በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደስታ የሰፈነበት ዓለም—እንዴት?

ደስታ የሰፈነበት ዓለም—እንዴት?

ደስታ የሰፈነበት ዓለም—⁠እንዴት?

“በእነዚህ ሁለት ሺህ ዓመታት ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ እንዳለው የሚጠቀስ ብቸኛ ሰው የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው” በማለት ታይም መጽሔት ዘግቧል። ኢየሱስ ምድር በነበረ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ታላቅነቱን ብቻ ሳይሆን አሳቢነቱንም ጭምር ተገንዝበዋል። ስለዚህ ሊያነግሡት መፈለጋቸው ምንም አያስገርምም። (ዮሐንስ 6:10, 14, 15) ይሁን እንጂ በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው ኢየሱስ በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ከመግባት ታቅቧል።

ኢየሱስ የሰጠው ምላሽ ቢያንስ የሚከተሉትን ሦስት ነገሮች መሠረት ያደረገ ነበር። ሰብዓዊ አገዛዝን ጨምሮ የሰው ልጅ የራሱን ምርጫ የሚያደርግባቸውን ነገሮች በተመለከተ አባቱ ያለውን አመለካከት ያውቅ ነበር። የሰው ልጆች በቅን ልቦና ተነሳስተው ከሚያደርጓቸው የአገዛዝ ጥረቶች በስተጀርባ እንኳ ሳይቀር ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የሚመራ አንድ ብርቱ ኃይል መኖሩን ተገንዝቧል። እንዲሁም አምላክ መላውን ምድር የሚያስተዳድር ሰማያዊ መንግሥት የማቋቋም ዓላማ እንዳለው ያውቅ ነበር። እነዚህን ሦስት ነጥቦች ይበልጥ ሰፋ ባለ መንገድ ስንመረምር የሰው ልጅ የተሻለ ዓለም ለማምጣት ያደረገው ጥረት ሁሉ ሳይሳካ የቀረበትን ምክንያት እንገነዘባለን። በተጨማሪም በዚህ ረገድ ስኬታማ መሆን የሚቻልበትንም መንገድ እናያለን።

ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ይችላሉ?

አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር በእንስሳት ላይ የመግዛት ሥልጣን ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:26) የሰው ዘር ግን በአምላክ ሉዓላዊ አገዛዝ ሥር ነበር። የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ” እንዳይበሉ የተሰጣቸውን ትእዛዝ በማክበር ለአምላክ ሉዓላዊነት መገዛታቸውን ማሳየት ነበረባቸው። (ዘፍጥረት 2:17) የሚያሳዝነው አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነጻነታቸውን አላግባብ በመጠቀም አምላክን ሳይታዘዙ ቀሩ። የተከለከለውን ዛፍ መብላት ሥርቆት ብቻ ሳይሆን በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ የተፈጸመ ዓመፅም ነበር። ዘ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል ከዘፍጥረት 2:​17 በታች ባሰፈረው የግርጌ ማስታወሻ ላይ አዳምና ሔዋን “ራሳቸው በራሳቸው የመወሰን መብት እንዳላቸው በማሰብ የሰው ልጅ ፍጡር መሆኑን አምኖ ለመቀበል አሻፈረን ማለታቸውን አሳይተዋል። . . . የመጀመሪያው ኃጢአት በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነበር” ብሏል።

የተነሳው አንገብጋቢ ጥያቄ ሥነ ምግባርን የሚመለከት በመሆኑ አምላክ፣ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ዘሮቻቸው ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚያስችሏቸውን የራሳቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንዲያወጡና የራሳቸውን የአኗኗር መንገድ እንዲከተሉ ፈቀደላቸው። (መዝሙር 147:19, 20፤ ሮሜ 2:14) በዚህ መልኩ የሰው ልጅ ራሱን በራሱ ለመግዛት የሚያደርገውን ሙከራ ጀመረ። ሙከራው ተሳክቶ ይሆን? ያለፉትን ሺህ ዓመታት መለስ ብለን በመመልከት አልተሳካም ብለን መናገር እንችላለን! መክብብ 8:​9 [NW ] ‘ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው’ በማለት ይናገራል። የሰው ልጅ ራሱን በራሱ በመግዛት ያስመዘገበው አሳዛኝ ታሪክ የኤርምያስ 10:​23ን እውነተኛነት ያረጋግጣል። “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” የሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው መመሪያ ውጪ ራሳቸውን በተሳካ መንገድ ማስተዳደር እንደማይችሉ ታሪክ አረጋግጧል።

ኢየሱስ በዚህ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ተስማምቷል። ከአምላክ ተለይቶ ራስን በራስ መምራት ለእርሱ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። ‘ከራሴ አንዳች አላደርግም . . . ዘወትር [አምላክን] ደስ የሚያሰኘውን አደርጋለሁ’ በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:34፤ 8:28, 29) ኢየሱስ ከአባቱ ያላገኘውን ሥልጣን ከሰው ለመቀበል ፈጽሞ አልፈለገም። ይህ ማለት ግን ኢየሱስ ሰዎችን የመርዳት ፍላጎት አልነበረውም ማለት አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ሰዎች አሁንም ሆነ ወደፊት ከፍተኛ ደስታ ማግኘት ይችሉ ዘንድ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። ሕይወቱን ሳይቀር ለሰው ልጆች ሰጥቷል። (ማቴዎስ 5:3-11፤ 7:24-27፤ ዮሐንስ 3:16) ሆኖም ኢየሱስ፣ አምላክ ሉዓላዊነቱን በሰዎች ፊት የሚያረጋግጥበትን ጊዜ ጨምሮ ‘ለሁሉም ጊዜ’ እንዳለው ያውቅ ነበር። (መክብብ 3:1፤ ማቴዎስ 24:14, 21, 22, 36-​39) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በገነት ውስጥ በሚታይ እባብ አማካኝነት ላነጋገራቸው ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ፈቃድ ራሳቸውን እንዳስገዙ አስታውስ። ይህም ኢየሱስ በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ከመግባት የታቀበበትን ሁለተኛ ምክንያት እንድንገነዘብ ይረዳናል።

የማይታየው የዓለም ገዥ

ኢየሱስ አንድ ጊዜ ብቻ ቢሰግድለት “የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም” እንደሚሰጠው ሰይጣን ቃል ገብቶለት እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ማቴዎስ 4:8-10) ኢየሱስ በሰይጣን በኩል ዓለምን የመግዛት ግብዣ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም ለፈተናው እጁን አልሰጠም። በእርግጥ ይህ ፈተና ነበር? ሰይጣን እንዲህ ያለውን ታላቅ ግብዣ ማቅረብ ይችላል? አዎን፣ ምክንያቱም ኢየሱስ ራሱ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” ብሎ የጠራው ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስም “የዚህ ዓለም አምላክ” እንደሆነ ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 14:30፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ኤፌሶን 6:12

እርግጥ ሰይጣን ለሰው ልጆች ጥሩ እንደማያስብ ኢየሱስ አሳምሮ ያውቅ ነበር። እንዲያውም ‘ነፍሰ ገዳይ፣’ “የውሸት እና የሐሰት ሁሉ አባት” በማለት ጠርቶታል። (ዮሐንስ 8:44 ዘ አምፕሊፋይድ ባይብል) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው እንዲህ ባለው ‘ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር የተያዘ’ ዓለም ፈጽሞ ደስተኛ ሊሆን አይችልም። (1 ዮሐንስ 5:19) ይሁን እንጂ ሰይጣን ይህን ሥልጣኑን እንደያዘ ለዘላለም ይቀጥላል ማለት አይደለም። አሁን ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር የሆነው ኢየሱስ በቅርቡ ሰይጣንንና ተጽእኖዎቹን ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ ያስወግዳቸዋል።​—⁠ዕብራውያን 2:14፤ ራእይ 20:1-3

ሰይጣን ራሱ የዚህ ዓለም ገዢ ሆኖ የሚቆይበት ጊዜ በፍጥነት እያለቀ እንደሆነ አሳምሮ ያውቃል። በዚህም የተነሳ በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውኃ በፊት እንዳደረገው አሁንም ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ሊጠገን ወደማይችል አዘቅት ውስጥ ለመክተት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። (ዘፍጥረት 6:1-5፤ ይሁዳ 6) ራእይ 12:​12 “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና” በማለት ይናገራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና የዓለም ሁኔታዎች በዚህ “ጥቂት ዘመን” መደምደሚያ ላይ እንደምንኖር ያሳያሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እፎይታ የምናገኝበት ጊዜ ቀርቧል።

ደስታ የሚያመጣ መንግሥት

ኢየሱስ በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ከመግባት የታቀበበት ሦስተኛ ምክንያት ደግሞ አምላክ ወደፊት መላውን ምድር የሚገዛ ሰማያዊ መስተዳድር የማቋቋም ዓላማ እንዳለው ያውቅ ስለነበር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን መስተዳድር የአምላክ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ሲሆን የኢየሱስ ትምህርት ዋነኛ ጭብጥም ይኸው መንግሥት ነበር። (ሉቃስ 4:43፤ ራእይ 11:15) የአምላክ ‘ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም የሚሆነው’ በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ብቻ ስለሆነ ኢየሱስ ተከታዮቹን ይህ መንግሥት እንዲመጣ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ‘ይህ መንግሥት መላዋን ምድር የሚያስተዳድር ከሆነ አሁን ያሉት ሰብዓዊ መንግሥታት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?’ በማለት ትጠይቅ ይሆናል።

ዳንኤል 2:​44 መልሱን ይሰጠናል:- “በእነዚያም ነገሥታት [በአሁኑ የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ ላይ እየገዙ ባሉት መንግሥታት] ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም [ሰው ሰራሽ] መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) የአምላክ መንግሥት ምድራዊውን አገዛዝ ‘መፍጨት’ የሚኖርበት ለምንድን ነው? ምክንያቱም እነዚህ መንግሥታት ሰይጣን የአምላክን አገዛዝ በመቃወም ከኤደን የአትክልት ስፍራ ጀምሮ ሲያስፋፋ የቆየውን በራስ የመመራት መንፈስ ስለሚያራምዱ ነው። ይህንን መንፈስ የሚያራምዱ ሁሉ የሰውን ልጅ ጥቅም የሚጻረሩ ከመሆናቸውም በላይ ከፈጣሪ ጋር ይጋጫሉ። (መዝሙር 2:6-12፤ ራእይ 16:14, 16) ስለዚህ ራሳችንን ‘የምደግፈው የአምላክን አገዛዝ ነው ወይስ የሰው?’ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል።

የምትመርጠው የማንን ሉዓላዊነት ነው?

ሰዎች አገዛዝን በተመለከተ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ ማድረግ እንዲችሉ ለመርዳት ኢየሱስ የዚህ የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ[ን] የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ” እንዲሰብኩ ተከታዮቹን አዝዟቸዋል። (ማቴዎስ 24:14) በዛሬው ጊዜ የአምላክን መንግሥት በመስበክ ረገድ በዓለም ዙሪያ የሚታወቁት እነማን ናቸው? የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። እንዲያውም ይህ መጽሔት በፊተኛው ገጹ ላይ “የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ” የሚሉትን ቃላት ይዞ ለረዥም ጊዜ ሲወጣ ቆይቷል። በዛሬው ጊዜ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ስድስት ሚልዮን የሚያክሉ ምሥክሮች ሰዎች ስለዚህ መንግሥት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኙ በመርዳት ላይ ናቸው።

የመንግሥቱ ተገዢዎች የሚያገኟቸው በረከቶች

ኢየሱስ ነገሮችን ሁልጊዜ በአምላክ መንገድ አከናውኗል። በራሱ ፈቃድ ከመመራትና ይህን የነገሮች ሥርዓት በፖለቲካዊ መንገድ ለመደገፍ አሊያም ለማሻሻል ከመሞከር ይልቅ ለዓለም ችግሮች ብቸኛ መፍትሄ የሆነውን የአምላክን መንግሥት ፍላጎቶች ለማራመድ ጠንክሮ ሠርቷል። በዚህ መንገድ ላሳየው ታማኝነት የዚሁ መንግሥት ንጉሥ የመሆን ክብራማ ዙፋን በሰማይ ተሰጥቶታል። ለአምላክ መገዛቱ ያስገኘለት ሽልማት ምንኛ አስደናቂ ነው!​—⁠ዳንኤል 7:13, 14

ዛሬም በተመሳሳይ የአምላክን መንግሥት በማስቀደምና ራሳቸውን ለአምላክ ፈቃድ በማስገዛት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ የተከተሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የዚሁ መንግሥት ምድራዊ ተገዢ የመሆን አስደናቂ መብት ያገኛሉ። (ማቴዎስ 6:33) በመንግሥቱ ፍቅራዊ አገዛዝ ሥር ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይዘው ስብዓዊ ፍጽምና ላይ ይደርሳሉ። (ራእይ 21:3, 4) አንደኛ ዮሐንስ 2:​17 “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት ይናገራል። ሰይጣንና ርዝራዦቹ ተጠራርገው ከጠፉ በኋላ ከፋፋይ ከሆነው ብሔረተኝነት፣ ብልሹ ከሆነው የንግድ ሥርዓትና ከሐሰት ሃይማኖት በጸዳችው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ምንኛ የሚያስደስት ነው!​—⁠መዝሙር 37:29፤ 72:16 የ1980 ትርጉም

አዎን፣ እውነተኛ ደስታ የሰፈነበት ዓለም ሊያመጣ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። መንግሥቱን የሚያሳውቀው መልእክትም ምሥራች መባሉ ተገቢ ነው። እስካሁን ምሥራቹን አልተቀበልህ ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ቤትህ መጥተው ምሥራቹን ሲነግሩህ ለምን አትቀበላቸውም?

የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት የሚደግፉ በመሆናቸው እገዳ በተጣለባቸው ወይም ስደት ባለባቸው አገሮች ውስጥ እንኳ ሳይቀር በፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም ወይም ደግሞ በመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ላይ ዓመፅ አያነሳሱም። (ቲቶ 3:1) ከዚህ ይልቅ ኢየሱስና የመጀመሪያው መቶ ዘመን ተከታዮቹ እንዳደረጉት ፖለቲካዊ ተዛምዶ የሌለው መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ይጥራሉ። ምሥክሮቹ በሚኖሩበት አካባቢ የሚገኙ የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ቤተሰባዊ ፍቅርን፣ ሃቀኝነትን፣ የሥነ ምግባር ንጽህናንና ጥሩ የሥራ ልማድ የመሳሰሉትን ጤናማ ቅዱስ ጽሑፋዊ እሴቶች በተግባር ላይ እንዲያውሉ ለመርዳት ይጥራሉ። በዋነኛነት ግን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት በተግባር ላይ ማዋልና የአምላክን መንግሥት ብቸኛ የሰው ልጆች ተስፋ አድርጎ መመልከት እንደሚቻል ለማስተማር ይጥራሉ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰው ልጆች ከአምላክ ርቀው ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዳልቻሉ ታሪክ ያረጋግጣል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰይጣን የዚህ “የነገሮች ሥርዓት” ገዢ በመሆኑ ለኢየሱስ “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ” ልስጥህ የሚል ግብዣ ማቅረብ ችሏል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ዓለም አስደሳች የመኖሪያ ቦታ እንደምትሆን ኢየሱስ አስተምሯል