በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ ፍቅር ማን ይለየናል?

ከአምላክ ፍቅር ማን ይለየናል?

ከአምላክ ፍቅር ማን ይለየናል?

“እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።”—⁠1 ዮሐንስ 4:19

1, 2. (ሀ) እንደምንወደድ ማወቃችን ለእኛ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ከሁሉ በላይ የምንፈልገው ማን እንዲወድደን ነው?

 እንደምትወደድ ማወቅህ ለአንተ ምን ትርጉም አለው? ልጅ አዋቂ ሳይል መላው የሰው ልጅ ፍቅር ሲያገኝ ይለመልማል። እናቱ በፍቅር እቅፍ አድርጋ የያዘችው ሕፃን አይተሃል? በዙሪያው የፈለገው ነገር ቢከናወን ይህ ጨቅላ ሕፃን በምትወደው እናቱ እቅፍ ውስጥ ሆኖ ፈገግታ የሚነበብባቸውን ዓይኖቿን ሲመለከት ውስጡ በእርጋታና ሰላም ይሞላል። ከፍተኛ የስሜት መለዋወጥ ይታይበት የነበረውን የጉርምስና ዕድሜህን ታስታውሳለህ? (1 ተሰሎንቄ 2:7) አንዳንድ ጊዜ ምን እንደምትፈልግ ሌላው ቀርቶ ምን እንደሚሰማህ ለማወቅ እንኳ ትቸገር ነበር። ሆኖም አባትህና እናትህ እንደሚወዱህ ማወቅህ እፎይታ አምጥቶልህ መሆን አለበት! ማንኛውንም ዓይነት ችግር ልትነግራቸው ወይም ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ ልትጠይቃቸው እንደምትችል ማወቅህ ጥቅም አላስገኘልህም? በእርግጥም በሕይወታችን ውስጥ በዋነኝነት ከሚያስፈልጉን ነገሮች አንዱ መወደድ ነው። ሌሎች እንደሚወዱን ማወቃችን ዋጋ እንዳለን ሆኖ እንዲሰማን ያደርገናል።

2 ወላጆች የሚያሳዩት ዘላቂ ፍቅር የተስተካከለና ሚዛኑን የጠበቀ ሕይወት እንድንመራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ሆኖም ሰማያዊው አባታችን ይሖዋ እንደሚወድደን እርግጠኞች መሆናችን ለመንፈሳዊና ለስሜታዊ ደህንነታችን ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። አንዳንዶቹ የዚህ መጽሔት አንባቢዎች ከልብ በሚያስቡላቸው ወላጆች አላደጉ ይሆናል። የአንተ ሁኔታ እንደዚያ ከሆነ አይዞህ። ያጣኸውን ወይም የጎደለብህን የወላጅ ፍቅር የአምላክ ታማኝ ፍቅር ያሟላልሃል።

3. ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚወድዳቸው ያረጋገጠላቸው እንዴት ነው?

3 ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት አንዲት እናት ልጅዋን ‘ልትረሳ’ ብትችል እንኳ እርሱ ግን ሕዝቡን እንደማይረሳ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 49:15) በተመሳሳይም ዳዊት “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” በማለት በትምክህት ተናግሯል። (መዝሙር 27:10) ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ራስህን ወስነህ ከይሖዋ አምላክ ጋር ዝምድና የመሠረትክ ከሆንክ ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ለአንተ ያለው ፍቅር ማንም ሰብዓዊ ሰው ለአንተ ሊኖረው ከሚችለው ፍቅር እጅግ የላቀ እንደሆነ ሁልጊዜ ማስታወስ ይኖርብሃል!

በአምላክ ፍቅር ራስህን ጠብቅ

4. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አምላክ ለእነርሱ ፍቅር እንዳለው ያረጋገጡት እንዴት ነበር?

4 የይሖዋን ፍቅር ለመጀመሪያ ጊዜ የቀመስከው መቼ ነው? አንተ የተሰማህ ስሜት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ከተሰማቸው ስሜት ጋር በመጠኑም ቢሆን እንደሚመሳሰል የታወቀ ነው። ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ 5ኛ ምዕራፍ በአንድ ወቅት ከአምላክ ርቀው የነበሩ ኃጢአተኞች እንዴት የይሖዋን ፍቅር ሊቀምሱ እንደቻሉ ውብ በሆነ መንገድ ይገልጻል። ቁጥር 5 ላይ “በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን . . . ፈሰሰ” የሚል እናነባለን። በቁጥር 8 ላይ ጳውሎስ “ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” በማለት አክሎ ተናግሯል።

5. የአምላክን ጥልቅ ፍቅር ማድነቅ የጀመርከው እንዴት ነው?

5 በተመሳሳይም ከአምላክ ቃል እውነትን ማጥናትና ባጠናኸው ላይ እምነት ማሳደር ስትጀምር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በልብህ ውስጥ መሥራት ጀመረ። ይሖዋ የሚወድደውን ልጁን በመላክ ለአንተ እንዲሞት በማድረግ የፈጸመውን ታላቅ ተግባር ቀስ በቀስ ማድነቅ ጀመርክ። በዚህ መንገድ ይሖዋ የሰውን ዘር ምን ያህል እንደሚወድድ እንድትገነዘብ ረዳህ። ከይሖዋ የራቅህ ኃጢአተኛ ሆነህ ብትወለድም እንኳ ሰዎች ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲኖራቸውና ጻድቃን ሆነው እንዲቆጠሩ ያደረገውን ዝግጅት ስትገነዘብ ልብህ በጥልቅ አልተነካም? ለይሖዋ ፍቅር አላደረብህም?​—⁠ሮሜ 5:10

6. አንዳንድ ጊዜ ከይሖዋ እንደ ራቅን ሆኖ የሚሰማን ለምን ሊሆን ይችላል?

6 በሰማዩ አባትህ ፍቅር በመሳብህና በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ትችል ዘንድ በአኗኗርህ ላይ ለውጥ በማድረግህ ራስህን ለአምላክ ወሰንክ። አሁን ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ዝምድና መሥርተሃል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ከአምላክ እንደ ራቅህ ሆኖ ይሰማሃል? ይህ በማናችንም ላይ ሊደርስ ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ እንደማይለወጥ ምንጊዜም አስታውስ። ፀሐይ ለምድር ሙቀትና ብርሃን መስጠቷን እንደማታቋርጥ ሁሉ የአምላክ ፍቅርም ቋሚና የማይለዋወጥ ነው። (ሚልክያስ 3:6፤ ያዕቆብ 1:17) በሌላው በኩል ግን እኛ ለጊዜውም ቢሆን ልንለወጥ እንችላለን። ምድር በምትዞርበት ጊዜ ግማሹ የፕላኔቷ አካል በጨለማ ይሸፈናል። በተመሳሳይም እኛ በተወሰነ መጠን እንኳ ከአምላክ ዞር ብንል ከእርሱ ጋር ያለን ዝምድና እንደቀዘቀዘ ሊሰማን ይችላል። እንዲህ ያለውን ሁኔታ ለማስተካከል ምን ልናደርግ እንችላለን?

7. ራስን መመርመር ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ እንድንኖር የሚረዳን እንዴት ነው?

7 ከአምላክ ፍቅር በተወሰነ መጠን እንደራቅን ሆኖ ከተሰማን ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘ለአምላክ ፍቅር የነበረኝ አድናቆት ቀንሶ ይሆን? እምነቴ እየተዳከመ እንዳለ የሚጠቁሙ የተለያዩ ነገሮችን በማድረግ ሕያውና አፍቃሪ ከሆነው አምላክ ቀስ በቀስ ሸርተት ማለት ጀምሬ ይሆን? ትኩረቴ ያረፈው “በመንፈሳዊ ነገሮች” ላይ ሳይሆን “በሥጋዊ ነገሮች” ላይ ነው?’ (ሮሜ 8:5-8፤ ዕብራውያን 3:12) ከይሖዋ እንደ ራቅን ሆኖ ከተሰማን ሁኔታዎቹን ለማስተካከል፣ ከእርሱ ጋር የቀረበና ሞቅ ያለ ዝምድና ለመመሥረት እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን። ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል። (ያዕቆብ 4:8) ይሁዳ “ወዳጆች ሆይ፣ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ . . . በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ” በማለት የተናገራቸውን ቃላት በጥብቅ ተከተል።​—⁠ይሁዳ 20, 21

የሁኔታዎች መለወጥ በአምላክ ፍቅር ላይ ለውጥ አያስከትልም

8. በሕይወታችን ውስጥ ምን ዓይነት ድንገተኛ ለውጦች ሊከሰቱ ይችላሉ?

8 በዚህ ሥርዓት በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ሁኔታዎች ተለዋዋጭ ናቸው። ንጉሥ ሰሎሞን ‘ጊዜና አጋጣሚ ሁላችንን ይገናኘናል’ በማለት ተናግሯል። (መክብብ 9:11 NW ) በአንድ ጀንበር ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ ሊለወጥ ይችላል። ዛሬ ሙሉ ጤና የነበረን ሰዎች ነገ በጠና ልንታመም እንችላለን። ዛሬ አስተማማኝ ሥራ አለኝ ብለን ስናስብ የነበርን ሰዎች ነገ ሥራ አጥ ልንሆን እንችላለን። ሞት የምንወደውን ሰው በድንገት ሊነጥቅብን ይችላል። በአንድ አካባቢ በሰላም ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች በድንገት ከባድ ስደት ሊደርስባቸው ይችላል። ምናልባት በሐሰት ልንከሰስና በዚህም የተነሳ አንድ ዓይነት ግፍ ሊፈጸምብን ይችላል። አዎን፣ ሕይወት ዋስትና ያለው ወይም ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ አይደለም።​—⁠ያዕቆብ 4:13-15

9. የሮሜ ምዕራፍ 8ን የተወሰነ ክፍል መመርመሩ ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው?

9 አሳዛኝ ሁኔታዎች በሚደርሱብን ጊዜ እንደተተውን አልፎ ተርፎም አምላክ ለእኛ ያለው ፍቅር እንደቀነሰ ሊሰማን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በሁላችን ላይ ሊደርሱ ስለሚችሉ በሮሜ ምዕራፍ 8 ላይ የሚገኙትን በጣም አጽናኝ የሆኑ የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት በጥንቃቄ ብንመረምር ጥሩ ይሆናል። እነዚህ ቃላት የተጻፉት በመንፈስ ለተቀቡ ክርስቲያኖች ነው። ሆኖም በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ ከክርስትና ዘመን በፊት ይኖር እንደነበረው እንደ አብርሃም ጻድቅ ወዳጆቹ እንደሆኑ አድርጎ ለሚመለከታቸው ለሌሎች በጎችም ይሠራሉ።​—⁠ሮሜ 4:20-22፤ ያዕቆብ 2:21-23

10, 11. (ሀ) ጠላቶች በአምላክ ሕዝቦች ላይ አንዳንድ ጊዜ የሚያነሷቸው ክሶች ምንድን ናቸው? (ለ) እንደነዚህ ያሉት ክሶች ክርስቲያኖችን እምብዛም የማያስጨንቋቸው ለምንድን ነው?

10 ሮሜ 8:​31-34ን አንብብ። ጳውሎስ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?” በማለት ይጠይቃል። እርግጥ ነው ሰይጣንና እሱ የሚቆጣጠረው ክፉ ዓለም ይቃወሙናል። ጠላቶቻችን በሐሰት ከስሰው ፍርድ ቤት ሊያቆሙን ይችላሉ። አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጋጩ የሕክምና ዓይነቶች እንዲሰጣቸው ወይም አረማዊ በሆኑ ክብረ በዓሎች ላይ እንዲካፈሉ ባለመፍቀዳቸው ምክንያት ለልጆቻቸው ፍቅር እንደሌላቸው ተደርገው ይከሰሳሉ። (ሥራ 15:28, 29፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14-16) ሌሎች ታማኝ ክርስቲያኖች ደግሞ ወደ ጦር ሜዳ አንዘምትም አንገድልም ወይም በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ አንገባም በማለታቸው ሕዝብን በመንግሥት ላይ ያሳምፃሉ ተብለው በሐሰት ተከስሰዋል። (ዮሐንስ 17:16) አንዳንድ ተቃዋሚዎች የይሖዋ ምሥክሮች አደገኛ ኑፋቄዎች እንደሆኑ አድርገው በሐሰት በመክሰስ በመገናኛ ብዙኃን የምሥክሮቹን ስም የሚያጠፉ የሐሰት ወሬዎችን አሰራጭተዋል።

11 ይሁን እንጂ በሐዋርያት ዘመን “ስለዚህ ወገን [“ኑፋቄ፣” NW ] በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአል” ተብሎ እንደተነገረ አስታውሱ። (ሥራ 28:22) ይሁን እንጂ በሐሰት መከሰሳቸው ለውጥ ያመጣ ይሆን? በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ ባላቸው እምነት መሠረት እውነተኛ ክርስቲያኖችን ጻድቃን ናችሁ ብሎ የሚፈርድላቸው አምላክ ነው። ይሖዋ በጣም ውድ የሆነ ስጦታ ማለትም የሚወደውን ልጁን ከሰጣቸው በኋላ ለአምላኪዎቹ ፍቅር ማሳየቱን ለምን ያቆማል? (1 ዮሐንስ 4:10) ከሞት የተነሳውና በአምላክ ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ለክርስቲያኖች ዘወትር ይማልዳል። ክርስቶስ ለተከታዮቹ እንዳይቆም ሊያደርግ ወይም አምላክ ለታማኝ አገልጋዮቹ እንዳይፈርድላቸው ሊቃወም የሚችል ማን ይኖራል? ማንም ሊኖር አይችልም!​—⁠ኢሳይያስ 50:8, 9፤ ዕብራውያን 4:15, 16

12, 13. (ሀ) ከአምላክ ፍቅር ምን ሁኔታዎች ወይም ምን ነገሮች ሊለዩን አይችሉም? (ለ) ዲያብሎስ በእኛ ላይ መከራ የሚያመጣበት ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው? (ሐ) ክርስቲያኖች ሙሉ በሙሉ ድል አድራጊ የሚሆኑት ለምንድን ነው?

12 ሮሜ 8:​35-37ን አንብብ። በግለሰብ ደረጃ እኛን ከይሖዋና ከልጁ ከክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሊለየን የሚችል አንዳች ኃይል ሊኖር ይችላልን? ሰይጣን በምድራዊ ወኪሎቹ በመጠቀም በክርስቲያኖች ላይ የተለያዩ ችግሮችን ሊፈጥር ይችላል። ባለፉት ዘመናት በብዙ አገሮች የሚኖሩ በርካታ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከባድ ስደት ደርሶባቸዋል። በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ ቦታዎች የሚኖሩ ወንድሞቻችን በየዕለቱ አስከፊ ከሆነ የኑሮ ሁኔታ ጋር ይታገላሉ። አንዳንዶች በረሃብ ይሠቃያሉ ወይም የሚለብሱት ልብስ በማጣት ይቸገራሉ። ዲያብሎስ እንዲህ ያሉ መከራዎችን የሚያመጣው ለምንድን ነው? አንዱ ዓላማው እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎችን ተስፋ ለማስቆረጥ ነው። ሰይጣን፣ አምላክ ለእኛ ያለው ፍቅር እንደቀዘቀዘ ሊያሳምነን ይጥራል። ይሁን እንጂ ይህ እውነት ነውን?

13 መዝሙር 44:​22ን ጠቅሶ እንደ ጻፈው እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም በጽሑፍ የሠፈረውን የአምላክ ቃል አጥንተናል። ስለ አምላክ ስም ስንል እነዚህ ሁሉ በእኛ ማለትም ‘በበጎቹ’ ላይ እንደሚደርሱ እናውቃለን። የአምላክ ስም መቀደስና የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊነቱ መረጋገጥ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ምክንያት ለእኛ ፍቅር ስለ ሌለው ሳይሆን በእነዚህ ዋና ዋና አከራካሪ ጉዳዮች የተነሳ ነው። ምንም ያህል አስከፊ ሁኔታዎች ቢደርሱብን አምላክ ለእያንዳንዳችን ያለውን ፍቅር ጨምሮ ለሕዝቡ ፍቅር ማሳየቱን እንዳላቆመ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ጽኑ አቋማችንን ጠብቀን ከኖርን አንዳንድ ጊዜ የተሸነፍን ቢመስለን እንኳ አሸናፊዎች እንሆናለን። አስተማማኝ የሆነው የአምላክ ጽኑ ፍቅር ብርታት ሰጥቶናል እንዲሁም ጠብቆናል።

14. ክርስቲያኖች መከራ ቢደርስባቸውም ጳውሎስ በአምላክ ፍቅር ላይ ጽኑ እምነት እንዲኖረው ያደረገው ምንድን ነው?

14 ሮሜ 8:​38, 39ን አንብብ። ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ምንም ነገር ከአምላክ ፍቅር ሊለያቸው እንደማይችል እርግጠኛ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ጳውሎስ በአገልግሎቱ ያጋጠሙት ተሞክሮዎች መከራ አምላክ ለእኛ ፍቅር ማሳየቱን እንዲያቆም ፈጽሞ ሊያደርጉት እንደማይችሉ የነበረውን ጽኑ እምነት እንዳጠናከሩለት ምንም ጥርጥር የለውም። (2 ቆሮንቶስ 11:23-27፤ ፊልጵስዩስ 4:13) እንዲሁም ጳውሎስ የይሖዋን ዘላለማዊ ዓላማና ለጥንት ሕዝቦቹ ያደረገላቸውን ነገሮች ያውቅ ነበር። አምላክ ለታማኝ አገልጋዮቹ ያለው ፍቅር በሞት ድል ሊደረግ ይችል ይሆን? በጭራሽ! በሞት ያንቀላፉት እነዚህ ታማኞች ፍጹም በሆነው በአምላክ አእምሮ ውስጥ የሚታወሱ በመሆናቸው ጊዜው ሲደርስ ከሞት ያስነሳቸዋል።​—⁠ሉቃስ 20:37, 38፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22-26

15, 16. አምላክ ለታማኝ አገልጋዮቹ ያለውን ፍቅር ከመግለጽ ሊያግዱት የማይችሉትን አንዳንድ ነገሮች ጥቀስ።

15 ለከፋ አካላዊ ጉዳት የሚዳርግ አደጋን፣ የማይድን በሽታን ወይም ከባድ የኢኮኖሚ ችግርን የመሰሉ መጥፎ አጋጣሚዎች ቢደርሱብን እንኳ አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር ሊያጠፉ አይችሉም። በኋላ ዓመፀኛ መልአክ እንደሆነው እንደ ሰይጣን ያሉ ኃያል መላእክትም ቢሆኑ ይሖዋ ለእርሱ ያደሩ አገልጋዮቹን መውደዱን እንዲያቆም ሊያደርጉት አይችሉም። (ኢዮብ 2:3) መንግሥታት የአምላክ አገልጋዮች እገዳ እንዲጣልባቸው፣ እንዲታሰሩና እንዲንገላቱ እንዲሁም ኅብረተሰቡ እንዲያገላቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 4:13) ብሔራት የሚያነሳሱት እንዲህ ያለው የተሳሳተ ጥላቻ ሰዎች በእኛ ላይ ተቃውሞ እንዲሰነዝሩ ሊያደርግ ቢችልም የዓጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ እኛን እንዲተወን ሊያደርግ ግን አይችልም።

16 ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ጳውሎስ “ያለውም ቢሆን” በማለት ከጠራቸው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከሚደርሱ ክስተቶች፣ ሁኔታዎችና ክንውኖች ወይም ወደፊት ሊመጡ ከሚችሉ ነገሮች መካከል አንዱም ቢሆን አምላክ ከሕዝቡ ጋር የመሠረተውን የጠበቀ ግንኙነት እንዲያላላ ሊያደርጉት ይችላሉ ብለን መፍራት አይኖርብንም። ምንም እንኳ ምድራዊና ሰማያዊ ኃይሎች ጦርነት የከፈቱብን ቢሆንም የአምላክ ታማኝ ፍቅር ደግፎ ያቆመናል። ጳውሎስ ጠበቅ አድርጎ እንደገለጸው “ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን” የአምላክን ፍቅር ሊያግድ አይችልም። አዎን፣ ተስፋ ሊያስቆርጥ የሚችል ማንኛውም ነገር ወይም በእኛ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል የትኛውም ኃይል ከአምላክ ፍቅር ሊለየን አይችልም። እንዲሁም ፈጣሪ ከታማኝ አገልጋዮቹ ጋር የመሠረተውን ዝምድና የትኛውም ፍጡር ሊበጥስ አይችልም። የአምላክ ፍቅር ፈጽሞ አይወድቅም፤ ለዘላለም ይኖራል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:8

የአምላክን ፍቅራዊ ደግነት ለዘላለም ከፍ አድርገህ ተመልከት

17. (ሀ) የአምላክን ፍቅር ማግኘት ‘ከሕይወት የሚሻል’ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የአምላክን ፍቅራዊ ደግነት ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

17 የአምላክን ፍቅር ምን ያህል ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ? ዳዊት “ምሕረትህ [“ፍቅራዊ ደግነትህ፣” NW ] ከሕይወት ይሻላልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል። እንዲህ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፣ በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ” ብሎ እንደጻፈው ይሰማሃል? (መዝሙር 63:3, 4) ከአምላክ ፍቅርና ታማኝ ወዳጅነት ጋር የሚወዳደር ይህ ዓለም ሊሰጥ የሚችለው ነገር ይኖራልን? ለምሳሌ ያህል ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና በመመሥረት ከሚገኘው የአእምሮ ሰላምና ደስታ ይሻላልን? (ሉቃስ 12:15) አንዳንድ ክርስቲያኖች ይሖዋን ከመካድ ወይም ከመሞት አንዱን እንዲመርጡ የሚያደርግ ፈተና ገጥሟቸዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ ማጎሪያ ካምፕ የነበሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ ሁኔታ ደርሶባቸው ነበር። በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር አብዛኞቹ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ሞት የሚያስከትልባቸው ቢሆን እንኳ በአምላክ ፍቅር ውስጥ ለመኖር መርጠዋል። በአምላክ ፍቅር ውስጥ በታማኝነት ለመኖር የመረጡ ሁሉ ወደፊት አምላክ ይህ ዓለም ፈጽሞ ሊሰጥ የማይችለውን የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው በእርግጠኝነት ሊጠባበቁ ይችላሉ። (ማርቆስ 8:34-36) ሆኖም የዘላለም ሕይወት ማግኘት ብቻ አይደለም።

18. የዘላለም ሕይወት ያን ያህል የሚያጓጓ የሆነው ለምንድን ነው?

18 ምንም እንኳ ከይሖዋ መመሪያ ርቆ ለዘላለም መኖር የማይቻል ቢሆንም ያለ ፈጣሪ ረዥም ዕድሜ መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። ሕይወታችን ባዶና ዓላማ ቢስ ይሆን ነበር። ይሖዋ በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሕዝቦቹ የሚሠሩት አርኪ የሆነ ሥራ ሰጥቷቸዋል። ታላቁ የዓላማ አምላክ ይሖዋ የዘላለም ሕይወት ሲሰጠን ልንማራቸውና ልንሠራቸው የምንችላቸው ቁጥር ስፍር የሌላቸው ማራኪና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችንም እንደሚሰጠን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (መክብብ 3:11) ከፊታችን በሚጠብቀን ሺህ ዓመት ‘ጥልቅ የሆኑትን የእግዚአብሔርን ባለ ጠግነት፣ ጥበብና እውቀት’ መርምረን መጨረስ እንደማንችል የታወቀ ነው።​—⁠ሮሜ 11:33

አብ ይወድድሃል

19. ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ከመለየቱ በፊት ምን ነገር አረጋገጠላቸው?

19 በኒሳን 14, 33 እዘአ ኢየሱስ ከአሥራ አንድ ታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ወደፊት ለሚጠብቃቸው ነገር ለማዘጋጀት በርካታ ነገሮችን ነገራቸው። በመከራው ሁሉ ከኢየሱስ ጋር ጸንተዋል፤ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወድዳቸው ተገንዝበዋል። (ሉቃስ 22:28, 30፤ ዮሐንስ 1:16፤ 13:1) ከዚያም ኢየሱስ “አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋል” በማለት አረጋገጠላቸው። (ዮሐንስ 16:27) የሰማዩ አባታቸው በርኅራኄ እንደሚመለከታቸው ከእነዚህ ቃላት ተገንዝበው መሆን አለበት!

20. ምን ለማድረግ ቆርጠሃል? ስለ ምን ነገርስ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ?

20 ይሖዋን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉ ብዙዎች ዛሬ በመካከላችን ይገኛሉ። ይህ የነገሮች ሥርዓት ከመደምደሙ በፊት ተጨማሪ ብዙ መከራዎች እንደሚደርሱብን የተረጋገጠ ነው። የሚደርስብህ መከራ ወይም ችግር አምላክ ለአንተ ያለውን ታማኝ ፍቅር እንድትጠራጠር እንዲያደርግህ ፈጽሞ አትፍቀድ። ይሖዋ እንደሚወድድህ ምንም ጥርጥር የለውም። (ያዕቆብ 5:11) ስለዚህ ሁላችንም የአምላክን ትእዛዞች በታማኝነት እየጠበቅን የበኩላችንን ማድረጋችንን እንቀጥል። (ዮሐንስ 15:8-10) የአምላክን ስም ለማወደስ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ሁሉ እንጠቀምባቸው። በጸሎትና ቃሉን በማጥናት ወደ ይሖዋ እየቀረብን መሄዳችንን ለመቀጠል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ማጠናከር ይኖርብናል። ይሖዋን ለማስደሰት የቻልነውን ሁሉ የምናደርግ ከሆነ የነገው ቀን ምንም ያምጣ ምን በሰላም እንኖራለን እንዲሁም ዘወትር በማይወድቀው ፍቅሩ ሙሉ በሙሉ እንታመናለን።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:14

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• መንፈሳዊና ስሜታዊ ሚዛናችንን ለመጠበቅ በተለይ የማንን ፍቅር ማግኘት ይኖርብናል?

• ምን ነገሮች ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለውን ፍቅር ሊገድቡበት አይችሉም?

• የይሖዋን ፍቅር ማግኘት ‘ከሕይወት የሚሻል የሆነው’ ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአምላክ ፍቅር እንደራቅን ሆኖ ከተሰማን ነገሮችን ለማስተካከል እርምጃ መውሰድ እንችላለን

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ስደት የሚደርስበት ለምን እንደሆነ ያውቅ ነበር