በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዛሬም እውነተኛ እምነት ማዳበር ይቻላልን?

ዛሬም እውነተኛ እምነት ማዳበር ይቻላልን?

ዛሬም እውነተኛ እምነት ማዳበር ይቻላልን?

“እምነት ማለት በአምላክ ጸጋ ላይ ሕያውና ጠንካራ ትምክህት ማዳበር ማለት ሲሆን ፍጹም አስተማማኝ ከመሆኑ የተነሣ አማኙ አንዴ ብቻ ሳይሆን ሺህ ጊዜ ሕይወቱን የሚሠዋለት ነገር ነው።”​—⁠ማርቲን ሉተር፣ 1522

“ያለነው ክርስቲያናዊው እምነትና ተግባራት ምውት በሆኑበት ዓለማዊ ሕብረተሰብ ውስጥ ነው ማለት ይቻላል።”​—⁠ሉዶቪክ ኬኔዲ፣ 1999

እምነትን አስመልክቶ የሚሰጡት አስተያየቶች ፍጹም ይለያያሉ። ባለፉት ጊዜያት በአምላክ ማመን የተለመደ ነበር። ጥርጣሬ በነገሠበትና መከራ በሞላበት በዛሬው ጊዜ ግን በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየተመናመነ ነው።

እውነተኛ እምነት

“እምነት” ማለት ለብዙዎች አንድ ሃይማኖታዊ እምነት መያዝ ወይም አንድ ዓይነት አምልኮ መከተል ማለት ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተሠራበት ከሆነ “እምነት” ማለት በአምላክና እሱ በሰጠን ተስፋዎች ላይ ሙሉና የማያወላውል ትምክህት መጣል ማለት ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ለይቶ የሚያሳውቅ ባሕርይ ነው።

በአንድ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ አዘውትሮ የመጸለይንና ‘ያለመታከትን’ አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ከጠቀሰ በኋላ በጊዜያችን ከቶ እውነተኛ እምነት ይገኝ እንደሆነ ጠየቀ። “የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ ይህን እምነት በምድር ያገኝ ይሆንን?” ኢየሱስ እንዲህ ያለ ጥያቄ ያነሳው ለምንድን ነው?​—⁠ሉቃስ 18:1, 8 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ

የእምነት መጥፋት

በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ነገሮች ሰዎች በአንድ ወቅት የነበራቸውን እምነት እንዲያጡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ከእነዚህም መካከል ዕለታዊው ኑሮ የሚያስከትለው የስሜት ቀውስና ጫና ይገኝበታል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1958 ሙኒክ ውስጥ በማንቸስተር ዩናይትድ የእግር ኳስ ቡድን ላይ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ምክንያት ብዙ የቡድኑ አባላት ሲሞቱ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ማይክል ጎልዳር እንግሊዝ ማንቸስተር ውስጥ የደብር ቄስ ሆነው ያገለግሉ ነበር። በአንድ የቢቢሲ ቴሌቪዠን ፕሮግራም ላይ ዜና ዘጋቢዋ ጆአን ቤክ ዌል፣ ጎልዳር “የሰዎቹን ኃዘን ጥልቀት ሲመለከቱ አንዳች ነገር ማድረግ እንደማይችሉ ተሰምቷቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ የተነሣ ጎልዳር “የሰውን ልጅ ዕጣ ፈንታ በሚወስነው አምላክ ላይ የነበራቸው እምነት ጠፋ።” ጎልዳር እምነታቸውን ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “መጽሐፍ ቅዱስ . . . ከስህተት የጠራ የአምላክ ቃል ሳይሆን ስህተት ያለበት የሰው ቃል ነው። ምናልባት አለፍ አለፍ ብሎ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ሐሳቦች ይኖሩት ይሆናል።”

አንዳንድ ጊዜ እምነት ብንን ብሎ ይጠፋል። ጸሐፊ እንዲሁም የራዲዮና የቴሌቪዠን ፕሮግራም አቅራቢ በሆነው ሉዶቪክ ኬኔዲ ላይ የደረሰው ተመሳሳይ ነገር ነው። ሉዶቪክ “ከልጅነቱ ጀምሮ [ስለ አምላክ] በውስጡ ይመላለስ የነበረው ጥርጣሬ እያደገ እንደመጣ” ተናግሯል። ለጥያቄዎቹ ምክንያታዊ መልስ ሊሰጠው የሚችል ሰው ያለ አይመስልም ነበር። የአባቱ በባሕር አደጋ መሞት በፊቱኑም ደካማ የነበረ እምነቱን ይበልጥ ያዳከመ ድንገተኛ ክስተት ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አባቱ ተሳፍሮበት የነበረው የመንገደኞች መርከብ በጀርመን የጦር መርከቦች አደጋ ደርሶበት ሲወድም “ከባሕር አደጋና ከጠላቶቻችን ደባ ጠብቀን” በማለት ለአምላክ የሚቀርበው ጸሎት ምላሽ የተነፈገው ያህል ነበር።​—ኦል ኢን ዘ ማይንድ​—ኤ ፌር ዌል ቱ ጎድ

ይህ እንግዳ ነገር አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እምነት ለሁሉ አይደለም’ በማለት ተናግሯል። (2 ተሰሎንቄ 3:1, 2) አንተስ ምን ይመስልሃል? እያደር ተጠራጣሪ እየሆነ በሄደው በዛሬው ሕብረተሰብ ውስጥ በአምላክና በቃሉ ላይ እውነተኛ እምነት ማዳበር ይቻላልን? የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጠውን ሐሳብ መርምር።