በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እያደረግን ነው!

አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እያደረግን ነው!

አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እያደረግን ነው!

“አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርግ።” በአንድ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነ አንድ ወንድም ይህንን ምክር ለአንድ ሚስዮናዊ ሰጥቶ ነበር። እንዲህ ያለውን መሠረታዊ ምክር ለአንድ ተሞክሮ ላካበተ አገልጋይ መስጠት ለምን አስፈለገ? አብዛኞቹ ሚስዮናውያን ትኋኖችን፣ እባቦችን፣ ሙቀትን፣ በሽታንና የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው የሚኖሩ መንፈሰ ጠንካራ ሰዎች አይደሉምን?

እንደ እውነቱ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናውያን እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያላቸውና ለይሖዋ እንዲሁም ለሰዎች ባላቸው ጥልቅ ፍቅር ተገፋፍተው በውጭ አገር ለማገልገል የተነሳሱ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ናቸው። ሚስዮናውያኑ ይሖዋ በሚሰጣቸው ብርታት ታምነው በሙሉ ኃይላቸው እርሱን ለማገልገል ይጥራሉ።​—⁠ኤፌሶን 6:10

ስለ ሚስዮናዊ ሥራ ይበልጥ ለማወቅ በአንድ ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ በሚገኝ የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ የአንድ ቀን ጉብኝት እያደረግን እንዳለን አድርገን እናስብ።

የሚስዮናዊ ውሎ

ጊዜው ከጠዋቱ 1:​00 ገደማ ይሆናል። ሚስዮናውያኑ የዕለቱን ጥቅስ ውይይት ከመጀመራቸው ትንሽ ቀደም ብለን ደረስን። አሥሩ ሚስዮናውያን ሞቅ ያለ አቀባበል ካደረጉልን በኋላ ወንበር ሰጥተው አብረናቸው እንድንቀመጥ አደረጉ። ከሁሉም ጋር ከተዋወቅን በኋላ በሚስዮናዊ አገልግሎት ብዙ ዓመት ያሳለፈች አንዲት ሚስዮናዊት በአገልግሎት ያጋጠማትን አንድ አሥቂኝ ተሞክሮ መናገር ጀመረች። የዕለት ጥቅስ ውይይቱን እንዲመራ የተመደበው ወንድም ውይይቱ የሚጀምርበት ሰዓት መድረሱን ለደስተኛው ቡድን ሲያሳውቅ ቀስ በቀስ ፀጥታ ሰፈነ። ከዚያም ውይይቱ በፈረንሳይኛ ቋንቋ መካሄድ ጀመረ። ቋንቋውን መናገር ባንችልም እንኳ ከባዕድ አገር የመጡት እነዚህ ሚስዮናውያን ቋንቋውን አቀላጥፎ በመናገር ረገድ ጥሩ መሻሻል እንዳደረጉ ከአነጋገራቸው መረዳት ይቻላል።

ቅዱስ ጽሑፋዊውን ውይይት ተከትሎ ልባዊ ጸሎት ከቀረበ በኋላ ቁርስ መመገብ ተጀመረ። ከጥራጥሬ የተሠራውን ምግብ ሰሃናችን ላይ እንዳደረግን አጠገባችን የተቀመጠው ሚስዮናዊ በስስ በስሱ የተቆረጠ ሙዝ እላዩ ላይ እንድንጨምርበት ነገረን። ሙዝ እንደማንወድ ብንነግረውም የዚህን አገር ሙዝ አንዴ ከቀመስነው እንደምንወድደው ገለጸልን። ስለዚህ ምግባችን ላይ ጥቂት የተቆራረጡ ሙዞች ጨመርን። ምንኛ ትክክል ነበር! ሙዞቹ ልክ እንደ አይስ ክሬም ይጣፍጣሉ! እየተመገብን ያለነው ትኩስ ዳቦ ከሚስዮናውያኑ ቤት ሻገር ብሎ በሚገኝ አንድ ትንሽ ሱቅ ውስጥ ጠዋት የተጋገረ መሆኑን ገለጹልን።

ቁርስ ከተመገብን በኋላ ቀኑን ቤንና ካረን ብለን ከምንጠራቸው ሚስዮናዊ ባልና ሚስት ጋር እናሳልፋለን። ፍሬያማ ስለሆነው ስለዚህ ምዕራባዊ አፍሪካ አገር ሰምተን ስለነበር እውነት መሆኑን ለራሳችን ማረጋገጥ ፈለግን።

አውቶቡስ ማቆሚያው ጋር ስንደርስ አውቶቡስ የሚ​ጠብቁ ብዙ ሰዎች አገኘን። ብዙም ሳይቆይ ሚስዮናውያኑ ጓደኞቻችን ከአንዲት ሴትና ከወንድ ልጅዋ ጋር ሞቅ ያለ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ማድረግ ጀመሩ። ፈረንሳይኛ ስለማናውቅ ቆመን እያየናቸው ፈገግ ከማለት በቀር ምንም ማድረግ አልቻልንም! ሴትዮዋ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎች እንደተቀበለች አውቶቡሱ መጣ። ወዲያው እዚያ ቆሞ የነበረው ሰው ሁሉ እየተጋፋ አውቶቡሱ ላይ መሳፈር ጀመረ! እኛም በግፊያው ውስጥ አልፈን ለመሳፈር ስንሞክር ከኋላችን የነበሩት ሰዎች ወደ ላይ ገፉን። በኋላ እንደምንም ብለን ወደ ውስጥ አለፍን። አውቶቡሱ ጉዞውን ሲጀምር አንዳችን ሌላችንን ሙጭጭ አድርገን ያዝን። አውቶቡሱ ሰው ለማውረድ በቆመ ቁጥር ተጨማሪ ሰዎች ይሳፈሩ ስለነበር በጣም ተጨናነቅን። ተሳፋሪዎቹን እያየን ፈገግ ስንል እነርሱም በአጸፋው ፈገግ ይላሉ። ከእነርሱ ጋር መነጋገር ብንችል ምንኛ ደስ ባለን ነበር!

አውቶቡሱ ፍጥነቱን ሲጨምር በመንገድ ላይ የሚካሄደውን እንቅስቃሴ በመስኮት መመልከት ጀመርን። ሁለት ሴቶች በጭንቅላታቸው ላይ ከባድ ዕቃ ተሸክመው ጎን ለጎን ይሄዳሉ። አንደኛዋ የተሸከመችው ትልቅ የውኃ ገንቦ እንዳይወድቅባት ተጠንቅቃ ትራመዳለች። አንድ ንቁ ሰው መንገድ ዳር በዘረጋው ብርድ ልብስ ላይ ጌጣ ጌጦች ዘርግፎ ገዢ ይጠባበቃል። በየቦታው ሰዎች ሲገበያዩ ይታያሉ።

ድንገት ከጎኔ የቆመው ቤን አንድ ነገር እግሩን ጠቅ እንደሚያደርገው ተገነዘበ። ምን ሊሆን ይችላል? አውቶቡሱ በሰው ተጨናንቋል። ግን አሁንም ጠቅ አደረገው። ወደታች ለመመልከት ሞከረ። ለካስ አልፎ አልፎ አንገቷን ብቅ እያደረገች ጠቅ የምታደርገው ዳክዬ እግሩ ሥር ባለ ዘንቢል ውስጥ ተቀምጣ ኖሯል! የዳክዬዋ ባለቤት ሊሸጣት ወደ ገበያ ይዟት እየሄደ ሊሆን እንደሚችል ቤን ገለጸልን።

አገልግሎት ክልላችን እንደደረስን አንድ ዓይነተኛ አፍሪካዊ መንደር እንደምንጎበኝ ሲነገረን ተደሰትን። መጀመሪያው ቤት ስንደርስ ቤን መምጣታችንን ለማሳወቅ እጁን በኃይል አጨበጨበ። በዚህኛው የዓለም ክፍል ሰዎች የአንድን ሰው “ቤት የሚያንኳኩት” በዚህ መንገድ ነው። ወዲያው አንድ ወጣት ልጅ ብቅ አለና አሁን ሥራ ላይ ስለሆነ ትንሽ ቆየት ብለን እንድንመለስ ነገረን።

በሚቀጥለው ቤት ለቤን እንግዳ የሆነ ቋንቋ ከምትናገር ሴት ጋር ተገናኘን። ሆኖም ሴትዮዋ ወንድ ልጅዋን ጠራችውና ቤን የሚለውን እንዲተረጉምላት ጠየቀችው። ቤን ተናግሮ ሲጨርስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሶችን የያዘ አንድ ብሮሹር ወሰደች፤ ወንድ ልጅዋም ብሮሹሩን ለመተርጎም ተስማማ። ሦስተኛው ቤት ስንደርስ ግቢው ውስጥ ቁጭ ያሉ በርካታ ወጣቶች አገኘን። ወዲያው ሁለቱ መቀመጫቸውን ለቀቁልን። ከዚያም መስቀልን በአምልኮ ስለመጠቀም አንዳንድ ነጥቦች አንስተን አስደሳች ውይይት ካደረግን በኋላ በሚቀጥለው ሳምንት ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ ያዝን። ከዚህ በኋላ የመጀመሪያውን ቤት ስናንኳኳ አሁን ሥራ እንደሚበዛበት ወደነገረን ወጣት ቤት አቀናን። ለካስ ይህ ወጣት ከወጣቶቹ ጋር ያደረግነውን ውይይት በሆነ መንገድ ሰምቶ ኖሯል። ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች ስለነበሩት መጽሐፍ ቅዱስ እንድናስጠናው ጠየቀን። ቤን ፕሮግራሙን ከተመለከተ በኋላ በሚቀጥለው ሳምንት በዚሁ ሰዓት ተመልሶ እንደሚመጣ ነገረው። ለምሳ ወደ ቤት ስንመለስ ቤንና ካረን በቀላሉ ብዙ አዳዲስ ጥናቶች ማስጀመር ስለሚችሉ ጥናት የሚመሩበትን ሰዓት አስቀድመው በጥንቃቄ መወሰን እንደሚኖርባቸው ገለጹልን።

ፈረንሳይኛ እንዲህ አቀላጥፈው መናገር በመቻላቸው አደነቅናቸው። ቤን እርሱና ካረን በሚስዮናዊነት ሥራ ስድስት ዓመታት ቢያሳልፉም ቋንቋውን ያለ ችግር መናገር የጀመሩት አሁን እንደሆነ ገለጸልን። አዲስ ቋንቋ መማር ቀላል ባይሆንም ጽናት ዋጋ እንደሚያስገኝ አረጋገጡልን።

ስድስት ሰዓት ተኩል ላይ ሁሉም ሚስዮናውያን ለምሳ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባሰቡ። በእያንዳንዱ ቀን ቁርስና ምሳ የሚያዘጋጅ እንዲሁም የተበላባቸውን ዕቃዎች የሚያጣጥብ አንድ ሚስዮናዊ እንደሚመደብ ተረዳን። ዛሬ ከሚስዮናውያኑ አንዷ የተካነችበትን የሚያስጎመጅ የቲማቲም ሰላጣ ከዶሮና ከድንች ጥብስ ጋር አዘጋጅታለች!

ቤን እና ካረን ከሰዓት በኋላ ምን ለማድረግ አስበው ይሆን? የአገሬው ሰው ከ7:​00 እስከ 9:​00 ሰዓት ያለውን ጊዜ በቤቱ ሆኖ የፀሐዩን ሐሩር እንደሚያሳልፍና ሚስዮናውያኑም ከዚህ ውስጥ የተወሰነውን ጊዜ ለማጥናት አሊያም ለመተኛት እንደሚጠቀሙበት ገለጹልን። ካረን አዳዲስ ሚስዮናውያን ይህንን ለመልመድ ብዙ ጊዜ እንደማይወስድባቸው ስትገልጽልን ብዙም አልገረመንም!

ከእንቅልፍ እረፍት በኋላ ተመልሰን ወደ መስክ አገልግሎት ሄድን። ቤን ብዙ ጊዜ ተመላልሶ ያጣውን አንድ ፍላጎት ያሳየ ሰው ፍለጋ ቤቱ ሲሄድ ሁለት ወጣት ወንዶች ብቅ አሉ። የቤቱ ባለቤት ቤን የተባለ ሰው እንደሚመጣ እንደነገራቸውና ከመጣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የተዘጋጀ መጽሐፍ ተቀብለው እንዲያስቀምጡለት አጥብቆ እንዳሳሰባቸው ገለጹልን። እኛም ደስ ብሎን የመጽሐፉን አንድ ቅጂ ተውንለት። ከዚያም አውቶቡስ ተሳፍረን ካረን ወደምታስጠናቸው አንዲት ፍላጎት ያሳዩ ሴት ቤት ሄድን።

በተጨናነቁት መንገዶች መካከል ስንጓዝ ካረን ሴትዮዋን ያገኘቻት በአንድ ታክሲ ውስጥ ከሌሎች ብዙ ተሳፋሪዎች ጋር አብረው ሲጓዙ እንደሆነ ገለጸችልን። በጉዞው ላይ እንዳሉ አንድ ትራክት አውጥታ ለሴትዮዋ ሰጠቻት። ሴትዮዋ ትራክቱን አንብባ ስትጨርስ ሌላም እንድትሰጣት ጠየቀቻት። ይኼኛውንም በከፍተኛ ጉጉት አንብባ ጨረሰች። የሚወርዱበት ቦታ ሲደርሱ ካረን ሴትዮዋን ቤቷ ድረስ ሄዳ ለመጠየቅ ዝግጅት አደረገች። ብዙም ሳይቆይ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተባለው ብሮሹር ውጤታማ ጥናት መምራት ጀመረች። ዛሬ አምስተኛውን ክፍል ታስጠናታለች።

ከሚስዮናውያኑ ጋር በመስክ አገልግሎት አስደሳች ጊዜ ብናሳልፍም የሚስዮናውያንን ሥራ በተመለከተ አሁንም ያልተመለሱልን አንዳንድ ጥያቄዎች ነበሩ። ጋባዦቻችን ቤት ከተመለስን በኋላ ቀለል ያለ ምግብ እየተመገብን ጥያቄዎቻችንን እንደሚመልሱልን ነገሩን።

ሚዛናቸውን መጠበቅ የቻሉት እንዴት ነው?

እንቁላል ጥብስ፣ ዳቦና ፎርማጆ እየተመገብን ስለ ሚስዮናዊ ሕይወት አንዳንድ ተጨማሪ ነገሮች ተገነዘብን። ብዙውን ጊዜ ሰኞ ሁሉም ሚስዮናውያን የሚያርፉበት ወይም የግል ጉዳዮቻቸውን የሚያከናውኑበት ዕለት ነው። አብዛኞቹ ሚስዮናውያን ቀኑን ለቤተሰቦቻቸውና ለጓደኞቻቸው ደብዳቤ በመጻፍ ያሳልፉታል። ከአገራቸው የሚመጣ ዜና በጣም የሚናፍቁት ነገር ነው፤ ሚስዮናውያኑ ደብዳቤ መጻፍም ሆነ መቀበል ያስደስታቸዋል።

ሚስዮናውያኑ አንድ ላይ የሚሠሩና የሚኖሩ በመሆናቸው እርስ በርሳቸው በመቀራረብና ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች በመወያየት ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት መስመር እንዲኖራቸው ማድረጋቸው የግድ አስፈላጊ ነው። ለዚህም እንዲረዳቸው አዘውትረው የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚያደርጉ ከመሆኑም በላይ ዘወትር ሰኞ ማታ አንድ ላይ ሆነው በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሉ። ቤን የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ሚስዮናውያን አንድ ላይ በሚኖሩበት ጊዜ በመካከላቸው ጥቃቅን የአስተሳሰብ ልዩነቶች መፈጠራቸው እንደማይቀር ከገለጸ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ለማጥናት የተደረገው ዝግጅት በመካከላቸው ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን እንደሚያደርግ ተናገረ። ለራስ ከፍ ያለ ግምት ከመስጠት መቆጠብም እንደሚረዳ ጠበቅ አድርጎ ገለጸ።

ትህትናም የግድ አስፈላጊ ነው። ሚስዮናውያን ወደ ውጭ የሚላኩት እንዲያገለግሉ እንጂ እንዲገለገሉ አይደለም። በየትኛውም ቋንቋ ለመናገር በጣም ከባድ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ በተለይ አንድ ሰው ሳያውቅ ለሠራው ወይም ለተናገረው ነገር “ይቅርታ” መጠየቅ እንደሆነ ሚስዮናውያኑ ተገንዝበዋል። ቤን ባሏ ለሠራው ስህተት ይቅርታ በመጠየቅ ከፍተኛ ጥፋት ያስከትል የነበረውን ሁኔታ ያረገበችውን የአቢጋኤልን ምሳሌ አስታወሰን። (1 ሳሙኤል 25:23-28) ‘በሰላም የመኖር’ ችሎታ ጥሩ ሚስዮናዊ ለመሆን የሚያስችል አንዱ ቁልፍ ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 13:11

ሚስዮናውያኑ ቤተሰቡን የሚመለከቱ ጉዳዮችን አንስተው ለመወያየትና በፕሮግራም ረገድ በተደረጉ ለውጦች ላይ ለመነጋገር በወር አንድ ጊዜ ይሰበሰባሉ። ከዚያም በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀ ማጣጣሚያ ይመገባሉ። ይህ ተግባራዊና ጠቃሚ ዝግጅት እንደሆነ ይሰማናል።

እራት በልተን ስንጨርስ በሚስዮናውያኑ ቤት ውስጥ አጭር ጉብኝት አደረግን። ቤቱ መጠነኛ ቢሆንም እንኳ ሚስዮናውያኑ ቤቱን በንጽሕና ለመያዝ ከፍተኛ ትብብር እንደሚያደርጉ አስተውለናል። ቤቱ ውስጥ አንድ ማቀዝቀዣ፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽንና የምግብ ማብሰያ ምድጃ አለ። ካረን እንደዚህ ያለ የአየር ጠባይ ባለባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ውስጥ አየር ማስማሚያ መሣሪያዎች እንደሚኖሩም ገለጸችልን። ተስማሚ መኖሪያ፣ የተመጣጠነ ምግብና ቀለል ያሉ የጤና አጠባበቅ ዘዴዎች ሚስዮናውያኑ ጤናማና ውጤታማ ሆነው እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል።

አዎንታዊ ገጽታ ላይ ማተኮር

ባየነው በእያንዳንዱ ነገር ተደንቀናል። እኛም ሚስዮናዊ መሆን እንችል ይሆን? እንዴት ማወቅ እንችላለን? ጋባዦቻችን ልናስብባቸው የሚገቡ ጥቂት ነጥቦች አካፈሉን።

በመጀመሪያ ደረጃ ክርስቲያን ሚስዮናውያን ወደ ውጭ አገር የሚሄዱት ጀብዱ ለመፈጸም ሳይሆን ስለ አምላክ አስደናቂ ተስፋዎች የመማር ፍላጎት ያላቸውን ቅን ሰዎች ለማግኘት እንደሆነ ገለጹልን። ሚስዮናውያን በየወሩ ቢያንስ 140 ሰዓታት በመስክ አገልግሎት ማሳለፍ ስለሚኖርባቸው ለአገልግሎቱ ፍቅር ማዳበር የግድ አስፈላጊ ነው።

ይሁን እንጂ እባቦቹ፣ እንሽላሊቶቹና ትኋኖቹስ? እነዚህ ነገሮች በብዙ ሚስዮናዊ ምድቦች ውስጥ ሊገኙ ቢችሉም ሚስዮናውያኑ ወዲያው እንደሚለምዷቸው ቤን ነገረን። አክሎም እያንዳንዱ የሚስዮናዊ ምድብ የራሱ የሆኑ አስደሳች ጎኖች ያሉት ሲሆን ከጊዜ በኋላ ሚስዮናውያኑ በምድባቸው አዎንታዊ ገጽታ ላይ ማተኮር እንደሚጀምሩ ገለጸልን። መጀመሪያ ላይ “እንግዳ” ተደርገው የታዩ ነገሮች ትንሽ ቆይተው የተለመዱ አልፎ ተርፎም አስደሳች ይሆናሉ። ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ ለብዙ ዓመታት በሚስዮናዊነት ካገለገለች በኋላ በቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ ምክንያት ወደ አገሯ ለመመለስ የተገደደች አንዲት ሚስዮናዊ ምድቧን ስትለቅቅ የተሰማት ሐዘን ከዓመታት በፊት ሚስዮናዊ ሆና አገሯን ስትለቅቅ ከተሰማት ሐዘን እንደሚበልጥ ተናግራለች። ሚስዮናዊ ምድቧ እንደ ቤቷ ሆኖላት ነበር።

አንተስ ዝግጁ ነህ?

ቤንና ካረን ብዙ ልናስብባቸው የሚገቡ ቁም ነገሮች አካፍለውናል። አንተስ? ሚስዮናዊ ሆኖ በባዕድ አገር ስለማገልገል አስበህ ታውቃለህ? ከሆነ ከምትገምተው በላይ ወደዚያ ግብ ቀርበህ ሊሆን ይችላል። ሚስዮናዊ ለመሆን የሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ፍቅር ማዳበርና ሰዎችን በመርዳት መደሰት ናቸው። ሚስዮናውያን ከሰው በላይ ችሎታ ያላቸው ፍጡራን ሳይሆኑ እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን አስታውስ። በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ ለመሥራት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እያንዳንዱን ቀን የዕለት ጥቅስ ውይይት በማድረግ ይጀምራሉ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚስዮናዊነት ሕይወት በጣም አርኪ ሊሆን ይችላል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ የአፍሪካ ቦታዎች