በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለምን የተሻለ መኖሪያ ማድረግ ይቻላልን?

ዓለምን የተሻለ መኖሪያ ማድረግ ይቻላልን?

ዓለምን የተሻለ መኖሪያ ማድረግ ይቻላልን?

“ፖለቲካ የተፈረካከሰውን የሕብረተሰብ መዋቅር መልሶ መገንባት አልቻለም። ባሕላዊ የሥነ ምግባር እሴቶችን መልሶ የመገንባት አቅሙም ተዳክሟል። ከሁሉ የተሻሉ ናቸው የተባለላቸው ፖሊሲዎች ቀደም ሲል ለጥናታዊ ቅርርብና ለጋብቻ ይሰጥ የነበረውን ከፍተኛ ግምት መልሰው ማምጣትም ሆነ አባቶች ለልጆቻቸው ይበልጥ ኃላፊነት እንዲሰማቸው ማድረግ አልቻሉም። ድሮ ድሮ ያስደነግጡ ወይም ያሳፍሩ የነበሩ ነገሮች ዛሬ በዚያ መልክ እንዲታዩ ማድረግም አልቻሉም። . . . በጊዜያችን ያሉትን አብዛኞቹን የሥነ ምግባር ችግሮች ሕግ ሊያስወግዳቸው አልቻለም።”

አንተስ የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አማካሪ ከተናገሩት ሐሳብ ጋር ትስማማለህ? የምትስማማ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በስግብግብነት፣ በቤተሰብ መካከል የተፈጥሮ ፍቅር በመጥፋቱ፣ የሥነ ምግባር እሴቶች በማዝቀጣቸው፣ በመሃይምነትና በሌሎች የሕብረተሰቡን መዋቅር በመሸርሸር ላይ ባሉ ነገሮች የተነሣ ለተከሰቱት ችግሮች መፍትሄያቸው ምንድን ነው? አንዳንዶች ምንም መፍትሄ እንደሌለ ስለሚሰማቸው የራሳቸውን ኑሮ በማሻሻሉ ተግባር ላይ ይጠመዳሉ። ሌሎች ደግሞ አንድ ቀን የሰዎችን ልብ መማረክ የሚችልና ልዩ የመግዛት ችሎታ ያለው መሪ ምናልባትም ሃይማኖታዊ ሰው ይነሣና በትክክለኛው መንገድ ይመራናል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።

ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በፊት ሰዎች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ የተላከ መሆኑንና ብቃት ያለው መሪ ሊወጣው እንደሚችል በመገንዘባቸው ሊያነግሱት ፈልገው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ፍላጎታቸውን ሲገነዘብ ወዲያው አካባቢውን ትቶ ሄደ። (ዮሐንስ 6:14, 15) ከጊዜ በኋላም ለሮማዊው ገዥ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” ብሎታል። (ዮሐንስ 18:36) ሆኖም በዛሬው ጊዜ ተከታዮቹ ነን የሚሉትን የሃይማኖት መሪዎች ጨምሮ ይህ ዓይነቱ አቋም ያለው ሁሉም አይደለም። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በዓለም መሪዎች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር በመሞከር አሊያም ራሳቸው ፖለቲካዊ ሥልጣን በመጨበጥ የዓለምን ሁኔታ ለማሻሻል ጥረት አድርገዋል። በ1960ዎቹና በ70ዎቹ ዓመታት የተፈጸሙትን ክንውኖች በመመልከት ይህንን መገንዘብ እንችላለን።

ዓለምን ለማሻሻል የተደረጉ ሃይማኖታዊ ጥረቶች

በ1960ዎቹ መገባደጃ ላይ ላቲን አሜሪካ በሚገኙ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ምሁራን ለድሆችና ለተጨቆኑት መብት ተሟጋች ሆነው ቀረቡ። ይህንን ዓላማቸውን ዳር ለማድረስ ክርስቶስ አዳኝ የሆነው በመንፈሳዊ መስክ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካውና በኢኮኖሚውም መስክ ጭምር ነው የሚል አንድ ዓይነት ነጻ አውጪ መንፈሳዊ ትምህርት አዳበሩ። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሥነ ምግባር እሴቶች ማዝቀጥ በጥልቅ ያሳሰባቸው አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሞራል ማጆሪቲ የሚል ስያሜ የተሰጠው ድርጅት አቋቋሙ። የድርጅቱ ዓላማ ግብረ ገብነት ያላቸውንና ቤተሰብን የሚመለከቱ የሥነ ምግባር ደንቦች ማውጣት የሚችሉ ሰዎች የፖለቲካ ሥልጣን እንዲጨብጡ ማድረግ ነበር። በተመሳሳይም በብዙ ሙስሊም አገሮች ውስጥ ያሉ ቡድኖች ቁርአንን አጥብቀው በመከተል ሙስናንና ግፍን ለማስቆም ጥረት አድርገዋል።

የተሻለ ዓለም ለማምጣት የተደረጉት እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ውጤት እንዳስገኙ ሆኖ ይሰማሃል? እውነታዎቹ እንደሚያሳዩት የሥነ ምግባር እሴቶች እያዘቀጡ መሄዳቸውንም ሆነ ነጻ አውጪ መንፈሳዊ ትምህርት በስፋት በሚሰጥባቸው አገሮች እንኳ ሳይቀር በድሃና በሃብታም መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ እየሰፋ መምጣቱን ቀጥሏል።

ሞራል ማጆሪቲ በዩናይትድ ስቴትስ ዓላማውን ዳር ማድረስ ባለመቻሉ የድርጅቱ መሥራች የሆኑት ጄሪ ፋልዌል በ1989 ድርጅቱ እንዲፈርስ አድርገዋል። ሌሎች ድርጅቶች በቦታው ተተክተዋል። “ሞራል ማጆሪቲ” የተሰኘውን ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙት ፖል ዌሪች ክርስቲያኒቲ ቱዴይ በተባለ አንድ መጽሔት ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “እጩዎቻችን ሥልጣን ቢጨብጡም በጣም ያስፈልጋሉ ብለን ያመንባቸውን ፖሊሲዎች መተግበር ሳይችሉ ቀርተዋል።” አክለውም የሚከተለውን ጽፈዋል:- “የሕብረተሰቡ ባሕል እያዘቀጠ ሄዷል። የዛሬውን ያህል የባሕላዊ እሴቶች ቀውስ ገጥሞን አያውቅም። ቀውሱ እጅግ የከፋ ከመሆኑ የተነሣ ለፖለቲካ እንኳ የሚበገር አልሆነም።”

የዓምድ አዘጋጅና ደራሲ የሆኑት ካል ቶማስ ፖለቲካን ተጠቅሞ የሕብረተሰቡን ችግር ለመፍታት የተደረገው ጥረት ሊሳካ ያልቻለበትን መሠረታዊ ምክንያት ሲገልጹ የሚከተለውን ብለዋል:- “እውነተኛ ለውጥ የፖለቲካ ምርጫ በማሸነፍ ሳይሆን እያንዳንዱን ግለሰብ በመለወጥ የሚመጣ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ መሠረታዊ ችግሮቻችን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ እንጂ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስላልሆኑ ነው።”

ታዲያ ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚያስችሉ ቋሚ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በሌሉበት ዓለም ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው? ተደማጭነት ያላቸው ወይም በቅን ልቦና የተነሳሱ ሃይማኖታዊ ወይም ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ሰዎች የተሻለ ዓለም ማምጣት ካልቻሉ ማን ሊያመጣ ይችላል? በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደምናየው ለዚህ የሚሆን መልስ አለ። እንዲያውም ኢየሱስ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለም ብሎ እንዲናገር ያደረገው ዋነኛ ምክንያት የዚህን መልስ ይሰጠናል።

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

COVER: Dirty water: WHO/​UNICEF photo; globe: Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ልጆች:- UN photo; ሉል:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.