልጠበቅናቸው ነገሮች

ኤሪክ እና ሃዘል ቢቭሪጅ እንደተናገሩት

“የስድስት ወር እስር ፈርጄብሃለሁ።” እነዚህ ቃላት ጆሮዬ ላይ እያቃጨሉእንግሊዝ አገር ማንቸስተር ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው ስትሬንጅዌስ እስር ቤት ተወሰድኩ። ጊዜው ታኅሣሥ 1950 ሲሆን ገና የ19 ዓመት ጎረምሳ ነበርኩ። ለወታደራዊ አገልግሎት እንድመለመል የቀረበልኝን ጥያቄ ባለመቀበሌ ምክንያት በወጣትነቴ ከገጠሙኝ ከባድ ፈተናዎች መካከል ይህ አንዱ ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 10:​3-5

የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንደመሆኔ ከወታደራዊ አገልግሎት ነጻ መሆን ይገባኝ ነበር፤ ሆኖም የብሪታኒያ ሕግ እኛን አገልጋይ አድርጎ አይቀበለንም። ስለዚህ ለእስር ተዳረግሁ። አባቴ ትዝ አለኝ። በተዘዋዋሪ መንገድ የታሰርኩት በእርሱ ምክንያት ነበር።

ምን መሰላችሁ፣ የወኅኒ ቤት ኃላፊ የነበረው አባቴ ጽኑ እምነት ያለውና በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ የዮርክሻየር ሰው ነው። በሠራዊቱ ውስጥም ሆነ በወኅኒ ቤት ኃላፊነት በቆየባቸው ዓመታት ባያቸው ነገሮች የተነሳ ለካቶሊክ እምነት ከፍተኛ ጥላቻ አድሮበት ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘው በ1930ዎቹ መባቻ አካባቢ ቤታችን ሲመጡ ከበር ሊያባርራቸው በወጣበት ጊዜ ነበር። ሲመለስ እነርሱ የሰጡትን አንዳንድ መጽሐፎች ይዞ ተመለሰ! ከጊዜ በኋላ መጽናኛ የተባለውን መጽሔት (አሁን ንቁ! ይባላል) ኮንትራት ገባ። ምሥክሮቹ ኮንትራቱን እንዲያድስ ለማበረታታት ብለው በየዓመቱ እየመጡ ያነጋግሩት ነበር። በ15 ዓመት ዕድሜዬ አካባቢ ከአባቴ ጋር ሌላ ውይይት ሲጀምሩ እኔ የይሖዋ ምሥክሮችን ደግፌ ተከራከርኩ። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመርኩት በዚህ ጊዜ ነበር።

መጋቢት 1949 በ17 ዓመቴ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን ለማሳየት ተጠመቅሁ። በዚያው ዓመት፣ ከጊልያድ ሚስዮናውያን ትምህርት ቤት በቅርብ ከተመረቁት ከጆን እና ከማይክል ቻሩክ ጋር ወደ ናይጄሪያ ከመሄዳቸው በፊት ተገናኘን። የሚስዮናዊነት መንፈሳቸው በእጅጉ ማርኮኝ ነበር። ብቻ አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት በውስጤ ይህን መንፈስ ተክለውብኛል።

መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ እያለሁ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ለመማር የነበረኝ ፍላጎት ጠፋ። ለንደን በሚገኘው ጉምሩክ መሥሪያ ቤት ለመሥራት ከቤት በወጣሁ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ ይህን የመንግሥት ሥራ ካልተውኩ ራሴን ለአምላክ መወሰኔ ትርጉም እንደሚያጣ ተሰማኝ። እዚያ ቢሮ መሥራቴን ሳቆም አብሮኝ ይሠራ የነበረ አንድ ቦርድ የወጣ ወታደር “ሞራል የሚያላሽቀውን” ይህን ሥራ ስለ ለቀቅሁ እንኳን ደስ ያለህ አለኝ።

ይህ ከመሆኑ በፊት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለመሆን ስል ሥራዬን መልቀቅ እንደምፈልግ ለአባቴ መንገሩ ፈተና ሆኖብኝ ነበር። ለእረፍት ቤት ሳለሁ አንድ ቀን ማታ የመጣው ይምጣ ብዬ ለአባቴ ነገርኩት። በንዴት ይጮኽብኛል ብዬ ጠብቄ ነበር። በጣም የሚያስገርመው “የራስህ ጉዳይ። አንድ ችግር ቢያጋጥምህ ግን እኔ አያገባኝም” ሲል መለሰልኝ። ጥር 1, 1950 የጻፍኩት ማስታወሻዬ እንዲህ ይላል:- “ለአባባ ስለ አቅኚነት ነገርኩት። በሰጠኝ ምክንያታዊ የሆነ ምላሽ በጣም ነበር የተገረምኩት። በደግነት ሲመልስልኝ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም።” ሥራውን በገዛ ፈቃዴ ለቅቄ የሙሉ ጊዜ አቅኚ በመሆን የአገልግሎት ምድብ ተቀበልኩ።

በደሳሳ “ጎጆ” እየኖሩ ማገልገል

ለአምላክ ያለኝ ፍቅር ፈተና ላይ የወደቀው በዚህ ጊዜ ነበር። ከዌልስ ከመጣ ሎይድ ግሪፍትዝ ከሚባል ወንድም ጋር በላንክሻየር በአንዲት ደሳሳ “ጎጆ” ውስጥ እየኖርን በአቅኚነት እንድናገለግል ተመደብን። ጎጆዋ ምን ልትመስል እንደምትችል በሐሳቤ እያወጣሁ እያወረድኩ ባከፕ ከተማ ደረስኩ። ዝናቡ ዙሪያውን ጭፍግግ አድርጎ ይዞ ይጥል ነበር። ጎጆ የተባለው ምድር ቤት መሆኑን ስረዳ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚጠብቀኝ ተገነዘብኩ! ሌሊት ሌሊት አይጦችና በረሮዎች ሲፈነጩብን ያድራሉ። ሁሉን እርግፍ አድርጌ ወደ ቤቴ ለመመለስ ዳድቶኝ ነበር። እንዲህ ከማድረግ ፋንታ ፈተናውን የምቋቋምበትን ብርታት እንዳገኝ ስል በልቤ ጸለይኩ። ወዲያው ከውስጥ ደስታ የተሰማኝ ሲሆን ያለሁበትን ሁኔታ በአዎንታዊ ጎኑ መመልከት ጀመርኩ። እዚህ የመደበኝ የይሖዋ ድርጅት ነው። ይሖዋ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግልኝ እተማመናለሁ። ችግሩን ተቋቁሜ በመጽናቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ፤ አቋርጬ ተመልሼ ቢሆን ኖሮ ሕይወቴ ለዘላለም ይለወጥ ነበር!​—⁠ኢሳይያስ 26:​3, 4

በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኔ ምክንያት ከመታሰሬ በፊት የኤኮኖሚ ውድቀት አጋጥሟት በነበረው ሮዜንዳል የምትባል ሸለቋማ ክልል ዘጠኝ ወር ያህል አገልግያለሁ። በስትሬንጅዌስ እስር ቤት ሁለት ሳምንታት ከቆየሁ በኋላ በእንግሊዝ ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ ወደሚገኘው ሉዊስ እስር ቤት ተዛወርኩ። ቀስ በቀስ እዚያ የታሰርነው ምሥክሮች ቁጥር አምስት በመድረሱ አንድ ክፍል ውስጥ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በዓል አከበርን።

አባባ አንድ ጊዜ መጥቶ ጠይቆኛል። ብዙ ሰዎች የሚያውቁት የወኅኒ ቤት ኃላፊ ስለነበር እኔን መጥቶ መጠየቁ ፈተና ሳይሆንበት አልቀረም! መጥቶ ስለጠየቀኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። በመጨረሻ ሚያዝያ 1951 ከእስር ተፈታሁ።

ከሉዊስ እስር ቤት ከተፈታሁ በኋላ አባቴ ዋና ኃላፊ ሆኖ የሚሠራበት እስር ቤት ወደሚገኝበት ወደ ካርዲፍ ዌልስ በባቡር ሄድኩ። ከሦስት ወንዶችና ከአንዲት ሴት መካከል እኔ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ። ራሴን እየረዳሁ አቅኚነቴን መቀጠል እንድችል የግማሽ ቀን ሥራ ማግኘት ነበረብኝ። በልብስ መሸጫ መደብር ውስጥ ተቀጥሬ መሥራት የጀመርኩ ቢሆንም በሕይወቴ ውስጥ የመጀመሪያው ዓላማዬ ክርስቲያናዊ አገልግሎቴ ነበር። እናታችን ጥላን የሄደችው በዚህ ጊዜ ነበር። ይህ ለአባታችንም ሆነ ከ8 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ለምንደርሰው ልጆች በጣም ከባድ ነበር። የሚያሳዝነው ከቤት የወጣችው ተፋትታ ነበር።

ጥሩ ሚስት ያገኘ...

በጉባኤያችን ውስጥ በርከት ያሉ አቅኚዎች ነበሩ። ከእነርሱ መካከል ለሥራና በስብከቱ እንቅስቃሴ ለመካፈል የድንጋይ ከሰል ከሚመረትበት ከሮንዳ ሸለቆ በየዕለቱ የምትመላለስ አንዲት እህት ነበረች። ስሟ ሃዘል ግሪን የሚባል ሲሆን በጣም ጎበዝ አቅኚ ነበረች። የሃዘል ወላጆች ከ1920ዎቹ ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (አሁን የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው ይጠራሉ) በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ይገኙ ስለነበር ሃዘል እውነትን የሰማችው ከእኔ ቀደም ብላ ነበር። እስቲ ታሪኳን ራሷ ትንገራችሁ።

“ሪሊጅን ሪፕስ ዘ ወርልዊንድ የተባለውን ቡክሌት እስካነበብኩበት እስከ 1944 ድረስ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በቁም ነገር አስቤ አላውቅም ነበር። እናቴ ካርዲፍ በሚደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጎተጎተችኝ። ምንም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ሳይኖረኝ የሕዝብ ንግግሩን ርዕስ የያዘ ከፊትና ከኋላ የሚነበብ ማስታወቂያ አንግቼ በከተማው እምብርት መዞር ጀመርኩ። ቀሳውስቱና ሌሎች ሰዎች ችግር ቢፈጥሩብንም ምንም ሳይመስለኝ ተመለስኩ። በ1946 ተጠመቅሁና በዚያው ዓመት በታኅሣሥ ወር አቅኚነት ጀመርኩ። ከዚያም በ1951 በዕድሜ ወጣት የሆነ አንድ አቅኚ ከወኅኒ ቤት ተለቅቆ ወደ ካርዲፍ መጣ። እሱም ኤሪክ ነበር።

“አብረን ለስብከት መሄድ ጀመርን። ቀስ በቀስ ተግባባን። ሁለታችንም በሕይወታችን ውስጥ የመንግሥቱን ፍላጎቶች የማስቀደም ግብ ስለነበረን በታኅሣሥ 1952 ተጋባን። ሁለታችንም በሙሉ ጊዜ የአቅኚነት አገልግሎት የተሰማራንና የነበረን ገቢም አነስተኛ ቢሆንም መሠረታዊ ነገሮችን አጥተን አናውቅም። አንዳንድ ጊዜ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ያላት አንዲት የይሖዋ ምሥክር በብዛት ከምታስገባው ማርመላታና ሳሙና ላይ እንዳጋጣሚ ሆኖ ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ትሰጠን ነበር! በአስፈላጊው ጊዜ ለምናገኘው እነዚህን ለመሰሉ ስጦታዎች በጣም አመስጋኞች ነን። ሆኖም እናገኛቸዋለን ብለን ያላሰብናቸው በረከቶች ከፊታችን ይጠብቁን ነበር።”

ሕይወታችንን የለወጠ ያልጠበቅነው ነገር

እኔና ሃዘል ኅዳር 1954 ጨርሶ ያልጠበቅነው ነገር ደረሰን። በየሳምንቱ የተለያዩ ጉባኤዎችን በመጎብኘት ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንድሆን ለንደን የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የማመልከቻ ቅጽ ላከልን። በስህተት የተላከ ሊሆን ይችላል ብለን ስላሰብን ጉባኤ ውስጥ ለአንድም ሰው አልተናገርንም። ይሁን እንጂ ቅጹን ሞልቼ ላክሁትና መልሱን በጉጉት መጠበቅ ጀመርን። ከጥቂት ቀናት በኋላ “ለሥልጠና ወደ ለንደን እንድትመጣ” የሚል መልስ መጣ!

በ23 ዓመቴ ለንደን በሚገኘው ቢሮ እንደ ፕራይስ ሂዩዝ፣ ኤምለን ዊንስ፣ ኧርኒ ቢቨር፣ ኧርኒ ጊቨር፣ ቦብ ጋው፣ ግሊን ፓር፣ ስታን እና ማርቲን ዉድበርን ካሉትና ከሌሎችም በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንድሞች መካከል መገኘቴን ሳስበው በጣም ይገርመኛል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በሕይወት የሉም። እነዚህ ወንድሞች በ1940ዎቹና 1950ዎቹ በብሪታንያ ውስጥ ቅንዓት በማሳየትና ንጹሕ አቋም በመጠበቅ ረገድ ጽኑ መሠረት ጥለዋል።

የወረዳ ሥራ በእንግሊዝ ውስጥ ፈጽሞ አይሰለችም

የተጓዥ የበላይ ተመልካችነትን ሥራ አንድ ብለን የጀመርነው በ1954/55 በበረዶ ወራት ነበር። ከሰሜን ባሕር ለሚነፍሰው ቀዝቃዛ ነፋስ በተጋለጠው የእንግሊዝ ሜዳማ ክልል በኢስት አንግሊያ ተመደብን። በወቅቱ በእንግሊዝ ውስጥ 31, 000 የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነበሩ። ይህ መጀመሪያ የሠራንበት ወረዳ በጣም ብዙ ችግሮችን ያሳለፍንበት ነበር። ገና ብዙ ተሞክሮ ስላልነበረኝና የዮርክሻየር ሰዎች ባለን ግልጹን የመናገር ባሕርይ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ወንድሞችን ስለማስቀይም ለእነርሱም ቢሆን ቀላል አልሆነላቸውም። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ከተቀላጠፈ አሠራር ይልቅ ደግነት ከአሠራር ደንብ ይልቅ የሰዎችን ስብዕና ማስበለጥን ተምሬአለሁ። አሁን ሙሉ በሙሉ ተሳክቶልኛል ማለት ባልችልም ኢየሱስ ለሌሎች እረፍት በመስጠት የተወውን ምሳሌ ለመኮረጅ ጥረት እያደረግሁ ነው።​—⁠ማቴዎስ 11:​28-30

በኢስት አንግሊያ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ከቆየን በኋላ በሰሜን ምሥራቅ እንግሊዝ በሚገኘው ወረዳ ማለትም በኒውካስል አፖን ታይን እና በኖርዘምበራንድ እንድናገለግል ተመደብን። ደጎች የሆኑትን የዚያ ውብ አካባቢ ሰዎች እወዳቸዋለሁ። ከሲያትል ዋሽንግተን ዩ ኤስ ኤ ሊጎበኘን የመጣ ዶን ዋርድ የሚባል የአውራጃ የበላይ ተመልካች በእጅጉ ጠቅሞኛል። ይህ ወንድም የጊልያድ ትምህርት ቤት 20ኛ ክፍል ተመራቂ ነበር። ንግግር ሳቀርብ ፍጥነቴ ለመከታተል የሚያስቸግር ነበር። ይህ ወንድም ግን ፍጥነቴን እንድቀንስ፣ ቆም እያልኩ እንድናገርና እንዳስተምር ረድቶኛል።

ሕይወታችንን የለወጠ ሌላ ያልተጠበቀ ነገር

በ1958 ሕይወታችንን የለወጠ አንድ ደብዳቤ ደረሰን። ዩ ኤስ ኤ ውስጥ ኒው ዮርክ፣ ሳውዝ ላንሲንግ በሚገኘው ጊልያድ ትምህርት ቤት ገብተን እንድንማር ተጋበዝን። ትንሿን የ1935 አውስቲን ሰቨን መኪናችንን ሸጥንና በመርከብ ወደ ኒው ዮርክ ለመሄድ ትኬት ገዛን። በመጀመሪያ በኒው ዮርክ ከተማ በሚደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘን። ከዚያም በስተ ደቡብ አቅጣጫ ወደሚገኘው ጊልያድ ትምህርት ቤት ከማቅናታችን በፊት ለስድስት ወራት ያህል በአቅኚነት ለመሥራት ወደ ፒተርቦሮ፣ ኦንታሪዮ ሄድን።

ከትምህርት ቤቱ መምህራን መካከል አሁን የአስተዳደር አካል አባል የሆነው አልበርት ሽሮደር እንዲሁም ማክስዌል ፍሬንድና አሁን በሕይወት የሌለው ጃክ ሬድፎርድ ይገኙበታል። ከ14 አገሮች ከመጡት 82 ተማሪዎች ጋር ያለን ቅርርብ በጣም የሚያንጽ ነበር። በመጠኑም ቢሆን አንዳችን የሌላውን ባህል ማወቅ ችለናል። እንግሊዝኛ ለመናገር ጥረት ከሚያደርጉ ተማሪዎች ጋር ያሳለፍነው ጊዜ እኛም ወደፊት አዲስ ቋንቋ ስንማር ምን ችግር እንደሚገጥመን የሚጠቁም ነበር። ስልጠናውን በአምስት ወራት ውስጥ አጠናቅቀን ወደ 27 አገሮች ተመደብን። ከዚያም የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተደረገና ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ አውሮፓ የምትመልሰንን ክዊን ኤሊዛቤት የምትባል መርከብ ለመጠበቅ ወደ ኒው ዮርክ ከተማ ሄድን።

የመጀመሪያው የባዕድ አገር ምድባችን

የት እንመደብ ይሆን? ፖርቱጋል! ኅዳር 1959 ሊዝበን ደረስን። ከአዲስ ቋንቋና ከአዲስ ባህል ጋር መላመድ መቻላችን የተፈተነው በዚህ ጊዜ ነበር። በ1959 ወደ 9 ሚልዮን ከሚጠጋው ሕዝብ መካከል 643 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ሆኖም የስብከቱ ሥራችን ሕጋዊ እውቅና አላገኘም ነበር። የመንግሥት አዳራሾች ቢኖሩንም እንኳ ከውጪ የሚታይ ምልክት አልነበራቸውም።

ኤልሳ ፒኮኔ የተባለች ሚስዮናዊት እህት የፖርቱጋል ቋንቋ ካስተማረችን በኋላ እኔና ሃዘል በሊዝቦን ዙሪያ ፋሮ፣ ኢቮራ እና ቤጃ በሚባሉ ከተማዎች የሚገኙ ጉባኤዎችንና ቡድኖችን መጎብኘት ጀመርን። ከዚያም በ1961 ሁኔታው መለወጥ ጀመረ። ጆዋ ጎንሳልቪሽ ማቲያስ የሚባል አንድ ወጣት መጽሐፍ ቅዱስ አስጠና ነበር። ወታደራዊ አገልግሎት የመስጠት ጉዳይ ሲነሳ እንደ አንድ ገለልተኛ ክርስቲያን የራሱን አቋም ለመውሰድ ወሰነ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለምርመራ እንደምፈለግ ተነገረኝ። ሌላ ያልጠበቅሁት ነገር! ከጥቂት ቀናት በኋላ በ30 ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀን እንድንወጣ ማሳሰቢያ ተሰጠን! ሌሎች ሚስዮናውያን ጓደኞቻችን ኤሪክ እና ክሪስቲና ብሪተን እንዲሁም ዶሜኒክ እና ኤልሳ ፒኮንም ተመሳሳይ ማሳሰቢያ ደረሳቸው።

ጉዳያችን እንደገና እንዲታይልን ጥያቄ አቀረብኩና የምስጢር ፖሊስ አዛዡን እንድናነጋግር ተፈቀደልን። እንድንወጣ የተጠየቅንበትን ምክንያት በማያዳግም ሁኔታ ከነገረን በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዬን የጆዋ ጎንሳልቪሽ ማቲያስን ስም ጠቀሰልን! ፖርቱጋል እንደ እንግሊዝ በሕሊና ምክንያት አንዋጋም የሚለውን አስተሳሰብ እንደማታስተናግድ ነገረን። ስለሆነም ፖርቱጋልን ለቅቀን መውጣት የተገደድን ሲሆን ከጆዋን ጋርም ተጠፋፋን። ከ26 ዓመታት በኋላ አዲሱ የፖርቱጋል ቤቴል ሲወሰን ጆዋንን ከባለቤቱና ከሦስት ልጆቹ ጋር ማየት መቻላችን ምንኛ የሚያስደስት ነበር! በፖርቱጋል ያከናወንነው አገልግሎት ከንቱ ሆኖ አልቀረም!​—⁠1 ቆሮንቶስ 3:​6-9

ቀጣዩ ምድባችን ደግሞ የት ይሆን? የሚያስገርም ነው! ጎረቤት አገር ስፔይን ተመደብን። የካቲት 1962 እያለቀስን ከሊዝበን ተነስተን በባቡር ወደ ማድሪድ ተጓዝን።

ከሌላ ባህል ጋር መላመድ

በስፔይን የስብከቱንም ሥራ ሆነ ስብሰባዎቻችንን በድብቅ ማከናወን መልመድ ነበረብን። ስንሰብክ ብዙውን ጊዜ ሁለት ቤቶችን በተከታታይ አናንኳኳም። አንድ ቤት ከመሰከርን በኋላ ቀጥለን በሌላ ጎዳና ላይ ወደሚገኝ ሌላ ቤት እንሄዳለን። እንዲህ ማድረጋችን ፖሊስ ወይም ቄሶች እንዳይዙን ይረዳናል። ፋሺስታዊ አገዛዝ በነገሠበት፣ የካቶሊክ ሃይማኖት አምባገነን በሆነበትና የስብከት ሥራችን በታገደበት አገር እንዳለን መዘንጋት የለበትም። የውጭ አገር ሰዎች መሆናችን እንዳይታወቅ በዚያ አገር ስም እንጠራ ነበር። እኔ ፓብሎ ስባል ሃዘል ደግሞ ጁዋና ትባል ነበር።

ማድሪድ ውስጥ ጥቂት ወራት ከቆየን በኋላ ለወረዳ ሥራ ባርሴሎና ተመደብን። በአንድ ጉባኤ ውስጥ ለሁለትና ሦስት ሳምንት እየቆየን በከተማው ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ጉባኤዎችን እንጎበኝ ነበር። ጉብኝቱ ያን ያህል ጊዜ የሚወስደው እያንዳንዱን የመጽሐፍ ጥናት ቡድን የአንድ ጉባኤ ያህል እንጎበኝ ስለነበረ ነው። ይህ ማለት ሁለት ቡድኖች በአንድ ሳምንት ይጎበኛሉ ማለት ነው።

ያልተጠበቀ ፈተና

በ1963 ስፔይን ውስጥ የአውራጃ ሥራ እንድንጀምር ተጋበዝን። 3, 000 የሚያክሉ የይሖዋ ምሥክሮችን ለማዳረስ በወቅቱ በአገሪቱ የሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎችን መጎብኘት ነበረብን። በሰቪሌ ጫካ፣ ኬኮን በምትባል ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ እርሻ እንዲሁም በማድሪድ፣ በባርሴሎና እና ሎግሮኖ አቅራቢያ በሚገኙ ወንዞች ዳርቻ ላይ ፈጽሞ የማይረሱ የወረዳ ስብሰባዎችን በድብቅ አድርገን ነበር።

ከቤት ወደ ቤት ስንሰብክ አንድ ችግር ቢፈጠር ማምለጥ እንድንችል በዚያ አካባቢ ያሉ መንገዶችን ቅያስ አስቀድሜ አጣራ ነበር። አንድ ቀን ማድሪድ ውስጥ እየሰበክን እያለን እኔና አንድ ሌላ ምሥክር ላይኛው ፎቅ ስንደርስ ድንገት ከታች ጩኸትና ጫጫታ ሰማን። ከፎቁ ወርደን ታች ስንደርስ ሂካስ ዲ ማሪያ (የእመቤታችን ሴት ልጆች) የሚባል አንድ የካቶሊክ ቡድን አባላት የሆኑ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጃገረዶች ነበሩ። የዚያ አካባቢ ሰዎች እኛን እንዳይሰሙ እያስጠነቀቁ ነበር። ፖሊስ እንዳይዘን ከፈለግን አካባቢውን በፍጥነት መልቀቅ እንዳለብን ስላወቅን ከእነርሱ ጋር እሰጥ አገባ አልገጠምንም። ከዚህ ይልቅ ከአካባቢው በፍጥነት ተሰወርን!

በስፔይን ያሳለፍናቸው እነዚህ ዓመታት በጣም አስደሳች ነበሩ። ልዩ አቅኚዎችን ጨምሮ እዚያ ያሉ ግሩም ወንድሞችንና እህቶችን ለማበረታታትና ለማነጽ ጥረናል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ፣ ጉባኤዎችን ለማቋቋምና ለማነጽ ሲሉ ራሳቸውን ለእስራት ከማጋለጣቸውም በላይ ረሃቡንና እርዛቱን ችለው ኖረዋል።

በዚህ ጊዜ ውስጥ አንዳንድ አሳዛኝ ዜናዎችም ደርሰውናል። ሃዘል እንዲህ ስትል ትገልጻለች:- “በ1964 ታማኝ የይሖዋ ምሥክር የነበረችው እናቴ ሞተች። ለመጨረሻ ጊዜ እንኳ ዓይኗን ሳላያት እሷን ማጣቴ ከባድ ሐዘን ፈጥሮብኛል። ሌሎች ሚስዮናውያንም በዚህ ሥራ ላይ ሲካፈሉ ከሚከፍሏቸው መሥዋዕትነቶች አንዱ ይህ ነው።”

በመጨረሻ ነፃነት ተገኘ

ከብዙ ዓመታት ስደት በኋላ ሐምሌ 1970 የፍራንኮ መንግሥት ለሥራችን ሕጋዊ እውቅና ሰጠን። እኔና ሃዘል የመጀመሪያው በማድሪድ ሁለተኛው ደግሞ ሌሴፕስ ባርሴሎና ውስጥ የመንግሥት አዳራሾች ሲከፈቱ በማየታችን በጣም ተደስተን ነበር። የመንግሥት አዳራሾቻችን ብዙውን ጊዜ ደመቅ ብለው የሚታዩ ትላልቅ ምልክቶች አላቸው። ሰዎች ሕጋዊ እውቅና ማግኘታችንንና አሁንም በስፔይን ውስጥ እንዳለን እንዲያውቁ እንፈልግ ነበር! በዚያ ወቅት በ1972 በስፔይን 17, 000 የሚያክሉ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ።

በዚያን ጊዜ ገደማ ከእንግሊዝ አንድ በጣም የሚያበረታታ የምሥራች ሰማሁ። አባቴ በ1969 ስፔይን ድረስ መጥቶ ጠይቆን ነበር። የስፔይን የይሖዋ ምሥክሮች ባደረጉለት አቀባበል በጣም በመደሰቱ ወደ እንግሊዝ ከተመለሰ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ከዚያም አባባ መጠመቁን በ1971 ሰማሁ! እቤት ሄደን በጠየቅናቸው ጊዜ እንደ አንድ ክርስቲያን ወንድም በቀረበው ምግብ ላይ ሲጸልይ ስመለከት ደስታዬ ወሰን አልነበረውም። ይቺን ቀን ለማየት ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ጠብቄአለሁ። ወንድሜ ቦብ እና ባለቤቱ አይሪስ በ1958 የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ወንድ ልጃቸው ፊሊፕ ከባለቤቱ ከጄን ጋር በስፔይን በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እያገለገለ ነው። በዚያች አስደሳች አገር ውስጥ ሲያገለግል ማየታችን እኛንም አስደስቶናል።

በቅርቡ ያገኘነው ያልተጠበቀ በረከት

በየካቲት 1980 አንድ የአስተዳደር አካል አባል በዞን የበላይ ተመልካችነት ስፔይንን ጎብኝቶ ነበር። አብሮኝ ማገልገል እንደሚፈልግ ሲነግረኝ በጣም ተገረምኩ። እየገመገመኝ እንደሆነ አላወቅሁም ነበር! ከዚያም መስከረም ውስጥ ብሩክሊን ኒው ዮርክ ወደሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት እንድንዛወር ተጋበዝን! በሁኔታው በጣም ተደነቅን። ምንም እንኳ የስፔይን ወንድሞቻችንን ትቶ መሄድ የሚያሳዝን ቢሆንም ግብዣውን ተቀበልን። በወቅቱ ስፔይን ውስጥ 48, 000 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ!

ከስፔይን ስንቀየር አንድ ወንድም አንድ የኪስ ሰዓት በስጦታ አበረከተልኝ። በሰዓቱ ላይ ሁለት ጥቅሶችን ይኸውም “ሉቃስ 16:​10፤ ሉቃስ 17:​10” ቀርጾበታል። እሱ እንደተናገረው ከሆነ እነዚህን ጥቅሶች አዘውትሬ እጠቅሳቸዋለሁ። ሉቃስ 16:​10 በጥቃቅን ጉዳዮችም ታማኞች መሆን እንደሚገባን የሚያሳስብ ሲሆን ሉቃስ 17:​10 ደግሞ “የማንጠቅም ባሪያዎች” ስለሆንን የምንኩራራበት ምክንያት እንደሌለ ይናገራል። በይሖዋ አገልግሎት ምንም እንሥራ ምን ራሳችንን የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ልንሠራው የሚገባንን እንደሠራን እገነዘባለሁ።

ያልተጠበቀ የጤና መታወክ

በ1990 የልብ ሕመም ጀመረኝ። ከጊዜ በኋላ ያጋጠመኝን የደም ሥር መጥበብ ለማሻሻል ስቴንት የተባለ መሣሪያ መጠቀም ነበረብኝ። የአቅም ማነስ ባጋጠመኝ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላይ ሃዘል መያዝ ያቃተኝን ቦርሳና ሻንጣ በመሸከም እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ትደግፈኝ ነበር። ከዚያም ግንቦት 2000 የልብ ምቴን የሚያግዝ መሣሪያ ተተከለልኝ። በጣም ትልቅ እርዳታ አበርክቶልኛል!

ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ እኔና ሃዘል የይሖዋ እጅ አጭር እንዳልሆነና እኛ ባሰብነው ጊዜ ሳይሆን እሱ በወሰነው ጊዜ ዓላማውን እንደሚያስፈጽም ለመመልከት ችለናል። (ኢሳይያስ 59:​1፤ ዕንባቆም 2:​3) በሕይወታችን ውስጥ ብዙ አስደሳች ገጠመኞችና ጥቂት አሳዛኝ ሁኔታዎች ያሳለፍን ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ የይሖዋ ድጋፍ ተለይቶን አያውቅም። አሁን ባለንበት የይሖዋ ሕዝቦች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ከአስተዳደር አካል አባላት ጋር በየዕለቱ መገናኘት በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነን። አንዳንድ ጊዜ ‘በእርግጥ የት ነው ያለሁት?’ እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። ይገባናል የማንለውን ቸርነት አግኝተናል። (2 ቆሮንቶስ 12:​9) ይሖዋ ከሰይጣን መሠሪ ዘዴዎች እንደሚጠብቀንና ጽድቅ ለሚሰፍንበት ምድራዊ አገዛዙ እንደሚ​ያበቃን እንተማመናለን።​—⁠ኤፌሶን 6:​11-18፤ ራእይ 21:​1-4

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመጀመሪያ ጊዜ ተፈርዶብኝ የታሰርኩበት ማንቸስተር የሚገኘው ስትሬንግዌስ ወኅኒ ቤት

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንግሊዝ ውስጥ በአውስቲን ሰቨን መኪናችን በወረዳ ሥራ ላይ እያለን

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1962 ስፔይን፣ ማድሪድ፣ ቴርሲዲልያ ውስጥ በድብቅ ያደረግነው የወረዳ ስብሰባ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብሩክሊን ውስጥ ጽሑፍ በምናሰራጭበት ጠረጴዛ አጠገብ