በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዘንባባ ዛፍ የሚገኝ ትምህርት

ከዘንባባ ዛፍ የሚገኝ ትምህርት

ከዘንባባ ዛፍ የሚገኝ ትምህርት

“አስደናቂ ውበት ያለው ደስ የሚል ጥላ።” አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፔዲያ የተምርን ዛፍ የገለጸው በዚህ መንገድ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ሆነ ዛሬ የተምር ዛፎች የግብፅን የናይል ሸለቆ ያስዋቡ ሲሆን በኔጌብ በረሃ በሚገኙ እርጥበት አዘል ቦታዎች ላይ ደግሞ መንፈስን የሚያድስ ጥላ ያስገኛሉ።

እንደ አብዛኞቹ የዘንባባ ዛፍ ዝርያዎች ሁሉ የተምር ዛፍም ወደላይ የተመዘዘ አስገራሚ ቁመት አለው። አንዳንዶቹ 30 ሜትር ርዝመት የሚኖራቸው ሲሆን ለ150 ዓመታት ፍሬ ይሰጣሉ። በእርግጥም የተምር ዛፍ ለዓይን ማራኪ ከመሆኑም በላይ በጣም ፍሬያማ ነው። ዛፉ በየዓመቱ በርካታ የተምር ዘለላዎች ይሸከማል። አንዱ ዘለላ ብቻ ከ1, 000 በላይ የተምር ፍሬዎች ሊይዝ ይችላል። አንድ ደራሲ የተምርን ፍሬ በተመለከተ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ለሽያጭ ከሚቀርብ ደርቆ ከታሸገ የተምር ፍሬ ሌላ ቀምሰው የማያውቁ ሰዎች ... ፍሬው ወዲያው ተቀጥፎ ሲበላ ምን ያህል እንደሚጣፍጥ ሊገምቱ አይችሉም።”

መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ሰዎችን ከዘንባባ ዛፍ ጋር ማመሳሰሉ ተገቢ ነው። ፍሬያማ እንደሆነው የዘንባባ ዛፍ ሁሉ አንድ ሰው በአምላክ ዓይን የሚያስደስት ሆኖ ለመገኘት ንጹሕ ሥነ ምግባር መከተልና መልካም ሥራዎችን መሥራት መቀጠል ይኖርበታል። (ማቴዎስ 7:​17-20) ከዚህም የተነሳ የሰሎሞንን ቤተ መቅደስም ሆነ ሕዝቅኤል በራእይ ያየውን ቤተ መቅደስ ለማስጌጥ የዘንባባ ዛፍ ምስሎች ተቀርጸዋል። (1 ነገሥት 6:​29, 32, 35፤ ሕዝቅኤል 40:​14-16, 20, 22) በመሆኑም አንድ ሰው አምልኮቱ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ የተምር ዛፍ ያሉት ተወዳጅ ባሕርያት ሊኖሩት ይገባል። የአምላክ ቃል “ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል” ሲል ይገልጻል።​—⁠መዝሙር 92:​12