ታማኝ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?
ታማኝ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?
በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ጀምሮ የኖሩት ሃሲዲም የተባለ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት ራሳቸውን ፍጹም ታማኝ አድርገው ይቆጥሩ ነበር። ስማቸውን ያገኙት “ታማኝ” የሚል ትርጉም ካለው ሃሲድ ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ነው። ይህ ቃል ብዙውን ጊዜ “ፍቅራዊ ደግነት፣” “ታማኝ ፍቅር፣” “ቸርነት፣” “በጎነት፣” “ምሕረት” ተብሎ ከሚተረጎመው ሄሴድ ከሚለው ስም የተገኘ ነው። ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት በሰጠው ፍቺ መሠረት ሄሴድ “ሕያው፣ ማኅበራዊና ጽኑ ከመሆኑም በላይ የስብዕና መገለጫ ባሕርይ ብቻ ሳይሆን ይህን ባሕርይ የሚያንጸባርቅ ተግባርንም ይጨምራል። ሕይወትን ለመታደግ ወይም ለማበልጸግ የሚወሰድ እርምጃ ነው። ችግር ወይም መከራ የደረሰበትን ሰው መርዳትን የሚያመለክት ሲሆን የወዳጅነት መገለጫም ነው።”
በብዙ ቋንቋዎች ይህ የዕብራይስጥ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተሠራበት መሠረት ሙሉ ትርጉሙን የሚያስተላልፍ ቃል ማግኘት እንደማይቻል ግልጽ ነው። ያም ሆነ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ታማኝነት ማለት የገቡትን ቃል በታማኝነት መጠበቅ ማለት ብቻ አይደለም። ሌሎችን ለመጥቀም ሲባል የሚወሰድ አዎንታዊ እርምጃን የሚጨምር ፍቅራዊ ትስስር ነው። እውነተኛ ታማኝነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት እንድትችል ይሖዋ ይህን ባሕርይ ለአብርሃም፣ ለሙሴ፣ ለዳዊት፣ ለእስራኤል ብሔር እንዲሁም ለሰው ዘር ባጠቃላይ እንዴት እንዳሳየ ተመልከት።
ይሖዋ ታማኝነት አሳይቷል
ይሖዋ ወዳጁን አብርሃምን “እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 15:1፤ ኢሳይያስ 41:8) ይሖዋ ይህን ተናግሮ ብቻ ዝም አላለም። አብርሃምንም ሆነ ቤተሰቡን ከፈርኦንና ከአቤሜሌክ ጥቃት ጠብቋቸዋል እንዲሁም አድኗቸዋል። ግንባር ፈጥረው ከመጡበት አራት ነገሥታት ሎጥን እንዲያስጥል ረድቶታል። ተስፋ የተሰጠበት ዘር በእነርሱ የዘር ሐረግ በኩል መምጣት እንዲችል ይሖዋ የ100 ዓመቱን አብርሃምንና የ90 ዓመቷን ሣራን ልጅ የመውለድ ችሎታ አድሶላቸዋል። ይሖዋ ከአብርሃም ጋር በራእይ፣ በሕልምና በመላእክት አማካኝነት ዘወትር የሐሳብ ግንኙነት ያደርግ ነበር። እንዲያውም ይሖዋ አብርሃም በሕይወት በነበረበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከሞተ ከብዙ ዓመታት በኋላም ታማኝነትን አሳይቶታል። የአብርሃም ዘር የሆኑት እስራኤላውያን አስቸጋሪዎች የነበሩ ቢሆኑም ይሖዋ የገባላቸውን ቃል ለብዙ መቶ ዓመታት ጠብቋል። ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የነበረው ግንኙነት ፍቅር በተግባር ሲገለጽ የሚያሳይ የእውነተኛ ታማኝነት ግሩም ምሳሌ ነው።—ዘፍጥረት ከምዕራፍ 12 እስከ 25
“እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር” ተብሏል። (ዘጸአት 33:11 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አዎን፣ ሙሴ ከኢየሱስ ክርስቶስ በፊት ከተነሳ ከማንኛውም ነቢይ ይልቅ ከይሖዋ ጋር የቀረበ ወዳጅነት ነበረው። ይሖዋ ለሙሴ ታማኝነት ያሳየው እንዴት ነው?
ሙሴ አካላዊ ጥንካሬና ችሎታ የነበረው የ40 ዓመት ሰው ሳለ ያለ ሥራ 7:23-30) ይሁን እንጂ ይሖዋ አልረሳውም። እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ሲደርስ ሙሴ እስራኤልን ከግብፅ መርቶ ለማውጣት እንዲመለስ ተደረገ።
ማንም እርዳታ ሕዝቡን ከባርነት ነፃ ለማውጣት ተነሳ። ሆኖም እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ስላልደረሰ ሕይወቱን ለማዳን መሸሽ ግድ ሆነበት። ለ40 ዓመታት በምድያም በግ ጠባቂ ሆነ። (በተመሳሳይም ይሖዋ ታዋቂ ለነበረው የእስራኤል ሁለተኛ ንጉሥ ለዳዊት ታማኝነት አሳይቷል። ዳዊት ገና ወጣት ሳለ ይሖዋ ነቢዩ ሳሙኤልን “ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው” ብሎት ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዳዊት የመላው እስራኤል ንጉሥ ለመሆን የሚያበቃውን ጉልምስና እንዲያገኝ በመርዳት ይሖዋ በታማኝነት ጠብቆታል እንዲሁም መርቶታል። ይሖዋ “ከአንበሳና ከድብ እጅ” እንዲሁም ግዙፍ ከነበረው ፍልስጥኤማዊ ከጎልያድ እጅ ታድጎታል። በእስራኤል ጠላቶች ላይ ተደጋጋሚ ድል ያቀዳጀው ሲሆን ጥላቻ የተሞላውና ቅናት ያበገነው ሳኦል ከወረወረበት ጦር አድኖታል።—1 ሳሙኤል 16:12፤ 17:37፤ 18:11፤ 19:10
እርግጥ ነው፣ ዳዊት ፍጹም ሰው ነበር ማለት አይደለም። እንዲያውም ከባድ ኃጢአቶችን ሠርቷል። ይሁን እንጂ አይረባም ብሎ ከመተው ይልቅ ይሖዋ ከልብ ንስሃ ለገባው ለዳዊት ታማኝ ፍቅር አሳይቶታል። በዳዊት የሕይወት ዘመን ሁሉ ይሖዋ የዳዊትን ሕይወት ለመጠበቅና ለማበልጸግ ሲል ብዙ ነገር አድርጓል። መከራ ውስጥ ለወደቁ ሰዎች ማልዷል። እውነትም እንዴት ያለ ፍቅራዊ ደግነት ነው!—2 ሳሙኤል 11:1–12:25፤ 24:1-17
መላው የእስራኤል ሕዝብ በሲና ተራራ ላይ የተሰጣቸውን የሙሴ ሕግ ለመጠበቅ በተስማሙ ጊዜ ከይሖዋ ጋር ልዩ ወዳጅነት መሥርተዋል። (ዘጸአት 19:3-8) ከዚህ የተነሳ እስራኤላውያን ከይሖዋ ጋር በጋብቻ እንደተሳሰሩ ሆነው ተገልጸዋል። እስራኤል ‘እግዚአብሔር እንደ ሚስት ጠርቶሻል’ ተብሎላታል። እንዲሁም ይሖዋ “በዘላለምም ቸርነት እምርሻለሁ” ብሏታል። (ኢሳይያስ 54:6, 8) ይሖዋ እንዲህ ባለው ልዩ ወዳጅነት ረገድ ታማኝነት ያሳየው እንዴት ነበር?
ይሖዋ የእስራኤላውያንን ፍላጎት ለማሟላትና ከእርሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማጥበቅ ቀዳሚ በመሆን እርምጃዎችን ወስዷል። ከግብፃውያን እጅ አድኗቸዋል፣ በብሔር አደራጅቷቸዋል እንዲሁም “ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር” አግብቷቸዋል። (ዘጸአት 3:8) በካህናት፣ በሌዋውያንና በየጊዜው በሚያስነሳቸው ነቢያትና መልእክተኞች አማካኝነት ዘወትር መንፈሳዊ መመሪያ ይሰጣቸው ነበር። (2 ዜና መዋዕል 17:7-9፤ ነህምያ 8:7-9፤ ኤርምያስ 7:25) ሕዝቡ ሌሎች አማልክት ወደ ማምለክ ዞር ሲሉ ይሖዋ ይገሥጻቸው ነበር። ንስሃ ሲገቡ ይቅር ይላቸዋል። እስራኤል አስቸጋሪ “ሚስት” እንደነበረች አሌ አይባልም። ሆኖም ይሖዋ ቸኩሎ አልተዋትም። ለአብርሃም የገባውን ቃል ለመጠበቅ ሲል ከእነርሱ ጋር የተያያዘውን ዓላማ ከዳር እስኪያደርስ ድረስ ታማኝነት አሳይቷቸዋል። (ዘዳግም 7:7-9) በትዳር ለተሳሰሩ ሰዎች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል!
ይሖዋ ጻድቅ ኃጢአተኛ ሳይል የሰዎችን መሠረታዊ ፍላጎት በማሟላት ረገድ ለሰው ዘር ባጠቃላይ ታማኝነትን አሳይቷል። (ማቴዎስ 5:45፤ ሥራ 17:25) በተጨማሪም መላው የሰው ዘር ከኃጢአትና ከሞት ነፃ በመውጣት በገነት ውስጥ ፍጹም ዘላለማዊ ሕይወት የማግኘት ክብራማ ተስፋ እንዲኖረው ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) ቤዛው ሕይወትን ለመታደግና ለማበልጸግ የተወሰደ የመጨረሻው ከፍተኛ እርምጃ ነው። በእርግጥም “ችግር ወይም መከራ የደረሰበትን ሰው ለመርዳት” የተወሰደ እርምጃ ነው።
አዎንታዊ ነገር በማድረግ ታማኝነትህን አሳይ
ታማኝነት የፍቅራዊ ደግነት ተመሳሳይ ቃል ስለሆነ ውለታ ለመመለስ መጓጓት የሚል ሐሳብ ይዟል። አንድ ሰው ፍቅራዊ ደግነት ካሳየህ አንተም እንደዚያው እንድታደርግ ሊጠበቅብህ ይችላል። ታማኝነት ለተደረገለት ነገር አጸፋውን ይመልሳል። ዳዊት ‘ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስምህንም አመሰግናለሁ’ ብሎ መናገሩ ሄሴድ የሚለውን ቃል አንድምታ መረዳቱን ያሳያል። ዳዊት ይሖዋን እንዲያመልክና እንዲያመሰግን የገፋፋው ምንድን ነው? ‘የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትና እውነት’ ነው። (መዝሙር 138:2) ዳዊት ይሖዋ ላሳየው ፍቅራዊ ደግነት አጸፋውን ለመመለስ ሲል እሱን ለማምለክና ለማወደስ እንደተነሳሳ ግልጽ ነው። እኛስ ይሖዋ ስላሳየን ፍቅራዊ ደግነት ስናሰላስል አጸፋውን ለመመለስ እንገፋፋለን? ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ስም ሲነቀፍ በምትሰማበት ጊዜ ለስሙ በመቆርቆር ነቀፋው ትክክል እንዳልሆነ ትናገራለህ?
አንድ አዲስ ክርስቲያንና ባለቤቱ፣ በሞተር ቢሲክሌት አደጋ ሕይወቱን ባጣ አንድ ዘመዳቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሃይማኖታዊ አልነበረም፤ ሆኖም በቀብሩ ላይ የተገኙት ስለ ሟቹ አንዳንድ አስተያየቶችን እንዲሰጡ ተፈቅዶላቸው ነበር። አንደኛው ተናጋሪ ‘አምላክ ከእርሱ ጋር እንዲኖር ስለፈለገ ወደ ሰማይ ወስዶታል’ በማለት ለወጣቱ በአጭር መቀጨት ተወቃሹ አምላክ መሆኑን ተናገረ። ክርስቲያን ወንድማችን በዚህ ጊዜ ዝም ማለት አላስቻለውም። መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ማስታወሻ ባይዝም ወደ መድረኩ ወጣና “መሐሪ፣ ርኅሩኅና ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እንደዚህ ያለ ሁኔታ ያስደስተዋል ብላችሁ ታስባላችሁ?” ሲል ጠየቀ። ከዚያም ለምን እንደምንሞት፣ አምላክ የሰውን ዘር ከሞት ለማዳን ምን እርምጃ እንደወሰደና ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ስለሚከፍተው አስደናቂ የትንሣኤ ተስፋ የሚያስረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እየጠቀሰ የአሥር ደቂቃ ንግግር አቀረበ። ለቀብር የተገኙት ከ100 የሚበልጡ ሰዎች በአድናቆት ጭብጨባቸውን አቀለጡት። ወንድም ከጊዜ በኋላ ሁኔታውን ሲያስታውስ “ከዚያ በፊት ተሰምቶኝ የማያውቅ ውስጣዊ ደስታ ተሰማኝ። ይሖዋ በጥበቡ አማካኝነት ስላስተማረኝና ቅዱስ ስሙን ለሚሰድቡ ሰዎች መልስ ለመስጠት አጋጣሚውን ስለከፈተልኝ አመሰግነዋለሁ” በማለት ተናግሯል።
ለይሖዋ ታማኝ መሆን ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ መሆንንም የሚጨምር ነው። ለምን? ምክንያቱም እንዴት መኖር እንዳለብን የሚያስተምረን በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሁሉም የላቁ ጠቃሚ የሕይወት መመሪያዎች ናቸው። (ኢሳይያስ 48:17) የሌሎች ተጽእኖ ወይም የራስህ ድክመቶች የይሖዋን ሕግ ከመከተል ዞር እንዲያደርጉህ አትፍቀድ። ለአምላክ ቃል ምንጊዜም ታማኝ ሁን።
ለአምላክ ታማኝ መሆን ለድርጅቱ ታማኝ መሆንንም ይጨምራል። ባለፉት ዓመታት በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ የነበረንን መረዳት ማረምና ማስተካከል አስፈልጎን ነበር። ይህ የእኛን ያህል በመንፈሳዊ በሚገባ የሚመገብ ሰው እንደሌለ የሚያሳይ ነው። (ማቴዎስ 24:45-47) ይሖዋ በዚህ ዘመን ካለው ድርጅቱ ጎን በታማኝነት እንደቆመ ምንም ጥርጥር የለውም። እኛስ እንዲህ ማድረግ አንችልም? ኤ ኤች ማክሚላን ይህን አድርጓል። ከመሞቱ በፊት እንዲህ ብሎ ነበር:- “የይሖዋ ድርጅት መስከረም 1900 በሃያ ሦስት ዓመት ዕድሜዬ ራሴን ለአምላክ በወሰንኩበት ጊዜ ከነበረው አነስተኛ ጅምር አንስቶ እሱ የገለጠውን እውነት በቅንዓት የሚያውጁ ደስተኛ ሕዝቦችን ያቀፈ ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ እስከመሆን ድረስ ሲያድግ ተመልክቻለሁ። . . . በምድር ላይ ለአምላክ የማቀርበው አገልግሎት ወደ ፍጻሜው ሲቃረብ ይሖዋ ሕዝቦቹን እየመራና የሚያስፈልጋቸውን በተገቢው ጊዜ እየሰጣቸው እንዳለ ከምንጊዜውም የበለጠ አምኛለሁ።” ወንድም ማክሚላን ነሐሴ 26, 1966 እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ 66 ለሚያክሉ ዓመታት በጽናትና በታማኝነት አገልግሏል። ለሚታየው የአምላክ ድርጅት ታማኝ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው።
ለይሖዋ ድርጅት ታማኝ ከመሆን በተጨማሪ እርስ በርሳችንስ እንዴት ነን? ጭካኔ የተሞላበት ስደት በሚደርስብን ጊዜ እንኳ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ታማኝ እንሆናለን? በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በኔዘርላንድ ይኖሩ የነበሩ ወንድሞቻችን ግሩም የታማኝነት ምሳሌ ትተውልናል። በግሮኒንገን ጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል በነበረ ክላስ ዲ ቭሪስ የሚባል ወንድም ቁራሽ ዳቦና ውኃ እየተሰጠው ለ12 ቀናት በአንዲት ክፍል ውስጥ ብቻውን ታስሮ በናዚ ጌስታፖ ጭካኔ የተሞላበት ተደጋጋሚ ምርመራ ይደረግበት ነበር። ሽጉጥ ከተደገነበት በኋላ በሁለት ደቂቃ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ወንድሞችን አድራሻና ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን ካልሰጠ እንደሚገደል ተነገረው። ክላስ “ምንም ነገር ይነግረናል ብላችሁ አታስቡ። . . . ከሐዲ መሆን አልፈልግም” ከማለት በስተቀር አንዳች አልተነፈሰም። ሦስት ጊዜ በሽጉጥ ማስፈራሪያ ደርሶበታል። በመጨረሻ ጌስታፖዎች ተስፋ ቆርጠው ክላስን ወደ ሌላ እስር ቤት አዛወሩት። ወንድሞቹን አሳልፎ አልሰጠም።
የቅርባችን ለምንለው ሰው ይኸውም ለትዳር ጓደኛችንስ? ይሖዋ ከእስራኤል ብሔር ጋር በቃል ኪዳን ለመሠረተው ዝምድና አክብሮት እንዳሳየ ሁሉ እኛስ ለጋብቻ መሐላችን ታማኞች ነን? ለትዳር ጓደኛህ የማያወላውል ታማኝነት ማሳየት ብቻ ሳይሆን የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። ቀዳሚ በመሆን ትዳርህን የሚያጠናክሩ አንዳንድ እርምጃዎችን ውሰድ። አብራችሁ ጊዜ አሳልፉ፣ ከልብ ግልጽ የሐሳብ ግንኙነት አድርጉ፣ እርስ በርስ ተደጋገፉ እንዲሁም ተበረታቱ፣ እርስ በርስ ተደማመጡ፣ አብራችሁ ሳቁ፣ አብራችሁ አልቅሱ፣ አብራችሁ ተጫወቱ፣ በጋራ ባወጣችኋቸው ግቦች ላይ ለመድረስ አብራችሁ ሥሩ፣ አንዳችሁ ሌላውን ደስ ለማሰኘት ጣሩ፣ ጓደኛሞች ሁኑ። በተለይ ደግሞ ለሌላ ተቃራኒ ጾታ የፍቅር ስሜት እንዳታዳብሩ ተጠንቀቁ። ከሌሎች ጋር መግባባትና የቅርብ ወዳጅነት መመሥረቱ ትክክልና ተገቢ ቢሆንም ከትዳርህ ውጪ ከሌላ ሰው ጋር በፍቅር ስሜት መሳሳብ አይገባም። በአንተና በትዳር ጓደኛህ መካከል ማንም ሰው ጣልቃ እንዲገባ አትፍቀዱ።—ምሳሌ 5:15-20
ለእምነት ባልንጀሮችህና ለቤተሰቦችህ ምንጊዜም ታማኝ ሁን። ዓመታት እያለፉ በሄዱ ቁጥር አትርሳቸው። በደብዳቤ፣ በስልክ እንዲሁም በአካል ተገናኙ። ኑሮህ ምንም ይሁን ምን እነርሱን ቅር ላለማሰኘት ጥረት አድርግ። አንተን በማወቃቸው ወይም ከአንተ ጋር በመዛመዳቸው ደስ እንዲላቸው አድርግ። ለእነርሱ ያለህ ታማኝነት ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ቆራጥ እንድትሆን ከማድረጉም በላይ የብርታት ምንጭ ይሆንልሃል።—አስቴር 4:6-16
አዎን፣ እውነተኛ ታማኝነት ውድ የሆነው ወዳጅነት እንዲቀጥል ለማድረግ ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠይቃል። ይሖዋ ለሚያሳይህ ፍቅራዊ ደግነት አጸፋውን ለመመለስ የምትችለውን አድርግ። ከክርስቲያን ጉባኤ፣ ከትዳር ጓደኛህ፣ ከቤተሰብህ እንዲሁም ከወዳጆችህ ጋር ባለህ ግንኙነት ይሖዋ ያሳየውን ታማኝነት ኮርጅ። ለጎረቤቶችህ ስለ ይሖዋ በጎነት በታማኝነት ንገራቸው። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ምሕረትህን [“ፍቅራዊ ደግነትህን፣” NW ] ለዘላለም እዘምራለሁ፣ እውነትህንም በአፌ ለልጅ ልጅ እናገራለሁ” ማለቱ እውነት አለው። (መዝሙር 89:1) እንደዚህ ወዳለው አምላክ በቀላሉ አንሳብም? በእርግጥም “ምሕረቱ [“ፍቅራዊ ደግነቱ፣” NW ] ለዘላለም” ነው።—መዝሙር 100:5
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤ ኤች ማክሚላን