ይሖዋ የሚደሰትበት ልብ ይኑራችሁ
ይሖዋ የሚደሰትበት ልብ ይኑራችሁ
“አቤቱ፣ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፣ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።”—መዝሙር 51:10
1, 2. ስለ ልባችን የማወቅ ፍላጎት ሊያድርብን የሚገባው ለምንድን ነው?
ቁመቱ ለግላጋና መልከ መልካም ነው። ነቢዩ ሳሙኤል ገና ሲያየው በመልኩ ስለተማረከ ከሳኦል በኋላ ንጉሥ እንዲሆን አምላክ የመረጠው የሁሉም ታላቅ የሆነው ይህ የእሴይ ልጅ መሆን አለበት ብሎ ደመደመ። ይሁን እንጂ ይሖዋ “ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ . . . ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” በማለት ተናገረ። ይሖዋ የመረጠው “እንደ ልቡ የሆነ ሰው” የእሴይ የመጨረሻ ልጅ ዳዊት ሆኖ ተገኘ።—1 ሳሙኤል 13:14፤ 16:7
2 አምላክ በሌላ ወቅት “እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኩላሊትንም እፈትናለሁ” ብሎ እንደተናገረው የሰዎችን ልብ ማንበብ ይችላል። (ኤርምያስ 17:10) አዎን፣ “እግዚአብሔር . . . ልብን ይፈትናል።” (ምሳሌ 17:3) ይሁን እንጂ ይሖዋ የሚመረምረው በአንድ ሰው ውስጥ የሚገኘው ልብ ምንድን ነው? አምላክ የሚደሰትበት ልብ እንዲኖረን ምን ልናደርግ እንችላለን?
“የተሰወረ የልብ ሰው”
3, 4. “ልብ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዋነኝነት የተሠራበት በምን መንገድ ነው? ምሳሌዎች ስጥ።
3 “ልብ” የሚለው ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አንድ ሺህ ያህል ጊዜ ሰፍሮ ይገኛል። በአብዛኛው የተሠራበት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ለነቢዩ ሙሴ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ስጦታ ያመጡልኝ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ በገዛ እጁ ሊሰጠኝ በልቡ ከሚያምረው [“ልቡ ካነሳሳው፣” NW ] ሰው ሁሉ መባ ተቀበሉ።” ‘ልቡ ያነሳሳው ሁሉ’ ስጦታ ያመጣ ነበር። (ዘጸአት 25:2፤ 35:21) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው የምሳሌያዊው ልብ አንዱ ገጽታ ለድርጊት የሚገፋፋ ውስጣዊ ኃይል ያለው መሆኑ ነው። በተጨማሪም ምሳሌያዊው ልባችን ስሜታችንን፣ ምኞታችንንና ፍቅራችንን ያንጸባርቃል። ልብ በንዴት ሊቃጠል ወይም በፍርሃት ሊርድ፣ በሃዘን ሊሰበር ወይም በደስታ ሊፈነጥዝ ይችላል። (መዝሙር 27:3፤ 39:3፤ ዮሐንስ 16:22፤ ሮሜ 9:2) ኩራተኛ ወይም ትሑት፣ አፍቃሪ ወይም በጥላቻ የተሞላ ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 16:5፤ ማቴዎስ 11:29፤ 1 ጴጥሮስ 1:22
4 በዚህ መሠረት “ልብ” አብዛኛውን ጊዜ ከውስጣዊ ግፊትና ስሜት ጋር የተዛመደ ሲሆን “አእምሮ” [NW ] ደግሞ ከማሰብ ችሎታ ጋር የተያያዘ ነው። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አንድ ላይ በሚጠቀሱበት ጊዜ እነዚህን ቃላት መረዳት ያለብን በዚህ መንገድ ነው። (ማቴዎስ 22:37፤ ፊልጵስዩስ 4:7) ይሁን እንጂ ምንም ዝምድና የላቸውም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል ሙሴ እስራኤላውያንን “እግዚአብሔር . . . አምላክ እንደ ሆነ፣ . . . በልብህም ያዝ [ወይም “በአእምሮህ አስታውስ፣” የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ]” በማለት ተናግሯል። (ዘዳግም 4:39) ኢየሱስ በእርሱ ላይ እያሴሩ የነበሩትን ጻፎች “ስለ ምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ?” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 9:4) ‘ማስተዋል፣’ ‘እውቀት’ እና ‘አሳብ’ ከልብ ጋር የተዛመዱ ሊሆኑ ይችላሉ። (1 ነገሥት 3:12፤ ምሳሌ 15:14፤ ማርቆስ 2:6, 7) ስለዚህ ምሳሌያዊው ልብ ከማሰብ ችሎታችን ማለትም ከአስተሳሰባችን ወይም ከማስተዋል ችሎታችን ጋርም የተያያዘ ሊሆን ይችላል።
5. ምሳሌያዊው ልብ ምን ያመለክታል?
5 አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ምሳሌያዊው ልብ “ማዕከላዊውን ክፍል በጥቅሉ፣ ውስጣዊውን ክፍል፣ እንዲሁም በተለያዩ ተግባሮቹ፣ በምኞቶቹ፣ በፍቅሩ፣ በስሜቶቹ፣ ለአንድ ነገር በሚያድርበት የመውደድ ስሜት፣ በዓላማዎቹ፣ በአስተሳሰቦቹ፣ በማስተዋል ችሎታው፣ በሚያልማቸው ነገሮች፣ በጥበቡ፣ በእውቀቱ፣ በሙያው፣ በእምነቱና በአስተሳሰቡ፣ በማስታወስ ችሎታውና በጥንቁቅነቱ ራሱን የሚገልጸውን ውስጣዊውን ሰው” ያመለክታል። ውስጣዊ ማንነታችንን ማለትም ‘የተሰወረውን የልብ ሰው’ ያመለክታል። (1 ጴጥሮስ 3:4) ይሖዋ የሚያየውና የሚመረምረው ይህንን ልብ ነው። በዚህም የተነሳ ዳዊት “አቤቱ፣ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፣ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” በማለት ሊጸልይ ችሏል። (መዝሙር 51:10) ንጹሕ ልብ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
በአምላክ ቃል ላይ “ልባችሁን አኑሩ”
6. እስራኤላውያን በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፍረው ሳሉ ሙሴ ምን ጥብቅ ምክር ሰጣቸው?
6 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ ተሰብስበው በነበረበት ጊዜ ሙሴ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸው ነበር:- “የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዙበት ዛሬ እናንተን ለማስጠንቀቅ በምነግራችሁ ቃል ሁሉ ላይ ልባችሁን አኑሩ።” (ዘዳግም 32:46 NW ) እስራኤላውያን “በጥሞና ማዳመጥ” ነበረባቸው። (ኖክስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) የአምላክን ትእዛዛት በልጆቻቸው ውስጥ መቅረጽ የሚችሉት እነሱ ራሳቸው እነዚህን ትእዛዛት ጠንቅቀው ካወቁ ብቻ ነው።—ዘዳግም 6:6-8
7. በአምላክ ቃል ላይ ‘ልባችንን ማኖር’ ምን ማድረግን ይጠይቃል?
7 ንጹሕ ልብ ለማግኘት የሚያስችለው አንዱ ወሳኝ ነገር ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማዎች ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ነው። ይህ እውቀት የሚገኝበት ብቸኛ ምንጭ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ይሁን እንጂ የጭንቅላት እውቀት ብቻውን አምላክን የሚያስደስት ልብ እንድናገኝ አይረዳንም። ያገኘነው እውቀት ውስጣዊ ማንነታችንን እንዲነካ ከተፈለገ ‘ልባችንን’ በተማርናቸው ነገሮች ላይ ‘ማኖር’ ወይም የተማርናቸውን ነገሮች ‘ልብ ማለት’ አለብን። (ዘዳግም 32:46) ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? መዝሙራዊው ዳዊት “የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፣ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ ተመለከትሁ” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 143:5
8. በምናጠናበት ጊዜ በየትኞቹ ጥያቄዎች ላይ ልናሰላስል እንችላለን?
8 እኛም በአድናቆት ተሞልተን በይሖዋ ሥራዎች ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስን ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በምናነብበት ጊዜ እንደሚከተሉት ባሉ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል:- ‘ይህ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል? እዚህ ላይ የተንጸባረቀው የትኛው የይሖዋ ባሕርይ ነው? ይሖዋ የሚወድደውንና የሚጠላውን በተመለከተ ይህ ዘገባ ምን ያስተምረኛል? ይሖዋ የሚጠላውን ጎዳና ከመከተል ጋር ሲወዳደር እርሱ የሚወድደውን ጎዳና መከተል ምን ጥቅም አለው? ይህ ያገኘሁት እውቀት ቀደም ሲል ከማውቀው ጋር ምን ዝምድና አለው?’
9. የግል ጥናትና ማሰላሰል ምን ያህል ጠቃሚ ናቸው?
9 የሠላሳ ሁለት ዓመቷ ሊዛ a ትርጉም ያለው ጥናትና ማሰላሰል የሚሰጡትን ጥቅም እንዴት እንደተገነዘበች ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “በ1994 ከተጠመቅሁ በኋላ ለሁለት ዓመታት ያህል በእውነት ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴ አደርግ ነበር። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ እገኝ ነበር፣ በየወሩ ከ30 እስከ 40 የሚደርስ ሰዓት በመስክ አገልግሎት አሳልፍ ነበር፤ እንዲሁም ከክርስቲያን ባልንጀሮቼ ጋር ጥሩ ቅርርብ ነበረኝ። ከዚያ ቀስ በቀስ ወደ ኋላ መንሸራተት ጀመርኩ። በጣም ርቄ ከመሄዴ የተነሳ የአምላክን ሕግ እስከ መጣስ ደረስኩ። ሆኖም ወደ ልቡናዬ ተመለስኩና አኗኗሬን ለማስተካከል ወሰንኩ። ይሖዋ ንስሐ መግባቴን ተመልክቶ ስለተቀበለኝ በጣም ደስተኛ ነኝ! ብዙውን ጊዜ ‘እንዴት ልወድቅ ቻልኩ?’ እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። ትርጉም ባለው መንገድ ማጥናትና ማሰላሰልን ችላ በማለቴ ምክንያት እንደሆነ አእምሮዬ በተደጋጋሚ ይነግረኛል። ልቤ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አልተነካም ነበር። ከአሁን ጀምሮ ግን የግል ጥናትና ማሰላሰል በሕይወቴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል።” ስለ ይሖዋ፣ ስለ ልጁና ስለ ቃሉ ያለን እውቀት እያደገ ሲሄድ ጊዜ መድበን ትርጉም ባለው መንገድ ማሰላሰላችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
10. ለግል ጥናትና ለማሰላሰል የሚሆን ጊዜ መመደብ አጣዳፊ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?
10 በዚህ ሩጫ በበዛበት ዓለም ለጥናትና ለማሰላሰል ጊዜ ማግኘት በጣም ተፈታታኝ ነው። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ወደ ተስፋይቱ ምድር ማለትም ጽድቅ ወደሚሰፍንበት የአምላክ አዲስ ዓለም ለመግባት ደፍ ላይ ይገኛሉ። (2 ጴጥሮስ 3:13) “በታላቂቱ ባቢሎን” ላይ የሚደርሰው ጥፋትና “የማጎጉ ጎግ” በይሖዋ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት የመሰሉ አስደንጋጭ ክስተቶች በቅርቡ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። (ራእይ 17:1, 2, 5, 15-17፤ ሕዝቅኤል 38:1-4, 14-16፤ 39:2) ከፊታችን የሚጠብቁን ነገሮች ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ፈተና ላይ ሊጥሉት ይችላሉ። አሁኑኑ ጊዜ መዋጀታችንና ልባችንን በአምላክ ቃል ላይ ማኖራችን ዛሬ ነገ የማይባልበት ጉዳይ ነው!—ኤፌሶን 5:15, 16
‘የአምላክን ቃል ለመፈለግ ልብህን አዘጋጅ’
11. ልባችን ከአፈር ጋር ሊመሳሰል የሚችለው ለምንድን ነው?
11 ምሳሌያዊው ልብ የእውነት ዘር ሊዘራበት ከሚችል አፈር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። (ማቴዎስ 13:18-23) የተዘራው እህል ጥሩ ሆኖ እንዲበቅል ከተፈለገ ማሳው በሚገባ መታረስ አለበት። በተመሳሳይም ልባችን የአምላክን ቃል ጥሩ አድርጎ መቀበል እንዲችል መለስለስ ወይም መዘጋጀት ይኖርበታል። ካህኑ ዕዝራ “የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ . . . ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።” (ዕዝራ 7:10) እኛስ ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
12. ልብን ለጥናት ለማዘጋጀት ምን ይረዳል?
12 የአምላክን ቃል በምንፈልግበት ጊዜ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ልብን ጥሩ አድርጎ ለማዘጋጀት ይረዳል። እውነተኛ አምላኪዎች የሚያደርጓቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚጀመሩትና የሚደመደሙት በጸሎት ነው። በግል የምናደርገውን እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍለ ጊዜ ከልብ በሚቀርብ ጸሎት መጀመራችንና ከዚያም ሙሉ በሙሉ በጥናታችን ላይ ትኩረት ማድረጋችን ምንኛ የተገባ ነው!
13. ይሖዋ የሚደሰትበት ልብ ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባናል?
13 ምሳሌያዊው ልብ አስቀድሞ በውስጡ የያዛቸውን የተሳሳቱ ሐሳቦች ለማስወጣት ዝግጁ መሆን አለበት። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኞች አልነበሩም። (ማቴዎስ 13:15) በሌላው በኩል ደግሞ የኢየሱስ እናት ማርያም በሰማችው እውነት ላይ ተመሥርታ ጥሩ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ “በልብዋ” ታስብ ነበር። (ሉቃስ 2:19, 51) ታማኝ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሆናለች። ከትያጥሮን የመጣችው ልድያ ጳውሎስን ያዳመጠች ሲሆን ‘ጌታም ልብዋን ስለከፈተላት’ አማኝ ሆናለች። (ሥራ 16:14, 15) እኛም የራሳችንን የግል አስተሳሰብ ወይም ከፍ አድርገን የምንመለከታቸውን መሠረተ ትምህርቶች የሙጥኝ ብለን መያዝ የለብንም። ከዚያ ይልቅ ‘ሰው ሁሉ ውሸተኛ ሆኖ ቢገኝ እግዚአብሔር እውነተኛ እንዲሆን’ ፈቃደኞች እንሁን።—ሮሜ 3:4
14. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለማዳመጥ ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
14 በተለይ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለማዳመጥ ልብን ማዘጋጀት በጣም አስፈላጊ ነው። ሐሳብ የሚከፋፍሉ ነገሮች የሚሰጠውን ትምህርት እንዳንከታተል ትኩረታችንን ሊሰርቁብን ይችላሉ። ስላሳለፍነው ቀን ወይም በሚቀጥለው ቀን ስለምናከናውነው ነገር የምናወጣ የምናወርድ ከሆነ የሚሰጡት ትምህርቶች ያን ያህል ላይነኩን ይችላሉ። ከሚሰጠው ትምህርት ጥቅም ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ለማዳመጥና ለመማር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶች ሲጠቀሱና ማብራሪያ ሲሰጥባቸው በጥሞና ለመከታተል ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን ከፍተኛ ጥቅሞችን ልናገኝ እንችላለን!—ነህምያ 8:5-8, 12
15. ትሕትና ለመማር ይበልጥ ፈቃደኞች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?
15 ማዳበሪያ ማድረግ የአንድን አፈር ለምነት እንደሚጨምር ሁሉ እኛም ትሕትናን፣ ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥማትን፣ እምነትን፣ አምላካዊ ፍርሃትንና ለአምላክ ፍቅር ማዳበራችን ምሳሌያዊ ልባችንን ለም ሊያደርጉት ይችላሉ። ትሕትና ልብን በማለስለስ ይበልጥ ለመማር ፈቃደኞች እንድንሆን ይረዳናል። ይሖዋ ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮስያስ “ልብህ ገር ሆኖአልና፣ . . . የተናገርሁትን ሰምተህ በእግዚአብሔር ፊት ተዋርደሃልና፣ . . . በፊቴም አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ” ብሎታል። (2 ነገሥት 22:19) ኢዮስያስ ትሑትና ተቀባይ ልብ ነበረው። ትሕትና ‘መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ’ የነበሩት ‘የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት’ ‘ጥበበኞችና አስተዋዮች’ የነበሩ ሰዎች ሊረዷቸው ያልቻሏቸውን መንፈሳዊ እውነቶች እንዲረዱና በሥራ ላይ እንዲያውሉ ረድቷቸዋል። (ሥራ 4:13፤ ሉቃስ 10:21) ይሖዋ የሚደሰትበት ልብ ለማግኘት ጥረት ስናደርግ “በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ።”—ዕዝራ 8:21
16. መንፈሳዊ ምግብ የመመገብ ፍላጎት ለማዳበር ጥረት ማድረግ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
16 ኢየሱስ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:3 NW ) ለመንፈሳዊ ነገሮች ተፈጥሯዊ ፍላጎት ያለን ቢሆንም እንኳ ይህ ክፉ ዓለም የሚያሳድራቸው ተጽዕኖዎች ወይም እንደ ስንፍና ያሉ ባሕርያት ይህን ፍላጎታችንን ለማሟላት ንቁ እንዳንሆን ሊያደርጉን ይችላሉ። (ማቴዎስ ) ለመንፈሳዊ ምግብ ጥሩ ፍላጎት ማዳበር ይገባናል። መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ስናነብና የግል ጥናት ስናደርግ ደስታ ባናገኝም እንኳ በጽናት ከቀጠልን እውቀት ‘ነፍሳችንን ደስ ታሰኛለች።’ ይህም የጥናት ፕሮግራማችንን በጉጉት እንድንጠብቅ ያደርገናል።— 4:4ምሳሌ 2:10, 11
17. (ሀ) ይሖዋ ሙሉ በሙሉ እምነት ልንጥልበት የሚገባ አምላክ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በአምላክ ላይ እምነት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
17 ንጉሥ ሰሎሞን “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ” በማለት አጥብቆ መክሯል። (ምሳሌ 3:5) በይሖዋ የሚታመን ልብ ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሚጠይቃቸው ነገሮች ወይም የሚሰጣቸው መመሪያዎች ትክክል መሆናቸውን ይገነዘባል። (ኢሳይያስ 48:17) ይሖዋ ሙሉ እምነት ልንጥልበት የሚገባ አምላክ ነው። ዓላማዎቹን ሁሉ ዳር የማድረስ ችሎታ አለው። (ኢሳይያስ 40:26, 29) “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም ያለው ስሙ ራሱ ቃል የገባቸውን ተስፋዎች በሙሉ ለመፈጸም ባለው ችሎታ ላይ እምነት እንድናሳድር የሚያደርገን ነው! እርሱ “በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር [“ታማኝ፣” NW ] ነው።” (መዝሙር 145:17) እርግጥ ነው በእርሱ ላይ እምነት ለማዳበር ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርናቸውን ሁሉ በግል ሕይወታችን በሥራ ላይ በማዋልና እንዲህ ማድረግ በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ላይ በማሰላሰል ‘የይሖዋን ጥሩነት መቅመስና ማየት’ ይኖርብናል።—መዝሙር 34:8
18. አምላካዊ ፍርሃት የአምላክን መመሪያዎች እንድንቀበል የሚረዳን እንዴት ነው?
18 ሰሎሞን ልባችን መለኮታዊ መመሪያን የሚቀበል እንዲሆን የሚረዳ ሌላ ባሕርይ ሲጠቅስ “እግዚአብሔርን ፍራ፣ ከክፋትም ራቅ” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 3:7) ይሖዋ የጥንት እስራኤላውያንን በሚመለከት “ለእነርሱ ለዘላለምም ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ፣ እንዲፈሩኝ ሁልጊዜም ትእዛዜን ሁሉ እንዲጠብቁ እንዲህ ያለ ልብ ምነው በሆነላቸው!” በማለት ተናግሯል። (ዘዳግም 5:29) አዎን፣ አምላክን የሚፈሩ ሁሉ እርሱን ይታዘዛሉ። ይሖዋ ‘ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን የማጽናትና’ የማይታዘዙትን የመቅጣት ችሎታ አለው። (2 ዜና መዋዕል 16:9) አምላክን ላለማሳዘን የምናሳየው አክብሮታዊ ፍርሃት ድርጊታችንን፣ አስተሳሰባችንንና ስሜታችንን ሁሉ እንዲቆጣጠር እናድርግ።
‘በፍጹም ልብህ ይሖዋን ውደድ’
19. ልባችን የይሖዋን መመሪያ እንዲቀበል በማድረግ ረገድ ፍቅር ምን ሚና ይጫወታል?
19 ከሌሎች ባሕርያት ሁሉ ይበልጥ ልባችን የይሖዋን መመሪያ እንዲቀበል የሚያደርገው ፍቅር ነው። አንድ ሰው በአምላክ ፍቅር የተሞላ ልብ ካለው አምላክን የሚያስደስተውንና የሚያስከፋውን ነገር ለመማር እንዲነሳሳ ያደርገዋል። (1 ዮሐንስ 5:3) ኢየሱስ “ጌታ [“ይሖዋ፣” NW ] አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:37) በአምላክ ጥሩነት ላይ ማሰላሰልን ልማድ በማድረግ፣ እንደ ቅርብ ወዳጃችን አድርገን ዘወትር ከእርሱ ጋር በጸሎት በመነጋገርና ስለ እርሱ ለሌሎች በቅንዓት በመናገር ለአምላክ ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ እናድርግ።
20. ይሖዋ የሚደሰትበት ልብ እንዴት ማግኘት እንችላለን?
20 እንግዲያው ለማጠቃለል ያህል:- ይሖዋ የሚደሰትበት ልብ ማግኘት የአምላክ ቃል ውስጣዊ ማንነታችንን ማለትም የተሰወረውን የልብ ሰው እንዲለውጥ መፍቀድን ይጨምራል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ትርጉም ባለው መንገድ በግል ማጥናትና በአድናቆት ማሰላሰል የግድ አስፈላጊ ነው። ይህንን ለማድረግ ዝግጁና ከተሳሳተ ግንዛቤ ነፃ የሆነ ልብ ማለትም ለመማር ፈቃደኞች እንድንሆን በሚያደርጉ ባሕርያት የተሞላ ልብ እንዲኖረን ያስፈልጋል! አዎን፣ በይሖዋ እርዳታ አምላክን የሚያስደስት ልብ ማግኘት ይቻላል። ይሁን እንጂ ልባችንን ለመጠበቅ ምን እርምጃዎች ልንወስድ እንችላለን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሟ ተቀይሯል።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
• ይሖዋ የሚመረምረው ምሳሌያዊ ልብ ምንድን ነው?
• በአምላክ ቃል ላይ ‘ልባችንን ማኖር’ የምንችለው እንዴት ነው?
• የአምላክን ቃል ለመፈለግ ልባችንን ማዘጋጀት የሚኖርብን እንዴት ነው?
• ይህን ትምህርት ካጠናህ በኋላ ምን ለማድረግ ተነሳስተሃል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት በአድናቆት ተሞልቶ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያሰላስል ነበር። አንተስ?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ቃል ከማጥናትህ በፊት ልብህን አዘጋጅ