በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድን “አባካኝ” ልጅ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

አንድን “አባካኝ” ልጅ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

አንድን “አባካኝ” ልጅ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

“ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን . . . ይገባናል።”​—⁠ሉቃስ 15:32

1, 2. (ሀ) አንዳንድ ልጆች ክርስቲያናዊውን እውነት በተመለከተ ምን እርምጃ ይወስዳሉ? (ለ) ይህ ሁኔታ የገጠማቸው ወላጆችም ሆኑ ልጆች ምን ሊሰማቸው ይችላል?

 “በእውነት ቤት መቀጠል አልፈልግም!” ልጆቻቸውን በክርስትና ጎዳና ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች እንዲህ ያለውን ቃል ከልጃቸው አፍ ሲሰሙ ምንኛ ይደ​ነግጡ! አንዳንድ ልጆች ይህ አዝማሚያ እንዳላቸው ሳይታወቅ ‘ይወሰዳሉ።’ (ዕብራውያን 2:1) ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰውን የአባቱን ቤት ጥሎ ወደ ሩቅ አገር በመሄድ ያገኘውን ውርስ አላግባብ የበተነውን አባካኝ ልጅ ይመስላሉ።​—⁠ሉቃስ 15:11-16

2 ብዙዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ ሁኔታ ባያጋጥማቸውም እንኳ እውነትን የተዉ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ምንም ዓይነት የማጽናኛ ቃል ቢነገራቸው ሙሉ በሙሉ ከሃዘናቸው ሊጽናኑ አይችሉም። ዓመፀኛው ልጅም ሃዘን ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ሊዘነጋ አይገባም። ሕሊናው ሊያሠቃየው ይችላል። በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው አባካኝ ልጅ ከጊዜ በኋላ ‘ወደ ልቡ የተመለሰ’ ሲሆን ይህም ለአባቱ ደስታ አምጥቶለታል። ወላጆችም ሆኑ የተቀሩት የጉባኤው አባላት እንደ አባካኙ ልጅ ያሉ ልጆች ‘ወደ ልቡናቸው እንዲመለሱ’ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?​—⁠ሉቃስ 15:17

አንዳንዶች እውነትን የሚተዉት ለምንድን ነው?

3. ልጆች የክርስቲያን ጉባኤን ትተው እንዲሄዱ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

3 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ይሖዋን በደስታ የሚያገለግሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች አሉ። ታዲያ አንዳንድ ልጆች እውነትን ትተው የሚሄዱት ለምንድን ነው? ከዓለም የሚገኝ አንድ የቀረባቸው ነገር እንዳለ ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:10) ወይም ይሖዋ በጎቹን ለመጠበቅ የሚጠቀምበት በረት የማያፈናፍን እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። የጥፋተኝነት ስሜት፣ ለተቃራኒ ፆታ ያለው ጠንካራ ስሜት ወይም በእኩዮች ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ፍላጎት አንድን ወጣት ከይሖዋ መንጋ እንዲወጣ ሊያደርገው ይችላል። አንድ ልጅ በወላጆቹ ወይም በሌላ ክርስቲያን ላይ ሊያይ የሚችለው የግብዝነት ባሕርይ አምላክን ማገልገሉን እንዲያቆም ያደርገው ይሆናል።

4. ብዙውን ጊዜ ልጆች የእውነትን መንገድ ትተው እንዲባዝኑ የሚያደርጋቸው ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?

4 አንድ ልጅ የሚያሳየው የዓመፀኝነት ዝንባሌና ጠባይ ብዙውን ጊዜ በመንፈሳዊ መድከሙን የሚያሳይ ምልክት ከመሆኑም በላይ በልቡ ውስጥ ያለውን ነገር የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 15:13፤ ማቴዎስ 12:34) አንድ ልጅ ከእውነት መንገድ ወጥቶ የሚባዝንበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን የችግሩ ዋነኛ መንሥኤ “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት” የራሱ አለማድረጉ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:7 NW ) ልጆች አምልኳቸውን እንዲያው በዘልማድ ከማከናወን ይልቅ ከይሖዋ ጋር የቀረበ የግል ዝምድና መመሥረታቸው አስፈላጊ ነው። እንዲህ እንዲያደርጉ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

ወደ አምላክ ቅረቡ

5. አንድ ወጣት ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና እንዲመሠርት ምን ነገር የግድ አስፈላጊ ነው?

5 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 4:8) አንድ ልጅ እንዲህ እንዲያደርግ ከተፈለገ ለአምላክ ቃል ፍቅር እንዲያዳብር እርዳታ ማግኘት ይኖርበታል። (መዝሙር 34:8) በመጀመሪያ ‘በወተት’ የተመሰሉትን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች መማር ይኖርበታል። ከዚያም በአምላክ ቃል እየተደሰተና “ጠንካራ ምግብ” የተባሉትን ጥልቅ መንፈሳዊ ትምህርቶች እየተመገበ ሲሄድ ብዙም ሳይቆይ ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና ማደግ ይጀምራል። (ዕብራውያን 5:11-14፤ መዝሙር 1:2) ሙሉ በሙሉ ዓለማዊ አኗኗር ይከተል እንደነበር ሳይሸሽግ የተናገረ አንድ ወጣት ከጊዜ በኋላ መንፈሳዊ ነገሮችን ማድነቅ ጀመረ። ለውጥ እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው? ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያነብ የቀረበለትን ሐሳብ ተቀብሎ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ማውጣቱ ነው። አዎን፣ የአምላክን ቃል አዘውትሮ ማንበብ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ለመመሥረት የግድ አስፈላጊ ነው።

6, 7. ወላጆች ልጆቻቸው ለአምላክ ቃል ፍቅር እንዲያዳብሩ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

6 ወላጆች ልጆቻቸው ለአምላክ ቃል ፍቅር እንዲያዳብሩ መርዳታቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ አንዲት ልጅ ዘወትር በሚደረግ የቤተሰብ ጥናት ላይ ትካፈል የነበረ ቢሆንም እንኳ ከመጥፎ ልጆች ጋር ትውል ነበር። የቤተሰብ ጥናቷን በተመለከተ ስትናገር “አባባ ጥያቄዎችን በሚጠይቅበት ጊዜ ቀና ብዬ ሳላየው አንገቴን አቀርቅሬ መልሱን አነብብ ነበር” ብላለች። ጠቢብ የሆኑ ወላጆች በቤተሰብ ጥናት ወቅት አንድ ጽሑፍ እንዲሁ ከመሸፈን ይልቅ ጥሩ የማስተማር ዘዴ ይጠቀማሉ። (2 ጢሞቴዎስ 4:2) አንድ ልጅ በጥናቱ እንዲደሰት ከተፈለገ ጥናቱ ከግል ሕይወቱና እሱን ከሚያሳስቡት ጉዳዮች ጋር በቀጥታ ግንኙነት እንዳለው ሊሰማው ይገባል። ስሜቱን ገልጦ እንዲናገር ለምን የአመለካከት ጥያቄ አትጠይቁም? ልጁ እየተጠና ያለውን ትምህርት በሥራ ላይ እንዲያውለው አበረታቱት። a

7 ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይቱን ሕያው አድርጉት። አመቺ በሚሆንበት ጊዜ ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮችና ድራማዎች በትዕይንት መልክ እንዲያቀርቡ አድርጉ። ታሪኩ የተፈጸመበትን አካባቢና መልከዓ ምድራዊ ገጽታ በዓይነ ሕሊናቸው እንዲመለከቱት እርዷቸው። ካርታዎችን መጠቀም ሊረዳ ይችላል። አዎን፣ ትንሽ ከታሰበበት የቤተሰብ ጥናቱን ሕያውና የማይሰለች ማድረግ ይቻላል። ወላጆችም ቢሆኑ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና መመርመር ይኖርባቸዋል። እነርሱ ራሳቸው ወደ ይሖዋ በቀረቡ መጠን ልጆቻቸውም እንዲሁ እንዲያደርጉ ሊረዷቸው ይችላሉ።​—⁠ዘዳግም 6:5-7

8. ጸሎት አንድ ሰው ወደ አምላክ መቅረብ እንዲችል የሚረዳው እንዴት ነው?

8 ጸሎትም አንድ ሰው ወደ አምላክ እንዲቀርብ ሊረዳው ይችላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ አንዲት ልጅ ከክርስቲያናዊ ሕይወትና እምነቷን ከማይጋሯት ጓደኞቿ የቱን እንደምትመርጥ ተቸግራ ነበር። (ያዕቆብ 4:4) ምን አደረገች? “ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ጉዳዩ የሚሰማኝን ለይሖዋ በጸሎት ነገርኩት” በማለት ገልጻለች። ከጊዜ በኋላ ሚስጥሯን ልታካፍላት የምትችል አንዲት ጓደኛ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በማግኘቷ ጸሎቷ እንደተመለሰላት በመናገር ሐሳቧን ደምድማለች። ይሖዋ እየመራት እንዳለ ሆኖ ስለተሰማት ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት ጀመረች። ወላጆች የራሳቸውን የጸሎት ጥራት በማሻሻል ልጆቻቸውን መርዳት ይችላሉ። በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነው በሚጸልዩበት ጊዜ ልጆች በወላጆችና በይሖዋ መካከል ያለውን የጠበቀ ዝምድና ማስተዋል ይችሉ ዘንድ ወላጆች የልባቸውን አውጥተው መጸለይ ይችላሉ።

ትዕግሥተኞች ሆኖም ጥብቅ ሁኑ

9, 10. ይሖዋ ለዓመፀኞቹ እስራኤላውያን ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?

9 አንድ ልጅ ከእውነት መንገድ ለመውጣት ዳር ዳር ማለት ሲጀምር ራሱን ሊያገልልና ወላጆቹ ከእርሱ ጋር መንፈሳዊ ውይይት ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ሁሉ አልቀበልም ሊል ይችላል። ወላጆች እንዲህ ያለ ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ይሖዋ የጥንት እስራኤላውያንን በተመለከተ ያደረገውን እንመልከት። “አንገተ ደንዳና” የነበሩት እስራኤላውያን በተሳሳተ መንገዳቸው መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ከመፍቀዱ በፊት ከ900 ለሚበልጡ ዓመታት በትዕግሥት ይዟቸዋል። (ዘጸአት 34:9፤ 2 ዜና መዋዕል 36:17-21፤ ሮሜ 10:​21) በተደጋጋሚ ‘ቢፈትኑትም’ ይሖዋ ‘ምሕረት’ አሳይቷቸዋል። “ቍጣውንም መመለስ አበዛ፣ መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም።” (መዝሙር 78:38-42) አምላክ በእርሱ በኩል ምንም ያጓደለው ነገር አልነበረም። አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ልጃቸውን ለመርዳት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ፈጣን ምላሽ ሳያገኙ ቢቀሩ በትዕግሥት በመያዝ የይሖዋን ምሳሌ ይከተላሉ።

10 በተጨማሪም ቻይ ወይም ታጋሽ መሆን አንድ የተበላሸ ግንኙት ፈጽሞ ሊሻሻል አይችልም ብሎ በማሰብ ተስፋ አለመቁረጥን ያመለክታል። ይሖዋ እንዴት ታጋሽ መሆን እንደሚቻል ምሳሌ ትቷል። መልእክተኞቹን “ደግሞ ደጋግሞ” [NW ] ወደ እስራኤላውያን በመላክ ቅድሚያውን ወስዷል። ሕዝቡ “በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፣ ቃሉንም ያቃልሉ” የነበረ ቢሆንም እንኳ ‘እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያዝን’ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 36:15, 16) “ሁላችሁ እናንተ ከክፉ መንገዳችሁና ከሥራችሁ ክፋት ተመለሱ” እያለ እስራኤላውያንን ይማጸን ነበር። (ኤርምያስ 25:4, 5) ሆኖም ይሖዋ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን አላላላም። እስራኤላውያን ወደ አምላክና ወደ መንገዶቹ ‘እንዲመለሱ’ ተነግሯቸዋል።

11. ወላጆች መንገዱን ከሳተው ልጃቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ታጋሽ ሆኖም ጥብቅ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

11 ወላጆች መንገዱን በሳተው ልጃቸው በችኮላ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ትዕግሥት በማሳየት ይሖዋን ሊመስሉት ይችላሉ። ተስፋ ሳይቆርጡ የሐሳብ ግንኙነት መስመሩ ክፍት ሆኖ እንዲቀጥል ወይም እንደገና እንዲጀምር በማድረግ ቅድሚያውን ሊወስዱ ይችላሉ። የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሳያላሉ ወደ እውነት መንገድ እንዲመለስ ልጁን “ደግመው ደጋግመው” ሊማጸኑት ይችላሉ።

ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ሲወገድ

12. ወላጆች በእነሱ ሥር ለሚኖር ሆኖም ከጉባኤ ለተወገደ ለአካለ መጠን ላልደረሰ ልጅ ምን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው?

12 በወላጆቹ ሥር የሚኖር ለአካለ መጠን ያልደረሰ አንድ ልጅ ከባድ ኃጢአት ቢሠራና ንሥሐ የመግባት ዝንባሌ ሳያሳይ በመቅረቱ ምክንያት ከጉባኤ ቢወገድስ? በዚህ ወቅትም ቢሆን የሚኖረው በእነሱ ሥር እስከሆነ ድረስ ከአምላክ ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ልጁን የማስተማርና የመገሠጽ ኃላፊነት አለባቸው። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?​—⁠ምሳሌ 6:20-22፤ 29:17

13. ወላጆች የተሳሳተ ልጃቸውን ልብ መንካት የሚችሉት እንዴት ነው?

13 ልጁን በግል መጽሐፍ ቅዱስን በሚያስጠኑት ጊዜ እንዲህ ያለውን ትምህርትና ተግሣጽ ሊሰጡት ይችላሉ። ደግሞም የተሻለ የሚሆነው ይሄ ነው። አንድ ወላጅ በልጁ ግትር አመለካከት ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ልቡን ለማግኘት መጣር ይኖርበታል። መንፈሳዊ ሕመሙ ምን ያህል ሥር የሰደደ ነው? (ምሳሌ 20:5) ልቡን ማግኘት ይቻል ይሆን? የትኞቹን ጥቅሶች ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ይቻላል? ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል:- “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ይወጋል፣ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” (ዕብራውያን 4:12) አዎን፣ ወላጆች ልጃቸው ዳግመኛ በኃጢአት ድርጊት እንዳይካፈል ከመንገር የበለጠ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ። ቁስሉ ቀስ በቀስ እንዲድን ማድረግ ይችላሉ።

14. ስህተት የፈጸመ አንድ ልጅ ከይሖዋ ጋር የነበረውን ዝምድና ለማደስ በመጀመሪያ መውሰድ ያለበት እርምጃ ምንድን ነው? ወላጆች ልጃቸው እንዲህ ያለውን እርምጃ እንዲወስድ እንዴት ሊረዱት ይችላሉ?

14 ስህተት የፈጸመው ልጅ ከይሖዋ ጋር የነበረውን ዝመድና እንደገና ማደስ ይኖርበታል። መውሰድ ያለበት የመጀመሪያው እርምጃ ‘ንስሐ መግባትና መመለስ’ ነው። (ሥራ 3:19፤ ኢሳይያስ 55:6, 7) ወላጆች አብሯቸው የሚኖረው ልጅ ንስሐ እንዲገባ በሚረዱበት ጊዜ ‘ትዕግሥተኛ መሆንና’ አስቸጋሪ የሆነውን ልጃቸውን ‘በየዋህነት ማቅናት’ ይኖርባቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24-26 አ.መ.ት) መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ‘ተግሣጽ’ መስጠት ይኖርባቸዋል። “መገሠጽ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (ራእይ 3:19፤ ዮሐንስ 16:8) ስለዚህ መገሠጽ ማለት ልጁ እየተከተለ ያለው ጎዳና የኃጢአት መንገድ መሆኑን ማስረጃ እያቀረቡ ማሳመንን ይጨምራል። እንዲህ ማድረጉ ቀላል እንደማይሆን እሙን ነው። የሚቻል ሆኖ በሚያገኙት ጊዜ ሁሉ ወላጆች ልጃቸውን ለማሳመን የሚያስችሉ አግባብነት ያላቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶች በመጠቀም ልቡን መንካት ይችላሉ። ‘ክፉን መጥላትና መልካሙን መውደድ’ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ለማስገንዘብ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (አሞጽ 5:15) ‘ወደ ልቡናው ተመልሶ ከዲያብሎስ ወጥመድ’ ሊወጣ ይችል ይሆናል።

15. በደል የፈጸመ አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር የነበረውን ዝመድና እንዲያድስ በማድረግ ረገድ ጸሎት ምን ሚና ይጫወታል?

15 አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር የነበረውን ዝምድና ለማደስ ጸሎት የግድ አስፈላጊ ነው። እርግጥ ነው በአንድ ወቅት ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ይተባበር የነበረ አንድ ግለሰብ ንስሐ ሳይገባ በኃጢአት ድርጊቱ የሚገፋበት ከሆነ ለእርሱ በጸሎት ‘ጥያቄ’ ማቅረብ አይገባም። (1 ዮሐንስ 5:16, 17፤ ኤርምያስ 7:16-20፤ ዕብራውያን 10:26, 27) ሆኖም ወላጆች የተከሰተውን ሁኔታ ተገቢ በሆነ መንገድ መያዝ እንዲችሉ ጥበብ እንዲሰጣቸው ይሖዋን ሊጠይቁ ይችላሉ። (ያዕቆብ 1:5) አንድ የተወገደ ልጅ ንስሐ የመግባት አዝማሚያ እንዳለው ቢገነዘቡና ‘ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስችል ድፍረት ግን ቢያጣ’ አምላክ ልጁ የፈጸመውን በደል ይቅር ለማለት የሚያስችል መሠረት ቢያገኝ ፈቃዱ እንዲሆን ወላጆች ሊጸልዩ ይችላሉ። (1 ዮሐንስ 3:21) ልጁ እንዲህ ያለውን ጸሎት መስማቱ ይሖዋ አምላክ መሐሪ መሆኑን እንዲገነዘብ ሊረዳው ይችላል። b​—⁠ዘጸአት 34:6, 7፤ ያዕቆብ 5:16

16. የተወገደ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ያላቸውን ቤተሰቦች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

16 አንድ የተጠመቀ ልጅ ከተወገደ የጉባኤው አባላት ‘ከእርሱ ጋር መተባበራቸውን’ ማቆም ይጠበቅባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 2 ዮሐንስ 10, 11) እንዲህ መደረጉ ልጁ ‘ወደ ልቡ እንዲመለስና’ ጥበቃ ወደሚገኝበት ወደ አምላክ በረት ተመልሶ እንዲመጣ ሊረዳው ይችላል። (ሉቃስ 15:17) ሆኖም ተመለሰም አልተመለሰም የጉባኤው አባላት የተወገደውን ልጅ ቤተሰብ ማበረታታት ይችላሉ። ሁላችንም ‘ችግራቸውን እንደ ችግራችን አድርገን ለመመልከት’ እና ‘የርኅራኄ’ ስሜት ለማሳየት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ልንፈልግ እንችላለን።​—⁠1 ጴ⁠ጥ​ሮስ 3:8, 9

ሌሎች መርዳት የሚችሉበት መንገድ

17. የጉባኤ አባላት የጠፋን ልጅ ለመርዳት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርባቸዋል?

17 ከክርስቲያን ጉባኤ ያልተወገደ ሆኖም በእምነት ስለ ደከመ ልጅስ ምን ለማለት ይቻላል? ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 12:26) ሌሎች እንዲህ ያለውን ልጅ ለመርዳት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ። እርግጥ ነው በመንፈሳዊ የታመመው ልጅ በሌሎች ልጆች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። (ገላትያ 5:7-9) በአንድ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ ወንድሞችና እኅቶች በቅን ልቦና ተነሳስተው በመንፈሳዊ የደከሙ ወጣቶችን ለመርዳት በማሰብ አብረው ሰብሰብ ብለው ሙዚቃ ለመጫወት ባደረጉት ፕሮግራም ላይ እንዲገኙ ጋበዟቸው። ወጣቶቹ ግብዣውን ተቀብለው በፕሮግራሙ ላይ በመገኘታቸው ቢደሰቱም ያሳደሩት አሉታዊ ተጽዕኖ ሌሎች ከጉባኤው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እንዲያቆሙ ምክንያት ሆኗል። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ይሁዳ 22, 23) በመንፈሳዊ የታመመን ልጅ እንዲያገግም መርዳት የሚቻለው መንፈሳዊ መመሪያ በማይሰጥበት ግብዣ ላይ እንዲገኝ በማድረግ ሳይሆን ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍቅር እንዲያዳብር ሊረዳው በሚችል ስብሰባ ላይ እንዲገኝ በማድረግ ነው። c

18. በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው የአባካኙ ልጅ አባት የነበረው ዓይነት ዝንባሌ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 ጉባኤ መመላለስ ያቆመ አንድ ወጣት ወደ መንግሥት አዳራሽ በሚመጣበት፣ ወይም በወረዳ ወይም በልዩ ስብሰባ ላይ በሚገኝበት ጊዜ ምን ዓይነት ስሜት ሊያድርበት እንደሚችል አስብ። በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተገለጸው የአባካኙ ልጅ አባት የነበረው ዓይነት አመለካከት ማሳየት አይኖርብንም? (ሉቃስ 15:18-20, 25-32) ወደ ክርስቲያን ጉባኤ መምጣት አቁሞ የነበረና ከጊዜ በኋላ በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኘ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ልጅ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እንደ እኔ ዓይነቱን ሰው የሚያናግር ይኖራል ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም ነበር፤ ይሁን እንጂ ወንድሞችና እህቶች እየመጡ ሞቅ ባለ ስሜት ሰላም አሉኝ። ይህም በጥልቅ ነካኝ።” እንደገና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረና ተጠመቀ።

ተስፋ አትቁረጡ

19, 20. አንድን አባካኝ ልጅ በተመለከተ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

19 አንድ “አባካኝ” ልጅ ‘ወደ ልቡ እንዲመለስ’ መርዳት ትዕግሥት የሚጠይቅና ለወላጆችም ሆነ ለሌሎች ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ተስፋ አትቁረጡ። “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” (2 ጴጥሮስ 3:9) ይሖዋ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡና በሕይወት እንዲኖሩ እንደሚፈልግ ቅዱሳን ጽሑፎች ያረጋግጣሉ። እንዲያውም ሰዎችን ከእርሱ ጋር ለማስታረቅ የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ ቅድሚያውን ወስዷል። (2 ቆሮንቶስ 5:18, 19) ያሳየው ትዕግሥት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ልቡናቸው እንዲመለሱ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል።​—⁠ኢሳይያስ 2:2, 3

20 ታዲያ ወላጆች ለአካለ መጠን ያልደረሰ አባካኝ ልጃቸው ወደ ልቡናው እንዲመለስ ለመርዳት ማንኛውንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘዴ መጠቀም አይኖርባቸውም? ልጃችሁ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ለመርዳት ቁርጥ ያለ እርምጃ በምትወስዱበት ጊዜ የይሖዋን የታጋሽነት ባሕርይ ኮርጁ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ ተከተሉ፤ እንዲሁም እንደ ፍቅር፣ ፍትሕና ጥበብ ያሉትን የይሖዋን ባሕርያት ለማንጸባረቅ ጥረት አድርጉ። ወደ እርሱም ጸልዩ። ደንዳና ልብ የነበራቸው ብዙ ዓመፀኞች ይሖዋ ወደ እሱ እንዲመለሱ ያቀረበውን ፍቅራዊ ግብዣ ተቀብለው እንደተመለሱ ሁሉ የእናንተም አባካኝ ልጅ ጥበቃ ወደሚገኝበት ወደ አምላክ መንጋ ይመለስ ወይም ትመለስ ይሆናል።​—⁠ሉቃስ 15:6, 7

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ልጆችን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት ማስተማር እንደሚቻል ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የሐምሌ 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13-17 ተመልከት።

b ሌሎች የተወገደው ግለሰብ ያለበትን ሁኔታ ላያውቁ ስለሚችሉ ለአካለ መጠን ላልደረሰ ለአንድ ለተወገደ ልጅ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በሕዝብ ፊት ጸሎት መቅረብ የለበትም።​—⁠የጥቅምት 15, 1979 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 31ን ተመልከት።

c ይህን በሚመለከት ዝርዝር ሐሳብ ለማግኘት የሰኔ 22, 1972 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 13-16፤ የመስከረም 22, 1996 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 21-23 ተመልከት።

ታስታውሳለህን?

• ልጆች ከጉባኤ እንዲርቁ የሚያደርጋቸው ዋነኛው ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?

• ልጆች ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና እንዲያዳብሩ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

• ወላጆች አንድን አባካኝ ልጅ በሚረዱበት ጊዜ ታጋሽ ሆኖም ጥብቅ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

• የጉባኤ አባላት አንድ አባካኝ ልጅ እንዲመለስ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና ለማዳበር የአምላክን ቃል ማንበብ እጅግ አስፈላጊ ነው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች የሚያቀርቡት ልባዊ ጸሎት በእነርሱና በይሖዋ መካከል የጠበቀ የግል ዝምድና እንዳለ ልጆቻቸው እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ አባካኝ ልጅ ‘ወደ ልቡ በሚመለስበት’ ጊዜ ሞቅ ባለ መንፈስ ተቀበሉት

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጃችሁ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ለመርዳት አዎንታዊ እርምጃዎችን ውሰዱ