በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአንዲስ በመፍሰስ ላይ ያለው ሕይወት ሰጪ ውኃ

በአንዲስ በመፍሰስ ላይ ያለው ሕይወት ሰጪ ውኃ

በአንዲስ በመፍሰስ ላይ ያለው ሕይወት ሰጪ ውኃ

የአንዲስ ተራሮች ፔሩን መሃል ለመሃል ሰንጥቀው የሚያልፉ ሲሆን አገሪቱን ለሁለት በመክፈል በስተ ምዕራብ ደረቅ የባሕር ዳርቻ በስተ ምሥራቅ ደግሞ ጥቅጥቅ ያለ ደን እንዲኖራት አድርገዋል። ከፔሩ 27 ሚልዮን ሕዝብ መካከል አንድ ሦስተኛው የሚኖረው በዚህ ተራራማ ሰንሰለት ላይ ነው። ሕዝቡ በአምባዎቹና ቀጥ ባሉት የተራራ ጥጋቶች አሊያም መጨረሻ የሌላቸው በሚመስሉትና ገደላማ በሆኑት ለም ሸለቆዎች ውስጥ ይኖራል።

የአንዲስ ተራራ ወጣገባነት ሰዎች በቀላሉ ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ከማድረጉም በላይ በሚልዮን የሚቆጠሩት የአካባቢው ነዋሪዎች ከሌሎች እንዲገለሉና ከአካባቢያቸው ውጪ ለሚፈጠሩት ክስተቶችና አዳዲስ ሁኔታዎች ባይተዋር እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

አልማስ፣ አልፓካስ እና ቪኩናስ የተባሉትን የግመል ዝርያዎች ጨምሮ ለበጎቹ መንጋና ለሰብሎች የሚያስፈልገውን ውኃ ለማግኘት በወንዞቹ ዳርቻ ትንንሽ መንደሮች ተቋቁመዋል። ይሁን እንጂ በአንዲስ የሚፈስስ እጅግ አስፈላጊ የሆነ የውኃ ዓይነትም አለ። ይህ ውኃ ‘የሕያው ውኃ ምንጭ’ ከሆነው ከይሖዋ የሚፈስስና በመንፈሳዊ የሚያነቃቃ ውኃ ነው። (ኤርምያስ 2:13) ይሖዋ በአንዲስ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ የሠፈሩት መንደርተኞች ስለ እርሱና ስለ ዓላማው ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት በምሥክሮቹ ይጠቀማል።​—⁠ኢሳይያስ 12:3፤ ዮሐንስ 17:3

የአምላክ ፈቃድ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ በመሆኑ አገልጋዮቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት ሰጪ መልእክት በጣም አስቸጋሪ በሆነው በዚህ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክት መንፈሳዊ ማስተዋል የሚሰጥና ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነው። ቅን ልብ ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ሙታንን፣ ክፉ መናፍስትንና የተፈጥሮ ኃይላትን እንዲፈሩ ካደረጓቸው አጉል እምነቶች አላቅቋቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህ መልእክት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መጨረሻ የሌለው ሕይወት የመኖር ክብራማ ተስፋ ሰጥቷቸዋል።

ጥረት ማድረግ

እነዚህን ራቅ ያሉ አካባቢዎች የሚጎበኙ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ብዙ ማስተካከያዎችን ማድረግ አስፈልጓቸዋል። የሰዎቹን ልብ ለመንካት የክልሉ ዋነኛ የመግባቢያ ቋንቋ የሆኑትን የኬችዋ ወይም የአይማራ ቋንቋዎች ማወቅ ይኖርባቸዋል።

አንዲስ ወደሚገኙት መንደሮች መግባት ቀላል አይደለም። የባቡር መንገዶች ውስን ሲሆኑ በትራንስፖርት መጠቀም ደግሞ አደገኛ ነው። የአየሩ ሁኔታና የመሬቱ አቀማመጥም ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው። ታዲያ ምሥክሮቹ የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎቹ ማድረስ የሚችሉት እንዴት ነው?

ደፋር የሆኑት የምሥራቹ ሰባኪዎች ይህንን ተፈታታኝ ሁኔታ በመቋቋም “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” በማለት የተናገረውን የነቢዩ ኢሳይያስን ዓይነት መንፈስ ያንጸባርቃሉ። (ኢሳይያስ 6:8) ወደ ሰሜን፣ ወደ መካከለኛውና ወደ ደቡባዊ ክልሎች ለመጓዝ ሦስት ተንቀሳቃሽ ቤቶች ይጠቀማሉ። ቀናተኞቹ አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በካርቶን ያጨቋቸውን መጽሐፍ ቅዱሶችና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ይዘው እንግዳ ተቀባይ፣ ቅንና ወዳጃዊ ወደሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎች በመሄድ በልባቸው ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን የእውነት ዘር ዘርተዋል።

በተለይ በተራራማው መንገድ ላይ የሚገኙት መታጠፊያዎች በጣም አደገኛ ናቸው። እነዚህን አደገኛ ቦታዎች ያለ ችግር ለማለፍ መኪኖቹ ጠመዝማዛ መንገዶችን መጠቀም ይኖርባቸዋል። በአንድ ወቅት እንዲህ ባለው መንገድ ላይ በአውቶቡስ እየተጓዙ ሳለ ኋለኛው ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረ አንድ ሚስዮናዊ በመስኮት ሲመለከት የአውቶቡሱ የኋለኛ ጎማ 190 ሜትር ርቀት ባለው ገደል አፋፍ ላይ እንደሆነ ተገነዘበ! ሚስዮናዊው አውቶቡሱ እስኪያልፍ ዓይኑን አልገለጠም።

አንዳንድ መንገዶች ደግሞ በጣም የተበላሹ ከመሆናቸውም በላይ ጠባብ ናቸው። ከተንቀሳቃሽ ቤቶቹ አንዱ እንዲህ ካለው ጎርበጥባጣ መሬት ጋር የሚያደርገው ትግል ሳያንስ በአንድ ጠባብ መንገድ ላይ ቁልቁል እየወረደ ሳለ ሽቅብ ከሚወጣ ከባድ መኪና ጋር ተፋጠጡ። በዚህ ጊዜ ተንቀሳቃሹ ቤት ሁለቱንም በጭንቅ የሚያሳልፍ ቦታ እስኪገኝ ድረስ የኋሊት ሽቅብ መመለስ ነበረበት።

ያም ሆኖ እነዚህ ጽናት የሚጠይቁ ጥረቶች ግሩም ውጤት አስገኝተዋል። ስለ እነዚህ ጥረቶች ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ?

የቲቲካካን ሐይቅ “ውኃ ማጠጣት”

ከባሕር ወለል በላይ 3, 800 ሜትር ከፍታ ላይ ከሚገኙት የአንዲስ ተራራዎች በታች ያለው የቲቲካካ ሐይቅ በዓለም ላይ ለመጓጓዣነት ከሚያገለግሉት በመሬት የተከበቡ የውኃ አካላት መካከል ከባሕር ወለል በላይ ባለው ከፍታው የሚተካከለው የለም። ወደ ቲቲካካ ከሚፈስሱት 25 ወንዞች መካከል አብዛኞቹ መነሻቸው አናታቸው በበረዶ የተሸፈነውና አንዳንዶቹም ከ6, 400 ሜትር የሚበልጥ ከፍታ ያላቸው ተራሮች ናቸው። ከቦታው ከፍተኛነት የተነሳ አየሩ ቀዝቃዛ ሲሆን ለአገሩ እንግዳ የሆኑ ሰዎች ከፍታው የሚያስከትልባቸውን ሕመም መቋቋም ይኖርባቸዋል።

ከተወሰነ ጊዜ በፊት ኬችዋ እና አይማራ ቋንቋዎችን የሚናገር አንድ የአቅኚዎች ቡድን ቲቲካካ ሐይቅ ላይ የሚገኙትን የአማንታኒና የታኩዊሊ ደሴቶች ለመጎብኘት ወደዚያው ተጉዞ ነበር። ቡድኑ የሕዝበ ክርስትናን ሐሰተኛነት የሚያጋልጥ “አብያተ ክርስቲያናትን መመርመር” የሚል ርዕስ ያለው አንድ የስላይድ ፊልም ይዞ የሄደ ሲሆን ፊልሙም ጥሩ ምላሽ አስገኝቷል። አንድ ግለሰብ ወንድሞችን በደስታ በመቀበል ማረፍና መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር የሚችሉበት አንድ ሰፊ ክፍል ሰጥቷቸዋል።

በአማንቲ በተደረገው የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ 100 ሰዎች የተገኙ ሲሆን በታኩዋሊ በተደረገው ስብሰባ ላይ ደግሞ 140 ሰዎች ተገኝተዋል። ፊልሙ የተዘጋጀው በኬችዋ ቋንቋ ነበር። ቀደም ሲል በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ብለዋል:- “እናንት የይሖዋ ምሥክሮች አሁን እኛን ማስታወስ የሚኖርባችሁ ጊዜ ነው። እንድትመጡ ስንጸልይ ቆይተናል።”

ምሥራቹ በእነዚህ ሁለት ትላልቅ ደሴቶች እና ወደ 40 በሚጠጉት የቲቲካካ ሐይቅ “ተንሳፋፊ” ደሴቶች ተዳርሷል። ተንሳፋፊ ደሴቶች? አዎን፣ እነዚህ ረግረጋማ በሆኑት በሐይቁ ዳርቻ አካባቢ ከሚያድጉት ቶቶራስ ከተባሉ የመቃ ተክሎች የሚሠሩ ናቸው። ቶቶራስ ከውኃው ውስጥ ወደ ላይ የሚበቅል ተክል ነው። ያገሬው ሰዎች ደሴት መሥራት ሲፈልጉ ሐይቁ ውስጥ የተደላደለ ሥር ይዘው ያደጉትን መቃዎች አጠፍ አጠፍ ያደርጉና እርስ በርስ ካጠላለፏቸው በኋላ ወለል ይሠራሉ። ከዚያም ወለሉን በጭቃ ከለሰኑት በኋላ ተጨማሪ መቃዎች ቆርጠው ያጠነክሩታል። ከዚያም በወለሉ ላይ የመቃ ጎጆ ሠርተው ይኖራሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች በቲቲካካ ሐይቅ ደሴቶች ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ለመስበክ የሚያስችል ጀልባ ያገኙ ሲሆን ጀልባው 16 ሰዎች የመያዝ አቅም አለው። ምሥክሮቹ ተንሳፋፊ ደሴቶቹ ጋር ሲደርሱ ከመቃ በተሠራው ወለል ላይ እየተራመዱ ከቤት ወደ ቤት ያገለግላሉ። በሚራመዱበት ጊዜ ወለሉ በትንሹ ሲንቀሳቀስ ይሰማቸው እንደነበር ተናግረዋል። ቦታው በጉዞ ምክንያት ለሚታመሙ ሰዎች አይሆንም።

በባሕር ዳርቻውና ወደ ሐይቁ በሚወስዱት ባሕረ ገብ መሬቶች ላይ በሚገኙ በርካታ መንደሮች ውስጥ የአይማራ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩ ሲሆን ወደነዚህ ክልሎች ለመድረስ ከእግር ይልቅ በጀልባ መጓዝ ይቀላል። እነዚህ ጀልባዎች የመንግሥቱን መልእክት በሚያዳርሱባቸው ቦታዎች በጠቅላላው ወደ 400, 000 የሚጠጉ ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። ጀልባዎቹ ወደፊት ሥራ እንደሚበዛባቸው ምንም ጥርጥር የለውም።

መንፈሳዊ ጥምን ማርካት

ፍላቪዮ የሚኖረው አንዲስ ውስጥ ከሆሊያካ አጠገብ በሚገኘው በሳንታ ሉሲያ መንደር ነው። የአንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን አማኝ እንደመሆኑ መጠን የሲኦል እሳትን መሠረተ ትምህርት ተምሯል። ለብዙ ዓመታት እንዲህ ያለው ዘላለማዊ እሳታማ ሲኦል ሲያስፈራው ቆይቷል። አፍቃሪ የሆነ አምላክ እንዴት የሰው ልጆችን ለዘላለም በእሳት ያቃጥላል የሚል ጥያቄ ሁልጊዜ በአእምሮው ይመላለስ ነበር። ቲቶ የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ይህን መንደር ሲጎበኝ ፍላቪዮን አነጋገረው።

ፍላቪዮ ያቀረበው የመጀመሪያ ጥያቄ “ሃይማኖታችሁ ሰዎች ለዘላለም እሳት ውስጥ ይቃጠላሉ ብሎ ያስተምራል?” የሚል ነበር። ቲቶም ይህ ዓይነቱ ሐሳብ ከፈጣሪ ሁለንተናዊ ባሕርይ ጋር የሚጋጭና የፍቅር አምላክ በሆነው በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ የሚያመጣ እንደሆነ ገለጸለት። ቲቶ ሙታን አንዳች እንደማያውቁና በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምድራዊ ትንሣኤ ለማግኘት እንደሚጠባበቁ ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ አሳየው። (መክብብ 9:5፤ ዮሐንስ 5:28, 29) በዚህ ጊዜ የፍላቪዮ ዓይን ተከፈተ። ወዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረና ብዙም ሳይቆይ የተጠመቀ ክርስቲያን ሆነ።

አመስጋኝ መንደር

መጽሐፍ ቅዱስ አይተው ለማያውቁ ሰዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን ማስተማርም ሆነ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ወይም ስለሚሰብኩት ምሥራች ሰምተው ለማያውቁት ሰዎች መስበክ ምንኛ አስደሳች እንደሆነ ገምት! ሮዛ፣ አሊሲያ እና ሴሲሊያ የተባሉ ሦስት አቅኚ እህቶች በመካከለኛው ፔሩ በሚገኙትና ከ3, 600 ሜትር በላይ ከፍታ ባላቸው ኢዝኩቻካ እና ኮናያካ በተባሉ መንደሮች ውስጥ ሲሰብኩ ያጋጠማቸው ይኸው ነበር።

መጀመሪያው መንደር ሲደርሱ የሚያርፉበት ቦታ ስላልነበራቸው ወደ አካባቢው ፖሊስ አዛዥ ቀርበው የመጡበትን ምክንያት በመግለጽ አነጋገሩት። ውጤቱስ ምን ነበር? ሌሊቱን በፖሊስ ጣቢያው እንዲያሳልፉ ፈቀደላቸው። በሚቀጥለው ቀን ይበልጥ ቋሚ የሆነ ማረፊያ ያገኙ ሲሆን ቤቱንም የስብከታቸው ማዕከል አደረጉት።

ብዙም ሳይቆይ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል የሚከበርበት ጊዜ ደረሰ። አቅኚዎቹ በኢዝኩቻካ መንደር ውስጥ የሚገኙትን ቤቶች በሙሉ የጎበኙ ሲሆን ብዙ መጽሐፍ ቅዱሶችም አበርክተዋል፤ እንዲሁም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አስጀምረዋል። የመታሰቢያው በዓል ከመከበሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ምሥክሮቹ የበዓሉን ዓላማና በበዓሉ ወቅት የሚዞረው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን ያዘለውን ትርጉም የሚገልጽ የመጋበዣ ወረቀት አሰራጩ። በዓሉን በማክበር ረገድ የተወሰነ እርዳታ እንዲያበረክቱ ጥቂት ወንድሞች የተጋበዙ ሲሆን ከመካከላቸው አንደኛው የመታሰቢያውን ንግግር ሰጥቷል። ከዚህች አነስተኛ መንደር የተውጣጡ 50 ሰዎች በዚህ ልዩ በዓል ላይ መገኘታቸውን መመልከት ምንኛ ያስደስታል! ሰዎቹ የጌታ እራት ያዘለውን ትክክለኛ ትርጉም ለመጀመሪያ ጊዜ የተረዱት በዚህ ወቅት ነበር። የአምላክን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ማግኘታቸው ምንኛ አስደስቷቸዋል!

ከባድ ከሆኑ ሸክሞች መላቀቅ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን አነቃቂ የእውነት ውኃ በሐሰት ሃይማኖት ምርኮ ለተያዙ ሰዎች ማድረስ ሁልጊዜ አስደሳች ነው። ፒሳክ የጥንቷ ኢንካ ጠንካራ ምሽግ ነበር። ዛሬ በዚህ አካባቢ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነውን የሲኦል እሳት ትምህርት ተምረዋል። በእነርሱ አማላጅነት ካልሆነ በቀር ፈጽሞ ወደ ሰማይ መሄድ እንደማይችሉ ቄሶቻቸው ነግረዋቸዋል።

እነዚህ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው አነቃቂ የእውነት ውኃ ጥማት እንዳላቸው ግልጽ ነው። ሳንቲያጎ የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ከቤት ወደ ቤት እያገለገለ ሳለ ለአንድ የቤት ባለቤት ጻድቃን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳላቸው የመግለጽ አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። (መዝሙር 37:11) ሳንቲያጎ ሙታን እንደሚነሱና የሰው ዘር ለዘላለም የመኖርን ተስፋ ይዞ ትክክለኛ የሆኑትን የይሖዋን የጽድቅ መንገዶች እንደሚማር ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየው። (ኢሳይያስ 11:9) ቀናተኛ ካቶሊክ የነበረው ይህ ሰው እስከዚህ ጊዜ ድረስ መናፍስታዊ ድርጊቶች ይፈጽምና ከልክ በላይ ይጠጣ ነበር። አሁን ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋና በገነት ውስጥ የመኖር ግብ አለው። ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር የተያያዙ ዕቃዎቹን በሙሉ ከማቃጠሉም በላይ ከልክ በላይ መጠጣቱንም አቁሟል። በመጨረሻ መላ ቤተሰቡን ሰብስቦ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ ወስነው ተጠመቁ።

መስተንግዷቸውን በደስታ ተቀብለናል

የተራራማው አካባቢ ነዋሪዎች በጣም እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። መኖሪያቸው ልከኛ፣ ኑሯቸው ዝቅተኛ ቢሆንም እንግዶች ሲመጡ ቤት ያፈራውን ሁሉ ያቀርባሉ። አንድ የቤት ባለቤት የመጽሐፍ ቅዱስን ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች ከመማሩ በፊት ቤቱ እንግዳ ሲመጣ በጨዋታው መካከል ሊታኘኩ የሚችሉ የኮካ ቅጠሎች ያቀርብ ነበር። ምሥክር ከሆነ በኋላ ግን ከኮካ ቅጠል ጋር የሚመጣጠን ዋጋ ያለውን አንድ የሻይ ማንኪያ ስኳር ያቀርብ ይሆናል።

አንድ አስፋፊ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ አብሮት እንዲሄድ አንድን ሚስዮናዊ ይጠይቀዋል። አስቸጋሪውን የተራራ አቀበት ከተወጡ በኋላ መምጣታቸውን ለቤቱ ባለቤት ለማሳወቅ እጃቸውን አጨበጨቡ። ወዲያው የሣር ክዳን ወዳለው ቤት እንዲገቡ ተጋበዙ፤ መግቢያው አጭር በመሆኑ ወደ ውስጥ ለመግባት በጣም ዝቅ ማለት ነበረባቸው። እናትዬዋ በቆሸሸው ቤት መሃል ላይ በቆፈረችው ጉድጓድ ውስጥ በብርድ ልብስ የተጠቀለለ ሕፃን ስለነበር እዚያ አካባቢ ሲደርሱ ተጠንቅቀው መራመድ ነበረባቸው። ከጉድጓዱ መውጣት ያልቻለው ሕፃን የሚያወሩትን ትላልቅ ሰዎች እያየ በደስታ ይፍለቀለቃል። መንግሥቱ የሚያመጣቸውን በረከቶች አስመልክቶ አስደሳች ውይይት ካደረጉ በኋላ ሴትዮዋ በአካባቢው የታወቀ መጠጥ የያዘ አንድ ትልቅ ዕቃ ይዛ መጣች። ብዙም ሳይቆይ ወንድሞች ከተራራው ጥጋት በታች ባሉት አካባቢዎች ተጨማሪ ተመላልሶ መጠየቆች ለማድረግ ጉዞአቸውን ተያያዙት።

የተትረፈረፈ መከር

በአሁኑ ጊዜ በዚህ ክልል ውስጥ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጠኑ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች የሚኖሩባቸው ከአንድ መቶ የሚበልጡ ገለልተኛ ቡድኖች አሉ። ከሊማ የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተመርቀው የወጡ ወንድሞች እነዚህን ቡድኖች በጉባኤ መልክ እንዲያደራጁ ወደ አካባቢው ተልከዋል። ለብዙ ዓመታት በሃሰት ሃይማኖትና በአጉል እምነት ተጠፍረው የነበሩ ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች በመንግሥቱ ምሥራች አማካኝነት ነጻ ወጥተዋል! (ዮሐንስ 8:32) ለእውነት ውኃ የነበራቸው ጥማት ረክቷል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቲቲካካ ሐይቅ ላይ በሚገኙት “ተንሳፋፊ” ደሴቶች መመሥከር